Hawassa University
24.5K subscribers
8.28K photos
33 videos
123 files
695 links
One of the top ranking first generation Universities in Ethiopia.
Download Telegram
የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር የኃላፊነት ርክክብ ተካሄደ።
**//*
ሚያዚያ 15/2017
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የኃላፊነት ጊዜያቸውን ያጠናቀቁት የቀድሞ ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ኢ/ር ፋሲካ ቤተ በውድድር ለተመረጡት አዲሱ ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ምህረት ዳናንቶ ሚያዚያ 14 ቀን በዩኒቨርሲቲው በተዋቀረዉ ጊዜያዊ የስልጣን አረካካቢ ኮሚቴ አማካኝነት ኃላፊነታቸውን አስረክበዋል።

ላለፉት አራት አመታት የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትን የመሩት ዶ/ር ፋሲካ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ትልቁን የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በመሪነት ማገልገል በመቻላቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዉ በኃላፊነት በቆዩባቸዉ ጊዜያት ከዩኒቨርሲቲውና ኢንስቲትዩቱ ማኔጅመንት እንዲሁም ከኢንስቲትዩቱ ጠቅላላ ማህበረሰብ ለተደረገላቸዉ ድጋፍ ምስጋናቸዉን በማቅረብ ለአዲሱ ኃላፊ መልካም የስራ ጊዜ ተመኝተዋል፡፡ 

አዲሱ ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ምህረት በበኩላቸው የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በልዩነት ከሚጠቀስባቸው ኮሌጆች መካከል አንዱ መሆኑን ገልፀው የዚህን ከፍተኛ ተቋም ቁመና ለማስቀጠልና በአጠቃላይ የመማር ማስተማር ሂደቱ፣ በምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም አዳዲስ የአሰራር ስነ-ዘዴዎችን በማከል የላቀ አፈጻጸም ለማስመዝገብ እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል:: ለዚህ ደግሞ በየደረጃው ያሉ የሁሉም ስራ ክፍል አመራሮች ትብብርና ድጋፍ እንዳይለያቸዉ ጠይቀዋል::
በዶ/ር ንጋቱ ወንድይፍራው የተመራዉ የስልጣን አረካካቢ ኮሚቴ አባላትና የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ማኔጅመንት አባላት አገልግሎታቸዉን ላጠናቀቁት ዶ/ር ኢ/ር ፋሲካ ቤተ ምስጋና በማቅረብ ለአዲሱ ተመራጭ ኃላፊ ዶ/ር ምህረት ዳናንቶ መልካም የስራ ዘመን በመመኘት ሽግግሩን አጠናቀዋል፡፡
ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ
ሁሌም ለልህቀት!
በንብ ማነብ ስራ ላይ ለተሰማሩ ወጣቶች ስልጠና ተሰጠ።
**
ሚያዚያ 15, 2017 ዓ/ም
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲና በኖርዌይ ኤምባሲ ድጋፍ በሲዳማ ክልል ዳሌ ወረዳ ናራሞ ዴላ ቀበሌ እየተተገበረ ባለው ፕሮጀክት በማህበር ለተደራጁ ወጣቶች ዘመናዊ የንብ ቀፎና ሌሎች ቁሳቁሶችን በድጋፍ መልክ የተበረከተ ሲሆን ለተከታታይ ሶስት ቀናት በዘመናዊ የንብ ማነብ ስራ ላይ ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ዛሬ ተጠቃሏል::

የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ማርቆስ ፍሰሀ በማህበሩ ታቅፈው እየሰሩ ያሉት ወጣቶች ከተለያዩ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው ስራ ያላገኙ መሆኑን ጠቁመው ስራ ጠባቂ ከመሆን በራሳቸው ማምረት የሚችሉበትን መንገድ ለማመቻቸት ከሀያ በላይ ዘመናዊ የንብ ቀፎዎች በድጋፍ መልክ መበርከቱንና ተከታታይነት ያለው ተግባር-ተኮር ስልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል። በስልጠናው እንዴት ዘመናዊ ግብዓቶችን ተጠቅመው ጥራቱን የጠበቀ ማር ማምረት እንደሚችሉ፣ የሰም ማምረትና ማተም ስራን የተመለከተ፣ በንብ ማነብ ስራ ላይ ራስን ከአደጋ ለመከላከል የሚረዱ አልባሳትን እንዴት መጠቀም እንደሚገባቸው አስፈላጊው ትምህርት መሰጠቱንም አክለዋል።

የዳሌ ወረዳ እንስሳት ሀብት ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሻላሞ ሹራሞ በበኩላቸው ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ማህበራዊ ኃላፊነቱን በስፋት ከሚወጣባቸው አካባቢዎች መካከል የዳሌ ወረዳ ዋነኛው መሆኑን ገልጸው በርካታ ስራ አጥ ወጣቶችን በአሳ ልማት፣ በከብትና በዶሮ እርባታ በማደራጀት ተጠቃሚ እያደረጋቸው እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ስልጠናውን ከወሰዱትና ድጋፍ ከተደረገላቸው አምስት የማህበሩ አባላት አንዱ የሆነው ወጣት ኤልያስ ቃሚሶ ዩኒቨርሲቲው ከማህበሩ ምስረታ አንስቶ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴዎች ላይ ቀጥተኛ ድጋፍ እያደረገላቸው እንደሚገኝ በመግለጽ ምስጋናውን አቅርቧል።

ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ
ሁሌም ለልህቀት!