Ministry of Urban and Infrastructure 🇪🇹🇪🇹
9.9K subscribers
18.4K photos
269 videos
16 files
507 links
This is the official Telegram page of Ministry of Urban and Infrastructure
Download Telegram
እየተጠናቀቀ ያለው ዓመት ኢትዮጵያ በማንሰራራት ላይ እንደምትገኝ የሚያመላክቱ ስኬቶች የተመዘገቡበት ነው ።

ነሃሴ 27፣ 2018 ዓ.ም አዲስ አበባ

እየተጠናቀቀ በሚገኘዉ 2018 ዓ.ም ኢትዮጵያ በማንሰራራት ላይ እንደምትገኝ የሚያመላክቱ ስኬቶችን እንዳስመዘገበች የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡ አገልግሎቱ የዘንድሮ የጳጒሜን ቀናት የሚከበሩበትን ዓውድ፣ የቀናቱን ስያሜ እና መሪ መልእክት ይፋ ያደረገበትን መግለጫ ሰጥቷል፡፡

መግለጫዉን የሰጡት የአገልግሎቱ ሚኒስትር ድኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳ “ጳጒሜን የኢትዮጵያ ማንሰራራት ወር ብሎ ለማክበር የሚያስችሉ ስኬቶች እየተጠናቀቀ ባለው ዓመት መመዝገባቸውን ገልጸዋል ፡፡

ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ቴክኖሎጂ ነክ ዓመታዊ ስኬቶችን በመግለጫቸዉ ያነሡት ሚኒስትር ድኤታዉ የጳጒሜን ቀናት በልዩ ልዩ ስያሜዎች እና ኹነቶች ለማክበር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተጠናቀቁ እንደሚገኙ አመላክተዋል፡፡ አካታች፣ ከ54 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የተሳተፉበት ነፃ እና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የተካሄደበት፣ ኅብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን በፅኑ መሠረት ላይ የሚያስቀምጥ አካታች እና የነበሩ ልዩነቶችን በመፍታት የጋራ ትልሞች ላይ እንዲተኮር የሚያስችል ሀገራዊ ምክክር በስኬት የተጠናቀቀበት፣ የውስጥ አንድነቷ የተጠናከረ እና የዲፕሎማሲ ዐቅሟ ያደገች ኢትዮጵያ የታየችበት ዓመት እንደነበር አቶ ከበደ በመግለጫቸዉ አመላክተዋል፡፡

ከኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች አንጻር የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ ለመፍጠር በወቅታዊ ዓለማቀፋዊ ቀውሶች ጭምር ታልፎ ስኬት የተመዘገበበት፣ የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር የተቻለበት፣ የዕዳ ጫና በከፍተኛ ደረጃ የቀነሰበት፣ ገቢ የመሰብሰብ ዐቅም ከ1.5 ትሪሊዮን ብር የተሻገረበት፣ የኢንዱስትሪ ምርታማነት እና የውጭ ምንዛሪ ግኝት ታሪካዊ ዕድገት ያስመዘገበበት፣ የወጪ ንግድ ገቢ ከ10.2 ቢሊዮን ዶላር የተሻገረበት፣ በአንድ ዓለማቀፍ የኢንቨስትመንት ፎረም ብቻ ከ13.2 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ የኢንቨስትመንት የመግባቢያ ሰነድ የተፈረመበት እና በአብዛኛዉ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወደ ማውጣት ደረጃ የተሸጋገሩበት፣ የግብርና ምርት እና ምርታማነት በጋ ከክረምት በግብዓት አቅርቦት ታግዞ በከፍተኛ ደረጃ የጨመረበት ስኬታማ ዓመት ነበር፡፡

የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ ያስቻሉ ከ100 በላይ የመሶብ አንድ ማእከል አገልግሎቶች የተስፋፉበት፣ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደትን በፅኑ መሠረት የሚያስቀምጥ እና ማኅበራዊ መስተጋብርን የሚያጎለብት ስኬታማ ምክክር የተደረገበት፣ የሕዝቡን የማኅበራዊ መሻቶች ለማሳካት ሰፋፊ የበጎ አድራጎት እና የመሠረተ ልማት ማስፋፋት ሥራዎች የተከወኑበት በውጤቱም ኢትዮጵያን ከተስፋ ብርሃን ወደ ሚጨበት ዕድገት ማሸጋገር የተቻለበት ዓመት እንደነበር ክቡር አቶ ከበደ በመግለጫቸዉ አመላክተዋል፡፡

በታዳሽ ኃይል አቅርቦት፣ ግዙፍ መሠረታዊ ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋት እና ዐዳዲስ መሠረተ ልማቶችን ወደ ግንባታ በማስገባት የተመዘገቡ ተጨባጭ ውጤቶችንም ዳስሰዋል፡፡ የዐፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ እና የቢሾፍቱ ዓለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ መጀመር ከሜጋ ፕሮጀክቶች መካከል በክቡር ሚኒስትር ድኤታዉ በአብነት ተነሥተዋል፡፡ እነዚህን ስኬቶች፣ ከተጀመሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች እና በዕቅድ ከተያዙ ሀገራዊ ትልሞች ጋር በማስተሳሰር ኢትዮጵያ በማንሰራራት ላይ መኾኗንም አመላክተዋል፡፡
የጳጒሜን ቀናት “የኢትዮጵያ ማንሰራራት” በሚል የጋራ መሪ መልእክት ይከበራሉ፡፡
ጳጉሜን 1 - የእመርታ ቀን፣
ጳጉሜን 2 - የማንሰራራት ቀን፣
ጳጉሜን 3 - የጽናት ቀን፣
ጳጉሜን 4- የኅብር ቀን እና
ጳጉሜን 5 - የነገ ቀን በሚሉ ስያሜዎች እንደ ቅደም ተከተላቸዉ በልዩ ልዩ ኹነቶች እንደሚከበሩ ያስታወቁት ሚኒስትር ድኤታዉ ለዚህም ቅድመ ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ እንደሚገኙ አስገንዝበዋል፡፡

ዜጎች በዐዲስ ዓመት ለግል ስኬቶቻቸዉ እንደሚያቅዱት ኹሉ ለኹለንተናዊ ሀገራዊ ብልጽግናም የሚጫወቱትን ሚና ታሳቢ እንዲያደርጉ፣ የመንግሥትን ፖሊሲ እና ስትራቴጂ እንዲሁም ዕቅድ ተገንዝበዉ ተሳትፏቸዉን እንዲያሳድጉ ለማነሣሣት ቀናቱ እንደሚከበሩም ገልጸዋል፡፡ የጳጒሜን ቀናቱን ስያሜ መሠረት በማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄዎች፣ የበጎ አድራጎት እና ማዕድ ማጋራት ተግባራት፣ ነፃ ጤና ምርመራ፣ የደም ልገሳ፣ የፓናል ውይይት እና መሰል መርሐ ግብሮች እንደሚኖሩም አስታውቀዋል፡፡

#FDREGovermentCommunication
❤2👍2
በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን የቤት መግዣ ብድር መልሶ ማጠናከሪያ ኩባንያ ለማቋቋም የሚያስችል ታሪካዊ የትብብር ማዕቀፍ፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (IFC) መካከል ዛሬ መፈረሙን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ ባሰፈሩት መልዕክት እንዳስታወቁት፣ ይህ አዲስ የሚቋቋመው ኩባንያ በ100 ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር ካፒታል የተቋቋመ ሲሆን፣ ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (IFC) ደግሞ ለተቋሙ እስከ 200 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ የፋይናንስ አስተዋፅኦ ያደርግበታል።

ይህ ተቋም ወደ ሥራ ሲገባ በባንክ ዘርፉ ውስጥ የሚታየውን የጥሬ ገንዘብ ፍሰት አለመመጣጠን ችግር የሚቀርፍ ከመሆኑም በላይ፣ በመላው ኢትዮጵያ ተደራሽ የሚሆን የቤት መግዣ ብድር ፋይናንስ አቅርቦትን እንደሚያስገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አብራርተዋል።

በተጨማሪም ይህ አጋርነት መንግሥት በተመጣጣኝ ዋጋ የኢትዮጵያውያንን ክብር የጠበቁ 1.5 ሚሊዮን ቤቶችን ለማቅረብ ያስቀመጠውን ግብ ለማሳካት፣ እንዲሁም በሀገራችን የፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ የግል ዘርፉን ተሳትፎ ይበልጥ ለማስፋት የሚያስችል ወሳኝ እርምጃ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ ፈጣን፣ ጠንካራ እና ሁሉንም ያካተተ ኢኮኖሚ የመገንባት ጥረቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አረጋግጠዋል።
❤2