ስንክሳር ወግጻዌ ዘተዋሕዶ
800 subscribers
3.46K photos
104 videos
194 files
1.2K links
የየዕለቱ ስንክሳር እና ግጻዌ የሚቀርብበት ቻናል ነው፡፡

ለማንኛውም አስተያየት እና እርማት
@zetaodokos ላይ ይላኩልን።

👇👇የYoutube Channel ይቀላቀሉ👇👇
https://youtube.com/channel/UCupqpIYe_mMpSM7jMT3Njhw
Download Telegram
#ደብረ_ዘይት
(የዐቢይ ጾም አምስተኛ ሳምንት)

የዐቢይ ጾም የአምስተኛው ሳምንት ደብረ ዘይት ይባላል፡፡ ጌታ በደብረ ዘይት የዳግም ምጽአቱን ነገር ማስተማሩ ይነገርበታል፡፡ ደብረዘይት የስሙ ትርጓሜ የዘይት ተራራ ማለት ነው ስያሜ የተሰጠው በቦታው ብዙ ወይራ ተክል ይበቅልበት ስለ ነበር ነው፡፡
እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ ደቀመዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው ንገረን ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድን ነው?›› አሉት (ማቴ. 24፥3፣  ዘካ. 14፥5 ፤ ሐዋ. 1፥11 ፤ 1ኛ ተሰ. 4፥16 ፤ ራዕ. 22፥7)

#አመጣጡስ_እንዴት_ነው?

ጌታ ይህንን ዓለም ለማሳለፍ ለሁሉም እንደ ሥራው ለመክፈል በግርማ መለኮቱ በክበብ ትስብዕቱ ይመጣል፡፡ ጊዜው ዘመነ ዮሐንስ ወርሃ መጋቢት ዕለት እሑድ መንፈቀ ሌሊት እንደሆነ ሊቃውንት ተናግረዋል፡፡ ምነው የሚያውቀው የለም ይባል የለምን? ቢሉ እውነት ነው የሚያውቀው የለም ብዙ የዮሐንስ ዘመን፤ ብዙ የመጋቢት ወር፤ ብዙ የእሑድ ዕለት አለና ለይቶ የሚያውቅ የለም፡፡ ሞት ለማንም አይቀርምና ሁሉም ይሞታል፡፡ ዘፍ. 3፥19 በዕለተ ምጽአት ቅዱስ ገብርኤል ስምንቱን ነፋሳተ መዓት ከየመዛግብታቸው ያወጣቸዋል፡፡ ዛፏን ነቅለው ደንጊያውን ፈንቅለው ምድርን እንደ ብራና ይዳምጧታል፡፡ ቅዱስ ሚካኤል መለከት ይነፋል፡፡ 1ኛ መቃ. 9፥8 ቅዱስ እግዚአብሔር ዘያነቅሖሙ ለሙታን ሲል በዱር በገደል በባሕር በየብስ በመቃብር ውስጥ ያሉት በአውሬ ሆድ ውስጥ ያሉ ሁሉ ይሰበሰባሉ፡፡ በሁለተኛው ነጋሪት ሲመታ አጥንትና ሥጋ አንድ ሆነው ፍጹም በድን ይሆናሉ፡፡ ሦስተኛው ነጋሪቱን መቶ (ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት) ንቃሕ መዋቲ ዘትነውም ባለ ጊዜ መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ደጉ ደግነቱን ክፉውም ክፋቱን ይዞ ይነሳል፡፡    

ወንዱ የ30 ዓመት ሴቲቱ የ15 ዓመት ሆነው ጻድቃን ብርሃን ለብሰው ብርሃን ተጎናጽፈው ከፀሐይ 7 እጅ አብርተው ማቴ.13፥43 ኃጥአን ጨለማ ለብሰው ፍጹም ዲያቢሎስን መስለው ይነሳሉ፡፡ ጻድቃን ስለሠሩት መልካም ሥራ ኑ የአባቴ ቡሩካን ብሎ መንግሥተ ሰማያትን ያወርሳቸዋል፡፡ ኃጥአንን ስለ ክፉ ሥራቸው (ከኔ ሂዱ) ገሃነም ይሰዳቸዋል፡፡ ጻድቃን ደስ ይላቸዋል ኃጥአን ግን ያዝናሉ፤ ዋይ ዋይ ይላሉ፤ ደረት ይደቃሉ እንባቸው ያፈሳሉ፡፡ የማይጠቅም ለቅሶ የማይጠቅም ሐዘን ሰቅለው የገደሉትም አይሁድ ክብሩን አይተው ላይጠቀሙ ይጸጸታሉ፡፡    

#ምልክቱስ_ምንድን_ነው? ብለው ጌታን ሲጠይቁ ‹‹ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፡- ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ፡፡ ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ፤ ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ አትደንግጡ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው፡፡ ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥት በመንግሥት ላይ ይነሳል፤ ረሃብም ቸነፈርም መናወጥም በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል፤ እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው፡፡ በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጧችኋል ይገድሉአችሁማል፤ ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ›› አላቸው፡፡ በዳግም ምጽአቱ ጊዜ ከቅዱሳኑና ከሰማዕታቱ ጋር ለመቆም ያብቃን፡፡

#የዕለተ_ሰንበት_መዝሙር_ከጾመ_ድጓ
እንዘ ይነብር እግዚእነ ውስተ ደብረ ዘይት ወይቤሎሙ ለአርዳኢሁ ዑቁኬ ኢያስሕቱክሙ ወንበሩ ድልዋኒክሙ ብዙኃን ይመጽኡ በስምየ እንዘ ይብሉ አነ ውእቱ ክርስቶስ ወዘአዝለፈ ትዕግሥቶ ውእቱ ይድኅን ወአመ ምጽአቱሰ....
(ጌታችን በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ ሳለ ለደቀ መዛሙርቱ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ፤ ተዘጋጅታችሁም ኑሩ፤ ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉ፤ እስከ መጨረሻው የጸና እርሱ ይድናል፡፡....)

#የዕለቱ_ምንባባት
1ኛ ተሰሎንቄ 4÷13-ፍጻ፡-
ወንድሞቻችን ሆይ÷ ስለ ሞቱ ሰዎች÷ ተስፋ እንደሌላቸው ሰዎች እንዳታዝኑ ልታውቁ እንወዳለን፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞቶ እንደ ተነሣ ካመንን እንዲሁ እግዚአብሔር ሙታንን በኢየሱስ ያስነሣቸዋል ከእርሱም ጋር ያመጣቸዋል፡፡.....

2ኛ ጴጥ.3÷7-14፡-
አሁንም ሰማይና ምድር በዚያ ቃል ለእሳት ተዘጋጅተዋል፤ ኃጥኣን ሰዎች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀንም ተጠብቀዋል፡፡ነገር ግን ወንድሞቻችን ሆይ÷ ይህን አትርሱ፤ በእግዚአብሔር ዘንድ አንዲት ቀን እንደ አንድ ሺህ ዓመት÷ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን ነውና፡፡.....

ሐዋ. 24÷1-21፡-
በአምስተኛውም ቀን ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ ከመምህራኑና ጠርጠሉስ ከሚባል አንድ ጠበቃ ጋር ወረደ፤ ጳውሎስንም በአገረ ገዢው ዘንድ ከሰሱት፡፡..... (ተጨማሪ ያንብቡ)

#የዕለቱ_ምስባክ
መዝ. 49÷2
እግዚአብሔርሰ ገሃደ ይመጽእ
ወአምላክነሂ ኢያረምም
እሳት ይነድድ ቅድሜሁ፡፡
ትርጉም፦
እግዚአብሔር በግልጥ ይመጣል፡፡
አምላካችንም ዝም እይልም፤
እሳት በፊቱ ይነድዳል በዙሪያውም ብዙ ዐውሎ አለ፡፡

#የዕለቱ_ወንጌል
ማቴ. 24÷1-25፡-
ጌታችን ኢየሱስም ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀርበው የቤተ መቅደሱን የሕንጻ አሠራር አሳዩት፡፡ ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው÷ “ይህን ሁሉ ታያላችሁን? እውነት እላችኋለሁ፤ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም፡፡.....” (ተጨማሪ ያንብቡ)

#የዕለቱ_ቅዳሴቅዳሴ አትናቴዎስ

ምንጭ፡-
(የማቴዎስ ወንጌል 24፥1 ትርጓሜ፣ መዝገበ ታሪክ ቁጥር 2፣ ግጻዌ)
#ገብር_ኄር (የዐቢይ ጾም 6ኛ ሳምንት)

የዐቢይ ጾም ስድስተኛው እሑድ ወይም ሳምንት ገብር ኄር ይባላል፡፡ በዚህ ሳምንት የሚዘመረው ዝማሬ፣ የሚሰበከው ስብከት፣ የሚሰጠው ትምህርት ገብርኄርን የሚያወሳ ነው። ማለትም ስለ ታማኝ አገልጋይ ነው፡፡

የማቴ.25፥14-25 የሚነግረን ይህን ነው፦ “አንድ ባዕለ ጸጋ ሰው ባሪያዎችን ጠርቶ ለአንዱ አምስት መክሊት ሰጠው፣ ሁለት መክሊት የሰጠውም አለ፣ አንድ መክሊትም የሰጠው አለ፡፡ ከዚህ በኋላ ወደሩቅ አገር ሄደ፡፡ አምስት መክሊት የተቀበለውም ወጥቶ ወርዶ ሌላ አምስት አትርፎ አስር አደረገ፡፡ ሁለት የተቀበለውም አትርፎ አራት አደረገ፡፡ አንድ የተቀበለው ግን ሄዶ መሬቱን ቆፍሮ በሻሽ ጠቅልሎ የጌታውን መክሊት ቀበራት፡፡

ከብዙ ጊዜ በኋላ ጌታቸው መጥቶ ተቆጣጠራቸው፡፡ አምስት መክሊት የተቀበለው ቀርቦ ጌታዬ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር እነሆ አምስት አተረፍኩ አለው፡፡ “ገብርኄር ወምዕመን ዘበሁድ ምዕምነ ኮንከ ዲበ ብዙህ እሰይመከ ባዕ ውስተ ፍስሐሁ ለእግዚእከ” “አንተ ታማኝ ባሪያ በጥቂቱ ታምነሃል በብዙ እሾምሃለሁ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ” አለው፡፡ ሁለት የተቀበለውም ቀርቦ ጌታዬ ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር እነሆ ወጥቼ ወርጄ ሌላ ሁለት አትርፌ አራት አድርጌአለሁ፡፡ “አንተ ታማኝ በጎ አገልጋይ በጥቂቱ ታምነሃል በብዙ እሾምሃለሁ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ” አለው፡፡ አንድ መክሊት የተቀበለው ግን ቀርቦ “ጌታዬ አንተ ክፉና ጨካኝ ካልዘራህበት የምታጭድ ካልበተንህበት የምትሰበስብ እንደሆንክ ስለአወቅሁ መሬቱን ቆፍሬ ቀበርኋት እነኋት መክሊትህ” አለው፡፡ “አንተ ሰነፍ ባሪያ መክሊቴን በጊዜ ልትሰጠኝ በተገባህ ነበር እኔም ወጥቶ ወርዶ ለሚያተርፍ በሰጠሁት ነበር”፡፡ ኑ የዚህን ሀኬተኛ መክሊት ውሰዱና አስር መክሊት ላለው ስጡት፡፡ ላለው ይሰጡታል ይጨመርለታል ለሌለው ግን ያለውን ይቀሙታል፡፡ ኑ ይህን ሰነፍና ሃኬተኛ ባሪያ እጅ እግሩን አሥራችሁ ጽኑዕ ጨለማ ወደአለበት ውሰዱት ጩኸትና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ጨምሩት” አለ ማቴ. 25፥14-25፡፡

ባለ ጸጋ የተባለው ጌታ ነው፡፡ መክሊት የተባለው ልዩ ልዩ የአገልግሎት ጸጋ ነው፡፡ ያተረፉት በሚገባ በታማኝነት ያገለገሉ ቅዱሳን ሰዎች ናቸው መክሊቱን የቀበረው ደግሞ በታማኝነት በተሰጠው ጸጋ ማገልገል ሲገባው ያላገለገለ ነው፡፡ ጌታቸው ሊቆጣጠራቸው መጣ ማለት በዕለተ ምጽአት ለሁሉም በአገለገለው አገልግሎት ዋጋ ለመስጠት እንደሚመጣ ያሳየናል፡፡ ያገለገሉትን ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አላቸው ማለት ታማኝ አገልጋዮች መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳሉና፡፡ ሰነፎች ደግሞ ጥርስ ማፋጨት ስቃይ ጽኑዕ ጨለማ ባለበት ሲዖል መግባታቸውን የሚያሳይ ነው፡፡

#የዕለተ_ሰንበት_መዝሙር_ከጾመ_ድጓ
መኑ ውእቱ ገብር ኄር ወምእመን ዘይረክቦ እግዚኡ በምግባረ ሠናይ ወይሠይሞ ዲበ ኲሉ ንዋዩ ካዕበ ይቤሎ እግዚአብሔር ገብር ኄር ወምእመን ዘበውኁድ ምእመነ ኮንከ ዲበ ብዙኅ እሠይመከ ባእ ውስተ ፍሥሐሁ ለእግዚእከ፡፡

ትርጉም፦ ጌታው በመልካም ሥራ የሚያገኘው በሐብቱ ኹሉ ላይ የሚሾመው፤ የታመነ በጎ አገልጋይ ማን ነው? ዳግመኛም እግዚአብሔር አንተ የታመንክ በጎ አገልጋይ በጥቂቱ የታመንህ ስለኾንህ በብዙ እሾምሃለሁ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ ይለዋል፡፡

#መልዕክታት
2ኛ ጢሞ.2÷1-15
"ልጄ ሆይ÷ አንተም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ በርታ፡፡ በብዙ ምስክሮች ፊት ከእኔ የሰማኸውን ትምህርት ለሌሎች ሊያስተምሩ ለሚችሉ ለታመኑ ሰዎች እርሱን አስተምራቸው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደሚያገለግል በጎ አርበኛ ሆነህ መከራ ተቀበል፡፡" (ተጨማሪ ያንብቡ)

1ኛ ጴጥ.5÷1-11
"እንግዲህ እኔ ከእነርሱ ጋር ሽማግሌ÷ የክርስቶስም መከራ ምስክር÷ ደግሞም ሊገለጥ ካለው ክብር ተካፋይ የሆንሁ በመካከላቸው ያሉትን ሽማግለዎችን እማልዳቸዋለሁ፡፡ በእናንተ ዘንድ ያሉትን የእግዚአብሔርን መንጋዎች ጠብቁ፤ ስትጠብቁአቸውም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ አይሁን፤ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘትም አይሁን፡፡" (ተጨማሪ ያንብቡ)

#ግብረ_ሐዋርያት
የሐዋ.1÷6-8
"እነርሱም ተሰብስበው ሳሉ÷ "ጌታ ሆይ÷ በዚህ ወራት ለእስራኤል ልጆች መንግሥትን ትመልሳለህን?” ብለው ጠየቁት፡፡ እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው÷ “አብ በገዛ ሥልጣኑ የወሰነውን ቀኑንና ዘመኑን ልታውቁ አልተፈቀደላችሁም፡፡ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኅይልን ትቀበላላችሁ፤ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ሁሉ፣ በሰማሪያና እስከ ምድር ዳርቻ ድረስም ምስክሮቸ ትሆኑኛላችሁ።"

#ምስባክ
መዝ. 39÷8
"ከመ እንግር ፈቃደከ መከርኩ አምላኪየ፡፡ ወሕግከኒ በማዕከለ ከርሥየ፡፡ ዜኖኩ ጽድቀከ በማኅበር ዐቢይ፡፡"

ትርጉም፦ አምላኬ ሆይ፥ ፈቃድህን ለማድረግ መከርሁ፥ ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው። በታላቅ ጉባኤ ጽድቅህን አወራሁ

#ወንጌል
ማቴ. 25÷14-30
“መንገድ እንደሚሄድ÷ አገልጋዮቹንም ጠርቶ ሊያተርፉበት ገንዘቡን እንደ ሰጣቸው ሰው እንዲሁ ይሆናልና፤ ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው ለአንዱ አምስት÷ ለአንዱ ሁለት÷ ለአንዱም አንድ ሰጠና ወዲያውኑ ሄደ፡፡” (ተጨማሪ ያንብቡ)

#የዕለቱ_ቅዳሴቅዳሴ ባስልዮስ