ስንክሳር ወግጻዌ ዘተዋሕዶ
813 subscribers
3.46K photos
104 videos
194 files
1.2K links
የየዕለቱ ስንክሳር እና ግጻዌ የሚቀርብበት ቻናል ነው፡፡

ለማንኛውም አስተያየት እና እርማት
@zetaodokos ላይ ይላኩልን።

👇👇የYoutube Channel ይቀላቀሉ👇👇
https://youtube.com/channel/UCupqpIYe_mMpSM7jMT3Njhw
Download Telegram
#መጋቢት_6

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

መጋቢት ስድስት በዚች ቀን #ቅዱስ_ዲዮስቆሮስ በሰማዕትነት አረፈ፣ ታማኝ የሆነ ኤጲስቆጶስ #የቅዱስ_ቴዎዶስዮስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፣ #የአቡነ_አርከሌድስ እረፍታቸው ነው፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ሰማዕት_ዲዮስቆሮስ

መጋቢት ስድስት በዚች ቀን በእስ*ላሞች ዘመነ መንግሥት ዲዮስቆሮስ በሰማዕትነት አረፈ። ይህም ቅዱስ ከእስክንድርያ ሰዎች ወገን ነው በማግባባት በመገፋፋት ከክርስቲያን አውጥተው ወደ እስ*ልምና አስገቡት በእምነታቸውም ጥቂት ጊዜ ኖረ።

ፍዮም በሚባል አገር ለአንድ ክርስቲያን ሰው የተዳረች አንዲት እኀት ነበረችው ወንድሟ የክብር ባለቤት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሃይማኖት እንደ ተወ በሰማች ጊዜ ታላቅ ኀዘንን አዘነች።

ከዚህም በኋላ እንዲህ ብላ ወደርሱ መልእክትን ላከች የክብር ባለቤት ክርስቶስን አንተ እንደ ካድከው ከምሰማ በክርስትናህ ሳለህ የሞትህ መርዶ ቢመጣልኝ እወድ ነበር። ከዚያም ከቅዱሳት መጻሕፍት ጠቅሳ ጻፈችለት በደብዳቤዋ ፍጻሜም እንዲህ ብላ ጻፈች። "ከዛሬ ጀምሮ ወደ ክርስትናህ ካልተመለስክ ይህቺ ደብዳቤ በእኔና በአንተ መካከል የፍቅር ፍጻሜ እንደሆነች ዕወቅ ከቶ ፊትህንም እንዳታሳየኝ መልእክትም ቢሆን አትላክልኝ። የእኅቱንም የመልእክት ደብዳቤ በአነበበ ጊዜ መሪር ዕንባን አለቀሰ ተጸጸተ ፊቱን ጸፋ ጽሕሙንም ነጨ ተነሥቶም ወገቡን ታጠቀ ረጅም ጸሎትንም በመጸለይ ማለደ ፊቱንም አዳኝ በሆነ መስቀል ምልክት አማተበ ከቤቱም ወጥቶ በእስክንድርያ ከተማ ውስጥ ተመላለሰ።

እስ*ላሞችም በአዩት ጊዜ ይዘው ወደ መኰንኑ አቀረቡት መኰንኑም ከእርሱ ስለሆነው ነገር ጠየቀው እርሱም ክርስቲያን ነኝ ሌላ ምንም ምን አላውቅም ብሎ መለሰ። መኰንኑም ደግሞ የክርስቲያንን ሃይማኖት ትተህ ወደእኛ እምነት ገብተህ አልነበረምን ብሎ መለሰለት።

ቅዱስ ዲዮስቆሮስም መልሶ እንዲህ አለ በወልድ የማያምን ሕይወትን አያያትም የእግዚአብሔር የቁጣው መቅሠፍት በላዩ ይወርዳል እንጂ የሚል በከበረ ወንጌል ተጽፏል። ስለዚህ እኔ በክብር ባለቤት በሕያው እግዚአብሔር ልጅ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምናለሁ እኔም ትውልዴ ከክርስቲያን ነው አሁንም በክርስትናዬ እሞታለሁ። መኰንኑም እጅግ ተቆጥቶ ከዚህ ምክርህ ካልተመለስክ እኔ የጸና ቅጣት እቀጣሃለሁ አለው። ቅጣቱንም ፈርቶ ከመልካም ምክሩ አልተመለሰም።

ከዚያም በኋላ ታላቅ ግርፋት ገርፎ አሠረው በእሥር ጥቂት ቀናት ቆየ ከእሥር ቤትም አውጥቶ ከምክሩ ከሐሳቡ ቢመለስ ብዙ ገንዘብ ሊሰጠው ቃል ገባለት። ይህ ካልሆነ ግን በእሳት እንደሚአቃጥለው ነገረው። ቅዱሱም ሕያው በምታደርግ ከክርስቲያን ሃይማኖት በቀር በሌላ አልሞትም ብሎ መለሰለት።

መኰንኑም በእሳት እንዲአቃጥሉት አዘዘ ከከተማም ውጪ ታላቅ ጉድጓድ ቆፈሩለት። ዕንጨትም መልተው አነደዱት ነበልባሉም እጅግ ከፍ ከፍ አለ ያን ጊዜም ብዙ ገርፈው ሥጋውን በሰይፍ ሰነጣጠቁ ። ወደ እሳትም ጨመሩት ነፍሱንም በእግዚአብሔር እጅ ሰጥቶ በመንግሥተ ሰማያት የሰማዕትነትን አክሊል ተቀበለ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ቴዎዶስዮስ

በዚችም ዕለት ታማኝ የሆነ ኤጲስቆጶስ የቅዱስ ቴዎዶስዮስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው። የዚህንም ቅዱስ ዜና ከዲዮቅልጥያኖስ የተሾመ የቆጵሮስ ገዥ ዮልዮስ ሰማ። ወደርሱም አስቀርቦ የክብር ባለቤት ክርስቶስን ክዶ ለረከሱ ጣዖቶች ዕጣን እንዲአጥን መሥዋዕትም እንዲአቀርብ ፈለገ፡፡ ቅዱስ ቴዎዶስዮስም እኔስ በሕያው እግዚአብሔር ልጅ በጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ አምናለሁ ለእርሱም ዕሠዋለሁ በሎ መለሰ።

ትእዛዙንም ባልሰማ ጊዜ ጽኑዕ ግርፋትን ከላም ቆዳ በተሠራ ጅራፍ ገረፈው። ከዚያም ሰቅሎ ሥጋውን ሁሉ ሰነጠቀ አውርዶም በእሳት በአጋሉት በብረት አልጋ ላይ አስተኛው ጌታችንም ከዚህ ሥቃይ ጠብቆ አዳነው።

ከዚህ በኋላ እጆቹንና እግሮቹን በረጃጅም ችንካሮች ቸንክረው እስከ ወህኒ ቤት ጐትተው በዚያ ጣሉት። እግዚአብሔርም ከሀዲው ዲዮቅልጥያኖስን አጥፍቶ ጻድቁ ቈስጠንጢኖስ እስከ ነገሠ ድረስ በወህኒ ቤት ኖረ።

ቈስጠንጢኖስም የመንግሥት ሥልጣን በያዘ ጊዜ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በማመን የታሠሩትን ሁሉ እንዲፈቷቸው አዘዘ። ከዚያም በኋላ ወደ አገሩ ተመልሶ በጵጵስናው ሹመት ላይ ሁኖ ምእመናንን በበጎ አመራር እየመራ ኖረ። ዕድሜውንም ፈጽሞ በሰላም አረፈ፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_አርከሌድስ

ዳግመኛም በዚህች እለት አቡነ አርከሌድስ እረፍታቸው ነው፡፡ አቡነ አርከሌድስ አገራቸው ግብፅ ሲሆን ከተሰዓቱ ቅዱሳ ቀጥሎ ነው ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ የመጡት፡፡ የነበሩበትም ጊዜ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በነበሩበት ጊዜ ነበር፡፡ወደ አገራችን ከመጡ በኋላ ወሎ ውስጥ ያለችውን እጅግ ጥንታዊቷን ቸር ተከል ማርያምን ቆረቆሯት፡፡ ጻድቁ የሚታወቁበት ትልቁ ገድላቸውም ሳይንት ውስጥ በቸር ተከል ማርያም ገዳም ውስጥ ለ21 ዓመታት ሳያርፉ ሳይቀመጡ በመቆም ጸሎት ያደረጉ ታላቅ አባት መሆናቸው ናቸው፡፡

አቡነ አርከሌድስ እጃቸውን ሲያጨበጭቡ 500 ርግቦች በአንድ ጊዜ ይሰበሰቡላቸው ነበር፡፡ እነርሱንም ወደፈለጉት ቅዱሳን መልእክት ይልኳቸው ነበር፡፡ በዚህ አስደናቂ ሥራቸውም በቅዱሳን ዘንድ ትልቅ ክብር ነበራቸው፡፡ለቅዱሳን የተለያየ ታሪክ አላቸው፣ ለአንዱ አንበሳ፣ ለአንዱ ጅብና አጋዘን፣ ለአንዱ ንብ፣ ለአንዱ ነብር፣ ለአንዱ አጋንንት ይታዘዙላቸው ነበር፡፡ ጻዲቁ በመጨረሻ ወደ ምረድ ግብፅ ተመልሰው ከሰማዕታት ጋር ተሰይፈው በሰማዕትነት ያረፉ ታላቅ አባት ናቸው፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢትና #ከገድላት_አንደበት)
††† እንኳን ለቅዱስ ቴዎዶስዮስ ተአማኒ ሰማዕት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ
ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

†††
#ቅዱስ_ቴዎዶስዮስ †††

††† በሃገረ ኒቅያ በእመቤታችን እና በአምላክ ልጇ የሚያምኑ 318ቱ ቅዱሳን ሊቃውንት ተሰብስበዋል:: ከእነዚህ አንዱ ቅዱስ ቴዎዶስዮስ እንደሆነ በትውፊት ይታመናል:: የጉባዔውስ ነገር እንደምን ነበር ቢሉ:-
የሊብያው ሰው አርዮስ ጌትነት ገንዘቡ የሆነ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ክዶ ሊያስክድ ሲሯሯጥ በፈቃደ እግዚአብሔር: በጻድቁ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ጥሪ: 2348 ምሑራን ከመላው ዓለም ተሰበሰቡ::

ጥሪው የተላለፈው በወርኀ ሚያዝያ ሲሆን በመንገድ ችግር ሁሉም ተጠቃለው ኒቅያ የገቡት መስከረም 21 ቀን ነበር:: ከተሰበሰበው ብዙ ሰው መካከል የአበውን ደቀ መዛሙርት ሳንቆጥር ሃይማኖታቸው የቀና: ምግባራቸው የጸና 318ቱ አበው ሊቃውንት ተገኙ::

እነዚህ አባቶች "ሊቃውንት" ሲባሉ እንዲሁ በእውቀት ብቻ የበሰሉ እንዳይመስሉን:: 318ቱ አበው እኩሎቹ በዘመነ ሰማዕታት እጅና እግራቸውን የተቆረጡና ለሃይማኖታቸው ብዙ ዋጋ የከፈሉ ናቸው::

እኩሎቹ ደግሞ በገዳማዊ ሕይወት ያጌጡ: ፍቅረ ክርስቶስ በውስጣቸው የሚነድ: የመንፈስ ቅዱስ ቤት ናቸው:: እስኪ እናውቃቸው ዘንድ የጥቂቶችን ማንነት በስምና በመገለጫ እንመልከት:-
1.ቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስ (በዘመነ ሰማዕታት ለ22 ዓመት ሲቆራርጡት ኖረው በጉባኤው ላይ የተገኘው ያለ እጅ: እግር: ጀሮ: ከንፈር: ቅንድብ ነው)

2.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ (ስለ ቀናች እምነት ለ50 ዓመታት የተጋደለና ለ15 ዓመታት በስደት የኖረ ነው)

3.ቅዱስ እለእስክንድሮስ ሊቅ (ከሰማይ ብርሃን ይወርድለት የነበረ አባት ነው)

4.ቅዱስ ቴዎዶስዮስ (በምድረ ቆረንቶስ መከራን የተቀበለ)

5.ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስ (በጸሎቱ አጋንንትን ያንቀጠቀጠ: ነፍሳትን ከሲዖል የቀማና ከከዊነ እሳት የደረሰ አባት ነው)

6.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘአርማንያ (ስለ ቀናች እምነት መጸዳጃ ጉድጓድ ውስጥ ለ15 ዓመታት ተጥሎ የኖረ ሰማዕት ነው)

7.ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሜራ (ከሕፃንነቱ የተቀደሰ: በበርሃ የተጋደለ: በዘመነ ሰማዕታት ብዙ መከራን የተቀበለ አባት ነው)

8.ቅዱስ ያዕቆብ ዘንጽቢን (በደግነቱ ሙታንን ያስነሳ: ወንዝን በጸሎቱ ያቆመ: በንጽሕና የተጋደለ አባት ነው)

9.ቅዱስ ሶል ጴጥሮስ (ቅዱሱን ንጉሥ ያጠመቀ: ቁስጥንጥንያን በወንጌል ያበራ ሊቅ ነው)

10.ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስ (ስለ ቀናች እምነቱ ብዙ ግፍ የደረሰበትና በስደት ያረፈ አባት ነው)

ለአብነት እንዲሆኑን እነዚህን አነሳን እንጂ 318ቱም ሊቃውንት ስለ ቤተ ክርስቲያን ተግተው የተጋደሉ: ብዙ ዋጋም የከፈሉ አባቶች ናቸው::

በወቅቱ ታዲያ ቤተ ክርስቲያንን የበጠበጡ ብዙ መናፍቃን ቢኖሩም የአርዮስ ግን ከመጠኑ አለፈ:: የእርሱ ኑፋቄ (ፈጣሪያችንን ፍጡር ማለቱ) መነሻው ከእርሱ በፊት ነው:: መናፍቃን ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ ቤተ ክርስቲያንን ሲያውኩ መኖራቸው ግልጽ ነው::

በተለይ ደግሞ ቢጽ ሐሳውያንና ግኖስቲኮች የወለዷቸው እሾሆች አባቶቻችንን እንቅልፍ ነስተው ነበር:: የሚገርመኝ በዘመኑ እንደ ነበሩ መናፍቃን ኃይለኝነት የእኞቹ ከዋክብት ሊቃውንት ባይኖሩ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ያሳስብ ነበር::

ግን እግዚአብሔር ለሁሉ እንደሚገባ ያዘጋጃልና አበው ብርቱ መናፍቃንን በብርቱ መንፈሳዊ ክንድ እያደቀቁ ከጐዳና አስወገዷቸው:: የዛሬውን ደካማ ትውልድ ደግሞ የአርዮስ ልጆች 2 (3) ጥቅስ ይዘው ሲያደናብሩት ይውላሉ::

ሐረገ መናፍቃን በርጉም ሳምሳጢ ጳውሎስ: በመርቅያንና በማኒ ይጀምራል:: በእርግጥ አርጌንስ እና የግብጹ ቀሌምንጦስም ተቀላቅለዋቸዋል:: ርጉም ሳምሳጢ ድያድርስን በኑፋቄ ወልዶታል:: ድያድርስ ሉቅያኖስን: ሉቅያኖስ ደግሞ አርዮስን ወልደዋል::

ይህ አርዮስ እጅግ ተንኮለኛ በመሆኑ ልክ እንደ ዘመኑ መሰሎቹ ግጥምና ዜማ እየጻፈ በየመንገዱ እያደለ: በየቤቱ እየሰበከ ብዙዎችን በኑፋቄው በከለ:: በመጀመሪያ ተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ (አስተማሪው) መከረው:: ባይሰማው ከአንዴም ሁለት ጊዜ አወገዘው::

ቆይቶ ሰነፉ ጳጳስ አኪላስ ቢፈታውም ሊቁ ቅዱስ እለእስክንድሮስ እንደ ገና አወገዘው:: እንደ አርዮስ ሐሳብ መድኃኒታችን ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ አይደለም (ሎቱ ስብሐት!) ማለት ክርስትናን ከሥሩ ፈንቅሎ መጣል ነው::

ስለ ክርስቶስ እግዚአብሔርነት ብሉይም ሐዲስም እየመሰከሩ (ኢሳ. 9:6, መዝ. 46:5, 77:65, ዘካ. 14:4, ዮሐ. 1:1, 10:30, ራዕይ. 1:8, ሮሜ. 9:5) አርዮስና የዛሬ መሰሎቹ አንዲት ጥቅስ ይዘው ክርስትናን ከመሠረቱ ለመናድ መሞከራቸው በእርግጥም ከሰይጣን መላካቸውን ያሳያል::

በወቅቱም በመወገዙ "ተበደልኩ" ብሎ የጮኸው አርዮስ ከሁለቱ አውሳብዮሶች ባልንጀሮቹ (ዘቂሣርያና ዘኒቆምድያ) ጋር ሆኖ ወደ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ሔዶ ከሰሰ:: ቅዱሱ ንጉሥም የጉዳዩን ክብደት ተመልክቶ የዓለም ሊቃውንት ይሰበሰቡ ዘንድ አዘዘ::

ከሚያዝያ 21 እስከ መስከረም 21 ተጠቃለው ገቡ:: በ325 ዓ/ም (በእኛው በ318 ዓ/ም) ለ40 ቀናት የሚቆይ ሱባኤን ያዙ:: ሱባኤውን ሲጨርሱም በአራቱ ፓትርያርኮች (እለእስክንድሮስ: ሶል ጴጥሮስ: ዮናክንዲኖስና ኤዎስጣቴዎስ) መሪነት: በእለእስክንድሮስ ሊቀ መንበርነት: በአትናቴዎስ ጸሐፊነት ጉባኤው ተጀመረ::

በጉባኤው ሙሉ ስልጣን በሰማይ ከፈጣሪ: በምድር ከንጉሡ የተሰጣቸው አበው አርዮስን ተከራክረው ከነ ጀሌዎቹ ምላሽ አሳጡት:: ክርስቶስ አምላክ ወልደ አምላክ: ሥግው ቃል: ራሱም እግዚአብሔር መሆኑን አስረዱት::
በጉባኤው መጨረሻም:-
1.አልመለስም በማለቱ አርዮስን አወገዙ::
2.ጸሎተ ሃይማኖትን "ለመንግስቱም ፍጻሜ የለውም" እስከሚለው ድረስ ተናገሩ::
3.ፍትሐ ነገሥትን ሥጋዊና መንፈሳዊ ብለው አዘጋጁ::
4.ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እንደሚገባ አደራጁ::
5.በስማቸው የሚጠራ አንድ ቅዳሴን ደረሱ::

ይህ ሁሉ ሲሆን መድኃኒታችን ክርስቶስ 319ኛ ሆኖና ገሊላዊ ጳጳስን መስሎ ሁሉን አከናውኖላቸዋል:: አባቶችም ሥራቸውን ከጨረሱ በኋላ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስን ባርከው ወደየ ሃገረ ስብከታቸው ተመልሰዋል:: ለክብረ መንግስተ ሰማያት በቅተዋል:: እኛም እነሆ "አባቶቻችን:
መምሕሮቻችን:
መሠረቶቻችን:
ብርሃኖቻችን:
ምሰሶዎቻችን" እያልን እናከብራቸዋለን::

ቅዱስ ቴዎዶስዮስ የቆረንቶስ ጳጳስ ሲሆን በዘመነ ሰማዕታት ብዙ መከራን አሳልፎ ከሰማዕታት ተቆጥሯል:: ነገር ግን አልተሰየፈም ነበርና እስከ ጉባኤ ኒቅያ ቆይቶ የጉባኤው ተሳታፊ ሆነ::

ከጉባኤው በኋላ ቅዱስ ቴዎዶስዮስ ወደ ሃገሩ ቆረንቶስ ተመልሶ : ሕዝቡን ሲመክር ቆይቶ በዚህች ቀን በመልካም ሽምግልና አርፏል::

††† አምላከ ቅዱሳን ሊቃውንት በጸሎታቸው እኛንም: ቤተ ክርስቲያናችንንም ከክፉ ጠላት ይጠብቅልን::

††† መጋቢት 6 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት