የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ /Addis Ababa Diocese Media
5.52K subscribers
8.52K photos
22 videos
23 files
1.08K links
አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ
Download Telegram
የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የብፁዓን አባቶች የሀገረ ስብከት ዝውውር መደባ ላይ ውሳኔ አሳለፈ።

ግንቦት ፳፬/፳፻፲፮ ዓ/ም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ

ርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የብፁዓን አባቶች የሀገረ ስብከት ዝውውር መደባ ላይ ውሳኔ አሳለፈ።

የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ለኢኦተቤ ቴቪ (#EOTCTV) በላከው መረጃ ጉባኤው ከግቦት 21 ቀን 2016 ዓም ጀምሮ ባካሄደው ስብሰባ በበርካታ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን፡- በ4ኛ ቀን ውሎው የብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትንና የጳጳሳትን ዝውውር ላይ ውሣኔ ማሳለፉን ገልጽዋል፡፡
በዚህም መሠረት፡-
1. ብፁዕ አቡነ አብርሃም፣ ከምዕራብ ካናዳ ሀገረ ስብከት ወደ ኤድመንተንና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣

2. ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ፣ ከኢትዮ ሶማሌ ሀገረ ስብከት ወደ የምዕራብ ካናዳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣

3. ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ ዳውሮ ኮንታ ሀገረ ስብከትን እንደያዙ የከንባታ አላባ ጠምባሮ ሀገረ ስብከትን ፣

4. ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ፣ ከምሥራቅ ወለጋ ሀገረ ስብከት ወደ የኢትዮ ሶማሌ ጅግጅጋ ሀገረ ስብከት ጳጳስ፣

5. ብፁዕ አቡነ ዳንኤል፣ ከምዕራብ ወለጋ ሀገረ ስብከት ወደ የአፋር ሀገረ ስብከት ጳጳስ፣

6. ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ፣ ከሆሮ ጉድሩ ወለጋ ሀገረ ስብከት ወደ የምሥራቅ ጉራጌ ሀገረ ስብከት ጳጳስ፣

7. ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል፣ ሌሎች አህጉረ ስብከታቸውን እንደያዙ የምሥራቅ ወለጋ ፣ የምዕራብ ወለጋ እና የሆሮ ጉድሩ ወለጋ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ሆነው እንዲያገለግሉ መመደባቸውን የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ለኢኦተቤ ቴቪ በላከው መረጃ ገልጽዋል።
©EOTC TV

#ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን
በአማን ተንሥአ እሙታን

#የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ
#ማስታወቂያ
ልዩ የአንድነት መንፈሳዊ ጉባኤ በጀሞ አንድ ደብረ መዊዕ ቅዱስ አማኑኤልና ቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን።

🎚🎚🎚🎚🎚🎚🎚🎚🎚🎚🎚🎚

“ከሰማችሁትም ከወንጌል ተስፋ ሳትናወጡ፥ በሃይማኖት ጸንታችሁ ብትኖሩ ይሆናል።”
ቆላስይስ ፩፥፳፫

በብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ መሪነት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት አዘጋጅነት የተሰናዳው ይህ የገዳማትና የአድባራት የአንድነት ጉባኤ ከሰኔ 1-2/2016 ዓ/ም ከቀኑ 10፡00 ጀምሮ በጀሞ ደብረ መዊዕ ቅዱስ አማኑኤልና ቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን ይካሄዳል፡፡

በዚህ የወንጌል ጉባኤ ላይ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የሀገረ ስብከቱና የክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት ከፍተኛ የሥራ ሐላፊዎች ፣ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣የዘመኑ የቅዱስ ወንጌል ባላደራዎች ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ሰባኪያነ ወንጌል ፣ በምስጋናው የሚሰላፉ መዘምራን፣ ዘወትር ቃሉን ለመስማት ልባቸው የተደላደለላቸው ኦርቶዶክሳውያን ይገኙበታል፡፡

እርስዎም
#ከሰማያዊው ተስፋ
#ከማያልቀው የሕይወት በረከት ይካፈሉ ዘንድ በክርስቶስ ፍቅር ተጋብዘዋል፡፡

ጥሪዋ ቤተ ክርስቲያን
ጥሪው ለዘለዓለም ሕይውት ነውና አይቀርም፡፡

“ኑ በሰማያዊው ማዕድ አንድ እንሁን”

“ይህም፥ ተመሥርታችሁና ተደላድላችሁ ከሰማችሁትም ከወንጌል ተስፋ ሳትናወጡ፥ በሃይማኖት ጸንታችሁ ብትኖሩ ይሆናል፤ ያም ወንጌል ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ የተሰበከ ነው፥ እኔም ጳውሎስ የእርሱ አገልጋይ ሆንሁ።”
— ቆላስይስ 1፥23

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት
የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት
#ደብረ ገሊላ ቅዱስ አማኑኤል ካቴድራል

ግንቦት ፳፯/፳፻፲፮ ዓ/ም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ከሚገኙትና ከ100 ዓመታት በላይ የምሥረታ ታሪክ ካላቸው ገዳማትና አድባራት መካከል አንዱ የመሳለሚያ ደብረ ገሊላ ቅዱስ አማኑኤል ካቴድራል ነው።

ካቴድራሉ የተተከለው በ1905 ዓ.ም በልጅ ኢያሱ ዘመነ መንግሥት ሲሆን ከመቃኞ ጀምሮ በተለያየ ቅርጽ ቤተ ክርስቲያኑ ተገንብቶ አገለግሎት እንደተሰጠበት ታሪኩ ያስረዳል።

ከፊታ አውታሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ እስከ ንግሥት ዘውዲቱ ፤ ከንቡረ ዕድ አባ ተፈራ መልሴ እስከ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ፓትርያርክ ድረስ ያካተተ በካቴድራሉ የታሪክ መቃን ላይ የተጻፉ ባለታሪኮችን የሚያስታውስ ካቴድራል ነው።

የደብረ ገሊላ ቅዱስ አማኑኤል ቤተ ክርስቲያንን የመጀመሪያውን መቃኞ ያሠሩት ፊት አውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ሲሆኑ ጽላቱም በጎንደር ክፍለ ሀገር የነበረና ከዚያ መጥቶም በቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን የተቀመጠ ነበር።ታድያ ፊት አውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ያሰሩት የመጀመርያው መቃኞ ለአገልግሎት ምቹ ስላልነበር ሁለተኛ መቃኞ ድጋሚ ተሠርቶ ታቦቱ እንዲገባ ተደረገ።

ንግሥት ዘውዲቱ በግንቦት 28 በ 1914 ዓ.ም የቅዱስ አማኑኤልን በዓል ተገኝተው ሲያስቀድሱ ምርጊቱ ተደርምሶ ሲወድቅ በማየታቸው ሦስተኛ መቃኞ እንዲሰራ አዘዙ። የደብሩ አስተዳዳሪም በጊዜው የተክለ ሃይማኖትን ቤተ ክርስትያንም አንድ ላይ ያስተዳድሩ ስለነበር ንግስቲቷ የቤተ መንግስታቸውን አጣኝ የመጀመርያው አስተዳዳሪ ሆነው ደብሩን እንዲጠብቁ አደረጉ። አለቃውም ሦስተኛ መቃኞ አሠርተው ታቦቱ ወደ ተዘጋጀለት መቃኞ ገባ።

ሕዝቡ እየበዛ መጣ። አገልግሎቱ መስፋት ኖረበት። ስለዚህም በንግሥት ዘውዲቱ አማካኝነት በ1920 አዲስ ሕንጻ ቤተ መቅደስ ግንባታ ተጀመረ። በ1931 ታህሳስ 28 ቀንም ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ታቦቱ ወደ መንበሩ ገብቷል። ንግስት ዘውዲቱ ፍጻሜውን ሳያዩ ያረፉ ሲሆን ቤተ መቅደሱ ደግሞ ክብ ቅርጽ ነበረው።

አሁን ያለው ቤተ ክርስቲያን በጥር 28 ቀን 1969 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የመሠረት ድንጋይ ተጥሎ ግንባታው የተጀመረ ሲሆን የወቅቱ የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ በነበሩት በሊቀ ሊቃውንት ንቡረ ዕድ አባ ተፈራ መልሴ አስተባባሪነት በምእመናን ርብርብና በቅዱስ አማኑኤል ሁሉን አከናዋኝነት ግንቦት 28 ቀን 1978 ዓ.ም ተጠናቆ ታቦተ ሕጉ ወደ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ገብቷል።

ምንጭ፦ የካቴድራሉ እግዚአብሔር ምስሌነ ሰንበት ትምህረት ቤት
እንኳን አደረሰን

#ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን
በአማን ተንሥአ እሙታን

#የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ "የአንድነት ገዳማት ኅብረት ረቂቅ መተዳደሪያ ደንብ" በቋሚ ሲኖዶስ ተመርምሮ በሥራ ላይ እንዲውል ወሳኔ አሳለፈ።

ግንቦት ፳፰/፳፻፲፮ ዓ/ም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ"የአንድነት ገዳማት ኅብረት መተዳደሪያ ደንብ" በቋሚ ሲኖዶስ ተመርምሮ በሥራ ላይ እንዲውል ወሳኔ አሳለፈ።

የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ተዘጋጅቶ በቀረበው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አንድነት ገዳም ኅብረት ረቂት መተዳደሪያ ደንብ ላይ ተነጋግሮ ውሳኔ ሰጥቷል።

የአንድነት ገዳማት ኅብረት ረቂቅ መተዳደሪያ ደንቡ በ22 አንቀጽ፣ በ3 ክፍልና በ14 ገጽ ተዘጋጅቶ የቀረበ መሆኑም ተብራርቷል።

ረቂቅ መተዳደሪያ ደንቡ ከሕገ ቤተ ክርስቲያንና ከዚህ በፊት በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ ከወጣው የአንድነት ገዳማት መተዳደሪያ ደንብ ጋር በማገናዘብ ሊስተካከሉ የሚገባቸው አንቀጾች ተስተካክለው በቋሚ ሲኖዶስ ታይቶና ተመርምሮ ከጸደቀ በኋላ ሥራ ላይ እንዲውል ይደረግ በማለት ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል። ዘገባው የኢኦተቤ ቴቪ ነው።

#ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን
በአማን ተንሥአ እሙታን

#የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ
የተሻሻለው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት መዋቅራዊ አደረጃጀት ጸደቀ።

ግንቦት ፳፰/፳፻፲፮ ዓ/ም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ በተለያዩ አጀንዳዎች ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

ከነዚህ የዐሥር ዓመታት የመሪ ዕቅድ ትግበራ ለማፋጠንና ውጤታማ ለማድረግ ያስችላል የተባለው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት መዋቅራዊ አደረጃጀት በቀረበው መሠረት ጸድቆ ሥራ ላይ እንዲውል ወስኗል።

በተሻሻለው መዋቅር የሚጨመሩ አዳዲስ የሥራ ክፍሎች እንዳሉት የጠቆመ ሲሆን በትግበራው የሚያጋጥሙ ችግሮች ካሉም እየታዩ በጥናት እንደሚስተካከሉ ተገልጿል።

የጸደቀ መዋቅር ከሀገረ ስብከት እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ባለው የአስተዳዳር መወቅር በምን መልኩ ተግባራዊ እንደሚሆን eotc tv በዘገባው ያለው ነገር የለም። የዘገባው ምንጭ eotc tv ነው።

#ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን
በአማን ተነገረ ሥአ እሙታን

#የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በ"ኦሲኤን ቴሌቭዥን" ጉዳይ ውሣኔ አሳለፈ።

ግንቦት ፳፰/፳፻፲፮ ዓ/ም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ

በግንቦቱ የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የኦሲኤን ቴሌቪዥን ዝርዝር ጉዳዩ ተጣርቶ የመጨረሻ ውሳኔ እስከሚሰጥበት ድረስ ሚዲያውን በጊዜያዊነት የሚመራ ሐላፊ በቋሚ ሲኖዶስ ተጠንቶ እንዲመደብ ውሳኔ አሳልፏል።

ከጉዳዩ አሳሳቢነት አንጻር ተገቢው ጥናት ሳይደረግ መወስን ስለማይችል 5 አባላት ያሉት ኮሚቴ በመመደብ ኮሚቴዎቹም ዝርዝር ጉዳዩን አጥንተው እና የሚዲያው መሥራች በምልዓተ ጉባኤው ፊት በአካል ቀርበው ንብረትነቱ የቤተ ክርስቲያኒቱ እንዲሆን በገቡት ቃል መሠረት ስመ ሀብቱ ወደ ቤተ ክርስቲያኒቱ እንዴት መዞር እንደሚችል አጠቃላይ የሚዲያውን አስተዳደር ምን መሆን እንዳለበት ከሁለት ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ አጣርተው እንዲያቀርቡ ጉባኤው ወስኗል።

ቅዱስ ሲኖዶስ ኦሴኤን ቴሌቭዥን ለአስተዳደርና ለቁጥጥር ያመች ዘንድ አሁን ካለበት ቦታ ወጥቶ ወደ ዋናው መ/ቤት ግቢ መጥቶ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በሚያዘጋጅለት ቦታ ሥራውን እንዲቀጥል ይደረግ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ከዚህ ቀደም በኦሲኤን ቴላቪዥን ጉዳይ ላይ #ጥቅምት 17/2014 ዓ/ም ባካሔደው ምልዓተ ጉባኤ ከዚህ የሚከተለውን ውሳኔ ማሳለፉን የወቅቱ የeotc tv ዘገባ ያመለክታል።

"ኦሲኤን በሚል ስያሜ የሚጠራውና በኦሮምኛ ቋንቋ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘውን ሚዲያ አስመልክቶ የቀረበለትን ጉዳይ የተመለከተው ምልዓተ ጉባኤው ፣ የቦታና የበጀት እንዲሁም ሌሎች የአሠራር ጉዳዮች በሚመለከተው አካል ጥናቱ ተጠንቶ እንዲቀርብ የወሰነ ሲሆን ፣ ተቋሙ በአንድ መገናኛ ብዙኀን ሊቀ ጳጳስና ቦርድ እንዲመራም መወሰኑን የወቅቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ገልጸዋል።"

ቅዱስ ሲኖዶስ ከሁለት ዓመታት በፊት ውሳኔ ከላይ ባለው መልኩ ውሳን ያሳልፍ እንጂ በተጨባጭ እስካሁን ድረስ ለምን በውሳኔው መሠረት ሳይተገበር የቆየ? የሚለውን ጥያቄ የሚመልስ ማብራሪያ በዘገባው አልተካተተም።

የዘገባው ምንጭ eotc tv ነው።

#ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን
በአማን ተንሥአ እሙታን

#የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ
ከቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ፡፡

በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በቅዱሳን አበው ሐዋርያት ትውፊት በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቁጥር 164 በተደነገገው መሠረት ምልዓተ ጉባኤው የርክበ ካህናት መደበኛ ስብሰባውን ከግንቦት 21 እስከ ግንቦት 28 ቀን 2016 ዓ/ም ድረስ በርካታ አጀንዳዎችን በመቅረጽ ውይይት ሲያካሄድ ሰንብቷል፡፡

ምልዓተ ጉባኤው ለቤተ ክርስቲያናችን አንድነት፣ ለሐዋርያዊ ተልእኮ መስፋፋት፣ ለመንፈሳዊ ዕድገትና ለምእመናን ደኅንነት ትኩረት በመስጠት ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን ጠቃሚ የሆኑ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡

በዚሁ መሠረት፡-

፩.በቅድስት ቤተ ክርስቲያንና በሀገራችን መንግሥት መካከል ሊኖር ስለሚገባው መልካም የሥራ ግንኙነት በቅዱስ ፓትርያርኩ መሪነት ከመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር የሚመካከር የብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ልዑክ ቅዱስ ሲኖዶስ ሰይሟል፤

፪.በመላው ሀገራችን በተፈጠሩ ግጭቶች፣ አለመግባባቶችና የሰላም ዕጦት በርካታ የሰው ሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት እንደቀጠለ መሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስን በእጅጉ አሳዝኗል፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉም ባለድርሻ አካላት ከግጭትና ከጥፋት ድርጊት ተቆጥበው የተፈጠረውን አለመግባባትና ግጭት በውይይትና በምክክር እንዲፈቱ እና ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንኦት ጥሪውን ያቀርባል፤

፫.በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እየተከናወነ ባለው የኮሪደር ልማት ምክንያት ለፈረሱ የቤተ ክርስቲያናችን ይዞታዎች የከተማ አስተዳደሩ ምትክ ቦታ በመስጠትና ቤተ ክርስቲያናችን ወደ መልሶ ማልማት እንድትገባ ድጋፍ በማድረግ፤ በተለይም ክብርት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አበቤ በፈረሰው የጽርሐ ምኒልክ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕንፃ ምትክ በከተማ አስተዳደሩ ሙሉ ወጭ ተጨማሪ ምድር ቤትና የቦታ ስፋት ያለው B+G+4 ሕንፃ ገንብቶ ለማስረከብ ቃል በመግባትና የቤተ ክርስቲያናችን የበላይ ኃላፊ አባቶች በተገኙበት የመሠረት ድንጋይ እንዲጣል ማድርጋቸውን ቅዱስ ሲኖዶስ ከምስጋና ጋር የተቀበለው ሲሆን በተሰጠን ምትክ ቦታ ላይም የከተማው ፕላን በሚፈቅደው መሠረት የመልሶ ማልማት ሥራው እንዲከናወን ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

፬.የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተቋቋመበት አዋጅ መረዳት እንደሚቻለው ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ ሁኔታ ሀገራዊ ችግሮችን በምክክርና በውይይት ለመፍታት የተቋቋመ መሆኑን ተረድተናል፡፡ ይሁን እንጅ ሀገረ መንግሥትን ከመመሥረት ጀምሮ በአስታራቂነትና በሰላም ግንባታ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ለሆነችው እናት ቤተ ክርስቲያን እስከአሁን ድረስ በይፋ የቀረበ የተሳትፎ ጥሪ ሳይኖር ኮሚሽኑ የተሳታፊ ልየታንና አጀንዳ መረጣ አጠናቆ ወደ ምክክር ትግበራ እየገባ መሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስን ቅር አሰኝቷል፡፡ በመሆኑም የቤተ ክርስቲያኒቱ ተሳትፎና አጀንዳ የማቅረብ መብቷ እንዲረጋገጥ ከኮሚሽኑ ጋር በመነጋገር ጉዳዩን ተከታትሎ ለፍጻሜ የሚያበቃ ኮሚቴ ቅዱስ ሲኖዶስ ሰይሟል፡፡

፭.የብፁዓን አባቶች የዝውውርና የአህጉረ ስብከት ሥያሜን አስምልክቶ የቀረቡ ጥያቄዎችን ምልዐተ ጉበኤው ተመልክቶ ተገቢውን ውሳኔ አሳልፏል፤

፮.የሃይማኖት ጉዳዮች ረቂቅ አዋጅ ላይ ቅዱስ ሲኖዶስ በሰፊው ከተወያየ በኋላ በረቂቅ አዋጁ ሊሻሻሉ ይገባቸዋል ብሎ ያመነባቸውን የማሻሻያ ሐሳቦች በማዘጋጀት ለሚመለከተው መንግሥታዊ ተቋም እንዲላክና ረቂቅ አዋጁ ከመጽደቁ በፊት የተሰጡት የማሻሻያ ሐሳቦች በረቂቁ ስለመካተታቸው ክትትል የሚያደርግ ኮሚቴ ቅዱስ ሲኖዶስ ሰይሟል፡፡

፯.በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ ተመሥርቶ አባታዊ ምክርና ተግሣጽ ማስተላለፍ ከቀድሞ ጀምሮ የነበረ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው መሆኑ ቢታወቅም በሀገራችን ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተፈጠሩ አለመግባባቶች የተከሰቱትን ወቅታዊ ችግሮች አስመልክቶ እየተላለፉ ያሉ ቤተ ክርስቲያንን የማይወክሉ መልእክቶችን ቅዱስ ሲኖዶስ የማይቀበላቸውና በጥብቅ የሚቃወማቸው መሆኑን እየገለጸ ወደፊት እንዲህ ዓይነት ተመሳሳይ ድርጊት እንዳይፈጸም ለማድረግ ይቻል ዘንድ ወጥ የሆነ የመግለጫ አሰጣጥና የትምህርተ ወንጌል ተልእኮ ሕገ ደንብ ተዘጋጅቶ ለምልዐተ ጉበኤ እንዲቀርብ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፤

፰.ግብረ ሰዶማዊነትና የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ በሕገ ተፈጥሮም ሆነ በሰው ልጅ የሰብዓዊ አኗኗር ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው፣ ፈጣሬ ዓለማት እግዚአብሔር መለኮታዊ ፈቃዱ በተገለጠባቸው ቅዱሳት መጻሕፍት ፈጽሞ የተከለከለ፣ በቀኖናተ ቤተ ክርስቲያን፣ በፍትሕ መንፈሳዊና በፍትሐ ብሔር ድንጋጌዎች፣ በሥነ ልቦና ደንቦች የተወገዘ፣ ሥነ አእምሮዊ ሚዛንን የሚያዛባ፣ ግለሰባዊ ማንነትን፣ ቤተሰባዊ ሕይወትን፣ ማኅበራዊ ትሥሥርን የሚጎዳ ተግባር በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ እያወገዘ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻና የግብረ ሰዶማዊነትን ኃጢአት በተመለከተ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አቋም በሚገልጽ መልኩ ራሱን ችሎ ዓለም አቀፋዊ ይዘቱን ባገናዘበ ሁኔታ ዝርዝር መግለጫ እንዲሰጥ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፤

፱.በደቡብ የሀገራችን ክፍል የቤተ ክርስቲያኒቱን አብነት ትምህርት ከማስፋፋትና ከፍ ያለ መዐርግ ከመስጠት አንፃር የጋሞና አካባቢው ዞኖች ሀገረ ስብከት የዝጊቲ ደብረ ሰላም አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን የአራቱ ጉባኤያት ማስመስከሪያ ትምህርት ቤት እንዲሆን በቀረበው ጥናት መሠረት ቅዱስ ሲኖዶስ ለምሥክር ጉባኤ ቤቱ ዕውቅና በመስጠት ወደ ትግበራ እንዲገባ ወስኗል፡፡

፲.ከሀገራችን ውጭ ባሉ አህጉረ ሰብከት መደበኛ አገልግሎት ለመስጠት የሚላኩ አገልጋዮች በክፍሉ ሊቀጳጳስ ሲጠየቅ በሙያ ብቃታቸው፣ በምግባራቸውና በመንፈሳዊነታቸው የተመሰከረላቸው አገልጋዮች ከሁሉም አህጉረ ስብከት በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አቅራቢነት በውድድር እየተለዩ በቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ እንዲላኩ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

፲፩.የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ዘመኑን የዋጀ እንዲሆን ቅዱስ ሲኖዶስ የዐሥር ዓመት መሪ ዕቅድ በማጽደቅ ወደ ትግበራ እንዲገባ መወሰኑ ይታወሳል፡፡ በዚሁም መሠረት ለአፈጻጸሙ ያመች ዘንድ በባለሙያዎች ተዘጋጅቶ የቀረበውን መዋቅራዊ አደረጃጀት በማጽደቅ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑና በቃለ ዓዋዲው ተካቶ ሥራ ላይ እንዲውል ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

፲፪.በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ተዘጋጅቶ የቀረበውን የ2017 ዓ.ም. ዓመታዊ በጀት በማጽደቅ በሥራ ላይ እንዲውል ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

በአጠቃላይ ቅዱስ ሲኖዶስ በመንፈስ ቅዱስ እየተመራ ላለፉት ተከታታይ ቀናት በመንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመወያየትና ተገቢውን ውሳኔ በማስተላለፍ መደበኛ ስብሰባውን በዛሬው ዕለት በጸሎት አጠናቅቋል፡፡ መሐሪና ሁሉን ቻይ የሆነ እግዚአብሔር አምላካችን ለሀገራችን፣ ለሕዝባችን፣ ለዓለሙ ሁሉ ሰላሙን፣ ፍቅሩንና አንድነቱን ይስጥልን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን

አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም
ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ግንቦት ፳፱ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም. ኢትዮጵያ አዲስ አበባ
©የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት

#ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን
በአማን ተንሥአ እሙታን
"ዛሬ የሕንጻ መሠረት ድንጋይ ብቻ አይደለም የምናስቀምጠው የሰላም መሠረት ድንጋይ እንዲሆንልን በመመኘት ነው" ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ

ሰኔ ፪/፳፻፲፮ ዓ/ም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ

ዛሬ በዕለተ ሰንበት ከረፋዱ 4:00 ጀምሮ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአዲስ አበባ ከተማ በኮሪደር ልማት ምክንያት በፈረሱ ቤቶች ምትክ በተሰጠው ቦታ ላይ ሁለገብ ህንጻ የመሠረተ ድንጋይ የማኖር ሥነ ሥርዓት ተካሒዷል።

የሕንጻው መሠረት ድንጋይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ከክብርት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጋር መሆን አስቀምጠዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት መልእክት አስተላልፈዋል።

ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው ላይ ከተማ አስተዳደሩ ላደረገው መልካም ተግባር በቤተ ክርስቲያን ስም አመስግነዋል።

ቅዱስ አባታችን ቀጥለውም ካሰብነው በላይ ብዙ ቁም ነገር ሠርተውልናልና እግዚአብሔር ይባርክዎ በቸርነቱ ይጠብቅዎ በማለት ክብርት ከንቲባ አዳነች አቤቤን በመመረቅ አመስግነዋል።

ለሀገር የምትጸልይ ለወገን የምትሳሳ በጸሎትና በምልጃ ሁልጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ለምትቆም ቤተ ክርስቲያን መልካም ማድረግ ለሀገረ እንደማድረግ መሆኑ በማስታወስ በዚህም የሁሉም ደስታ መሆኑን ገልጸዋል።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ አክለውም ዛሬ የሕንጻ መሠረት ድንጋይ ብቻ አይደለም የምናስቀምጠው #የሰላም መሠረት እንዲሆንልን በመመኘት ነው ብለዋል።

ክብርት ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን የከተማውን ልማት ሥራ ትውልዳዊ አሻራ መሆኑን በማመን ድጋፍ ማድረጓን የገለጹ ሲሆን በልማቱ ዕቅድ መሠረት እንዲፈርሱ የታመነባቸውን ቤቶች ከማፈረስና በመልሶ ግንባታም ሆነ ሕንጻዎችን በማደስ በተግባር የተገለጠ ከፍተኛ ሥራ ማከናወናቸውን በማስታወስ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ክብርት ከንቲባ አዳነች አቤቤ አክለውም የመልሶ ልማት ግንባታው በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ ከማጋዝ ባለፈ ክትትል እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።

ብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባህር ዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በበኩላቸው ለሆነው ነገር ሁሉ አመስግነው በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት በዚህ መልካም ሥራ መሪ ለሆኑና ለተሳተፉ አካላት የዕውቅና ምስጋና ሰርተፊኬት መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በቀዳሚነት ለክብርት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለሰጡት የመልካም አስተዳዳራዊ ምላሽና ድጋፍ የዕውቅናና ምስጋና ሰርቴፊኬት የዘለዓለም ሕይወት መዝገብ የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስ ከብፁዕ ወቅዱስ አባታችን እጅ ተበርክቶላቸዋል።

ከከንቲባዋ በተጨማሪም ለሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ለመልካም አስተዳዳራዊ ሥራቸው ምስጋና ለአገልግሎታቸው የዕውቅና ሰርተፊኬት ከቅዱስነታቸወ ተቀብለዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስና ክብርት ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የከተማ አስተዳደሩና የክፍለ ከተማው የመንግሥት የሥራ ከፍተኛ የሥራ ሐላፊዎች፣ የመንበረ ፓትርያርክ የመምሪያና የድርጅት የሥራ ሐላፊዎች ተገኝተውበታል።

#ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን
በአማን ተንሥአ እሙታን

#የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ