ዝክረ ቅዱሳን zikre kidusan
13.1K subscribers
2.36K photos
1 video
20 files
901 links
ዝክረ ቅዱሳን
በጎ/መ/መ/መድኃኔዓለም ቤ/ክ ሰ/ት/ቤት በመምህር ዲ.ን ዮርዳኖስ አበበ ዝክረ ቅዱሳን የተሰኘ ዘወትር ረቡዕ ከ10 ጀምሮ የሚተላለፍ የየለቱን ቅዱሳን በዓል የሚያዘክር ጉባኤ ነው ።

በ you tube ማግኘት ለምትፈልጉ ሊንኩን ተጫኑት
https://www.youtube.com/channel/UCMVZ5_h0K5_w2EKPxIdNmdw

🔴⭕️⚪️ ለወዳጅ ዘመድዎ በማካፈል ቃለ እግዚአብሔርን ያዳር
Download Telegram
Dn Yordanos Abebe
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡
❖ ሚያዝያ ፳፱ ❖
✞✞ እንኩዋን ለጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወርሐዊ በዓለ ልደትና ለቅዱሳኑ ዓመታዊ በዓለ ዕረፍት በሰላም አደረሳችሁ ✞✞
+"+ ተዝካረ በዓሎሙ ለቅዱሳን ቅዱስ አርስጦስ ሐዋርያ ወአባ አካክዮስ ጻድቅ +"+
=>ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዚህ ዕለት ከምታስባቸው ቅዱሳን ሐዋርያው ቅዱስ አርስጦስና አባ አካክዮስ ቅድሚያውን ይይዛሉ::
+"+ አርስጦስ ሐዋርያ +"+
=>ቅዱስ አርስጦስ ከ72ቱ አርድእት አንዱ ሲሆን ከጌታችን እግር ለ3 ዓመታት ቁጭ ብሎ የተማረ: ፈጣሪው ከዋለበት ውሎ: ካደረበት አድሮ: የእጁን ተአምራት ያየ: የቃሉንም ትምሕርት ያደመጠ ሐዋርያ ነው::
+ከጌታችን ዕርገት በሁዋላም በጽርሐ ጽዮን መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ ለስብከተ ወንጌል ወደ ዓለም ወጥቷል:: መጀመሪያ ከዋኖቹ ሐዋርያት ጋር በረዳትነት አገልግሏል:: ከቆይታ በሁዋላ ግን ሃገረ ስብከት ተሰጥቶት ብዙ ነፍሳትን ማርኩዋል:: አሕዛብንም ካለማመን ወደ ማመን አምጥቷል::
+በነዚህ ጊዜያት ጭንቅ ጭንቅ መከራዎች ደርሰውበታል:: ቅዱስ አርስጦስ ሐዋርያ በተሰጠው መክሊት አትርፎ ፈጣሪውንም ደስ አሰኝቶ በዚሕች ቀን አርፏል::
+"+ አባ አካክዮስ +"+
=>ዳግመኛ በዚህ ቀን አባ አካክዮስ አርፏል:: ቅዱሱ ከሕጻንነቱ ጀምሮ ንጽሕናን ያዘወተረ: በገዳማዊ የቅድስና ሕይወቱ የተመሠከረለት ነው:: ምሑርነቱንና ቅድስናውን የተመለከቱ ሰዎች በኢየሩሳሌም ላይ ዽዽስናን ሹመውታል::
+በመንበረ ዽዽስናውም ላይ እያለ ዕረፍት አልነበረውም:: ኢ-አማንያን ይገርፉት: ያስሩት: ያረሰቃዩትም ነበር:: ቤተ ክርስቲያን ስለ ተጋድሎው ጻድቅ: የዋሕና ንጹሕ ብላ ትጠራዋለች::
=>እግዚአብሔር ከቅዱሳኑ ረድኤት: ጸጋና በረከት ይክፈለን::
=>ሚያዝያ 29 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ አርስጦስ ሐዋርያ (ከ72ቱ አርድእት)
2.አባ አካክዮስ ዘኢየሩሳሌም (ጻድቅና ንጹሕ)
3.አባ ገምሶ ሰማዕት
=>ወርኀዊ በዓላት
1.የፈጣሪያችንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት
2.ቅድስት አርሴማ ድንግል
3.ቅዱስ ዼጥሮስ ተፍጻሜተ ሰማዕት
4.ቅዱስ ማርቆስ ዘቶርማቅ
5.ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ኢትዮዽያዊት
6.ቅዱስ ዘርዐ ክርስቶስ (ጻድቅና ሰማዕት)
=>+"+ ሰብዓውም በደስታ ተመልሰው ጌታ ሆይ! አጋንንት
ስንኩዋ በስምህ ተገዝተውልናል አሉት:: እንዲህም
አላቸው:- 'ሰይጣንን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ
አየሁ:: እነሆ እባቡንና ጊንጡን ትረግጡ ዘንድ በጠላትም
ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችሁአለሁ::
የሚጐዳችሁም ምንም የለም:: ነገር ግን መናፍስት ስለ
ተገዙላችሁ በዚህ ደስ አይበላችሁ:: ስማችሁ ግን
በሰማያት ስለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ:: +"+
(ሉቃ.10:17-20)
<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
Dn Yordanos Abebe
<<< በስመ አብ : ወወልድ : ወመንፈስ ቅዱስ : አሐዱ አምላክ . . . አሜን:: >>>
<< በበዓለ ሃምሳ ንስሃ ለምን ተከለከለ? >>
=>በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያለ ምክንያት የሚደረግ : ያለ ምሥጢርም የሚከወን ምንም ነገር የለም:: የሃይማኖትን ትምህርት አብዝተን በተማርን ቁጥር የምናውቀው አለማወቃችን ነውና ምንም ያህል ብንማር : የአዋቂነት መንፈስም ቢሰማን ከመጠየቅ ወደ ጐን አንበል:: መጠየቅ ለበጐ እስከሆነ ድረስ ሁሌም ሸጋ ነው:: ግን ልብን እያጣመሙ ቢያደርጉት ደግሞ ገደል ይከታል::
+ወደ ጉዳዬ ልመለስና ሁሌ የሚገርመኝ የትውልዱ አመለካከት ነው:: ጾም ሲመጣ "ለምን? . . . አልበዛም? . . ." ዓይነት ቅሬታዎች ይበዛሉ:: በዓለ ሃምሳ ሲመጣ ደግሞ "እንዴት ይህን ያህል ቀን ይበላል? . . ." ባዩ ይከተላል::
+ቤተ ክርስቲያን ግን ሁሉን የምትለን ለጉዳይ : ለምክንያትና ለእኛ ጥቅም ነው:: ለምሳሌ:- በዓለ ሃምሳ ድንገት እንደ እንግዳ ደርሶ : እንደ ውሃ ፈሶ የመጣ ሥርዓት አይደለም:: ይልቁኑ ምሳሌ ተመስሎለት በብሉይ ኪዳንም ሲከወን የነበረ እንጂ::
+እንደሚታወቀው እስራኤል ከግብጽ ባርነት በ9 መቅሰፍት : በ10ኛ ሞተ በኩር ወጥተው : በ11ኛ ስጥመት ጠላት ጠፍቶላቸው ወደ ምድረ ርስት ተጉዘዋል:: ቅዱስና የእግዚአብሔር ሰው ሙሴም ከእግዚአብሔር እየተቀበለ ብዙ ሥርዓቶችን ለቤተ እስራኤል አስተምሯል::
+እነዚህ ሥርዓቶች ሁሉ ለሐዲስ ኪዳን ምሥጢረ ድኅነት ጥላና ምሳሌዎችም ነበሩ:: በኦሪት ዘሌዋውያን ላይ ጌታ እንዲህ ይላል:-
". . . ከሰንበት ማግስት ፍጹም ሰባት ጊዜ ሰባት ቀን ቁጠሩ:: እስከ ሰባተኛ ሰንበት ማግስት ድረስ አምሳ ቀን ቁጠሩ:: አዲሱንም የእህል ቁርባን ወደ እግዚአብሔር አቅርቡ::" (ዘሌ. 23:15)
+ይህም "በዓለ ሰዊት (የእሸት በዓል)" የሚባል ሲሆን ከፋሲካ 7 ሱባኤ (49 ቀን) ተቆጥሮ : በሰንበት (ቅዳሜ) ማግስት (እሑድ ቀን) በዓለ ሃምሳ ይውላል:: በዓሉ በግሪክኛው "ዸንጠቆስቴ (Pentecost)" ይባላል:: "በዓለ ሃምሳ" እንደ ማለት ነው::
+ለዚያም ነው ቅዱስ መጽሐፍ የመንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት በዚህ ቀን መሰጠትን ሊነግረን ሲጀምር "ወአመ ተፈጸመ መዋዕለ ዸንጠኮስቴ . . ." የሚለው:: (ሐዋ. 2:1) በዓለ ሃምሳ (50ው ቀናት) በብሉይ "የእሸት በዓል" ቢባሉም ለሐዲስ ኪዳን ግን "የሰዊት (እሸት) መንፈሳዊ" ዕለታት ናቸው::
+ጌታ መድኃኔ ዓለም ስለ እኛ መከራ ተቀብሎ : ሙቶ ከተነሳ በሁዋላ 50 ያሉት ቀናት የዕረፍት : የተድላ : የመንፈሳዊ ሐሴት ቀናት ናቸው:: በእነዚህ ዕለታት ማዘን : ማልቀስ : ሙሾ ማውረድ : ንስሃ መግባት ወዘተ. አይፈቀድም::
=>ለምን?
1.ለእኛ ካሣ በጌታችን መፈጸሙን የምሰናስብባቸው ቀናት ናቸውና:: በእነዚህ ዕለታት ብናዝን "አልተካሰልንም" ያሰኛልና::
2.በዚህ ጊዜ መስገድ : መጾም "ክርስቶስ በከፈለልን ዋጋ ሳይሆን በራሴ ድካም (ተጋድሎ) ብቻ እድናለሁ" ከማለት ይቆጠራልና::
3."ፍስሐ ወሰላም ለእለ አመነ - ላመን ሁሉ ደስታና ሰላም ተደረገልን" ተብሎ በነግህ በሠርክ በሚዘመርበት ጊዜ ማዘን . . . ሲጀመር ካለማመን : ሲቀጥል ደግሞ "ደስታው አይመለከተኝም" ከማለት ይቆጠራልና::
4.50ውም ቀናት እንደ ዕለተ ሰንበት ይቆጠራሉና:: መጾምና መስገድ በዓል ያስሽራልና::
5.ዋናው ምሥጢር ግን እነዚህ 50 ዕለታት የአዝማነ መንግስተ ሰማያት (የሰማያዊው ዕረፍት) ምሳሌዎች ናቸው::
ስለዚህ በእነዚህ ቀናት መጾም : መስገድ "መንግስተ ሰማያት ውስጥ ከገቡ በሁዋላ ድካም : መውጣት መውረድ አለ" ያሰኛልና ነው::
+በዚያውም ላይ "ኢታጹርዎሙ ጾረ ክቡደ (ከባድ ሸክም አታሸክሙ)" የተባለ ትዕዛዝ አለና ቅዱሳን አበው በጾም የተጐዳ ሰውነት ካልጠገነ ወጥቶ ወርዶ : ሠርቶ መብላት ይቸግረዋልና ሰውነታችን እንዲጠገን : ይህንን በፈሊጥ ሠርተዋል::
+ስለዚህም:-
"ሐጋጌ አጽዋም እምስቴ::
ወሠራዔ መብልዕ በዸንጠኮስቴ::" እያልን አበውን እናከብራለን:: (አርኬ)
+ስለዚህ በበዓለ ሃምሳ ጾም : ስግደት : ንስሃ : ሐዘን : ልቅሶ . . . የለም:: አይፈቀድምም::
<<ግን ይህንን ተከትሎ 50ውን ቀን ሙሉ ሆድ እስኪተረተር ከበላን ጉዳቱ ሥጋዊም : መንፈሳዊም ይሆናል!!>>
+አበው እንደነገሩን "እንደ ልባችሁ ብሉ" ሳይሆን የተባለው "ጦም አትዋሉ" ነው:: ለምሳሌ:-
1.በልቶ ጠጥቶ ከሚመጣ ኃጢአት : ክፋትና ፈተና ለመጠበቅ 50ውን ቀናት ጥሬ የሚበሉ አሉ::
2.ጠዋት ተመግበው ከ24 ሰዓት በሁዋላ ጠዋት የሚመገቡ አሉ::
3.መጥነው ጥቂት በልተው አምላካቸውን የሚያመሰግኑ አሉ::
4.ነዳያንን አጥግበው እነርሱ ከነዳያን ትራፊ የሚቀምሱ አሉ::
+እኛም ከእነዚህ መካከል የሚስማማንን መርጠን ልንከውን : በተለይ ደግሞ በጸሎት ልንተጋ ይገባል:: አልያ ብሉ ተብሏል ብለን ያለ ቅጥ ብንበላ : ብንጠጣ እኛው ራሳችን የሰይጣን ራት መሆናችን ነውና ልብ እንበል:: ማስተዋልንም ገንዘብ እናድርግ::
"እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ የሥጋን ነገር ያስባሉና:: እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን የመንፈስን ነገር ያስባሉ::
ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና:: ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው::
ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነውና:: ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛምና:: መገዛትም ተስኖታል::
በሥጋ ያሉትም እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኙት አይችሉም::" (ሮሜ. 8:5)
=>አምላከ ቅዱሳን ማስተዋሉን ያድለን::
<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>
Dn Yordanos Abebe
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ
አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞
❖ ሚያዝያ ፴ ❖
❖ እንኳን አደረሳችሁ ❖
❖ሚያዝያ 30 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
=>እንዲህ ኃጢአታችን ጽዋዑን ሞልቶ በተረፈበት በዚህ
ዘመን አንዲት ሰዓትም ውድ የሆነች የንስሃ ዕድሜ ናት::
እግዚአብሔር
ግን ደግ ነውና ይሔው ሚያዝያን አስፈጸመን::
+ባይገባን ነው እንጂ በዚሕች ወር ውስጥ:-
*ሚሊየኖች በደዌ የአልጋ ቁራኛ ሁነዋል::
*ሚሊየኖችም ለንስሃ ሳይበቁ እንዲሁ አንቀላፍተዋል
(ሙተዋል)::
+እስኪ እርሱ አምላካችን ቀሪዋን ዘመን ደግሞ ለንስሃና
ለመልካም ሥራ ባርኮ ይስጠን::
+"+ ቅዱስ ማርቆስ ወንጌላዊ +"+
+በዚሕች ዕለት ከ72ቱ አርድእት አንዱ የሆነ: ወንጌላዊ:
ሐዋርያ: ሰማዕት: ዘአንበሳና ርዕሰ ሊቃነ ዻዻሳት የተባለ
ቅዱስ ማርቆስ በሰማዕትነት ግብፅ ውስጥ ዐርፏል::
+ቅዱስ ማርቆስ እናቱ ማርያም: አባቱ አርስጥቦሎስ
ይባላሉ:: በልጅነቱ ኦሪትንና የዘመኑን ጥበብ ሥጋዊ
በሚገባ ተምሮ
ክርስቶስን ከቤተሰቦቹ ጋር ተከትሏል::
+የመጀመሪያ ስሙ ዮሐንስ ሲሆን ከ120ው ቤተሰብ
በእድሜ በጣም ትንሹ (20 ዓመት) እርሱ ነበር:: ለ3
ዓመታት ከጌታ
እግር ሥር ተምሮ: በበዓለ ሃምሳ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን
ተቀብሎ ለሐዋርያዊ አገልግሎት ብዙ ደክሟል::
+በተለይ የግብፅና የኢትዮዽያ ቤተ ክርስቲያን አባት ነው::
ክህነትን ያገኘን ከርሱ ነውና:: ቅዱስ ማርቆስ 16 ምዕራፍ
ያለውን ወንጌሉን ሲጽፍ ኪሩብ ገጸ አንበሳ በቀኙ: ሊቀ
ሐዋርያት በግራው ሆነው ይራዱት ነበር::
+ቅዱሱ ክቅዱስ ዻውሎስ: ከበርናባስና ዼጥሮስ ጋር
ተጉዟል:: ከብዙ ስቃይና መከራ በኋላ ሰሜን አፍሪካ
አካባቢ በዚህ ቀን [በ60 ዓ/ም አካባቢ]
አረማውያን ገድለውታል::
=>ዳግመኛ በዚህ ቀን የቅዱስ ማርቆስን ወላጆችን
እናስባቸው ዘንድ ይገባል::
❖ቅዱስ አርስጥቦሎስ (አባቱ) የጌታ ቅን አገልጋይ
የነበረ፡፡
❖ቅድስት ማርያም (እናቱ)
*ከ36ቱ ቅዱሳት አንስት አንዷ:
*ጌታችንን ያገለገለች:
*ቤቷን ለሐዋርያትና ለጌታ በስጦታ ያበረከተች ቅድስት
ናት::
+ቤቷም (ጽርሐ ጽዮን) የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን
ስትሆን ይህች ቤት መንፈስ ቅዱስ ወርዶባታል::
የእመቤታችን ግንዘትም
ተከናውኖባታል::
❖እግዚአብሔር ከሐዋርያዊው ቅዱስ ቤተሰብ በረከትን
ያድለን::
=>ሚያዝያ 30 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ማርቆስ ሐዋርያ
2.ቅዱስ አርስጥቦሎስ (አባቱ)
3.ቅድስት ማርያም (እናቱ)
=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
2.አባ ሣሉሲ ክቡር
3.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ነባቤ መለኮት
4.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
=>+"+ . . . እጅግ ሰዎች ተከማችተው ይጸልዩበት ወደ
ነበረው ማርቆስ ወደ ተባለው ወደ ዮሐንስ እናት ወደ
ማርያም ቤት መጣ:: ዼጥሮስም የደጁን መዝጊያ
ባንኩዋኩዋ ጊዜ ሮዴ የሚሏት አንዲት አገልጋይ ትሰማ
ዘንድ ቀረበች:: የዼጥሮስ ድምጽ መሆኑንም ባወቀች ጊዜ
ከደስታዋ የተነሳ ደጁን አልከፈተችም:: ነገር ግን ወደ
ውስጥ ሮጣ ዼጥሮስ በደጅ ፊት ቆሞ እንዳለ አወራች::
+"+ (ሐዋ. 12:12-15)
<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
Dn Yordanos Abebe
እንኩዋን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ
+*" ልደታ ለማርያም ድንግል "*+
<< ኢያቄም ወሐና ወለዱ ለነ ሰማየ:
ሰማዮሙኒ አስረቀት ለነ ፀሐየ:: >>
" ኢያቄምና ሐና ሰማይን ወለዱልን:
ሰማያቸው ደግሞ ፀሐይን አወጣችልን (ወለደች-አስገኘችልን) "
=>የዓለማችን ወላጆች ነቢያት ሐዋርያትን: ጻድቃን ሰማዕታትን ወልደው ከብረዋል: ተመስግነዋል:: ኢያቄምና ሐና ግን ፍጥረት ሁሉ በአንድነት ቢሰበሰብ በእግሯ የረገጠችውን ትቢያ እንኩዋ መሆን የማይችል: የሰማይና የምድር ንግሥት: የእግዚአብሔርን እናት: እመቤታችን ማርያምን ወለዱልን::
+ኢያቄም ወሐና ለእግዚአብሔር የሥጋዌ አያቶቹም ተባሉ:: እስኪያረጁ ድረስ በመካንነት አዝነው ፀልየዋል:: ንጽሕናቸውና ደግነታቸው ተመስክሮላቸው ድንግል ማርያምን አግኝተዋል::
+እመቤታችን ከአዳም ስሕተት በሁዋላ ያለ ጥንተ አብሶ የተወለደች የመጀመሪያዋ ሰው ድንግል ማርያም ሆናለች:: (ኢሳ. 1:9)
+ለጨለማው ዓለም የብርሃን መቅረዝ ሆና ትጠቅመን ዘንድ: አንድም ትንቢቱና ምሳሌው ይፈጸም ዘንድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ ቀን: በሊባኖስ ተራራ ከ2,022 ዓመታት በፊት ተወልዳለች::
"ሙሽራዬ ሆይ! ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነይ" (መኃልይ. 4:8)
=>ከነገደ ይሁዳ የሚወለድ ቅዱስ ኢያቄም የሚባል ደግ ሰው ከነገደ ሌዊ (አሮን) የተወለደች ሐና የምትባል ደግ ሴት አግብቶ: በሕጉ ጸንተው: በሥርዓቱ ተጠብቀው ይኖሩ ነበር:: ነገር ግን በዘመኑ ሰዎች ልጅ የላችሁም በሚል ይናቁ ነበር::
+ኦሪታውያን ልጅ የሌለውን "ኅጡአ በረከት-ከጸጋ እግዚአብሔር የራቀ" ነው ብለው ያምኑ ነበር:: ኢያቄምና ሐና ልጅ እንዲሰጣቸው ሲያዝኑ: ሲጸልዩ ዘመናቸው አልፎ አረጁ::
እነሱ ግን የሚያመልኩት የአብርሃምና ሣራን አምላክ ነውና ተስፋ አልቆረጡም::
+የለመኑትን የማይነሳ ጌታ በስተእርጅናቸው ድንቅ ነገርን አደረገላቸው:: አንድ ቀን እርግቦች ከጫጩቶቻቸው ጋር ሲጫወቱ የተመለከተች ቅድስት ሐና ፈጽማ አለቀሰች:: "እንስሳትና አራዊትን: እጽዋትን ሳይቀር በተፈጥሯቸው እንዲያፈሩ የምታደርግ አምላክ ምነው ሐናን ድንጋይ አድርገህ ፈጥረሃታልን?" ብላ አዘነች::
+ይህን የተመለከተ ቅዱስ ኢያቄም ወደ ተራራ ወጥቶ ሱባኤ ያዘ:: ለ40 ቀናትም ሲጸልይና ሲማለል ቆየ:: በ40ኛው ቀን 2ቱም ሕልምን ያልማሉ:: እርሱ:- ነጭ ርግብ ሰማያትን ሰንጥቃ ወርዳ: በሐና ቀኝ ጀሮ ገብታ: በማሕጸኗ ስትደርስ አየ::
+እርሷ ደግሞ:- የኢያቄም በትር አብቦ: አፍርቶ: ጣፋጭ ፍሬውን ሰው ሁሉ ሲመገበው ታያለች:: ቅዱስ ኢያቄም ከሱባኤ እንደ ተመለሰ ያዩትን ተጨዋውተው "ፈቃደ እግዚአብሔር ይሁን" አሉ:: ለ7 ቀናትም በጋራ እግዚአብሔርን ሲለምኑ ሰነበቱ::
+በ7ኛው ቀን (ማለትም ነሐሴ 7) መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ክንፉን እያማታ ወደ እነርሱ ወረደ:: "ዓለም የሚድንባት: የፍጥረት ሁሉ መመኪያ የሆነች ልጅ ትወልዳላችሁ" ብሏቸው ተሠወራቸው:: እነርሱም ደስ ብሏቸው እግዚአብሔርን አመሰገኑ::
+እንደ ሥርዓቱም አብረው አድረው እመ ብርሃን ተጸነሰች::
"ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተጸነስኪ . . .
ድንግል ሆይ! ኃጢአት ባለበት ሥጋዊ ፍትወት የተጸነስሽ አይደለም" እንዳለ ሊቁ:: (ቅዳሴ ማርያም)
+"ለጽንሰትኪ በከርሥ: እንበለ አበሳ ወርኩስ: ወለልደትኪ እማሕጸን ቅዱስ . . ."
"ድንግል ሆይ! መጸነስሽ ያለ በደል (ያለ ጥፋት) ነው: የተወለድሽበት ማሕጸንም ቅዱስ ነው . . ." (መጽሐፈ ሰዓታት, ኢሳ. 1:9)
+እመቤታችን ነሐሴ 7 ቀን ተጸንሳ ግንቦት አንድ ቀን ተወልዳለች::
=>የእመቤታችን የዘር ሐረግ:-
*አዳም-ኖኅ-አብርሃም-ይስሐቅ-ያዕቆብ=
*በእናቷ:-
-ሌዊ-ቀዓት-እንበረም-አሮን-ቴክታና በጥሪቃ-ሔኤሜን-ዴርዴን-ቶና-ሲካር-ሔርሜላና ማጣት-ሐና::
*በአባቷ በኩል:-
-ይሁዳ-ፋሬስ-ሰልሞን-ቦኤዝ-እሴይ-ዳዊት-ሰሎሞን-ሕዝቅያስ-ዘሩባቤል-አልዓዛር-ቅስራ-ኢያቄም ይሆናል::
+ለጨለማው ዓለም የብርሃን መቅረዝ ሆና ትጠቅመን ዘንድ: አንድም ትንቢቱና ምሳሌው ይፈጸም ዘንድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም: በሊባኖስ ተራራ ከ2,025 ዓመታት በፊት ተወልዳለች::
=>የእመቤታችን ድንግል ማርያም ጣዕሟ: ፍቅሯ: ጸጋዋና በረከቷ ይደርብን::
=>ግንቦት 1 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም (ልደታ)
2.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
3.ቴክታና በጥሪቃ
4.አባ ሕርያቆስ ዘሃገረ ብሕንሳ (የእመቤታችንን ቅዳሴ የደረሰበት)
=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ራጉኤል ሊቀ መላዕክት
2.ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
3.ቅዱስ ሚልኪ ትሩፈ ምግባር
=>+"+ መሠረቶቿ በተቀደሱ ተራሮች ናቸው::
ከያዕቆብ ድንኩዋኖች ይልቅ እግዚአብሔር የጽዮንን ደጆች ይወዳቸዋል::
የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ! በአንቺ የተደረገው ድንቅ ነው . . .
ሰው እናታችን ጽዮን ይላል::
በውስጧም ሰው ተወለደ::
እርሱም ራሱ ልዑል መሠረታት:: +"+ (መዝ. 86:1-6)
<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
Dn Yordanos Abebe
"" እወ በአማን! ""
Dn Yordanos Abebe
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ
አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞
❖ ግንቦት ፪ ❖
❖ ግንቦት 2 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
+"+ ቅዱስ ኢዮብ +"+
+የትዕግስት አባት ቅዱስ ኢዮብ በቅዱስ መጽሐፍ ላይ
እንደተመለከትነው ያልተፈተነበት ነገር የለም:: ሐረገ
ትውልዱም
ከአባታችን አብርሃም ይመዘዛል::
*አብርሃም ይስሐቅን
*ይስሐቅ ኤሳውን
*ኤሳው ራጉኤልን
*ራጉኤል ዛራን
*ዛራ ኢዮብን ይወልዳሉ::
+ቅዱስ ኢዮብ የነበረው እሥራኤል በግብፅ በባርነት ሳሉ
ነበር:: ኢዮብ ይሕ ቀረህ የማይሉት ባለጠጋ: ደግና
እግዚአብሔርን
አምላኪ ነበር:: የኢዮብ ደግነት የተመሰከረው በሰው
(በፍጡር) አንደበት አልነበረም:: በራሱ በፈጣሪ አንደበት
እንጂ::
+በዚህ የቀና ጠላት ዲያብሎስ ግን ኢዮብን ይፈትነው
ዘንድ ከአምላክ አስፈቀደ:: ጌታችን የጻድቁን የትዕግስት
መጠን
ሊገልጥ ወዷልና ሰይጣን ኢዮብን በሐብቱ መጣበት::
በአንድ ጀምበርም ድሃ ሆነ:: እርሱ ግን ፈጣሪውን ባረከ::
+ሰይጣን ቀጠለ:- የአብራኩን ክፋዮች (ልጆቹን)
አሳጣው:: ኢዮብ አሁንም አመሰገነ::
+በሦስተኛው ግን ሰውነቱን በቁስል መታው:: ቁስል ሲባል
በዘመኑ እንደምታዩት ዓይነት አልነበረም:: ከሰው ሕሊና
በላይ
የሆነ አሰጨናቂ ደዌ ነበር እንጂ:: ጻድቁ የአንድ ወጣት
እድሜ ያሕል በመከራው ጽናት እየተሰቃየ ገላውን በገል
ያከው
ነበር::ከአፉ ግን ተመስገን ማለትን አላቁዋረጠም::
+በመጨረሻም ሰይጣን በሚስቱ መጣበት::
"እግዚአብሔርን ተሳደብ" አለችው:: እርሱ ግን መለሰ:-
"እግዚአብሔር ሰጠ:
እግዚአብሔርም ነሣ: ስሙ የተባረከ ይሁን::"
+ከዚሕ ሁሉ ነገር በኋላ እግዚአብሔር ሰይጣንን ከጎዳናው
አስወገደው:: ጤናውን: ሐብቱን: ልጆቹን ለኢዮብ
መለሰለት::
ካለው እድሜ ላይ 140 ዓመት ጨመረለት:: ጻድቅና
የትዕግስት ሰው ቅዱስ ኢዮብ በ248 ዓመቱ በዚሕች ቀን
ዐረፈ::
=>እግዚአብሔር አምላክ ከጻድቁ ትዕግስትና በረከት
አይለየን::
❖ግንቦት 2 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ (የትእግስት አባት)
2.አባ ቴዎድሮስ ሊቀ ምኔት (የታላቁ ቅዱስ ዻኩሚስ ደቀ
መዝሙርና የአቡነ አረጋዊ ጉዋደኛ)
3."22" ሰማዕታት (የአባ ኤሲ ማሕበር)
❖ወርኃዊ በዓላት
1፡ ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ
2፡ ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ
3፡ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ
4፡ ቅዱስ አቤል ጻድቅ
5፡ አባ ጳውሊ ገዳማዊ
6፡ አባ ሕርያቆስ ዘብሕንሳ
++"+ ወንድሞች ሆይ! የመከራና የትዕግስት ምሳሌ
የሆኑትን በጌታ ስም የተናገሩትን ነቢያትን ተመልከቱ::
እነሆ
በትዕግስት የጸኑትን ብጹዓን እንላቸዋለን:: ኢዮብ እንደ
ታገሠ ሰምታቹሃል:: ጌታም እንደፈጸመለት አይታቹሃል::
ጌታ እጅግ የሚምር: የሚራራም ነውና:: +"+ (ያዕ.
5:10)
<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
Dn Yordanos Abebe
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ
አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞
❖ ግንቦት 3 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
+"+ ቅዱስ ያሶን ሐዋርያ +"+
+ባለንበት ዘመን አሳዛኝ ከሆኑ ነገሮች አንዱ የቅዱሳኑ
ስማቸው ከነሥራቸው መዘንጋቱ ነው:: ለቅድስት ቤተ
ክርስቲያን
ደማቸው እንዳልፈሰሰ: አጥንታቸውም እንዳልተከሰከሰ
ይሔው አስታዋሽ አጥተው ስማቸውም ተዘንግቶ ይኖራል::
+አንዳንድ ንፉቃን ደግሞ ከዚሁ ብሶ ጭራሹኑ ኦርቶዶክስ
ተዋሕዶ ስለ ክርስቶስ ትታ ስለ ቅዱሳኑ ብቻ ትሰብካለች
ይሉናል::
+በእጅጉ ከሚያሳዝኑኝ ነገሮች አንዱ የቅዱሳን ሐዋርያት
(የ120ው ቤተሰብ) መዘንጋት ነው:: ከ120ው ቤተሰብ
የአብዛኞቹ
ስም በመዘንጋቱ: ሊቃውንቱም ዝምታን በመምረጣቸው
"ያሶን: አርስጦስ: አፍሮዲጡ: ቆሮስ . . . እያልን የ72ቱን
አርድእት ስም ስንጠራ ግር የሚለው ዓይነት ትውልድ
ተፈጥሯል::
+እስኪ እንዲያው ቢያንስ ሐዋርያትንና ዐበይት ቅዱሳንን
እናስባቸው:: አስበናቸው የሚጨመረልን እንጂ
የሚጨመርላቸው የለምና::
+ዛሬ የምናስበው ቅዱስ ያሶን ሐዋርያ ከ72ቱ አርድእት
አንዱ ነው:: ጌታችንን ከጥምቀቱ በኋላ ተከትሎ ለ3
ዓመታት
ከእግሩ ሥር ቁጭ ብሎ ተምሯል:: ከጌታችን ዕርገት በኋላ
መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ ለስብከተ ወንጌል ወጥቷል::
+ለብዙ ጊዜ ከቅዱስ ዻውሎስ ጋር ተመላልሶ ሰብኳል::
በመከራውም ተካፍሎታል:: ታላላቆቹ ሐዋርያት
ሰማዕትነትን ከተቀበሉ
በኋላ ለመጣው አዲስ ክርስቲያን ትውልድ ከጌታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ ቃል በቃል የሰማውን አስተላልፏል::
+ወንጌልን ስለ ሰበከላቸው አሕዛብ ብዙ ጊዜ አስረው
ይደበድቡት: ያንገላቱት ነበር:: አንዳንድ ጊዜም እሳት
እያነደዱ
ያቃጥሉት ነበር:: ፈጣሪው ግን በተአምራት እያዳነው
ከርሱ ጋር አልተለየም::
+ከከተማ ወጥቶ በዱርና በእስር ቤቶች ብዙ ነፍሳትን:
ሽፍቶችንም ሳይቀር ወደ ክርስትና ማርኳል:: ቅዱስ ያሶን
ለረዥም
ዓመታት ሰብኮ በመልካም ሽምግልና አርፏል::
❖ ንግሥት ወለተ ማርያም ❖
+ዳግመኛ በዚህ ቀን ኢትዮዽያዊቷ እናታችን ቡርክት
ወለተ ማርያም ትታሰባለች::
+ወለተ ማርያም ማለት የደጉ አፄ ናኦድ ሚስት: የአፄ
ልብነ ድንግልና የቅድስት ሮማነ ወርቅ እናት ናት::
በንግስትነት
በቆየችባቸው ዘመናት (ከ1487-1500 ዓ/ም) የረሃብ
ጊዜ በመሆኑ ብዙ ሕዝብ አልቆ ነበር::
+ቡርክት ወለተ ማርያም ከጾምና ከጸሎት ባሻገር
የተራቡትን በማብላት ብዙዎችን ታድጋለች:: የንጉሡን
ቤተሰብ ወደ መልካም
ክርስትና በመምራትም የተመሰገነች ነበረች:: በዚህ ቀንም አርፋ ተቀብራለች::
❖አምላካችን ከቅዱሳኑ በረከት አይለየን::
❖ግንቦት 3 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ያሶን ሐዋርያ (ከ72ቱ አርድእት አንዱ)
2.አባ ብሶይ ሰማዕት
3.ቅዱስ አውሳብዮስ ቀሲስ
4.ቡርክት ወለተ ማርያም ንግሥት (የዐፄ ልብነ ድንግል እናት)
❖ወርኃዊ በዓላት
1፡ በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም
2፡ ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
3፡ ካህናት ዘካርያስ ወስምዖን
4፡ አባ ሊባኖስ ዘመጣዕ
5፡ አባ ዜና ማርቆስ
6፡ አቡነ መድኃኒነ እግዚእ
7፡ ቅዱስ ቄርሎስ ዓምደ ሃይማኖት
8፡ ቅዱስ ስምዖን ዘዓምድ
++"+ ሰብዓውም በደስታ ተመልሰው ጌታ ሆይ! አጋንንት
ስንኳ በስምህ ተገዝተውልናል አሉት:: እንዲህም አላቸው
. . .
እነሆ እባቡንና ጊንጡን ትረግጡ ዘንድ በጠላትም ኃይል
ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችሁአለሁ:: የሚጐዳችሁም
ምንም የለም::
ነገር ግን መናፍስት ስለ ተገዙላችሁ በዚህ ደስ
አይበላችሁ:: ስማችሁ ግን በሰማያት ስለ ተጻፈ ደስ
ይበላችሁ:: +"+ (ሉቃ.10:17)
<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
Dn Yordanos Abebe
††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††
††† እንኩዋን ለጻድቁ አቡነ መልከ ጼዴቅ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ †††
+"+ አቡነ መልከ ጼዴቅ +"+
=>ኢትዮዽያዊው ጻድቅ አቡነ መልከ ጼዴቅን ብዙ ሰው ሽዋ (ሚዳ) ውስጥ በሚገኘው አስደናቂ ገዳማቸው ያውቃቸዋል:: ገዳሙ በእድሜ ጠገብ ዛፎች ያጌጠ ከመሆኑ ባሻገር በጻድቁ ቃል ኪዳን ምክንያት በቦታው የሚቀበር ሁሉ አካሉ አይፈርስም:: የጻድቁስ ዜና ሕይወታቸው እንደምን ነው ቢሉ:-
+አቡነ መልከ ጼዴቅ በሸዋ ነገሥታት ዘመን የነበሩ: የንጉሱ ዓምደ ጽዮን የቅርብ ዘመድ ነበሩ:: የጻድቁ ወላጆች ፍሬ ጽዮንና ዐመተ ማርያም ይባላሉ:: አቡነ መልከ ጼዴቅ ገና በሕጻንነታቸው ሥርዓተ መንግስትን አጥንተዋል::
+በሁዋላ ከመምሕር ዘንድ ገብተው ብሉይ ከሐዲስ ተምረው ሲያጠናቅቁ ይሕንን ዓለም ናቁና ከቤተ መንግስቱ አካባቢ ጠፍተው ወደ አቡነ አሮን መንክራዊ ዘንድ ሔደው መንኩሰዋል::
+ነገሩ በቤተ መንግስት አካባቢ ሲሰማ ወላጆች አለቀሱ:: አቡነ አሮንም ተከሰው ነበር:: ነገሩ ግን ከእግዚአብሔር ነበርና አቡነ መልከ ጼዴቅን መልዐክ እየመራ አምጥቶ አሁን ገዳማቸው ያለበት ሸዋ (ሚዳ) አደረሳቸው::
+በዚያ ትንሽ በዓት ሰርተው ለዘመናት ተጋድለዋል:: ዋሻዋም ደብረ መድኃኒት ትባላለች:: ጻድቁ ከጾምና ጸሎታቸው በተረፈ ዓርብ ዓርብ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሕማማት በማሰብ ጀርባቸውን 300 ጊዜ ይገርፉ: ደቀ መዛሙርቱንም ግረፉኝ ይሉ ነበር:: አንድ ጊዜም እጃቸውንና እግራቸውን በትልልቅ ችንካሮች ቸንክረውት ደማቸው ሲፈስ ተገኝቷል::
+በመጨረሻ አቡነ መልከ ጼዴቅ ጌታን ኢትዮዽያውያንን ማርልኝ አሉት:: ጌታችንም መለሰ:- "በስምህ ያመኑትን: በቃል ኪዳንህ የተማጸኑትን: ገዳምሕን የተሳለሙትን እምርልሃለሁ::"
+ጻድቁም ብዙ ተአምራትን ሰርተው በዚሕች ቀን አርፈዋል:: አቡነ አምሃ ኢየሱስም በክብር ገንዘው በበዓታቸው ውስጥ ቀብሯቸዋል::
=>አምላካችን እግዚአብሔር ከጻድቁ ዋጋና በረከት አይለየን::
=>ግንቦት 4 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.አቡነ መልከ ጼዴቅ ካህን (ኢትዮዽያዊ ጻድቅ)
2.አባ ዮሐንስ ሊቀ ዻዻሳት
3.ቅዱሳን ሶሲማና ኖዳ ሰማዕታት (የታላቁ ፊቅጦር ተከታዮች የነበሩ)
=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጉዋድ (ወንጌላዊው)
2.ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ
3.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
4.ቅዱስ ዮሐንስ ዘሐራቅሊ (ሰማዕት)
=>+"+ ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተ ክርስቲያን ቀሳውስትን ወደ እርሱ ይጥራ:: በጌታም ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት:: የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል:: ጌታም ያስነሳዋል:: ኃጢአትም ሠርቶ እንደ ሆነ ይሠረይለታል:: እርስ በርሳችሁ በኃጢአታችሁ ተናዘዙ:: ትፈወሱም ዘንድ እያንዳንዱ ስለ ሌላው ይጸልይ:: የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች:: +"+
(ያዕ. 5:14)
††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
Dn Yordanos Abebe
††† እንኳን ለነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ኤርምያስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††
††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††
††† ቅዱስ ኤርምያስ †††
††† ታላቁ ነቢይ ቅዱስ ኤርምያስ ከዐበይት ነቢያት አንዱ ሲሆን ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በስድስት መቶ አካባቢ የነበረ ነቢይ ነው:: አባቱ ኬልቅዩ ይባላል:: ከካህናተ እስራኤል አንዱ ነበር::
እግዚአብሔር ኤርምያስን የጠራው ገና በሕፃንነቱ ነበር:: "ከእናትህ ማኅጸን ሳትወጣ መርጬሃለሁ: ቀድሼሃለሁ" ሲልም በገሃድ መስክሮለታል:: (ኤር. 1:5)
ከቅዱሳን ነቢያት እንደ ኤርምያስ የተሰቃየና ያለቀሰ የለም:: ከሰባ ዘመናት በላይ ስለ ወገኖቹ አልቅሷልና ሊቃውንት "ነቢየ ብካይ" (ባለ እንባው ነቢይ) ይሉታል::
ዘመኑ ዘመነ-ኃጢአት (ዘመነ ዐጸባ) ነበር:: እሥራኤላውያን ከመሪዎቻቸው ከነ ሴዴቅያስ ጋር በክፋት ተባብረውም ነበርና ኤርምያስን አልሰሙትም:: ይልቁኑ ክፉ ቦታ ውስጥ አስረው አሰቃዩት:: እግዚአብሔር ግን በኢትዮጵያዊው አቤሜሌክ አማካኝነት ከመከራው አዳነው::
የተሰበከላቸውን የንስሐ ጥሪ አልሰሙምና ስልምናሦር የሚባል የአሕዛብ ንጉሥ መጥቶ አሥሩን ነገድ ማርኮ በ722 አሦር (ነነዌ) አወረዳቸው:: በኋላ ደግሞ በኃይለኝነቱ የታወቀው የባቢሎን ንጉሥ ይማርካቸው ዘንድ ወደ ሁለቱ ነገድ ኢየሩሳሌም ደረሰ:: ኤርምያስ ወደ ከተማዋ ዳር ወጥቶ ስለ ኢየሩሳሌምና ስለ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አለቀሰ::
ከቤተ መቅደስ ንዋያት እኩሉን ለምድር አደራ ሰጣትና ሸሸገችው:: ነቢዩ የተናገረው አይቀርምና ንጉሡ ናቡከደነጾር እኩሉን ገድሎ: እኩሉንም ማርኮ: ኢየሩሳሌምን አቃጥሎ: የአሕዛብ መዘባበቻ አድርጐ በ586 ባቢሎን አወረዳቸው::
ቅዱስ ኤርምያስን ግን ትሩፋን (ከመከራው የተረፉት) ይዘውት ወደ ግብጽ ወረዱ እንጂ አልተማረከም::
በዚያም ተአምራትን አድርጐ አራዊትን አጥፍቷቸዋል:: ትንሽ ቆይቶ ግን እውነተኛ አባት : ነቢይ : መምሕርም ነውና ወደ ሕዝቡ (ወደ ባቢሎን) ወረደ:: በዚያም ትንቢትን እየተናገረ : ሕዝቡን ከሰባ ዓመታት በኋላ ወደ ሐገራቸው እንደሚመለሱ እያስተማራቸው በባቢሎን ቆይቷል:: ያለ በደሉም በመከራቸው ተካፋይ ሆኗል::
ሰባው ዘመን ሲፈጸም እግዚአብሔር እንደ ቃል ኪዳኑ በኤርምያስ መሪነት እሥራኤል ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ:: አሁንም ግን ክፋታቸውን ይተው ዘንድ ፈቃደኞች አልነበሩምና ኤርምያስ ገሠጻቸው::
በዚህ ተበሳጭተው ሊወግሩት ሲሉ ጸጋ በዝቶለት : ምሥጢርም ሰፍቶለት ስለ ነገረ ሥጋዌ (ስለ ክርስቶስ የማዳን ሥራ) አምልቶና አጉልቶ ትንቢት ተናገረ:: አንዴ ልቡናቸው ታውሮ ኤርምያስ ነው ብለው ድንጋዩን በድንጋይ ሲወግሩት ውለዋል:: ዘግይቶ ግን ኤርምያስ ራሱን ገለጠላቸው:: ስለ እነርሱ ሲል ሰባ ዘመን ያለቀሰውንና ምትክ የሌለውን አባታቸውን ወግረው ገደሉት::
ታላቁ ነቢይ ቅዱስ ኤርምያስ ሃምሳ ሁለት ምዕራፎች ያሉት ሐረገ ትንቢት ተናግሯል / ጽፏል:: ዜና ሕይወቱ ከራሱ የትንቢት መጽሐፍ በተጨማሪ በተረፈ ኤርምያስ : በመጽሐፈ ባሮክ : በገድለ ኤርምያስ : በዜና ብጹዐን : በመጽሐፈ ስንክሳርም ተጽፏል::
††† ቸር እግዚአብሔር በኤርምያስ ምልጃ ሃገራችንን ከጥፋት: ሕዝቦቿን ከስደትና ከመቅሰፍት ይሰውርልን::
††† ግንቦት 5 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ኤርምያስ ነቢይ (ከታላላቆቹ ነቢያት አንዱ)
††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
2.ቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያ
3.አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ
4.ቅዱስ ዮሐኒ ኢትዮጵያዊ
5.ቅዱስ አሞኒ ዘናሒሶ
††† "ኢየሩሳሌም ሆይ ነቢያትን የምትገድል : ወደ እርሷ የተላኩትንም የምትወግር : ዶሮ ጫጩቶቿን ከክንፎቿ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ! አልወደዳችሁምም:: እነሆ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላቹሃል:: እላችሁአለሁና : በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እስክትሉ ድረስ እንግዲህ ወዲህ አታዩኝም::"
(ማቴ. ፳፫፥፴፯-፴፱)
††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††