Ethiopian Coffee and Tea Authority
5.74K subscribers
5.49K photos
30 videos
66 files
358 links
Ethiopian Coffee and Tea Authority
Download Telegram
የቡና ምርታማነትን በማሳደግ ከዘርፉ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የስልጤ ዞን ግብርና መምሪያ የቡናና ቅመማ ቅመም ጽ/ቤት ገለፀ፡፡

ወራቤ፤ ታህሳስ 26/2018 ስልጤ ኤፍ ኤም፤ የቡናና ቅመማ ቅመም ልማት ጽ/ቤት በቡና ወቅታዊ ተግባራት ዙሪያ ለወረዳና ከተማ አስተዳደር ለተውጣጡ የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች የክህሎት ስልጠና ሰጥቷል፡፡

ያረጀ ቡና ጉንደላና ምቀሳ እንዲሁም በተከላ ቡና ቅየሳ አወጣጥና በቡና ችግኝ አተካከል ፣በቡና በሽታና በግብይት መመሪያ ዙሪያ በጽ/ቤቱ ከፍተኛ ባለሙያዎች ተሰጥቷል፡፡

በስልጠና ማጠቃለያ ላይ የዞኑ ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊና የቡና ቅመማ ቅመም ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ቶፊቅ ኑሪ ስልጠናው የዘርፉ ባለሙያዎች በእውቀትና በክህሎት ታግዘው አርሶ አደሩን እንዲደግፉ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ለቡና ምርታማነት መቀነስ ዋናው ምክንያት የቡና ማሳ አያያዝና እንክብካቤ ያለው አንዱ ጉድለት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በእርጅና ምክንያት ምርታማነታቸው የቀነሱ የቡና ዛፎችን ሳይንሱን ተከትለው ለማደስ እና ለመጎንደል የሚያስችል በንድፈ ሀሳብና በተግባር የተደገፈ ስልጠና ለአመራሮችና ለዘርፉ ባለሙያዎች መሰጠቱን አቶ ቶፊቅ ተናግረዋል፡፡

የቡና ምርታማነት በሁለት መንገድ ማሳደግ ይቻላል ያሉት አቶ ቶፊቅ አንደኛው ያረጁ ቡናዎች በማደስ (በመጎንደል) ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ያረጁ ቡናዎችን በንቀል በአዲስ መተካት እንደሆነ አስረድተዋል ።

ጉንደላ እና እድሳት የሚደረግላቸው ቡናዎች በተለይ በበሽታ የተጠቁ፣ ምርት መስጠት የማይችሉና እንዲሁም ከተተከሉ ረጅም ዕድሜ የሆናቸው እንደሆነም ኃላፊው አያይዘው ተናግረዋል።

አቶ ቶፊቅ አክለውም የቡና ምርታማነትን በማሳደግ ከዘርፉ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በዞኑ በዘንድሮ ዓመት ከ272 ሄክታር መሬት በላይ ቡናን ለመጎንደል ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በስልጠናው የተሳተፉ አካላት ከቅየሳ ጀምሮ እስከ የቡና የተከላ አይነት፣ ጎንደላ፣ ምቀሳ እና ግረዛ ድረስ በንድፈ ሀሳብና በተግባር የተደገፈ ግልፅና አስተማሪ የሆነ ግንዛቤ የተገኘበት እንደሆነ አንስተዋል፡፡

በመጨረሻም ያረጀ ቡና ጉንደላና ምቀሳ እንዲሁም በቡና ጉድጓድ ቁፋሮ ቅየሳ አወጣጥና በቡና ችግኝ አተካከል
በወራቤ ከተማ 01 ቀበሌ ወርኮ መንደር በአርሶ አደር የቡና ማሳ ላይ በተግባር የተደገፈ ስልጠና በመስጠት ተጠናቋል፡፡
የሻይ ልማትን ለማላቅ እየታተረች ያለችው ኢትዮጵያ

አዲስ አበባ፤ታኅሣስ 28/2018 (ኢዜአ)፡-በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች ለሻይ ልማት ተስማሚና ምቹ ሥነ-ምኅዳር መኖሩን መረጃዎች ያመላክታሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአረንጓዴ ዐሻራ አካል የሆነው የሻይ ልማት ኢኒሼቲቭ ተከላ በጥሩ ሁኔታ እየተከወነ መሆኑን ሰሞኑን በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው አስታውቀዋል።

በመትከል የታየው መልካም ጅማሮ በአግሮ-ፕሮሰሲንግ ከተደገመ ሙሉ እንደሚሆንም አስገንዝበዋል።

በዚህም መሠረት የግሉ ዘርፍ ዕሴት በማከል ቢሳተፍ ከሀገር ውስጥ ፍጆታ በተጨማሪ በኤክስፖርት ሀገራችንን ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።

እስካሁን በኢትዮጵያ ስላለው የሻይ ልማት እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የቡና፣ሻይና ቅመማቅመም ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍቃዱ ደፈረስ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በቆይታቸውም፥ እስካሁን ባለው መረጃና ልየታ መሠረት በኢትዮጵያ ለሻይ ቅጠል ልማት ተስማሚና ምቹ የሆነ ከ6 ሚሊየን ሔክታር የሚልቅ መሬት መኖሩን አመላክተዋል።

ካለው የመልማት ዐቅም አንጻር እየለማ ያለው አነስተኛ መሆኑን አንስተው፤ በዘርፉ በቀጣይ የተሻለ ለመሥራት መንግሥት ትኩረት መስጠቱን ጠቁመዋል።

ለዚህም ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአረንጓዴ ዐሻራ አካል የሆነው የሻይ ቅጠል ልማት ኢኒሼቲቭ ተከላ በጥሩ ሁኔታ እየተከወነ መሆኑን መግለጻቸው ማሳያ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የሻይ ቅጠል ወደ ተለያዩ ሀገራት በመላክ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎቷን እንደምትደጉምም አንስተዋል።

ለአብነትም በ2017 የበጀት ዓመት 882 ነጥብ 45 ቶን የሻይ ቅጠል ምርት ወደ እንግሊዝ፣ ሕንድ እና ጀርመን በመላክ 1 ነጥብ 61 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን አረጋግጠዋል።

በተያዘው የበጀት ዓመትም 898 ቶን በመላክ 1 ነጥብ 72 ሚሊየን ዶላር ለማግኘት መታቀዱን ጠቁመው፤እስካሁን በእርሻ ልማቶች እና በአርሶ አደሮች በሻይ ቅጠል ተክል ከለማው 4 ሺህ 936 ሔክታር 4 ሺህ 854 ቶን ምርት መሰብሰቡን ጠቅሰዋል።

ከዚህ አንጻር ዘርፉ እንደ ሌሎች የወጪ ምርቶች የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው አስገንዝበው፤ በይበልጥ አጠናክሮ በማስቀጠል ሀገር የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ማድረግ እንደሚገባ አስረድተዋል።

የሻይ ቅጠል ተክል አንድ ጊዜ ከተተከለ ለ80 እና 90 ዓመታት ምርት በመስጠት የሚቆይና በየ15 ቀኑ ምርቱን በመልቀም ገቢ ማግኘት የሚያስችል ስለመሆኑም አስገንዝበዋል።

እንደ አቶ ፍቃዱ ገለጻ፤ በኢትዮጵያ በሰፋፊ እርሻዎች ውስጥ አምስት የሻይ ቅጠል ምርት ማዘጋጃ ፋብሪካዎች አሉ።

በሻይ ማዋሀድ (ዕሴት በመጨመር) ላይ ተሰማርተው ለሀገር ውስጥና ለዓለም አቀፍ ገበያ ልዩ ምርቶችን እያቀረቡ ያሉ ኩባንያዎችም፤ ኢትዮ አግሪ ሴፍት (ውሽውሽና ጉመሮ ሻይ ልማት)፣ ኢስት አፍሪካ አግሪ ቢዝነስ፣ ሄሪቴጅ ሻይ ኢትዮጵያ እና መታድ የግብርና ልማት መሆናቸውን አብራርተዋል።

የሻይ ቅጠል ተክል (Assam tea type) ወደ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የገባው በፈረንጆቹ 1927 የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳስ በነበሩት ጆርጅ ሆላንድ አማካኝነት እንደሆነም አውስተዋል።

ጆርጅ ሆላንድ ከውጭ ያመጡትን የሻይ ቅጠል ተክል ዘር በቦንጋ ከተማ ቶንጎላ አካባቢ ለሚኖሩ አርሶ አደሮች እንዲያለሙት ማሠራጨታቸውንም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም በፈረንጆቹ 1928 የእንግሊዝ ቆንስል የነበሩት አብዱል መጅድ ከሕንድና ኬንያ የሻይ ቅጠል ተክል ፍሬዎችን በማስመጣት በኢሉአባቦር ዞን አሌ ወረዳ ጉመሮ አካባቢ ማሠራጨታቸውን አመላክተዋል።

እንዲሁም በኢትዮጵያ ከ1950 እስከ 1960 ዓ.ም አማራጭ የግብርና ልማት ማስፋፋት ሥራዎች አካል በመሆን የሻይ ቅጠል ልማት እና ኢንቨስትመንት ሥራ መጀመሩን አንስተዋል።

ልማቱ በተጠናከረ መልኩ የተጀመረው ሁለቱ ሰፋፊ የሻይ ቅጠል ተክል እርሻዎች በሚገኙባቸው በውሽውሽ እና ጉመሮ አካባቢዎች ከ1950 ዓ.ም ጀምሮ መሆኑንም ይጠቅሳሉ።

ከ1972 ዓ.ም ጀምሮም በቡናና ሻይ ልማት ሚኒስቴር እየተመራ በተጠናከረ መልኩ ሲሠራበት መቆየቱን አውስተዋል።

ከወቅቱ መንግሥት ለውጥ በኋላ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በመፍረሱ የሻይ ልማት ድርጅቶቹ ወደ ግል ይዞታ (ኢትዮ-አግሪሴፍት አ.ማ) ተዛውረው እየተመሩ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ፣በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና ጋምቤላ ክልሎች በአራት የሻይ ልማት ድርጅቶች (ውሽውሽ፣ ጉመሮ፣ኢስት አፍሪካ (የጨዋቃ ኡቶ) እና ቨርዳንታ) እንዲሁም በአነስተኛ አርሶ አደሮች በአውት ግሮዎርስ ትሥሥር እና በኩታ ገጠም እየለማ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

እስካሁን ባለው መረጃም የሻይ ልማት ዘርፍ ከ80 ሺህ ለሚልቁ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፈጠሩን አስታውቀዋል።

#ኢዜአ
በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት መሠረት ዕሴት የታከለበት ቡናን መላክ ተጀምሯል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 30/2018

በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት መሠረት ዕሴት የታከለበት የኢትዮጵያ ቡናን ለአፍሪካ ሀገራት ገበያ መላክ መጀመሩን የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።

የአፍሪካ ሕብረት መረጃ እንደሚያሳየው የአፍሪካ ሀገራት 85 በመቶ ምርታቸውን ለአውሮፓ፣ እስያ፣ ሰሜንና ላቲን አሜሪካ ገበያ የሚልኩ ሲሆን በአንፃሩ የእርስ በእርስ የንግድ ልውውጣቸው ከ15 በመቶ ያልበለጠ ነው።

የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራም የሀገራቱን የእርስ በእርስ የንግድ ትስስር በማሳለጥ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን እንደሚያሳደግ ታምኖበታል።

አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነቱም የአፍሪካ ሀገራትን የንግድ ታሪፍና መሰናክል በማስወገድ ወጥ በሆነ የአሰራር ሥርዓት የእርስ በእርስ የገበያ ትስስርን ማሳለጥ ዋና ዓላማው ያደረገ ነው።

ይህም የአህጉሪቱን አባል ሀገራት የንግድ ልውውጥ በማሳደግ፣ የኢንዱስትሪ ዕድገትን በማፋጠንና ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር የአፍሪካን ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለማሳለጥ ከፍተኛ ፋይዳ አለው።

በዚህም ኢትዮጵያ በአህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነቱ መሰረት ከመስከረም 29 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ገበያ ምርቶችን መላክ ጀምራለች።

የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሻፊ ዑመር ለኢዜአ እንዳሉት፤ በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ሥምምነት መሰረት የኢትዮጵያ ቡና ገበያ መዳረሻን ለማስፋት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የአፍሪካን ሰፊ የገበያ ዕድል ለመጠቀም የኢትዮጵያን ጥሬ ቡና ከመላክ ይልቅ ዕሴት ጨምሮ ለማቅረብ ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዚህም በአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት ዕሴት የተጨመረበትን ቡና የመላክ ጅማሮን የበለጠ ለማስፋት በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ አዳዲስ የቡና ገበያ መዳረሻዎችን እያሰፋች ነው ያሉት አቶ ሻፊ፤ ለአብነትም በ2016 ዓ.ም የኢትዮጵያን የቡና ገበያ መዳረሻ ከ64 ሀገራት በ2017 ዓ.ም ወደ 84 ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።

የኢትጵያን ነባር የቡና ገበያ መዳረሻን በማጠናከርና አዳዲስ ገበያን ለማስፋት በተለያዩ ሀገራት ከሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

ቻይናን ጨምሮ አስር የእስያ ሀገራት የኢትዮጵያን ቡና እየገዙ እንደሚገኝ ጠቁመው በቀጣይም ቡና ላይ ዕሴት በመጨመር የአፍሪካ እና እስያ ገበያን ለመጠቀም ከኢትዮጵያ ቡና ላኪዎችና የአውሮፓ ባለሃብቶች ጋር በመቀናጀት ዕሴት ጨምሮ መላክ ላይ እንዲሳተፉ ይሰራል ብለዋል።
ኢትዮጵያ እና ቻይና በግብርና በተለይም በቡና ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ እያሳደጉ ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 30/2018
ኢትዮጵያ እና ቻይና በግብርና በተለይም በቡና ዘርፍ ያላቸውን ስትራቴጂካዊ አጋርነትና ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ እያሳደጉ መሆኑን የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ።
ቻይና የኢትዮጵያ ቡና መዳረሻ በመሆን ባለፉት አምስት ዓመታት ከ33ኛ ወደ አራተኛ ደረጃ ከፍ ማለቷ ታውቋል።
የኢትዮጵያን ቡና በቻይና እና በዓለም ገበያ የማስተዋወቅ ዓላማ ያለው የንግድና የኢኮኖሚ ትብብር በቻይና ጁጆ ከተማ ተካሂዷል።
የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኢትዮጵያ እና ቻይና በግብርናው ዘርፍ ያላቸው ትብብር ከንግድ ባለፈ ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
ለዚህ ትብብር መጠናከርና ለቡና ወጪ ንግድ ዕድገት መነሻ ከሆኑት መካከልም የቻይና የቡና መዳረሻነት ማደግ፣ የነፃ ታሪፍ ዕድል፣ የቴክኖሎጂ እና የዕውቀት ሽግግር፣ የኢ-ኮሜርስ ትስስር እንዲሁም የሁናን ግዛት የንግድ ማዕከልነት ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ኢፋ ሙለታ(ዶ/ር) እንደገለጹት፤ መንግሥት የግብርና ምርቶችን በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ለማድረግ ሰፊ የሪፎርም ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
ለዚህም የምርት ጥራትንና መጠንን ለማሳደግ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን፣ አዳዲስ ኢኖቬሽኖችንና የግብርና ግብዓቶችን በስፋት ጥቅም ላይ ማዋል ዋነኛው የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ጠቁመዋል።
በቻይና የተካሄደው ኮንፍረንስም የሀገሪቱን የወጪ ንግድ ገቢ ለማሳደግ ከሚደረጉ ጥረቶች መካከል አንዱ ነው ብለዋል።
ከቡና ምርት ባለፈ የእንስሳት ተዋጽኦን፣ የዓሳ ምርቶችንና ሌሎች የግብርና ውጤቶችን በስፋት ቻይናን ጨምሮ ወደ ሌሎችም ሀገራት ለማቅረብ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ይህም በኢትዮጵያ እና በቻይና መካከል ያለውን የንግድ ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ጠቁመው፤ ለኢትዮጵያ ላኪዎች አዳዲስ የገበያ ዕድሎችን እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ለቡና ምርታማነትና ጥራት የሰጠችው ትኩረት በዘርፉ የወጪ ንግድ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቱን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ቡና በበርካታ ሀገራት ተመራጭነቱ እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመው፤ በተለይም ቻይና ዋነኛ የቡና መዳረሻ እየሆነች ነው ብለዋል።
ለአብነትም ቻይና ከአምስት ዓመት በፊት የኢትዮጵያ ቡና የወጪ ንግድ መዳረሻ ከሆኑ ሀገራት መካከል ከነበረችበት 33ኛ ደረጃ ወደ 4ኛ ደረጃ ከፍ ማለቷንም ተናግረዋል፡፡
ይህ ውጤት የተመዘገበው በአንድ በኩል የቻይናውያን የቡና ፍላጎት መጨመር በሌላ በኩል የቻይና መንግሥት ለአፍሪካ ሀገራት በሰጠው የነፃ ታሪፍ ዕድል የተነሳ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ባለ ልዩ ጣዕም ቡና በቻይናውያን ዘንድ ተወዳጅነትን እያተረፈ መምጣቱንም ጨምረው ጠቅሰዋል።
የሁለቱ ሀገራት የቡና ንግድ ትስስር እያደገ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በቅርቡ በጁጆ ከተማ በተካሄደው ኮንፍረንስ በርካታ ገዥ ኩባንያዎች መሳተፋቸውንና አዳዲስ የገበያ ትስስር ስምምነቶች መፈረማቸውን ገልጸዋል፡፡
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ፤ በቻይና የተካሄደው ኮንፍረንስ የኢትዮጵያን ቡና በስፋት ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል የፈጠረ ነው ብለዋል።
ቻይና ያላት ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር እና በየጊዜው እያደገ የመጣው የቡና ፍላጎት ለኢትዮጵያ ቡና ወደፊትም ሰፊና አስተማማኝ የገበያ መዳረሻ እንድትሆን ያደርጋታል ነው ያሉት።
በመድረኩ ከቡና አፈላል ጀምሮ ያለውን ኢትዮጵያዊ ሥርዓት ለቻይናውያን ማስተዋወቅ መቻሉን ጠቅሰው፤ ቡና በሀገር ገጽታ ግንባታ በኩል ያለውን ትልቅ አቅም ለመጠቀም እየተሠራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የቡና ንግድ ትብብር ይበልጥ ለማስፋት አዲስ ምዕራፍ መከፈቱንም አቶ ተስፋሁን ለኢዜአ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እሴት የተጨመረበት ቡና ለዓለም ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ገቢዋን ለማሳደግ እየሠራች ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 1/2018: ኢትዮጵያ ቡናን በጥሬው ከመላክ ይልቅ እሴት ጨምሮ ለዓለም ገበያ በማቅረብ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሬ ገቢ በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ በቁርጠኝነት እየሠራች መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ገለጸ።
ኢትዮጵያ የቡና መገኛና ከአፍሪካ ቀዳሚዋ አምራች ሀገር ስትሆን ቡናን እሴት ጨምሮ ወደ ውጭ በመላክ የተጀመረው ጥረት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ነው፡፡
ባለፈው በጀት ዓመት ኢትዮጵያ 470 ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አግኝታለች፡፡
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ(ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት የ15 ዓመት የቡና ስትራቴጂ ፍኖተ ካርታ ተቀርጾ ወደ ሥራ ተገብቷል።
በዚህም በዘርፉ የነበሩ መዋቅራዊ ችግሮችን በመለየት በምርትና ምርታማነት እንዲሁም በገበያ አድማስ ማስፋት ላይ ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡
ምርታማነታቸው ዝቅተኛ የነበሩ ያረጁ የቡና ተክሎችን በመጎንደል የማሳ ላይ ምርታማነትን የማሳደግ ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡
በሀገር አቀፉ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር ታግዞ አዳዲስ የቡና ተክሎች በስፋት መተከላቸውን ጠቁመዋል።
በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን የምርት መጠን ብቻ ሳይሆን ጥራት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው ቡናው በከፍተኛ ጥራት እንዲመረት ጥብቅ ክትትል እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ምርታማነትን ከማሳደግ ጎን ለጎን የግብይት ሰንሰለቱን ማሳጠር ዋነኛው የትኩረት አቅጣጫ ሆኖ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው በዚህም ለውጥ እየመጣ ይገኛል ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል የነበረውን የተንዛዛ የገበያ ሥርዓት በፖሊሲ ማሳጠር በመቻሉ ይባክን የነበረውን የምርት መጠን መቀነስና በጥራት ላይ ይፈጠሩ የነበሩ አሉታዊ ተፅዕኖዎችን ማስቀረት መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ ካላት የቡና አቅም አንጻር የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ እሴት ጨምሮ ለገበያ የማቅረብ ሥራ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ቀደም ሲል እሴት የተጨመረበት ቡና በምን ዓይነት የጥራት ደረጃና ሁኔታ ወደ ውጭ መላክ እንዳለበት የሚወስኑ ግልጽ መመሪያዎች ባለመኖራቸው ዘርፉ ሳይነቃቃ መቆየቱን አስረድተዋል።
ይህንን ክፍተት በመሙላት ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥር አዲስ መመሪያ ጸድቆ ወደ ሥራ መገባቱን ጠቁመው አዲሱ መመሪያ በሀገር ውስጥ የተቆላና የተፈጨ ቡናን በውጭ ምንዛሬ የመሸጥ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡
በዚህም በርካታ የቡና ቆይ ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን በኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በትላልቅ ሆቴሎችና በቱሪስት መዳረሻዎች በውጭ ምንዛሬ መሸጥ መጀመራቸውን ጠቁመዋል፡፡