Ethiopian Coffee and Tea Authority
5.77K subscribers
5.52K photos
30 videos
66 files
358 links
Ethiopian Coffee and Tea Authority
Download Telegram
ምርታማነታቸው በምርምር የተረጋገጠ የቡና ዝርያዎች ለአልሚዎች ተላልፈዋል

አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 18/2018፡-

ሥነ-ምኅዳርን መሠረት በማድረግ ምርታማነታቸው በምርምር የተረጋገጠ ከ42 በላይ የቡና ዝርያዎች ለአልሚዎች መተላለፋቸውን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን አስታወቀ።

የቡናን ምርትና ምርታማነት ለመጨመር ከሚያስፈልጉ ቁልፍ ጉዳዮች አንዱ ምርጥ ዘርን መጠቀም መሆኑን ባለሥልጣኑ አስገንዝቧል።

በመረጣ እና በማዳቀል በጅማ ግብርና ምርምር ማዕከልና በሥሩ በሚገኙ ንዑስ የምርምር ማዕከላት አማካኝነት ሥነ-ምኅዳርን መሠረት ያደረጉ የቡና ዝርያዎች መለቀቃቸውን በባለሥልጣኑ የቡና፣ ሻይና ቅመማቅመም ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍቃዱ ደፈረስ ለኢዜአ ተናግረዋል።

በዚህም መሠረት ለደጋ አካባቢ ተስማሚ የሆኑ 14 የቡና ዝርያዎች መለቀቃቸውን ጠቁመው፤ ምርታማነታቸውም በምርምር ማሳ ላይ በሔክታር ከ12 ነጥብ 2 እስከ 24 ነጥብ 41 ኩንታል መሆኑን አስረድተዋል።

በተመሳሳይ ለወይና ደጋ አካባቢ ተስማሚ የሆኑ 16 የቡና ዝርያዎች መለቀቃቸውን የገለጹት አቶ ፍቃዱ፤ የእነዚህ ቡና ዝርያዎች ምርታማነት ከ14 ነጥብ 8 እስከ 24 ኩንታል በሔክታር መሆኑን ተናግረዋል።

እንዲሁም ለሞቃታማ (ዝቅተኛ) አካባቢ ተስማሚ የሆኑ 12 የቡና ዝርያዎች መለቀቃቸውን ጠቅሰው፤ ከ13 ነጥብ 2 እስከ 25 ነጥብ 4 ኩንታል በሔክታር ምርት እንደሚያስገኙ አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል አካባቢ በቀል የሆኑ ለወለጋ አካባቢዎች አራት፣ ለምዕራብ ሐረርጌ አራት፣ ለይርጋ ጨፌ ስድስት እና ለሊሙ አንድ የቡና ዝርያዎች መለቀቃቸውን ነው የተናገሩት።

የቡናን ምርታማነት በምርምር በማጎልበት ከዘርፉ የሚገኘውን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።
በምርምር በተገኘ ዝርያ የቡና ምርታማነትን በሄክታር 28 ኩንታል አድርሰናል - ንጉሴ ደቻሳ (ፕ/ር)

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 18፣ 2018
በምርምር በተገኘ ዝርያ የቡና ምርታማነትን በሄክታር 28 ኩንታል አድርሰናል አሉ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ንጉሴ ደቻሳ (ፕ/ር)።

በ2017 በጀት ዓመት በቡና ምርት ለመጀመሪያ ጊዜ ከ2 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ መመዝገቡ ይታወሳል።

ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በዘርፉ ከፍተኛ የሆነ እመርታዊ ለውጦች እየተመዘገበ በመምጣቱ ባለፈው በጀት ዓመት 470 ሺህ ቶን ቡና በመላክ ከ2 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል።

በዚህም የተመረጡ የዘር ዓይነቶችን ከመጠቀም ጀምሮ የቡና ጥራት እና ምርታማነትን የሚጨምሩ ስራዎች በቅንጅት በመሰራት ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ንጉሴ ደቻሳ (ፕ/ር) ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፤ የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን ለማፍለቅ በትኩረት በተሰራው ስራ አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል።

በሄክታር ሰባት ኩንታል ብቻ የነበረውን የቡና ምርታማነት በምርምር በፈለቀ ዝርያ 28 ኩንታል አድርሰናል ብለዋል።

ውጤቱ ሊመጣ የቻለው የቡና ዝርያዎችን በመለየት የተሻለ ምርት ሊሰጡ የሚችሉ ዝርያዎችን በማዳቀል እንደሆነም ተናግረዋል።

የዲቃላ ቡና ዝርያን ቆርጦ በመውሰድ (ቲሹካልቸር ቴክኖሎጂ) ብዙ ችግኞችን ለማዘጋጀት የሚያስችል ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የዲቃላ ዝርያን ከአንድ ጊዜ በላይ መጠቀም የማይቻል በመሆኑ ሁልጊዜ የዝርያ ማዘጋጀት ስራ እንደሚጠይቅ ጠቅሰው፤ ለዝርያ ማሻሻል በተሰጠው ትኩረት ችግኙን በብዛት በማዘጋጀት ለአርሶ አደሩን የማድረስ ስራ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
ምንጭ ኤፍ ኤም ሲ
የቻይና ገበያ ለኢትዮጵያ ቡና ያለው ፍላጎት እያደገ መምጣቱ  ለኢትዮጵያ ትልቅ እድል ነው-አዱኛ ደበላ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 19/2018(ኢዜአ)፦ የቻይና ገበያ ለኢትዮጵያ ቡና ያለው ፍላጎት እያደገ መምጣቱ  ለኢትዮጵያ ትልቅ እድል ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አዱኛ ደበላ  ገለጹ።

የኢትዮጵያን  ቡናን በቻይና ገበያ የበለጠ ለማስተዋወቅ እና ኤክስፖርቱን ለማሳደግ ያለመ ኮንፍረንስ በቻይና ሁናን ግዛት እየተካሄደ ነው።

ኮንፍረንሱ እያደገ የመጣውን የኢትዮጵያ እና ቻይና ጠንካራ ግንኙነት የሚያሳይ ሲሆን  ወዳጅነታቸው በሁኔታዎች የማይለዋወጥ ስትራቴጂክ አጋርነት(all-weather strategic partnership) ምዕራፍ መሸጋገሩም ተገልጿል።

ሁነቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካን ጥልቅ የኢኮኖሚ አቅም እንደሚያሳይ ተነግሯል።

ቻይና የኢትዮጵያ ቡና ዋና መዳረሻ እየሆነች የመጣች ሲሆን የዛሬ አምስት አመት የኢትዮጵያን ቡና በመግዛት ከነበረችበት 33ኛ ደረጃ በተያዘው አመት ወደ 4ኛ ደረጃ ከፍ ብላለች።

የቻይና ገበያ ለኢትዮጵያ ቡና ያለው ፍላጎት እያደገ መምጣቱ  ለኢትዮጵያ ትልቅ እድል መሆኑን  የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አዱኛ ደበላ በወቅቱ ገልጸዋል።

በቻይና የኢትዮጵያ  አምባሳደር ተፈራ ደርበው በበኩላቸው፥ እያደገ የመጣውን የሁለቱን ሃገራት ግንኙነት በማንሳት ቡናም አንድ አስተሳሳሪ  እየሆነ መምጣቱን አፅንኦት ሰጥተው ገልፀዋል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ኢፋ ሙለታ(ዶ/ር)  በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ በግብርና መስክ እያከናወነቻቸው ያሉ ተግባራትን በማንሳት በግብዓት፣ በውጤታማ የምርት አሰባሰብ፣ ክምችትና ሥርጭት መስኮች ተባብሮ ለመስራት ጥሪ አቅርበዋል።

የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ፣ቡና ለኢትዮጵያ ምርት ብቻ ሳይሆን ባህላዊ እሴትም መሆኑን በመግለፅ የሁለቱን ሃገራት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚያግዝ አንስተዋል።
ኮንፍረንሱ ቻይና በኢትዮጵያ ቡና ያላትን ተደራሽነት የበለጠ ለማሳደግና ወደ ቻይና የሚላከውን የቡና ኤክስፖርት መጠን ማሳደግ ያለመ መሆኑን ኢዜአ ከስፍራው ያገኘው ያመለክታል።
470 ቶን ቡና ወደ ማዕከላዊው ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

በበጀት ዓመቱ በወረዳው ከቅርብ ዓመታት በፊት የቡና ልማት ብዙም ያልተለመደና ከ600 ሄክታር ያልበለጠ የጫካ ቡና መኖሩን በማስታወስ አሁን በተሰጠው ትኩረት ከ10 ሺህ 400 ሄክታር በላይ ማሳ በቡና መሸፈኑን የጣሎ ወረዳ ግብርና ደን፣ አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አፈወርቅ አደመ ገልጸዋል።

በወረዳው አሁን በሁሉም ቀበሌዎች ማልማት የተጀመረ መሆኑን በመጥቀስ ከዚህ ውስጥ አራቱ ቡናን ስፔሻላይዝ በማድረግ የሚያመርቱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ቡናን በብዛትና በጥራት በማልማት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ በትኩረት እየተሰራ ነው ያሉት አቶ አፈወርቅ በበጀት ዓመቱ 5 ሺ ቶን ቡናን በማሰባሰብ 470 ቶን ቡና ወደ ማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ዕቅድ መያዙን ተናግረዋል።

ከዚህም ከ3400 ቶን በላይ ምርት አሁን መሰብሰቡንና 347 ቶን በላይ ቡና ደርቆ ወደ መጋዘን መግባቱን ጠቁመዋል።

ምርታማነት ማሻሻያ ፓኬጅን ከመጠቀም አንጻር ቡናን በክላስተር ማልማት፣ ለባለድርሻ አካላት ስልጠና መሰጠቱ፣ ከ155 ሄክታር በላይ ቡና መጎንደሉን፣ የኮምፖስት ዝግጅት እና ሌሎች ምርታማነትን የሚጨምሩ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በግብይት ሂደት ጥራትንና የዕዝ ሰንሠለትን ጠብቆ ወደ ገበያ ከማቅረብ አንጻር ህገወጥነትን የመከላከል፣ 4 አቅራቢ ነጋዴዎችን ማዘጋጀት፣ 2 እሸት ማጠቢያ ኢንዱስትሪ መቋቋሙ፣ የተሻለ የግብይት ማዕከል በወረዳው መታጠሩን አብራርተዋል።

በወረዳው በአርሶ አደሩ ማሳ ከሚለማው ቡና በተጨማሪ የግል አልሚና ማህበራት ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።

ዘርፉን ለማበረታታት ወረዳው ከሰጠው 116.8 ሄክታር ውስጥ በ2002 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ስራ በመግባት 96 ሄክታርን በማልማት ላይ ያለው የብ አግሮ ቡና ልማት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ነው።

ከተተከለው ውስጥ 63 ሄክታር አሁን ምርት እየሰጠ መሆኑን ያነሱት የማህበሩ ስራ አስኪያጅ፤ አቶ አስራት በቀለ ከማልማቱ ጎን ለጎን ምርታማነትን ለመጨመር 25 ሄክታር ጉንደላ ስራና 8 ሄክታር ነቅሎ ተከላ መደረጉን ገልጸዋል።

በያዝነው ዓመት 1398 ኩንታል ቀይ እሸት ቡና ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ ሲሆን ከዕቅዱ 130 በመቶ መሳካቱን ጨምረው ገልጸዋል። እስካሁን 937 ኩንታል ደርቆ ወደ መጋዘን መግባቱን ተናግረዋል።

የለማው ቡና ወደ አረብ ኢምሬትስ በመላኩ የተሻለ የገበያ ትስስር መፈጠሩንና ገቢ ማግኘቱን የገለጹት አቶ አስራት፤ 22 ቋሚና ከ300 እስከ 400 ለሚሆኑት ለአካባቢው ማህበረሰብ የስራ ዕድል እየተፈጠረላቸው መሆኑን ጨምረው አንስተዋል።

በመጨረሻም ድርጅቱ በዞኑ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች እርሻን ማስፋፋት ላይ እየሰራ መሆኑን አንስተው፤ መንግስት በቦንጋ ከተማ ቦታ ካመቻቸ ዘመናዊ የቡና ማበጠሪያ በማዘጋጀት ቡናውን ቀጥታ ኤክስፖርት ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ምንጭ፡ የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ