Ministry of Urban and Infrastructure 🇪🇹🇪🇹
9.97K subscribers
18.7K photos
276 videos
16 files
510 links
This is the official Telegram page of Ministry of Urban and Infrastructure
Download Telegram
እየተጠናቀቀ ያለው ዓመት ኢትዮጵያ በማንሰራራት ላይ እንደምትገኝ የሚያመላክቱ ስኬቶች የተመዘገቡበት ነው ።

ነሃሴ 27፣ 2018 ዓ.ም አዲስ አበባ

እየተጠናቀቀ በሚገኘዉ 2018 ዓ.ም ኢትዮጵያ በማንሰራራት ላይ እንደምትገኝ የሚያመላክቱ ስኬቶችን እንዳስመዘገበች የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡ አገልግሎቱ የዘንድሮ የጳጒሜን ቀናት የሚከበሩበትን ዓውድ፣ የቀናቱን ስያሜ እና መሪ መልእክት ይፋ ያደረገበትን መግለጫ ሰጥቷል፡፡

መግለጫዉን የሰጡት የአገልግሎቱ ሚኒስትር ድኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳ “ጳጒሜን የኢትዮጵያ ማንሰራራት ወር ብሎ ለማክበር የሚያስችሉ ስኬቶች እየተጠናቀቀ ባለው ዓመት መመዝገባቸውን ገልጸዋል ፡፡

ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ቴክኖሎጂ ነክ ዓመታዊ ስኬቶችን በመግለጫቸዉ ያነሡት ሚኒስትር ድኤታዉ የጳጒሜን ቀናት በልዩ ልዩ ስያሜዎች እና ኹነቶች ለማክበር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተጠናቀቁ እንደሚገኙ አመላክተዋል፡፡ አካታች፣ ከ54 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የተሳተፉበት ነፃ እና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የተካሄደበት፣ ኅብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን በፅኑ መሠረት ላይ የሚያስቀምጥ አካታች እና የነበሩ ልዩነቶችን በመፍታት የጋራ ትልሞች ላይ እንዲተኮር የሚያስችል ሀገራዊ ምክክር በስኬት የተጠናቀቀበት፣ የውስጥ አንድነቷ የተጠናከረ እና የዲፕሎማሲ ዐቅሟ ያደገች ኢትዮጵያ የታየችበት ዓመት እንደነበር አቶ ከበደ በመግለጫቸዉ አመላክተዋል፡፡

ከኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች አንጻር የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ ለመፍጠር በወቅታዊ ዓለማቀፋዊ ቀውሶች ጭምር ታልፎ ስኬት የተመዘገበበት፣ የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር የተቻለበት፣ የዕዳ ጫና በከፍተኛ ደረጃ የቀነሰበት፣ ገቢ የመሰብሰብ ዐቅም ከ1.5 ትሪሊዮን ብር የተሻገረበት፣ የኢንዱስትሪ ምርታማነት እና የውጭ ምንዛሪ ግኝት ታሪካዊ ዕድገት ያስመዘገበበት፣ የወጪ ንግድ ገቢ ከ10.2 ቢሊዮን ዶላር የተሻገረበት፣ በአንድ ዓለማቀፍ የኢንቨስትመንት ፎረም ብቻ ከ13.2 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ የኢንቨስትመንት የመግባቢያ ሰነድ የተፈረመበት እና በአብዛኛዉ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወደ ማውጣት ደረጃ የተሸጋገሩበት፣ የግብርና ምርት እና ምርታማነት በጋ ከክረምት በግብዓት አቅርቦት ታግዞ በከፍተኛ ደረጃ የጨመረበት ስኬታማ ዓመት ነበር፡፡

የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ ያስቻሉ ከ100 በላይ የመሶብ አንድ ማእከል አገልግሎቶች የተስፋፉበት፣ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደትን በፅኑ መሠረት የሚያስቀምጥ እና ማኅበራዊ መስተጋብርን የሚያጎለብት ስኬታማ ምክክር የተደረገበት፣ የሕዝቡን የማኅበራዊ መሻቶች ለማሳካት ሰፋፊ የበጎ አድራጎት እና የመሠረተ ልማት ማስፋፋት ሥራዎች የተከወኑበት በውጤቱም ኢትዮጵያን ከተስፋ ብርሃን ወደ ሚጨበት ዕድገት ማሸጋገር የተቻለበት ዓመት እንደነበር ክቡር አቶ ከበደ በመግለጫቸዉ አመላክተዋል፡፡

በታዳሽ ኃይል አቅርቦት፣ ግዙፍ መሠረታዊ ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋት እና ዐዳዲስ መሠረተ ልማቶችን ወደ ግንባታ በማስገባት የተመዘገቡ ተጨባጭ ውጤቶችንም ዳስሰዋል፡፡ የዐፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ እና የቢሾፍቱ ዓለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ መጀመር ከሜጋ ፕሮጀክቶች መካከል በክቡር ሚኒስትር ድኤታዉ በአብነት ተነሥተዋል፡፡ እነዚህን ስኬቶች፣ ከተጀመሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች እና በዕቅድ ከተያዙ ሀገራዊ ትልሞች ጋር በማስተሳሰር ኢትዮጵያ በማንሰራራት ላይ መኾኗንም አመላክተዋል፡፡
የጳጒሜን ቀናት “የኢትዮጵያ ማንሰራራት” በሚል የጋራ መሪ መልእክት ይከበራሉ፡፡
ጳጉሜን 1 - የእመርታ ቀን፣
ጳጉሜን 2 - የማንሰራራት ቀን፣
ጳጉሜን 3 - የጽናት ቀን፣
ጳጉሜን 4- የኅብር ቀን እና
ጳጉሜን 5 - የነገ ቀን በሚሉ ስያሜዎች እንደ ቅደም ተከተላቸዉ በልዩ ልዩ ኹነቶች እንደሚከበሩ ያስታወቁት ሚኒስትር ድኤታዉ ለዚህም ቅድመ ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ እንደሚገኙ አስገንዝበዋል፡፡

ዜጎች በዐዲስ ዓመት ለግል ስኬቶቻቸዉ እንደሚያቅዱት ኹሉ ለኹለንተናዊ ሀገራዊ ብልጽግናም የሚጫወቱትን ሚና ታሳቢ እንዲያደርጉ፣ የመንግሥትን ፖሊሲ እና ስትራቴጂ እንዲሁም ዕቅድ ተገንዝበዉ ተሳትፏቸዉን እንዲያሳድጉ ለማነሣሣት ቀናቱ እንደሚከበሩም ገልጸዋል፡፡ የጳጒሜን ቀናቱን ስያሜ መሠረት በማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄዎች፣ የበጎ አድራጎት እና ማዕድ ማጋራት ተግባራት፣ ነፃ ጤና ምርመራ፣ የደም ልገሳ፣ የፓናል ውይይት እና መሰል መርሐ ግብሮች እንደሚኖሩም አስታውቀዋል፡፡

#FDREGovermentCommunication
❤3👍3
በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን የቤት መግዣ ብድር መልሶ ማጠናከሪያ ኩባንያ ለማቋቋም የሚያስችል ታሪካዊ የትብብር ማዕቀፍ፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (IFC) መካከል ዛሬ መፈረሙን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ ባሰፈሩት መልዕክት እንዳስታወቁት፣ ይህ አዲስ የሚቋቋመው ኩባንያ በ100 ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር ካፒታል የተቋቋመ ሲሆን፣ ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (IFC) ደግሞ ለተቋሙ እስከ 200 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ የፋይናንስ አስተዋፅኦ ያደርግበታል።

ይህ ተቋም ወደ ሥራ ሲገባ በባንክ ዘርፉ ውስጥ የሚታየውን የጥሬ ገንዘብ ፍሰት አለመመጣጠን ችግር የሚቀርፍ ከመሆኑም በላይ፣ በመላው ኢትዮጵያ ተደራሽ የሚሆን የቤት መግዣ ብድር ፋይናንስ አቅርቦትን እንደሚያስገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አብራርተዋል።

በተጨማሪም ይህ አጋርነት መንግሥት በተመጣጣኝ ዋጋ የኢትዮጵያውያንን ክብር የጠበቁ 1.5 ሚሊዮን ቤቶችን ለማቅረብ ያስቀመጠውን ግብ ለማሳካት፣ እንዲሁም በሀገራችን የፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ የግል ዘርፉን ተሳትፎ ይበልጥ ለማስፋት የሚያስችል ወሳኝ እርምጃ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ ፈጣን፣ ጠንካራ እና ሁሉንም ያካተተ ኢኮኖሚ የመገንባት ጥረቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አረጋግጠዋል።
❤5
የፕሬስ መግለጫ

እመርታ ለዘላቂ ከፍታ!

እንኳን ለእመርታ ቀን አደረሳችሁ! እመርታ ከአሉበት የከፍታ ደረጃ ወደ ላይኛዉ መስፈንጠር ነው፡፡ ከፍታን በአዝጋሚ ሂደትም ዘመናትን ወስዶ ማሻሻል ይቻላል፤ በዚያ አግባብ የሚመጣ መሻሻል ከታለመዉ ግብ ለመድረስ የትውልዶችን ጥረት የሚጠይቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ግን በቁጭት ለዘመናት ከቆየንበት ኋላ ቀርነት እና ድህነት በአዝጋሚ ጉዞ ለመላቀቅ ስለማይቻል እመርታዊ ለውጥ ማምጣትን ግብ አድርገን ሠርተን ስኬቶችን እያስመዘገብን ነው፡፡ ያለፉት ጥቂት ዓመታት ጥረቶቻችን ውጤቶች የሚያሳዩትም ይህንኑ ነው፡፡

የኢትዮጵያን ጀርባ ያጎበጡ የውጭ ዕዳዎችን ጫና በመቀነስ፣ ገቢ የመሰብሰብ ዐቅምን በማሳደግ፣ የኢንዱስትሪዎችን የማምረት ዐቅም በማሻሻል፣ የማዕድን ሀብቶች አጠቃቀምን በማላቅ እመርታዊ ለውጦች ተመዝግበዋል፡፡ የመንግሥት አጠቃላይ የማድረግ ዐቅም በእጅጉ ተለውጧል፡፡ ይህንን እመርታዊ ስኬት ማስመዝገብ የተቻለው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን በማድረግ፤ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል፤ የዜጎችን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት በማሳደግ፤ የቢዝነስ ሥርዐቱን ቀልጣፋና ግልጽ በማድረግ፤ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ዐቅም ከዜጋ ተኮር እና ብሔራዊ ጥቅም አንጻር በመግራት የመደመር መንግሥት ባደረገዉ ሰፊ ጥረት ነው፡፡

ኢትዮጵያ የማዕድን ሀብቶቿን በላቀ የኃላፊነት ስሜት በሕጋዊ አግባብ መጠቀም ጀምራለች፤ ታዳሽ ኃይልን በማምረት ከራስ አልፎ ለቀጠናዉ የኃይል ምንጭ ኾናለች፤ ብዝኃ ዘርፍ ኢኮኖሚን በመተግበር ኹለንተናዊ ዕድገቶችን እያስመዘገበች መጥታለች፤ የኢንዱስትሪ ምርቶችን በዓለም ገበያ ተወዳድራ የመሸጥ ዐቅም ፈጥራለች፡፡ የመንግሥት የልማት ዕቅድ ከቁጥ ቁጥ ወጥቶ ትውልድን ታሳቢ ያደረገ ግብ አስቀምጦ እየተተገበረ ነው፡፡ በ2018 ዓ/ም በሁሉም መስክ ከተስፋ ብርሃን ወደሚጨበጥ ለውጥ የመሸጋገር ሀገራዊ ራዕይን ማሳካት ተችሏል፡፡ ኢትዮጵያን በ2023 ዓ.ም አፍሪካዊት የብለጽግና ተምሳሌት የማድረግ ግብ ተቀምጦ ርብርብ እየተደረገ የስኬቱ ዋዜማ እየተቃረበ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በመደመር መንግሥት በተነደፉ የፖሊሲ ሐሳቦች ኹለንተናዊ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ጉዞን ጀምራለች፡፡ በገቢ አሰባሰብ ላይ የታየዉ እመርታ አንዱ አብነት ነው፡፡ የግብር እና ታክስ መሠረትን በማስፋት፣ ገቢ የመሰብሰብ ዐቅምን በማሳደግ፤ የግብር ከፋዩን የመንግሥት አገልግሎት እርካታ በመሶብ አንድ ማእከል እና በዲጂታል አገልግሎቶች ከፍ በማድረግ የላቀ አፈጻጸም ማሳየት ተችሏል፡፡ በዚህም የበጀት ጉድለትን በእጅጉ ማጥበብ ተችሏል፡፡

ባለፉት ጥቂት ዓመታት የመንግሥት ፕሮጀክቶችን የመፈጸም ዐቅም በእጅጉ አድጓል፡፡ ፕሮጀክቶች መቼ እንደሚጀመሩ እና በምን ያህል በጀት እንደሚፈጸሙ ብቻ ሳይኾን መቼ ተጠናቅቀው በትክክል አገልግሎት እንደሚሰጡ ጭምር በከፍተኛ የራስ መተማመን የመሠረት ድንጋይ ሲቀመጥ መናገር የሚቻልበት ቁመና ላይ ተደርሷል፡፡

እመርታዊ ስኬቶችን ዕውቅና ለመስጠት፣ በቀጣዮቹም ዓመታት የበለጠ እመርታዊ ስኬቶችን ለማስመዝገብ መዘጋጀት አስፈላጊ በመኾኑ ዛሬ ጳጒሜን 01 ቀንን “የኢትዮጵያ ማንሰራራት!” በሚል መሪ መልእክት እያከበርን ነው፡፡

እንኳን ለእመርታ ቀን አደረሳችሁ፣ አደረሰን!

ጳጒሜን 01 ቀን 2018 ዓ.ም
የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
አዲስ አበባ
❤2
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መልዕክት

"የእመርታ ቀን

አባቶቻችን የኢትዮጵያን ዳር ድንበር በደምና በአጥንታቸው አስከብረው ታላቅ ሀገር አውርሰውናል፤ ዛሬ ደግሞ እውነተኛ ሉዓላዊነትን እያረጋገጥን ያለነው ከልመናና ከጥገኝነት በተላቀቀው አዲሱና ታሪካዊው መንገዳችን ነው! በሚሊዮን በሚቆጠር ዶላር ስንዴ ከማስገባት ተነስተን ዛሬ የአፍሪካ ቀዳሚ ስንዴ አምራች በመሆን የሚሊዮን ዶላሮችን ወጪ ማስቀረት ችለናል። በ«ሌማት ትሩፋት» የምግብ ዋስትናን በተግባር እያረጋገጥን፣ በ«ኢትዮጵያ ታምርት» ንቅናቄም አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋትና የሥራ ዕድል በመፍጠር ሉዓላዊነታችንን እያረጋገጥን እንገኛለን። ከዚህ ቀደም የማይደፈሩና አይነኬ ይባልላቸው የነበሩ ከባድ የማክሮ-ኢኮኖሚ ሪፎርም ውሳኔዎችን በቁርጠኝነት በመተግበር፤ የሀገራችንን ኢኮኖሚ በፅኑ መሠረት ላይ እየገነባን እንገኛለን። እነዚህ ሁሉ ታላላቅ ድሎች ኢትዮጵያ በሚያጋጥሟት ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች ሸብረክ ሳትል በፅናት መጓዝ መቻሏን የሚያረጋግጡ ህያው ምስክሮች ናቸው፤ ይህ የእመርታ ጉዟችን ለመጪው ዓመት የሰነቀው ተስፋ እጅግ ግዙፍ ነው!"
👎1
እመርታችን ይቀጥላል!
ኢትዮጵያ በራሷ አቅም ትቆማለች!
የተሻለ ነገን ዛሬ እንገነባለን!

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)  መልዕክት፡-
ጳጉሜን -2
የማንሠራራት ቀን

ከቃል ባለፈ በተጨባጭ ስኬት የቆመችው ኢትዮጵያ!

ትናንት “ኢትዮጵያ ተነሥታለች” ስንል ምኞት ሳይሆን ዛሬ በተጨባጭ ያረጋገጥነው እውነት ነው! ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማማ እስከ ዘመናዊው የኮሪደር ልማት፣ ከቢሾፍቱ ሜጋ አውሮፕላን ማረፊያ እስከ ማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ድረስ ሀገራዊ መነቃቃታችን በተግባር ተመስክሯል። ይህ ለውጥ በዜጎቻችን የኑሮ ደረጃ፣ በከተሞች መዘመንና የሥራ ዕድል ላይ እውነተኛ ብርሃን ከመሆኑም በላይ ለልጆቻችን የነገ ብሩህ ተስፋን የሚሰንቅ ታላቅ ርዕይ ነው። ከእንግዲህ ወደኋላ አንመለስም! በጀመርነው ታሪካዊ የማንሠራራት ጉዞ የልማት ኃይላችንን ይበልጥ በማፋጠን የኢትዮጵያን ትንሣኤ ወደ ዘላቂ ብልጽግና ከፍ እናደርጋለን።

#EthiopiaDelivers