ማኅበረ ቅዱሳን አዳማ ማዕከል ሕዝብ ግንኙነት
460 subscribers
1.11K photos
17 videos
1 file
84 links
Download Telegram
አደራ አለብኝ! በሚል መሪ ቃል
ሁለተኛው ዙር አለማቀፍ የድህረ ግቢ ጉባኤ ምሩቃን መርሐግብር መጋቢት 08/2016 ዓ.ም በአዳማ ማዕከል ተካሄደ።

በመርሐ ግብሩ ላይ በመጋቤ አዲስ ቀሲስ ቴድሮስ ትምህርተ ወንጌል የተሰጠ ሲሆን የበገና አገልግሎት በማዕከሉ ዘማሪያን ቀርቦ የልምድ ልውውጥ ያደረጉልን ወንድማችን ዶ/ር ሽመልስ( የማዕከለሉ ልማት ተቋማት ተጠሪ )እና እህታችን ወ/ሮ ቤዛዊት ለማ ነበሩ። ይህ ጉባኤ ከግቢ ጉባኤ በማንኛውም ዓ.ም ተመርቀው ለወጡ ሁሉ በየሶስት ወሩ ይዘጋጃል።
‹‹ነገን ዛሬ እንሥራ!››

ክፍል አንድ

ቤተ ክርስቲያን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደሙ ዋጅቶ የመሠረታት፣ በክርስቶስ ክርስቲያን ለተባልን በሙሉ መሰብሰቢያችን የተቀደሰች ቤታችን ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያን ስንልም ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን፣ የክርስቲያን ወገን፣ የምእመናን አንድነት ወይንም ማኅበረ ምእመናን እያንዳንዱን ማለታችን ነው፡፡ (የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ቁጥር ፩)

ውድ አንባብያን! የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ስለ ቤተ ክርስቲያን ምንነት፣ ታሪክ ወዘተ መተንተን አይደለም፡፡ የነገዋ ቤተ ክርስቲያን ምን መምሰል አለባት? እንዴትስ ለትውልዱ እስከ ክብሯና ግርማ ሞገሷ ትሻገር? የሚለውን አሳሳቢ ጉዳዮችን መዳሰስ ነው እንጂ፡፡

ትውልድ ጅረት ነው፡፡ አንድ ትውልድ አልፎ ሌላ ትውልድ ይተካል፡፡ አንዱ አልፎ ሌላው ሲተካ ግን ተተኪው ትውልድ በቅብብሎሽ የሚተላለፉ ነገሮችን እየተቀበለና እየጨመረባቸው እንደ ዘመኑና እንደ ወቅቱ እያሳደጋቸው፣ እርሱም በተራው ለሌላው ትውልድ እያወረሳቸው ይተላለፋሉ፡፡

ቤተ ክርስቲያን ከትውልድ ወደ ትውልድ በበርካታ ትውልዶች ቅብብሎሽ ከዛሬው ትውልድ ከደረሱ ሀብቶች ዋናዋ ናት፡፡ ሀብት ብዙ ወገን ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሀብተ ሥጋና ሀብተ ነፍስን የምታሰጥ ናት፡፡ በተጋድሎ በጠንካራ ሥራ፣ በብዙ ውጣ ውረድ ደምና ላብ ፈስሶበት የተገነባን ሀብት የተቀበለ ትውልድ ብቻውን ተጠቅሞ ጨርሶ ለተተኪው ትውልድ በተለይ መንፈሳዊ ውርስ ሳያተርፉ መሄድ ዕዳና በደል ነው፡፡ ይህ ሀብት የምንጠቀመው ብቻ ሳይሆን የምናስተላልፈው አደራ ጭምር ነው፡፡

አባቶቻችን ይህን አደራ አላፋለሱም፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ከተቀበሉት አብልጠው፣ ከተጠቀሙት አትርፈው ከጥፋትና ከብክነት ጠብቀው ከእኛ ዘመን ያደረሱልን መተኪያ የሌላት መንፈሳዊ ሀብታችን ናት፡፡
ቁም ነገሩ የዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን ለነገው ትውልድ በምን ሁኔታ ነው የምትተላለፈው? ትውልዱስ እንዴት ነው የሚቀበላት? እኛ የዛሬዎቹ ትውልዶችስ እንዴት ለማስተላለፍ ለማውረስ አስበናል? አባቶቻችን ካወረሱን አጉድለን ወይስ አትርፈን ነው የምናስተላልፋት? የሚሉ ጥያቄዎች መጠየቅ ያለባቸው ናቸው፡፡

ከላይ እንደጠቀስነው ቤተ ክርስቲያን (ምእመኑን፣ ጉባኤውን ወይም አንድነቱን እና ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑን እስከ ሥርዓትና ትውፊቱ) በጥቅል ቤተ ክርስቲያን ብለን ወስደን እንዴት ተቀበልናት እንዴትስ እናስተላልፋት የሚለውን ሐሳብ ማንሳት አስፈላጊ ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያንን እንዴት ተቀበልናት?

አባቶቻችን ቤተ ክርስቲያን እንድትሰፋ፣ ዶግማና ቀኖናዋ እንዲጠበቅ፣ ምእመናን ወንጌል ሰምተው፣ ሃይማኖትን ጠብቀው፣ ምግባር ትሩፋት ሠርተው፣ በንስሓ በሥጋ ወደሙ ተጠብቀው መንግሥቱን ርስቱን እንዲወርሱ፣ ጉባኤው ሰፍቶ፣ አንድነቱ ጸንቶ አንዲኖር፣ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያንም በዓለም እንድትታነጽ፣ ጉባኤም እንዲ ሠራባት፣ ምእመናንም እንዲገለገሉባት ለማድረግ አገልግሉኝ ሳይሉ አገልግለው፣ ለራሳቸው ክብር ሳይሆን ለቤተ ክርስቲያን ክብር፣ ለራሳቸው ምቾት ሳይሆን ለምእመናን ምቾት፣ ለራሳቸው ሥጋዊ ጥቅም ሳይሆን ለቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ ጥቅም በትጋት ሠርተው አልፈዋል፡፡

‹‹ስለዚህም አንታክትም፤ ነገር ግን የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳን የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል›› እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ቤተ ክርስቲያን ስለ ወንጌል የማይታክቱ፣ አደራ ጠባቂ አደራ አስጠባቂ አባቶች ቤተ ክርስቲያንን እስከ ክብሯ ከትውልድ ትውልድ እያሸጋገሩ ከዚህ ትውልድ አድርሰዋታል፡፡ (፪ኛ ቆሮ. ፬፥፲፮፡) ሃይማኖት ለማጽናት፣ ምግባር ለማቅናት፣ ቤተ ክርስቲያንን ለማስፋት፣ ምእመናንን ለማብዛት፣ መናፍቃንን /ከሐድያንን ለመለየት፣ ሕግና ሥርዓት ለማውጣትና ለማስፈጸም በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያንን ሁለንተናዊ ጥቅም ለማስጠበቅ መብቷን ለማስከበር አስተምህሮዋን ለማስፋት እና ለማስቀጠል የጥረት የሚያደርጉ አባቶች በየዘመኑ ስለነበሯት ነው፡፡ በደሙ ለዋጃት ቤተ ክርስቲያን፣ በደሙ ለዋጃቸው ምእመናን /ለመንጋው/ እንዲሁም ለራሳቸው እንዲጠነቀቁ አደራ የተሰጣቸው ባላደራ ናቸውና የአደራቸውን አላጓደሉም፡፡ (ሐዋ.ሥራ ፳÷፳፰)

አባቶቻችን ቤተ ክርስቲያንን ከእኛ ለማድረስ ብዙ መከራን ተቀብለዋል፡፡ መከራው የጀመረው ገና ከሐዋርያት ዘመን ነው፡፡ ገና ከጅምሩም ነው፡፡ ‹‹በኢየሩሳሌም ባለችው ቤተ ክርስቲያን ላይ ታላቅ ስደት ሆነ›› ብሎ መጽሐፍ እንደነገረን (የሐዋ.ሥራ ፰፥፩)፡፡ ይህም የቅዱስ እስጢፋኖስን በድንጋይ ተወግሮ መሞት የጉባኤውን መበተን፣ በቤተ ክርስቲያን ላይ የደረሰውን ስደትና ሥቃይ የሚያስታውስ ቃል ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን በትውልድ ቅብብሎሽ ስትመጣ እንዲሁ አይደለም የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡ ብዙዎች በድንጋይ ተወግረው፣ በእሳት ተቃጥለው፣ በምሳር ተወግተው፣ በሰይፍ ተቀልተው፣ በገደል ተወርውረው በእስራት፣ በእርዛት፣ በረኃብ በጽም ተፈትነው ያቆዩን ናት ለማለት ነው፡፡ (ገድለ ሐዋርያት)

ከሐዋርያት ዘመንም በኋላ በሐዋርያት አበውም በሊቃውንትም ዘመን የቤተ ክርስቲያን ጉዞ አልጋ በአልጋ እንዳልነበር የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ምስክር ነው፡፡ ጥርሱ እንደወለቀው፣ ጺሙ እንደተነጨው፣ ፊቱ እንደተጸፋው እንደ ዲዮስቆሮስ፣ በፓትርያሪክነት ዘመኑ አምስት ጊዜ እንደተጋዘው አትናቴዎስ፣ ንግሥቲቱን በመዝለፉ፣ ሥርዓት አልበኛ ካህናትና ጳጳሳትን ከሹመታቸው በመሻሩ በስደትና በመከራ ሕይወቱ እንዳለፈው እንደ ዮሐንስ አፈወርቅ ያሉ አባቶችን ስናስብ ቤተ ክርስቲያንን ወደ እኛ ለማሸጋገር የተከፈለው ዋጋ ይገባናል፡፡ (የሃይማኖተ አበው ትርጓሜ መቅድም/የቤ ክርስቲያን ታሪክ)

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ከመርቅያን ንጉሥና ከብርክልያ ንግሥት፣ መከራን ተቀብሏል፡፡ በጉባኤ ኬልቄዶን የተነሣውን ምንፍቅና በመቃወሙ፣ የሊቀ ጳጳሱን ደብዳቤ ባለ መቀበሉ፣ ንግሥቲቱና ደንገጡሮቿ ፊቱን ጸፍተው ጺሙን ነጭተው ጥርሱን ሰብረው ወደ ግዞት እንደላኩት የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያስረዳል፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅም ሰነፍና ሥርዓት አልበኛ ካህናትንና ጳጳሳትን በመሻሩ፣ ከተማ ለከተማ የሚዞሩ መነኮሳትን በመገሠፁ፣ በሚሠሩት ግፍ ንግሥቲቱንና ባለ ሥልጣናቱን በድፍረት በመገሠፁ መከራ ደርሶበታል፤ በግፍም በግዞት ሞቷል፡፡ (የቤተ ክርስቲያን ታሪክ/ግንቦት ፲፪ ስንክሳር፣ ሰማዕትነት አያምልጣችሁ) ይህም ለራስ ክብር ሳይሆን ለቤተ ክርስቲያን የተደረገ ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያን በዘመነ ሰማዕታት፣ ከዚያ በኋላም ሆነ በፊት እስከ ዛሬዋ ዕለት ቤተ ክርስቲያን እንድትቀጥል፣ ዘመናትን ተሻግራ ሙሽራዋ ክርስቶስ እስኪመጣ ተከብራ ትጠብቀው ዘንድ፣ ትውልዱ በየዘመኑ የበረከት ፍሬዋን ይመገብ ዘንድ፣ የጸጋ ግምጃዋን ይለብስ ዘንድ፣ የአጋንንትና ክፉ ሰዎችን ውጊያ የተዋጉላት ለክብሯና ለህልውናዋ ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡላት፣ ብርቱ የማይታክቱ አገልጋዮች፣ መሪዎች፣ አማኞች ስለ ነበሯት መሆኑን እንረዳለን፡፡ (፪ኛ ቆሮ. ፬፥፩)

ጠፍር ታጥቀው፣ ጥሬ ቆርጥመው፣ ውኃ ጠጥተው፣ ሰሌን አንጥፈው፣ ማቅ ለብሰው ቤተ ክርስቲያንን የጠበቋት ክፉ ቀንን ያሳለፏት፣ የዚህ ዓለም ሀብት፣ ሹመት ሽልማት፣ ሥጋዊ ደማዊ ጥቅም ያላበላሻቸው አባቶቻችንና እናቶቻችን ብዙ የብዙ ብዙ ነበሩ፡፡ ‹‹የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ዐሳብ ነው›› እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ የወንጌል አለመሰበክ፣ የምእመናን አለ መብዛት፣ የቤተ ክርስቲያን አለ መስፋት፣ የዕለት ዕለት ዐሳብ ሸክም የሆነባቸው፣ እየሠሩ የማይደክሙ፣ ትጉሃን ጽኑዓን አባቶቻችንና እናቶቻችን ለእኛ አደረሱልን፡፡ (፪ኛ ቆሮ.፲፩፥፳፰)

በዚህም የተነሣ ዳር ደንበሯ ሰፍቶ፣ ምእመኖቿ በዝተው፣ አጥር ቅጥሯ ተከብሮ፣ ጉባኤዋ ሰፍቶ፣ መንፈሳዊ ሀብት ንብረቷ ፋፍቶ ደርጅቶ፣ ክብሯ ገናንነቷ ዓለምን ናኝቶ፣ ለወዳጅ ትምክሕት፣ ለጠላት ኀፍረት ቁጭት ፈጥሮ፣ በየአህጉሩ ያለች ገናና ቤተ ክርስቲያንን አስረከቡን፤ እኛም ተረከብን፡፡

ውድ የዚህ ጽሑፍ ተከታታዮች! አምላካችን ቢፈቅድ በሕይወትም ብንኖር ክፍል ሁለትን ይዘንላችሁ እንቀርባለን፤ ቸር እንሰንብት!
"ነገን ዛሬ እንሥራ!"

ክፍል ሁለት


ውድ አንባብያን! እንደምን ሰነበታችሁ? ባለፈው ሳምንት ‹‹ነገን ዛሬ እንሥራ›› በሚል ርእስ ባቀረብንላችሁ ጽሑፍ ቤተ ክርስቲያን ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዴት እየተላለፈች ወደ እኛ እንደደረሰችና እኛም እንዴት ከአባቶቻችንና እናቶቻችን እንደተረከብናት በጥቂቱ የዳሰስንበትን ክፍል አድርሰናችኋል፡፡ በዚህ በክፍል ሁለት ደግሞ ከክፍል አንድ የቀጠለውንና “ቤተ ክርስቲያንን እኛስ እንዴት ለቀጣዩ ትውልድ እናስተላልፋት?፡ የሚለውን ክፍል ይዘንላችሁ ቀርበናል፤ መልካም ንባብ!

ቤተ ክርስቲያንን እንዴት እናስተላልፋት?

ቤተ ክርስቲያን እንዲሁ አልጋ አልጋ በሆነ ሁኔታ ወደ እኛ እንዳልደረሰች በክፍል አንድ አይተናል፡፡ ራሳቸውን የካዱና ሁለንተናዊ ሕይወታቸውን ለቤተ ክርስቲያን ክብር አሳልፈው የሰጡ አባቶች ለዚህ ትውልድ በቅብብሎሽ ያደረሷትን ቤተ ክርስቲያን እኛ የዛሬዎቹ ትውልዶችስ እንዴት ለማስተላለፍ ለማውረስ አስበናል? አባቶቻችን ካወረሱን አጉድለን ወይስ አትርፈን ነው የምናስተላልፋት? ክብረ ክህነትን አጎድለን ነው፤ ወይስ አሙልተን? ክብረ ምንኩስናንስ? የምእመናንስ ቁጥር ጨመርን ወይስ ቀነስን? ዶግማ ቀኖናዋንስ ሸራረፍን ወይስ ጠብቀን ዘለቅን? መታፈርና መከበሯንስ ጨመርንላት? ወይስ አጎደልነባት?
በርካታ ልንመልሳቸው የሚከብዱብን ጥያቄዎች፣ ልናስተካክላቸው የሚገቡ ብልሽቶች፣ ልንሞላቸው የሚገቡ ጎደሎዎች እንዲሁም ልንጠግናቸው የሚገቡ ስብራቶች አሉብን፡፡ በብዙ መልኩ ከተቀበልነው አጉድለናል፣ ለክብሯ የሞቱላትን ቤተ ክርስቲያን ተረክበንና ለክብራችን ስንል ዝቅ እንድትል ምክንያት ሁነናል፡፡ ለጥቅሟ ሲሉ በታሰሩላት አባቶችና እናቶች ቦታ ተቀምጠን ለጥቅማችን ስንል ልእልናዋን አስደፍረናል፤ እንድናገለግላት ተመርጠን አገልግይን ብለናታል፤ ወይም ተገልጋይ ሆነንባታል፤ የተሰበሰቡትን እየበተንን፣ የተከበሩትን እያቃለልንና የታፈሩትን እያስደፈርን ቤተ ክርስቲያኗን ሸክሟን በማቅለል ፋንታ ሸክም ሆነንባታል፡፡

ዶግማዋ እየተሸራረፈ፣ ቀኖናዋ እየተጣሰ፣ መታፈር መከበሯ ቀርቶ የውስጥም የውጭም ጠላት በዝቶባት፣ የዜና ማሟሟቂያ የውሬ ማድመቂያ፣ የልጆቿ ማሸማቀቂያ፣ የጠላቶቿ መሳለቂያ የሆነችን ቤተ ክርስቲያን ለልጆቻችን እናወርሳለን? ወይስ በቀደመ ገናንነቷና ክብሯ እናሸጋግራተለን? የሚለው ለነገ የማይባል የቤት ሥራችን ነው፡፡

አሁን ላይ የቤተ ክርስቲያኗ ተግዳሮት በጣም ዘርፈ ብዙ መሆኑ ለማንም የተደበቀ አይደለም፡፡ ከምንም በላይ ተሰሚነቷን፣ ተከባሪነቷን፣ ሉዓላዊነቷን መመለስ የታፈረችና የተከበረች ማድረግ፣ አጥር እንደ ሌለው ቤት ማንም አልፎ ሄያጅ፣ ዘው ብሎ የሚገባባትና የፈለገውን የሚፈጽምባት፣ ቤተ ክርስቲያን ለልጆቻችን ላለማውረስና የትውልድ ባለዕዳ ላለመሆን አብዝተን መትጋት አለብን፡፡ በኦሪት ዘጸአት ላይ ያለውን ታሪክ እናስታውስ፡፡ ‹‹እግዚአብሔርም እንዲህ አለ፤ በግብጽ ያለውን የሕዝቤን መከራ በእውነት አየሁ፤ ከአስገባሪዎቻቸውም የተነሣ ጩኸታቸውውን ሰማሁ፤ ሥቃያቸውንም አውቃለሁ›› (ዘጸ. ፫፥፯)

በዘመናችን ክርስቲያኖች ካስገባሪዎቻቸው የተነሣ መከራቸው በዝቷል፡፡ ደማቸውን በከንቱ የሚያፈሱ፣ ሀብት ንብረታቸውን የሚዘርፉባቸው፣ መድረሻ እንዲያጡ በሜዳ ተበትነው እረኛ እንደሌላቸው በጎች እንዲቅበዘበዙ የተደረገበት ወቅት መሆኑንና በጥቅሉ ቤተ ክርስቲያን በስደት ላይ ያለችበት መሆኑን ማንም አይዘነጋውም፡፡

ከገዥዎቻቸውና ከአስገባሪዎቻቸው የሚታደግ፣ ባሕርን ከፍሎና ደመና ጋርዶ የሚያሻግር፣ ነጻ ሆኖ ነጻ የሚያወጣ ሙሴ መሆን ከቤተ ክርስቲያን አባቶችና አገልጋዮች አሁን ይጠበቃል፡፡ ያለበዚያ አደራውን መብላት ነው፡፡ ክፉ ገዥዎች ሕዝቡን ሊለቁት ይገባል፤ ብዙዎቹን በዘረኝነት፣ በቋንቋ፣ በፖለቲካ አመለካከት፣ በልዩ ልዩ ሁኔታ፣ ግማሾቹን በኃይል ተብትበው ይዘዋቸዋል፡፡ ያገለግሉት ዘንድ ደግሞ እግዚአብሔር ይፈልጋቸዋልና፤ ሙሴን ሆኖ መገኘት በፈርኦን ፊት በድፍረት ቆሞ ያገለግሉት ዘንድ እግዚአብሔር ይፈልጋቸዋልና ሕዝቡን ልቀቅ፡ ብሎ መናገር እውነተኛ ሙሴ መሆን አሁን ያስፈልጋል፡፡ (ዘጸ.፭፥፩) ምክንያቱም በደሙ የዋጃት ቤተ ክርስቲያን በደሙ የዋጃቸው ምእመናን ናቸውና፡፡

ቤተ ክርስቲያን ስደቷ እንዲቆም፣ መከራዋ ዳርቻ እንዲኖረው፣ የሀገር ባለውለታነቷ ተዘንግቶ እየደረሰባት ላለው መከራና ስደት ማብቂያና መቋጫ እንዲኖረው፣ አንድነቷን የሚፈታተኗት ኃይሎች አደብ እንዲገዙ፣ እንደ ወርቅ የነጻው፣ እንደ ዕንቁ የሚያበራው ዶግማዋና ቀኖናዋ ለነገው ትውልድ ተጠብቆ ይተላለፍ ዘንድ ከምንም በላይ የተሰሚነትና ቅቡልነት ደረጃዋን ለማሳደግ ብዙ ሥራዎች መሥራት ይገባናል፡፡

የነገዋ ቤተ ክርስቲያን በክብረ ክህነት፣ በክብረ ምንኩስና፣ በምእመናን መንፈሳዊ ሕይወት፣ በመልካም አስተዳደር ረገድ፣ በሀብትና ንብረት አስተዳደርና በሰው ኃይል ስምሪት፣ በጋብቻ ሕይወትና በሕፃናት አስተዳደግ እንዲሁም በወጣቶች ሕይወት፣ በወንጌል አገልግሎትና በዓለም አቀፍ ግንኙነት፣ በመንፈሳዊና በቁሳዊ ልማት ረገድ፣ ማኅበራዊ ተሳትፎዋ የጎላ፣ ተጽእኖ ፈጣሪነቷ ታላቅ እንደ ጥንቱ እንዲሆን፣ ተነጋግረው ብቻ ሳይሆን በዐይን ጥቅሻ የሚግባቡ አባቶች፣ አገልጋዮች እንዲሁም ምእመናን እንዲኖሯት ከፍተኛ ሥራ መሥራት ከዚህ ትውልድ ይጠበቃል፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ከእነ ክብሯ ለልጆቻችን ለማስተላለፍ አዲስ ነገር መፍጠር የሚጠበቅብን አይደለም፡፡

ትናንትን ለመመለስ፣ የአባቶቻችንን መንገድ ብቻ መፈተሽ፣ የጥንካሬያቸው ምክንያት ምን እንደነበር መረዳት፣ ቤተ ክርስቲያንን ገናና ያደረጓት፣ ታፍረው ተከብረው ያስከበሯት፣ “ምን ቢያደርጉ፣ እንዴት ቢሠሩ፣ ምን ዓይነት ሰብእናን ቢላበሱ ነው” ብሎ መጠየቅ፣ መልሱንም ከታሪካቸው ከገድላቸው መረዳት ብቻ በቂ ነው፡፡ በእኛ እምነት ቤተ ክርስቲያንን ያተለቃት፣ ያገዘፋት፣ የታፈረች የተከበረች ያደረጋት፣ በጨለማው ዓለም ውስጥ የምትበራ ድንቅ ፋኖስ ያደረጋት ዋና ነገሮች አልጫውን የሚያጣፍጥ፣ ጨለማውን የሚያበራ ድንቅ የሆነ የቅድስና ሕይወት ያላቸው አባቶችና እናቶች የነበሩ መሆኑ ነው፡፡

እነዚህ የቤተ ክርስቲያን ብርሃን የነበሩ አባቶቻችን ደግሞ ክብራቸውና ቅድስናቸው ከክብረ ክህነትና ክብረ ምንኩስና የሚመነጭ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን በዘመናችን የተፈተነችውና ከቀደመ ልዕልናዋ ዝቅ ያለችው ክብረ ክህነትና ክብረ ምንኩስና በገጠመው ተግዳሮት ነው ብሎ መናገር ድፍረት አይሆንም፡፡ የነገዋ ቤተ ክርስቲያን ከፍ ያለች እንድትሆን፣ የቀደመ ተወዳጅነቷን፣ ተሰሚነቷን፣ ተከባሪነቷንና ተገዳዳሪነቷን ለመመለስ ብዙ ሥራዎችን መሥራት የሚጠበቅብን መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን ከሁሉም ሥራዎች የሚቀድሙ፣ ለሁሉም ሥራዎች መሠረትና መሥሪያ ሆነው የሚያገለግሉ ናቸው ብለን የምናምንባቸው ነገሮች ክብረ ክህነትና ክብረ ምንኩስና ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ የቤት ሥራዎቻችን መሆን ሲችሉ ነው፡፡

እነዚህ ሁለት ዐበይት ጉዳዮች ትናንት ለነበረችው፣ ቤተ ክርስቲያን የቅድስና፣ የክብር፣ የልዕልና፣ የመታፈር የመከበር ምንጭ ምክንያት እንደነበሩ፣ እንዚህ ሁለት የቤተ ክርስቲያን ቁልፍ ጉዳዮች ተግዳሮት ሲገጥማቸው ቤተ ክርስቲያን ተግዳሮት እንደገጠማት ፈተና ውስጥ መግባቷን መረዳት አይከብድም፡፡ ስለሆነም ከዛሬዋ ከፍ ያለች፣ ቤተ ክርስቲያን ነገ እንድትኖረን ሐዋርያዊ የሆነው የክህነት ቅብብሎሽና የምድር መላእክት የሰማይ ሰዎች ያስባለው ምንኩስና ወደ ክብሩ ወደ ታሪኩ ሊመለስ ግድ ይላል፡፡

ውድ አንባብያን! የክብረ ክህነትንና ምንኩስናን ምንነትና ለነገዋ ቤተ ክርስቲያን እንዴት መተላለፍ እንዳለበት በቀጣይ ክፍሎች ይዘን እንቀርባለን፤ ቸር እንሰንብት!
Join @mkpublicrelation
Forwarded from Sun Printing
#Guyyaa 5 Qofa Hafe

Maqaa Abbaa Kan Ilmaa Kan Hafuura Qulqulluu Waaqa Tokko Ameen

*BORUU Meedaa* Marsaa 2ffaa
Sagantaan Waltajjii Gaaffii Fi Deebii Kallattii “BORUU MEEDAA” Jedhamu  marsaa 2ffaan mata duree "Bu'uurri Kiristaanummaa eenyu? fi Gaaffiwwan Dubbii Kiristoos Irratti ka'an kanneen biroo" Jedhuun Waldaa Qulqullootaa Wiirtuu Adaamatti Afaan Oromootiin Qophaa’eera!
  Waltajjii Gaaffii fi deebii kanarratti Kallattiin  Argamtanii gaaffii akka gaafattanii fi deebii gahaa akka argattan affeeramtaniittu.
Guyyaa:- 22/7/2016 B.G
Sa'aatii:- 7:30 irraa eegalee

Qoph:- Kutaa Olaanaa Tajaajila  Miidiyaa Wiirtuu Adaamaa

Iddoo:- Galma Biyyaa Lallaba Shawaa Bahaa

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
፭ቀን ብቻ ቀረው

#''ቦሩ ሜዳ''   ፪ኛ ዙር

ቦሩ ሜዳ  የፊት ለፊት የጥያቄ እና መልስ መርሐ ግብር ለ2ኛ ጊዜ በአፋን ኦሮሞ በአዳማ ማዕከል ተዘጋጀ፡፡ “የክርስትና መሠረቱ ማን ነው?” እና ሌሎች የነገረ ክርስቶስ ጥያቄዎችን  በቦሩ ሜዳ የፊት ለፊት የጥቄ እና መልስ መድረክ ላይ  ተገኝተው እንዲጠይቁ እና መልስ እንዲያገኙ ተጋብዘዋል፡፡

ቀን፡- መጋቢት 22/2016 ዓ.ም  ሰዓት፡- ከቀኑ 7፡30 ጀምሮ
አዘጋጅ፡ አዳማ ማዕከል ሚዲያ አገልግሎት ዋና ክፍል
ቦታ:-በም/ሸዋ ሀ/ስብከት አዳራሽ
Forwarded from Sun Printing
Qophiin/Waraabbin Boruu Meedaa Jalqabamee Jiraa .
Forwarded from Sun Printing
"Guyyaa Beellame Jiraati Ni Dhufa"

#"ቀን ቀጥሯልና ይመጣል" 
በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ወርኃዊ ጉባኤ ዛሬ ከቀኑ  8:00 ሰዓት ጀምሮ በአዳማ ማዕከል ጽ/ቤት ይከናወናል::
እርሶም ሌሎችን በመጋበዝ እንዲገኙ በልዑል እግዚአብሔር ስም እናሳስባለን::
#ማኅበረ ቀዱሳን አዳማ ማዕከል አባላት እና ወረዳ ማስተባበሪያ::