ስንክሳር ወግጻዌ ዘተዋሕዶ
803 subscribers
3.46K photos
104 videos
194 files
1.2K links
የየዕለቱ ስንክሳር እና ግጻዌ የሚቀርብበት ቻናል ነው፡፡

ለማንኛውም አስተያየት እና እርማት
@zetaodokos ላይ ይላኩልን።

👇👇የYoutube Channel ይቀላቀሉ👇👇
https://youtube.com/channel/UCupqpIYe_mMpSM7jMT3Njhw
Download Telegram
እንኳን ለጻድቃን ቅዱሳን አቡነ ዘርዓ ቡሩክ እና 7ቱ ደቂቅ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ

#አቡነ_ዘርዓ_ቡሩክ

=>ሃገራችን ኢትዮዽያ:-
*ብሉይ ከሐዲስ ያልጐደለባት
*በክርስቶስና በድንግል እናቱ ኪደተ እግር የተቀደሰች
*የቅዱሳን መጠጊያ እና
*ብዙ ቅዱሳንን ከእቅፏ ያፈራች ስለ ሆነች የተባረከች ሃገር ትባላለች::

+ሁሉም የሃገራችን ክፍሎች ቅዱሳንን አፍርተዋል:: በምሥራቅም: በምዕራብም: በሰሜንም: በደቡብም ያሉ አካባቢዎች ሁሉ የቅዱሳን ቤቶች ናቸው:: ቅዱሳንን በብዛት ካፈሩ አካባቢዎች አንዱ ደግሞ ምድረ ጐጃም ነው::

+በጐጃም አካባቢ ከተነሱ ቅዱሳን ደግሞ አንዱና ስመ ጥሩ ጻድቅ አቡነ ዘርዓ ቡሩክ ናቸው:: አቡነ ዘርዓ ቡሩክ በብዙ ጐዳና የተለዩ አባት ናቸው:: ለመጥቀስ ያህል እንኩዋ:-

1.በታሪክ ዓለምን ከበው የያዙ 2ቱ ግሩማን አራዊት (ብሔሞትና ሌዋታንን) ጥርስ ቆጥረው: ብዙ ምሥጢራትንም ተመልክተው ተመልሰዋል:: (በነገራችሁ ላይ ይህ ጉዳይ ዛሬም ድረስ ሳይንሱ በብዙ ድካም ያልደረሰበት ነው)
2.ጻድቁ በልደታቸው ጊዜ ዓይነ ስውራንን አብርተዋል:: ለራሳቸው ግን ይህን የግፍ ዓለም ላለማየት ጸልየው ዓይናቸው እንዲጠፋ አድርገዋል::
3.መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚል ቅዱስ ኢያሱ በገባኦን ፀሐይን አቁሟል:: ዘርዓ ቡሩክ ግን በጥበበ እግዚአብሔር ፀሐይን ለ5 ዓመት አቁመዋል::
4.ጻድቁ ከንጽሕናቸው ብዛት 12 ክንፍ (መንፈሳዊ ክንፍ) ተሰጥቷቸው ነበር:: ከዚህ በተረፈም በጾም: በጸሎት: በትርምትና በስብከተ ወንጌል ፍጹም ጽሙድ ነበሩ::

+ጻድቁ የተወለዱት በ16ኛው መቶ ክ/ዘመን እዚያው ጐጃም ውስጥ ሲሆን አባታቸው ደመ ክርስቶስ: እናታቸው ደግሞ ማርያም ሞገሳ ይባላሉ:: ወላጆች በልጅ እጦት ተማለው ይህን የተቀደሰ ፍሬ አገኙ:: "ጸጋ ኢየሱስ" ብለውታል:: ከኢየሱስ ክርስቶስ ተሰጥቷቸዋልና::

+ቀጥሎ የወለዱትንም "ተስፋ ኢየሱስ" ብለውታል:: ይህም የጻድቁ ታናሽ ወንድም ነው:: በሒደት ግን የጸጋ ኢየሱስ ስም በፈቃደ እግዚአብሔር ወደ ዘርዓ ቡሩክነት ተቀይሯል:: ጻድቁን ስመ ጥር ካደረጉዋቸው ሥራዎቻቸው መካከል በአፄ ሱስንዮስ ዘመን የሠሩት ቅድሚያውን ይወስዳል::

+ነገሩ እንዲህ ነው:: በ1598 ዓ/ም በኢትዮዽያ ላይ የነገሡት አፄ ሱስንዮስ ዼጥሮስ ፓኤዝ (ፔድሮ ፓኤዝ) ከሚባል ፈረንጅ መናፍቅ ጋር በፈጠሩት ወዳጅነት ሃይማኖታቸውን ለወጡ:: ካቶሊክ (ሮማዊ)ም ሆኑ::

+በሁዋላም አልፎንሱ ሜንዴዝ የሚሉት እሾህ መጥቶ ሁሉም የኢትዮዽያ ሕዝብ መናፍቅ እንዲሆን ከንጉሡ ጋር መከረ:: ለጊዜው በቤተ መንግስቱ አካባቢ የነበሩ መሣፍንት ተቀላቀሉ:: እየቆየ ግን ዜናው በመላ ሃገሪቱ ተሰማ::

+በተለይ በ1611 በተዋሕዶ አማኞችና በመናፍቁ ንጉሥ መካከል ነገሩ ተካሮ ዻዻሱ አቡነ ስምዖን ጠዳ ላይ መገደላቸው ተሰማ:: በዚህ ጊዜ ገበሬው ከእርሻው: ሴቷ ከማዕድ ቤት: ካህኑ ከመቅደሱ: ነጋዴው ከገበያው እየወጡ ስለ ቀናችው ሃይማኖት ደማቸውን አፈሰሱ::

+በበዓት የተወሰኑ በሺህ የሚቆጠሩ ቅዱሳንም ወጥተው ተሰየፉ:: በዚህ ጊዜም የግሺው አቡነ ዘርዓ ቡሩክ ዳዊታቸውን አንግበው ለሰማዕትነት ሔዱ:: ዓባይ ወንዝ ላይ ሲደርሱ ዳዊታቸውን ወደ ወንዙ ውስጥ ጣሉት::

+ተሻግረውም ከንጉሡ አደባባይ ደንቀዝ ደረሱ:: በጊዜውም ልክ እንደነ ፍቅርተ ክርስቶስና ወለተ ዼጥሮስ እርሳቸውም መከራ ደረሰባቸው:: ንጉሡም ሳይገደሉ እንዲታሠሩ አደረገ:: በጨለማ እስር ቤትም 5 ዓመታትን ሲያሳልፉ ትኩስ ምግብን ያመጡላቸው ነበር::

+እርሳቸው ግን ምግባቸው ሰማያዊ ነበርና አልነኩትም:: ከ5 ዓመት በሁዋላም ያ ሁሉ ምግብ በተአምራት በትኩስነቱ እየጨሰ ተገኝቷል:: ዘርዓ ቡሩክም ከእሥር ተፈትተዋል::
+እግዚአብሔርም በከሐዲው ንጉሥ ላይ ፈርዶ ፋሲል ነግሷል: ሃይማኖት ተመልሷል:: ጻድቁም በዓባይ ወንዝ ላይ የጣሉት ዳዊታቸውን ሳይርስ አግኝተውታል::

+ጐጃም ሲደርሱም ሰይጣን እርሳቸውን መስሎ ሲያስት ስላገኙት ወደ ጥልቁ አስጥመውታል:: በተረፈ ዘመናቸው አቡነ ዘርዓ ቡሩክ ብዙ ተጋድለው ጥር 13 ቀን ዐርፈዋል:: ታኅሳስ 13 ቀን ልደታቸው ነው::

<< ድንቅ ሠሪ አባት ናቸውና ዛሬም በግሺ ብዙ ተአምራት ይደረጋሉ >>

+" #ቅዱሳን_7ቱ_ደቂቅ "+

=>እነዚህ 7 ቅዱሳን ከዘመነ ሰማዕታት እስከ ዘመነ ጻድቃን የተዘረጋ ታሪክ አላቸው:: 7ቱም ባልንጀሮች ሲሆኑ በ2ኛው መቶ ክ/ዘመን በኤፌሶን ተወልደው አድገዋል:: ክርስትናን ተምረውም በወጣትነታቸው የንጉሥ ጭፍሮች ሁነዋል:: የተቀጠሩትም የቤተ መንግስቱን ግምጃ ቤት ለመጠበቅ ነው::

+በሥራቸውም ሆነ በጠባያቸው ደጐች ነበሩና ንጉሡ ዳኬዎስም: ሕዝቡም ይወዷቸው ነበር:: እነርሱ ግን በጉብዝና ወራት ፈጣሪን ማሰብን መርጠው በፍቅር: በጸሎትና በምጽዋት ይተጉ ነበር:: ከጥቂት ዓመታት በሁዋላ ግን ጭንቅ መከራ መጣ::

+ንጉሡ ዳኬዎስ ክርስትናውን ትቶ ጣዖት አምላኪ ሆነ:: አዋጅም አስነገረ:: አዋጁም "ክርስቶስን ያልካደ: ለጣዖትም ያልሰገደ: ሃብት ንብረቱ ለዘረፋ: እጅ እግሩ ለእስር: ደረቱ ለጦር: አንገቱ ለሰይፍ: ቤቱም ለእሳት ይሰጣል" የሚል ነበር:: በዚህ ምክንያት ብዙ ክርስቲያኖች ተሰደዱ::

+የበርካቶቹም ደማቸው ፈሰሰ:: ኤፌሶን የግፍና የአመጻ ከተማ ሆነች:: የመከራ ጽዋው ጊዜውን ጠብቆ ወደ 7ቱ ወጣቶች ዘንድ ደረሰ:: ንጉሡ እነሱንም አስጠርቶ "ለጣዖት ስገዱ" አላቸው:: እነርሱ ግን የአምላካቸውን ፍቅር በዋዛ የሚቀይሩ አልነበሩምና "እንቢ" አሉት::

+ንጉሡ ምንም ክፉና አውሬ ቢሆንም ይወዳቸዋል:: ሊገድላቸው አልፈለገምና አሳሰራቸው:: ከቀናት በሁዋላ አስጠርቶ ሊያታልላቸው ሞከረ:: ግን አልተሳካለትም:: በዚያ ወራት ጦርነት ይበዛ ነበርና ግዛት ለማስፋትም ቢሉ ለማስገበር ዳኬዎስ ወጣ::

+ከመውጣቱ በፊት ግን 7ቱን አስጠርቶ "አሁን ከእስር ፈትቻቹሃለሁ:: ከጦርነት እስክመለስ ከልባችሁ ጋር ምከሩ:: ካልሆነ ሞት ይጠብቃቹሃል" ብሏቸው ነበር የወጣው:: ቅዱሳኑ ንጉሡ እንደ ወጣ ተቀምጠው መከሩ:: ውሳኔንም አስተላለፉ::

+ዓለምን ንቀው: ሃብት ንብረታቸውን መጽውተው: ትንሽ ሳንቲም ብቻም ይዘው በድብቅ ወጡ:: አንድ ወታደር (በጐች አሉት) ይከተላቸው ነበርና የት እንደ ገቡ ተመለከተ:: ቅዱሳኑ ዘወትር በመዓልትና በሌሊት በበዓታቸው ውስጥ ይተጉ ነበር:: ከእነሱም አንዱ በተራ እየወጣ ቂጣ ይገዛ ነበር::

+አንድ ቀን ግን ከእነሱ አንዱ ራት ሊገዛ ሲወጣ ንጉሡ መመለሱን ሰማ:: ወደ በዓቱ ተመልሶ ለወንድሞቹ ነገራቸው:: ከዚያች ቀን በሁዋላ 7ቱም አልወጡም:: በዓታቸውን ዘግተው ሲጸልዩ ደክሟቸው ተኙ:: ከዚያች ቀን በሁዋላ ግን አልነቁም::

+ያ የበጐች ባለቤት (ወታደር) ለብዙ ቀናት አለመውጣታቸውን ሲመለከት "ሙተዋል" ብሎ አዘነ:: በድብቅ ክርስቶስን ያመልከው ነበርና:: እርሱ የቅዱሳኑን ተጋድሎ በድንጋይ ሰሌዳ ላይ ጽፎ ወደ በዓታቸው ውስጥ ጣለው::

+ትልቅ ድንጋይም አምጥቶ ገጠመው:: እነዚህ ቅዱሳን ተኝተዋልና አልነቁም:: ቀናት: ወራት: ዓመታት ተዋልደው ለ372 ዓመት ተኙ:: አንድ ቀን አንድ እረኛ ለሥራ ፈልጐት ድንጋዩን ፈነቀለው:: በዚህ ጊዜ ቅዱሳኑ ነቁ::

+በወቅቱ መልካቸው የወጣት ነው:: እድሜአቸው ግን 400 ሊሞላ ትንሽ ቀርቶት ነበር:: ልክ እንደ አቤሜሌክ ብዙ መተኛታቸው አልታወቃቸውምና ከመካከላቸው አንዱ የራት ዳቦ ሊገዛ ቢወጣ ግራ ተጋባ:: ኤፌሶን የማያውቃት ሌላ ሃገር ሆነችበት:: ከተማዋ ዘምናለች::
††† እንኳን ለጻድቃን ቅዱሳን አቡነ አረጋዊ እና አባ አርከሌድስ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

†††
#አቡነ_አረጋዊ_ዘደብረ_ዳሞ †††

††† ጻድቁ ገድላቸውን የፈጸሙት በኢትዮዽያ ቢሆንም ሃገረ ሙላዳቸው የጥንቱ የሮም ግዛት የሆነችው ታናሽ እስያ ናት:: አቡነ አረጋዊ ከዘጠኙ (ተስዓቱ) ቅዱሳን አንዱ ናቸው:: ዘጠኙ ቅዱሳን ተወልደው ያደጉት ምንም በአንድ የሮም ግዛት ሥር ቢሆንም መነሻ ቦታቸው ግን የተለያየ ነው::

ሁሉንም አንድ ያደረጋቸው መንፈስ ቅዱስ በኪነ ጥበቡ ነው:: በምክንያት ደረጃ እንግለጸው ከተባለ ደግሞ የአንድነታቸው ምሥጢር:-
1.የቀናች ሃይማኖታቸው ተዋሕዶ:
2.ዓላማ (የእግዚአብሔር መንግስት) እና
3.ገዳማዊ ሕይወት ነው::

አቡነ አረጋዊን ጨምሮ ሁሉም ቅዱሳን ዘራቸው ከቤተ መንግስት ነው:: እነርሱ ግን ምድራዊውን ክብር ንቀው ሰማያዊውን ክብር ገንዘብ ማድረግን መርጠዋል:: አስቀድመው ቅዱሳት መጻሕፍትን ያጠኑት አበው በተለያየ ጊዜ እየመነኑ ከሮም ግዛት ወደ ግብጽ በርሃዎች ወርደዋል::

በምናኔ ቅድሚያውን አባ ዸንጠሌዎንና አቡነ አረጋዊ ይይዛሉ:: ዘመኑ የተዋሕዶ አማኞች የሚሰደዱበት 5ኛው መቶ ክ/ዘመን ነበርና እምነትን ላለመለወጥ ዘጠኙ ቅዱሳን ስደትን መረጡ::

በወቅቱ ደግሞ ለስደት መጠለያ የምትሆንና ከኢትዮዽያ የተሻለች ሃገር አልነበረችም:: ስለዚህም በ470ዎቹ ዓ/ም አልዓሜዳ በኢትዮዽያ ነግሦ ሳለ ቅዱሳኑ በአረጋዊ መሪነት መጡ::

ንጉሡም ሲጀመር የእግዚአብሔር እንግዳ ስለሆኑ: ሲቀጥል ደግሞ ቅድስናቸውን ተመልክቶ መልካም አቀባበልን አደረገላቸው:: ማረፊያ ትሆናቸውም ዘንድ አክሱም ውስጥ አንዲት ቦታን ወስኖ ሰጣቸው:: ይህች ቦታ ቤተ ቀጢን ትባላለች:: አቡነ አረጋዊና 8ቱ ቅዱሳን ወደ ሃገራችን እንደገቡ የመጀመሪያ ሥራቸው ቋንቋን መማር ነበር::

ልሳነ ግዕዝን በወጉ ተምረው እዛው አክሱም አካባቢ ሥራቸውን አንድ አሉ:: በወቅቱ በአቡነ ሰላማ: በአብርሃ ወአጽብሐና በአቡነ ሙሴ ቀዳማዊ የተቀጣጠለው ክርስትና በተወሰነ መንገድ ተቀዛቅዞ ነበርና እነ አቡነ አረጋዊ እንደገና አቀጣጠሉት::

ሕዝቡን በራሱ ልሳን ለክርስትና ይነቃቃ ዘንድ ሰበኩት:: የካደውን እየመለሱ: የቀዘቀዘውን እያሟሟቁ ለዓመታት ወንጌልን ሰበኩ:: ቀጣዩ ሥራቸው ደግሞ መጻሕፍትን መተርጐም ሆነ::

ከሃገራቸው ያመጧቸውን ቅዱሳት መጻሕፍት ተከፋፍለው ወደ ግዕዝ ልሳን ተረጐሟቸው:: በዚህም ለሃገራችን ትልቁን ውለታ ዋሉ:: ይህ ሁሉ ሲሆን እነ አቡነ አረጋዊ የሚመገቡትም ሆነ የሚጸልዩት በማሕበር ነበር:: በመካከላቸውም ፍጹም ፍቅር ነበር:: ጸጋ እግዚአብሔር አልተለያቸውም::

የነ አቡነ አረጋዊ ቀጣዩ ተግባራቸው ደግሞ ገዳማዊ ሕይወትን ማስፋፋት ሆነ:: ይህንን ለማድረግ ግን የግድ መለያየት አስፈለጋቸው:: እያንዳንዱም መንፈስ ቅዱስ ወደ መራው ቦታ ሔደ::

*ዸንጠሌዎን በጾማዕት:
*ገሪማ በመደራ:
*ሊቃኖስ በቆናጽል:
*አባ ይምዓታ በገርዓልታ:
*ጽሕማ በጸድያ:
*ሌሎችም በሌላ ቦታ ገዳማትን መሠረቱ::
*አባ አረጋዊ ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ምርጫቸው ዳሞ (እዛው ትግራይ) ሆነ::

በሃገራችን ስም አጠራራቸው ከከበረ አባቶች አንዱ እኒህ ጻድቅ ናቸው:: ጻድቁ የተወለዱት በ5ኛው መቶ ክ/ዘ አጋማሽ አካባቢ ሲሆን ወላጆቻቸው ንጉሥ ይስሐቅና ቅድስት እድና ይባላሉ:: የተወለዱበት አካባቢም ሮም ነው::

ስማቸው ብዙ ዓይነት ነው:: ወላጆቻቸው "ዘሚካኤል" ሲሏቸው በበርሃ "ገብረ አምላክ" ተብለዋል:: በኢትዮዽያ ደግሞ "አረጋዊ" ይባላሉ:: አቡነ አረጋዊ ምንም የንጉሥ ልጅ ቢሆኑም በልጅነታቸው መጻሕፍትን ተምረው ነበርና ጠፍተው ገዳም ገቡ::

በዚያም በገዳመ ዳውናስ (ግብጽ) የታላቁ ቅዱስ ዻኩሚስ ደቀ መዝሙር ሆነው ከነ አባ ቴዎድሮስ ጋር ሥርዓተ መነኮሳትን ተምረዋል:: ከመነኮሱ ከዓመታት በሁዋላም ወደ ሃገራቸው ሮም ተመልሰው በማስተማር 7 ያህል የቤተ መንግስት ሰዎችን ወደ ምናኔ ማርከዋል::

"የት ልሒድ" ብለው ሲያስቡም ቅዱስ መልአክ በክንፉ ጭኖ ወስዶ ኢትዮዽያን አሳያቸው:: ተመልሰውም ለ8 ባልንጀሮቻቸው "ሃገርስ ባሳየሁዋችሁ! ሐዋርያ ሳያስተምራት በሕጉ በሥርዓቱ ጸንታ የምትኖር" ብለው ከ8ቱ ጋር ወደ ኢትዮዽያ መጡ::

በዚህ ጊዜም እናታቸው ቅድስት እድናና ደቀ መዝሙራቸው አባ ማትያስ አብረው ነበሩ:: ወደ ሃገራችን የመጡ በ470ዎቹ አካባቢ ሲሆን አልዓሜዳ በክብር ተቀብሏቸዋል:: በቤተ ቀጢን (አክሱም) ተቀምጠውም መጻሕፍትን እየተረጐሙ: ወንጌልን እየሰበኩ ቆይተዋል::

ለሥራ በተለያዩ ጊዜም አቡነ አረጋዊ በዓት ፍለጋ ብዙ ደክመዋል:: በመጨረሻ ግን ደብረ ዳሞን (ደብረ ሃሌ ሉያን) አይተው ወደዷት:: የሚወጡበት ቢያጡም ጅራቱ 60 ክንድ የሚያህል ዘንዶ ተሸክሞ ከላይ አድርሷቸዋል::

እንደ ወጡም "ሃሌ ሉያ ለአብ: ሃሌ ሉያ ለወልድ: ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ" ብለው ቢያመሰግኑ ከሰማይ ሕብስት ወርዶላቸው ተመግበዋል:: በዚህም ቦታዋ "ደብረ ሃሌ ሉያ" ተብላለች:: ጻድቁ ቦታውን ከገደሙ በሁዋላ ከተለያየ ቦታ መጥተው 6ሺ ያህል ሰዎች በእጃቸው መንኩሰዋል::

ምናኔን በማስፋፋታቸውና ሥርዓቱን በማስተማራቸውም "አቡሆሙ ለመነኮሳት ዘኢትዮዽያ - የኢትዮዽያ መነኮሳት አባት" ይባላሉ:: አቡነ አረጋዊ በሕይወታቸው ከተጋድሎ ባሻገር በወንጌል አገልግሎትና መጻሕፍትን በማዘጋጀትም ደክመዋል::

ቅዱስ ያሬድና አፄ ገብረ መስቀልም ወዳጆቻቸው ነበሩ:: በተራራው ግርጌ ያለችውን ኪዳነ ምሕረትን ለሴቶች ሲገድሟት ቀዳሚዋ መነኮስ እናታቸው ንግስት እድና ሁናለች::

ጻድቁ ንጹሕ ሕይወታቸውን ፈጽመው በተወለዱ በ99 ዓመታቸው በገዳሙ በስተ ምሥራቅ አካባቢ ተሰውረው ብሔረ ሕያዋን ገብተዋል:: ጌታም 15 ትውልድን የሚያስምር የምሕረት ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል:: ዛሬ ጻድቁ የተወለዱበት ቀን ነው::

††† #አባ_አርከሌድስ †††

††† በዚህ ስም የሚጠሩ ቅዱሳን በግብጽም በሃገራችንም አሉ:: ዋናውና በብዙ መጻሕፍት ዜናቸው የተጻፈላቸው ግን ዛሬ የምናከብራቸው ናቸው:: አባ አርከሌድስ የነበሩት በዘመነ ጻድቃን ሲሆን ሃገረ ሙላዳቸው ሮም ናት::

ወላጆቻቸው ክርስቲያን: በዚያውም ላይ ባለ ጠጐች ነበሩ:: አባታቸው ደግሞ መስፍነ ሃገር ነበር:: ቅዱሱን ወልደው: በሕግ በሥርዓት አሳድገዋል:: ለአካለ መጠን አባ አርከሌድስ ሲደርሱ ግን አባታቸው ሞተ::

መዋዕለ ሐዘናቸው ከተፈጸመ በሁዋላም እናት አባ አርከሌድስን ጠርታ:- "ልጄ! ሒድና የአባትህን ሹመት እጅ አድርግ" አለችው:: ለመንገድ የሚያስፈልገውን ሁሉ አሰናድታ: አገልጋዮችንና ብዙ ወርቅ (ለሿሚው አካል የሚሰጥ) ጨምራም ልጇን ሸኘች::

ቅዱስ አርከሌድስም ከእናታቸው ተለይተው በአገልጋዮች ተከበው ወደ መርከብ ገቡ:: በባሕር መካከል ሳሉ ግን ታላቅ ማዕበል ተነስቶ መርከቡን በታተነው:: በመርከቡ የነበረው ሰው ሁሉ ሲያልቅ አባ አርከሌድስ ግን በስባሪ ላይ ተንጠልጥለው ተረፉ::

ዋኝተው ወጥተው ወደ ዳርቻ ሲደርሱም ማዕበል የተፋው አንድ በድን ወድቆ ተመልክተው ፈጸመው አለቀሱ:: ወዲያውም በልባቸው የዚህን ዓለም ኃላፊነት አሰቡ:: ሹመት ፍለጋ መሔዳቸውን ትተው ወደ ገዳም ሔዱ::
††† እንኳን ለጻድቅ አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ዘጉጉቤን ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††


††† #አቡነ_ያፍቅረነ_እግዚእ_ዘጉጉቤን †††

††† በኢትዮዽያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ መካከለኛው ዘመን (በተለይ ከ13ኛው እስከ 15ኛው መቶ ክ/ዘመን ድረስ ያለው) የብርሃን ዘመን ይባላል:: ምክንያቱም ዘመኑ
*ክርስትና ያበበበት::
*መጻሕፍት የተደረሱበት::
*ስብከተ ወንጌል የተስፋፋበት::
*ገዳማዊ ሕይወት የሠመረበት ወቅት በመሆኑ ነው::

ለዚህ ትልቁ አስተዋጽኦ ደግሞ:-
¤አቡነ ተክለ ሃይማኖት::
¤አቡነ ኤዎስጣቴዎስ::
¤አባ ሰላማ ካልዕ::
¤አቡነ ያዕቆብ::
¤ቅዱሱ ንጉሥ ዘርዓ ያዕቆብ::
¤አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ::
¤አቡነ መድኃኒነ እግዚእን የመሰሉ አበው መነሳታቸው ነው::

በተጨማሪም:-
¤12ቱ ንቡራነ ዕድ::
¤7ቱ ከዋክብት::
¤47ቱ ከዋክብት::
¤5ቱ ከዋክብት የሚባሉ አበው አስተዋጽኦም ልዩ ነበር:: ከእነዚህ መካከልም የ7ቱ እና የ47ቱ ከዋክብት አስተማሪ: የአበው 3ቱ ሳሙኤሎች (ዘዋልድባ: ዘጣሬጣና ዘቆየጻ): የሌሎችም እልፍ አእላፍ ቅዱሳን አባት የሆኑት አባ መድኃኒነ እግዚእ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ::

ጻድቁ ቅዱሳኑን ሰብስበው: አስተምረው: አመንኩሰው: መርቀው ሰደው: ሃገራችንን እንዲያበሩ በማድረጋቸው እንደ አባ ኢየሱስ ሞዐ እርሳቸውም "ወላዴ አእላፍ ቅዱሳን" ይባላሉ::

ከእነዚህ ቅዱሳን የጻድቁ ፍሬዎች አንዱ አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ናቸው:: ጻድቁ አንዳንዴ "አፍቀረነ እግዚእ" እየተባሉም ይጠራሉ:: ትርጉሙም "ጌታ ወደደን" እንደ ማለት ነው::

ያፍቅረነ እግዚእ የነበሩት በ14ኛው መቶ ክ/ዘ ሲሆን ቁጥራቸው ከ7ቱ ከዋክብት ነው:: ጻድቁ ከልጅነት ጀምሮ በሥርዓቱ ከማደጋቸው ባሻገር እጅግ የተማሩ እንደነበሩም ይነገርላቸዋል::

ለምናኔ ከወጡ በሁዋላ ከኖሩባቸው ቦታዎችም 3ቱ ተጠቃሽ ናቸው:: የመጀመሪያውና ትልቁን ሥፍራ የሚይዘው ደግሞ ደብረ በንኮል ነው:: ጻድቁ በዚህ ገዳም ከታላቁ ቅዱስ አባ መድኃኒነ እግዚእ ሥርዓተ ገዳምን : ትኅርምተ አበውን : ተጋድሎተ ቅዱሳንን አጥንተው ለመዓርገ ምንኩስና በቅተዋል::

በገዳሙም ለተወሰነ ጊዜ አገልግለው ወደ ጣና አካባቢ ከአቡነ ያሳይና ከአባ ሳሙኤል ዘዋሊ ጋር መጥተዋል:: የመምጣታቸው ምክንያትም ስብከተ ወንጌልን ለማዳረስና ገዳማትን ለመመሥረት ነው::

ሶስቱ ቅዱሳን ለተወሰነ ጊዜ ከቆዩ በሁዋላ አቡነ ሳሙኤል ወደ ዋልድባ ሲሔዱ አቡነ ያሳይ ደግሞ ማንዳባን አቀኑ:: ያፍቅረነ እግዚእም ጌታ ባዘዛቸው መሠረት ጣና ውስጥ ገዳም አቅንተው ኑረዋል:: ይህ ገዳማቸው ዛሬም ድረስ በስማቸው ይጠራል::

ጻድቁ አፍቀረነ እግዚእ 3ኛው የሚታወቁበት ገዳም ማኅበረ ዴጌ (ጻድቃነ ዴጌ) ሲሆን ገዳሙ በአክሱም ዙሪያ ይገኛል:: እርሳቸው 3ሺ ቅዱሳን የተሠወሩበትን ገዳም በማገልገላቸውም ዛሬም ድረስ በአካባቢው የታወቁ ሆነዋል::

በተረፈም አክሱም አካባቢ ሌሎች ገዳማትን እንዳቀኑም ይነገርላቸዋል:: ጻድቁ አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ለብዙ ዘመናት በተጋድሎ : በስብከተ ወንጌልና ገዳማትን በማስፋፋት ከኖሩ በሁዋላ በዚህች ቀን ዐርፈው ለክብሩ : ለርስቱ በቅተዋል::

††† አምላከ ቅዱሳን በጻድቁ አማላጅነት ይቅር ብሎ በረከታቸውን ያሳድርብን::

††† ጥር 19 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ጻድቁ አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ (አፍቀረነ እግዚእ ዘጉጉቤ - ጣና ውስጥ - ከሰባቱ ከዋክብት አንዱ)
2.አባ ባሱራ
3.ቅድስት ኔራ
4.ቅድስት በርስጢና
5.አባ ዝሑራ

††† ወርሐዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላዕክት
2.ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት
3.አባ ዓቢየ እግዚእ ጻድቅ (ታቦታቸው ጎንደር ከተማ ቀበሌ 09 አካባቢ ይገኛል)
4.አቡነ ሥነ ኢየሱስ
5.አቡነ ዮሴፍ ብርሃነ ዓለም

††† ቅዱሳንን ታስቡ ዘንድ ቸል አትበሉ::

††† "እግዚአብሔር ፍርድን ይወድዳልና::
ቅዱሳኑንም አይጥላቸውምና::
ለዘለዓለምም ይጠብቃቸዋል . . .
ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ::
በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ::
የጻድቅ አፍ ጥበብን ያስተምራል::
አንደበቱም ፍርድን ይናገራል::
የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው::
በእርምጃውም አይሰናከልም::" †††
(መዝ. 36፥28-31)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ  ]

💚💛
@sinkisar_gisawe_z_tewahedo
💚💛
    🇯 🇴 🇮 🇳 &🇸 🇭 🇦 🇷 🇪   
        ✥┈┈•◦●◈◎❖◎◈●◦•┈┈✥
  ✧━━━━━━━━━━━━━━━━━✧
      ❍ㅤ           ⎙ㅤ         ⌲ 
ᶜᵒᵐᵐᵉⁿᵗ         ˢᵃᵛᵉ          ˢʰᵃʳᵉ
ጥር 29
ወበዛቲ ዕለት አዕረፈ አብ ክቡር አረጋዊ፡ ወሰማዕተ ጽድቅ
አቡነ ታዴዎስ ዘጽላልሽ፡፡ በዚህች ዕለት ኢትዮጵያዊው ፃድቅ አቡነ ታዴዎስ አረፉ

#አቡነ_ታዴዎስ_ዘጽላልሽ

ትውልድ ሀገራቸው ጽላልሽ (ዞረ) ነው። አባታቸው ሮማንዮስ እናታቸው ማርታ ይባላሉ። አባታቸው ሮማንዮስ ቄስ ነው። የአቡነ ተክለ ሃይማኖት አጎት ናቸው።
በእናታቸው ማኅፀን ሳሉ በጽላልሽ ረሀብ ፀንቶ ነበር። እሳቸው ግንቦት ፳፫ ቀን በመንፈቀ ሌሊት በልብሰ ብርሃን ተጠቅልለው ተወለዱ። ቤታቸው በበረከት ተመላ። ለሀገሬው ዝናብ ዘንቦለት ህዝቡ ከፃድቁ እናትና አባት የተመፀወቱትን ከፍለው ዘሩ።

አቡነ ታዴዎስ በተወለዱ በ፵ ቀናቸው ሐምሌ ፪ ቀን ሲጠመቁ የተዘራው እህል አንድ ሳይቀር አፍርቶ ተገኝቷል።

ዕድሜአቸው ለትምህርት ሲደርስ ለሊቀ ካህናቱ ለሕይወት ብነ ሰጥተዋቸው ሲማሩ አደጉ። አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዳሞት (ወላይታ) ተሻግረው መተሎሚን አስተምረው “በእግዚአብሔር ቸርነት በአንተ ፀሎት መተሎሚን በሃይማኖት ወልጄዋለሁ። በምግባር አሳድጌዋለሁና እህትህን ይዘህ በቶሎ ና፤” ብለው ላኩባቸው።
እህታቸው ትቤጽዮን ትባላለች። የመተሎሚን ወንድም ዝግናን አግብታ አባ ኤልሳዕን ወልዳለች። ከባሏ ተጣልታ ነበርና እሷን ከባሏ አስታርቀው እሳቸው አቡነ ተክለሃይማኖትን እያገለገሉ ፱ አመት ኖረዋል።

በኋላ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወደ አባ በጸሎተ ሚካኤል ሲሄዱ እሳቸውም ወደ ጽላልሽ ተመልሰው ስለነበር አፄ ይኩኖ አምላክ እንድትመክረኝ እንድትገስፀኝ ከቤቴ ተቀመጥ ብለው ከቤተመንግስት አስቀመጣቸው።
ሰይጣን ለፀብ ለምቀኝነት አያርፍምና ጠላ ቤቷን ክፉ የሚገድል ሽታ አሸተታትና ሞተች። አባ ታዴዎስ ወንዝ ገብተው ሲፀልዩ ሙቷ ተነሥታለች። ከዚህ በኋላ ውዳሴ ከንቱ ይሆንብኛል ብለው ወደ ደብረ ሊባኖስ ተመለሱ።

አቡነ ተክለሃይማኖት ወደ ጽጋጋ (ጅጅጋ) ሂድ አሏቸው። ለምን ቢሉ? አባ አኖሬዎስ ሄደው ሲያስተምሩ ያገሬው ሰዎች ደብድበው አስረዋቸው ነበርና እሳቸውን ለማስፈታት ነበር።
የአካባቢው ንጉስ መዩጥ ይባላል። በነፋስ ሰረገላ ተጭነው ሄደው ከፊቱ ወርደው ሲቆሙ ደንግጦ ከሰማይ መላእክት ነህ ወይስ ከሰው ወገን? ቢላቸው። እኔ ከሰው ወገን ነኝ አሉት። ክርስትናንም አስተማሩት ጋኔን ከእሳት ላይ ጥሎት ሲሰቃይ የሚኖር ልጅ ነበረው አድነውለታል።
ይህን አይቶ አምኖ ሕዝቡም እንዲያምኑና ክርስትናን እንዲቀበሉ አዋጅ ነገረ።

እንደ ሐዋርያው ታዴዎስ ፳፭ ግመል በመርፌ ቀዳዳ በተአምራት አሳልፈው በማሳየታቸው አፍጃል የሚባል ያንድ ባለጠጋ ልጅ በምትሐት እንደሚያደርጉት አድርጎ በመናገሩ ከግመሎቹ አንዲቱ ረግጣው ሞተ፤ ይህን ሙሳ የሚባል ልጅም በተቀበረ በሦስተኛው ቀን «አልዓዛርን ከሙታን በአስነሳው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ልጄ ና ተነስ» ብለህ ይህንን መቋሚያዬን ወስደህ ከመቃብሩ ላይ አኑር ብለው በአፍጃል ሰጥተውት እንዳሉት ቢያደርግ አፈፍ ብሎ ተነስቷል።
ይህን አይተው ህዝቡ ሁሉ አምነዋል። ከዚህ በኋላ ሙሳን ሙሴ ብለው ሊቀ ካህናት አድርገው ፲፪ አብያተ ክርስቲያናት አሳንፀው አኖሬዎስን ይዘው ተመልሰዋል።

አቡነ ተክለሃይማኖትም ከንጉሱ ተማክረው ሊቀካህናት ዘጽላልሽ ብለው ሾመዋቸዋል።
ንጉስ ዓምደ ጽዮን ፍቅረ ዝሙት አድሮበት የአባቱን ቅምጥ ቢያገባት ሄደው ገሰፁት። በዚህ የተናደደች የንጉሱ ሚስት የኋሊት አሳስራ ከጥልቅ ገደል አሰጣለቻቸው።
በዚህ ጊዜ የመቶ ሃያ አመት አረጋዊ ነበሩ።

የታዘዘ መልአክ ገብረ እግዚአብሔርና ውቢት የተባሉ ደጋግ ሰዎችን አስነስቶ ስጋቸውን ወስደው ከበዓታቸው ቀብረው የተሰጣቸውንም ቃል ኪዳን በዳግማዊ አፄ ዳዊት ዘመን በህዝቡ ፊት መስክረዋል።
ንጉስ ዳዊትም ዜና ገድላቸውን አጽፈዋል፤ ስጋቸውንም ወደ ከተማቸው በክብር አፍልሰው በተቀደሰ ስፍራ አኑረውታል።

የጻድቁ አባታችን ረድኤት በረከት ይደርብን አሜን!!!