Ethiopian Coffee and Tea Authority
5.75K subscribers
5.52K photos
30 videos
66 files
358 links
Ethiopian Coffee and Tea Authority
Download Telegram
አርሶ አደሮች ቡናን በጥራት አምርቶ ለገበያ ለማቅረብ ያላቸው ተነሳሽነት እያደገ መጥቷል - ሚኒስትር አዲሱ አረጋ

ሀዋሳ፤ ታህሳስ 22/2018 በሁሉም ቡና አብቃይ ወረዳዎች በተደረገ የባለሙያ ድጋፍ አርሶ አደሮች ቡናን በጥራት አምርቶ ለገበያ ለማቅረብ ያላቸው ተነሳሽነት እየተሻሻለ መምጣቱን የግብርና ሚኒስትሩ አዲሱ አረጋ ገለጹ።

በሲዳማ ክልል ሸበዲኖ ወረዳ በቡና ልማት ላይ የተሳተፉ አርሶ አደር ማሳ የጎበኙት የግብርና ሚኒስትሩ አዲሱ አረጋ እንዳሉት በተያዘው ዓመት 600ሺህ ቶን ቡና ለውጪ ገበያ ለማቅረብ ታቅዷል።

ለውጭ ገበያ ከሚቀርበው የቡና ምርት ከ3 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት ግብ ተይዞ ውጤታማ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

በሲዳማ ክልሉ ቡና አምራች በሆኑ አካባቢዎች የቡና ጥራትና ምርታማነትን በማሳደግ ተጠቃሚ ለመሆን እየተሰራ ያለው ሥራ በዘርፉ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ማሳያ መሆኑንም ተናግረዋል።

የቡና ዝርያን ለማሻሻል፣ የአመራረት ዘዴን ለማዘመን፣ ኩታ ገጠም የቡና ልማትን ለማስፋፋትና ምርታማነታቸው የተረጋገጠ የቡና ዝርያዎችን ለማልማት የተሰራው ሥራ ዕቅዱን ለማሳካት እንደሚያስችል ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያን ቡና በቻይና የማስተዋወቅ ሥራ እየተሰራ ነው ያሉት ሚኒስትሩ በተለይ ከባለ ልዩ ጣዕም ቡና ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በቀጣይ በተለያዩ ሀገራት የማስተዋወቅ ሥራ ይሰራል ብለዋል።

ዘንድሮ ለውጪ ገበያ ለማቅረብ የተያዘውን ዕቅድ ማሳካት የሚያስችሉ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እንዳሉ ጠቁመው፣ በሁሉም ቡና አብቃይ ወረዳዎች በተደረገ የባለሙያ ድጋፍ አርሶ አደሮች ቡናን በጥራት አምርቶ ለማቅረብ ያላቸው ተነሳሽነት መሻሻሉን ገልጸዋል።

የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ሀላፊ መምሩ ሞኬ በበኩላቸው በክልሉ ቡና እና አቮካዶ ለውጪ ገበያ እንደሚቀርብ ታሳቢ ተደርጎ እየሰተራ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ የተለያዩ ስትራቴጂዎችን በመጠቀም የቡና ጥራትና ምርታማነትን ለማሻሻል ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመው አዳዲስ የቡና ዝርያዎችን መጠቀምን ጨምሮ ምርታማነትን የሚያሳድጉ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በእርጅና ምክንያት ምርታማነቱ የቀነሰ የቡና ተክልን በአዲስ የመተካትና ባህር ዛፍን ነቅሎ በቡና የመተካት ሥራ እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።

የክልሉ ቡና፣ ቅመማቅመምና ፍራፍሬ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መስፍን ቃሬ በክልሉ በተያዘው ዓመት ወደ ውጪ ከሚላከው 40ሺህ ቶን ቡና 17 በመቶ የሚሆነው ባለልዩ ጣዕም እንደሚሆንና ይህንንም በሂደት ወደ 20 በመቶ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

አርሶ አደሮችም ባለልዩ ጣዕም ቡና አምርተው ለውጪ ገበያ በራሳቸው በቀጥታ መላክ እንዲችሉ ለ400 አርሶ አደሮች ፈቃድ በመስጠት ክትትልና ደጋፍ እየተደረጋላቸው መሆኑንም ተናግረዋል።

በክልሉ ሸበዲኖ ወረዳ ባለልዩ ጣዕም ቡና አምርተው ለውጪ ገበያ ቀጥታ ለማቅረብ ፈቃድ ከተሰጣቸው አርሶ አደሮች መካከል ቦዳ ሳጉና እንዳሉት በሁለት ሄክታር መሬት ቡና እንዳለሙና ከሄክታር 30 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን አስታውቀዋል።

ያመረቱትን ምርት በቀጥታ ወደ ውጪ ለመላክ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ጠቁመው ከክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ እና ከቡና፣ ቅመማቅመምና ፍራፍሬ ባለስልጣን ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል። ኢዜአ
የኢትዮጵያ የቡና ምርታማነት የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነትን በማሳደግ ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ከፍተኛ አቅም እየፈጠረ ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 23/2018

የኢትዮጵያ የቡና ምርታማነት ዓለም አቀፍ የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነትን በማሳደግ ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ከፍተኛ አቅም እየፈጠረ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን አስታወቀ።

ኢትዮጵያ የግብርናውን ምርታማነት የሚያሳድጉ የተሻሻሉ ዝርያዎችንና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በዘርፉ ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበች ትገኛለች።

የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ዋነኛ ምንጭ የሆነው ቡናም የዚህ አካል ሲሆን ባለፉት የለውጥ ዓመታት በቡና ምርታማነት ላይ በተከናወኑ ስራዎች አበረታች ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሻፊ ዑመር ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ተከናውነዋል።

መንግስት ቡናን በብዛት፣ በጥራትና ዓለም አቀፍ ፍላጎትን ባገናዘበ መልኩ በማምረት ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት ያለው አበርክቶ እንዲያድግ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ያረጁ የቡና ተክሎችን በአዲስ የመተካት እንዲሁም ቴክኖሎጂን የመጠቀም ባህል እያደገ መምጣቱ በቡና ምርታማነትና በውጭ ምንዛሬ ግኝት ላይ ከፍተኛ ለውጥ አንዲመዘገብ ማስቻሉን ተናግረዋል።

በተለይም በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የሚተከሉ የቡና ችግኞች የዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ አቅም እየፈጠሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የቡና ምርታማነትን ለማሻሻል የተደረጉ የሪፎርም ሥራዎች ከወጪ ንግድ የሚገኘውን ገቢ በከፍተኛ መጠን ማሳደግ ማስቻላቸውን ገልጸዋል።

የለውጡ መንግስት በ2013 ዓ.ም የሪፎርም ሥራውን ሲጀመር ከቡና ወጪ ንግድ 907 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን አስታውሰው በ2014 ዓ.ም ደግሞ ገቢው ወደ አንድ ነጥብ አራት ቢሊየን ዶላር ማደጉን ጠቅሰዋል።

የሪፎርሙ ስኬታማ ጉዞ ለዘርፉ በፈጠረው መልካም ዕድል በመታገዝ  በ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት አምስት ወራት ከቡና ወጪ ንግድ አንድ ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን አስታውቀዋል።

ጥሬ ቡናን ብቻ ከመላክ ባለፈ ዕሴት የተጨመረበት የቡና ምርትን ለዓለም ገበያ ለማስተዋወቅ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡና ማኅበር ፕሬዝዳንት ሁሴን አምቦ(ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የአርሶ አደሩን ግንዛቤ በማሳደግና የተሻሻሉ የቡና ችግኞች እንዲሰራጩ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በ2018 በጀት ዓመት 600 ሺህ ቶን የቡና ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከሶስት ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ከባለሥልጣኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።