መልዕክተ ቅዳሜ - በያሬድ ጏ/ማርያም
1.12K subscribers
2 files
57 links
Download Telegram
1ኛ/ ከልጅነት እስከ እውቀት እና ምናልባትም እስከ ሞት ድረስ በአፋኝ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ መቆየት (Childhood Socialization) የመጀመሪያው ነው፡፡ ከላይ እንዳልኩት በአፋኝ ሥርአት ውስጥ ተወልዶ፣ አድጎ፣ ጎልምሶ፣ ሸምግሎ፣ ልጆችና የልጅ ልጆች አፍርቶ መሞት፡፡ መልጅነት እድሜ ጀምሮ እጅግ አስከፊ (harsh)፣ ቅጣት ላይ ባተኮረ ስነልቦና (punitive) እና በልጆችና በወላጆች መካከል ያለውም ግንኙነት የፈላጭ ቆራጭ (domineering parenting) እንዲሆን በማድረ ልጆች ጠያቂ እንዳይሆኑና የታዘኡትን ነገር ብቻ እንዲፈጽሙ በማስተማር (learn to obey without question) አፈናን እንዲለማመዱ ማድረግ አንዱ ስልት ነው፡፡ በእንዲህ ያለው ሁኔታ ያደጉ ልጆች ሁሌም ታዛዥና ጠያቂዎች ባለመሆናቸው ለአገዛዝ ሥርዓት የታጩ ታዛዦችና ምቹ ናቸው፡፡

2ኛ/ ጥልቅ ፍርሃት መፍጠር እና ባልተጨበጡ ስጋቶች ውስጥ መውደቅ (Fear and threat Perception)፤ ይህ ብዙ የአንባገነን ሥርአቶች ልክ እንደ የሕዝብን ስሜት፣ ቁጣ እና ጥያቄ አፍነውና ተቆጣጥረው የሚያቆዩበት ዋነኛ ሥልት (coping mechanism) ነው፡፡ ሕዝብን ሁሌ ስጋት ውስጥ በመጣል የውጪ ጠላት እንዳለው እንዲያስብ (እገሌ አገር ሊወረን ነው)፣ የኢኮኖሚ አለመረጋጋት በመፍጠር እና በፍጥነት የሚለዋወጡ ማህበራዊ ቀውስ አስከታይ ልወጦችን በመፍጠር ማህበረሰቡ እንዳይረጋጋና ሽብር ውስጥ እንዲገባ ማድረግ፡፡

3ኛ/ ሁሉም የአገዛዝ ሥርአቶች ከሌላው እንለያለን ብለው ሕዝቡን አስገድደው የሚግቱት የፖለቲካ ትርክት፣ እሳቤና ስብከት (Political Indoctrination) ስላላቸው ሁሉም ዜጋ በተሰመረለት የእሳቤ መስመር ላይ ብቻ እንዲቆም ማድረግ (official line of the government)፡፡ መንግስት ካሰመረው መስመር መውጣት ወይም ማፈንገጥ እንደ አገር ክህደት እንዲቆተር ማድረግ፡፡ አብይ ያልተደመረ ሁሉ የአገር ጠላት ነው ብሎ ያሰመረው የቅርቡን መስመራችንን መጥቀስ ይቻላል፡፡

4ኛ/ ወጥ የሆነ እና አንድ ገዢ ሃሳብ ብቻ እንዲንሰራፋና በማህበረሰቡ ውስጥም እንዲሰርጽ በማድረግ ሌሎች ተፎካካሪ ሃሳቦች ጭርሱኑ እንዳይኖሩ ማድረግ ወይም ማክሰም (Cognitive Rigidity) ሌላው ስልት ነው፡፡ የዚህ ስልት ዋነኛው አላማ እጅግ አንባገነን የሆኑ ግለሰቦች (High-authoritarian individuals) ሃሳብ ብቻ ገዢና ብቸኛ ሆኖ እንዲወጣ በማድረግ የአንድ ሰው ወይም የአንድ ቡድን የበላይነት እንዲሰፍን ማድረግ ነው፡፡ የአብይ ተከታታይ የመደመር ፍልስፍና በሚል የተሰነዱ መጽሃፎች ዋነኛ ግባቸውም ይሄው ነው፡፡

እነዚህ ከላይ የጠቀስኳቸው በአንድ ሕዝብና አገር ላይ የሚፈራረኩ የአንባገነናዊ ሥርአቶች ማህበረሰቡን በቆይታ ውስጥ እራሱን ከግፍ አገዛዞች ጋር አላምቾና አዋህዱ እንዲያኖር የማድረጊያ ስልቶች ናቸው፡፡ ውጤታቸውም ግልጽና አስተማማኝም እንደሆነ ብዙ ርቀት ሳንሄድ ይህ ሁሉ መከራና ሰቆቃ የሚወርድበት የኢትዮጵያ ሕዝብ ለግፈኞቹ የሚሰተውን እድልና አንዳንዴም ግፈኞቹን ሺ አመት ይግዙኝ እያለ ደጅ የሚጠናበት ስነ ልቦናው ከየት እንደመነጨ ያሳያል፡፡ እራሱን ከግፍ ጋር ያዋሃደ ማህበረሰብ ከዚህ የሚከተሉት መገለጫዎችን ያሳያል፤

ሀ/ ለሚመጣው አንባገነናዊ ሥርአት ሁሉ እራሱን አዋርዶና አኮስሶ እንዲረግጡት እራሱን መሬት ላይ የማነጠፍ ባህሪ ይላበሳል (Authoritarian Submission)፡፡ መንግስትን ተደብቆ ቢያማ እንኳ በአደባባይ አይተችም፣ ለባለሥልጣናት በሚያሳየው እጅግ ተለማማጭነትና መንበርከክ የተነሳ ለሚፈጽሙበት ግፍ ሁሉ የመቀበል እውቅናን ይሰጣል፡፡

ለ/ የተለመዱ ወጎችን፣ ባህሎችን፣ ሃይማኖቾችን እና ልማዶችን በመጣስ እራሳቸውን ከማህበረሰቡ ጫና ነጻ በማውጣት ሃሳባቸው በነታነት የሚገልጹ፣ በአለባበሳቸውም ሆነ በሃሳብ መስመራቸው ወጣ ያሉ ግለሰቦችን እያደነ የጥቃት ኢላማ ያደርጋል፣ ያወግዛል፣ ያዋርዳል አንዳንዴም የደቦ እርምጃ በመውሰድ እና አንዳንድ ገደቦችንም በመጣል ከአንባገነን ገዢዎቹ በከፋ ሁኔታ የአገዛዝ ባህሪ ይላበሳል፡፡ (እዚህ ላይ የቲክቶከሮቹን ጉዳይ ማየት ይቻላል፡፡)

ሐ/ ጽንፍ የያዘ የሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶች ተቆርቋሪ በመሆኑ (Conventionalism) ለውጦችን መቃወም፣ መንቀፍ እና ዘመኑን ለሚዋዡ አስተሳሰቦች ጭምር በተቃርኖ መቆም የሚታይበት ማህበረሰብ ይሆናል፡፡

እንዲህ አይነት ባህሪዎችን ከአገዛዝ ሠንሰለት የወረሰ ማህበረሰብ ለሁሉም አይነት ለውጦች ሁሌም ተገዳዳሪ ነው የሚሆነው፡፡ የራሱንም ሆነ የሌሎችን ዜጎች ነጻነት እና ሰብአዊ መብቶች ጭምር ከመጣስና የአገዛዝ ሥርአቶቹም የዜጎችን መብት ሲጥሱ አብሮ ድጋፍ በመስጠት አፈናን እና ግፍን በራሱ ላይ ያጽናል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የደቦ ፍርድ እንዲስፋፋ ምክንያት ከሆኑት በርካታ ነገሮች አንዱ ይህ የማህበረሰቡ የአገዛዝ ባህሪን፣ የአፋኝነት ስነ ልቦናን እና ጭካኔን በሂደት ከአገዛዝ ሥርአቶቹ እየወረሰ ከመምጣቱ ጋር እንደሚያያዝ የሚያሳዩ ብዙ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
3
መልዕክተ ቅዳሜ፤

ርሃት፣ ችጋር እና ድህነትን እንደ አንድ የፖለቲካ መሳሪያ መጠቀም፤
Weaponization of hunger and poverty for political repression
++++++++

የዛሬው መልዕክተ ቅዳሜ ዋነኛ ትኩረት ክፉ የሚባሉ የአገዛዝ ሥርአቶች ሕዝብን በድህነት አረንቋ ውስጥ ዘፍቆ ማቆየት እና ችጋርን እንዴት የፖለቲካ መሳሪያ በማድረግ እንደሚጠቀሙበት በማሳየት ሕዝብ ራሱን ከድህነትና ከችጋር ለማላቀቅ ምን ላይ ማተኮር እንደሚኖርበት ለመጠቆም የተለመ ነው፡፡

ሕዝብን ለተራዘመ ጊዜ በድህነት ውስጥ ደፍቆ ማቆየትም ሆነ አልፎ አልፎ በሚከሰቱ ተፈጥሯዊ አደጋዎች፣ የአየር መዛባት፣ ጦርነት ወይም የፖለቲካ አለመረጋጋቶች የሚፈጥሯቸውን የኑሮ መዛባቶች ተከትለው በሚከሰቱ ርሃቦች ወይም ችጋር እንዲማቅቅ ማድረግ በብዙ አንባገነናዊ ሥርአቶች ውስጥ እንደ አንድ በደንብ ታስቦባቸውና ውጤታቸውም ተፈልጎ የሚደረጉና ሕዝብን በአፈና ውስጥ አምቆ ለማቆየትና ለመግዣነት የሚያገለግል ስልት አድርገው የሚጠቀሙበት መሆኑን የጋራ ግንዛቤ መፍጠር የግድ ይላል፡፡ ርሃብን እና ድህነትን እንደ መሳሪያ የመጠቀሙን የአንባገነኖች ስልት ለየብቻ በምሳሌ ጭምር እንያቸው፡፡

1ኛ/ ርሃብን ወይም ችጋርን እንደ ጦር መሳሪያ መጠቀም/weaponization of hunger

ርሃብን የመግዣ መሳሪያ ማድረግ (weaponization of hunger) በሙስና ውስጥ የተዘፈቀና የሕዝብን ሃብት ያለ አግባብ በሚጠቀም፣ መድሎ እና ወገንተኝነት በሰፈነበት ወይም የዘር ፖለቲካ ሥር በሰደደበት፣ መሠረታዊ ሰብአዊ መብቶች በከፋ ሁኔታ በሚፈጸሙበት፣ ግጭቶችና ጦርነቶች በተስፋፉበት እና የዲሞክራሲ ባህል ባልዳበረበት አገር የአገዛዝ ሥርአቶቹ የፖለቲካ ምህዳሮቹን ከማጥበብ፣ ሕዝብን በግፍ አድራጎት ሰላም ከመንሳት፣ አፈና እና እስርን በመጠቀም ተቀናቃኞቻቸውን ከፖለቲካ ምህዳሩ እንዲወገዱ ከማድረግ እና ጠመንጃን ዋነኛ የመግዣ መሳሪያቸው ከማድረግ ባልተናነሰ ሚሊዮኖችን የምግብ ዋስትና (food scarcity) እንዲያጡ፣ ግጭቶች ባሉባቸው አካባቢዎች ደግሞ የምግብና ሌሎች ሰብአዊ እርዳታዎች በበቂ ሁኔታ እንዳይቀርቡ ወይም የሚቀርቡበትን መንገዶች በማስተጓጎል በአንድ አካባቢ ያለን ሕዝብ ወይም አንድን ማህበረሰብ ለመቅጫነት ወይም አንበርክኮ ለመግዣ የፖለቲካ መሳሪያ አድርገው ይጠቀሙበታል፡፡

በተለይም በግጭቶች ወቅት ለተፋላሚ ወገኖች ድጋፍ ሊሰጡ ይችላሉ ያሏቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች በርሃብ እንዲማቅቁ በማድረግ፣ ሰብአዊ እርዳታዎችን እንዳያገኙ መከላከል፣ እርዳታዎቹን ለሌላ አላማ ማዋል የተለመደ የተፋላሚ አካላትን አቅም የማዳከሚያ፣ አካባቢውን እና ሕዝቡን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣተር (weaken, or subjugate populations)፣ የወታደራዊ የበላይነት ለማግኘት በማሰብ የሚወስዷቸው እርምጃዎች ሲሆኑ በአለም ደረጃ የሚታወሱ በርካታ ሕዝብን በርሃብ የማሰቃየት እና የመፍጀት የጦር ወንጀሎች ተፈጽመዋል፡፡ ለዚህም የቅርቦቹን የሴሪያ እና የጋዛ ጦርነቶች በዋነኝነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ወደ አገራችንም መለስ ያልን እንደሆን በትግራዩ ጦርነት የብልጽግና መንግስት የትግራይ ሕዝብ ላይ ከፈጸማቸው አለም አቀፍ ወንጀሎች መካከል አንዱና ዋነኛው ከጥይት እና ከድሮን ጥቃት የሚተርፈውን ሕዝብ መሰረታዊ የሆኑ የሰብአዊ እርዳታዎችን ሙሉ በሙሉ በመንፈግ በርሃብ የመቅጣትና ለህውሃት ሊሰጥ ይችላል ተብሎ የሚታሰበውን ድጋፍ እንዲያቆም የማድረግ ስልት አንዱ ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ በቅርቡም በአማራ ክልል የሚገኙ ተፈናቃዮች ላይ ሲፈጸም ተስተውሏል፡፡
ርሃብን እንደ አንድ የጦር መሳሪያ በመጠቀም አንድን ማህበረሰብ ኢላማ በማድረግ ማዳከምና መጉዳት በብዙ ስልቶች ሊገለጽ ይችላል፡፡ አካባቢውን በመክበብ ምንም አይነት አቅርቦቶች እንዳያገኝ ማድረግ፣ ገበሬዎችን እና አምራች የሆኑ አካላትን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶችን መፈጸም፣ የምግብ ክምችት ያለባቸውን አካባቢዎች ሆን ብሎ ኢላማ በማድረግ ማውደም፣ ከውጭ ለጋሶች ወይም ከሕዝብ የሚሰበሰቡ እርዳታዎችን በመቆጣጠር፣ እርዳታውን ለሌሎች አላማዎች ማዋል፤ ለምሳሌ በትግራዩ ጦርነት ወቅትና ከጦርነቱም ማቆም በኋላ የአለም አቀፍ የምግብ ድርጅት ኢትዮጵያን መንግስት ላይ ካቀረባቸው ክሶች አንዱ ለእርዳታ የተለገሱ እህሎችን ለወታደሩ በማደልና ስንዴውንም ወደ ውጭ በመላክ እና ገበያ ላይ በማዋል እርዳታው ለተረጂዎቹ እንዳይደርስ ማድረጉን በአለም አቀፍ መድረክ የተነገረ ከባድ ወንጀል ነበር፡፡ እንዲሁም ሆን ብሎ የምግብ እጥረት እንዳለ በማስመሰል (creating artificial shortages)፣ አዳዲስ የግጭት ስጋቶችን በመፍጠር ሕዝብን ማሸበር፣ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዳይመለሱ እንቅፋቶችን በመፍጠር እና ሌሎች በ Geneva Conventions እና UN የተለያዩ ሰነዶች የተቀመጡ መስፈርቶችን በመጣስ ሕዝብን በርሃብ ውስጥ በማቆየት ለከፋ ችጋር መዳረግ ወደ ግጭት ውስጥ የገቡ የአንባገነን መንግስታት የተለመዱና አደገኛ የወንጀል አድራጎቶች ናቸው፡፡

ርሃብን እንደ መሳሪያ መጠቀም በጦርነት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ጦርነት ከመነሳቱ በፊት በሚኖሩ የፖለቲካ ፍጥጫዎች እና ከጦርነት በኋላም የአገዛዝ ሥርአቶቹ ሙሉ በሙሉ የበላይነት ያሳዩበት ሁኔታ ባልተፈጠረበት የፖለቲካ አውድ ውስጥም ርሃብን እንደ መሳሪያ ይጠቀሙበታል፡፡ ዛሬ በትግራይና በአማራ ክልል አፍጠው የሚታዩት የችጋር አደጋዎች የፖለቲካ ሃይሎች የፈጠሯቸው እና በተለይም የአገዛዝ ሥርአቱ ማህበረሰቡን በርሃብ በመቅጣት ተፋላሚዎቹን ወይም እንደ ህውሃት ያሉ ተገዳዳሪዎቹን የማዳከሚያ አንድ መንገድ አድርጎ እንደሚጠቀምባቸው ብዙ ማሳያዎችን ከጦርነቱ በፊት፣ በሁለቱ አመታት የብልጽግና መንግስት የወሰዳቸውን እርምጃዎች እና ከጦርነቱ በኋላም የተስተዋሉ ጉልህ እርምጃዎችን በመዘርዘር የአገዛዝ ሥርአቱ ርሃብን እንደ ጦር መሳሪያ የሚጠቀም መሆኑን ማሳየት ይቻላል፡፡ ህውሃት በጫካም፣ በሥልጣን ዘመኑን፣ አሁንም በክልል ገዢነት ዘመኑ ርሃብን እና ድህነትን እንደ ማፈኛ ስልት እንደሚጠቀም ታሪክን መለስ ብሎ መቃኘት ይቻላል፡፡

በዛው ልክ የአገዛዝ ሥርአቱ ብቻ ሳይሆን በዋነኝነት የህውሃት አመራሮችም የትግራይን ሕዝብ እንደ hostage ወይም ለፖለቲካ አላማ የመጠቀሚያ ምርኮኛ አድርገው በመያዝ በክልሉ ውስጥ ዛሬ እየታየ ላለው የከፋ ድህነትና ችጋር መባባስ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ መሆኑን እንዲሁ የድርህቱን የሃላ ታሪክ ጭምር እየመዘዝን ማሳየት እንችላለን፡፡ የአውሬነት ባህሪ የተላበሱት የህውሃት አመራሮች የትግራይን ሕዝብ እላዩ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቀው ደሙን እየመጠጡ ለርሃብ፣ ለእልቂት፣ ለድህነት እና መከራ የዳረጉት አልበቃ ብሏቸው ሌሎች የፖለቲካ ሃይሎችም ለህውሃት በሚሰነዝሩት ጥቃት ሁሉ ኢላማ እንዲሆን እና የበቀልና የጥላቻ ማወራረጃ እንዲሆን አድርገውታል፡፡ የትግራይ ሕዝብ በሁለት አቅጣጫ፤ አንድም ከራሱ ከህውሃት እና ሌላም ህውሃትን ኢላማ ካደረጉ ሃይሎች በሚሰነዘርበት የጭካኔ ጥቃት ክፉኛ ሲመታ፣ ሲራብ፣ ሲሰደድና ማቅ ሲለብስ ይህ የቅርቡ ክስተት የመጀመሪያው አይደለም፡፡
ሰሞንኑ ከትግራይ ሕጻጽ የሚባል አካባቢ የወጣውን አስደንጋጭ በፎቶ ግራፍ የተደገፈ የችጋር ማሳያ ምስል ተከትሎ በበይነ መረብ የተደረገውን ንቅናቄና ቁጣ ተከትሎ ከህውሃትም ሆነ ከፌደራል መንግስቱ የተሰጡት ምላሾችና እና ሁለቱም ያሳዩዋቸው እጅግ አስነዋሪና ጭካኔ የተሞላው እራስን ከተጠያቂነት የመከላከል የፖለቲካ አካሄድ ሁለቱም አካላት በክልሉ ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን መከራ፣ ርሃብና ችግር እንደ አንድ መሳሪያ እየተጠቀሙበት መሆኑን ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ እነዚህ፤ በተለይም የፌደራል መንግስቱ ሕዝብን ከርሃብና ስቃይ የመታደግ ሃላፊነቱን መወጣት ተስኖት ለነፍሳቸው ያደሩ ወጣቶች የጀመሩትን የእርዳታ ማሰባሰብ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር የሄደበት መንገድ በዛው ልክ አገሪቱ ምን አይነት ጨካኝ እና ርህራሄ የሌላቸው ፖለቲከኞች እጅ ላይ መውደቋን ማሳያ ነው፡፡

2ኛ/ ሕዝብን ለተራዘመ ግዜ በድህነት ማቆየትን እንደ መሳሪያ መጠቀም (weaponization of poverty as political strategy)

በዚህ ክፍል ስር የምናየው ደግሞ አንባገነናዊ የአገዛዝ ሥርአቶች ሕዝብን በከፋ ድህነት ውስጥ ሰንቅሮ በማቆየት የሥልጣን እድሜን እንዴት ማራዘም እና እንደ ፖለቲካ ስልት እንደሚጠቀሙበት በመጠኑ የምናይበት ነው፡፡ በብዙ የአፍሪካ አገራት እና በአንዳን የላቲን አሜሪካ አገሮች እንደተስተዋለው የሥልጣን ላይ የሚቆጣጩ የአገዛዝ ሥርአቶች እና በሥርአቶቹ ተጠቃሚ የሚሆኑ ጥቂት ልሂቃን ስልት በመንደፍና የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ሰፊውን ሕዝብ ለረዥም ጊዜ በድህነት አረንቋ ውስጥ እንዲቆይ እና ድህነቱም እንዲባባስ በማድረግ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ ህይወቱም ሆነ በፖለቲካ ብቃቱ እራሱን ችሎ እንዳይቆም፣ ሞጋች እንዳይሆን፣ አገሩን እና ርብረቱን ከዘራፊ ልሂቃን መታደግ እንዳይችል እና ሁሌም የእነሱ ጥገኛ እንዲሆን የሚጠቀሙበት ስልት ነው፡፡ ዜጎች የዕለት ጉርሳቸውን፣ መጠለያቸውን እና አንዳንድ ለመኖሩ የሚያስችሏቸውን መሰረታዊ አቅርቦቾች ከማሳደድና እነሱን ለማግኘት ደፋ ቀና ከማለት ባለፈ በአገራቸው ፖለቲካም ሆነ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ወሳኝ ሚና እንዳይኖራቸውና አቅሙንም እንዳያገኙ የማድረጊያ አዋጪ ስልት አድርገው ይወስዱታል፡፡

የዚህ ድህነትን እንደ አንድ የመግዣ መሳሪያ አድርጎ የመውሰድ/ Weaponization of Poverty የተለያዩ መገለጫዎች ያሉት ሲሆን ከብዙዎቹ ጥቂቶቹን ልጥቀስል

1ኛ/ አብላጫው የአገሪቱ ሕዝብ በአገዛዝ ሥርአቱ እና እሱ በፈጠራቸው ጥቂት ልሂቃን ባለሃብቶች ላይ ጥገኛ ሆኖ እንዲኖር ማድረግ (Manufacturing Dependence)፡፡ በዚህም የተነሳ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው የአገሪቱ ሕዝብ የመንግስት ተቀጣሪና የተረፈውን ደግሞ ጥቂት ባለሃብቶች ቀጥረው የሚያሰሩት አገልጋይ ይሆናል፡፡ ይህ የመንግስትና የጥቂት ባለሃብቶች ጭሰኛ የሆነው የአገሪቱ አብላጫ ሕዝብ ኑሮው ከእጅ ወደ አፍ ስለሚሆን ሁሌም የቀጣሪዎቹን እጅ አይቶና በእነሱ ፈቃድ ውሎ አዳሪ ስለሚሆን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ነጻነት የለውም፡፡

2ኛ/ አብላጫው ሕዝብ ልጆቹን የሚያስተምርባቸው ተቋማትም እንዲሁ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የአገዛዝ ሥርአቶቹና ጥቂት ባለባብቶች እጅ ስለሚወድቅ የትምህርት ፖሊሲዎችን ከመቅረጽ አንስቶ በመረጃ አቅርቦትም ላይ የቀጣዩትን ትውልድም እጣ ፈንታ የሚወስኑት እነሱ ይሆናል (Controlling Information and Education)

3ኛ/ የሕዝቡን የፖለቲካ ፈቃድ ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር በሚያስችል ድህነት ውስጥ የሚኖርን ሕዝብ የምርጫ ውጤትም መቆጣጠር ያስችላቸዋል (Electoral Manipulation)፡፡ ድሃው ማህበረሰብ ቤት ለማግኘት፣ ሥራ ለማግኘት፣ ወይም የያዘውን ሥራ ላለማጣት እና ሌሎች ከመንግስት እና ከአገዛዝ ሥርአቱ ደጋፊ ልሂቃን የሚያገኛቸውን ጥቅማጥቅሞች ላለማጣት ሲል በነጻነት የመምረጥ መብቱን አሳልፎ ይሰጣል፡፡ ወ/ሮ አዳነች የምርጫ ጊዜ ሲቃረብ የኮንደሚኒየም ቤቶችን ቁልፍ በኪሳቸው ይዘው እየዞሩ ላሻቸው የሚያድሉት ከዚህ አይነቱ የቁጥጥር ስልት የሚመነጭ በመሆኑ ነው፡፡

4ኛ/ የአገሪቱን የኢኮኖሚ አቅም ክፉኛ የሚያዳክሙ፣ የዜጎችን የማምረት አቅም የሚፈታተኑ፣ ጠንካራ ነጋዴዎች እንዳይፈጠሩ የሚያደርጉ፣ የአግገር ውስጥ አምራቾችን አቅም የሚጎዱ የግብር እና ሌሎች ገዳቢ ፒሊሲዎችን በማውጣት የዜጎችን በኢኮኖሚ ቶሎ የማደግ አቅም መገደብ (Stunting Economic Growth)፡፡

5ኛ/ በሰላም እጦት፣ በወንጀሎች መበራከት፣ አፈና እና ሌሎች አደገኛ የሆኑ የጸጥታ ችግሮችን ሆን ብሎ በመፍጠር ወይም ችላ ብሎ እንዲባባሱ በማድረግ ዜጎች ደህንነት እና ጥበቃ ፍለጋ የአገዛዝ ሥርአቱ ላይ ጥገኛ እንዲሆኑ ማድረግ (Social and Security Consequences) ሌላው ድህነትን ማባባሻ እና እንደ መሳሪያ የመጠቀሚያ ስልት ነው፡፡ ለዚህም ዛሬ ኢትዮጵያ የምትገኝበት ወቅታዊ ሁኔታ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ በአገሪቱ ውስጥ እየተካሄዱ ያሉ ግጭቶች፣ የዜጎች ታፍኖ መሰወር፣ የመንገዶች ለአደጋ የተጋለጡ መሆን፣ የእርስ በርስ ግጭቶች እና የታጣቂዎች መበራከት ዜጎች አንድ አፋኝም ቢሆን ጉልበት ያለው አንባገነን ሃይል መኖር ላይ ጥያቄ እንዳያነሱና እንደውም ጥገኛ እንዲሆኑ የሚያደርግ ነው፡፡

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ለብዙ አሥርት አመታት ርሃብን፣ ችጋርን እና ድህነትን እንደ አንድ ሕዝብን የማሸበሪያ፣ የማቆርቆዣና አፍኖ የመግዣ መንገድ ተደርጎ ሲተገበርባት የኖረች አገር ነች፡፡ ይህ ችግር ከእለት እለት እየከፋና መልኩን እየቀያየረ ዛሬ የደረስንበት እጅግ አደገኛና ስነዋሪ ሁኔታ ውስጥ ከቶናል፡፡ ትልቁ ነገር የአገዛዝ ሥርአቶቹ አስበውበትና ውጤቱን ፈልገውን እየተገበሩት ያለው ርሃብን፣ ችጋርንና ድህነትን እንደ መግዣ መሳሪያ የመጠቀም ስልት በግጭት ወቅት ወይም በጦርነት አውድ ውስጥ የሚፈጸም ሲሆን ደግሞ እንደ አንድ የጦር ወንጀል የሚቆጠርና በአለም አቀፍ የወንጀል ሕግም ጭምር የሚያስጠይቅ የከፋና የጭካኔ አድራጎት መሆኑን በመግለጽ ላቁም፡፡

መልካም ሰንበት!
👍2
መልዕክተ ቅዳሜ፤
ምሁርነት እና አንባገነን
Philo-tyrants
+++++

''Every tyrant fears a thinker more than any army" Voltaire

የዛሬው መልዕክተ ቅዳሜ ትኩረት በዚህ ሳምንት 75ኛ አመቱን የሚያከብረውን የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ እንግዳ ያደረጋቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባላጡት ርዕስ ምሁርን ምን ላመት ነው? በሚል ርዕስ ለምሁራን የሰጡት ማብራሪያ ቀልቤን ስለሳበኝ እና የጠቅላዩን ዲስኩር ስሰማ የ Enlightenment philosopher ተብሎ የሚገለጸው ፈረንሳያዊው ፈላስፋ François-Marie Arouet ወይም በሌላ ስሙ Voltaire ስለ ምሁርና አንባገነን የተናገረው ነገር ወደ አእምሮዮ ብቅ አለ፡፡ ቮልቴር ምንድን ነው ያለው 'አፋኝና አንባገነናዊ የሆነ ሥርአትን የጦር መሳሪያ ከታጠቀ ሃይል ይልቅ ሁሌም ስጋት ውስጥ የሚከተውና እጅግ የሚያስፈራው ምሁራኖች የሚያፈልቋቸው አዳዲስ አስተሳሰቦች፣ የሚያነሷቸው የሰሉና ጥልቅ ጥያቄዎች እና ነጻ አስተሳሰብ ነው ይላል፡፡ አዎ፤ ሁሉም አምባገነኖች እውቀትን እና ምሁራንን ይፈራሉ፡፡ አንዳንዴም ፍርሃታቸው ሲበረታ ምሁር ጠል ይሆኑና የአደባባይና ደፋር ምሁራንን ማሳደድ፣ ማዋከብ፣ ማሰር፣ ማሰደድ ሲከፋም እስከ መግደል ይደርሳሉ፡፡

አንባገነኖች እውቀትን እና በድፍረት ለእውነትና ለእውቀት የሚቆሙ ምሁራንን የሚጠሉት ያለምክንያት አይደለም፡፡ የተወሰኑትን ምክንያቶች ለማሳያነት ለመጥቀስ ያህል፤

+ የአገዛዝ ሥርአት ጥይትና ወታደራዊ ጉልበትን በማደራጀት ሕዝብን ለማፈን ሲዘጋጅ ረዘም ያለ ጊዜ ይወስድበታል፡፡ ምሁራን ግን በቀላሉ እና በአጭር ጊዜ ውስጥ በእውቀትና በምርምር የተደገፈ ሃሳባቸውን በቀላሉ በማህበረሰቡ ውስጥ በማስረጽ ህዝብን ያነቃሉ፣ ማህበረሰቡን ለእውነት እንዲወግንና ፍርሃትን እንዲያሸንፍ የመንፈስ ጥንካሬን በመፍጠርና በመገንባት ጉልበተኞችን እንዲጋፈጥ ማድረግ ይችላሉ፡፡ (Ideas vs. Bullets)

+ የአገዛዝ ሥርአቶቹ ሕዝብን በፕሮፓጋንዳ አሳስተው ለመግዛት የሚያሰራጯቸውን የውሸት መረጃዎች በእውቀትና በእውነት ላይ የተመሰረተ መርጃ በማሰራጨት ይቀለብሳሉ፣ ሕብዝን ያነቃሉ፣ የውሸት ፕሮፓጋንዳ ሰለባ እንዳይሆን የመንገስትን ውሸት በቀላሉ በማጋለጥ ገዢ ሃሳብ እንዳይሆን ያደርጋሉ፣ ሙስናን እርቃኑን ያስቀራሉ፣ የተዛቡ ትርክቶችን ያቀናሉ፣ ኢፍትሃዊነትን ያጋልጣሉ፡፡ (Exposing Lies)

+ ማህበረሰቡን በሳይንሳዊ እውቀት በመገንባት፣ በማስተማርና በማንቃት ከጨለማ ያወጡታል፣ በራሱም ህይወት ይሁን በአገሩ ጉዳይ ታዛቢ ብቻ ሳይሆን ንቁ ዜጋ እንዲሆን እና አንባገነኖች ያሰማሯቸው ካድሬዎች መናጆ እንዳይሆን ያደርጉታል፡፡ አብላጫውን የማህበረሰብ ክፍል ንቁና በእውቀት የሚመራ የማድረግ አቅም አላቸው፡፡ (Awakening the Masses)

+ በማህበረሰቡ እና በተለምይም በወጣቱ ትውልድ ላይ ምሁራን የሚያካሂዱት ስር ነቀል የሆነ የአስተሳሰብ ለውጥ በቀላሉ የማይሰበር፣ በእውቀት የተገነባ፣ ዘላቂነት ያለው ወይም የጸና እድገትና ብልጽግና እንዲመጣ ስለሚያደርግ ይህ አይነቱ ማህበረሰብ ለአንባገነኖች አይመችም፡፡ የአገዛዝ ሥርአቶች ወደ አንባገነንነት ቢቀየሩ እንኳ በእንዲህ ያለ ማህበረሰብ ውስጥ እድሜ አይኖራቸውም፡፡ ይህ አይነቱ በእውቀትና በእውነት የታነጸ ማህበረሰብ አንባገነናዊነትን ገና በእንጭጩ የማክሰም አቅም አለው፡፡ ያንን የሚፈጥሩት ደግሞ ምሁራን ናቸው፡፡ (Long-Term Instability)

ከላይ በጠቀስኳቸውን እና ሌሎች መሰል ምክንያቶች አንባገነንን ሥርአቶች ሁሌም ምሁር ጠል ወይም ምሁርን የሚፈሩ ናቸው፡፡ ሌላኛው ታዋቂ የቋንቋና ምሁርና የፖለቲካ ተንታኝ Noam Chomsky በሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ሁሌም የተማረውን የማህበረሰብ ክፍል አጥብቀው ይፈራሉ፡፡ ምክንያቱም ሁሉን ነገር በቁጥጥራቸው ሥር እንዳያደርጉ እንቅፋት ይሆንባቸዋል (those in power fear an educated populace because it makes them harder to control.) ይላል፡፡

የአንባገነን ሥርአቶች የምሁራንን እውቀት ለአገዛዛቸው አጥብቀው ቢፈልጉም ምሁራንን እና የሚያፈልቋቸውን አዳዲስ ሃሳቦች ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ስለሚቸገሩ ሁሌም ከምሁራን ጋር ያለቸው ግንኙነት በፍርሃት የተሞላ እና ጥንቃቄ የታከለበት ነው፡፡ የመጀመሪያ ጥረታቸው ሁሉንም ምሁራን በቁጥጥራቸው ሥር አውለው ማህበረሰቡን ሳይሆን እነሱን እንዲያገለግሏቸው ማድረግ ነው፡፡ ያ ከጠመንጃው ያልተናነሰ ማህበረሰቡን ለማፈን እና በግዞት ውስጥ ለማቆየት ትልቅ አቅም ይፈጥርላቸዋል፡፡ በመሆኑም ፈሪና ከሕሊናቸው የተጣሉ ወይም ሆዳቸው አገር የሆነባቸው ምሁራንን ከጎናቸው በማሰለፍ በሕዝብ ላይ የሚፈጽሟቸውን ግፎች፣ የአፈና እርምጃዎች እና ስህተቶቻቸውን ሁሉ ምሁራዊ አመክንዮ የተላበሱ ለማስመሰል ብዙ ይጥራሉ፡፡ ከሁሉም አፋኝ ሥርአት ጎን ጠመንጃ የታጠቀ ወታደር እንዳለ ሁሉ የተማሩና የተመራመሩ ሆድ አደር ወይም ፈሪ ምሁራኖችም አሉ፡፡

ሁለተኛው አምባገነኖች ምሁራንን የሚጠቀሙባቸው በማስፈራራት እና አስፈላጊም ሲሆን እርምጃ በመውሰድ ከላይ የተጠቀሱትን ምሁራዊ ሚናቸውን እንዳይጫወቱ በማድረግ እራሳቸውን ልክ አንገቷን አሸዋ ውስጥ እንደቀበረች ሰጎን ህሊናቸውን ደፍነው ከሕዝብም ሆነ ከአገዛዙ ጎን እንዳይቆሙ፣ ለአገራቸው እና ለሕዝባቸው ችግርና ጉዳይ ባዳ እንዲሆኑ በማድረግ አልሰማሁም፣ አላየሁም፣ አላወኩም፣ አይመለከተኝም ብለው በዝምታ እንዲኖሩ ማድረግ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈራረቁት አንባገነኖች ሁሉ የዛሬውን አብይ አህመድን ጨምሮ እውነት ጠል፣ ምሁራንን የሚፈሩ፣ ነጻ አስተሳሰብን የማይፈልጉ፣ ጠያቂ ትውልድ እንዳይፈጠር የሚሰጉና ነጻ አስተሳሰብን እንደ አደጋ የሚቆጥሩ ናቸው፡፡ በመኑም አብዛኛውን የአገሪቱን ምሁር አሽከርና ታዛዥ፣ ህሊናውን በሆዱ የቀየረ፣ የአገዛዞኡ ክሽፈትን በእውቀት ደጋፊ፣ ሕዝብን ለግፍና የአፈና አገዛዝ አመቻችና እጅ አሰጪ ወይም አንበርካኪ አድርገውታል፡፡ ጥቂት ደፋርና እውነቱን ሁሌም በአደባባይ የሚናገሩ ምሁራን ደግሞ እጣ ፈንታቸው መሳደድ፣ መታሰር፣ መዋከብና በድህነት መሰቃየት በመሆኑ ለአገዛዙ ለመወገን ህሊናቸው ያልፈቀደላቸው በርካቶች በዝምታ ውስጥ ተውጠው የሕዝብን መከራ ተመልካችና የመንግስትን ክሽፈት ታዛቢ አድርጓቸዋል፡፡

አብይ አህመድ እንደሌሎቹ አምባገነኖች ምሁር ጠል ወይም የአደባባይ ምሁራንን አጥብቆ ቢፈራም ህሊናቸውን ሸጠው ሲያጠፋ ከመገሰጽ ይልቅ የአጨብጫቢነት ሚና ተላብሰው የሚያዳንቁትን ምሁራን ከጎኑ አሰልፏል፡፡ ጦርነት ሲያውጅ ዘራፍ እያሉ ቀድመን እንዘምት ከሚል የውሸት ብርታት ከመስጠትም አልፈው አብረውት ቀረርቶ ያሰማሉ፣ ሰላም እፈልጋለው ያለ እለት ስለሰላም ዘማሪ ይሆናሉ፡፡ በቅርቡ በትግራይ የተካሄደውን ጦርነት ተከትሎ እነዚህ ምሁራን ጦርነቱን ከማባባስ ባለፈ የአብይ አህመድን ወንጀል ለመሸፋፈን መከፈኛ ይዘው በየሚዲያው የተሰለፉት እነሱ ነበሩ፡፡
2
ለማንኛውም እውነተኛ ምሁርነት እና አፋኝና ጨካኝ የአገዛዝ ሥርአት አብረው አይሄዱም፡፡ ምሁርና ከአንባገነናዊ ሥርአት ጋር ተዋህደውና ተስማምተው ማደር የጀመሩ ጊዜ ጠመንጃ አንግቦ ገዢዎቹን ከሚጠብቀው ወታደር የተሻለ ቦታና ዋጋ አይኖራቸውም፡፡ ወታደሩ በጥይትና በጡንቻ አፈናውን ሲያጽና ህሊና ቢስና ሆድ አደር ምሁራን ደግሞ በቃረሙት እውቀት የአፈና ሰንሰለቱን በቀላሉ የማይበጠስ ያደርጉታል፡፡ በዛሬዋ ኢትዮጵያ የእነ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ (የፍልስፍና ምሁሩ) እና የእነ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ሚና በብልጽግና ስም ኢትዮጵያን የተጣባትን የአዛዛዝና የአፈና ሥርአት እድሜ ከማራዘምና የሕዝቡንም የተጠረነፈበትን ሰንሰለት ሸክም ከማክበድ የዘለለ ሚና የላቸውም፡፡

ምሁራን የሕዝብን እውነታ ለመሸፈንና ለአገዛዝ ሥርአት ገጽታ ተጨንቀው እውነትን መከፈን ሲጀምሩ፣ ኢፍትሐዊነትን ደግፈው በአደባባይ ሲቆሙ፣ ግፍን ከመጠየፍ ይልቅ ለግፈኞች ከለላ መሆን ሲጀምሩ፣ ለአገዛዝ ሥርአቱ የአፈና እርምጃዎች አመክንዮ ለመስጠት ሲጥሩ እንደ እውቁ ፈላስፋ ፕሌቶ በአንባገነን መንግስት ፍቅር የተጠለፉ፣ ከእውቀትና እውነት ይልቅ ሥልጣንን እና የግል ጥቅማቸውን ያስቀደሙ ምሁራን Philo-tyrants ይሆናሉ፡፡ እንደ Plato አገላለጽ እነኚህ አንባገነን አፍቃሪ ምሁራን በጡንቻ ለተደገፈ ሥልጣን እራሳቸውን ባሪያ ከማድረግም አልፈው እውቀታቸውን፣ ብልሃታቸውን፣ ምሁራዊ አምክንዮአቸውን ሁሉ እርግ አድርገው በመተው ራሳቸውን ለአንባገነኖች ከማንጠፍም አልፈው ሕዝባቸውን ተነጣፊ፣ ተገዢ፣ ታዛዥና ግፍን የማይቃወም እንዲሆን እንቅልፍ አጠተው

መልካም ሰንበት!
13
አለም በጨካኝ ፖለቲከኞች እጅ፤ ሃያላን እና ግልገል Demagogue
(A Century of Demagogue Leaders)
++++++++
በቴሌግራም ለመከታተል ለምትፈልጉ፤ t.me/yaredH_2024

የዛሬው መልዕክተ ቅዳሜ ትኩረት አለማችንን እያመሱና እያስጨነቁ ያሉ እጅግ ጨካኝ፣ በደመ ነፍስ የሚጋልቡ፣ ሕግ እና ሞራል የማይገዛቸው ትላልቅ እና ግልገል አምባገነን ወይም አመጸኛ የፖከቲካ መሪዎች (Demagogue Leaders) ነው፡፡ በዚህ ርዕስ ላይ እንዳተኩር ያደረገኝ የሰሞኑ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራም የአለም አቀፍ ሕግ አይገዛኝም፣ የአሜሪካንን ሃያልነት ለማሳየት እና ጥቅማችንን ለማስጠበቅ ያሻኝን አደርጋለሁ በሚል የእብሪት እና የጭካኔ መንፈስ ተነሳስቶ አሜሪካ ውስጥ የሚገኙ ስደተኞችን ከማዋከብ አንስቶ ሉአላዊት የሆነችውን አገር ቬንዚዌላን የወረረበት፣ ፕሬዚዳቷን አፍኖ የወሰደበት፣ ከዴንማርክ ላይ ግሪንላንድን እነጥቃለሁ እያለ መፎከሩ፣ ከኔቶ አባል አገርነት ለመልቀቅ መወሰኑ እና አሜሪካ ቢያንስ ከ66 አለም አቀፍ ስምምነቶች፣ የተባበሩት መንግስታት አባልነት እና ሌሎች በርካታ አለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ ያላትን አባልነት ጭምር ለመሰረዝ ቆርጦ መነሳቱ አለም ወዴት እየሄደች ነው የሚያስብል ክስተት ሆኖ ስላገኘሁት ነው፡፡ እጅግ የሚያስፈራው ነገር የትራንፕ እብደት ብቻ ሳይሆን እንደሱ ሃያላን የሆኑ ሌሎች Demagogue የፖለቲካ መሪዎች በሃያላኑ አገራትም ጭምር መበራከታቸው እና እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሰው ሰራሽ ድህነት በተንሰራፋባቸው እና ዲሞክራሲ በተዳፈነባቸው አገሮችን ልክ የእነ ዶናልድ ትራምፕ አይነት ባህሪ የተላበሱ የአብይ አህመድ አይነት ጨካኝ እና የታይታ አምባገነኖች መበራከታቸውም ስላሳሰበኝ ነው፡፡
በመጀመሪያ Demagogue የሚለው ቃል ምንን ለመግለጽ እንደሆነ እና ይህን ባህሪ የተላበሱ ፖለቲከኞች እነማን እና መገለጫቸውስ ምንድን ነው የሚለው ነጥብ ላይ ላተኩር፡፡ ይህ ቃል ከጥንታዊ ክሪክ ሥልጣኔ ጀምሮ Cleon of Athens ለሚባሉት የሕዝብ መሪዎች ነገር ኝ አሉታዊ የሆኑ የመሪነት ባህሪዎችን የተላበሱ፣ የማህበረሰቡን ስሜት እየኮረከሩ፣ የተገፉ የማህበረሰብ ክፍሎችን ቁስል እየጎፈደሩ ሕዝብን ስሜት ውስጥ በመክተት ድጋፍ ለማግኘት የሚጥሩና ዋና መገለጫቸው ግን ጭካኔ የተሞላባቸው እርምጃዎችን በመውሰድና በሕዝብ ውስጥ ፍርሃትን በምስረጽ ሃይልን ዋነኛ የመግዣ መሳሪያቸው የሚያደርጉ የፖለቲካ መሪዎች ናቸው፡፡
በ20ኛ ክፍለዘመን ታሪክ ውስጥ ይህን ባህሪ ተላብሰው አገር ካስተዳደሩና ሕዝብን ከመሩ መሪዎች መካከል የጀርመኑ አዶልፍ ሂትለር፣ የጣሊያኑ ቤኒቶ ሞሶሎኒ፣ የቀድሞ የአሜሪካን ፖከቲከኛና ሴኔተር የነበረው ሁዪ ሎንግ እና ጠበቃና የአሜሪካ ሴኔተር የነበረው ጆሴፍ ማካርቲ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ባለንበት የ21ኛ ክፍለ ዘመን ደግሞ የአሜሪካው ዶናልድ ትራፕ፣ የሃንጋሪው ቪክቶር ኦርባን፣ የሕንዱ ናረንድራ ሞዲ፣ የእንግሊዙ ኒጌል ፍራገ፣ የእስራኤሉ ቤንጃሚን ኔታኒያሁ፣ የሩሲያው ቭላድሚር ፑቲን ዋነኛ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ እነዚህ ሃያላን የሆኑ በጭካኔያቸው እና popuist ባህሪያቸው የሚታወቁት ሃያላኖች የሚደግፏቸው ግልገል Demagogue የሆኑ የፖለቲካ መሪዎች በየቀጠናው አሉ፡፡ የእነዚህ ተላላኪና ግልገል Demagogue ፖለቲከኞች ዋነኛ ተልዕኮ በየሚገኙበት የአለማችን ቀጠና ውስጥ የሃያላኖቹን Demagogue ዎች የጂኦፖለቲካ ጥቅሞች ማስጠበቅና በዋነኝነትም የራሳቸውን ሥልጣንም በሚያስተዳድሩት አገርና ሕዝብ ላይ አጽንተው መቆየት ነው፡፡
የDemagogue ፖለቲካ መሪዎች ዋና ዋና የሚባሉት የባህሪ መገለጫዎች ከዚህ የሚከተሉት ናቸው፡፡
1ኛ/ የፖለቲካ አስተሳሰባቸውም ሆነ ምሪታቸው በሳይንሳዊ አስተሳሰብ ወይም በአመክንዮ ላይ የተመሰረተ ከመሆን ይልቅ በስሜታዊነትና ግብታዊ በሆኑ እሳቤዎች የሚነዳ (Emotional Appeals) ነው፡፡ ፍርሃትን፣ ቁጣን እና ቁጥጥርን ያማከለ አስተሳሰብ ላይ የተወሰነ ነው፡፡
2ኛ/ “እኛ እና እነሱ” ("Us vs. Them" ) የሚሉ የልዩነት ግንቦችን በመፍጠር ማህበረሰብን የመከፋፈል፣ ሙሰኛ ወይም በልዩ ሁኔታ ተጠቃሚ የሆነ የማህበረሰብ ክፍል በምፍጠርና ገሚሱን በማግለል የጋራ እሴቶችን እና አስተሳሰቦችን የሚጋራ ወጥ ማህበረሰብ እንዳይኖር ተግተው ይሠራሉ፡፡
3ኛ/ ሕዝብን ወደ ስሜት ውስጥ የሚከቱና የሚኮረኩሩ ሃሳቦችን በማንሳት ውስብስብ ለሆኑ የማህበረሰቡ ችግሮች ቀላልና ተስፋ የሚሰጡ መፍትሄዎችን አፍላቂ (Populist Promises) በመምሰል ራሳቸውን ለሕዝብ ማቅረብ፡፡
4ኛ/ የተለመዱ የዲሞክራሲያዊ ሂደተቾን እና የሕግ ሥርአቶችን በማፋለስ፣ በማንኳሰስ እና በመጣስ ሕግ የማይገዛቸው ወይም ራሳቸውን ከሕግ በላይ በማድረግ (Challenge to Rules) አለም አቀፍ ሕጎችን፣ ልማዶችን እና አሠራሮችን በመጣስ ይታወቃሉ፡፡ ለምሳሌ ሰሞኑን ዶናልድ ትራምፕ እየፈጸሟቸው እንዳሉት ሕገ ወጥ ወረራዎች እና በይፋ አለም አቀፍ ሕጎችን እና ስምምነቶችን አንቀበልም ማለታቸውን ልብ ይለዋል፡፡
5ኛ/ በአስተዳደራቸው ውስጥ ለሚገጥሟቸው ፈተናዎችና መሰናክሎች ወይም ለሚተቹባቸው መጥፎ ነገሮች ሁሉ ወይም ቀውሶች ሌሎች አካላትን በመወንጀል (Scapegoating) እና ራሳቸውን የቀላል መፍትሄዎች ብቸኛ አፍላቂ፣ መከራን አሻጋሪ፣ ተአምራዊ ለውጦችን አምጪ አድርገው ማቅረብ፣ ሁሌም የማይፈጸሙ አዳዲስና አጓጉ የስኬት እቅዶችን በማስተዋወቅ ይታወቃሉ፡፡ (በዚህ ባህሪ የኛውን አብይ አህመድን የሚስተካከላቸው ያለ አይመስለኝም)
6ኛ/ አደጋዎችን እጅግ አግዝፎ በማቅረብ ሕዝብን ሽብር እና ጥልቅ ፍርሃት ውስጥ መክተት፣ ስጋት የሚፈጥሩ አደጋዎችን ሆን ብሎም ጭምር እስከ ማቀናበር በመድረስ ማህበረሰቡ ደህንነት እንዳይሰማው የማድረግ እና ራሳቸውን አዳኝ መሲህ አድርገው እኛ ከሌለን ትጠፋላችሁ፣ እኛድ ከደገፋችሁ ትድናላችሁ የሚል የስጋት ድባብን የመግዣ ምሳሪያ የማረግ ዝንባሌ አላቸው (Fearmongering)፡፡
7ኛ/ ውስብስብ ለሆኑ አገራዊ ችግሮችን ታዕምራዊ በሆነ ሁኔታ የመቅረፍ ብልሃት፣ እውቀትና አቅም እንዳላቸው አድርገው ራሳቸውን ማቅረብ (Gross Oversimplification)፡፡ ሕዝብ እየተራበ ተአምራዊ የኢኮኖሚ እድገት አስመዝግበናል፣ ሕዝብ ሰላም አጥቶ መውጫ መግቢያ እያጣ በሰላማችን ይቀናብናል፣ የአገሬው ሕዝብ ደህንነት አጥቶ እየተሰደደ የሌሎች አገሮች አገሮች ዜጎች እኛጋ መጥተው ለመኖር እየተመኙ ነው የሚሉት የአብይ አህመድ የሕዝብን ችግርና መከራ እንደ ገለባ አቃሎ ዋጋ ማሳጣት ስልት፡፡
8ኛ/ ስሜታዊ የሆነ የሕዝብ ድጋፍን ለአጭር ጊዜም ቢሆን ለማግኘት ከማሰብ በመነጨ የማያባራ ውሸት እና የትኩረት አቅጣጫዎችን የማሳት ስልት፡፡ ቀደም ሲል የዋሹትን ውሸት ወይም ቃል ገብተው ያልፈጸሙትን ነገር በሌላ አዳዲስ ምኞቾችና ምህላዎች በመተካት ውሸትን በውሸት እየቀየሩ ሕዝብን በተስፋና በምኞት ማቆየት፡፡ የሕዝብን ቁጣ፣ ችግርና መከራ ለራሳቸው የፖለቲካ ግብ የመጠቀም ስልት (Exploitation of Grievances)፡፡
4
9ኛ/ ሁሌም ራሳቸውን ለሕዝብ የቆሙ፣ በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅና ተመራጭ እንደሆኑ አድርጎ ለማቅረብ እያንዳንዱን የሕዝብ ትኩረት ማስገኛ አጋጣሚዎችን መጠቀም፡፡ ሕዝብ በሚሳተፍባቸው ባህላት፣ አውዳመቶች፣ ልዩ ትክረት የሚያገኙ ዝግጅቶች ላይ በመገኘት ወይም ኮርኳሪ የሆኑ መልዕክቶችን በማስተላለፍ በሕዝብ አዕምሮ ውስጥ መታወስ (Folksy Posturing)፡፡ ለዚህም በየባዕላቱ የአብይ አህመድን ማዕድ ማጋራት የሚል የማስመሰል ልግስናን እና የሚያስተላልፋቸውን መልዕክቶች ልብ ይለዋል፡፡ (Rhetorical Manipulation)
10ኛ/ የሰላ ትችት የሚሰነዝሩባቸውን እና የሚያጋልጧቸውን ምሁራንን እና መገናኛ ብዙሃንን አጥብቆ ማነወር፣ መንቀፍ፣ መወንጀል እና ማሳደድ ሌላው መገለጫቸው ነው፡፡ የእውቀት ተቋማቶችን፣ የምርምር ሥራዎችን፣ ምሁራንን እና ጋዜጠኞችን ማጣጣል (Anti-Intellectualism)፤ ለዚህም ዶናልድ ትራምን ከሃያላኖቹ እና አብይ አህመድን ከግልገል አንባገነኖች መጥቀስ ይቻላል፡፡

ከላይ እንደዘረዘርኩት የ Demagogue ባህሪ የሚታይባቸው የ21ኛ ክፍለዘመን ጨካኝና አምባገነን መሪዎች እየተበራከቱ መምጣት የአለምን ሰላም እና የሰብአዊ መብቶች አያያዝን እጅግ የከፋ ሁኔታ ላይ ከመጣልም ባለፈ ሊጣሲ ይችላሉ ተብለው የማይታሰቡ አለም አቀፍ ሕጎች እየተደረማመሱና አለም ወደ ከፋ ግጭት ውስጥ እንድተገባም ሁኔታዎችን እያመቻቹ መሆኑን በሰፊው መዘርዘር ይቻላል፡፡ በአንድ መልኩ አለም መልሶ ለክ እንደ ቀዝቃዛው የአለም ጦርነት ዘመን በሁለት ትላልቅ ጎራ እየተከፈለ መምጣቱን የሚያሳዩ ምልክቶች ቢኖሩም በሌላ መልኩ ግን በሁሉም ጎራዎች ውስጥ ያሉት ሃይሎች የ Demagogue ባህሪ የተጫናቸው አስፈሪ ሃይሎች መሆናቸው የአለማችንን ቀጣዩን ዘመን እጅግ ከባድና የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመንም በብዙ መልኩ የከፋ የሚያደርገው ስለመሆኑ ከወዲሁ ብዙ ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡
ይህ አይነቱ የአለም ሃያላን አገሮች በግራም ሆነ በቀኝ በ Demagogue ፖለቲከኞች የተሞላ መሆኑ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የግጭት ቀጠና ውስጥ ለተዘፈቁ አገሮች አደጋው እጅግ በብዙ እጥፍ የከፋ ነው የሚሆነው፡፡ ወደ አገራችን ስንመለስ የኢትዮጵያው አብይ አህመድ አገሪቱን ብቻ ሳይሆን የቀጠናውን ፖከቲካ እየገፉ አደጋ ውስጥ የጨመሩበት እሳቤዎቻቸውን የመረመርን እንደሆነ መገለጫቸውና ምንጩም ይህ Demagogue የፖለቲካ መሪዎች ባህሪን በደንብ ተላብሰው የሚተውኑ ግልገል አምባገነን ወይም ጨካኝ መሪ በመሆናቸው ነው፡፡ በየጊዜው ለሕዝብ የሚገቧቸውን የውሸት ንግግሮች፣ ምኞቶች እና ከነባራዊው የአገሪቱ ሁኔታ የራቀ እቅዶች፣ በአፍሪካ ቀንድ ፖከቲካ ውስጥ እየተጫወቱት ያለው አሉታዊ ገጸባህሪ፣ በአገሮች መካከል ለመፍጠር እየሞከሩ ያሉት ቅጥ ያጣ መከፋፈል እና ግጭት፣ በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የግጭት አዙሪት ዋነኛ የማስተዳደሪያ ስልታቸው አድርገው መጠቀማቸው፣ ሕዝብን ስሜት ውስጥ ሊከቱ የሚችሉ የወደብ፣ የባህር በር፣ የአገርሉ አላዊነትና መሰል አጀንዳዎችን እንዴት እየተጠቀሙባቸው እንደሆነ ማጤት በቂ ነው፡፡ የቀጠናው አልበቃ ቡሏቸው ኤዢያ ድረስ በመሄድ ቻይና ታይዋንን ጠቅልላ እንድትገዛ ትላንት የሰጡት የድጋፍ መግለጫ በተዘዋዋሪ የዶናልድ ትራምፕን የቬንዝዌላ ወረራም ሆነ የግሪንላንድን ምኞት መደገፋቸውን ማሳያ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ዝም ብሎ የተደረገ ስሜታዊ ንግግር ሳይሆን ነገ እሳቸው ላቀዱት ሃሰብን በጉልበት ከኤርትራ ላይ የመንጠቅ አጀንዳ ከወዲሁ ድጋፍ ከሃያላኖቹ ለማግኛ የቀረበ እጅ መንሻ ለመሆኑ በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡
ለማንኛውም ዛሬ ያለንበት ዘመን የሃያላን አገሮቹ Demagogue የፖለቲካ መሪዎች እና እንደ አብይ ያሉ Demagogue የድሃ አገራት መሪዎች በባህሪም ሆነ በምግባር አንድ የሆኑበት እና እየተደጋገፉ የለምን ሰላም፣ የቆዩ አሰራሮች፣ አለማቀፍ ልማዶችና ሕጎችን ጭምር እየናዱ የአለምን ፖለቲካ አዲስ መልክ (New World Order) ለማስያዝ እየተረባረቡ ያለበት ወቅት ላይ ነን፡፡ የእስራኤል ለሶማሌላንድ እውቅና መስጠት፣ የኢትዮጵያና የአፍሪካ ህብረት ለቻይ ድጋፍ በመስጠ ታይዋንን ወራ ትጠቅልል ማለት፣ የአሜሪካና የእስራኤል ፍልስጤማዊያንን ወደ ሶማሌላንድ የማስፈር እቅድ፣ የኢትዮጵያ የወደብና የባህር በር ጥያቄ፣ የአሜሪካ የግሪንላንድ ወረራ እቅድ እና ቬንዙዌላን በቅኝ ግዛት ለማስተዳደር የመፈለኛ መሪዋን የማገት፣ የሩሲያና የዩክሬን ፍጥጫ መላ አውሮፓን ማስጨነቁና ስጋት ላይ መጣሉ፣ የ NATO መፍረክረክና አሜሪካ ከአውሮፓዊያን ጋር ያላት ግንኙነት መልሶ አደጋ ውስጥ መውደቁ፣ የኢራን የውስጥ ትርምስ፣ የተባበሩት አረብ ኢሚሬት ከሱዳን አንስታ የመን እና ሌሎች አገሮች የሚካሄዱ የተገንጣይ ቡድኖችን መደገፍና አገሮችን የማፈራረስ እቅዶች እና ሌሎች ቁልፍ የሆኑ ክስተቶችን አንድ ላይ ገጣጥሞ ማየት የግድ የሚልበት ወቅት ላይ ደርሰናል፡፡ ይህ የአለም አዲስ አቅጣጫ አንድም Geopolitical ያማከለ ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ በፖለቲካ አሻጥር እሳቤዎች (conspiracy theories) የተሞላ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ስደተኞችን በመጥላትና በማሳደድ ላይ አተኩሮ እየቀነነ የመጣውን የምዕራቡን አለም የቀኝ ፖለቲከኞች መጠናከርና መስፋፋት እንድ ጥሩ እድል ሊጠቀሙበት ያሰፈሰቡ የአብይ አህመድ አይነት የአፍሪካ አምባገነኖችን ሁኔታ በጥንቃቄ ሲገመገም አለማቀፋዊ ባህሪን ከተላበሰ አንባገነናዊነት (global totalitarian government) ጋር ያፋጥጠናል፡፡

መልካም ቅዳሜ
10👍3
ምርጫ በነጻነት ወይስ ለነጻነት? ኡጋንዳ ---- ኢትዮጵያ
+++++

የዛሬው የመልዕክተ ቅዳሜ የትኩረት ነጥብ ሰሞኑን በምርጫ ትኩሳት እየታመሰች ያለችው ኡጋንዳ እና እየቀረበ የመጣው የኢትዮጵያ ምርጫ በማሰብ ነው።

ኡጋንዳ 40 አመታት በአንድ አንባገነን የሆነ ግለሰብ እጅ እንደ ግል ንብረት ተይዛ የቆየች አገር ነች። ፕሬዚደንት ዮሪ ሙሴቪኒ በቀጠናው ከቆዩ እድሜ ጠገብ አንባገነኖች አንዱ ናቸው። በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2006 የተካሄደውን የኡጋንዳ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ በታዛቢነት የመሳተፍ እድል ገጥሞኝ ስለነበር እና ኡጋንዳ የስደት ኑሮዩን ሀ ብዬ የጀመርኩባት አገርም ስለሆነች ፖለቲካቸውን በቅር እከታተላለሁ። ባለፉት አሥርት አመታት አገሪቱ ያካሄደቻቸው ምርጫዎች በጠቅላላ ማለት ይቻላል በግጭት የተሞሉ፣ የተቃዋሚ መሪዎችና ደጋፊዎች በገፍ የሚታሰሩባቸዎ፣ ሰዎች የሚገደሉበት፣ ብዙዎች እስር፣ ወከባና እንግልት የሚያዩበት፣ ኢንተርኔት እና ሶሻል ሚዲያ ለሳምንታትና ለወራት የሚጠረቀሙበት፣ ከፍተኛ የፖለቲካ ውጥረት የሚታይባቸው ናቸው።

በቅርቡ ወደ ኡጋንዳ በተጓዝኩም ጊዜ ያናገርኳቸው የአገሬው ነዋሪዎች ከመቼውም ጊዜ በከፋ ሁኔታ ስጋታቸው ጨምሮና በአገራቸው ተስፋ ቆርጠው ነው ያገኘዋቸው። ኡጋንዶች በስደት አይታወቁም ነበር አሁን ግን ብዙዎች አገራቸውን ለቀው ለመሰደድ እንደሚያስቡ ነግረውኛል። ከዛውንቱ አምባገነን ሙሴቪኒ አሁንም ለ45ኛ አመት አገሪቱን ለመምራት ቆርጠው በመነሳታቸው ወታደሮቻቸውን አዝምተው የሚያስሩትን እያሰሩና የተወሰኑትንም ባለፉት ጥቅት ቀናት ገድለው፣ ምርጫውን በጫና እና በማጭበርበር አሸናፊነታቸውን ከትናንት ማታ ጀምሮ እያወጁ ነው።

እንግዲህ ወደዋናው ርዕሴ ስመለስ ምርጫን ነጻነት ውስጥ ሆኖ ማካሄድና ምርጫን በአፋኝ ሥርዓት ውስጥ ተሁኖ ነጻነትን ለመቀዳጀት እንደ አንድ ሰላማዊ የትግል ስልት ሲወሰድ ያለውን እንድምታ ባጭሩ ልግለጽ።

+ በነጻነት ውስጥ የሚካሄድ ምርጫ፤

ይህ አይነቱ ምርጫ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በሰፈነበት፣ ሰብአዊ መብቶች በሚከበሩበት እና የሕግ የበሌይነት በተረጋገጠበት የፖለቲካ አውድ ውስጥ የሚካሄድ ምርጫ ነው። በዚህ አይነቱ ምርጫ ሁሉም ተፎካካሪዎች እኩል ተጻነትና መብት አላቸው። የመወዳደሪያው መድረክ ለሁሉም እኩል ነው እድልችን የሚፈጥረው። መበላለጥም ካለ በራሳቸው በእጩዎቹ አቅም ውሱንነት እንጂ በምህዳሩ አይደለም። በነጻነት በተሞላ አውድ ውስጥ የሚካሄድ ምርጫ በመሆኑ አንዳንድ ጉድለቶች ቢታዩም የምርጫ ሂደታቸው ሁሌም ነጻ፣ ፍትሀውና ሰላማዊ ነው።

+ ነጻነትን ለመቀዳጀት የሚደረግ ምርጫ

የዲሞክራሲ ባህል ባልዳበረባቸው፣ አምባገነን ሥርዓቶች በተንሰራፉባቸው፣ የሕግ የበላይነት በጠፋበት፣ አፈና እና ግፍ በጸኑበት የፖለቲካ አውድ ውስጥ የሚካሄዱ ምርጫዎች ተቀዳሚ ግባቸው ሕዝብን ከአፈና እና ከግዞት በማላቀቅ የነጻነቱ እና የሥልጣን ባለቤት እንዲሆን ማድረግ ነው። ይህን ያልተረዱ አንዳንድ ተፎካካራ ፖርቲዎች ትግሉን ከሥልጣን መወጣጫነት የዘለለ ትርጉም ስለማይሰጡት በየአምስ አመቱ ካደፈጡበት ብቅ ብለው ይንደፋደፉና ብዙዎችን አሳስረው፣ አስገድለው፣ ለወከባ አጋልጠውና ራሳቸውንም አደጋ ላይ ጥለው በምርጫ ማግስት መልሰው ወደ ምሽጋቸው ይከታሉ። የተሳካላቸውም ምክር ቤት ገብተው ደሞዛቸውን የትግላቸው ውጤት ያደርጉታል።

ኡጋንዳን አንድ አምባገነን ተንሰራፍቶ አራት አሥርት ያስተዳደረበት ዋነኛ ምክንያት ፖለቲከኞቹ ትግሉን ሕዝብን የነጻነትና የሥልጣን ባለቤት ለማድረግ ሳይሆን በሙሴቪኒ እግር እራሳቸውን ለመተካት የተለሙ በመሆናቸው ነው።

ወደ ኢትዮጵያ የተመለስን እንደሆነ ባለፉት አርባ አመታት ከኡጋንዳ እኩል ምርጫዎችን አካሂደናል። መለስን በሞት እኔ ጏይለማርያመን በበቃኝ የተገላገልን ቢሆንም ከአንባገነናዊ ሥርዓት ሳንላቀቅ እና የኢትዮጵያም ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት ሳይሆን ይሄው ሌላ የነጻነት ትግልን የሚጠይቅ ምርጫ ከፊታችን ተደቅኗል።

የዛሬዋ ኢትዮጵያ ጨካኝ የሆነ አምባገነን የተጣባት፣ በጦርነት የምትታመስ፣ ተቃዋሚ ፖርቲዎች በነጻነት በመላ አገሪቱ መንቀሳቀስ የማይችሉበት፣ የመደራጀት፣ የመሰብሰብ፣ ሃሳብን፣ ነጻነት የመግለጽ መብት የጠበበበት እና የአገዛዝ ሥርዓቱ የአገሪቱን ሀብት እና መገናኛ ብዙሀንን ተቆጣጥሮ ፈላጭ ቆራጭ በሆነበት አውድ ውስጥ እንገኛለን።

እንደ እኔ የኢትዮጵያ ሕዝብ መታገል ያለበት እላዩ ላይ የተጫነውን ጨካኝ፣ አፋኝ እና ደካማ የብልጽግና አስተዳደር በሕዝባዊ እምቢተኝነት አንበርክኮ አገሪቱ ወደ ተረጋጋ ሰላማዊ የሽግግር ሥርዓት የምትሻገርበትን ትግል ነው። ይህም ካልሆነ መጪው ምርጫ ለነጻነት የሚደረግ እንጂ ተቃዋሚዎቹን የፖርላማ ወንበር ለማስይዝ መሆን የለበትም።

መልካም ሰንበት!
10🔥2
መልዕክተ ቅዳሜ፤

War Hawks ልሂቃን እና ጦር ሰባቂ ፖለቲከኞች፤
++++++

ጦር ሰባቂ፣ ግጭት ጠማቂ፣ በትንሽ በትልቁ ጉልበታቸውን መፈተን የሚፈልጉ የፖለቲካ መሪዎች ባሉበት አገር war hawks (ጦርነት ቀስቃሽ እና ግጭት አራጋቢ) ልሂቃን ሲኖሩ ያ አገር መቸም ቢሆን ሰላም አይኖረውም፡፡ ኢትዮጵያ ዛሬ የገጠማት ፈተና ይሄው ይመስለኛል፡፡ የአገሪቱ ፖለቲከኞች በተለይም በሥልጣን ዙሪያ ያሉት፤ የሄዱትንም ሆነ ያሉትን ጨምሮ ጦርነትን የችግር ሁሉ መፍቻ፣ ጠላቶቻቸውን ማጥፊያ ወይም ማንበርከኪያ፣ ጉልበታቸውን መፈተሻ እና ሥልጣናቸውን ማራዘሚያ አድርገው ስለሚቆጥሩ በትንሽ በትልቁ ይዋጣልን ማለት መለያቸው ነው፡፡ ይህን የፖለቲከኞቹን እብደት የሚያባብሱ እና ትንሽ ኮሽ ባለ ቁጥር ሰላምን፣ ውይይትን እና ድርድርን ከመስበክ ይልቅ ጎራ ለይተውና አንድ ወገን ይዘው ግጭትን የሚያራግቡ፣ ፖለቲከኞችን ለግጭት የሚያደፋፍሩ፣ የሚያበረታቱ፣ በሃሳብ፣ በገንዘብና በእውቀት ግጭትን የሚደግፉ ልሂቃን ቁጥራቸው በርከት ሲል ደሞ የሰላም ድምጾች ይታፈናሉ፡፡

ኢትዮጵያ ዛሬ የገጠማት ፈተና በአንድ ወገን ያለጦርነት ፖለቲካ መስራት የማይችሉ እና ግጭትን ዋና የፖለቲካ መሳሪያቸው ያደረጉ የህውሃት እና የብልጽግና መሪዎች፤ በሌላ በኩል ደግሞ ዳር ቆመው የእሳቱን ወላፈን በርቀት እያዩ ህውሃትን ወይም አብይን ደግፈው ግፋ በለው እያሉ ጦርነትን የሚያራግቡ እና የሚያበረታቱ ልሂቃን በሌላ ጫፍ ሆነው አገሪቱ ማባሪያ በሌለው ግጭት ውስጥ እንድትማቅቅ እያደረጓት ነው፡፡ ስለ ጦረኞቹ ፖለቲከኞች ብዙ ጊዜ ደጋግሜ ስለጻፍኩና ስለተናገርኩ የዛሬ ትኩረቴ War Hawks ልሂቃን ላይ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ የተካሄዱ ጦርነቶች ወይም ግጭቶች እና አሁንም በመካሄድ ላይ ያሉ ጦርነቶች ከፍተኛ ቁጥር ያለው ልሂቃን ድጋፍ የተቸራቸው ናቸው፡፡ ከዩንቨርሲቲ ፕሮፌሰሮች አንስቶ በርካታ ምሁራን፣ ቄሱ፣ ሼሁ፣ ፓስተሩ፣ የአገር ሽማግሌው፣ ባለሃብቱ፣ ጋዜጠኛው እና የማሕበረሰብ አንቂ የሚባሉት ሳይቀሩ ፖለቲከኞች እርስ በርስ መነጋገር እና ሥልጡን ፖለቲካ መስራት አቅቷቸው ልዩነታቸውን በጡንቻና በአፈሙዝ ለመፍታት ሲሰናዱ የዘረዘርኳቸው ልሂቃን ሰልፋቸውን አሳምረው ከአንዱ ወይም ከሌላው ተፋላሚ ፖለቲከኛ ጀርባ ሆነው ጦርነቱን በቃላት ከመቀላቀል አልፈው ይባርካሉ፡፡ ግጭት አባባሽ የሆኑ ትዕርክቶችን፣ ትንታኔዎችን፣ አመክንዮዎችን፣ ማበረታቻዎችን ይዘው ከየመሸጉበት ጉድጓድ በመውጣት ከፖለቲከኞቹ ጎን ይቆማሉ፡፡ በዚህ የተነሳ ጸባችን ሁሌም መራር፣ ቶሎ የማይበርድ፣ ብዙ ደም አፋሳሽ እና አገር አውዳሚ የሚሆነውም ለዚህ ይመስለኛል፡፡

ጦርነት አያስፈልግም፣ አያዋጣንም፣ አንተም ተው አንተም ተው፣ ሰላም ይስፈን የሚሉ ድምጽች ይታፈናሉ ወይም ጥቂት ከመሆናቸው የተነሳ አድማጭ የላቸውም፡፡ በመንጋ ልሂቃን እና በጦረኛ ፖለቲከኞች ጩኸት የሰላም ድምጾች ሁሉ ይዋጣሉ፡፡ እንዴት አንድ የዩንቨርሲቲ ፕሮፌሰር፣ እንዴት አንድ በእውቀት ዘልቆ የተማረ ሰው፣ እንዴት አንድ የሃይማኖት አባት፣ እንዴት አንድ የአገር ሽማግሌ፣ እንዴት አንድ ባለሃብት፣ እንዴት አንድ ጋዜጠኛ፣ እንዴት አንድ የሲቪክ ማህበር መሪ ጦርነትን ደግፎ ከከሸፉ ፖለቲከኞች ጎን ቆሞ ግጭትን ያራግባል???

የዛሬ አምስት አመት በህውሃት እና በፌደራል መንግስቱ በኩል ጦርነቱ እንደተጀመረ ቁጥሩ ቀላል የማይባል ከሊቅ እስከ ደቂቅ ያለ ልሂቃን ዋና የጦርነቱ አራጋቢ በመሆን አገሪቱን ቢያንስ ከግማሽ ሚሊዮን ሰው በላይ ላሳጣት ጦርነት ትልቁን አስተዋጽዎ አድርጓል፡፡ ከፕሮፌሰሮቹም፣ ከቄሶቹም፣ ከሼሆቹም፣ ከባለሃብቱም፣ ከብዙ ጋዜጠኞችና የሲቪም ማህበራት መሪዎች ይልቅ አንድ ታሪኩ ጋንኪሴ (ዲሽታ ጊኔ) ተሽሎ ሰው ሆኖ ቢገኝም አሳዳጁ በዝቶ መከራውን አይቷል፡፡ ጦርነቱ እንደተጀመረ ሰሞን የዛሬው የብልጽግና የደህንነት ቢሮ ሃላፊ የሆነው እና ያኔ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ የፖለቲካ አማካሪ መሰለኝ የነበረው አቶ ሬድዋን ሁሴን አገር በቀል የሲቪክ ማህበራትን በኤሊያና ሆቴል ሰብስቦን የተናገረን ነገር ትዝ አለኝ፡፡ መንግስት ሕግ ለማስከበር ህውሃት ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን አውቃችሁ ከዛሬ ጀምሮ ይህን ሕገወጥ አካል ጁንታ ብላችሁ እንድትጠሩት እና ሽብርተኛ ስለሆነ መንግስት የሚፈጽመውን እርምጃ ያለምንም ማቅማማት እንድትደግፉ ነው የጠራናችሁ አለን፡፡ እኔ ይህን ንግግሩን እንደሰማው ከግማሽ ሰአት በላይ ሳልቆይ አዳራሹን ጥዬ ወጣሁ፡፡ እጅግ በርካታ የሚባሉ የሲቪክ ማሕበራት መሪዎች፤ የሰብአዊ መብት ድርጅቶችን የሚመሩ ሳይቀሩ አዳራሽ ውስጥ እየፎከሩ እንዝመት፣ ህውሃትን እናወግዛለን፣ ከመንግስት ጎን እንቆማለን የሚሉ መፈክር አዘል ንግግሮችን ያሰሙ ነበር፡፡ ልክ የፕሪቶሪያ ስምምነት ሲፈረም ደግሞ እነዚሁ ሰዎች ዋና የሰላም ሰባኪ መስለው ነጭ እርግብ ይዘው ተከሰቱ፡፡

አሁንም ሰሞኑን የተጀመረውን ግጭት ተከትሎ እነዚሁ War Hawks ልሂቃን ከያሉበት እየወጡ ፍለጠው፣ ቁረጠው፣ በለው ማለታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ባለፈው ጦርነት ከሃሰት የፕሮፓጋንዳ ወሬ ከመፈብረክ አንስቶ ግጭቶቹን በማባባስ ትልቅ ሚና የተጫወቱት ልሂቃን መካከል የላቀ የውሸት እና የጥላቻ የፕሮፖጋንዳ አበርክቶ ላደረጉት ሰዎች በሰላሙ ጊዜ የመከላከያ የክብር ኒሻን ሽልማትና እውቅና ተበርክቶላቸዋል፡፡ አንዳንዶቹ በጦርነቱ ወቅት የዶ/ር ደብረጽዮን አንገት ተቆርጦ የሆነ ቤተክርስቲያን ውስጥ መገኘቱን አረጋግጠናል ብለው ሰበር ዜና የሰሩ ሰዎች ዘንድሮ ምን ይሉን ይሆን?

ለማንኛውም ልሂቅም የፖለቲካ መሪም የከሸፈበት አገር መከራው ብዙ ነው፡፡ ልሂቅም ፖለቲከኛውም ጽብ አጫሪ፣ ግጭት ጠንሳሽና ጸረ ሰላም በሆነበር አገር የግጭት አዙሪት አይበጠስም ይከራል እንጂ፡፡ ኢትዮጵያ እጅግ ጨካኝና አምባገነን በሆነው አብይ አህመድ፣ ከታሪክና ከውድቀታቸው በማይማሩ ጨካኝ የህውሃት መሪዎች እና War Hawks ልሂቃን እጅ እስካልወጣች ድረስ ሚሊዮኖች በጦርነት ያልቃሉ፣ ሚሊዮኖች ከቅያቸው ይፈናቀላሉ፣ ሚሊዮኖች የአካል ጉዳተኞች ይሆናሉ፣ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች እና ሕጻናት የወሲባዊ ጥቃት ሰለባ ይሆናሉ፣ ከጦርነት የተረፉና ያመለጡ ወጣቶች አገራቸውን ጥለው ይሸሻሉ፣ የአገር ሃብት ይወድማል፡፡

እንግዲህ ለፖለቲከኞችም ሆነ ለWar Hawks ልሂቃን ልቦና እስኪሰጣቸው ድረስ የኢትዮጵያ ሕዝብ እናንተ ጠንስሳችሁ በምታቀጣጥሉት ጦርነት ውስጥ እራሴንም ሆነ ልጆቼን አልማግድም በማለት በአንድ ድምጽ እምቢኝ ለጦርነት! ጦርነት በቃኝ1 የግፍ አገዛዝ በቃኝ! ብሎ በመነሳት ሊታገላቸው ይገባል፡፡

መልካም ሰንበት!
16👍2
የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታ መነሻ በማድረግ የተዘጋጀ የሰላማዊ ሕዝባዊ ንቅናቄ የትግል ጥሪ ሰነድ።
1
መልዕክተ ቅዳሜ

በቅጥፈት አገር አይመራም! የአገር መሪ pathological liar ሲሆን፤
++++++

"... አብይ አህመድ፤ አንዳንድ ጊዜ ፈጣሪም መሆን ያምርሃል፣ አገሪቱን ልክ እንደ አውሎ ንፋስ ውሸት በተንክባት፣ በጣም ያስናል፣ የእናቶች ግፍ ይድረስብህ" አንዲት ስማቸው ያልተጠቀሰ እናት የተናገሩት

እንደምን ከርማችኋል የመልዕክተ ቅዳሜ ታዳሚዎች፡፡ የዚህን ሳምንት መልዕክቴን በተለመደው ሰአት ባለማድረሴ ይቅርታ እየጠየኩ ጨርሶ እንዳልተወው የሚያደርግ ነገ ስለገጠመኝ በእሁድ ምድር ብቅ ብያለሁ፡፡ ከአንድ አመት በፊት ይመስለኛል አብይ አህመድ እየደጋገመ የኢትዮጵያ እናቶች ይጸልዩልኛል ይል ስለነበር የትግራይ እናቶች በጦርነት ያለቁባቸውን ልጆቻቸውን መርዶ ተነግሯቸው በየሜዳው እየተንደባለሉ፣ ደረታቸውን እየደቁ፣ ማቅ ለብሰው ሲያለቅሱ በዛው እለት አብይ ምንም እንዳልተፈጠረ የሚሰራቸውን ፕሮጀክቶች እያስመረቀ ሳይ "የኢትዮጵያ እናቶች እያለቀሱብህ ነው፣ እየረገሙኽ ነው፣ እያዘኑብህ ነው" ብዮ ጽፌ ነበር፡፡ ዛሬ አንዲት እናት በአጭር ቪዲዮ ያስተላለፉትን እና የአብይን pathological liar ተብሎ ሊያስፈርጀው በሚችል መልኩ ፓርላማ ውስጥ ያደረገውን ቅጥፈትና ማጭበርበር ሳስብ የተውኩትን መልክዕክተ ቅዳሜ ልጭር ተነሳሁ፡፡

እኚህ ጀግና እናት በአጭር የቪዲዮ መልዕክታቸው እጀግ እያዘኑ እና እየተማረሩ ባስተላለፉት አጭር መልዕክት ውስጥ ቀልቤን የሳበው "... አብይ አህመድ፤ አንዳንድ ጊዜ ፈጣሪም መሆን ያምርሃል፣ አገሪቱን ልክ እንደ አውሎ ንፋስ ውሸት በተንክባት፣ በጣም ያስናል፣ የእናቶች ግፍ ይድረስብህ" በማለት የአብይን ከዝናብ እያዘነብኩ ነው እስከ ሰሞኑ ያለውን የፓርላማ ቅጥፈቱን በመጥቀስ በተማረረ ስሜት እርግማናቸውን አውርደውበታል፡፡

ዛረ በአብይ አህመድ ቅጥፈት፣ በፈጸማቸው እጅግ አስከፊና ሰቅጣጭ ወንጀሎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን እናቶች ማቅ ለብሰብ ደም እንባ እያለቀሱ ነው፡፡ በጦርነቶች ልጆቻቸው የነጠቃቸው እናቶች፣ በድሮን ሙሉ ቤተሰቦቻቸውን የፈጀባቸውና ንብረታቸውን ያወደመባቸው፣ ቤታቸውን አፍርሶ በየሜዳው የጣላቸው፣ ቀያቸውን የጦር አውድማ አድርጎ በየመጠለያ ካምፑ አጉሮ የረሳቸውና በርሃብ አለንጋ የሚቀጣቸው ኢትዮጵያዊ አናቶች ደም እምባ እያለቀሱ ሲረግሙት ውለው ሲረግሙት እያደሩ ነው፡፡ ከላይ የጠቀስኳቸው እናት እንዳሉት የእናቶች ግፍ ይድረስብህ ከማለት ሌላ ምን ይባላል፡፡

ለማንኛውም አንድ የአገር መሪ የሆነ ሰው pathological liar ወይም ቅትፈትና ውሸት ብቸኛ መገለጫ ሲሆን ሊፈጠሩ የሚችሉትን አንዳንድ ነገሮች ልጥቀስ፡፡

Pathological liar ወይም የስነልቦና አጥኚዎች Pseudologia fantastica ብለው የመዋሸት በሽታ እንደ ስነልቦና ህመም የሚወሰድ ሲሆን ሰቦች ማቆሚያ የሌለው ውሸት በመናገር የሆነውን እንዳልሆነ ያልሆነውን እንደሆነ አድርገው የውሸት ታሪክ በመፍጠር ሰዎችን ለማሳመን፣ የሰዎችን አትኩሮት ለማግኘት፣ የራሳቸውን ego ለማስተንፈስ አንዳንዴ መዋሸታቸው ለራሳቸውም ጭምር በማይታወቃቸው ደረጃ አዕምሯቸው የውሸት ታሪኮችን የሚያመርት ወደ በሽታ የተጠጋ ወይም በሽታ የሆነ እና ሕክምና የሚፈልግ ነገር ነው፡፡ ይህ በውሸት የተሞላ የባህሪ መገለጫ አሉት፡፡ ከብዙ በጥቂቱ፤
+ የሚያቀርቧቸው ውሸቶች እውነተኛ ታሪክ ወይም ክስተት ላይ ያተኮሩ እና ከፌል እውነታዎችን መነሻ ያደረጉ ናቸው፡፡ በዛም የተነሳ እጅግ ጥልቅና ዝርዝር ነገሮችን የካተቱ (highly detailed) እና dramatic በሆነ አቀራረብ ስለሚገልጿቸው ብዙ ሰዎችን በቀላሉ ማሳመን ይችላሉ፡፡
+ ውሸቶቹ Causes and Motivations ያላቸው በመሆናቸው ሊያሳኩት የሚፈልጉት ግብ ስላላቸው በእያንዳንዱ ክስተት ላይ ተመርኩዘው የሚቀርቡ ናቸው፡፡ የራስን ስብዕና አሳምሮና አሳብጦ ለማቅረብ፣ ያልሰሩትን ሰሩ ተብሎ ለመመስገንና ውዳሴን ከመሻት፣ ጀግና ለመባልና መስሎ ለመታየት የሚደረጉ ውሸቶች ሲሆኑ ብዙውን ጊዜ በማንነት ቀውስ (personality disorders) ከገጠማቸው ሰዎች ጋር የሚያያዝ ባህሪ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ narcissistic ባህሪ ያላቸው ሰዎች ላይ የሚከሰት ችግር ነው፡፡
+ ብዙውን ጊዜ በሚናገሩት ነገሮች ውስጥ ዝርዝር ነገሮችን በማንሳት ታሪኩን አሳማኝ ለማድረግ ቢሞክሩም ለውሸቶቻቸው ማስረጃ ማቅረብ ስለማይችሉ በአንድ ጉዳይ እንደ ወቅቱና እንደሚናገሩበት አውድ አሥር አይነት የቅጥፈት ታሪክ ሊናገሩ ይሰማሉ፡፡

አብይህ አህመድ እንደ እኔ ትዝብት ከሆነ personality disorders ወይም ከራስ ማንነት ጋር የተያያዘ ቀውስ የቀጠመው narcissistic ባህሪ የተላበሰ pathological liar ሊባል የሚችል የአገር መሪ ነው፡፡ አንድ አገር በእንዲህ አይነት የታወከ ሰው እጅ ስትወድቅ ምን ልትመስል እንደምትችል ለማወቅ የዛሬዋ በግጥቶች የተሞላች፣ ዜጎቿ የሚሰቃዩባትና የሚሳደዱባት፣ ዙሪያዋን በጠላት የተከበበች መጻጉ አገር ኢትዮጵያን ማየት በቂ ነው፡፡

አብይ ባለፉት 7 አመታት ቁልፍ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ከተናገራቸው በርካታ ነገሮች ውስጥ የሚያመዝኑት ንግግሮቹ በተለይም በኢኮኖሚ፣ በሰላም፣ በአገሪቱ ውስጥ በተካሄዱት ጦርነቶች ዙሪያ፣ ስለመንግታቸው የጦር አቅም፣ ስለሚሰሩት የፕሮጀት ሥራዎች፣ በዲፕሎማሲው እና ሌሎች ዘርፎች ከተናገራቸው ነገሮች ውስጥ አዘምዝኙ በውሸት የተሞሉ ብቻ ሳይሆኑ በአንድ ጉዳይ ላይ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ውሸቶችን በመናገር ሪኮርድ የሰበረ pathological liar ነው ማለት ይቻላል፡፡

አንድ ሰው አንድ ጊዜ ወይም ሁለት ጊዜ በመዋሸት ሊያታልል ይችላል፡፡ ነገር ግን አሥር ጊዜም ሲዋሽ አሥር ጊዜ የሚታለል ሰው ካለ፤ ዋሺው ብቻ ሳይሆን የስነ ልቦና ችግር የገጠመው ሁሌም በውሸቱ የሚታለለውም ሰው ችግር የገጠመው ነው ማለት ነው፡፡ የገዢዎችን ሁሉንም አይነት ቅጥፈት እና የማጭበርበሪያ ወይም የማደናገሪያ የውሸት ታሪኮችን ሁሉ አምኖ መቀበት (blindly accepting falsehoods) በአንድ አገር ውስጥ እየቆየና እየደነደነ ሲመጣ ለአፋኝና አንባገነናዊ መሪዎች አይንን ጨፍኖ የመገዛትን ልምምድ ወይም ባህል (Blind Obedience to Authority) ያመጣል፡፡ ያ ደግሞ አብዛኛው ሕዝብ ከመንግስት የሚመጡ መረጃዎችን ያለምንም ተጠራጣሪነት እና ያለምንም ጠያቂነት አምኖ እንዲቀበል ያደርጋል፡፡ ያ ደግሞ ታዋቂም ተመራማሪ አልበርት አንሽታይን እንዳለው መሪዎቹም ተመሪዎቹም "the greatest enemy of truth" ይሆናሉ ማለት ነው፡፡

በቅጥፈት አገር አይመራም፡፡ በቅጥፈት ዘላቂ የዲፕሎማሲ ስኬት አይገኝም፡፡ በቅጥፈት አገር ሰላም አይሆንም፡፡ በቅጥፈት ጥሩ ጎረቤት አይፈራም፡፡

መልካም ሰንበት!
12
የዚህ አጭር ጽሑፍ ዓላማ በቅርቡ “የግፍ አገዛዝ ይብቃ፣ በምርጫ ካርድ ግፍን አላጸናም” በሚል ርዕስ ለንባብ ያቀረብኩትን 29 ገጽ ጽሑፍ ተከትሎ የተለያዩ አስተያየቶችና ሃሳቦች ሲንጸባረቁ ቆይተዋል፡፡ ምርጫው ላይ እቀባ ማድረግ በፍጹም ትክክል አይደለም፣ ኢ-ዲሞክራሲያዊ ነው የሚሉና ምርጫውን በጥቅሉ ከመቃወምና፤ ጠቅላላ እቀባ ከማድረግ ይልቅ በምርጫው በመሳተፍ፣ ሂደቱን በቅርብ እየተከታተሉ፣ ኢ-ፍትሐዊነትና ነጻነት የጎደለው መሆኑን ሲያረጋግጡ የድምጽ መስጫው ጊዜ ሲቃረብ መሳተፉን አቁሞ ወደ እቀባ መሄድ ይሻላል የሚሉ ሃሳቦች ከተለያዩ አካላት ተንጸባርቀዋል፡፡
የእኔ ከምርጫው ሙሉ በሙሉ በመታቀብ የአገዛዝ ሥርአቱ ላይ ጫና መፍጠር የሚችል የሕዝባዊ እምቢተኝነት ንቅናቄ ማድረግ ይበጃል ከሚለው ሃተታ አዘል የትግል ጥሪ ይፋ ከተደረገ በኋላ በምርጫ እቀባ ዙሪያ የተንጸባረቁ የተቃውሞም ሆኑ የድጋፍ ሃሳቦች በጥንቃቄ የተከታተልኳቸው ሲሆን አንዳንዶቹም ለእኔ ጥሪ የተሰጡ ምላሾች መስለው ስላገኘኋቸው የምርጫ እቀባ ምን ማለት ነው? መቼ እና በምን ወቅቶች ላይ ነው ሊካሄድ የሚችለው? እንዴትና ምን አይነት ስልቶችን ነው መከተል የሚገባው? እንዲሁም ለምን አላማ ሲባል ነው የምርጫ እቀባ ንቅናቄ የሚያስፈልገው? የምርጫ እቀባን እና ሰላማዊ ሕዝባዊ እምቢተኝነትንስ የሚያገናኛቸው ምንድን ነው? የሚሉትን ጥያቄዎች መመለስ አስፈላጊ ሆኖ አገኝቸዋለሁ፡፡
7
መልዕክተ ቅዳሜ፤

አፈሙዝ ወደ መሬት!
++++

የዛሬው መልዕክተ ቅዳሜ በትንታኔ የተደገፈና ማብራሪያም የሌለው አጭር ልመና አዘል የሰላም ጥሪ ነው።

ውድ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ፤ አገርህ እጅግ ጨካይ በሆኑ እኩይ ፖለቲከኞች እጅ ከወደቀች አመታት ተቆጠሩ። የዛሬዎቹ በግራና በቀኝ የተሰለፉት የሥልጣን ጥም ናላቸውን ያናወዛቸው የፖለቲካ ነጋዴዎች ዳግም ማቆሚያ የሌለው ግጭት እየጠመቁ ሞትህን፣ እልቂትህን፣ ውድመትህን እየደገሱልህ ነው። ከዛሬ ነገ በተፋላሚ ሃይሎች መካከል የሰላም፣ የእርቅና የድርድር መንፈስ ወርዶ ጦርነቶቹ ይነጥፋሉ፣ የንጹሐን ዜጎች ሞት ይቆማል ብለህ ስትጠብቅ ይሄው ሌላ ማቆሚያ የማይገኝለት እስከ ዛሬ ካየኸውም በጭካኔም፣ በእልቂትም ሆነ በሃብት ውድመት እጅግ የሚያስንቅ ጦርነት ሊከፈቱ ከሁሉም አቅጣጫ ፊሽካ እየተነፋ ነው።

ነውር የማይነጥፍባቸው የቀነጨሩ ልሂቃንም (ምሁራን፣ ከበርቴዎችና አንቂ ተብዬዎች) ከግራና ከቀኝ ተሰልፈው ያበዱትን ፖለቲከኞች ጃስ ኩቲ እያሉ ለእልቂት እያበረታቷቸው ነው። እነኚህ privileged elites ጦርነትን የሚሰብኩትና ብቸኛ የችግር መፍቻ አድርገው የሚደሰኩሩትን ያህል አንዳቸውም ወላፈኑ በራሳቸው ሆነ በቤተሰቦቻቸው አይደርስባቸውም። ከግማሽ ሚሊየን በላይ ዜጎችን የጨረሰውና በፕሪቶሪያ ስምምነት የተቋጨው የእርስ በእርስ ጦርነት ለአገዛዙ፣ በተቃርኖ ለቆሙት የህውሃት ጏይሎችም ሆነ ሁለቱንም ደግፈው ለቆሙ ልሂቃን ትምህር አልሆናቸውም። የሞትክም፣ ልጆችህንም ያጣህም፣ መንደርህ በቦንብና በድሮን ጥቃት የጋየብህም፣ የተፈናቀልክም፣ የተሰደድክም፣ ሃብትህ የወደመብህም አንተ ነህ። ጦርነቱን ያስጀመሩ፣ ለመጀመሩ ምክንያት የሆኑ፣ የቀሰቀሱ፣ ባንተ ሞት የተማማሉና የዶለቱት የፖለቲካ ነጋዴዎች ግን ከሚጠጡት ቡና ላይ እንኳ አንድ ማንኪ ስኳር አልጎደለባቸውም።

ዛሬም ሞትህን እያዘጋጁልህ ነው። አስሬንህን ከየሜዳው የሚለቅም የተራበ ጩልፊት አሞራ በላይህ ላይ እያንጃበበ ነው። በአማራ ክልልና በኦሮሚያ ክልል የሚካሄዱ ጦርነቶች ተባብሰው በቀጠሉበት በዚህ ወቅት አንባገነኑ እና ጨካኙ አብይ አህመድ ሌላ ጦርነት በማዶ ከቆሙት የጨካኝ ጨካኝ ከሆኑት ከህውሃትና ከሻቢያ ጋር ሊጀምር ሠራዊቱን አሰልፏል። በዛኛውም አቅጣጫ እንዲሁ።

ውድ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ፤ ከእንቅልፍህ ንቃ። ጦርነት አልፈልግም፤ በስሜና በአገር ሉዓላዊነት ማስጠበቅ ሽፋን የሚካሄዱትም ጦርነቶች የእኔ ስላልሆኑ በአፋጣኝ ይቁሙ በል! የግፍ አገዛዝም በቃኝ! ብለህ ተነስ።

ትላንት ልጆችህንና ንብረትህን ነው ያሳጡህ። ነገ አገር አልባ ያደርጉሀል። አገርህን ለእብድ፣ ጨካኝ እና ጦርነት ጠማቂ ፖለቲከኞች ትተህ የጥፋትህ ጎርፍ ጠራርጎ እስኪወስድህ አትጠብቅ፣ ተመልካችም መሆንህን አቁም! እምቢኝ ለጦርነት! እምቢኝ ለግፈኞች! እምቢኝ ለእርስ በርስ እልቂት! ብለህ ባለመተባበር ብቻ አይደለም ጦርነትን በመቃወም እና የሰላም ድምጽ በመሆን ቁጣህን ግለጽ።

መልካም ሰንበት!
15
መልዕክተ ቅዳሜ፤

መንግስታዊ መክሸፍ (Governance failure)
++++++
በቴሌግራም ለመከታተል፤ https://t.me/yaredH_2024

በዛሬው መልዕክተ ቅዳሜ አንድ ሀገር በከሸፈ ወይም አገር የማስተዳደር ብቃት ባጣ ጏይል እጅ ሥር ስትወድም ምን ልትመስል እንደምትሽል የብልጽግናን አቋምና የዛሬዋን ኢትዮጵያ ሁናታ በመገምገም ላይ የሚያተኩር ነው። አንባቢዎቼን አስቀድሜ ለማሳሰብ የምወደው ትኩረቴ በ failed state ላይ ሳይሆን failed governance ላይ መሆኑን ነው። ሁለቱ አንዱ ሌላውን ተከትሎ የሚመጣ ነገር ቢሆንም ፍጹም የተለያዩ ነገሮች ናቸው።

አንድ አገር እያስተዳደረ ያለ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ቡድን ከሸፈ፣ ውዳቂ ሆነ፣ አገር ለማስተዳደር የሚያስችል አቅምም ሆነ ብቃት የለውም፣ ደካማና ልፍስፍስ ነው የሚባለው መቼ እን ምን ሁኔታዎች ሲሟሉ ነው የሚለውን መጀመሪያ በግርድፉ እንመልከት። አንድ የመንግስትን መንበር ላይ የተቆናጠጠ ጏይል የሕግ የበላይነትን አረጋግቶ፣ ሰላምና ጸጥታን አስጠብቆ፣ የመንግስታዊ መዋቅሮችን በአግባቡ አደራጅቶ ሥርዓት በያዘ መንገድ ተቋማቱ የተፈጠሩለትን እና በሕግ የተጣለባቸውነ ሃላፉነቶች በአግባቡ ተናበው በቅንጅትም ሆነ በተናጠል መምራት ሲችል፣ የአገሪቱን ሉዐላዊነት እና የዜጎቹን ደህንነት መጠበቅና ማስጠበቅ ሲችል እና ልማት ላይ ያተኮረ የኢኮኖሚ መሠረት መገንባትና በየጊዜው እድገትና መሻሻል ማስመዝገብ ሲችል ነው የመንግስትነት ሥራውን በብቃት እየተወጣ ወይም ለመወጣት እየጣረ ነው የሚባለው።

ከላይ ያሉትን ጏላፊነቶች መወጣተት የተሳነው፣ ያልቻለና አቅሙ ያልፈቀደለት ቡድን ውዳቂ ወይም አቅመ ቢስ ይባላል። ሦስት አይነት የመንግስታዊ ሥርዓት መውደቅ መገለጫዎች አሉ። እነሱም፤

1ኛ/ Corporate failure የመጀመሪያው ሲሆን ይህም ቁልፍ የሆኑ የመንግስት ተቋማት አመራሮች ላይ በሚፈጠር ድክመት የተነሳ በተተለይም ወደ ውንብድና ያደሉ የተቀናጁ ዝርፊያዎችን ተከትሎ የሚከሰት የኢኮኖሚ መላሸቅ፣ የሥራ ተነሳሽነት መጥፋት እና የሲስተሞች መዛባት የሚያስከትለው ነው።

2ኛ/ State & Political Failure: ይሄ የአንድ ወይም የተወሰኑ ተቋማት መክሸፍ ሳይሆን ራሱ አገረ መንግስቱ እና የፖለቲካ መዋቅሩ መሠረታዊ የሆኑ የአገርና የዜጎችን ደህንነት መጠበቅና ማስጠበቅ ሲሳነው ነው። ለዚህ ብዙ ጊዜ ሶማሌ ነበረች እንደ ሀገር የምትጠቀሰው።ይህ አይነቱ ልሽቀት የአገዛዝ ሥርዓቱ ስር የሰደደ የመምራት አቅም ማጣትን ተከትሎ የሚመጣ በመሆኑ አገሪቱ በግጭቶች፣ በጦርነቶችና በከፍተኛ የሆነ ተቃርኖና ጥላቻ አዘል ልዩነቶችን የምታስተናግድ በመሆኑ መንግስት ቦታ ላይ የተቀመጠው አካል በብሔራዊ ደረጃ በቂ በጀት መመደብን ጨምሮ ተቋማተቶቹ በሙሉ አቅማቸው እንዲሰሩ ማድረግ አይችልም።

3ኛ/ Global Governance Failure: ይሄ ደግሞ በአለም አቀፍ፣ በአህጉርና ቀጠናዊ ትብብሮች፣ የዲፕሎማሲ ግንኙነቶች፣ የኢኮኖሚ ትስስሮችና ሌሎች የፖለቲካ ጉዳዬች ላይ እጅግ ደካማ፣ በሌሎች ተጽዕኖ ስር ሙሉ በሙሉ የወደቀ፣ ተጽዕኖ መፍጠር የማይችል፣ የድንበርም ሆነ ሌሎች የሉአላዊነት መገለጫ የሆኑ ጉዳዮችን በበቂ ሁኔታ ማስጠበቅ የማይችል ጏይል ሲሆንና በዚህ ድክመቱም ምክንያት አገሪቱን ወደ ድንበር ተሻጋሪ ግጭቶች፣ የሌሎች አገሮች ጉዳይ ፈጻሚ ወደማረግ ወይም ሌሎች አገሮች አገሪቱንና ዜጎቿን ሲንቁና ያለምንም ከልካይ ያሻቸውን ሲያደርጉ ማስቆም የማይችል ሲሆን ነው።

ይህን መነሻ አድርገን በመደመር እሳቤ በሚመራው ብልጽግና እጅ የወደቀችውን ኢትዮጵያ እና መሪዎቹን እንመልከት። እንደ እኔ ግምገማ ብልጽግና በሦስቱም መስፈርት failed governance መሆኑን በተጨባጭ ካሳየ ውሎ አድሯል። የብልጽግና ክሽፈት ግን ከሚገመተውም በላይ እጅግ እጅግ የወረደ በመሆኑ አገሪቱንም ጭምር ይዞ ሊጠፋ እየተውረገረገ ያለበት ሁኔታ ውስጥ ነው የሚገኘው።

አንዳንድ failed government ቶሎ የእርምት እርምጃዎችን በመውሰድ፣ ፖሊሲዎችን በመቀየር፣ ተቋማቶችን በማጠናከር ጨርሶ ከመንኮታኮት እራሳቸውንም አገራቸውንም ይታደጋሉ። ብልጽግና ግን እነዛንም እድሎች ካጣቸው ውሎ አድሯል። አሁን የቀረው አማራጭ ብልጽግና ብቻውን ይክሰም ወይስ አገሪቷንም ይዞ አብሮ ይንኮታኮት የሚለው ነው። እሱን ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው የሚወስነው። ከፈቀደላቸው ግን እንጦሮጦስ ይዘው ከመውረድ የሚመለሱ አይደሉም።

ኢትዮጵያ ዛሬ በኢኮኖሚው፣ በፖለተቲካው፣ በጸጥታና ደህንነት፣ በሉዐላዊነት ዙሪያ እየከፈለች ያለቻቸው ከፍተኛ ዋጋዎች ከብልጽግና እጅግ ደካማ የሀሆነ የማስተዳደር ብቃት መታጣት የመነጩ ናቸው። አብይ እንደግለሰብ እና በሱ የመደመር ፍልስፍና የሚመራው ድርጅት፤ ብልጽግና የአቅም ችግር ብቻ ሳይሆን ቅንነት የጎደለው፣ ድንቁርናም የተጫነው፣ አገር የማስተዳደር እውቀትና ብልሃቱ የጠፋው፣ በሙስና አንገቱ ድረስ የተዘፈቀ፣ በጥላቻም የተሞላ እና ጭካኔን መገለጫው ያደረገ ጏይል መሆኑን መዘርዘር ለቀባሪው እንደማርዳት ይቆጠራል። ኢትዮጵያን ለማዳን ብልጽግናን ማስወገድ ብቻ መፍትሔ ሆኖ ይታየኛል። እሱም ግን ካልዘገየ ነው።

መልካም ሰንበት!!
15👏1🙏1
መልዕክተ ቅዳሜ

አሥርቱ የብልጽኛ ክሽፈቶች፤ ለአቅመ መንግስት ባልደረሰ አካል እጅ የወደቀች አገር
+++++++
በቴሌግራም ለመከታተል፤ https://t.me/yaredH_2024

እንደምን ከርማችኋል የመልዕክተ ቅዳሜ አንባቢዎች፤ ላለፉት ሁለት ሳምንታን በሥራ ብዛት የተስተጓጎለችው መልዕክተ ቅዳሜ የዛሬ ትኩረቷ በተደጋጋሚ በቃለ ምልልሶቼ የገለጽኳቸው የአብይ አስተዳደር አገር ለመምራት የሚያስችል ብቃት እና ቁመና ማጣት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ለዚህም ምክንያቴ ሰዎች ብልጽግና አገር የመምራት ብቃቱ እንደውም ጨምሯል፣ ተጠናክሯል የሚሉ ጥቅል መከራከሪያዎችን ሲያነሱ ስላስተዋልኩ ነው፡፡

በመጀመሪያ ለአንባቢዎች ግንዛቤ ለማስጨበጥ ያህል አንድ መንግስታዊ አስተዳደር ጥሩ ወይም ጠንካራ ወይም ጤኔኛ እና መካከለኛም ቢሆን አገር የማስተዳደር አቅም አለው የሚባለው ከዚህ በሚከተሉት መመዘኛዎች ተፈትኖ ነው፡፡ እነሱም፤ የሕግ የበላይነት እና ፍትሃዊ የሆነ የጸና የሕግ ሥርአት ሲኖር፣ ተጠያቂነት እና ግልጽነትን ያረጋገጠ መንግስታዊ ሥርአት ሲኖር፣ የመንግስታዊ አገልግሎቶችን የማቅረብ ውጤታማነትና ብቃት ሲኖር፣ የፖለቲካ መረጋጋት እና ቅቡልነት ሲኖር ወይም ሲረጋገጥ፣ የተደላደለና የተረጋጋ ኢኪኖሚያዊ አቅም መፍጠር ሲቻል፣ ለሕዝብ ጥያቄዎችና ፍላጎቶች በበቂ ሁኔታ ምላሽ መስጠት የሚችል እና የረዥም ጊዜ ግቦችን ሊያሳካ የሚችል ፖሊሲና እቅዶች ያሉት፣ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋትን መፍጠር የቻለ ሲሆን፣ የአገሪቱን ግዛቶች በበቂ ሁኔታ መስጠበቅ እና ሉአላዊነቷን አለማስደፈር፣ ሰብአዊ መብቶችን በአግባቡ የሚያስጠብቅ እና ለህዳጣን ልዩ ጥበቃዎችን ማድረግ የሚችል ሆኖ መገኘት እና ጠንካራ እና ብቃት ያለው የምርጫ ሥርአት በመዘርጋት ዜጎች በዲሞክራሲያዊ ሥርአት ግንባታ ላይ ቁልፍ ሚና እንዲጫወቱ መደላድሎችን መፍጠር መቻል ናቸው፡፡ እያንዳንዳቸው ቁልፍ የመመዘኛ ነጥቦች በውስጣቸው ዝርዝር ንዑስ የመመዘኛ መስፈርቶችንም ይያዙ ናቸው፡፡

ከላይ በዘረዘርኳቸው አሥር ነጥቦት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የሚመራው መንግስት ሲመዘን አንድም ለመንግስትነት የሚያበቁትን ሥራዎች እንዳልሰራ ብዙ ጥናቶችን እያመላከትኩ እና መረጃዎችን እያቀረብኩ ለማሳየት እችላለሁ፡፡ ይሁንና በዚህ አጭር እበይነ መረብ ጽሑፍ እያንዳንዱን ነጥብ በዝርዝር ማብራራት ባልችልም ዋና ዋና ነገሮችን በማንሳት ሃሳቡን ለውይይት ክፍት ላድርገው፡፡

1ኛ/ Rule of Law and Legal Certainty/ የሕግ የበላይነት እና ፍትሃዊ የሆነ የጸና የሕግ ሥርአትን በተመለከተ የአገዛዝ ሥርአቱ ለሕግ የበላይነት ያለው የተዛባ ግንዛቤ የተስተዋለው ገባ በጊዜ የአብይ አስተዳደር ሥልጣኑን በተቆናጠጠ ጥቂት ወራቶች ውስጥ ነበር፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያለው ፓርላማ ከመሰየሙ በፊት የነበረው ምክር ቤት የለውጡ መንግስት ለሕግ የበላይነት መስፈን ያለው ተነሳሽነት እጅግ ዝቅተኛ በመሆኑ የደቦ ፍርድ እና ሥርአት አልበኝነት ሰፍኗል በሚል ለጠቅላዩ ማሳሰቢያ ሰጥቶ መሰናበቱን ማስታወስ ይቻላል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ግን በአገሪቱ ውስጥ የታየው የሕግ የበላይነት መጥፋት እና የተረጋጋ የሕዝ ሥርአት አለመኖር አገሪቱ ዛሬ ለገባችበት ውጥንቅጥና ሥርአት አልበኝነት ቁልፍ ሚና ተጫውቷል፡፡ ብልጽግና እና የሕግ የበላይነት ፈጽሞ የማይተዋወቁ እስኪመስሉ ድረስ ብዙ ዘግናኝ የሆኑ ነገሮችን አስተናግደናል፡፡ ፍትህ በብሄር፣ በጥላቻና በቂም ስትጠለፍ አይተናል፡፡

2ኛ/ Accountability and Transparency/ ተጠያቂነት እና ግልጽነትን ያረጋገጠ መንግስታዊ ሥርአት መጥፋት እንዲሁ የብልጽግና መንግስት አንዱ መገለጫው ነው፡፡ ከጠቅላዩ አንስቶ በየደረጃው ያሉ ሹማምንት ለፈጸሟቸው ከሙስና አንስቶ በጦርነቶች ወቅት ለተፈጸሙ አስከፊ አለም አቀፍ ወንጀሎችና የሰባአዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂ የለም፡፡ ወንጀለኞች በነጻነት ጠያቂ ሳይኖራቸው የሚንጎማለሉበትና የሚሾሙበት፣ ግፏን የሚሳደዱባት አገር ሆናለች፡፡ ጠቅላዩ ለምሰራው የኮሪደር ልማት ማንም በጀቱንም ሆነ አፈጻጸሙን ሊጠይቀኝ አይችልም ብለው ፓርላማውን እና ሕገ መንግስቱን ከጫማቸው ሥር ያደረጉበት አስከፊ ወቅት ነው፡፡

3ኛ/ Government Effectiveness and Efficiency/ የመንግስታዊ አገልግሎቶችን የማቅረብ ውጤታማነትና ብቃት እንዲሁ በወሬ የቀረበት፣ ዜጎች በሄዱበት የመንግስት ተቋማት ሁሉ አልቅሰው፣ ተጉላልተው፣ አይን ባወጡ ሙሰኛ የመንግስት ሠራተኞች በጠራራ ጸሐይ ተዘርፈው እና ተራቁተው የሚሸኙበት፣ መሰረታዊ የሚባሉ የመንግስት አቅርቦቶች በጠቅላላ ዜጎች በአስተዳደሩ ብቃት ማነስ የተነሳ የተስተጓጎሉበት፣ መሰረታዊ አቅርቦቶች እንደ ኤለክትሪክ፣ ውሃ፣ ኢንተርኔት፣ ሕክምና፣ ትራንስፖርት፣ ነዳጅ፣ የአህል እና ሌሎች አቅርቦቶች ከዋጋ መናር በላይ በበቂ ሁኔታ ማቅረብ ያልቻለ መንግስት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሽንኩርት ከሱዳን እና ከቻይና፣ ብርቱካን ከግብጽ የምታስገባ አገር የሆነችው በዘመነ ብልጽኛ ነው፡፡

4ኛ/ Political Stability and Legitimacy/ የፖለቲካ መረጋጋት እና ቅቡልነት መጥፋት ሌላው የብልጽኛ መንግስት ዋነኛ መገለጫ ነው፡፡ ጠቅላዩ በማጭበርበር ኢህአዴን አፍርሰው፣ የቅርብ ወዳጆቻቸውን እነ አቶ ለማ መገርሳን ክደው ብልጽግናን ከፈጠሩበት እለት አንስቶ ላለፉት ሰባት አመታት ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ መረጋጋት ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ጠፍቷል፡፡ በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በአማራና በአፋር የተከሰቱት ጦርነቶችና ግጭቶች፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የተከሰቱን ግጭቶችና አለመረጋጋቶች፣ በጋምቤላ አልፎ አልፎ የሚታየው ጥቃት ከአገዛዝ ሥርአቱ ቅቡልነት ማጣት ጋር የተያያዙ የፖለቲካ አለመረጋጋቶች የፈጠሯቸው ናቸው፡፡ ዛሬም አገሪቱ በግጭትና የጦርነት አውድ ውስጥ ትገኛለች፡፡ ብልጽግና ጦርነትን መጥመቅና መጀመር የሚችለውን ያህል ጦርነትን አቁሞ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚያስችል ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ብቃትም ያለው ድርጅት አለመሆኑ በበቂ ሁኔታ ታይቷል፡፡

5ኛ/ Economic Performance/ የተደላደለና የተረጋጋ ኢኪኖሚያዊ አቅም መፍጠር አለመቻሉን የማህበረሰቡ የእለት ተዕለት ኑሮ ከሚናገረውም በላይ የአለም አቀፍ አበዳሪ ተቋማት ሳይቀር ለመጀመሪያ ጊዜ አገሪቱ ብድሯን መክፈል የማትችልበት ደረጃ ላይ የደረሰች መሆኗን ለአለም ያጋለቱት በአብይ አስተዳደር ነው፡፡ የአገሪቱ ሃብትና ገንዘብ በሁለት መንገድ ሲባክን ተስተውሏል፡፡ አንደናው ማቆሚያ የሌለው እና የአገሪቱን በጀት እንክት አድርጎ እየበላ ያለው የእርስ በርስ ጦርነት ነው፡፡ ጦርነት በሁለት መልኩ የአገርን ሃብት ያቆረቁዛል፡፡ አንደኛው ጦርነቱን ለማካሄድ፣ ወድ የሆኑ የጦር መሳሪያዎችን እና ድሮኖችን ለመግዛት እና ለሰራዊቱ አቅርቦት ለማሟላት የሚወጣው በጀት በብዙ እጥፍ መጨመሩ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በጦርነቱ የሚወድሙ ተቋማት፣ ፋብሪካዎች፣ መንደሮች፣ የግለሰቦች ሃብት እና የሚፈናቀለው ሕዝብ ብዛት ነው፡፡ ሌላኛው የአገሪቱ ሃብት ብክነት ደግሞ ከጦርነት የተረፈውን ገንዝብ ለቅንጡ ሪዞርቶች፣ ለመንግስት ቢሮዎች ማስዋቢያ፣ አዳዲስ ቤተመንግስቶች መገንቢያ እና የቱሪስት መዳረሻ ለሆኑ ግንባታዎች ማዋሉ ነው፡፡ ጦርነት ባለበት አገር ቱሪስት ምንስ ሊሰራ ይመጣል?
2
6ኛ/ Responsiveness and Long-term Vision / የለሕዝብ ጥያቄዎችና ፍላጎቶች በበቂ ሁኔታ ምላሽ አለመስጠት እና የረዥም ጊዜ ግቦችን በጥናት ላይ ተመስርቶ ሳይሆን በጠቅላዩ ምኞትና ቅዠቶች ላይ ተመስርቶ መቅረጽ ሌላው አደጋ ነው፡፡ የአገዛዝ ሥርአቱ ሕዝብ ለሚያነሳቸው መሰረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ካቆመ እና ጆሮ ዳባ ልበስ ካለ ቆይቷል፡፡ መቼም የኢትዮጵያ ሕዝብ የማይችለው ጉድ የለም እንጂ ዱሮ ነበር የአብይ ሥርአት በዚህ ዝንባሌው ብቻ በሕዝባዊ አመጽ ከሥልጣን ሊወገድ የሚገባው፡፡ ሌላው አሳዛኝ ነገር የአገሪቱ የቅርብም ሆነ የሩቅ ተስፋዎች በጠቅላይ ሚኒስትሩ እውቀት፣ ፍላጎት፣ እና ቅዠት የመሰሉ እሳቤዎች ላይ የተመሰረቱ መሆናቸው አገሪቱ እጅግ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ መግባቷን ያሳያል፡፡ በየመድረኩ ብቅ እያሉ የዛሬ ሰላሳ፣ አርባ፣ አምሳ አመት ከአለም ሁለተኛ ተጽእኖ ፈጣሪ አገር፣ የዛሬ 10 አመት የአፍሪካን ኢኮኖሚ በአንደኝነት ወዘተ የሚሉ የቅዠት ንግግሮችን መስማት እጅግ ያሳዝናል፣ ያሳስባልም፡፡

7ኛ/ Peace and Stability/ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋትን መፍጠር ያለመቻል ብቻ ሳይሆን ያለመፈለግም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሩ የመገለጫ ነው፡፡ አገሪቱ ከአንድ ግጭት ወደ ሌላ ግጭት እንድታመራ እና የእርስ በርስ ጦርነቱ አልበቃ ቡሏቸው የአፍሪቃ ቀንድ ቀጠናን ወደ ለየለት ትርምስ ለመክተት እጅግ በተሳሳተ እና ጥናት ባልታከለበት የጭፍን ዲፕሎማሲ እና ሁሉንም የመዋጥ ምኞት ያለው የፖለቲካ እቅድ እየተመሩ አገሪቱ ብቻ ሳይሆን የአፍርካ ቀንድ ሰላም እና የተረጋጋ እንዳይሆን ብዙ እርቀት በመሄድ ኢትዮጵያን አጣብቂን ውስጥ ከተዋታል፡፡

8ኛ/ Effective control over territory and Sovereignty / የአገሪቱን ግዛቶች በበቂ ሁኔታ ማስጠበቅ እና ሉአላዊነቷን ማስከበር አለመቻላቸውም እንዲሁ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ኤርትራን ጋብዘው በደ ትርግራይ በማስገባት ከማስወረርና የገዛ ሕዝባቸውን ከማስጨፍጨፍ አንስቶ ኢትዮጵያን የሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች እንዳሻቸው የሚፈነጩባት አገር አድርገዋታል፡፡ የሱዳን ታጣቂዎችን ቤኒሻንጉል ጉምዝ ውስጥ አስገብቶ ማሰልጠን፣ አገሪቱን UAE የአፍሪካ ቀንድን ለማተራመስ እንደልቧ መሳሪያ የምታራግፍባት እና ከመቼውም ጊዜ በከፋ ሁኔታ ኢትዮጵያ ለውጪ ሃይሎች ወረራ የተጋለጠችበትን ሁኔታ ፈጥረዋል፡፡

9ኛ/ Respect for human rights and Protection of minority groups/ ሰብአዊ መብቶችን በአግባቡ ማስጠበቅ አለመቻል ብቻ ሳይሆን ሆነ ብሎ እጅግ አስከፊ በሆነ ሁኔታ መጣስ፣ ለህዳጣን ልዩ ጥበቃዎችን ማድረግ ሲገባው ለጥቃት እንዲጋለጡ ትርክቶችን ከማዛባት አንስቶ ጥላቻዎችን በማባዛት ዜጎች በመንግስት እና መንግስታዊ ባልሆኑ ታጣቂ ሃይሎች ኢላማ ተደርገው እንዲገደሉ፣ በገፍ እንዲሳደዱና እንዲፈናቀሉ፤ ከዛም አልፎ በጦርነት በተጎዱ አካባቢዎች ሰብአዊ እርዳታዎች እንዳይደሩስ በማድረግ ዜጎችን መቀጣጫ የሚያደርግ ሥርአት ፈጥረዋል፡፡

10ኛ/ Strong and effective election governance (Democratization process)/ ጠንካራ እና ብቃት ያለው የምርጫ ሥርአት በመዘርጋት ዜጎች በዲሞክራሲያዊ ሥርአት ግንባታ ላይ ቁልፍ ሚና እንዲጫወቱ ማድረኛ መደላድሎችን መፍጠር ሲገባ ምርጫውን ለሥልጣናቸው መቀጠል እና የግፍ ሥርአቱን ለማጽኛነት በማዋል ኢትዮጵያ ውስጥ ታይተው የነበሩ የዲሞክራሲ ጭላንጭሎች እንዲዳፈኑና እንዲጠፉ አድርገዋል፡፡

አሁን የሚካሄደው 7ኛው አገር አቀፍ ምርጫም ግፍን እና አፈናን ከማጽኛነ የዘለለ ሚና እንዳይኖረው ተደጎ የተዘጋጀ በመሆኑ ቀደም ብዮ በጻፍኳቸው ጽሁፎች ላይ ይህን ምርጫ በሰላማዊ ሕዝባዊ እምቢተኝነት በማስቆም አገሪቱ ለቀውስ ጊዜ መፍትሄ የሚሰጥ የሽግግር መንግስት ሥርአት ውስት እንድትገባ ጥሪ ያደረኩትም በእነዚህ ምክንያቶች መሆኑን በመጠቆም እዚህ ላይ ላብቃ፡

በእነዚህ ነጥቦች ላይ የአገዛዝ ሥርአቱ የተሻለ ውጤት ሊሰጠው ይገባል የሚል ሰው ካለ እንዲሞግተኝ ጥሪ በማቅረብ ጽሑፌን ልዝጋ፡፡

መልካም ሰንበት!
14👍5
መልዕክተ ቅዳሜ፤

ሰላም ይስፈን፣
ጦርነት ይቁም፣
የግፍ አገዛዝ ይቁም፣
ከምርጫ በፊት የሽግግር መንግስት!
👍133