ቀለም መጽሔት
866 subscribers
49 photos
1 video
6 files
11 links
ቀለም ዲጅታል መጽሔት🗞️

ቀለም መፅሔት ብቻ አይደለም፤ የሥነ ፅሁፍ እንቅስቃሴም ጭምር እንጂ……
💚💛❤️

telegram group -https://t.me/kelemMetsehet
Instagram- kelem_magazine
Download Telegram
ባይተዋሩ

እስኪ ስለዚህ መፅሐፍ እንካቹ ልበል ይህ መፅሐፍ አልበርት ካሙ The stranger ብሎ ከፃፈው ወደ አማርኛው ባይተዋሩ በሚል በ 2006 የተተረጎመ ነው።

መፅሐፉ በሁለት ትኩረቱን በ ኒሂሊዝም ላይ ትኩረቱን አድርጎ የተፃፈ ሲሆን ገፀ ባህሪው በወለፈንዲነት የሚሰቃይ በሁለት ክፍል ተዋቅሮ የተቀነበበ ነው። የመጀመሪያው ክፍል ገፀ ባህሪው በአልጀርስ የሚኖር መርሳልት የሚያልፍበትን የህይወት ክፍል የሚያትት ሲሆን ሁለተኛው ክፍል በ አጋጣሚ ሰው በመግደሉ ምክንያት እስር ቤት ከገባ ቡኋላ ያለውን ታሪክ ያትትልናል።

ልክ መፅሐፉ ሲጀምር
ዛሬ እማዬ ሞተች ምናልባትም ትላንት ይሆናል አላውቅም። በሚለው የመፅሐፉን ጭብጥ በያዘው ኒሂሊዝም ማለትም ስሜት አልባውን በወለፈንዲነት በሚቸገረው መርሳልት የህይወቱን ታሪክ ይተርክ ይጀምራል።

ዋና ገፀ ባህሪው መርሳልት ሁሉን ነገር የሰለቸ ለምንም ግድ የሌለው የ እናቱን እድሜ የማያውቅ በፈጣሪ መኖር የማያምን ሲሆን በህይወቱ ለሚያጋጥሙት ነገሮች ምላሽ መስጠት የተሰላቸ ሰው ነው። ታዲያ እናቱ ሞታ እንኳን ምንም የማያለቅስ ስሜት አልባ ሰው ነው። ለምንም ነገር ግድ የሌለው ከመሆኑ የተነሳ አብዛኛውን ነገር በዝምታ የሚያልፍ ብናገርም ባልናገርም ዋጋ የለውም ብሎ የሚያስብ ሰው ነው።

ታዲያ ሜሪ የምትባል የድሮ የስራው ባልደረባ የነበረች ሴት ተገናኝተው አብረው ጊዜ ማሳለፍ ይጀምራሉ በጊዜ ሂደት ከሱ በፍቀር ክንፍ ብላ እንጋባ ስትለው አንቺ ደስ ካለሽ እሺ እንጂ እኔ ቢሆን ባይሆን ግድ የለኝም የሚል አይነት ነው። ፍቅርም ተራ ነገር መሆኑን ቢጋቡም ባይጋቡም ልዩነት እንደሌለው የሚያምን ሁሉም ነገር ተራ ድግግሞሽ መሆኑን የሚያምን ሰው ነው።

ሁለተኛው ክፍል ላይ መርሳልት በድንገት ሰው በመግሉ በእስር ቤት ያለውን ቆይታ የሚያስቃኘን ሲሆን እስር ቤትም ገብቶ የተለመደውን ለአለም ፊቱን የማዞር የመሠልቸት ሁኔታ እስር ቤት ቆይታውን ተላምዶ ሲኖርና ነገሮች እስኪለመዱ ብቻ ከባድ መሆናቸውን ከዛ ውጪ ከተለመደ በኋላ ግን ምንም ልዩነት እንደሌለው ያትትልናል። እስር እራሱ እስኪለመድ እንጂ ከለመደ ከውጪው ህይወት የተለየ ነገር እንደሌለውና ተመሳሳይ መሆኑን ያትታል በፍርድ ሂደቱ ወቅት ራሱ የሚያሳየው ስሜት አልባነት የፍርድ ሂደቱን ብዙ ጊዜ ከልቡ አይሰማም ሀሳቡን ሌላ ቦታ የሚጠል ሰው ነው።

ወደ መጨረሻ መዝጊያው ላይ መርሳልት የሞት ፍርድ ተፍርዶበት ትንሽ ከተጨናነቀ ቡኋላ የሰው ልጅ መሞቱ አይቀርም ወይ ይዘገያል እንጂ ሁሉም ሟች ነው የተለየ ነገር የለውም ብሎ ለሞቱ ሲዘጋጅ የሚያሳይ ድንቅ መፅሐፍ ነው።

አልበርት ካሙ እዚች ምድር ላይ ትልቁ የፍልስፍና ጥያቄ አንድ ነው ይለናል እራሴን ላጥፋ ወይስ ቡና ልጠጣ? ሌላው ሁሉ ቀሽም ጥያቄ ነው ይለናል። ስለ ኒሂሊዝም ማወቅ ከፈለጋቹ መፅሐፉን ፈልጋቹ ብታነቡት ይበረታታል።

ኃይለአብ

@kelemofficial
10🔥4
ቀለም መፅሔት ቅፅ 1 እትም 5.pdf
8 MB
ቀለም መጽሔት🗞️

ቅፅ 1 እትም 5


እያነበባቹህ ለወዳጅዎ ያጋሩ
ለሀሳብ አስተያየት

@KelemMagazine

Telegram 👇❤️
@kelemofficial
🔥83🥰2🙏1
የቀለም እንግዳ

ቀለም መጽሔት በቅፅ 1 ቁጥር 4 የቀለም 
እንግዳ አድርጋ ወደ አንባቢያን ግጥምን 
ሲያሻው ሸራ ላይ ስሎ ነብስ እየዘራ አይንን  የሚመግብ ፤ ስዕልን ከሸራ አውርዶ  በፊደላት ቀርፆ በጣፋጭ አንደበቱ ቀልብን  የሚገዛ ሰዓሊ ፤ ገጣሚ እና ተዋናይ  አርቲስት ቸርነት ወልደ ገብርኤልን ይዛ  ብቅ ብላለች::

ቀለም ፦ ከሁሉ አስቀድመን የቀለም መጽሔት ቅፅ 1 4ኛ  ዕትም እንግዳ ሆነው ስለመጡ ከልብ እናመሰግናለን:: 
በእርሶ የኪነ ጥበብ ጉዞ ፤ የሕይወት ፍልስፍና ላይ  ያተኮረ ጥያቄ ይዘን ቀርበናል:: አንባቢያን ቸርነት 
ወልደ -ገብርኤል ማነው ቢሉ ማን እንበላቸው? ቃለ  መጠየቀቻንን አንቱ ወይስ ማን ብለን እንቀጥል ?

ቸርነት ወልደ -ገብርኤል ፦ ሰዓሊ እና ገጣሚ ቸርነት  ወልደ-ገብርኤል እባላለው:: አንቱታውን ወደ ጎን ተወት 
አድርገኸው አንተ እያልክ ብትቀጥል ደስ ይለኛል::

ቀለም ፦ እሺ እናመሰግናለን 

ቸርነት ወልደ ገብርኤል ፦ ቸሬ እያልክ ያውም 

ቀለም ፦እሺ በደስታ (ሳቅ ) ቸሬ ሸራን ከማናገር ፣  ብዕርን ከመግራት እና በገፀባህሪ ከመንገስ ለቸርነት 
ነፍስ የቱ ይቀለዋል?

ቸርነት ወልደ-ገብርኤል ፦ ብዙ ጊዜ ጥያቄዎች  የራሳቸውን መልስ ይዘው ነው ሚመጡት:: ማለትም  በዚ በኩል ግለፀን እያሉ:: አንዳንዴ በአንድነት ይገለፃሉ  ሲያሻቸው በተናጥል:: አንዳንዴ ወቅታዊ ጉዳዮች  ሲሆኑ ፤ ደስታም ሆነ ሀዘን ቆንጠጥ ሲያደርገኝ ብዙ 
ጊዜ ወደ ስነ-ፅሁፍ ይመራኛል:: ያው ገጣሚ ጋር ሀዘን  በቀላሉ የማይታለፍ ከበድ የሚል ጉዳይ ነው:: በዚህ 
ጊዜ ለነብሴ ግጥም ዘንበል ይላል:: ስዕል ደሞ የሆነ ጊዜን ፈልጎ ቢሆንም ይወጣል :: 

ቀለም ፦ እሺ ስዕል እና ግጥም በቸርነት አንደበት  እንዴት ይገለፃል? ማለት ስዕል ላንተ ምንድን ነው?

ቸርነት ወልደ -ገብርኤል ፦ አንደኛ ስዕል ሐሳቤን  የምገልፅበት ከፈጣሪ የተሰጠኝ መናገሪያ መንገዴ 
ነው:: ሌላኛው ስዕል ለኔ እንጀራዬ ነው:: ማለትም  የምተዳደረው በስዕል ነው:: ግጥም መተዳደሪያዬ  ባይሆንም እንድደሰትበት ከፈጣሪዬ የተሰጠኝ ፀጋ 
ነው:: ይሄን ደስታ ግጥሜን ማለቴ ነው ለሌሎች  ስሰጣቸው ስሜቴ ወደ እነሱ ሲጋባ የነሱ ደስታ መልሶ  ውስጤን ሐሴት ይሞላዋል። በዚህም ፈጣሪዬን 
በጣም አመሠግነዋለሁ:: እኛ የፈጣሪ መሳሪያዎች ነን  ፈጣሪ ለልጆቹ መስጠት የፈለገውን ጥበብን ገልፆ  በስዕል በግጥም በተለያየ መንገዶች ከማያልቀው  ቸርነቱ ይመግበናል:: ምክንያቱም ካልተሰጠን  ከየትም አናመጣውም:: ይሄን የማውቀው ደግሞ  አንዳንዴ ግጥም ፅፌ ሀሳቡ ይገዝፍብኝ እና ከኔ የወጣ  እስከማይመስለኝ ድረስ እገረማለሁ::

ቀለም ፦ ግሩም አገላለፅ ነው። ቸሬ እንዳው ስዕላትህ  ፤ ግጥሞችህ ለሀገር ያለህን ስሜት ያሳብቁብሃል እስቲ 
ዛሬ ደግሞ ከአንደበትህ ለዚሁ ሁሉ ስሜት መነሻ  የሆነህን ነገር ፤ ለሀገርህ ያለህን ፍቅር ፤ ቁጭትም ካለ 
ብታወጋን።

ቸርነት ወልደ-ገብርኤል ፦ ከምን እንደምጀምርልህ  አላውቅም። ብቻ ብዙ ሰው ባለበት መኖር እራሱን  የቻለ ተፅህኖ አለው። ለሰዎች ያለህን አመለካከት 
ይገራዋል። ስለ ሰው ያገባኛል የሚል ስሜት  ይፈጥራል። ሀገር ማለት ሰው አይደል? በጣም ብዙ  ሕዝብ ፤ ብዙ አይነት እንቅስቃሴ ባለበት መርካቶ 
መሃል ነው ያደኩት:: መነሻዬ ይሄ ነው የሀገር ፍቅር  ስሜት ፤ ከኔነት ይልቅ የእኛነትን ስሜት በውስጤ  ሞልቶ ያኖረው:: አሁን ለምሳሌ ኤርትራ ተገንጥላ  ሄደች ፤ የሆኑ ሰዎች ተነስተው የሆኑ ስብስብ አዋቅረው  ስጡን ቢሉ የዛን ጊዜ ምድሪቱን አስቀድማለሁ:: ያኔ  ኢትዮጵያ የሁላችን ስለሆነች ኢትዮጵያዬን አልሰጥም  እላለሁ:: እነሱን እጂ ሀገሬን ልሸኝ አልሻም:: ምንኖረው 
ኢትዮጵያ ውስጥ ነው አንዳንድ ብልጣብልጦች  ተነስተው እንውሰድ ቢሉ ምናልባት ቀምተውኝ እንጂ 
ዘርግቼ አልሰጥም:: ኤርትራም ለኔ ያስቀሙን ርስታችን  እንጂ የሰጠናቸው ሀገር አይደለችም:: እነሱም የኛ 
እኛም የነሱ ነን አይደለም እንዴ? አያገባኝም ብዬ  ቆርጬ የምሰጠው ድንበር የለኝም:: እጅግ በጣም 
ጨዋ ሕዝቦች ወጥተው የሞቱላት ሀገር ነች ኢትዮጵያ  እኔ የእነርሱ ልጅ ነኝ:: ከእኛነት ይልቅ እኔነት ሲገዝፍ 
፤ ራስ ወዳድ ሲበዛ እጅግ በጣም በሽተኛ ያደርገኛል።  በየ ቦታው የግለሰብ አስተሳሰብ ሌላውን የማይጠቅም 
ሀሳብ ማየት በጣም ያማል። ምክንያቱም ይሄ የኛነት  መገለጫችን ፣ ባህላችን አይደለም። ያደኩትም  ይሄን እያየው አይደለም በግለኝነት ስሜት ተሰርቼ 
አላደኩም። ከዚ ተነስቶ ሌላ ቦታ ሄዶ በሰላም መኖር  የሚችል ሕብረተሰብ የነበረ ዛሬ ላይ በሀገሩ እንደ ባዳ 
ተቆጥሮ መሄድ ማለፍ አትችልም ሲባል ያስደነግጠኛል  ፣ ያሳስበኛል ፣ ያስቆጨኛል ፤ ያስለቅሰኛል ፤ ስሜቴን 
አውኮት ብዙ ነገሮቼን ያበላሽብኛል። ተሰባስቦ ሲኖር  ደግሞ በፍቅር ሳየው ፤ አንዱ ለ አንዱ ሲሆን ፤ በዘር 
ሳይታጠር ተጋብቶ ሲኖር እሱን ሳይደግሞ ተስፋዬ  ይለመልማል።

ቀለም ፦እሺ በደስታ (ሳቅ ) ቸሬ ሸራን ከማናገር ፣ እንደው ከዚህ ጋር ተያይዞ የኪነጥበብ 
ሥራ ለተጎዳ ስሜት ማገገሚያ ፤ አንደበት ለሌለው  አንደበት ፤ ለተገፉት መሸሸጊያ እንደሆነ ይታወቃል::  ይህን ሁላ ሃይል እንዳንጠቀም ፖለቲካ የሚባል 
አጥር አለ። እንዴት ናቹ ግን አንተና ፖለቲካ? የጥበብ  ሰውስ በዚህ አጥር ተከልሎ መኖር ይችላል? 

ቸርነት ወልደ-ገብርኤል ፦ አይደለም የጥበብ ሰው  ማንም ሰው ከፖለቲካ ውጪ መሆን አይችልም።  ሌላው ቢቀር ወላፈኑ ይነካሃል። ምክንያቱም የሚወሰነው ውሳኔ ቤትክ የሚገባ ነው። እኛ ሀገር  ጥቅም ሲኖር ኪሳችን አልገባም እንጂ ጥቅምም  ሲኖር ቤትህ ይገባል። የእውነት ለመናገር ጥቅም 
ኖሮ የተካፈልኩት ያለ አልመሰለኝም። ቤቴ  መብራት የለም ውሃም በልክ አይደርሰኝም የአባይ  ልጅ ውሃ ጠምቶኛል። የኪነ-ጥበብ ሰው ስትሆን 
ደግሞ ያገባኛል የሚለው ስሜት ብዙ ይኖርሃል።  ምክንያቱም የኪነ-ጥበብ ሰው ከሕብረተሰቡ  ነው እየወሰደ ሚሰራው ግጥም ቢፅፍ ፤ ስዕል 
ቢስል ፤ ቲያትር ቢሰራ ፤ ድርሰት ቢፅፍ ካራክተር  የሚወስደው ከሕብረተሰቡ ነው። እንዳውም ቀጥታ  የሚመለከተው ነገር ሆኖ ቁጭ ይላል:: አንድ ግጥም 
ነበረኝ ካስታወስክ ጠቅላይ ሚንስተሩ አክቲቪስት  መሆን አትችሉም ባሉ ሰዓት የፃፍኩት። ተማር ልጄን  ፤ ስለ ቀጠሮ አይነት የመሰሉ የኪነ ጥበብ ስራዎችን 
ብቻ እንድንሠራ የነገሩን:: ነገር ግን ፖለቲከኞቻችን  ሰዎች ናቸው ሊሳሳቱ ይችላሉ ምክንያቱም ፍፁም 
ያልሆኑ ሰዎች ስለሆኑ በዚህ ጊዜ የኪነጥበብ ሰው  ነው ከፊት ሆኖ ጠቋሚ መሆን ያለበት። መልካም  ለሰራውም ማስጨብጨብ አለበት::

ቀለም ፦ ግጥሙን ልትልልን ትችላለህ? 
ቸርነት ወልደ -ገብርኤል ፦ እሺ እልልሃለሁ።

ደጉን የሚመራ ፈራጅ ደግሞ እንደ ቅን 
ዳኛ 
አምላክ ከሰው መሃል ሰው ሲሰጥ አርጎ 
ጥበበኛ 
ቀለሙ የማይነጥብ ሸራው የልብ አድራሽ 
ሕሊናው ያልተላላጠ
ጥበበኛ ንብረት ነው ከፈጣሪ ለሕዝቡ 
በችሮታ የተሰጠ
አምላክ ከሕዝብ መሃል ጥበብን የሰጠው  ሰው
እሱ የሱ አይደለም የሕዝቡ ንብረት ነው ።

ይቀጥላል....


አዘጋጅ 
ዳግም ተስፋ
ቀለም መፅሔት ቅፅ 1 ዕትም 4 
ጥቅምት 15/2018 ዓ.ም
6🥰3🙏2
የቀጠለ

ቀለም ፦ ዋው ድንቅ ነው ቸሬ

ቸርነት ወልደ -ገብርኤል ፦ ግጥሙ ረጅም ነው። ነገር ግን በነዚህ ስንኝ ውስጥ ዋና ሀሳቡ አለ። ስለዚህ በሕዝብ ታምኖበት ሀላፊነት የተሰጠው ፖለቲከኛ ጠቋሚ ማግኘት አለበት ባይ ነኝ። የጥበብ ሰው የሕዝብ ንብረት ስለሆነ ባለቤቱ ሀብቱ ሕዝብ ነው። አርቲስት ምን ደሀ ቢሆን ባይሞላለት ለሕዝቡ እና ለሕሊናው ታማኝ የሆነ ፤ እውነት በነፈሰበት ብቻ የሚነፍስ ነው::

ቀለም ፦ እስቲ ደግሞ የኋሊት እንመልስህ 1987 የሁለተኛ መሰናዶ ትምህርትህን ከጨረስክ በኋላ መድኋኒዓለም የስዕል ትምህርት ቤት ለአራት አመት ያህል ተምረሃል በዛን ወቅት አቶ ተስፋዬ የሚባሉት መምህርህን በእጅጉ ታከብራቸዋለህ ፤ ያልተዘመረላችው ሊቅ ፤ የሀገር ባለውለታ ናቸው ብለህ ነበር። አቶ ተስፋዬ ማን ናቸው? ቀለም እሳቸውን ባንተ በኩል ይዛ መቅረብ ትሻለች።

ቸርነት ወልደ-ገብርኤል ፦ ስዕል ሳጠና በእርሳስ ያስተማሩኝ እርሳቸው ናቸው። ከዛ በፊት ከታላቅ ወንድሜ ኮፒ እያደረኩኝ አጠና ነበር። በይበልጥ ግን ባለውለታዬ እሳቸው ናቸው:: ምንም አንድና ሁለት የለውም። ብር ኖረኝ አልኖረኝ ገብቼ እማራለሁ ፤ ደርሶብሃል ክፍያ የሚሉ አይነት አይደሉም። ቤታቸው ኮተቤ ነበር። ተርፏቸው ወይም ኖሯቸው አይደለም ከቤታቸው በባስ ነበር የሚመላለሱት። እኔን ግን ዛሬ ባለመኪና አድርገዋል። እሳቸው ባስተማሩኝ ጥበብ እኔ መተዳደሪያ አግኝቻለሁ:: የእውነት ለመናገር በሕይወት እያሉ አምስት ሳንቲም ያደረኩላቸው ነገር የለም። ከጓደኞቼ ጋር የሆነ ነገር ላደርግ አስቤ አልተሳካም ነበር። እግዚአብሔር ነብሳቸውን ከደጋጎቹ አጠገብ ያሳርፍልኝ።

ቀለም ፦ አሜን አሜን (ፀጥታ ሰፈነ ለትንሽ ደቂቃ) ምናልባት ምትጨምርልን ካለ ስለሳቸው

ቸርነት ወልደ-ገብርኤል ፦ ሁለት ልጆቻቸው ፡ወንድና ሴት ሰዓሊ እንደነበሩ አውቅ ነበር። የዘሩት ግን አሽቷል። እኔ ማውቀው ሰዓሊ አብዛኛው ከእሳቸው የወጣ ነበር። በእኔ እድሜ ያሉት አሁን የሚታዩት ጎበዝ የሚባሉ ሰዓሊዎች አብዛኞቹ የእሳቸው ፍሬ ናቸው። ባለውለታ ናቸው ምን አልባት አንድ ቀን ሊዘመርላቸው ይችል ይሆናል ።

ቀለም ፦ እንደው እሳቸው ያስተማሯቸውን የስዕል ባለሞያዎች መጥቀስ ይቻላል ?

ቸርነት ወልደ-ገብርኤል ፦ ማንን ትቼ ማንን ልጥቀስ በጣም ብዙ ናቸው። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአርት ስኩል
ትምህርት ቤት መምህራን ጭምር የእሳቸው ተማሪዎች የነበሩ አሉ።

ቀለም ፦ ከ ባለቅኔ ሙሉጌታ ተስፋዬ (አያ ሙሌ) ነብሳቸውን ይማርና ከእሳቸው ጋር ያለህ ቀረቤታ ምን ያህ ነበር?
ቀጥረውህ በመቅረትህ እንደቆጨህ ተናግረሃል። እስቲ የዛኔ ስለነበረው ሁኔታ አውጋን ምን ነበር የተፈጠረው?

ቸርነት ወልደ-ገብርኤል ፦ ቀረቤታ የለኝም ነገር ግን ሙሌን አውቀዋለሁ። ግጥሞቹ ለሊቱን ሙሉ ቁጭ
የሚያደርጉኝ ናቸው። በጣም እጅግ አከብረዋለሁ አንዳንድ ግጥሞቼ ከእሱ ዜማ ጋር ሲሄደብኝ እናደዳለሁ።
ይሄን ያህል በኔ ሥራዎች ላይ ተፅህኖ ማሳደር ችሏል። የተገናኘነው አራት ኪሎ ስንዱ ጋር ነበር። አራት ኪሎ
ደግሞ አርት ስኩል ትምህርት ቤቴ ያለበት ነው። ኑሮዬም እዛ ነበርና ማለዳ የሚባል ካፌ ቡና እየጠጣሁ መጣ። ቸሬ እባላለሁ ብዬ ተዋወኩት። ቸሬ አንቺ ነሽ አወኩሽ አለኝ። ከዛ ላገኘው እንደምፈልግ ስነግረው ከሰዓት ቀጠረኝ
ተቀምጠን እንድናወራ። ያው ተቀምጠን ሲል እየቃምን ለማለት ነው። እኔ ደግሞ የዛ ሰው አይደለሁም እና ቀረሁ
ባደርገውም አይደብረኝም። ግን በቃ በጊዜው አልቻልኩም። እና በነጋታው ሳገኘሁ ጠብቄህ ነበር ቁጭ ብይ
አለኝ። ነገርኩት እንደዚህ እንደዚህ ነውና መጥቼ ባላደርግ እንዳልደብርህ ብዬ ነው አልኩት። ጭንቅላቴን በእጁ እያሻሸው። ምን ችግር አለው እንዲሁ ቢሆንስ መጥተህ ብትቀመጥ ብሎኝ ነበር። ይሄው ነው እንግዲህ ከሳቸው
ጋር ያለኝ ቀረቤታም ቁጭትም።

ቀለም ፦ ብዙ ጊዜ ስዕል የምትስለው ለሊት ነው። ሆኖም ዛሬ ላይ ትልቅ ቦታም የደረሱም ሆነ ለመድረስ የሚፍጨረጨሩ እየደወሉልህ ግጥም ያነቡልሃል። አንተም ለስዕል የመደብከውን ጊዜ ሳትሰስት ቀንሰህ በመስጠት ትሰማቸዋለህ። እስቲ ሰለ እዚህ ትንሽ አውጋን

ቸርነት ወልደ-ገብርኤል ፦ ከብዙ ገጣሚያን ጋር እገናኛለሁ። ግጥማቸውን ያነቡልኛል። ግጥም ሲፃፍ አንብቡኝ ይል የለ? ያነቡልኛል:: መድረክ የማግኘት ፍላጎት ይኖራቸዋል። የዛኔ ለምን እንዲ እንዲ አታደርጉም እከሌን ብታገኘው ጥሩ መድረክ ይሰጥሃል። የሚል ምክር እለግሳለሁ እኔ ደውዬ ማውራት ካለብኝ አናግርላቸዋለሁ። አንዳዴ ግጥማቸው ሲያሰክረኝ እዚህ ቦታ መድረክ አለ ብዬ ጋብዛቸዋለሁ። በቅርብ ደግሞ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባህል ማዕከል ተከፍቶ ስለ ነበር ለምን እዛ አትሄዱም ብዬ መክራለሁ ምክንያቱም እንዳልኩህ ግጥም አንብቡኝ ይላል።

ቀለም ፦ በእውነቱ እያደረክላቸው ያለው ነገር ትልቅ ሥራ ነው ፈጣሪ ያክብርልን። ነገርን ነገር ያነሳዋል እና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባህል ማዕከል ካነሳኸው አይቀር አንተም በግጥም የተሰራህበት እንደሆነ ተናግረህ ነበር። ባንተ ጊዜ የነበረው ድባብ ምን ይመስላል? በባህል ማዕከል ቆይታ ትዝታህን ያደመቀው ልዩ ገጠመኝ  ካለህም ብታጋራን ።

ቸርነት ወልደ -ገብርኤል ፦ ባህል ማዕከል ትልቅ ሃይል ይሰጥሃል። ማለት የሚነበበው ግጥም የምታገኛቸው ገጣሚዎች በጣም ያነቃቁሃል። እኔ ደግሞ ትንሽዬ መቅጃ ነበረችኝ እና የሁሉንም ግጥም ቀድቼ ቤቴ ገብቼ ካሴቶቹን እንደገና ከፍቼ እሰማ ነበር። በባህል ማዕከል ቆይታዬ እጅግ በጣም የተጠቀምኩበት ከብዙ ነገር መናገር የተቆጠብኩበት አንደበቴን ጭምር የገራሁበት ነው። አንዳንድ አመት ረቡዕ አንዳንድ አመት አርብ ነበር የሚቀርበው። ስነ ፅሁፍ ግጥም ፅፌ እዛ መድረክ ላይ ለማቅረብ ያለኝ ጉጉት በጣም ነው የሚገርመው። ከአራት ኪሎ አርት ስኩል እኔ ብቻ ነበርኩ። ከስፖርት ዲፓርትመንት ደሞዝ ጎሽሜ (በኋላ ነው ስነ -ፅሁፍ ዲፓርትመንት የተማረው ፤ ይርጋ ገላው ከ ሕግ ዲፓርትመንት ፤ ሕይወት እምሻው እና ሕይወት ታደሰ ከ ፖለቲካል ሳይንስ መሰሉኝ ፤ በኋላ ላይ እነ ሰለሞን ሳህለ እና ትግስት ማሞ ፤ ዳዊት ተስፋዬ (ደጃፍ) ፤ ሙዴ የሚባል አንድ ልጅም ነበር ከደብረብርሃን አካባቢ ሙድ የሚባል አንድ መፅሐፍ አሳትሞ ነበር። አሁን በሕይወት የለም ነብሱን ይማረው። ለአብነት ያህል ነው የጠቀስኳቸው በጣም ብዙ ናቸው። በቃ ምሽቱን በስነ-ፅሑፍ ያደምቁት ነበር። እዛ ለማቅረብ ያለውን ትንቅንቅ ልነግርህ አልችልም። አንዳዴ ወረቀት ይበዛባቸው እና የተመረጡት ብቻ ናቸው የሚያቀርቡት:: የሚገርመው ግጥም አንብቦ መውረድ የለም እዛው ቆመህ ሂስ ይሰጥሃል። ቴዎድርስ ፀጋዬ (ርዕዮት) አንዱ አቅራቢ ነበር። የሚሰጡት ሂስ ራሱ በጣም የሚገርም ነበር። እንዲ አሥራ ምናምነኛው መስመ ር ላይ እንዲ ያልከው ከምን ይገናኛል ምን ለማለት ፈልገህ ነው? እስቲ አንዴ ደግመህ በለው የሚል ልቅም ያለ ሂስ አይነት የሚገራርም ጆሮዎች ነበሯቸው። በተለይ የስነ ፅሁፍ ተማሪዎቹ በጣም ጎበዝ ነበሩ። ለኔ የባሕል ማዕከል ቆይታዬ እንደ መዝናኛም ፣ መሰሪያም ፣ መደበቂያዬም ነበር።

ቀለም ፦ ግሩም ነው ቸሬ ዓመተ ምህረቱ ስንት አካባቢ ነበር?

ቸርነት ወልደ -ገብርኤል ፦ ከ 1993 - 1994 አካባቢ ነው። አሁን በቅርብ እራሱ በ 2017 ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ፕሮግራም አዘጋጅተው ጠርተውን ነበር። ከብሔራዊ ትያትር ሔኖክ በሪሁን ፣ ከዘፋኞች ሚካኤል በላይነህ ጨምሮ በቃ ትዝታዬን ቀሰቀሱት ነው የምልህ።
1
ቀለም ፦ ግጥምን በጃዝ በሀገራችን ያስጀመርከው አንተ እንደሆንክ ይታወቃል:: ሂደቱ ምን ይመስላል? ለምንስ ጥለኸው ወጣህ?

ቸርነት ወልደ-ገብርኤል ፦ ይሄን ጥያቄ ተደጋጋሚ ተጠይቄ በቂ ምላሽ ሰጥቻለሁ ብዬ አስባለሁ:: አሁን ላይ በየሚዲያው ይሄን መናገር ብዙ ደስተኛ አያደርገኝም:: መጠየቁ ተገቢ ነው ብዬ አላስብም።

ቀለም ፦ ከስዕላትህ መካከል አሁን ላይ ያለህበትን ስሜት የሚገልፅልህ ስዕል የትኛው ነው? የአሳሳል ሂደቱንም ጭምር ብትዳስስልን?

ቸርነት ወልደ -ገብርኤል ፦ ይገርምሃል ስዕላቶቼ አብዛኞቹ ስለ ሀገር ናቸው። እና ነጥዬ ይሄ ልልህ አልችልም:: በራሴ ቀለም በራሴ መንገድ ስለ ፍቅር እና አንድነት በዛ አራት ማዕዘን ሰሌዳ አሰፍራለሁ:: አሁን ለምሳሌ ዳግማዊ ምኒልክን ብንወስድ አሁን ላይ ሰው መሆኑ ቀርቶ የአንድነት አርማ ሰንደቅ አላማችን ሆኗል:: ምኒሊክን ስናስብ ሁሌ የምናስበው ትልቅ ሀገር ነው:: በራሱ አንድነትን ፣ አብሮ መኖርን የሰራ ጀግናችን ነው:: ይሄን ትልቅነት በአንድ ሰው መግለፅ እያቃተን መጥቷል። እንዲ ነው እንግዲህ ሰዎች ሲተልቁ:: ጣልያኖች ያነሷቸዋል ፣ ዘፈኞች ያወድሷቸዋል። በዚህም በጎ አድራጎታቸው ይወጣል ምን አልባት ሰው ናቸው እና የተሳሳቱት ነገር ካለ በጎነታቸው በዝቶ ለጨለምተኛ ጣት ቀሳሪዎች ይሸፍንባቸዋል ። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አንድነትን የሰራ ፤ ዲፕሎማሲ የሚችል ከ ጃንሆይ በፊት አላውቅም። ምኒልክ እኮ ያሸነፈውን የረታውን መልሶ ይሾማል። ይሄን ትልቅ ጉዳይ ብስል እንዴት ላመጣው እችላለሁ? ዛሬም ንጉስ ነው ለማለት ምን ማድረግ አለብኝ? በምን አይነት ቀለሞች ብሰራው ፤ ምን ውስጥ ብከተው አንድነትን እሰራለሁ።
ምኒልክን ለመሳል አይደለም የተነሳሁት:: አንድነት የሰራውን ፤ ሀገር የሰራውን እሱን እንደ ሰንደቅ አላማ ለማስቀመጥ ምን ማድረግ አለብኝ የሚለው ሀሳቦች ይይዙኛል።

ቀለም ፦ ከዚህ ጋር ተያይዞ አሁን ላይ ፖለቲካዊ ስሜት የሚቀሰቅሱ ፤ አወዛጋቢ ርዕሰ ጉዳዮችን በስዕል አልያም
በግጥም ይዘህ በምትቀርብበት ጊዜ ምን አይነት ተግዳሮቶች ገጥመውሃል?

ቸርነት ወልደ -ገብርኤል ፦ እግዚአብሔር ይመስገን ብዙ የገጠመኝ የለም። በወያኔ ጊዜ ከትልልቆቹ ይልቅ ካድሬዎች ናቸው የሚያስቸግሩህ። እንዳውም ለትልልቆቹ ደውለን በአንድ ስልክ አስቁመውልን ያውቃሉ።
ለምን ፃፍክ ፤ ለምን ሳልክ ተብዬ አልታሰርኩም ምንም አልሆንኩምም። በዚህ ልክም ነፃነት አሁን አላየሁም::
የትላንቱ ካድሬ እንድትደነብር እንድትፈራ ሊያደርግ ይችል ይሆናል። እሱንም በዘዴ ነው እንጂ ፊት ለፊት መጥቶ ላይጋፈጥህ ይችላል:: የዛሬ ካድሬ ግን እንደሱ አይደለም። ማንም ሳያዘው እንደ ከፍተኛ ባለስልጣን ነው የሚያወራህ። የማንንም ትዕዛዝ ሳልጠብቅ እንደፈለገኝ ማድረግ እችላለሁ የሚል ነው ያለው:: ይሄ ደሞ ሀገርን እንደ ሀገር እንዳትቀጥል በማድረግ ሕዝቡን በሥጋት ውጦ የነገዋን ኢትዮጵያ ስጋት ውስጥ የሚከት ነው:: ደስ ካላለው የፃፍከውን ፅሑፍ ባለማስተዋል አንተን ከፍተኛ የኦሮሞ ፣ ጉራጌ ፤ ትግራይ ወይም የፈለገውን ብሔር ጥላቻ አለብህ ሊልህ ይችላል። አንተ ግን እሱ ጥላቻ አለብህ የሚለው ብሔር አካል ልትሆን ትችላለህ። ይሄን እንኳን አመዛዝኖ ለማየት ያልታደለ ነው:: አንድ ሁለት ሰዎች እንደዚህ ቢያጋጥሙኝም አብዛኞቹ ግን ወዳጆቼ እና አካባሪዎቼ ናቸው። ደሞም ብዙ ግርግር ያለው ቦታ አልሄድም ከስንት አንዴ እንዲህ አይነት ነገር ሲያጋጥመኝ
ያለሜዳዬ የማይመጥነኝ ቦታ ተገኝቼ ብዬ አልፈዋለሁ። ምን ልልህ ፈልጌ ነው በሜዳዬ ምንም አይነት ችግር አጋጥሞኝ አያውቅም ።

ቀለም ፦ ስለ ሀገርህ ወቅታዊ ሁኔታ ትልቁ ስጋትህ ምንድን ነው? ለሀገርህስ የወደፊት ተስፋህ ምንድን ነው?

ቸርነት ወልደ-ገብርኤል ፦ ጊዜው ያስፈራል! እንደምታየው የእርስ በእርስ ጦርነት ያለበት ፤ ሰው ሰራሽ ችግር ጎልቶ የሚታይበት ፤ ሕዝቡ ላቡን ጠብ አድርጎ ያገኘውን ገቢ ከመቀማት ባልተናነሰ ሁኔታ የኑሮ ውድነት ከምን ጊዜውም በላይ የናረበት ዘመን ላይ ነን። መንግስት ሊቆጣጠረው አልቻለም ወይ? ብትለኝ መንግስት እራሱ የፈጠረው ችግር ሆኖ ታገኘዋለህ። እንገንጠል የሚሉ ፤ እኛ አትዮጵያን ነፃ እናወጣለን የሚሉ ሁሉ በመሳሪያ ስለመጡ አካሄዳቸው ያስፈራኛል። ሀገሬን የሚበትኗት ይመስለኝ እና እጨነቃለሁ:: ያመናቸው ኢሊቶች ትላንት ይቃወሙት የነበረውን ዛሬ ላይ ጥብቅና ሲቆሙለት ስናይ ሀገራችን ወዴት እየሄደች ነው? ብለን እናስባለን ፣ እንሰጋለን ፣ እንጨነቃለን። የሐይማኖት ተቋማት ሀላፊነታቸውን በአግባቡ እየተወጡ አይደለም:: ሀገር ሰርተዋል የሚባሉ ተቋማትን በዜሮ ማባዛት ሀገር እንዳይቆም ያደርጋል። ይሄ አደገኛ አካሄድ በጣም ያሳስበኛል:: የተከበሩ ሽማግሌዎች ወደ ልመና ተሰማርተው ሳይ ፤ ጡረታ የወጡ የተለያየ መስሪያ ቤት በመስራት ሀገር ያገለገሉ የሀገር ባለውለታዎች በጎዳና ወጥተው ጠጋ ብለው እባክህ ልጄ እንደው ትንሽ ሳንቲም ካለ ሲሉ ያናድደኛል፣ ይከፋኛል እንደ አንድ ወገን የሚረብሸኝ ነገር ነው:: ሀገር መክፈል እንደማትችል ባለውለታዋን እንደማታነሳ ሳስብ ያማል ይሄ ትልቅ ስብራት ነው:: ከትላንት ዛሬ ነገሮች እየከበዱ ነው:: ያውም ሰው ሰራሽ መንግስት ሰራሽ በሆነ ችግር። እንደውም አንዳዴ ያለንበት አየር ይለያያል። እንዴ ብዬ እራሴን ጠይቃለሁ ምንድን ነው እየተካሄደ ያለው? ሰዎች አያውቁትም ነው? እኔ ተሳስቻለሁ? አንዳንዴ እኔ ጨለምተኛ ነኝ እንዴ ያስብላል። ያናድድሃል! አሁን የሙሰኛ ብዛት ሀገር ያለችበትን አይነግርህም? በየ ቀበሌው ፣ በየ መንግስት አስተዳደሩ ያለ ፍጥጥ ያለ ሙስና:: ተደብቆ ሁላ አይደለም የሚቀበልህ ፊት ለፊት ሆኖ ነው። ወዴት እየሄድን ነው? ይሄም በጣም ያሰጋኛል:: ኢትዮጵያ ረሀብተኛ ናት ተብሎ ድሮ ታስታውሳለህ? መዝገበ ቃላት ላይ እንኳን እንደምሳሌ እስክንጠቀስ የደረስንበትን? የሚገርምህ የሰዉ ፊት ግን ደስታ አለው ፤ ሳቅ ፈገግታ በእጅጉ ሞልቶት ነበር:: መጥተው ሲያዩ የሚራመደው ሰዉ እንደ መስከረም አደይ ፊቱ ፍክት ብሎ በፈገግታ ረሃብ ያለ አይመስልም ነበር:: አሁን እኮ ብቻውን የሚያወራ ሕዝብ ነው ያለው። መንገደኛውን ብታየው ሳቅ ይናፍቅሃል በፊቱ ላይ ፈገግታው የደረቀ ነው:: ሀገሪቱ ወዴት እያመራች ነው የሚያስብለው ይሄ ነው አንደኛው:: የተሰራ ሥራ የለም ወይ? የምትተቸው ነገር በዛ እስኪ ከተሰራው ስራዎች ተናገር ብትለኝ አንተ ፐ ያልክበትን እኔም ፐ ብያለሁ:: ነገር ግን ሰው በየቤቱ የሚበላው የሚጠጣው ነገር ቢኖር ባይቸገር እመርጣለሁ። ይሄ ነው ለኔ ቀዳሚው ልማት:: የትም ቦታ ሰርቶ የሚበላበት ሀገር ሲፈጠር እሱ ለኔ ልማት ነው::

ይቀጥላል ...

አዘጋጅ 
ዳግም ተስፋ
ቀለም መፅሔት ቅፅ 1 ዕትም 4 
ጥቅምት 15/2018 ዓ.ም
2
የቀጠለ...

ቀለም ፦ እንደው ይሄን ስትናገር የበዓሉ ግርማ የኔ  ውብ ከተማ የሚለውን ግጥም አስታወስከኝ

ቸርነት ወልደ-ገብርኤል ፦ ዋው በጣም ጥሩ ነገር ነው  ያመጣኸው።

የኔ ውብ ከተማ
ሕንፃ መች ሆነና ፣ የድንጋይ ክምር
የኔ ውብ ከተማ
መንገድ መች ሆነና ፣ የድንጋይ አጥር
የኔ ውብ ከተማ ፣ የኔ ውብ አገር
የሰው ልጅ ልብ ነው 
የሌለው ዳርቻ ፣ የሌለው ድንበር
ሕንጻው ምን ቢረዝም ፣ ምን ቢፀዳ ቤቱ
መንገዱ ቢሰፋ ፣ ቢንጣለል አስፓልቱ
ሰው ሰው ካልሸተተ ፣ ምንድነው ውበቱ ? 

ቀለም ፦ ዋው ስሜትህን በግጥሙ ውስጥ አነበብኩት::  አንተም የበዓሉ ግርማ ልብ አለህ::

ቸርነት ወልደ -ገብርኤል ፦ አመሰግናለሁ በጣም  ወንድሜ

ቀለም ፦ በዚ ሁሉ ነገር ውስጥ የቸሬ ተስፋው ምንድን  ነው?

ቸርነት ወልደ -ገብርኤል ፦ ምንም አንድ እና ሁለት  የለውም እግዚአብሔር ነው ተስፋዬ። በየገዳማቱ  የአባቶቻችን ፀሎት ፤ በየ መስጅዱ የሚደረግ ፀሎት  ኢትዮጵያን ይታደግ ነው የምለው። ይሄን ስል  እጃችንን አጣምረን እንቀመጥ ማለቴ አይደለም::  ሁሉም በየመክሊቱ በታማኝነት እና በቅንነት መስራት  እንዳለበት ሊዘነጋ አይገባም።

ቀለም ፦ ግሩም ነው ቸሬ። እስኪ ደግሞ ወደ ስዕላትህ  ልመልስህ እና ከስዕላቶችህ መሐል ላንተ ልዩ ስሜት  የሚሰጥህ የትኛው ነው?

ቸርነት ወልደ -ገብርኤል ፦ ሁሉም ስሜት የሰጡኛል።  ልዩ ስሜት ካልከኝ አራት አመት አካባቢ የሳልኩት  ስዕል ነበር። አንድ ኮረብታ ላይ ወጥቶ ሰንደቅ ዓላማ  በጥርሱ ይዞ ብቻውን የቆመ ፈረስ ፤ ከርቀት መንደር  ላይ ደግሞ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማ የሰቀለ  መንደር ፤ መሐል ላይ ማሳዎች ያሉበት ፤ ሰማዩ እጅግ  በጣም ክብድ ብሎ ሊወድቅ የደረሰ የሚመስል::  እንደዚህ አይነት ስዕል ነበረኝ:: አንድ እጅግ በጣም  የማከብረው ዶ/ር ቤተ መንግስቱ የሚባሉ ሰውዬ  የራሳቸው አድርገውታል:: እና እሱን ስዕል በጣም  ወደዋለሁ። ሀገር እንስራ የሚል ፤ ጀግና ፈላጊ ፈረስ ፤  ለሆነ መንደሮች ሊታይ ኮረብታ ላይ የቆመ ፤ ባንዲራ  እየወደቀ ነው ይኸው ከመሬት አንስቼ ነው የቆምኩት  የሚል ፈረስ ፤ ሀገር የሚሰራ ንጉስ ፈላጊ። እሱ በጣም ልዩ ስሜት ይሰጠኛል።

ቀለም ፦እስቲ ደግሞ ወደ ተተኪው ወጣት እንውሰድህ  አሁን ላይ ብዙ ወጣቶች አርዐያ አጥተው መንገዱ  ጠፍቷቸው ግራ የተጋቡበት ሁኔታ አለ:: ይሄን ክፍተት  ለመሙላት ቀደምት የኪነ-ጥበብ ስዎችን አሁን ካሉት  የኪነ ጥበብ ወጣቶች ለማገናኘት ምን መደረግ አለበት  ብለህ ታስባለህ ?

ቸርነት ወልደ -ገብርኤል ፦ ከባድ ጥያቄ ነው።  ወጣቱ አንድን ነገር አጣርቶ የማወቅ ፍላጎት ያላቸው  አይመስለኝም:: ትውልዱን ጥራዝ ነጠቅነት በሽታ  የተጠናወተው ይመስለኛል። ይሄን ለማስቀረት  ቀደምቶቹ ምን ማድረግ አለባቸው? ብትል  አላውቅም። ተደማምጠው የሚያሸንፉ አይመስለኝም።  ቴክኖሎጂው ብዙዎቹን ሰዎች አሸንፏቸዋል። እንደ  መፍትሄ ላቀርብ የምችለው ነገር የለም:: ባይሆን  ልጆቻችንን ጓደኛ ማድረግ ከቻልን በቂ ነው:: ሌላው  በጊዜ ሂደት ቀስ እያለ ይስተካከላል::

ቀለም ፦ አሁን ላይ ብዙ ወጣቶች ወደ ኪነ -ጥበብ  መግባት ቢፈልጉም መንገዱ ግን ቀላል አልሆን  ብሏቸዋል። ላንዳንዶቹ ደግሞ በቀላሉ በ ማህበራዊ  ሚዲያ በኩል እራሳቸውን እያወጡ ነው። የጥበብ ሰው  የማህበራዊ ሚድያ ተግዳሮቱ ምን መምሰል አለበት ብለህ ታስባለህ ?

ቸርነት ወልደ-ገብርኤል ፦ እንዳውም አሁን እድል  አለ። የኪነ-ጥበብ ሰው እራሱን ማውጣት የሚችልበት  እድል አለ:: ድሮ የተወሰነ ነበር። ክበባት ናቸው  የነበሩት:: በክበባትም ወጥተህ የሚያይልህ ውስን  ሰው ነው:: ትያትር ቤት እኮ የሚደንቅ በጣም ትላልቅ  ቲያትር ተከፍቶ ትያትር ቤቱ ሞልቶ አታየውም::  ግማሽ እራሱ ከደረሰ በጣም ትልቅ ነገር ነው። እድሜ  ለሶሻል ሚድያ አሁን በኪነ-ጥበብ ውስጥ ያለ ሰው  በሶሻል ሚድያ ብዙ ሚልየን ሰው አይቶለት በገቢ  ደረጃ ሳንቲም ሰርቶ ያድራል። ትረካ ሁሉ ተጀመረ  አይደል እንዴ? መፅሐፍ ገዝተን ከምናነብ ማዳመጥ  የምንመርጥ በዝተናል እኮ። ሶሻል ሚድያው የሰጠው  መድረክ ቀላል አይደለም። ስለዚህ ከበፊቱ አሁን  ቀንሷል የምንለው አይደለም። የነፃነቱ ጉዳይ እንዳለ  ሆኖ። እንዳውም በአለም ዙሪያ መታየት የሚችል  ነገር መስራት ተችሏል።

ቀለም ፦ እንዳው ከዚህ ጋር ተያይዞ አሁን ላይ  የውስጣቸውን ክህሎት እና ዝንባሌ ተከትለው  በሞያው ለመሰማራት ያሰቡ ወጣቶች ምን አይነት  ምክር አለህ?

ቸርነት ወልደ-ገብርኤል ፦ መስራት ነው ቀጣይነት  ባለው መንገድ። ሰው በሰራ ቁጥር ልምድ ያገኛል ፤ ልምድ ያዳብራል። ልምድ ደግሞ ያው ስህተትን  ይቀንሳል:: ዘመኑን በመዋጀት ጊዜው በሚፈልገው  ቦታ መገኘት። ሶሻል ሚድያውንም ሲጠቀም በተቻለ  መጠን እውነተኛ ለመሆን መሞከር። ሳንቲም  ለማግኘት ተብሎ ሀገር የሚጎዳ ፤ ትውልድ የሚያሶቅስ  ነገር አለመስራት። አንዳንድ ወጣት አቅማቸውን  ሲያወጡ አያለሁ። ድርሰት ፅፈው በሥነ ሥርዓት  አጫጭር ፊልም ሲሰሩ አያለሁ:: በሰሩ ቁጥር ደግሞ  ልምዱ የሚሰጣቸው ነገር አለ። በዓመቱ ትልቅ ፊልም  ሊሰሩ ይችላሉ::

ቀለም ፦ ቅኔ ነው ትዝታ የሚለው የሚካኤል  በላይነህ ዘፈን ላይ የሳልከውን ስዕል ከሸጥከው በኋላ  ለማስመለስ የሄድክበት መንገድ ነበር:: እስኪ ስለሱ  አውጋን

ቸርነት ወልደ -ገብርኤል ፦ እሱን አይደለም ይሄን  ጥያቄ ሌላም ሰው ጠይቆኛል። እንዴት ጥያቄው ሊነሳ  እንደቻለ አላውቅም። በነገራችን ላይ ይሄ የሁሉም  ሰዓሊ ፍላጎት ነው። ስዕል ትሸጣለህ ብሩ ያልቃል ያ  ስዕል አጠገብህ የለም ያንተ ቢሆን ግን ትፈልጋለህ።  ባልሸጥኩት ልትል ትችላለህ ይሄን ቸሬ ብቻ አይደለም  ሁሉም ሰዓሊ ነው። አንድ ሰዓሊ ይሄን ማሰቡ እንደ  ትልቅ ነገር ሊቆጠር የሚገባው ጉዳይ አይደለም።  ምክንያቱም ማነው የወለደውን ልጅ የማይናፍቅ? ስዕል  እኮ ለሰዓሊ እንደዚህ ነው። አንዳንዴ ሰው ቤት ሔጄ  ሥራዬን እያየውሁ ባልተሸጠ ይሄ ነገር እላለሁ። ባለቤቴ  የአክሱም ጫፍ አቅማዳ የደበበ ሰይፉን ግጥም ስየው  ነበር። እና በምሸጥበት ጊዜ ቤቴ አልነበረችም። መሸጡን  ያወቀች ጊዜ በጣም አዝና ነበር። አስታውሳለሁ እስከ  ምደነግጥ ድረስ ነበር የተቆጣችው። እንግዲህ ሰዓሊ  ሆነህ ከሆነ ጊዜ በኋላ ቤትህ አለመኖሩ ምን ያህል እንደ  ሚደብርህ አስበው። ገንዘብ ኖሮኝ ሁሉንም ስዕሎቼን  ብገዛ በጣም ደስ ይለኛል። ሰብስቤ የኔ ባደርጋቸው ደስ  ይለኛል። ስለዚህ ወንድሜ ሁሉም ስዕላቶቼ ላይ ይሄ  ስሜት አለ።

ቀለም ፦ ከፍተኛ የሸጥከው የስዕል ዋጋ ምን ያህል ይሆነናል ? ዝቅተኛውስ ?

ቸርነት ወልደ -ገብርኤል ፦ ኧ ለመንግስት አሳልፈህ  ልትሰጠኝ ነው? (በቀልድ ቢጤ በሳቅ በመታጀብ  የተመለሰ) ምኖረው በስዕል አይደል መተዳደሪያዬ  ስዕል ነው። ባለቤቴ በጣም ታግዘኛለች::

ቀለም ፦ (ረጅም ሰዓት ሳቅ )

ቸርነት ወልደ-ገብርኤል ፦ ይሄን መናገሬ ምንም አይጠቅማቸውም ወንድሜ::

ቀለም ፦ እሺ (ሳቅ) ባለቤትህን ካነሳሀት አይቀር ቤተሰብህ ሥራዎችህን እንዴት ባለ አኳኋን ይቀበሉታል?
2
ቸርነት ወልደ -ገብርኤል ፦ አንድና ሁለት የለውም በጠም ጥሩ ነው:: ያው ትልቁ ቤተሰብ የሚባለው መጀመሪያ ባለቤትህ ናት ። ሌላው በረከቶችህ ናቸው:: ልጆቼ በረከቶቼ ሥራዎቼን በጣም ይወዳሉ። ባለቤቴ ዋጋ እስክትከፍል ድረስ ትረዳኛለች ታግዘኛለች በሰራው ቁጥር ደስተኛ ናት:: ካልሰራው እሷንም ስለምበጠብጥ ነው። እጨቃጨቃለሁ ይደብረኛል ደስተኛ አልሆንም። የኔ ደስታ በሥራዎቼ ውስጥ ነው ያለው። ደስታ ወደ ቤተሰቤ ይጋባና ቤቱ ሙሉ ደስተኛ ይሆናል።

ቀለም ፦ ጥያቄያችንን ወደ ማጠቃለል እየሄድን ነው ዛሬ ላይ ምን እየሰራህ ነው ወደፊትስ ካንተ ምን እንጠብቅ? በቀለም በኩል ሹክ የምትለን ካለ?

ቸርነት ወልደ-ገብርኤል ፦ አሁን ላይ እንደተለመደው ያው ለሊት ከስድስት ሰዓት በኋላ ስዕል እስላለሁ:: የቅኔ ቤት የሚል መፅሐፍ ፅፌ ጨርሻለሁ። ተስፋሁን ከበደ (ፍራሽ አዳሽ ) የሚመሰገን ሥራ በዚህ መፅሐፍ ሰርቷል። እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ሕዳር መጨረሻ አካባቢ ለንባብ ይቀርባል::

ቀለም ፦ ቸሬ መጻፍህ ምን አይነት ይዘት አለው?

ቸርነት ወልደ-ገብርኤል ፦ ስለፍቅር ፣ ስለትዝታ ፣ ስለ ሀገራችን፤ ስለባንዲራ ፍቅር ፣ ስለ ፍትህ እና እውነት ጭምር ተዳሶበታል::የእውነት እውነት ነው ሀገር ሊያኖር የሚችለው? ትክክለኛነት ነው ሀገር የሚያኖረው የቱ ነው? አንዳንዴ ትክክል ሆኖ እውነት ላይሆን ይችል የለ? እነዚህን ሀሳብም ይዳስሳል። ከትላንትናውም አለመማራችንን ኪነ-ጥበባዊ ለዛ ባለው መንገድ እንወቅሳለን።

ቀለም :- በጣም ደስ ይላል ቸሬ በምን መልክ ነው እነዚህን ሀሳቦች ይዘህ የቀረብከው?

ቸርነት ወልደ-ገብርኤል ፦ ሙሉ በግጥም መልክ ነው ይዤ የቀረብኩት።

ቀለም ፦ ግሩም በጉጉት እንጠብቃለን። ተስፋሁን ከበደ (ፍራሽ አዳሽ ) በግጥም መድብለህ ምን አይነት ሚና ተጫውቷል?

ቸርነት ወልደ-ገብርኤል ፦ ከኔ ጋር በመሆን ትልቁን የአርትዖት ሥራ የሰራው እሱ ነው:: አሁን ምስጋና አቅርብ ብባል ተስፋሁን ከበደ ከዝግጅቱ ጀምሮ አብሮኝ ስለነበር አመሰግናለሁ የምለው ወዳጄ ነው::

ቀለም ፦ በጣም ደስ የሚል ዜና ነው መፅሐፍሕን በጉጉት እንጠብቃለን ቸሬ

ቸርነት ወልደ-ገብርኤል ፦ አመሰግናለሁ ከልብ

ቀለም፦ እንደው በመጨረሻ ብትጠየቅ ደስ የሚልህ ጥያቄ ፤ ማስተላለፍ የምትፈልገው መልዕክት ካለ እድሉን ላንተ ሰጥተናል

ቸርነት ወልደ-ገብርኤል ፦ ሃገር እንውደድ ነው የምለው። ሃገር ማለት ደግሞ ጎንህ ያለው ጓደኛህ ፤ አጠገብህ ያለ ሰው ብታውቀውም ባታውቀውም እሱ ነው አገርህ። ከመሃላችን አንድ ሰው እጅግ በጣም የምንቃወመው እና የምንጠላውን ሃሳብ ይዞ ቢቀርብ ሀሳቡን ሞግተን እሱን ግን በሰውነቱ መውደድ  ብንችል ። ምክንያቱም ሐሳብ ይወለዳል ፣ ያድጋል  ይሞታል ወደ እውነቱ ፈጣሪ እንዲመልሰው በመመኘት ክቡር
ሰውነቱን ግን ማክበር እጅግ በጣም ጠቃሚ ነው። አካልህ ነውና ቆርጠህ አትጥለውም:: ሃገር እንዲቀጥል ይህ
አይነት አመለካከት ቢኖረን እላለሁ። የሰው ሁሉ ጭንቀቱ ሀገሩ ነው። ደጋግመህ ብትጠይቀኝ ደስ የሚለኝ እራሱ ሀገሬን ነው። ምን ደስ ይልሃል ብትለኝ ሃገር የሚወድ ሰው ፤ ለእውነት በእውነት የቆመ ሰው ፤ የራሱን ፍላጎት ወደጎን ትቶ ለሌሎች ፍላጎት ዘብ የቆመ ሰው ማየት:: እንደዚህ ደጋግመህ ስለ ሀገሬ ብትጠይቀኝ ደስ ይለኛል። ይሄው ነው ወንድሜ

ቀለም ፦ አክብረኸን ጥያቄያችንን ስለተቀበልክ በእውነቱ ስለነበረን ቆይታ ከልብ እናመሠግናለን ቸሬ

ቸርነት ወልደ -ገብርኤል ፦ መርጣችሁኝ ፣ አክብራቹሁኝ እንግዳ ስላደረጋችሁኝ እግዚአብሔር ያክብርልኝ
ሐሳባችሁን እግዚአብሔር ይሙላላቹህ

ቀለም ፦ አሜን አሜን ቸሬ በድጋሜ ስለነበረን ቆይታ ከልብ እናመሠግናለን !


አዘጋጅ 
ዳግም ተስፋ
ቀለም መፅሔት ቅፅ 1 ዕትም 4 
ጥቅምት 15/2018 ዓ.ም
3
ቀለም መጽሔት እስካሁን 5 እትሞችን ለንባብ ያበቃች ሲሆን ፤ ለስድስተኛ እትሟ ሽርጉድ እያለች ትገኛለች ።

እያነበቡ ለወዳጅዎ ያጋሩ !
ለሃሳብ አስተያየት
@KelemMagazine
9🥰2
የእንግዳ ወጥ

በልጅነቴ በቤታችን ውስጥ ከእናቴ ጋር በጣም ያስተዛዝበን የነበረ አንድ ነገር ነበር። ይኸውም እኛ ቤት  እንግዳ በመጣ ቁጥር የሚሰራው ድራማ ነበር። በተለይ ደግሞ የእንግዳ ወጥ።  በቤታችን አንድ የሩቅ እንግዳ በመጣ ቁጥር ደሳሳ ጎጇችን በቅፅበት ከአሰለፈች የቁርስ ቤት ማዕረግ ወደ ባለ  አምስት ኮከብ ሆቴልነት ከፍ ትላለች። አቧራ አይንካቸው ተብለው ፣ በዳንቴል ተጀቡነው ፣ የVIP ክላስ  ተበጅቶላቸው የተቀመጡ እና እኔ እንኳን በኛ ቤት መኖራቸውን የማላውቃቸው አዳዲስ ሰሀን ፣ ጭልፋ ፣  ብርጭቆ እና ብረት ድስቶች ከየመሸጉበት ብቅ ብቅ ይላሉ።  ቦርጫሙ ቴሌቭዥን ዳንቴሉን ይለብሳል ፤ ትንሽ ተርተር ብሎ ሊሾ ያልሆነውን የቤታችንን የአፈር መሬት  ገበና ያጋለጠው ላስቲክ ይሸጋሸግና መሬቱ ይደበቃል።  ብቻ ይሄንን ሳስታውስ ምን ትዝ አለኝ ... ለካ እነ እከሌ ሰፈራችንን ሊጎበኙ ሲመጡ ቆሻሻው ተፀድቶ ፣  የኔ ቢጤው ተፈናቅሎ ፣ ሊስትሮውና ሱቅ በደረቴው ከቦታው ተባሮ ፣ ሻይ አዟሪዋም እንዳትዞር ተደርጋ  የየመንገዱ ዳር ቆርቆሮውና ግድግዳው ቀለም ተቀብቶ “ እንደምትመለከቱት እንግዲህ ባለ ሁለት አሀዝ  እድገት አስመዝግበናል ...” የሚለው ዲስኩር እናቶቻችን በቤታቸው እንግዳ ሲመጣ ከሚሰሩት ድራማ  የተኮረጀ ነው ለካ።  ብቻ እኔ ሌላ ምን አስቀባጠረኝ። ስለ እንግዳ ወጥ ላውራችሁ። ከሽንኩርቱ እንጀምር።  እንግዳ ሲመጣ በአንድ ራስ ሽንኩርት ወይንም በግማሹ ተጠቅሞ ወጥ የመወጥወጥ ህገ ደንብ ይፈርስና አያሌ  ሽንኩርቶች በጅምላ አንገታቸው ይቀላል። እኔም ለወጡ ግብዓት የሚሆኑ እንደ ጨው ፣ ዘይት እና ቅመማ  ቅመም ያሉትን ነገሮች እንድገዛ ስላላክ እውላለሁ።  በተለይ ደግሞ ከቁሌቱ ጀምሮ ያለው መዓዛ የረሀብ ስሜትን በሁለት አሀዝ ከፍ የሚያደርግ ነው። ብቻ እኔም  እየተላላኩኝ እናቴም ወጧን ሰርታ ስትጨርስ እንግዳው ይመጣል። 
እንግዳ ሲመጣ ልጆች ወደ ጓዳ በሚለው መርህ መሰረት እናቴ በአይኗ ጠቀስ ታደርገኛለች። እኔ ግን ምኔ  ሞኝ ነው። ቀኑን ሙሉ እየተላላኩኝ ያሰራሁትን ወጥ ለእንግዳው ትቼለት እኔ ኋላ ላይ ጥራጊውን ልበላ? ...  እናቴ ትሙት አልሰማውም።  እናቴ ትጠቅሰኛለች። እኔ ግን ባለየ ዝም እላታለሁ። እንግዳው ከተሸኘ በኋላ በስሊፐርና በማማሰያ  እያፈራረቀች እንደምትወቅጠኝ አልጠፋኝም። ነገር ግን በስንት ጊዜ አንዴ የተሰራው ወጥ እንዲያመልጠኝም  አልፈልግም። ባይሆን ከተመታው አይቀር በደንብ ልብላና ምቱን ልቋቋመው ብዬ የቀረበለትን ወጥ ከሚበላው  እንግዳ ላይ ቁልጭ ቁልጭ ማለት እጀምራለሁ።  ያው እንግዳውም ሀበሻ አይደለ ... ሀፍረት ቢጤ ይዞት “ማሙሽዬ ብላ” ይለኛል። እኔም ግግም ብዬ 
ከእንግዳው ጋር ብልት ...እናቴም እኔን በ ነብር አየኝ በል ለዛ እያየችኝ ግልምጥ ፣ እንግዳውም በይሉኝታ  የቀረበለትን ወጥ ለኔ ስጥት ...


ፍቅር ካሳሁን
ቀለም መፅሔት ቅፅ 1 ዕትም 4
ጥቅምት 15/02/2018 ዓ.ም

እያነበቡ ለወዳጅዎ ያጋሩ!
ለሃሳብ አስተያየት

@KelemMagazine

Telegram 👇❤️
@kelemofficial
13👏2👍1
ተፈጥሮአዊ ተቃርኖ

ዓለም ላይ ዝነኛ የሆኑት ወርቅ እና አልማዝ በአንድ  ቦታ መገኘት አይችሉም አሉ። እነዚህ ማዕድናት  በተፈጥሮአቸው ተቃርኖ አለባቸው። አልማዝ 
በከፍተኛ ሙቀት እና ጫና ውስጥ ወደ ካርቦን  በመቀየር በምድር ውስጥ ጠልቆ ይሠራል። በአንፃሩ  ወርቅ በመሬት ቅርፊት ውስጥ ወይም በወንዞች ውስጥ 
የደለል ክምችቶች ውስጥ የሚገኝ ማዕድን ነው። ይህ  የተነሳው ያለ ምክንያት አይደለም። ሁሌም ቢሆን 
በዕለት ከዕለት ህይዎታችን የወርቅን እና የአልማዝን  አይነት ተፈጥሮ ስለሚያጋጥመን ነው። ሰዎች በተለያየ አጋጣሚ አብረዋቸው ከሚኖሩት  ሰዎች ጋር አልያም ከጓደኞቻቸው አልያም በተለያየ  ስያሜ ውስጥ ካለ የግንኙነት አጋራቸው ጋር መግባባት  ሲያቅታቸው ይታያል። ካልሆነም ደግሞ መስማማት 
እንዳልቻሉ ሲናገሩ ይደመጣል። ታዲያ ይሄ ምን  ይገርማል? ይሄ ሁሉም ሰው ሊያጋጥመው የሚችል  ጉዳይ ነው። የሚል ሰው አይጠፋም ይሆናል። ልክ 
ነው ሁሉም ሰው ይሄ አይነት ችግር ያጋጥመዋል።  ነገር ግን አሁን የምናወራው አለመግባባታቸው በምን 
ምክንያት እንደተከሰተ ስለማያውቁት እና ለግጭት  ምክንያት ሳይኖራቸው የተጋጩበትን ምክንያት ይሄ  ነው ብለው ማስቀመጥ ስለማይችሉት ሰዎች ነው።  ሁሉም ነገር በልክ እና በትክክለኛው መንገድ እየሄደ  አልያም ደግሞ አንድም ቀን ከሁለቱም ወገን ክፉ ደግ  የሚያመላልስ እና ለጠብ የሚጋብዝ ምክንያቶ ሳያገኙ  ለቀሩት። እርሷ፦ “እወደው ነበር እኮ፤ ሃሳቡንም እቅዱንም  እርሱነቱንም እወደው ነበር። መልክ እና ቁመናውም  ልክ የምፈልገውን የህልሜን አይነት ሰው ነው።  አንድም ቀን አስቀይሞኝም አያውቅ። ግን አብረን 
መሆን አልቻልንም።” እርሱም፦ “በህይወቴ እንደርሱዋ ያለ ቆንጆ እና 
ተግባቢ ከሰዎች ጋር አብራ ለመኖር ፍፁም ምቹ  የሆነች ሴት አጋጥማኝ አታውቅም። በቤት ውስጥም  ከቤት ውጭም ለኔ የምትስማማ ነበረች። ግን አብሮ  መኖር ዳገት የመውጣት ያህል ከበደኝ።”ሲባል ሰምተን  እናውቅ ይሆናል።  ነገሩ የሚደንቀው ደግሞ እርሱዋም ሆነ እርሱ  በሁኔታው አለማጉደላቸውን ሲገልፁ ለግንኙነታቸው 
ሌት ተቀን ሲለፉ እንደኖሩ ሲነግሩን ነው። ታዲያ  እርሱም ካላጠፋ እርሷም መልካም ከሆነች በምን  ጥፋት ወይም መጉደል ተለያዩ? ታዲያ ምኑ ጋር ነው 
ችግሩ? ምኑስ ነበር ክፍተት መሆን የቻለው? ብለን  ስንጠይቅ መልሱ ወደ አንድ ሀሳብ የሚያመዝን  ይመስላል።
እርሱም ተፈጥሮአዊ ተቃርኖ ነው። ወይም  አለመጣጣም። እንግዲህ እዚህጋ ነው ከላይ አትኩሮት 
እና አፅንዖት ሰጥተን ያነሳነው ሀሳብ የሚመጣው።  የማዕድን ባለሙያዎች ሁለቱን የከበሩ ማዕድናት  አንድ ላይ ለማግኘት ብዙ ጊዜ እንደማይቻል ሲናገሩ  ይሰማል። ያም የሆነበት ምክንያት አንድም ማዕድናቱን  ከሚሰሩበት የአየር ሁኔታ እና ተፈጥሮአዊ ግብአት  መለያየት ሲሆን። አንድም ደግሞ የሚገኙበት የመሬት  አቀማመጥ ወይም የጂኦግራፊካል መገኛ መለያየት 
ነው። በዋናነት ግን ተመሳሳይ ነገር ሁለቱንም መፍጠር  ስለማይችል ነው። 
አልማዝ በከፍተኛ ሙቀት እና ጫና ውስጥ እጅግ  በጣም ወደ መሬት ውስጥ ጠልቆ የሚገኝ ማዕድን ሲሆን 
ወርቅ ደግሞ በአንፃሩ የላይኛው የመሬት ክፍል ውስጥ  በወንዞች ደለል አከባቢ የሚገኝ ተፈጥሮአዊ ማዕድን 
ነው። ለዛ ነው አልማዝ እና ወርቅ ምንም ያህል ውድ  እና ለጌጥነት የምንጠቀማቸው የተፈጥሮ ስጦታዎች 
ቢሆኑም አንድ ላይ ግን መገኘት አይችሉም።ምናልባት ግን ከብዙ ጊዜ አንዴ ወይም እንደው እንደ  እድል ሆኖ አብረው ቢገኙ ያንን የዘርፉ ባለሙያዎች 
የተፈጥሮ ስህተት ብለው ይጠሩታል። ተፈጥሮአዊ  ተቃርኖአቸውን ጥሰው በመገኘታቸው። ሰውም እንደዚህ ነው ብዬ አምናለሁ። አንዳችን  ለአንዳችን ችግር ሳንሆን አንዳችን ሌላችንን ሳንበድል  ግን አብረን መኖር ይከብደናል። ምክንያቱን  በማናውቀው ሁኔታ የፍቅራችን ወረት እንደማስቲካ  ጣዕም አልባ ሲሆን እናገኘዋለን። ሁላችንም ስሪታችን  ይለያያል በህይወት ዘመናችን ያለፍንበት ውጣ ውረድ  ልምዳችን እና የዕውቀት ክምችታችን እንዲሁም  ተሰጥኦ እና ዝንባሌያችን የተለያየ ፅንፍ ላይ ያውለናል።  ፍላጎታችን እና ትኩረታችን በፍፁም የተለያየ ይሆናል።  በስሪታቸን መለያየት የተነሳ የሚያስደስተንም 
የሚያስከፋንም የተለያየ ነገር ሆኖ እናገኘዋለን።  እንጂማ ሁሉም ሰው በቦታው ጌጥ መሆኑ ግልፅ  ነው። ጌጥ ላይሆን የተሰራ የለም። ግን እንደ አጋጣሚ  ያለቦታ መብቀል ይኖር እና አረም ተብሎ ተነቅሎ መጣል ያጋጥማል። እንጂማ እንዴትሰዎች ጥሩ ሆነው  ይሄ ነው የሚባል ክፋት ሳይታይባቸው አብሮ መኖር  ሊሳናቸው ይችላል? ይሄን የሚፈጥረው ተፈጥሮአችንን  አለመረዳት ነው። ማንም ሰው እኔ ማን ነኝ? የትኛው  አይነት ጌጥ ነኝ? ብሎ የጠየቀ ጊዜ መልሱን ማግኘቱ 
አይቀርም። ምንነትን ማጠየቅ ምንጭን እና ባህሪን  ለማወቅ የሚጠቅም መልስ ይሰጣል ያ ደግሞ መገኛን  ለመለየት ትልቁ መልስ ይሆናል። ያኔ ማንም መጥቶ  አረም ብሎ ማንንም አይነቅልም። በቦታው የበቀለን  ማን አረም ሊለው ይችላል።  ሳርን ከብት ይበላዋል ለምለም ለምለሙን እያጣጣመ  ለሰውነቱ ተስማምቶት ያኖረዋል። ያኖረዋል። ስንዴን 
የሰው ልጅ ይመገበዋል። ታዲያ ከሁለቱ ማነው አረሙ? ማንም አረም ሊሆን  አልተገባውም ነገር ግን ገበሬው ስንዴን ብሎ ባዘጋጀው  መሬት ላይ የበቀለ ማንኛውም ነገር ከስንዴው ውጪ  አረም ነው። 


ደግሞ በሌላ በኩል እንየው። ያለቦታ መገኘት  እንደማይቻል። ከገበሬ እና ከሸክላ ሰሪ ማንኛቸው  ናቸው ጥሩ? ማንኛቸውስ ክፉ ሆኑ? የዚህ መልስ 
ከላይ እንዳነሳነው ሀሳብ ነውየሚሆነው። ከብዙ ጊዜ  በፊት እንዲህ ሆነ።
አንድ መነኩሴ በመንገድ ጉዞ ላይ ነበር። በመንገዱም  በሚያቀናበት ሰዓት ብዙ አይነት ሰዎችን እያየ ሲጓዝ  ቆየ። አንድ ሰው ካረሰው እርሻ መሬት ፊት ቆሞ በታላቅ  ድምፅ ፈጣሪውን ሲለምን ሰማው። ያ ሰው ገበሬ ነበር።  ገበሬውም በከፍተኛ ድምፅ እንዲህ ብሎ ተማፅኖውን  ለፈጣሪው አቀረበ...” የሰማይ አምላክ ሆይ የዝናብ  አምላክ ሆይ...አፈር እጆቼን እንዲታዘዝ የገሰፅክ  ጌታዬ ፤ እጆቼን ለአፈር ጌትነት የሾምክ አርሼ እና  ጎልጉዬ ባሳመርኩት መሬት ላይ እህል ዘርቼ አገሬውን  አጠግብ ዘንድ ዝናብ ያሻኛል የዝናብ አምላክ ሆይ  ዝናብን ላክ መሬቴም ይረስርስ በዝናብህ ያሳመርኩት  መሬት ዘር ይሰጥ ዘንድ የዝናብ አምላክ ሆይ ዝናብን  ላክልን።” ብሎ ሲጮህ ይሰማዋል። መነኩሴውም  እግዜር የመሻትህን ይስጥህ ብሎት አለፈው። ጉዞውን  ቀጠለ አለፍ ብሎም ወደ መንደሩ ገባ። በመንደሩ  ውስጥም ሲዘዋወር የአንድ ሸክላ ሰሪ ቤት ደረሰ። 
ሸክላ ሰሪውም እጅግ የተዋጣለት ባለሞያ ነበር። ነገር  ግን ይህም ሸክላ ሰሪ ከሰራቸው ቅርፃቅርፆች ፊት ቆሞ 
ፈጣሪውን በከፍተኛ ድምፅ ሲለምን ሰማው። “አቤቱ  የፀሐይ አምላክ ሆይ ውበትን በእጆቼ የሳልክ ባለ  ጥበብ እጅ አርገህ የመረጥከኝ ጌታዬ። እንሆ በስጦታህ  እና በባርኮትህ ድንቅ ቅርፆችን መስራት ቻልኩ። ነገር  ግን የሰራኋቸው የውበት አመሀዎች ፀሐይህን ካላገኙ መድረቅና ለአገልግሎት መዋል አይችሉም ።
2👍1
አምላኬ ሆይ ፀሐይ በመዳፍህ ነፋሳትም የእጆችህ ናቸው እና ፀሐይን ስጠኝ። ሙያ እና ስጦታዬም ለተጠቃሚው 
ይደርስ ዘንድ ፀሐይን ታዝልኝ ዘንድ እለምናለሁ።” መነኩሴው ይህን በሰማ ግዜ እንደምኞትህ ይስጥህ አለው። 
በመንገዱ ግን እጅጉን አዘነ። ማንኛቸው ናቸው ትክክል? ማንኛቸውስ ተሳሳቱ? ብሎ ራሱን ጠየቀ። መልስ ግን 
አጣ። እዚህ ላይ ማየት ያለብን እንድ ሸክላ ሰሪ ሸክላውን ከሰራው በኋላ ዋናው ፀሎቱ ፀሐይ ነች። ፀሐይ የሰራውን ሸክላ  አድርቃለት ሸክላውን ሸክላሰሪው ለፈለገው አላማ እንዲያውል ታደርገዋለች። ለዚህ ነው ሸክላ ሰሪው ፀሐያማ  የአየር ንብረት ወይም ሞቃት አየርን መፈለጉ። ዝናብ ከበዛ እና ቅርፅ ያስያዘው ሸክላ ፀሐይን በደንብ ካላገኘ 
የሚፈልገውን የሸክላ ስራ መስራት እና ማምረት አይችልም። ደግሞ በሌላ በኩል ገበሬው አርሶ እና አለስልሶ  እንዲሁም ጎልጉሎ ባሳመረው መሬት ላይ የሚዘራው እህል እንዲበቅል ዝናብ ያሻዋል። ሳያቋርጥ ለረጅም ጊዜ 
የሚዘንብ ዝናብን ካላገኘ የዘራው አይበቅልም። መሬቱም ፍሬ መስጠት ይሳነዋል።  ስለዚህ ለአንድ ገበሬ ዝናብ ለዘራው እህል ህይወትን የሚዘራበት የህይወት እስትንፋሱ ነው።ለኛ ሸክላውም  ጤፉም ያስፈልጉናል። ሁለቱን አንድላይ ተጠቅመን ማዕድ እናበስላለን በሸክላ ሰሪው ምጣድ ላይ የገበሬውን  ጤፍ እንጀራ እናደርገዋለን። ያንን በልተን እናድራለን። ገበሬው እና ሸክላ ሰሪው ግን ባንድ መኖር አይችሉም።  ለበጎነታቸው ጥያቄ አያሻም። ለሙያቸውም እንከን የለውም። ግን ጎረቤት ሆነው መኖር አይቻላቸውም።  የጌጣጌጥ ሰሪው በወርቅ ጌጥን ይሰራል። በአልማዝም እንደዛው ያደርጋል። ሁለቱን አንድ ላይ ተጠቅሞ ባለ ፈርጥ  ጌጥን ወይም መዋቢያን ሊሰራ ይቻለዋል። ሁለቱ አልማዝ እና ወርቅ ግን ባንድ ቦታ አይፈጠሩም። በአንድ አፈር  ላይ በአንድ አየር ንብረት ውስጥ እንደገበሬው እና እንደሸክላ ሰሪው ጎረቤት ሊሆኑ አይቻላቸውም። ሰውም  እንዲያ ነው በወዳጅነታችን ውስጥ፤ በፍቅር ግንኙነታችን ውስጥ አንዳንዴ እንዲሁ መለያየት ይኖራል ያለፀብ  ፍቅር ያልቃል አብሮነታችን ያለ ግጭት ብዙ መራመድ ያቅተዋል። ያኔ ታድያ ምናልባት እራሳችንም ላይ ሆነ  አጋራችን ላይ ያላስተዋልነውን ስህተት እያሰሱ ለማግኘት ከመድከም እንዲሁ መሄድ የተሻለው ውሳኔ ይሆናል።  ምክንያቱም አልማዝ እና ወርቅ ባንድ አፈር ሊገኙ አይችሉም። ሸክላ ሰሪ እና ገበሬም ሊጎራበቱ አይቻላቸውም።  ምናልባት በእኛ መሀል አንዳችን ገበሬ አንድኛችን ደግሞ ሸክላ ሰሪ ሆነን ይሆናል። አልያም አንዳችን አልማዝ  አንዳችን ወርቅ እንደስጦታችን መኖርያችን ለየቅል ሆኖ።


አል-አዛር ጥበቡ
ቀለም መጽሔት ቅፅ 1 እትም 3
መስከረም 15 2018 ዓ.ም

እያነበቡ ለወዳጅዎ ያጋሩ!
ለሃሳብ አስተያየት
@KelemMagazine

Telegram 👇❤️
@kelemofficial
6
ቀለም መጽሔት ቅጽ 1 እትም 6.pdf
5.7 MB
ቀለም መጽሔት🗞️

ቅፅ 1 እትም 6


እያነበባቹህ ለወዳጅዎ ያጋሩ
ለሀሳብ አስተያየት

@KelemMagazine

Telegram 👇❤️
@kelemofficial
12🔥1👌1
የታኀሣሥ ወር እትማችንን እንዴት አገኛችሁት???

📩ሀሳብ አስተያየታችሁን አጋሩን!


ቀለም ዲጂታል መጽሔት🗞️

የማህበራዊ ሚዲያ ገጾቻችን ቤተሰብ ይሁኑ!

Facebook- ቀለም መፅሔት
Instagram-kelem_magazine
Telegram- @kelemofficial
🔥6👍31
እንኳን ለብርሃነ ልደቱ በሰላም አደረሳችሁ!

ቀለም መጽሔት🗞️
4🔥2
አንዳንድ የጥበብ ትሩፋቶች ከዘመን አውድ ተሻግረው፣  ከውልደት ታዛቸው አልፈው የመሄዳቸውን  ያህል አንዳንዴ የጠቢቡን ጥቅል ውስጠ - ምስል 
በማንጸባረቅ ለዘመናት ሲያስደምሙን ማየት የተለመደ  ነው፡፡ ከጠቢባን ሥራዎች የምንመርጠውም ባይሆን 
የምናበላልጠው መኖሩ፣ ለመንፈሳችን ቀርቦ አልያም  ለአተያያችን ስቦ የምናጎላው ሥራ መታዘቡ እንግዳ 
ነገር አይደለም፡፡

እዚህ ላይ የበዓሉ ግርማ ‘ኦሮማይ’፣ 
የሐዲስ ዓለማየሁ ‘ፍቅር እስከ መቃብር’ እንዲሁም  የስብሐት ገ/እግዚአብሔር ‘አምስት፣ ስድስት፣ ሰባት …’ ከሥራዎቻቸው ሁሉ በተለይ ተጠቃሽ የሆኑበት  አብይ ምስጢር ደራሲዎቹ የነፍስ ጩኸታቸውንና  የመንፈስ ሽራፊያቸውን አጥንትና ደም ከሥራዎቻቸው  ጋር በመቀላቀላቸው ሳይሆን አይቀርም፡፡  በዓሉ ኦሮማይን ከመፃፉ በፊት የመጽሐፉ ጭብጥ 
ሊያስከትል ያለውን ዳፋ በገለጸባት “የመጨረሻው  መጀመሪያ” የተሰኘች አጭር ልብወለድ ላይ ውስጠ ስብዕናውን እንድናይ ማድረጉን ስናስታውስና  በትርክቶቹ የኦሮማይ ውልደት ዋዜማዎችን  አስጨናቂነት በገሃድ ማየታችን ከመጽሐፉ ጋር 
በአንዳች ስውር መንፈስ እንድንተሳሰር አስተዋጽዎ  ማድረጉ አልቀረም፣ ከቁጭትና ሕመም ጋር፡፡ ክቡር 
ሐዲስም የሕይወት ሽራፊያቸውን በፍቅር እስከ  መቃብሩ በበዛብህ በኩል ግዘፍ ነስቶ እንድናይ  ማድረጋቸው ልቦለዱን የአንድ ዘመን እውነተኛ 
ክስተት እንጂ የፈጠራ ውጤት ብቻ አድርገን  እንዳንወስድ በሚያስገድድ የደም ትስስር ከሥራቸው  ጋር ቋጥረውናል፡፡

ደራሲው ራሳቸው ‘በጣም የምወደው ሥራዬ  ወንጀለኛው ዳኛን ነው’ ቢሉም እኛ ግን ከፍቅር እስከ  መቃብር አስከትለን እንጂ አስቀድመን ላንጠራው 
ምለናል፡፡ ‘ሥራዎቼ የእውነተኛው ዓለም ቅጂ እንጂ  ፈጠራ አይደሉም’ የሚለን ስብሐትም ‘አምስት ስድስት  ሰባት’ መጽሐፉ ላይ በሳላቸው ገጸባሕሪያት አማካይነት  የዘመንተኞቹን ሕመምና ጉስቁልና አጥንታችን ድረስ  ዘልቆ እንዲሰማን በሚያደርግ የገለፃ አቅሙ የሰው  ጉዳይ ለስብሐት ምን ድረስ እንደሚሄድም እንድናይ  በማድረግ ጭምር ገጸባሕሪያቱን አትሞብናል::

ከቀለም መጽሔት ቅጽ 1 እትም 6 ላይ የተቀነጨበ ። በድልድይ የቀረበ ። ሙሉውን ለማንበብ መጽሔቱን ይጎብኙ ።

እያነበቡ ለወዳጅዎ ያጋሩ!
ለሃሳብ አስተያየት

@KelemMagazine

Telegram 👇❤️
@kelemofficial
6
እስር

“ስንቶች ግዜያዊ ረሃባችንን ኣጥግበው ዘላለማችንን ቀሙን?
በጣሉልን ጣፋጭ ፍርፋሪ ሰንሰለት በጥልቅ እስር ቤት ውስጥ ወረወሩን?
የቅርቦቻችን በውለታቸው አደንዝዘው ነፃነታችንን ከስስ ስጋችን ቀደው አውጥተው ጣሏት? "

አሁን

እስረኛ ነን…..
ግን….የሚዳሰስ ግንብ ኣላጠረንም፣
ባሪያዎች ነን ግን…
ን ግርፋቱ ፍቅርን በሚመስል ጅራፍ ነው።
ከሳቆቻችን ውስጥ የዕንባ ዘለላዎች ይፈለቀቃሉ።
ማን ያውቅልናል?? እወድሃለሁ ከሚለው ቃል የምንሰማውን ድምፅ።

ብዙ ጊዜ ሰውነታችን ሲሸጥ ኣይታወቀንም። ይህን ስል መሠረታዊ የሆነ ሃሳብን ይዞ በመነሳት ነው። አንዳንዴ  በህይወታችን የበሬው ታሪክ ይገጥመናል። ‘’ በሬ ሆይ በሬ ሆይ ሳሩን አየህና ገደሉን ሳታይ’’ እንደሚለው አባባል  ኣይነት። በመሠረቱ ነገሮች ሲደረጉልን የሰዎችን በጎ ማንነት ወይም ጥሩ ጎናቸውን አልያም ደግነታቸውን በማየት  ብቻ መስጠታቸው ወይም የተደረገልን ነገር ምን ያህል ለእስር እንደሚዳርገን አናስተውልም። ከላይ ሃሳቡ  ሊነግረን እንደሞከረው ግዜያዊ ረሃባችን ሲታገስ ወይም ችግሮቻችን በሌሎች ለጋስነት ሲያልፉ የነገሩን ማለፍ  አልያም የችግራችን መሸነፍ ላይ ያላቸውን አበርክቶት ብቻ እንመለከታለን።

ነገር ግን ባላወቅነው እና ባልተረዳነው መንገድ  ለችግራችን መቀረፍ ምክንያት ለሆኑን ሰዎች እስረኞች  መሆናችንን አናስተውልም። ይሀ እርግጥ የብዙዎቻችን  ችግር ሆኖ ይስተዋላል። ማለትም ዛሬ ላይ ለተደረጉልን 
ነገሮች ፣ ውለታዎች መቀበልን ለባህሪያችን ስንነግረው 
ሰውነታችን ቀጥሎ ለሚመጣው የውለታ ጥያቄ ምንም  እንኳን በጉዳዩ ላይ ያለን ምቾት ጥያቄ ውስጥ ቢሆንም 
አልያም የኛ የውለታው ቅቡልነት ባይታወቅም ቀድመን  በተቀበልነው እና ለአዕምሮአችን በነገርነው የውለታ 
ታሪክ ብቻ ቀጥሎ ከባለውልታችን ለሚሰነዘረው  ማንኛውም ዋጋ አስከፋይ ጥያቄ ቀድመን እጅ ሰጥተናል 
ማለት ነው። ለዚህም ይመስላል ኦሾ ስለ ውለታ  የሚከተለውን ሃሳብ የሰነዘረው ’’በግድ የሚያስፈልግህን  ሳታደርግ ሌላውን ማርካት ማለት ራስን ማታለል ነው።’’  ለዚህ ነው ራስን ስለመሸጥ ቀድሞ ማንሳት ያስፈለገው። 
ውለታ ሰዎች ራሳቸውን የሚሸጡበት ስርዓት ነው።

እርግጥ ነው በብዙ ማሕበራዊ ሥርዓቶች ውስጥ  ውለታ እንደ ጥሩ ባሕሪ ይቆጠራል። ነገርግን የውለታ 
ተቀባዩን ነፃነት የሚነጥቅ መሆኑን እራሱ ተቀባዩ እንኳን  አይረዳውም። ይባስ ብሎም የረጅም ጊዜ እስርቤት 
እንደሚሆንበት በፍፁም አይገነዘብም። በተቃራኒው  ደግሞ ውለታ ሰጪው በመስጠቱ ወይም በለጋስነቱ 
ውስጥ ያለው ርህራሄ እና ደግነት እንጂ በመስጠቱ  ውስጥ መስጠቱ ለለሎች እስር ቤት እንደሚሆንባቸው  በፍፁም አይረዳም።

በህይወት ሰዎች ሲኖሩ መቸገራቸው ኣይቀርም። ያንንም  ችግር በማህበራዊ ግንኙነታቸው ወቅት በሚያገኟቸው 
ሰዎች አማካኝነት ነው ማለፍ የሚችሉት። አልያም  ቀድሞ ወደ አዕምሮአቸው የሚመጣላቸው መፍትሄ 
ከሚያውቋቸው ሰዎች ድጋፍ መጠየቅ ሊሆን ይችላል።  እርግጥ ይሄ ጉዳይ ብዙ መልካም ጎን እንዳለው  የማይካድ ሃቅ ነው። ነገር ግን አንድ ሰው ከሌሎች 
ውለታን ሲጠይቅ የመጀመርያው ጉዳይ ማሕበራዊ  ሽንፈት ነው(በተለይም በእኛ ማሕበረሰብ ዘንድ)  ምክንያቱም ሁላችንም እንደምናውቀው እርዳታ 
ሊጠይቅ የሚችለው አካል የደከመ ሰው ብቻ ነው።

ከዚህ ለየት የሚለው እና የከፋው ጉዳይ ደግሞ  እርዳታ ሰጪው በገዛ ፈቃዱ መቸገርህን አይቶ  ወይም ደግሞ ያስፈልገዋል ብሎ ያሰበውን ጉዳይ 
በገዛ ፈቃዱ ሲያደርግ ነው። ይህ በተለይም ቤተሰባዊ  ግንኙነታችን ላይ ወይም ደግሞ በዝምድና ግንኙነት 
ላይ ይበረታል። ይኼኛው የውለታ አይነት ደግሞ  ሙሉ በሙሉ በሌሎች ቁጥጥር ውስጥ እንድንወድቅ  የሚያደርገን እና ነገሮችን በመቃወም እርምጃዎቻችን 
በሙሉ በባለውለታችን ቁጥጥር ውስጥ እንዲወድቁ  አሳልፎ የሚሰጠን የኑሮ አጋጣሚያችን ይሆናል።  በእርግጥ ይህ በሌሎች የማሕበረሰብ ክፍሎች የ አኗኗር  ሂደት ውስጥ ቢሆን ውጠቱ የዛን ያህል ላይከፋ ይችል  ይሆናል። ነገር ግን በእኛ የኢትዮጵያውያን አኗኗር እና  የ አዕምሮ ግንባታ ውጠቱ የከፋ ይሆናል። በተለይም  ደግሞ ውለታ ሰጪው ያደረገውን የሚቆጥር ወይም 
ማድረጉ ላይ ትኩረት የሚሰጥ አይነት ሲሆን ምን  ያህል የውለታ ተቀባይን ሕልውና የሚፈታተን እና  እስረኛ የሚያደርግ ነጥብ መሆኑ የማይካድ ሃቅ ነው። በተለይም ደግሞ የይሉኝታን ጥቅም በየሥነ-ቃሉ  እና በየሙዚቃው ጭምር መዝግቦ ለያዘ ማሕበረሰብ 
ይህንን የ ይሉኝታ አጥር ለማለፍ ይቸገራል።  እንደሚታወቀው ለብዙ ነገሮቻችን አጥር ሆኖ ከ  አያሌ ጥፋቶች የሚጠብቀን ቅጣት አልያም ነገሩን  አለመፈለግ እንደሆነ ግልጽ ነው ።

በዋናነት ከሁሉ ነገር የሚጠብቀን የሰዎችን ፍርድ ፍራቻ ነው። በእርግጥ ይህ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው 
እሙን ነው። ይህ በራሱ ችግር መሆን የሚጀምረው ግን በግድ የሚያስፈልግህን ሳታደርግ ሌላውን ማርካት  ደረጃ የደረሰ ጊዜ ነው። ያን ጊዜ መወደዳችንን እንኳን መጠርጠር መጀመራችን አይቀርም። ምክንያቱም ሌሎች  መውደዳቸውን በሚገልፁበት በጎነት ነዋ እስርቤት ውስጥ የከተቱን።

እንደ እውነቱ ይህ እስር ቤት አገባቡ ቀላል ነው። ልክ ‘’ውሃ ሲወስድ እያይሳሳቀ ነው’’ እንዲሉ! መውጫው ግን  ልክ እንደ ማር ወጥመድ ነው መጀመርያ የጉዳዩ ጣዕም ብቻ ነው የሚታየው። ሲቆይ ግን መውጫው እሩቅ ነው።  በተለይም ደግሞ መስጠታችን እና ደግነታችን ከልብ በሆነ የመስጠት ፍላጎት ሳይሆን በ “ምን ይሉ ይሆን??” ላይ  የተመሰረተ ሲሆን ፈተናው ይጨምራል። ውለታ ሰዎች ራሳቸውን ለሌሎች በሚያስደስት መልኩ ለመቅረፅ የሚገደዱበትም ሃይል ነው። ሰዎች በሌሎች  ውለታ በተያዙ ጊዜ “ምን ይሉኝ”ን በመፍራት እና በተደረገላቸው ነገር እንዲሁም በተቀረፈላቸው ችግር ግዝፈት  ልክ ለዋለላቸው ብድር ለመመለስ በመጣር ውስጥ ራሳቸውን ወደማጣት ቀስበቀስ ያዘግማሉ። ያን ጊዜ በማወቅም  ሆነ ባለማወቅ ለውለታ ሰጪው በሚመች መልኩ ራስቸውን መቅረፅ ይጀምራሉ።

በውለታ መታሰር በ ህይወት ውስጥ ያለ የተሳሳተ ግንኙነትም ጭምር ነው። ይህም ከራስ ማንነት እና ተጨባጭ 
እውነት ጋር ግጭትን ይፈጥራል። መጨረሻም ደግሞ ከራስ እውነት አፈንግጦ ለሌሎች ያለፍላጎት መኖርን 
ያስከትላል። ለዚህ ደግሞ ዋናው መፍትሄ ራስን መቀበል በተለይም የራስን ኣቅም እና ለሰዎች ልናደርግ እና  ለውለታቸው ለመመለስ ያለንን አቅም መረዳት እና መቀበል አንዱ መፍትሄ ሲሆን።
ዋናው እና ኣስፈላጊው ጉዳይ ግን ውለታ ሰጪ በመስጠት ውስጥ ስለሚገኘው እርካታ ብቻ ብሎ በጎን ማድረግን 
መለማመድ። ማለትም በመስጠታችን ውስጥ በምንም አይነት መንገድ ከረዳነው ወይም ከሰጠነው ሰው ተመሳሳይ  መልስን አለመጠበቅ ወይም በጎነታችንን ከ ብድር አለመቁጠር። ሲሆን ውለታ ተቀባይም ማጣት እና መቸገርን 
ሰባዊ ጉዳይ መሆኑን መቀበል ከዛም አልፎ የተቀበልነውን እርዳታ ከግዜያት በኋላ እንደምንመልሰው ብድር 
አለመቁጠር ዋናው ከ ይሉኝታ መራቂያ መንገድ ነው ብዬ አምናለሁ።

አልአዛር ጥበቡ
ነሐሴ 10 2017 ዓ.ም
ቀለም መጽሔት ቅጽ 1 ዕትም 2

እያነበቡ ለወዳጅዎ ያጋሩ!
ለሃሳብ አስተያየት

@KelemMagazine

Telegram 👇❤️
@kelemofficial
👍74
እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ በሰላም አደረሳችሁ!

ቀለም መጽሔት🗞️
🥰7🙏3
እንኳን ለ 130ኛው የ አድዋ ድል በዓል በሰላም አደረሳቹህ
13