የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ አገልግሎት /Addis Ababa Diocese Media service
5.97K subscribers
12.3K photos
31 videos
23 files
1.36K links
ይህ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ የቴሌግራም ቻናል ነው።
መንፈሳዊ አገልግሎትና ሰሞነኛ ጉዳዮች ይቀርቡበታል።
አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ
Download Telegram
" #ደብረ_መቅደሱ [ ቅዱሱ ተራራ]፣
(ደብረ ታቦር) ፪ ጴጥ 1 ፥ 18
---------------------------------------------------------------
‎በመልአከ ምሕረት አባ ገብረመድኅን ንጉሤ (ቆሞስ)
‎የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራአስኪያጅ
‎---------------------------------------------------------------

ሙሉ ቃል " ንሕነ ሰማዕናሁ ከመ እምሰማይ ወረደ ሎቱ እንዘ ሀሎነ ምስሌሁ #በደብረ_መቅደሱ፣ ከወደ ሰማይ ለሱ እንደ ተነገረለት በቅዱሱ ተራራ ሁነን ሰማን" 2 ጴጥ 1:18

ቅዱስ ጴጥሮስ ለዚህ ዓለም ሠራዒ፣ መጋቢ ያለው መሆኑን፣ ትንሣኤ ሙታን እንደሚደረግና ኅልፈተ ሰማይ ወምድር ስለሚደረግ ለምግባር ለትሩፋት መቸኮል እንደሚገባና መልካም ማድረግ እንደሚያስፈልግ የራት ማቆየ ተረት እንዲሉ ኦሪት የወንጌል ማቆያ ናትና በኦሪት ሳይሆን ጥበብ በሆነችው ወንጌል አስተማርናችሁ።

ይኸውም የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ ዓለም መኖሩን፣ አምጻኤ ዓለማትነቱን፣ በሥጋ መምጣቱን በኦሪት የነገርናችሁ አይደለምና በወንጌል እንጂ

#አንድም በሥጋ መምጣቱን፣ በኅቱም ድንግልና መወለዱን፤ በኅቱም ድንግልና መፀነሱን፡ በዚህ ዓለም ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር መኖሩን በወንጌል ነገርናችሁ።

#አንድም፡ ይህን ዓለም ለማሳለፍ መምጣቱን፡ ይህን ዓለም ማሳለፉን፤ ይህን ዓለም አሳልፎ መኖሩን በኦሪት የነገርናችሁ ያስተማርናችሁ አይደለም በወንጌል እንጂ።

#ሐተታ፦ በኦሪት በቀዳሚ፡ ገብረ እግዚአብሔር ሰማየ ወምድረ ስለሚል በኦሪት ሆነን የነገርናችሁ አይደለም ሲል ነው።

አንድም፣ ከመዝ ይቤ እግዚአብሔር እንደሚሉ እንደ ዓበይተ ነቢያት ከመዝ ይቤ ሙሴ ከመዝ ይቤ ሳሙኤል እንደሚሉ እንደ ደቂቀ ነቢያት የነገርናችሁ አይደለም ዘነሥአ እምእግዚአብሔር አብ ክብረ ወልዕልና ወስብሐተ= ከእግዚአብሔርነቱ ዘንድ ገንዘብ ያረገውን ፍጹም ክብሩን አይተን ነገርናችሁ እንጅ "ይቤ ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር ዘአነ ኅረይኩ { በሱ ሕልው ሁኜ ልመለክበት ለመሥዋዕትነት የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው} የሚለውን ቃል " ንሕነ ሰማዕናሁ ከመ እምሰማይ ወረደ ሎቱ እንዘ ሀሎነ ምስሌሁ በደብረ መቅደሱ፣ ከወደ ሰማይ ለሱ እንደ ተነገረለት በቅዱሱ ተራራ ሳለን ሰማን። በማለት የደብረ ታቦርንና የቅዱሱን ተራራ ምሥጢር ይናገራል።

የደብረ ታቦር በዓል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሦስቱን ትውልድ ( ትውልደ ሴም፣ ካምና ያፌት) የሦስቱን የሃይማኖት ገመድ ( እምነት፣ ተስፋማ ፍቅር) ምሳሌ የሆኑትን ሦስቱን የምሥጢር ሐዋርያት ( ጴጥሮስ ፣ ያዕቆብና ዮሐንስን) ይዞ ወደ ረጅም (ታቦር) ተራራ ላይ ወጥቶ ኤልያስና ሙሴንም አምጥቶ ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት፣ አምላክነቱ በአባቱ፣ በሙሴና ኤልያስ፣ በብሩህ ደመና፣ በገጹ መለወጥ፣ በልብሱ ጸአዳ መሆን የተገለጠበት ልዩ በዓል ነው።

ጌታ ሦስቱን ይዞ ወደ ተራራው ወጥቶ 8ቱን ሐዋርያት ይዟቸው ያልወጣው በይሁዳ ምክንያት ነው።

ይሁዳ ጌታን ከምሥጢረ መንግሥቱ ቢለየኝ ከሞቱ ገባኹበት ብሎ ምክንያት ያገኝ ነበርና ምክንያት እንዳያገኝ ነው፤ ነገር ግን በተራራው ላይ ለ3ቱ የተገለጸው ምሥጢር ከተራራው ሥር ላሉት ከይሁዳ በስተቀር ተገልጾላቸዋል።

#ደብረ_ታቦር ( ታቦር ተራራ) ከገሊላ ባሕር በስተ ደቡብ ምዕራብ በ10 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ደብረ ታቦር ከባሕር ጠለል በላይ 572 ሜትር ከፍ ይላል::

ይህ ተራራ በብሉይ ኪዳንና በሐዲስ ኪዳን ታላላቅ ሥራዎች ተሠርተውበታል፡፡

በዓለ ደብረ ታቦር ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘጠኝ ዐበይት በዓላት መካከል በዐራተኛ ደረጃ የሚከበር በዓል ነው።

#ጥንተ_በዓሉ_መች ነው ?

"ጌታ ከተወለደ በ32 ዓመት ከሰባት ወር ከ15 ቀን ነሐሴ 13 በዕለተ እሁድ በዘመነ ማቴዎስ የተፈጸመ በዓል ነው"

ይኽ ታሪክ ከተፈጸመ ዘንድሮ በ2017 ዓ.ም 1984ኛ ዓመታትን አስቆጥሯል ማለት ነው። (መጽሐፈ ታሪክ ወግስ )

ከ2017 ዓ.ም ላይ 33ኛ ዓመትን ስንቀንሰው 1984 ዓመታትን ያስቆጠረ መሆኑን ልብ ይሏል።

ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “ታቦር ወአርሞንኤም በስመ ዚአከ ይትፌሥሑ፤ ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል" በማለት እግዚአብሔር በሚሠራው ሥራ በተራራው አካባቢ የሚኖሩና የአምላክነቱ ሥራ የሚፈጸምላቸው ሰዎች የሚደሰቱ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡

ባርቅና ዲቦራ የእሥራኤል ጠላት የነበረውን ሲሣራን ድል አድርገው በታል፡፡ መሳ4 ፥ 4-24፡፡ በሐዲስ ኪዳንም የጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የክብሩን ብርሃን የገለጠው በዚህ ተራራ እንደ ሆነ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡ ማቴ 17፥1-8

በደብረ ታቦር ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የክብሩን ብርሃን በመግለጡ (በገለጠ ጊዜ) ፡-

✍️ 1ኛ ደቀመዛሙርቱን ሲፈታተን የነበረውን ዲያብሎስን ድል ነስቶበታል፤

✍️ 2ኛ ሙሴን ሰው ከማያውቀው መቃብሩ ከ1644 ዓመታት በኋላ አሥነስቶ፣ ኤልያስን አሳርጎ ከወሰደበት የሕያዋን ሀገር አምጥቶ የባሕርይ አምላክነቱን እንዲመሰክሩ አድርጎአ ቸዋል፡፡ “ወናሁ መጽአ ሙሴ ወኤልያስ ኀቤሁ እንዘ ይትናገሩ ምስሌሁ ለእግዚእ ኢየሱስ ከመ ያእምሩ ኲሎሙ ሰብእ ከመ ውእቱ እግዚአ ለሙሴ ዘአንሥኦ እሙታን፤ ወአምላኩ ለኤልያስ ዘአውረዶ እምኀበ አዕረጎ፤ ሰዎች ሁሉ እርሱ ለሙሴ ጌታውና ከሞት ያስነሣው እንደሆነ ለኤልያስም ፈጣሪው እንደሆነና ካሳረገበትም ያወረደው እርሱ እንደሆነ ያውቁ ዘንድ ከጌታ ከኢየሱስ ጋር እየተነጋገሩ ሙሴና ኤልያስ ወደ እርሱ መጡ፡፡”

“ወአአመሩ ሐዋርያት ከመ አምላክ ወሰብእ ፍጹም ዘውእቱ ዘአንሥኦ ለሙሴ እመቃብር ወውእቱ ዘእዕረጎ ወአውረዶ ለኤልያስ እስመ ኢኮነ መኑሂ ዘየአምር መቃብሪሁ ለሙሴ ዘእንበሌሁ ወኢኮነ መኑሂ ዘየአመር ኀበ ሀሎ ኤልያስ ዘእንበለ ዘአዕረጎ፤ ሐዋርያትም ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው የሆነ እርሱ ሙሴን ከመቃብር ያስነሣው ኤልያስንም ያሳረገው አውርዶም ያመጣው እርሱ እንደሆነ አወቁ፡፡ ከእርሱ በቀር ማንም ማን የሙሴን መቃብር የሚያውቅ የለም፡፡ ከአሳረገው ከእርሱ በቀር ማንም ማን ኤልያስ ያለበትን የሚያውቅ የለም” እንዲል ስንክሳር ዘነሐሴ 13

❖ 3ኛ በብሉይ ኪዳን የነበሩ ቅዱሳንና በሐዲስ ኪዳን ያሉት ቅዱሳን አንድ ሆነውበታል፡፡ በዚህም የተነሣ ደብረ ታቦር የቤተ ክርስቲያን አምሳል ሆነ፡፡

“ወኮነት ደብረ ታቦር አምሳለ ቤተክርስቲያን እስመ አስተጋብአት ውስቴታ እምነ ብሉይ ወሐዲስ፤ ደብረ ታቦርም የቤተ ክርስቲያን አምሳል ሆነች፤ ከብሉይና ከሐዲስ በውስጧ ሰብስባለችና" እንዲል ስንክሳር ዘነሐሴ 13፡፡

❖ 4ኛ ደብረ ታቦር በቅዱስ ጋብቻ የተወሰኑና ክብረ ድንግልናቸውን ጠብቀው በድንግልና የጸኑ፣ ሙተው ሥጋቸው በመቃብር የፈረሰና በዚህ ዓለም በሕይወተ ሥጋ ያሉ እኩል በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙ መሆናቸው የተረጋገጠበት ተራራ ነው፡፡

በዚያ ጌታችን፡-

➢ በቅዱስ ጋብቻ የኖረውንና በሥጋ ሞቶ የተቀበረውን ሙሴን፣ በድንግልና ያገለገለውንና ወደ ብሔረ ሕያዋን አርጎ የነበረውን ኤልያስን፣
➢ በሕይወተ ሥጋ የነበሩ ሐዋርያትን ሰብስቧቸዋል፡፡
ብርሃነ መለኮቱ ተገለጠ የሚለውን አዳም በገነት በነበረበት ጊዜ ለብሶት በነበረው የጸጋ ልብስ አንጻር እንጂ የመለኮቱን ብርሃን ዓይቶ በሕይወት የሚኖር የለም ይላል።

#ነጭ_ልብሱ_እንደ_በረዶ_ነጭ_ሆነ
የልብሱን ጸአዳነት ሊቁ ርቱዓ ሃይማኖት (አባ ጊዮርጊስ) መጀመሪያ በአዳም የነበረው የብርሃን ልብስ ዛሬ ተመለስ፡፡ ያረጀ የአዳም ሰውነት ዛሬ ታደሰ፤ መጀመሪያውና ኋለኛው ዛሬ በደብረ ታቦር ታደስ፡፡ ፊቱም እንደ ፀሐይ አበራ፤ ዛሬ ክርስቶስ በፍጥረቱ ሁሉ ተሾመ፡፡ ዛሬ ንግሥናው ከዓለም አስቀድሞ የነበረ የነገሥታቱ ንጉሥ የሹመቱ ዕለት ነው፡፡ ዛሬ ነጭ ልብሱ እንደ በረዶ ነጭ ሆነ፡፡ በምድር ያለ አጣቢም እንዲህ ሊያነጻው አይችልም፡፡ ባለሳሙናዎቹም በትክክል አጥበው የሚያነጹት አይደለም፡፡ ይህ የንግሥና ልብስም በውኃ የሚያጥቡት አይደለም፡፡ በወይን ደም ነው እንጂ፡፡ በማለት አመሥጥሮታል።

#የጴጥሮስ_ልመና

ሊቀ ሐዋርያ ቅዱስ ጴጥሮስም በትሕትና ሁኖ አንዱን ላንተ፣ አንዱን ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ ሦስት ዳስ እንሥራና በዚህ እንኑር ብሎ ጠየቀ፤ ለእርሱና አበረውት ለነበሩት ወንድሞቹ ግን እንሥራ ባለማለቱ ትሕትናውን ገለጠ።

አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ "ምንት ይበቊዕ ፈትለ ማኅቶት ዘእንበለ ቅብዕ፣ ወትጋሀ ጾም ወጸሎት ዘእንበለ የውሀት፣ ወዴግኖ ቤተ ክርስቲያን ዘእንበለ ምሕረተ ነዳያን ፣ ወድንግልና ዘእንበለ ትሕትና?" { የመብራት ፈትል ያለ ዘይት፤በጾምና ጸሎት መትጋትስ ያለ የዋህነት፣ ቤተክርስቲያንን መከተል ለድሆች ያለ መራራት፣ ድንግልናም ያለ ትሕትና ምን ይጠቅማል}" ? በማለት ገልጦታል። መ.ምሥጢር 30፥26

ብሩህ ደመና ጋረዳቸው ከደመናውም የምወደው ልጄ ይኽ ነው እርሱን ስሙት የሚል ቃል ተሰማ። ማቴ 16:13-17 2 ጴጥ 1:18

#ኢየሱስ_ክርስቶስ_ከተራራው_ወረደ ማቴ 17:14

ለምኑ ይሰጣችኋል፣ ፈልጉ ታገኛላችሁ፣ አንኳኩ ይከፈትላችኋል ያለ አምላክ ቅዱስ ጴጥሮስ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው ብሎ እየለመነው እርሱ ግን ከተራራው ወረደ።

ለምንድነው የወረደው ስንል ከተራራው ካልወረደ የሰው ልጅ አይድንምና ነው።

አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በመጽሐፈ ምሥጢር የደብረ ታቦርን ምንባብ በጻፈበት ክፍል ላይ " ጴጥሮስ ሆይ ላንተ በታቦር ተራራ ላይ ድምጹን እየሰማሁ የሙሴ የኤልያስ ጌታ ይበሉህ እንጂ ሙሴ፣ ኤልያስ ልትባል አይገባህም የሚለውን ምሥክርነት እያደመጥክ በዚያ መኖር መልካም ነው። ለእኛ ግን ከተራራው ወርዶ በጥፊ ካልተመታልን ( ካልተሰቀለልን) አንድንምና በተራራው እንዲኖር አትለምነው። ክርስቶስ ከተራራ ካልወረደ " እደ መኑ ይትቀነው በቀራኒዮ ለመድኃኒተ ዓለም፣ እምገቦ መኑ ይውኅዝ ማየ ሕይወት ኀበ መቃብሪሁ ለአዳም፣ መኑ ይጥዕም ሞተ በሥጋ ከመ ይኩን ሕይወተ ለምዉታን..." በማለት ጌታ ከተራራው የወረደበትን ዓላማ በግልጥ አስቀምጦልናል።

ደብረ መቅደሱ የተባለ ቅዱሱ ተራራ (ደብረ ታቦር) ምንድነው ?

✍️ደብረ ታቦር ቤተክርስቲያን ናት ። ደብረ ታቦር ከፍ ያለ ተራራ እንደሆነ ሁሉ ቤተክርስቲያን በዚህ ዓለም ካሉ ቤቶች ሁሉ ክብሯ ከፍ ያለ ነውና " የመቅደሳችን ስፍራ ከጥንት ጀምሮ ክፍ ያለ የክብር ዙፋን ነው። "እንዲል ኤር17:12

✍️ እመቤታችን ደብረ ታቦር (ታቦር ተራራ) ትባላለች። ፈልፈለ ማኅሌት የሆነ ቅዱስ ያሬድ "አድባረ ድኁኃን ተሰምየት ዛቲ ይእቲ ቅድስት ድንግል= ያቺ ተራራ የረጃጅሞች ተራሮች ራስ ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፤

ዳግመኛም " ሰላም ለኪ ኦ ማርያም ደብረ መቅደሱ ለእግዚአብሔር እንተ መልዕልተ ኵሎሙ ቅዱሳን" በማለት ቅዱስ ተራራ እመቤታችን መሆኗን ገልጧል።

ልበ አምላክ ዳዊትም "መሠረታቲሃ ውስተ አድባር ቅዱሳን" በማለት ክብራቸው ከከበሩ አበው እንደተወለደች ተራራ በማለት መስክሯል።

✍️ ደብረ ታቦር በወንጌል ትመሰላለች ። ተራራ ከፍ ያለ ነው ወንጌልም ከመጻሕፍተ ምኑናት፣ ከመጻሕፍ ርኵሳት፣ መጻሕፍተ ዕዳ ይልቅ የከበረች ናትና።

አንድም ተራራን ሲወጡት ያደክማል፣ ወንጌልን ሲፈጽሟት ያደክማል። ተራራ ከወጡት ኋላ ሁሉን እንዲያሳይ ወንጌልን ከተማሯት ኋላ ጽድቅን ከኃጢአት ለይታ ታሳያለችና ነው።

✍️ ደብረ ታቦር የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ነው። ተራራ ላይ በብዙ ጥረት እንደምንወጣ ሁሉ መንግሥተ ሰማያትም በብዙ መከራና ሕማም እንገባለንና ነው። ሐዋ 14:21
✍️ ደብረ መቅደሱ የተባለው አባታችን አብርሃም ነው። አብርሃምን መቅደስ አለው ማኅደረ እግዚአብሔር ነውና፡ ማቴ፡ ፲፯፡ ፭፡

ከዚህ ሁሉ የተነሣ ቅዱስ ጴጥሮስ ደብረ ታቦርን “ቅዱስ ተራራ” ብሎታል፡፡ ፪ጴጥ.፩ ፥ ፲፰፡፡

ከበዓሉ በረከትን ያሳትፈን። አሜን

#ቅድስት ሀገሬ ኢትዮጵያ!!!

#የወለድሻቸው ልጆችሽ ይውለዱሽ!!!

#ልጆችሽ ይሟገቱልሽ እንጂ አይሞግቱሽ!!!

#በስደት ያሉ ልጆችሽ በበረከት ይመለሱልሽ!!!

#ድንበርሽን እሳት መሀልሽን ገነት አድርጐ የዓለም ማረፍያ ያድርግሽ #አሜን

‎መልአከ ምሕረት አባ ገብረመድኅን ንጉሤ (ቆሞስ)
‎የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራአስኪያጅ
----------------------

ነሐሴ 12 ቀን 2017 ዓ.ም
አዲስ አበባ, ኢትዮጵያ
ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ሊቀ ጳጳስ ለ295 ደቀ መዛሙርት ሥልጣነ ክህነት ሰጡ።

ነሐሴ ፲፬/፳፻፲፯ ዓ/ም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ

ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ዜና ማርቅስ መንፈሳዊ ኮሌጅ መሥራችና የበላይ ኃላፊ፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ሰብሳቢና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ለ278 የአብነት ተማሪዎች የዲቁናን ማዕረግና ለ17 ዲያቆናት ማዕረገ ቅስናን ሰጥተዋል። በዛሬው ዕለት ሥልጣነ ክህነቱን የተቀበሉት የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች በዘጠኝ ወረዳ ቤተ ክህነት ሥር ካሉ ገዳማትና አድባራት የአብነት ትምህርት ቤቶችና መጋቢ የአብነት ት/ቤቶች ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ ደቀ መዛሙርት ሲሆኑ ሁሉም የመመዘኛ ፈተናውን በብቃት ያለፉ ናቸው።

ከእነዚህ ሥልጣነ ክህነት ከተቀበሉት አገልጋዮች መካከል ሁለት ካህናትና ሰባት ዲያቆናት ከእስልምና የመጡና ቤተሰቦቻቸውም ጭምር ተጠምቀው የሥላሴን ልጅነት እንዲያገኙ ብርቱ ተጋድሎ የፈጸሙ እንደሆኑ የሀገረ ስብከቱ የካህናት ዋና ክፍል ኃላፊ የሆኑት ሊቀ ኅሩያን መሠረት ዳኘው ለብፁዕነታቸው ገለጻ አድርገውላቸዋ።

በብፁዕነታቸው መልካም ፈቃድ ለተሿሚዎች መልዕክት እንዲያስተላልፉ የታዘዙት የሀገረ ስብከቱ ሥራ አሰኪያጀ መጋቤ ጥበብ ታምሩ መመረጣችሁ ከሰው ዘንድ አይደለም ከእግዚአብሔር እንጂ፤ የመረጣችሁን እግዚአብሔርን በሕይወታችሁ አክብሩ፤ ለክህነታችሁና ለአገልግሎታችሁ ተጠንቀቁ፤ ታማኞችና ቅን አገልጋዮች እንድትሆኑ ብለዋል።

ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በቃለ በረከታቸው ክህነታችሁ የሠመረ እንዲሆን አሁን የታዘዛችሁትን ሁሉ የምትፈጽሙ መሆን ይገባችኋል፣ እራሳችሁን በሁለንተና የምታበቁ ሁኑ፣ በትምህርት ላይ ትምህርት፣ በእውቀት ላይም እውቀትን የምትጨምሩ ጎበዞች መሆን አለባችሁ፣ ካህናት የሆናችሁ መንፈሳዊ ኮሌጅ ገብታችሁ ለመማር ዝግጁ ሁኑ፣ ዲያቆናትም ገና በዕድሜ ትንንሽ ብትሆኑም የሳይንሱን ትምህርታችሁንም ሆነ የአብነቱን በብቃት አጠናቃችሁ ካህናትና መነኮሳት ሆናችሁ ቤተ ክርስቲያናችሁን በበለጠው ሥልጣን የምታገለግሉ ለመሆን በርቱ ብለዋል።

በሰዎች ፊት የተመሰከረላቸው አገልጋዮች ለመሆን አርዓያ ክህነታችሁን አጥብቃችሁ ጠብቁ፤ ሰው ሲፈልጋችሁ መገኛ አድራሻችሁ ቤተ ክርስቲያን መሆን አለበት፣ እናንተ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል እርቅ የምትፈጽሙ፤ አገልግሎታችሁም ሆነ ሥልጣናችሁ ሰማያዊ ነው በማለት አባታዊ መመሪያዎቻቸውን ሰጥተዋል።

ከእስልምናው ዓለም ከነቤተሰባችሁ ተጠምቃችሁ በዲቁናም ስታገለግሉ የነበራችሁ ካህናት ታሪካችሁ አስተማሪ ነው፤ አሁንም ወደ በለጠው የቅድስና ሥራ እሱ እግዚአብሔር ተጠርቷችኋልና እንኳን ደስ አላችሁ ያሉት ብፁዕነታቸው የሳይንስ ትምህርቱን አጠናቆ ዲግሪ ለያዘው በ2018 ዓ.ም የቅዱስ ዜና ማርቆስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የትምህርት ዕድል ሰጥተውታል። ለሁለቱ ከእስልምናው ዓለም ለመጡ ካህናት የእጅ መስቀል፣ ለዲያቆናቱ ደግሞ ወንጌል ሸልመዋቸዋል።

በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ምሥጢረ ክህነት ከሚፈጸምባቸው ቋሚ መርሀ ግብሮች መካከል ይህ የደብረ ታቦር በዓል አንዱ ነው።

©ሳሌም የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሚዲያ
እንኳን ለወላዲተ አምላክ ቅድስት ድንግል ማርያም
በዓለ ትንሣኤና በዓለ ዕርገት በሰላም አደረሳችሁ።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ለበርካታ ዓመታት በርእሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ገዳም በሊቃውንት ጉባዔ ሰብሳቢነት በንቡረእድነትና በድጓ መምህርነትና ምስክርነት ያገለገሉት ወላዴ አእላፍ ንቡረ እድ በላይ መረሳ ዕረፍት የተሰማቸውን ጥልቅ ኀዘን በመግለጽ አባታዊ መልእክት አስተላለፉ::

የቅዱስነታቸው መልእክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ነው፦

መልእክተ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

"ዘጻመወ በዓለም የሐዩ ለዝሉፉ፤ እስመ ኢይሬኢ ሙስና፦ በዓለም የደከመ ለዘለዓለም ይድናል፤ ጥፋትን አያይምና። መዝሙር 48፥9

ንቡረ ዕድ በላይ መረሳ ሃይማኖት ያላቸው፣ ሃይማኖትን የመሰከሩ፣ ሃይማኖትም የመሰከረችላቸው፣ ወላዴ አእላፍ፣ መምህረ አሕዛብ፣ ፍቅረ እግዚአብሔርና ፍቅር ቢጽ የጸናላቸው፣ ዘመናቸውን በሙሉ ያስተማሩ፣ ሁሉን በእኩል ዓይን የተመለከቱ፣ ቃለ ወንጌልን በምእመናን ልብ ላይ የዘሩ ታላቅ ገበሬ፣ ፍሬአቸውን በብዙኃን ልጆቻቸው ላይ ያዩ፣ አበ ብዙኃን፣ አንደበታቸው ድንቅፍ የማይልባቸው፣ የዘመን ጎርፍ የማይወስዳቸው፣ በስፍራቸው የተገኙ፣ በትክክል ያወቁ፣ በነጻ የተቀበሉትን በነጻ የሰጡ፣ ተንቀሳቃሽ ቤተ መጻሕፍት ነበሩ።

እኒህ የሁላችን የዘመን እኩያ፣ የትምህርት ቤት ባልንጀራ፣ ማኅቶተ ቤተ ክርስቲያን የሆኑት አባት ከዚህ ዓለም ድካም ማረፋቸውን የሰማነው በከፍተኛ ኀዘን ውስጥ ነው።

የሕዝባቸውን መከራ በልባቸው ተሸክመው ለኖሩት ለእርሳቸው ይህ ዕረፍት ቢሆንም ለቤተ ክርስቲያን አባቶችና ለምእመናን ግን ትልቅ ጉዳት ነው።

ስለሆነም የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቅርስ ከመሆናቸው አንጻር የእርሳቸው ኅልፈት እንደ አንድ ሰው ኅልፈት የሚታይ ባለመሆኑ በቅዱስ ሲኖዶስና በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም የተሰማንን ኀዘን እንገልጻለን!

በታላቁ ሊቅ ዕረፍት ያዘናችሁ ሁሉ እርሳቸው በሚታወሱበት መልካም ተግባራቸው እና በደቀ መዛሙርቶቻቸው ሕያው ናቸውና ልትጽናኑ ይገባችኋል።

እግዚአብሔር አምላካችን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቅልን። በሕይወተ ሥጋ ለተለዩን ዕረፍተ ነፍስን ፣ በዚህ ለቆየነውም መጽናናትን ይላክልን!

እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!
አሜን።

አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃን ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም
ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ነሐሴ 16 ቀን 2017 ዓ.ም

ዋሽንግተን ዲሲ አሜሪካ
©የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት