Ministry of Urban and Infrastructure 🇪🇹🇪🇹
9.84K subscribers
18.4K photos
268 videos
16 files
507 links
This is the official Telegram page of Ministry of Urban and Infrastructure
Download Telegram
የኢትዮጵያ የመንገድ መሠረተ ልማት እመርታና የመፃኢ እድገት አቅጣጫ

የአንድ ሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የማህበራዊ ትስስር እና የለውጥ ደረጃ ከሚለካባቸው ዋነኛ መስፈርቶች አንዱ የመንገድ መሠረተ ልማት ዝርጋታ፣ ስርጭትና ጥራት ነው።
መንገድ የሀገር የደም ስር ነው ሲባል ማጋነን አይደለም፤ ያለ መንገድ ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚ፣ ልማትና ዕድገት ሊታሰብ አይችልም።

የመንገድ መሠረተ ልማት በጥራትና በብዛት መኖር የዜጎችን እንቀስቃሴ ከማቀላጠፉ ባሻገር፣ ምርቶችና ጥሬ ዕቃዎች በፍጥነት ወደ ማምረቻዎችና ገበያዎች እንዲደርሱ በማድረግ ረገድ ቁልፍ ሚና ይጫወታል።

ኢትዮጵያ ላለፉት አስርት ዓመታት፣ በተለይም ባለፉት ስምንት ዓመታት፣ ለመንገድ መሠረተ ልማት ልዩ ትኩረት በመስጠት ክልሎችን እርስ በርስ፣ ዋና ከተማውን ከክልሎች እንዲሁም ዞኖችን ከዞኖች የሚያስተሳስሩ መጠነ ሰፊ ሥራዎችን ስታከናውን ቆይታለች።
በ2010 ዓ.ም የነበረው የ126 ሺህ 773 ኪሎ ሜትር አጠቃላይ የመንገድ ሽፋን በ2018 ዓ.ም አጋማሽ ወደ 180 ሺህ 232 ኪሎ ሜትር አድጓል። ይህም ባለፉት ስምንት ዓመታት ውስጥ ብቻ ከ53 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ አዳዲስ መንገዶች መገንባታቸውን ያሳያል።

በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ደግሞ ይህንን አኃዝ ወደ 245 ሺህ ኪሎ ሜትር ለማድረስ በዕቅድ እየተሰራ ይገኛል። በ2010 ዓ.ም ከ30 ቢሊየን ብር በታች የነበረው የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በጀት በ2019 ዓ.ም ወደ 121 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በማደግ ከአራት እጥፍ በላይ ጭማሪ አሳይቷል።

ተቋሙ በየዓመቱ ከሀገሪቱ አጠቃላይ የካፒታል በጀት 21 ነጥብ 4 በመቶ ድርሻ በመውሰድ ቀዳሚው የመሠረተ ልማት ተጠቃሚ ለመሆን ችሏል።

የ75 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋው የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር፣ ሀገራዊ የንግድ ኮሪደሮችን የሚያጠናክር ጠንካራ የፌዴራል የመንገድ መረብ በመዘርጋት ላይ ይገኛል። ባለፉት ስምንት ዓመታት ውስጥ ብቻ 182 ፕሮጀክቶች ወደ ግንባታ የገቡ ሲሆን፣ 71 ግዙፍ ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ተጠናቆ ለትራፊክ ክፍት ሆነዋል።

የሀገሪቱን የንግድና የኢንዱስትሪ ማዕከላት የሚያገናኙ እንደ አዲስ አበባ-አዳማ፣ ሞጆ-መቂ-ባቱ-አርሲ ነገሌ እና ድሬዳዋ-ደዋሌ ያሉ የፍጥነት መንገዶች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።
ከለውጡ በፊት የነበረው የፍጥነት መንገድ ሽፋን 84 ነጥብ 7 ኪ.ሜ ብቻ የነበረ ሲሆን÷ በአሁኑ ወቅት ተጨማሪ የፍጥነት መንገዶች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት በቅተዋል።

በቀጣይም ከአዲስ አበባ ወደ ደሴ፣ ጅማ፣ ደብረ ማርቆስ እና ነቀምቴ የሚዘልቁ አራት አዳዲስ የፍጥነት መንገዶችን ለመገንባት የአዋጭነት ጥናት ተጠናቅቋል።

በሚቀጥሉት 10 ዓመታት የሀገሪቱን የፍጥነት መንገዶች ርዝመት ወደ 1 ሺህ 600 ኪሎ ሜትር ለማድረስ ታቅዷል። ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያን ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚያገናኙ እና ቀጣናዊ ትስስርን የሚያጠናክሩ ግዙፍ የመንገድ ፕሮጀክቶች ተገንብተው ለኢኮኖሚው ከፍተኛ አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው።

አዳዲስ መንገዶችን ከመገንባት ባሻገር የነበሩትን ደረጃ ማሻሻል፣ መጠገን እና የዕድሜ ዘመናቸውን ማራዘም የመንገድ አስተዳደሩ ዋነኛ ትኩረት ነው።

በተለይም የከባድ ተሽከርካሪዎችን የጭነት መጠን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የሚዛን ጣቢያዎች ተስፋፍተዋል፤ ያሉትም ዲጂታላይዝ ተደርገዋል። ይህ አሰራር የተሽከርካሪዎችን ክብደት ከሰው እጅ ንክኪ ነፃ በሆነ መንገድ በመመዝገብ፣ የአሰራር ግልጽነትን ለማስፈንና በከባድ ጭነት ምክንያት የሚደርስ የመንገድ ብልሽትን በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

በጥቅሉ፣ የገጠርና የከተማ ትስስርን በማጠናከር፣ የኢኮኖሚ ኮሪደሮችን በማሳደግና ሀገር አቀፍ ልማትን በማፋጠን ረገድ የመንገድ መሠረተ ልማት ዝርጋታው ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ የዕድገትና የብልጽግና ምዕራፍ እየመራት ይገኛል።
የገጠር ልማት መለካት ያለበት በሚገነቡት መሠረተ ልማቶች ብቻ ሳይሆን፣ ተከትሎ በሚመጣው የሰዎች ሕይወት ለውጥ መሆን አለበት።

‎በመሆኑም የገጠር ኮሪደር ልማት ውጥን ተግባራዊና ሰውን ማዕከል ያደረገ አካሄድን በመከተል ላይ ይገኛል። ይህም ትስስርን ማሻሻል፣ ምቹ የኑሮ ሁኔታዎችን መፍጠር እና በገጠር ማሕበረሰብ ውስጥ የኢኮኖሚ ዕድሎችን ማስፋፋት ነው።

‎የዚህ ዐበይት ግብ የተበታተነና የተቆራረጠ ሐብትን በማስተካከል አምራች፣ እርስ በርስ የተሳሰሩ፣ ዘላቂ ልማት ያላቸው እንዲሁም ለመኖርና ለመሥራት ማራኪ የሆኑ የገጠር አካባቢዎችን መገንባት ነው።

Rural development must be measured not only by what is built, but by how people’s lives change as a result.

The rural corridors initiative is therefore taking a practical, people-centered approach: improving connectivity, creating better living conditions, and unlocking economic opportunities within rural communities.

The goal is to move beyond fragmented interventions and build rural areas that are productive, connected, resilient, and attractive places to live and work.

#PMOEthiopia #EthiopiaDelivers
ምክክሩ በስኬት ተጠናቋል- ኮሚሽኑ

ነሐሴ 16 ቀን 2018 ዓ.ም

ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም በይፋ የተጀመረው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ከሳምንታት የምክክር ሂደት በኋላ በዛሬው እለት በስኬት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ገ/ስላሴ የጉባኤውን መጠናቀቅ አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ በዚህ ታሪካዊ መድረክ 4ሺ ኢትዮጵያውያን በአንድ ላይ በመሰባሰብ እጅግ መሰረታዊ በሆኑ ስምንት ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ሲመካካሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡

ተመካካሪዎቹ በመጨረሻም ለዘመናት ለቆዩ አለመግባባቶች መፍትሄ የሚሆኑ ምክረሃሳቦችን አጠናቅረው ለኮሚሽኑ ማስረከባቸውን አክለዋል፡፡

በሂደቱ ተመካካሪዎች በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ በቀላሉ እየተግባቡ፣ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ደግሞ ጊዜ ወስደው ጠንከር ያሉ ውይይቶችን እያደረጉ በመጨረሻም በአብዛኞቹ ጉዳዮች ላይ መግባባት መቻላቸውንም ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ ሂደቱን ሲከታተል ሁሉም የምክክር መድረኮች በመደማማጥ፣ በመከባባር እና በመቻቻል ሲከናወኑ እንደነበር ማረጋገጥ እንደቻለም ነው ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት የተናገሩት፡፡

የሀገራዊ ምክክሩ ዓላማ ልዩነት ያላቸው ባለድርሻ አካላት ተወያይተው የጋራ መግባባት በመፍጠር በጋራ ወደፊት መራመድ የሚችሉበትን እድል መፍጠር እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

ሀገራዊ ምክክር አሸናፊና ተሸናፊን የመለየት ሂደት አይደለም ያሉት ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ይህ ሂደት አንዱ ወገን ተሸንፎ ሌላው ወገን የሚያሸንፍበት ውድድርም አይደለም ብለዋል።

እንደ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ገለፃ በዚህ የምክክር ሂደት ኢትዮጵያዊያን እርስ በእርስ ተዋውቀዋል፣ ጠንካራ ግንኙነቶችን ፈጥረዋል፣ የተለያዩ አመለካከቶችን አዳምጠዋል፣ እንዲሁም የሀገራችንን ፈተናዎች በተመለከተ ሃሳቦችን ተለዋውጠዋል፤ በመጨረሻም መግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡

ይህ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ያሉባትን የሃሳብ ልዩነቶች በምክክር መፍታት መቻሏን ያሳየችበት ታሪካዊ ምእራፍ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ መሳካት አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት በሙሉ በኮሚሽኑ ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
#ENDC
4