ሙሉጌታ የሕግ ቢሮ(Mulugeta Law Office)
279 subscribers
74 photos
44 files
10 links
በማንኛውም የህግ ጉዳዮች የማማከር እና የጥብቅና አገልግሎት
Download Telegram
በኮንስትራክሽን ውል ጉዳይ የክፍያ ምስክር ወረቀት/payment certificate/ ምንድን ነው?እንዴትስ ይፈጸማል?
#የክፍያ ምስክር ወረቀት/payment certificate/ በአሰሪው በሚመደብ አማካሪ/ተቆጣጣሪ መሀንዲስ እና በተቋራጩ ተረጋግጦና ተማምነውበት የሚፈረም ሲሆን ለተቋራጩ የሚከፈለውን የገንዘብ መጠንም በግልጽ ያስቀምጣል፡፡
#የክፍያ ምስክር ወረቀት ጋር ቴክ ኦፍ ሽት እና ግራንድ ሳመሪ አባሪ ተደርጐ ይያያዛል፡፡
*ቴክ ኦፍ ሽት የአሰሪው አማካሪ/ተቆጣጣሪ መሀንዲስ እና የተቋራጩ መሀንዲስ በግንባታ ቦታ በአካል የሳይት ቪዚት በማካሄድ የተሰራውን ስራ መጠን እና አይነት ከለቀሙ በኋላ በቢል ኦፍ ኳንቲቲ ከተመለከተው የእያንዳንዱ ስራ አይተም ዩኒት ሬት/ነጠላ ዋጋ አንጻር በዝርዝር በተናጠል በዋጋ የሚያስቀምጡበት የተሰራውን ስራ መጠን እና የገንዘብ መጠን ገላጭ ዝርዝር ሰነድ ነው፡፡
*ግራንድ ሳመሪ ደግሞ በዋናነት የግንባታወችን ዝርዝር/ብሎክ በማስቀመጥ የውሉን ዋጋ፣አስቀድሞ የተከናወነ ስራ መጠን፣አሁን የተከናወነ ስራ መጠን እና አጠቃላይ በተቋራጩ የተሰራውን የግንባታ ስራ መጠን ይጠቅሳል፡፡
#የክፍያ ሰርተፍኬት በአብዛኛው በአንድ ገጽ ተጠቃሎ የሚዘጋጅ ሲሆን በይዘት ደረጃ ግን ብዙ መረጃወችን አምቆ የያዘ ሰነድ ነው፡፡
#የክፍያ ሰርተፍኬት በተለይ ክፍያው የመጀመሪያ ዙር፣ሁለተኛ ዙር እያለ በሚታወቅበት መንገድ የሚዘጋጅ ሲሆን የመጨረሻ ዙር ክፍያ የሚባልም አለው፡፡
#የመጀመሪያ ዙር ክፍያ የሚፈጸመው በአብዛኛው ከቅድሚያ ክፍያ በኋላ ሲሆን ክፍያውም ለተሰራ ስራ የሚፈጸም ነው፡፡
#የመጨረሻ ዙር ክፍያ ደግሞ ግንባታው ተጠናቆ ጊዜአዊ ርክክብ/provisional acceptance/ ከተከናወነ በኋላ በህግ ከተቀመጡ ተቀናሾች በስተቀር ቀሪውን የስራ ክፍያ ጠቅልሎ አካቶ ወዲያውኑ በግንባታ ውሉ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ የሚፈጸም ክፍያ ነው፡፡
#የክፍያ ሰርተፍኬት የፕሮጀክቱን ስም፣ቦታ፣አሰሪውን፣ተቋራጩን፣አማካሪውን ይጠቅሳል፡፡ ዋናውን የውል ገንዘብ መጠን፣ተቀጽላ ስራዎችን፣ቫሬሽንን እና የተከናወነውን የስራ መጠን ያመለክታል፡፡ውሉ የተደረገበትን ጊዜ እና ኮመንስመንት ዴት ይጠቁማል፡፡በተጨማሪም የቅድሚያ ክፍያ መጠን እና አድቫንስ ሪፔይ ያመለክታል፡፡በዚህም አስቀድሞ የነበሩ የክፍያ ቁጥሮችን ጭምር ይጠቁማል፡፡ እንደዚሁም የሪቴንሽን መጠን እና የቅጣት መረጃንም የሚሰጥ ነው፡፡ እንግዲህ ይሄን ሁሉ መረጃ በያዘ የክፍያ ሰርተፍኬት ላይ አሰሪው/ተቆጣጣሪው/አማካሪው እና ተቋራጩ የሚፈራረሙበት ይሆናል፡፡
#ስለዚህ የክፍያ ሰርተፍኬት ጸደቀ ማለት በሰርተፍኬቱ ላይ የተመለከተው ስራ ስለመሰራቱ እና ዋጋውንም ጭምር አሰሪውና ተቋራጩ አምነውበታል ማለት ነው፡፡
#እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ነገር የአሰሪው ዋና ግዴታ ለተቋራጩ በወቅቱ ክፍያ መፈጸም ነው፡፡
#የፌዴራል ፕሮክዩርመንት ዳይሬክቲቭ ክሎስ 28.5 ላይ ስለኮንስትራክሽን ስራዎች ክፍያ እንዴት መፈጸም እንደሚገባው ይዘረዝራል፡፡
#በዚህ ረገድ በተለይ ክሎስ 28.5(a) ላይ የተቀመጠው እንደሚያስገነዝበው በኮንስትራክሽን ስራዎች ጉዳይ ክፍያ የሚፈጸመው በአማካሪው/ተቆጣጣሪው የተረጋገጠና የጸደቀ የክፍያ ምስክር ወረቀት/payment certificate/ እንዲቀርብ በማድረግ መሆኑን አስገዳጅ በሆነ ሁኔታ ይደነግጋል፡፡
#እንግዲህ የክፍያ ጥያቄ የሚያቀርብ በመጀመሪያ ተቋራጩ እንደመሆኑ አማካሪው/ተቆጣጣሪው መሀንዲስ የሳይት ቪዚት በማካሄድ የክፍያ ጥያቄውን ትክክለኛነት ካረጋገጠ በኋላ የክፍያ ሰርተፍኬቱን፣ቴክ ኦፍ ሽት እና ግራንድ ሳመሪውን ጨምሮ የሚያጸድቅና አረጋግጦ የሚፈርምበት እና በማህተምም የሚያረጋግጥ ይሆናል፡፡
#አማካሪው/ቶጣጣሪው በተቋራጩ የክፍያ ጥያቄ እንደቀረበለት በ7(ሰባት) ቀናት ውስጥ የማረጋገጡን ስራ ማጠናቀቅ እንደሚገባው በዳይሬክቲቩ ክሎስ 28.5(d) ላይ በአስገዳጅ ሁኔታ ተቀምጧል፡፡
#እንደዚሁም አሰሪው ደግሞ በአማካሪው/ተቆጣጣሪው የተረጋገጠ የክፍያ ሰርተፍኬት በደረሰው በ14(አስራ አራት) ቀናት ውስጥ ለተቋራጩ ክፍያውን መፈጸም እንደሚገባው በአስገዳጅ ሁኔታ ተደንግጓል፡፡
#እንግዲህ ተቋራጩ የክፍያ ሰርተፍኬት በእጁ ይዞ እያለ እና አሰሪውም ደርሶት እያለ ሳይከፍለው ያዘገየበት እንደሆነ በግንባታ ውሉ እና የውል አካል በሚያደርጉት ጀኔራል ኮንዲሽን በተመለከተው አግባብ ተቋራጩ ኪሳራ ከአሰሪው ላይ ለመጠየቅ እንደሚችል ዳይሬክቲቩ ክሎስ 28.5(g) በግልጽ እና በአስገዳጅ ሁኔታ ይደነግጋል፡፡
#ፒፒኤ 2011 ክሎስ 59 እንደዚሁ የኮንስትራክሽን ጉዳይ የስራ ክፍያ የሚፈጸመው በክፍያ ሰርተፍኬት አማካይነት ስለመሆኑ ይገልጻል፡፡
#በአጠቃላይ ከላይ የተመለከተው የክፍያ ሰርተፍኬት ባህሪ እና የህጉ ድንጋጌ የሚያስገነዝበው ተቋራጩ የክፍያ ሰርተፍኬት በአማካሪው/ተቆጣጣሪው እስከጸደቀለት ድረስ ያለምንም ተጨማሪ ቅድመ ሁኔታ ክፍያ ሊፈጸምለት እንደሚገባ ነው፡፡
ጉባኤ አሰፋ
'እንዳልተሰጠ የሚቆጠር ውሳኔ' ሊከሰት የሚችልባቸው አምስት 5ሁኔታዎች፦
አንድ ፍርድ ቤት የሰጠው ውሣኔ በሕግ ከተሰጠው የስረ ነገር የዳኝነት ስልጣን ውጭ የሆነ ጉዳይ በማየት የሰጠው ቢሆንም፣ ይህ ውሣኔ በይግባኝ ታይቶ እንዲታረም ካልተደረገ በስተቀር በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 212 በጉዳዩ ላይ አስገዳጅነት ያለውና የመጨረሻ ውሣኔ ነው፡፡ /ሰ/መ/ቁ. 85718 ቅጽ 15 /
በሰበር መ/ቁ. 38041 ቅጽ 8 እንዲሁ ይህንን በሚያጠናክር መልኩ የሰበር ችሎት እንዳተተው በሕግ አግባብ በፍ/ቤት የተሰጠን ውሣኔ የሞራልን ወይም የሕሊናን አስተሳሰብ መሠረት በማድረግ ዋጋ አልባ ሆኖ እንዲቀር ማድረግ በየትኛውም መለኪያ ተቀባይነት የሚኖረው አይደለም፡፡
ሆኖም በተወሰኑ ሁኔታዎች በፍርድ ቤት የተሰጠ ውሳኔ እንዳልተሰጠ ተቆጥሮ ዋጋ ሊያጣ ይችላል። ከእንዚህ ውስጥ የሚከተሉት አምስቱ የሚከተሉት ናቸው። /የመጀመሪያው በመርህ ደረጃ ነው።/
1/ የሥረ ነገር የዳኝነት ስልጣን በሌለው ፍርድ ቤት የተሰጠ ውሳኔ
አንድ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ከማየቱ በፊት የስረ ነገር የዳኝነት ስልጣን ያለው መሆኑን ማረጋገጥ ያለበት ሲሆን የስረ ነገር የዳኝነት ስልጣን በተከራካሪ ወገኖች ባይነሳም በማናቸውም የክርክር ደረጃ ፍርድ ቤቱ በራሱ ሊያነሳው የሚገባው ጉዳይ መሆኑ ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 9 እና 231/1/ ሰ ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ጉዲይ ነው፡፡ የሥረ ነገር የዳኝነት ስልጣን በሌለው ፍርድ ቤት የተሰጠ ውሳኔ ደግሞ በመርህ ደረጃ እንዳልተሰጠ የሚቆጠር ነው፡፡
ሰ/መ/ቁ. 64703 ቅጽ 12፣ ፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 9፣ 231/1/ ሰ
2. ችሎት ለማስቻል በህጉ የተቀመጠው የዳኞች ቁጥር ባልተሟላበት ሁኔታ የሚሰጥ ውሳኔ
ጉዳዮች በሥነ ሥርዓት ሕጉ መሠረት የሚመሩበት አይነተኛ አላማ ክርክሮችን ፍትሃዊ በሆነ እና ሥርዓት ባለው መንገድ በመምራት በአጭር ጊዜ እና በአነስተኛ ወጭ እንዲቋጩ ማድረግ ስለመሆኑ ይታመናል፡፡ ይህንኑ የሥነ ሥርዓት ሕጉን አላማ ለማሳካት ደግሞ በሕጉ የተመለከቱትን የስነ ሥርዓት ድንጋጌዎችን እንደየአግባብነታቸው መከተልን የግድ ይላል፡፡ በስነ ሥርዓት ሕጉ የተመለከቱት ድንጋጌዎችን እንደየአግባብነታቸው ያለመከተል በተከራካሪ ወገኖች መሰረታዊ መብት ላይ አሉታዊ ውጤት ማስከተሉ አይቀሬ ነው፡፡ ስለሆነም በስነ ስርዓት ሕጉ የተመለከቱት ድንጋጌዎች ተፈፃሚነት ሊኖራቸው የሚገባው ለጉዳዩ አግባብነት ሲኖራቸው እንጂ በዘፈቀደ ሊሆን አይገባም፡፡
ድንጋጌዎቹ አግባብነት ያላቸው ስለመሆኑ ከመለየቱ በተጨማሪ በጉዳዩ ላይ ተገቢነት አለው የሚለውን ትዕዛዝ ወይም ውሣኔ የሚሰጠው ችሎትም በሕጉ አግባብ የተመለከተው የዳኞች ቁጥር የተሟላ ሊሆን ይገባል፡፡ በሕጉ አግባብ ሊሟላ የሚገባው የዳኞች ቁጥር ሳይሟላ የሚሰጠው ትእዛዝ ወይም ውሣኔ እንደተሰጠ የማይቆጠርና ሕጋዊ ውጤት ሊኖረው የሚገባ አይደለም፡፡
ሰ/መ/ቁ 73696 ቅጽ 13
3/ በሞተ ሰው ስም ቀደም ብሎ የተሰጠን ውክልና በመያዝ የሚቀርብ ክስ፣ የሚደረግ ክርክር እና የሚሰጥ ውሣኔ ህጋዊ ዕውቅናና ውጤት ሊሰጠው የማይገባው ነው፡፡
ሰ/መ/ቁ. 95587 ቅጽ 17፣ ፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 57፣ ፍ/ህ/ቁ. 2232/1/
4/ በሕግ አግባብ ባልተቋቋመና አሳሪ ውሳኔ ለመስጠት የህግ ብቃት በሌለው ፍርድ ቤት ወይም ሌላ አካል የተሰጠ ውሳኔ
ፍርድ ቤቶች በፍርድ መሰረት እንዲፈጸም ትዕዛዝ ከመስጠታቸው አስቀድሞ በሕግ አግባብ የተሰጠ የሚፈጸም ውሳኔ መኖሩን የማረጋገጥ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ተከራካሪው የዘመድ ዳኛ አድርጎ ባልመረጠው አማካሪ መሀንዲስ በሚሰጥ ውሳኔ መሰረት እንዲፈጽም ሊገደድ የሚችልበት ሕጋዊ ምክንያት አይኖርም፡፡ የፍትሐ ብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 392 (1) ድንጋጌ አነጋገርም ይህንኑ የሚደግፍ ነው፡፡ ባልተስማማበት እና ባልመረጠው የዘመድ ዳኛ ተሰጠበት የተባለውን ውሳኔ ለማስለወጥም ይግባኝ እንዲያቀርብ የፍትሐ ብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 350 ድንጋጌ ግዴታ አይጥልበትም፡፡
ሰ/መ/ቁ. 97021 ቅጽ 18፣ ፍ/ህ/ቁ. 3325፣ 3326-3346፣ ፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 392 /1/፣ 350
5/ ኢትዩጵያ በፈረመችው አለም አቀፍ ስምምነት መሰረት
ኢትዩጵያ በፈረመችው አለም አቀፍ ስምምነት መሰረት በኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች ላለመዳኘት ነገር ግን ከኢትዩጵያ ዜጎች ጋር ለመሰረተው ግንኙነት በሌላ አግባብ ጉዳዩን ለመጨረስ የሚያስችል ስርዓት ያለው ወገን በዋናው ክርክር ጊዜ ቀርቦ ባለመከራከሩና በይግባኝ ጉዳዩን ባለማሳረሙ ምክንያት ብቻ ስልጣን የሌለው ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ እንዲፈጽም የሚገደድበት አግባብ የለም፡፡
ሰ/መ/ቁ. 98541 ቅጽ 17
Abrham Yohannes
የክስ ምክንያት ምንድነው?

ለጥያቄው ምላሽ የሰበር ችሎት በ 6 መዝገቦች ላይ እንደሚከተለው የህግ ትርጓሜ ሰጥቷል።

1/ አንድ ሰው አንድን ነገር ከአንድ ሰው ላይ ለማግኘት ፍ/ቤቱ እንዲወስንለት ክስ ለማቅረብና ዳኝነት ለማግኘት የሚያስችለው የፍሬ ነገር ሁኔታ

ማንም ሰው በህግ ችሎታ ኖሮት በሌላ ሰው ላይ ማናቸውንም ክስ ለማቅረብ እንዲችል አስቀድሞ ለክሱ መነሻ በሆነው ነገር ወይም ክሱ በተመሠረተበት ነገር ላይ ጥቅም ወይም መብት ያለው መሆኑ መረጋገጥ እንደሚገባው የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 33 ይደነግጋል፡፡ በዚህም ከሣሽ ከተከሣሽ ላይ ሊፈፀም የሚችል መብት አለኝ ብሎ ለማለት አስቀድሞ ለመብቱ መገኘት መነሻ የሆነውን ነገር በማረጋገጥ የተጠየቀውን ዳኝነት ለማግኘት ከሣሹ በሕግ መብት ያለው መሆን ይኖርበታል፡፡
የክስ ምክንያት አለ ብሎ ለመወሰን የሚቻለው በክሱ ላይ የቀረበው ነገር ቢረጋገጥ ከሣሹ የጠየቀውን ዳኝነት ለማግኘት ሕግ ይፈቅድለታል ወይ? ለሚለው ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ መስጠት ሲቻል ነው፡፡
ሰ/መ/ቁ. 16273 ቅጽ 2፣ ስለ አሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ የወጣ አዋጅ ቁ. 42/85 አንቀጽ 9፣ ፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 29፣ 80/2/፣ 224/2/፣ 23/1/ ሀ ፣ 224/2/፣ 23/1//ሀ/፣ 33፣ ሮበርት አለን ሴድለር በችሎቱ እንደተጠቀሰ

2/ ሻጭ ከሽያጭ ውሉ በሚመነጭ ግዴታ የተሸጠውን ነገር ስመ ሀብትነት በሚመለከተው ክፍል ቀርቦ ለማዛወር እንደገባው ግዴታ ይፈጽምልኝ የሚል ክስ የክስ ምክንያት አለው፡፡
ሰ/መ/ቁ. 82234 ቅጽ 15

3/ አንድ ክስ ሊቀርብ የሚገባው የክስ ምክንያት ሲኖረው ሲሆን የክስ ምክንያትም ተከሣሽ ለከሣሽ ሊፈጽመው የሚገባው ግዴታ መኖሩ ጋር ተያይዞ ሊነሣ የሚችለውን ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ መስጠት የሚቻልበት ሁኔታ ስለመኖሩ ሲረጋገጥ የሚታወቅ ነው፡፡
ሰ/መ/ቁ. 33945 ቅጽ 12፣ ፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 231(1) ሀ

4/ ክስ ለማቅረብ የሚያስችል መነሻ ምክንያት
በፍ/ብ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ. 231 ላይ እንደተመለከተው ማንኛውም ፍርድ ቤት የክስ አቤቱታ ሲቀርብለት ተከሣሽ የሆነው ወገን ክሱን እንዲከላከል ከመጥራቱ በፊት ከሳሽ ክሱን ለማቅረብ የሚያስችል መነሻ ምክንያት ያለው ስለመሆኑና ፍ/ቤቱም አቤቱታውን ተቀብሎ ለማየት ስልጣን ያለው ስለመሆኑ መመርመር ይኖርበታል፡፡
ሰ/መ/ቁ. 32147 ቅጽ 6፣ ፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ 231

5/ አንድ ሰው በተለያዩ ምክንያቶች በአባቱ ብቻ ሳይሆን በአሳዳጊው ስም ጭምር ሊጠራ የሚችልባቸው አጋጣሚዎች መኖራቸው የሚታወቅ ሲሆን እንዲህ ዓይነቱ ሰው ተገቢ ሆኖ ባገኘው ጊዜ በአሳዳጊው ስም ጭምር መጠራቱ ቀሪ ሆኖ በፍትሐብሔር ሕጉ መሰረት በአባቱ ስም ብቻ እንዲጠራ የመወሰን መብት ያለው በመሆኑ ይህንኑ መብቱን በፍርድ ለማረጋገጥ የሚያቀርበው የዳኝነት ጥያቄ የክስ ምክንያት የለውም የሚባልበት ሕጋዊ ምክንያት አይኖርም፡፡
ሰ/መ/ቁ. 95995 ቅጽ 15

6/ ከባዶ ቦታ ሽያጭ የመነጨ ግዴታ ለማስፈጸም የሚቀርብ አቤቱታ የክስ ምክንያት የለውም፡፡
ሰ/መ/ቁ. 27739