Hawassa University
24.7K subscribers
8.69K photos
33 videos
129 files
718 links
One of the top ranking first generation Universities in Ethiopia.
Download Telegram
ለዳዬ ካምፓስ ተመራቂ ተማሪዎች የስራ ፈጠራ ክህሎትና የመቀጠር ዝግጁነት ስልጠና ተሰጠ።
*//*
የካቲት 30 ቀን 2017 ዓም
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የበንሳ ዳዬ ካምፓስ ከዩኒቨርሲቲው የሙያ ማበልጸጊያ ማዕከል ጋር በመተባበር ለተመራቂ ተማሪዎች የስራ ፈጠራ ክህሎት እና የመቀጠር ዝግጁነት ላይ ስልጠናተሰጥቷል::

የበንሳ ዳዬ ካምፓስ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ፍሬው ካሳ ባስተላለፉት መልዕክት በየሙያ ዘርፉ ሳይንሳዊ እውቀት ገብይተው ከዩኒቨርሲቲ የሚወጡ ምሩቃን እውቀታቸውን በመጠቀም ራሳቸውንም ሆነ ሀገራቸውን የሚጠቅሙበትን ስርዓት ለማመቻቸት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትኩረት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል። አዳዲስ ተመራቂ ተማሪዎች ገበያው የሚፈልገውን ልምድና ክህሎት በቀላሉ ለማግኘት እንደሚቸገሩ የገለጹት ዶ/ር ፍሬው ይህንን ታሳቢ በማድረግ መሰል የስራ ፈጠራና የስራ ዝግጁነት ክህሎት ማጠናከርያ ስልጠናዎች ለተማሪዎች መስጠት ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ ገልፀዋል።

ስልጠናውን ያስተባበሩት የካምፓሱ ፕላንና ዳታ ማኔጅመንት ኃላፊ መ/ር መብራቱ ክፍሌ በበኩላቸው ስልጠናው በተመራቂ ተማሪዎች አዕምሮ ውስጥ ስለ ስራ ፈጠራም ሆነ የቅጥር ስራ ማፈላለግ ተነሳሽነትና ዝግጁነትን ለመፍጠር የስራው አለም ነባራዊ ሁኔታ ምን እንደሚመስልና ምን ዓይነት ክህሎቶች እንደሚያስፈልጉ ግንዛቤ ማስጨበጥ ላይ እንደሚያተኩት ጠቁመዋል።

በሀ/ዩ /የሙያ ማበልጸጊያ ማዕከል አስተባባሪና አሰልጣኝ መ/ር ከብረት ፍቃዱ ስልጠናው ከሁለት የትምህርት ክፍሎች ለተወጣጡ የ2017 ዓም ተመራቂ ተማሪዎች እንደሚሰጥና ከግንዛቤ ማስጨበጫነቱ ባሻገር በዓመቱ መጨረሻ ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር የማገናኘት እድልን የሚያካትት እንደሆነ ገልጸዋል።

ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ
ሁሌም ለልህቀት!
የስራ ፈጠራና ሙያ ማበልጸጊያ ክለብ ምስረታ ተካሄደ።
**//*
የካቲት 30 ቀን 2017 ዓም
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ተማሪዎች በ "ReRed Project" በመታገዝ የስራ ፈጠራና ሙያ ማበልጸጊያ ክለብ (Entrepreneurship & Career Development Club /ECDC /) የካቲት 29/2017 ዓም መስርተዋል::

በምስረታው ላይ የተገኙት የሀ/ዩ/ም/ት/ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ታፈሰ ማቴዎስ የወ/ደ/ተ/ሀ/ኮሌጅ የአየር ንብረት ጉዳይ እንዳሁኑ አንገብጋቢ አጀንዳ ባልነበረበት የዛሬ 48 ዓመት በአርቆ እሳቢዎች ተመስርቶ ዛሬ ላይ ከሀገራችን አልፎ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፅዕኖ ፈጣሪ ምሁራንን ያፈራ መሆኑን አስታውሰው ኮሌጁ ክለቡን ለማቋቋም የሄደበትን ዝግጅትና ርቀት አድንቀዋል:: ዶ/ር ታፈሰ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ሥራ ፈጠራን ማዕከል ያደረገ አስተሳሰብ እንዲያጎለብቱ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት እንደመሆኑ ክለብ ከመመስረት ባለፈ ውጤታማ ሥራ እንዲሰራ የአስተዳደሩ ድጋፍና ክትትል መጠናከር እንደሚገባው አሳስበዋል።

ቀደም ሲል የነበረው የሀገራችን የስራ ባህል ስራ ፈጣሪዎችን የሚያበረታታ ባለመሆኑ በተለመደው የስራ ቅጥር ስርዓት ሁሉንም ምሩቅ ተጠቃሚ ማድረግ የወቅቱ ፈተና ሆኖ መምጣቱን የገለጹት የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ተሻለ ወልደአማኑኤል መሰል ክለቦችን ማቋቋም የስራ እድል ፈጠራ ተነሳሽነትን ለተማሪዎች የበለጠ ቅርብ ለማድረግ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

የተፈጥሮ ሀብትና ኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ሁለተኛ ዓመት ተማሪና የክለቡ ፕሬዚደንት የሆነው ተማሪ ተራማጅ ታመነ ክለቡ ተማሪዎች የስራ ፍላጎቶቻቸውን በመለየት ለየዘርፉ የሚያስፈልጋቸውን ክህሎት ተላብሰው ህልማቸውን መኖር የሚያስችላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስረድቷል።

ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ
ሁሌም ለልህቀት!
ማስታወቂያ

ጉዳዩ፡- የብሄራዊ ድህረ-ምረቃ (NGAT) መግቢያ ፈተና ቀንን
ስለማሳወቅ
በ2017 ዓ.ም የሶስተኛ ዙር የNGAT አመልካቾች ምዘገባ ተጠናቅቋል፡፡ በዚሁ መሰረት ለመፈተን ያመለከታችሁ አመልካቾች ፈተናው የሚሰጠው ዓርብ መጋቢት 5 ቀን 2017 ዓ.ም ከጠዋቱ 3፡00 ጀምሮ መሆኑን አውቃችሁ በተጠቀሰው ቀንና ሰዓት በምትመደቡበት የፈተና ማዕከላት እንድትገኙ እናሳውቃለን፡፡

ማሳሰቢያ፡-
1. ተፈታኞች ወደ ፈተና ማዕከል በምትሄዱበት ወቅት ማንነታችሁን የሚገልጽ መታወቂያ መያዝ ይጠበቅባችኋል፡፡
2. ማንኛውም ተፈታኝ ፈተናው ከመጀመሩ 3 ደቂቃ በፊት በፈተና ማዕከል መገኘት ይጠበቅበታል፡፡
3. የሞባይል ስልክ ይዞ በፈተና ማዕከል መገኘት ፈጽሞ የተከለከለ ነው፡፡
4. የፈተና ማዕከላት ምደባ በምዝገባ ፕላትፎርም የሚገለጽ ይሆናል፡፡
የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ለመምህራኑ የአቅም ግንባታ ስልጠና ሰጠ።
**//**
መጋቢት 2 ቀን 2017 ዓም
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ በስራ ላይ ለሚገኙ መምህራኑ "አሳታፊ የመማር ማስተማር ስትራቴጂ የተማሪዎችን ተሳትፎና የአካዳሚክሱን ስኬት ለማሳደግ" በሚል መሪ ቃል ለአምስት ዙሮች የሚሰጥ ስልጠና መጋቢት 01/2017 ዓ ም በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ መስጠት ጀምሯል።

የኮሌጁ ዲን ፕ/ር ዘለቀ አርፍጮ በስልጠናው መክፈቻ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት በተማሪዎች የትምህርት አቀባበልና ውጤታማነት ላይ የመምህራን ሚና የማይተካ መሆኑን ጠቁመው መምህራንን ማብቃትና ንቁና አሳታፊ የመማር ማስተማር ስነዘዴ እንዲጠቀሙ ማበረታታት በቀጥታ ተማሪዎችን እንደመጥቀም ይወሰዳል ብለዋል። መማር ማለት መጠየቅና ለማወቅ መጓጓት ማለት እንደመሆኑ የትምህርት አሰጣጡ ከተማሪውም ከመምህሩም በኩል የሁለት አቅጣጫ ተግባቦት ያለበት እንዲሆን ማስቻል እንደሚገባ ፕ/ር ዘለቀ ጨምረው ገልጸዋል።

አሳታፊ የመማር ማስተማር ስትራቴጂ አዳዲስ ጥያቄዎችን በመፍጠር የተሻለ ግንዛቤ እንደሚያስጨብጥ በጥናት የተረጋገጠ ስለመሆኑ የገለጹት የትምህርት ኮሌጅ መምህርና ስልጠናውን የሰጡት አቶ ተከተል አዳነ ያለ ሁሉም ባለድርሻዎች በተለይም ያለ መምህራንና ተማሪዎች የጋራ ትብብር በትምህርት ዘርፉ ላይ ስር ነቀል ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል ተናግረዋል። መምህር ተከተል አክለውም ስልጠናውን በቀጣይነት በተከታታይ ለመስጠት መታሰቡንና በተማሪዎች አጠቃላይ ውጤት ላይ ተጨባጭ ለውጥ ያመጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ
ሁሌም ለልህቀት!

በዚህ ይከታተሉን:-
**
Facebook: https://www.facebook.com/Hawassa.University?mibextid=ZbWKwL
ማስታወቂያ

ጉዳዩ፡- የብሄራዊ ድህረ-ምረቃ (NGAT) መግቢያ ፈተና እና ምዝገባ ቀናት የተራዘሙ መሆኑን ስለማሳወቅ

በ2017 ዓ.ም የሶስተኛ ዙር የNGAT አመልካቾች ምዘገባ መጋቢት 01/2017 መጠናቀቁ እና ፈተናው መጋቢት 05/2017 ከ3፡00 ጀምሮ እንደሚሰጥ መገለጹ ይታወሳል። ይሁን እንጂ በአንዳንድ ተፈታኞች ጥያቄ መሰረት ምዝገባው እስከ መጋቢት 04/2017 ዓ.ም እስከ ምሽቱ 12:00 የተራዘመ ሲሆን ፈተናው ደግሞ መጋቢት 12/2017 ከ3:00 ጀምሮ ይሰጣል።

በዚሁ መሰረት በተለያየ ምክንያት ምዝገባ ያመለጣችሁ አመልካቾች ምዝገባችሁን ቀደም ሲል በተገለጸው ሊንክ በመግባት መመዝገብ የምትችሉ መሆኑን እየገለጽን ፈተናውን ከላይ በተጠቀሰው ቀንና ስዓት በምትመደቡበት የፈተና ማዕከላት ተገኝታችሁ እንድትፈተኑ እናሳስባለን፡፡

ማሳሰቢያ፡-
1. ተፈታኞች ወደ ፈተና ማዕከል በምትሄዱበት ወቅት ማንነታችሁን የሚገልጽ መታወቂያ መያዝ ይጠበቅባችኋል፡፡
2. ማንኛውም ተፈታኝ ፈተናው ከመጀመሩ 30 ደቂቃ በፊት በፈተና ማዕከል መገኘት ይጠበቅበታል፡፡
3. የሞባይል ስልክ ይዞ በፈተና ማዕከል መገኘት ፈጽሞ የተከለከለ ነው፡፡
4. የፈተና ማዕከላት ምደባ በምዝገባ ፕላትፎርም የሚገለጽ ይሆናል፡፡
To All Interested HU Staff
**//**
The Department of Psychology at Hawassa University is hosting a special event next Friday, March 14, 2025 morning @ AU Hall, Main Campus.

Don't Miss it!

Hawassa University
Ever to Excel!