EBC (Ethiopian Broadcasting Corporation)
138K subscribers
31.8K photos
323 videos
79 files
12.3K links
EBC (Ethiopian Broadcasting Corporation) @etvafaanoromoo1
@ETVkidschannel
@EBCWORLD1
@etventertainment1
Download Telegram
በበዓል ወቅት ሊከሰቱ ከሚችሉ የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎችን ለመከላከል ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ
********************

በአዲስ አበበ ከተማ ከ2012 የዘመን መለወጫ በዓል ጋር ተያይዞ ሊነሱ የሚችሉ የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎችን ለመከላከል ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አሳሰበ፡፡

የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ስለሺ ተስፋዬ በተለይ ለኢቲቪ እንደገለጹት፣ በከተማዋ በበዓላት ዋዜማና በበዓላት እለት የሚነሱ የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት ሊያደርሱ ስለሚችሉ ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

በ2011 ዓ.ም 525 የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከሰታቸውን የገለጹት የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው፣ በአደጋው የ6 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ከ239 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሀብት ከጥቅም ውጭ ሆኗል፤ ከ80 በላይ ሰዎችም ከከፍተኛ እስከ ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል ነው ያሉት፡፡

ከ525 አደጋዎች ውስጥ 365ቱ የእሳት ቃጠሎ አደጋ ሲሆኑ በዚህም የደረሰው የሀብት ውድመት 200 ሚሊዮን ብር የሚገመት ነው ብለዋል ባለሙያው፡፡

በመሆኑም ህብረተሰቡ በዓሉን በሚያከብርበት ወቅት በመዝናኛ ስፍራም ሆነ በቤት ውስጥ የከሰል፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የጋዝ፤ የጧፍ፣ የካውያ አጠቃቀም ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ አየር ሃይል ለ735 አባላቱ የማእረግ እድገት ሰጠ

********

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ አየር ሃይል ለ735 አባላቱ የማእረግ እድገት የሰጠ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 10ሩ ከመስመር መኮኖንንነት ወደ ከፍተኛ መኮንንነት የማእረግ እድገት ያገኙ ናቸው፡፡

በተቋሙ ውስጥ ለ ረጅም አመታት ላገለገሉ እንዲሁም ሃገራቸውን እና ህዝባቸውን አገልግለው ጡረታ ለወጡ 56 የቀድሞ አባላቶቹም የእውቅና ሰርተፍኬት ሰጥቷል።

በአየር ሃይል ደረጃ በተለያዩ ስራዎች ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላስመዘገቡ የተለያዩ የስራ ክፍሎችም ማበረታቻ ሰርተፍኬት ተሰጥቷል።

ከዚህ በተጨማሪ የኢፌዲሪ አየር ሃይል ከመላው ሰራተኞች የሰበሰበውን 200 ሺህ ብር ለኢትዮጵያ ልብ ህሙማን መርጃ ማእከል ለግሷል።

ሪፖርተር፡- ኮሰን ብርሃኑ
የዘንድሮው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ነጥብ ይፋ ተደረገ

**************************

የዘንድሮው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ነጥብ በተፈጥሮ ሳይንስ ለወንዶች 176፣ ለሴቶች 166 እንዲሆን ተወስኗል፡፡ በማህበራዊ ሳይንስ ደግሞ ለወንዶች 174፣ ለሴቶች 164 እንዲሆን ተወስኗል፡፡

ለታዳጊ ክልሎች የመግቢያ ነጥቡ በተፈጥሮ ሳይንስ ለወንዶች 166፣ ለሴቶች 156፤ በማህበራዊ ሳይንስ ለወንዶች 164፣ ለሴቶች 154 እንዲሆን ተወስኗል፡፡

የግል ተፈታኞች መግቢያ ነጥብ በተፈጥሮ ሳይንስና በማህበራዊ ሳይንስ ለወንዶች 190 ፣ ለሴቶች ደግሞ 185 ሆኗል፡፡

ለአካል ጉዳተኞች ደግሞ መስማት ለተሳናቸው በተፈጥሮና በማህበራዊ ሳይንስ ለወንዶች 120፣ ለሴቶች 115፣ ለአይነ ስውራን በማህበራዊ ሳይንስ ለወንዶች 110፣ ለሴቶች 105 እንዲሆን መወሰኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

በአማረ ተመስገን
መከላከያ ሰራዊት የአይ ኤስ አባላትን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገለፀ

*****************************************************

የኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሰሞኑን የተወሰኑ የአይኤስ አባላትን በቁጥጥር ስር ማዋሉንና ያልተያዙትም በጥብቅ ክትትል ውስጥ መሆናቸውን የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹምና የዘመቻ መምሪያ ኃላፊ ጄኔራል ብርሀኑ ጁላ አስታወቁ፡፡ ሰራዊቱ በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ሀገርና ሕዝብን ከአደጋ ለመጠበቅ እየሰራ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

ጄኔራሉ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ልዩ ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት፤ አይ ኤስ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ለመንቀሳቀስ በተደጋጋሚ ጥረት አድርጎ ቢመክንበትም በአገሪቱ ከተለያዩ አካባቢዎች የመለመላቸው፣ ስልጠና የወሰዱና የታጠቁ ሰዎች እንዳሉ መንግስት በሚገባ እንደሚያውቅ ተናግረዋል፡፡

‹‹በአሁኑ ወቅት የአይኤስ አባላት ምን እያደረጉ እንዳሉ፣ የት የት ቦታ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኙ፣ ከእነማን ጋር ግንኙነት እንዳላቸው፣ በከተሞች ውስጥ ያሉት ሰዎቻቸው እነማን እንደሆኑ፣ ምን እየሰሩ እንዳሉ፣ እቅዳቸው ምን እንደሆነና ሌሎች መግለጽ የማያስፈልጉ ጉዳዮችም እጅግ ከፍተኛ ክትትል እየተደረገባቸው ነው›› ብለዋል ጄኔራሉ ፡፡

ምንጭ፡- የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት
ዛሬ በመላ አገሪቱ የብሔራዊ አንድነት ቀን ሆኖ ይውላል

*******************

ዛሬ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ የብሔራዊ አንድነት ቀን በመላ አገሪቱ ተከብሮ ይውላል፡፡

ዛሬን ጨምሮ ስድስቱ የጳጉሜ ቀናት በተለያዩ መሪ ቃላት እየተከበሩ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

ያለፉት አምስት ቀናትም የብልፅግና፣ የሰላም፣ የሀገራዊ ኩራት፣ የዴሞክራሲ እና የፍትሕ ቀን በሚል መከበራቸው የሚታወስ ነው፡፡
አዲሱን ዓመት አስመልክቶ ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐቢይ መልእክት አስተላልፈዋል

***********

አዲሱን 2012 ዓመት አስመልክቶ ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በመላው ዓለም ለምትገኙ ኢትዮጵያውያን በሙሉ መልካም አዲስ ዓመት እንዲሆን ተመኝተዋል::

አዲሱ ዘመን 2012 ለሀገራችን ሰላምና ብልጽግና በጋራ የምንተጋበት እንዲሆንም ነው መልእክታቸውን በትዊተር ገፃቸው ያስተላለፉት::
በሌላ ፕላኔት ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ውሃ ተገኘ

***********

የሥነ ህዋ ተመራማሪዎች በአንዲት ፕላኔት ላይ ውሃ ለመጀመሪያ ጊዜ ማግኘታቸውን ይፋ አድርገዋል።

ግኝቱን በበላይነት የመሩት ተመራማሪ ፕሮፌሰር ጂኦቫንያ ቲኔቲ፤ K2-18b የተባለችው ፕላኔት ላይ ውሃ የመታየቱን ዜና "እጅግ ድንቅ" ብለውታል።

"በፕላኔት ላይ ውሃ ስናገኝ ይህ የመጀመሪያው ነው። ሙቀቱም የሰው ልጅ ሊኖርበት ከሚችለው የሙቀት መጠን ጋር የሚመጣጠን ነው" ብለዋል።

K2-18b የተባለው ፕላኔት ከመሬት 650 ሚሊየን ማይል ይርቃል።

ከመሬት ሥርዓተ ጸሐይ ውጪ ያሉ ፕላኔቶች ኤክሶፕላኔት ይባላሉ።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2020 ይሠራል ተብሎ በሚጠበቅ ቴሌስኮፕ፤ ፕላኔቷ ላይ ሕይወት ባላቸው ነገሮች የሚወጣ አየር ስለመኖሩ እንደሚፈተሽ ተመራማሪዎች ገልጸዋል።

"በህዋ ውስጥ ያለነው የሰው ልጆች ብቻ ነን? የሚለው በሳይንስ ውስጥ ካሉ ጥያቄዎች ዋነኛው ነው" ሲሉ ፕሮፌሰር ጂኦቫንያ ተናግረዋል።

የምርምር ቡድኑ ግኝቱ ላይ የደረሰው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ2016 እስከ 2017 በሚገኙት ወራት በተደረገ ጥናት ነው። ከK2-18b ክፍል 50 በመቶው በውሀ የተሸፈነ እንደሆነ የሚታመን ሲሆን፤ ምናልባትም ለሰው ልጆች ምቹ መኖሪያ ልትሆን እንደምትችል መላ ምቶች አሉ።

ፕላኔቷ ከመሬት ሁለት እጥፍ የምትበልጥም ናት ተብሏል።

ምንጭ፡- ቢቢሲ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመንግስት ትምህርት ቤቶች ለሚማሩ ተማሪዎች የትምህርት መማሪያ ቁሳቁስ እና የደንብ ልብስ ማደል ጀመረ
***************************

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2012 አዲስ የትምህርት ዘመን ትምህርታቸው ለሚከታተሉት ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ፣ የትምህርት ቤት የደንብ ልብስ (ዩኒፎርም) ማደል ጀምሯል፡፡

ለተማሪዎቹ በጎ ፍቃድ ባለሐብቶች እንዲሁም በከተማው በሚገኙ ተቋማት የመማሪያ ቁሳቁስ ገዝተው ድጋፍ ማድረገቸውን የአዲስ አበባ የከንቲባ ፅ/ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪ ወ/ሪት ፌቨን ተሾመ በተለይ ለኢቲቪ ተናግረዋል።

ዕቅዱ ለ600,000 ተማሪዎች ደብተር በነፃ ማቅረብ የነበረ ሲሆን፣ ከዛ በላይ የሆነ የመማሪያ ቁሳቁስ መለገሱ ተገልጿል፡፡

የተማሪዎች ደንብ ልብስ (ዩኒፎርም) በአዲስ መልክ በፋሽን ዲዛይነሮች የተሰራ ሲሆን፣ ለውድድር እና ዕይታ ምርጫ የተማሪዎች ተወካዮች፣ መምህራን፣ ቤተሰቦች እና ታዋቂ የሥና ልቦና ምሁራን በተገኙበት ምርጫ እንደተደረገ ተነግሯል።

የደንብ ልብሱን የከተማ አስተዳደሩ በራሱ ወጪ ነው ማሰረቱንና የስፌት ስራው በአሁኑ ወቅት ሙሉ ለሙሉ መጠናቀቁን ወ/ሪት ፌቨን ገልጸዋል፡፡

በገንዘብ ሲተመን ወደ 80 ሚለዮን ብር በላይ የሚሆን የትምህርት መርጃ ቁሳቁሶች ከተቋማት እና ከባለሀብቶች መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት የመማሪያ ቁሳቁስ ሆነ ዩኒፎርሙ ወደ ክፍለ ከተማ የማሰራጨት ስራ እየተሰራ ነው፤ ክፍለ ከተሞች ከአዲስ አመት በኋላ ወደ ትምህርት ቤቶች እና ተማሪዎች ጋር የማድረስ ስራ ያከናውናሉ ሲሉ ኃላፊዋ ተነናግረዋል።

በዘንድሮ የትምህርት ዘመን ማንኛውም በመንግስት ትምህርት ቤቶች የሚከታተል ተማሪ የደብተር፣ የዩኒፎርም እና ሌሎች የትምህርት መማሪያ ቁሶች ወጪ አይኖርበትም ተብሏል።
ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ካርቱም ገቡ

************

የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ሃላፊ ሌተናል ጀኔራል አብድል ፋታ አል ቡርሃን ባቀረቡላቸው ግብዣ መሰረት በፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሚመራ የኤርትራ ልኡካን ቡድን ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ዛሬ ጠዋት ሱዳን ገብቷል።

ፕትሬዝዳንት ኢሳያስ በቆይታቸው የሀገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች እንዲሁም ባለፉት አመታት የነበረውን መልካም ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ፕሬዚዳንቱ ለሁለት ቀናት የስራ ጉብኝት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው እና የደህንነት አማካሪያቸው ጋር በዛሬው ዕለት ሱዳን ካርቱም ገብተዋል።

የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ሃላፊ ሌተናል ጀኔራል አብድል ፋታ አል ቡርሃን በቅርቡ በኤርትራ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።

ምንጭ፦ የሱዳን የዜና ኤጀንሲ
27 ሚሊዮን ብር የሚገመት አደንዛዥ ዕፅ ወደ አገር ውስጥ ሊገባ ሲል ተያዘ

**************************

የገቢዎች ሚኒስቴርና የጉምሩክ ኮሚሽን በቦሌ አለም አቀፍ አየርመንገድ በኩል ወደ አገር ሊገባ የነበረ 27 ሚሊዮን ብር የሚገመት 10.8 ኪ.ግ የሚመዝን አደንዛዥ ዕፅ በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል።

የጉምሩክ ተቆጣጣሪዎች ባደረጉት ክትትል በቁጥጥር ስር ያዋሉት ሄሮይን እና ኮኬን የተባሉ አደንዛዥ እፆችን ነው፡፡

አደንዛዥ እፆቹን አንድ ናይጄሪያዊ ዜጋ በያዘው ቀላል ሻንጣ ውስጥ ደብቆ ለማለፍ ሲሞክር በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተደረገበት እንደሚገኝ የቦሌ ኤርፖርት ጉምሩክ ቅ/ፅ/ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ተገኔ ደረሰ በተለይ ለኢቢሲ ገልፀዋል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ህገ ወጥ ንግድን ለመከላከል እየሰራው ባለው ስራ የተለያዩ የኮንትሮባንድ እቃዎች በመያዝ ላይ ይገኛሉ።

በናትናኤል ፀጋዬ
ባለስልጣኑ 17 የምግብ ዘይት ምርት አይነቶችን ህብረተሰቡ እንዳይጠቀማቸው አሳሰበ
የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን በአዲስ አበባና ሌሎች አካባቢዎች ባደረገው የገበያ ጥናት በ17 የምግብ ዘይት ምርቶች ላይ መሰረታዊ ችግር ስላለባቸው ህብረተሰቡ እንዳይጠቀማቸው አሳስቧል፡፡ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ባደረገው የገበያ ጥናት የዘይት ምርቶቹ የሚመረቱበት ቦታና የተመረተበት ሃገር፣ የምርት መለያ ቁጥር፣ የአምራች አድራሻ የሌላቸው፣ የገላጭ ጽሁፍ ችግርና ለጤና ጠቀሜታ እንዳለው ተደርጎ የተቀመጠ፣ የመጠቀሚያ ጊዜና ማብቂያ ቀን የሌላቸው እንዲሁም የሀገሪቱን የደረጃ ምልክት ያለጠፉና ደረጃውንም የማያሟሉ መሆናቸው በተደረገው ጥናት መረጋገጥ መቻሉን ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ አስታውቋል፡፡ ህብረተሰቡ የትኛውም የምግብ ምርት ከገበያ ሲገዛ የተመረተበትና የመጠቀሚያ የአገልግሎት ጊዜው ትክክለኛነት፣ ያልተፋቀና ያልተሰረዘ መሆኑን፤ የአምረች ድርጅቱ ስምና ሙሉ አድረሻ፣ የምርት መለያ ቁጥር ያለው መሆኑን በማረጋገጥ እንዲገዛ የተጠየቀ ሲሆን፤ የምርት ገላጭ ጹሁፍ ይዘቶች ያላሟላ ምርት ህብተሰቡ መግዛት እንደሌለበት ተገልጿል፡፡ በገበያ ጥናቱ ችግር የተገኘባቸው የምግብ ዘይቶች ዝርዝር 1. ሉሉ ዘይት 2. አርሲ ዘይት 3. አሃዱ ዘይት 4. ድሬ ንጹህ የምግብ ዘይት 5. አሚን ንጹህ የምግብ ዘይት 6. ሮያል የምግብ ዘይት 7. ዳግም የተጣራ የኑግ ዘይት 8. ጄጃን የምግብ ዘይት 9. ዉብ የተጣራ የኑግ ዘይት 10. ለማ የኑግ ዘይት 11. ኑድ ንጹህ የምግብ ዘይት 12. ገበታ የምግብ ዘይት 13. ዘመን ዘይት 14. አጋር ዘይት 15. አናጅና ዘይት 16. ሳባ ዘይት 17. ጃሎ ዘይት ናቸው፡፡