Ethiopian Coffee and Tea Authority
5.72K subscribers
5.48K photos
30 videos
66 files
358 links
Ethiopian Coffee and Tea Authority
Download Telegram
22ኛው የAFCA ኤግዚቢሽንና ኮንፈረንስ እንዲሁም 3ኛው የአፍሪካ ቡና ሳምንት በይፋ ተከፍቶ በመካሄድ ላይ ይገኛል

ጥር 28/2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ

የሁነቱ የክብር እንግዳ የግብርና ሚንስቴር ሚንስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር መለስ መኮንን፣ የዓለም አቀፍ የቡና ድርጅት ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ቬኑሲያ ንግዌሮ፣ የAFCA ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ጊልበርት ጋታሊ፣ የኢትዮጵያ ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች ክቡር አቶ ሻፊ ዑመር እና ክቡር አቶ ታጋይ ኑሩ እንዲሁም የተለያዩ የቡና ሴክተር አካላት የስራ ኃላፊዎችና የአሀጉሪቱም ከሌላው ዓለምም የተገኙ የቡናው ሴክተር ማኅበረሰብ በተገኙበት 22ኛው የAFCA ኤግዚቢሽንና ኮንፈረንስ እንዲሁም 3ኛው የአፍሪካ ቡና ሳምንት በይፋ ተከፍቶ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በመክፈቻ መርሀግብሩ ሚኒስትር ዴኤታው ክቡር ዶ/ር መለስ መኮንን ንግግር ያሰሙ ሲሆን በንግግራቸው ሁነቱ ለቡና ቅምሻ፣ ለልዩ ልዩ ውድድሮች፣ ለእውቀት ሽግግር እና ስልታዊ ትስስር ለመገንባት 2000 የቡናው ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ከመላው ዓለም እንደሚሳተፉበት ተናግረዋል። ኮንፈረንሱ ቀጥታ የገበያ ትስስር፣ የቡና ዱካ እና ቀጣይነት ላይ በማተኮር የአፍሪካ ቡና ልህቀትን እንደሚያስተዋውቅ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ የግብርናው ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ነው ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው የእድገት ፖሊሲው ምርታማነትን ለማሳደግ፣ ጥራትን ለመጨመር እሴት ጭመራን ማስፋት፣ አግሮ ፕሮሰሲንግንና ኤክስፖርትን ማጠናከርን ቅድሚያ እንደሚሰጥ አውስተዋል። ዓለማቀፍ የቡና ስፔሻሊቲ፣ የቡና ዘላቂነትና የቡና ዱካ ፍላጎት መጨመር ትልቅ እድልን ለአፍሪካ በተለይም ለፕሪሚየም የአረቢካ ቡና አምራቾች ይዞ እንሚመጣ ገልጸዋል።

ንግግራቸውን ሲቀጥሉም በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድ የተጀመረው ግሪን ሌጋሲ ምን ያህል የቡና ልማቱን እንዳፋፋመው ከገለጹ በኋላ ሌጋሲው የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በቀጣይ የኢትዮጵያን ብሎም የአፍሪካን ምርታማነት ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተቋቋሚነትንና ዓለማቀፍ ተወዳዳሪነትን የሚያሳድግ ስትራቴጂያዊ ኢንቨስትመንት እንደሆነ አብራርተዋል። ለዚህም እውናዊነት የአፍሪካ የቡናው ሴክተር ትብብር እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል።

ይህን ካሉም በኋላ ጥር 28 እና 29 የሚካሄደውን 22ኛውን የአፍሪካ የቡና ኤግዚቢሽንና ኮንፈረንስ እንዲሁም 3ኛው የአፍሪካ ቡና ሳምንት ቀን በይፋ መጀመሩን አብስረዋል፤ ለዝግጅቱም ሚና የተጫወቱ አካላትን አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ም/ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ ሻፊ ዑመር በበኩላቸው እንግዶቻቸውን እንኳን ደህና መጣችሁ ካሉ በኋላ ኢትዮጵያ ኤግዚቢሽኑንና ኮንፈረንሱን አዘጋጅ ሀገር በመሆኗ ክብር እንደሚሰማቸው ገልጸው ሁነቶቹ ኤግዚቢሽኖች፣ ከፍተኛ ደረጃ ያላቸው ኮንፈረንሶችና የቢዝነስ ለቢዝነስ ተሳትፎ የአፍሪካን ቡናን በእጅጉ ለማሳደግ ያለንን ቁርጠኝነት ማሳያ ነው ብለዋል። ሁነቱም ከአፍሪካና ሌሎች አህጉራት በአምራቾች፣ በገዢዎች፣ በፖሊሲ አዘጋጆች፣ በተመራማሪዎችና በኢንቨስተሮች መካከል ትብብርን በማጠናከር ለውይይት፣ ለአጋርነት፣ ለፈጠራ እንዲሁም ለንግድ ልዩ ዕድል እንደሆነ ተናግረዋል።

የአፍሪካ ፋይን ኮፊ አሶሴሽን ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ሚስተር ጊልበርት ጋታሊም ንግግር አሰምተዋል። በንግግራቸው የዘንድሮው 22ኛው ኤግዚቢሽንና ኮንፈረንስ በአይነቱ ትልቁና ምርጡ ዝግጅት ነው ብለዋል። ድርጅቱም በቡና ኢንዱስትሪው ውስጥ ያሉ ፕሮፌሽናሎችን መምራትና ማነቃቃት ኃላፊነቱ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ በዛሬውና በቀጣዩ ቀን በሁነቱ የሚከናወኑ ተግባራት ማሳያ ይሆናሉ ሲሉ ተናግረዋል።

ከኤግዚቢሽኑና ኮንፈረንሱ ሁነት ጋር በተያያዘ ስለተከናወኑት ተግባራት ሲያወሱም ቴስት ኦፍ ሀርቨስት ክንውን አንዱ ነው ካሉ በኋላ የዘንድሮው ውድድር ወደጫረታ የሚያመራ መሆኑን ልዩ ያደርገዋል ብለዋል። ሌላው የዘንድሮው ሁነት ለየት የሚያደርገውን ሲናገሩ በሁነቱ ከ30 ሀገራት 25 ተወዳዳሪዎች የሚሳተፉበት ከእስከዛሬው ሰፋ ያለ የባሬስታ ሻምፕዮንሺፕ ውድድር እንደሚካሄድበት አውስተዋል። በመቀጠልም በዘንድሮ ኤግዚቢሽንና ኮንፈረንስ EUDR LEARNING COMMUNITY for AFRICA የሚል ፕሮጀክት የማስጀመር መርሀግብር እንደሚከናወን ተናግረዋል። ሌላው ለየት ያለ ክንውን ሲያሳውቁም ከዓለማቀፉ የቡና ፕላትፎርም ጋር አጋርነት እንደተፈጠረና ድርጅቱ አባል እንደሆነ ገልጸው አጋርነቱ የአፍሪካን እምቅ አቅም ወደተግባር መቀየርን ያለመ ነው ብለዋል። ከአጋርነት ጋር በተያያዘ የተፈጸመው ሌላውን ተግባር ይፋ ሲያደርጉም ከቡና ጥራት ኢንስቲትዩሽን ጋር እንደሆ ተናግረዋል። የዚህ አጋርነትንም ሲገልጹ የአፍሪካን የቡና ጥራት ለማሳደግ ነው ብለዋል።

በወቅቱ የዓለም የቡና ድርጅት ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተርም ንግግር ያሰሙ ሲሆን ሁኑቱ ልምድ መለዋወጫና የቡናው ሴክተር ያሉበት ችግሮች መፍትሄ ማበጃ እንደሚሆን እምነታቸውን ገልጸዋል። ችግሮችም እንዳሉ ሁሉ መልካም እድሎችም እንዳሉ ከወሱም በኋላ ለዚህ ተፈጻሚነት መተባበር እንደሚያሻ አጽንኦት ሰጥተዋል። በስመጨረሻም ከደን ምንጣሮና ሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ቡና የመፍትሄ እንጂ የችግር አካል አደለም ካሉ በኋላ ወጣቱ ትውልድ በሴክተሩ ውስጥ በስፋት እንዲሳተፍ መክረዋል።

ከቤት ውስጥ መርሀ ግብሩም በኋላ እንግዶቹና ሌሎች ታዳሚዎች በየቡዞቹ በመዘዋወር የቡና አካላቱን ኤግዚቢሽን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

አሸናፊ ጌታሁን እንደዘገበው
ከጉጂ ዞን ባለፉት ስድስት ወራት ከ8 ሺህ 200 ቶን በላይ የቡና ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ቀርቧል
አዶላ፤ ጥር 26/2018 (ኢዜአ)፡- ከኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ከ8 ሺህ 200 ቶን በላይ የቡና ምርት ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን የዞኑ ንግድ ጽህፈት ቤት ገለጸ።
የጽህፈት ቤቱ ሀላፊ አሬሩ ዋሬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በተያዘው በጀት ዓመት ከዞኑ ከ75 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ ነው፡፡
ከዞኑ 12 ወረዳዎች እስካሁን ድረስ 8 ሺህ 233 ቶን ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ የቡና ምርት ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን ገልጸዋል፡፡
እስካሁን ከቀረበው የቡና ምርት ውስጥ 2 ሺህ 71 ቶን የሚሆነው የታጠበ፤ 6 ሺህ 161 ቶን በላይ ደግሞ የተቀሸረ እና የደረቅ ቡና ምርት እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
በዞኑ ባሉት 350 የደረቀና እሸት ቡና ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ጥራት ያለው ምርት ተዘጋጅቶ ለገበያ እየቀረበ መሆኑንም ገልፀዋል።
የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ረጋሳ ጦሬ በበኩላቸው፤ በዞኑ 377 ሺህ ሄክታር መሬት በቡና ልማት መሸፈኑን አስታውቀዋል፡፡
በየአመቱ በአማካይ ከዞኑ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል በላይ የቡና ምርት እየተሰበሰበ እንደሆነ አመልክተው ዘንድሮ ከፍተኛ ምርት እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።
#Ethiopian_News_Agency
የሻይ ልማት ኢንሼቲቭን ተግባራትን በማጠናከር የገጠር ትራንስፎርሜሽን አጀንዳን ውጤታማ ማድረግ እንደሚገባ ተገለጸ

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን በካፋ ዞን ገዋታ ወረዳ የቦጊንዳ ‎የሻይ ችግኝ ዝግጅት ጣቢያ ከአካባቢው ለተወጣጡ አርሶ አደሮችና የግብርና ባለሙያዎች ስልጠና ተሰጥቷል።

ዓላማው የተዘጋጀውን የሻይ ቅጠል ችግኝን ከተከላ በፊት ከውጪው አየር ጋር በተገቢ ማላመድ፣ የመንከባከብና ከተላመደ በኃላ ወደ አርሶ አደሩ ማሳ በመውሰድ ለመትከል ከማሳ ልየታ እስከ ተከላና ምርት አሰባሰብ ሂደት ላይ ግንዛቤ ለማስጨጥ የተዘጋጀ ስልጠና ነው።

በተግባር የተደገፈ ስልጠናው በውሽውሽ የሻይ ልማት ባለሙያ በሆኑት በአቶ ጋዲሳ ተስፋዬ ለሰልጣኞች ተሰጥቷል።

በስልጠናው ችግኙን በአግባቡ የማላመድ ሂደቱ በአግባቡ መተግበር የችግኞችን ሞት እንደሚታደግ እንዲሁም ተገቢውን ግብዓትና ጥንቃቄ ማድረግ ለምርታማነት ሚናው የጎላ መሆኑ ተነስቷል ።

መድረኩን ያጠቃለሉት የክልሉ ቡና ሻይና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አስራት መኩሪያ፣ የገጠር ትራንስፎርሜሽንን ዕውን ለማድረግ በአካባቢው ያለውን ዕምቅ አቅምን በመለየት ወደ ውጤት በመቀየር ከአካባቢው ፍጆታ አልፍ ለማዕከላዊና ውጪ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን በብዛትና በጥራት ማምረት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከነዚህም አንዱ በክልሉ የተጀመረው የሻይ ቅጠል ኢንሼቲቭ መሆኑን በመጥቀስ በዞኑ ውስጥ ያለው ተስማሚ የአየር ንብረት፣ የዝናብ ስርጭትና ለምና ተስማሚ መሬትን በተገቢው በመጠቀም ለተጠቃሚነት በትኩረት በዕቅድ መስራት አለበት ብለዋል።

አክለዉም መንግስት እንደ ቡና ልማት ሁሉ ለሻይ ልማቱ ሥራ ትኩረት በመስጠት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ያነሱት አቶ አስራት ከሂደት እስከ ውጤት ያለው ድካም የሚጠይቅ በመሆኑ ለተሻለ ውጤት በትዕግሥት መስራት እንደሚገባው አንስተዋል።

ለተከላ የሚመረጠው ማሳ ለኢንዱስትሪው የሚመች፤ በኩታ ገጠም በማልማት አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ በቅንጅት መስራት ይገባል ያሉት የክልሉ ቡና ሻይና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ ኮጅአብ ናቸው።

ስልጠናውን በግብዓትነት በመጠቀም ለአርሶ አደሮች ግንዛቤ በመፍጠር ከዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ጨምረው ተናግረዋል።

የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የገዋታ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አርጋው ኃይሌ፤ የክልሉ ግብርና ቢሮ በወረዳው የተጀመረው ኢንሼቲቭ ውጤታማ እንዲሆን ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።

ስልጠናው ኢንሼቲቩ አድስ እንደመሆኑ መጠን የነበሩ የግንዛቤና የክህሎት ክፍተት እንደሚሸፍን ሰጣኞቹ አንስተዋል።

በስልጠናው ላይ የክልሉ ቡና ሻይና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ ኮጅአብን ጨምሮ ተከላ ከሚካሄድባቸው 8 ቀበሌዎች የመጡ የቀበሌ ዋና አስተዳዳሪዎች፣ የግብርና ባለሙያዎችና የችግኝ ጣቢያ አስተባባሪዎችና የባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።