መንፈሳዊ ህይወት
4.02K subscribers
437 photos
5 videos
8 files
62 links
✟✟✟በስመአብ ወወልድ በመንፈስ ቅድስ አሀድ አምላክ አሜን ✞✞✞
በዚህ ቻናል የኢ/ኦ/ተ/ቤ ስርአት የጠበቁ ለመንፈሳዊ ህይወታችን ይጠቅሙናል ያስተምሩናል የምንላቸውን መንፈሳዊ
ትምህርቶች ብሒሎች ምክሮች እናስተላልፋለን።
ለሌሎች ሼር በማድረግ ቻናሉን ያጋሩ ✟✟✟

መንፈሳዊ ህይወት (ሰው)
✍️✍️ ሀሳብ ወይም አስተያየት ;👇👇

https://t.me/Ortodoxe21 በዚ ይላኩልን
Download Telegram
✍️ዶግማና ቀኖና: ትምህርት ሃይማኖት (የሃይማኖት ትምህርት) በሁለት ይከፈላል፡፡ ይኸውም ዶግማና ቀኖና በሚል ነው።

✍️ዶግማ ቃሉ የግሪክ ሲሆን ፍችውም የእምነት መሠረት ማለት ነው፡፡ ዶግማ ወይም እምነት አይጨመርበትም፤ አይቀነስበትም፤ አይሻሻልም፤ ችግርና ፈተናም ቢመጣ እስከ ሞት ድረስ አጥብቀን የምንይዘው ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ይህን ዓለም ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ የፈጠረ፤ ቢመረምር እንጂ የማይመረመር ሁሉን ቻይ አምላክ፤ የሚሳነው ነገር የሌለ ፈጣሪ፤ የሰማይና የምድር ባለቤት የሠራዊት ጌታ ሕያው እግዚአብሔር ነው፡፡ እግዚአብሔር (ፈጣሪ) የአካል ሦስትነት አለው፡፡ በመለኮት፣ በመፍጠር፣ በሥልጣን፣ በአገዛዝ፣ በፈቃድ ግን አንድ ነው፡፡ በሦስትነቱ አብ፤ ወልድ፤ መንፈስ ቅዱስ ሲባል በአንድነቱ አንድ መለኮት አንድ እግዚአብሔር ይባላል፡፡ በአዳም ምክንያት ከመጣው የዘለዓለም ሞትና ከዲያብሎስ ባርነት ነጻ የወጣነው ከሦስቱ አካላት በአንደኛው አካል ማለትም በወልድ በኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ይህን የመሰለው መሰረታዊ ትምህርት ዶግማ ወይም መሰረተ እምነት ይባላል፡፡

ቀኖና የሚለው ቃልም የግሪክ ሲሆን ሥርዓት ማለት ነው፡፡ ቀኖና በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው ያደጉ ክርስቲያኖች የሚመሩበት ሥርዓት ስለሆነ፤ በሃይማኖት አባቶች ወይም በቅዱስ ሲኖዶስ አማካኝነት እንደጊዜው ሁኔታ የሚሻሻል በመሆኑ የሚጨመርበት፤ የሚቀነስለት ነው፡፡ ለምሳሌ በቤተ ክርስቲያናችን የቀዳስያን ብዛት መነሻው አምስት ነው፡፡ ምናልባት ከአምስቱ አንዱ፤ ሁለቱ፤ ሦስቱ ቢታጡና ሌላም ተፈልጎ እስከ መጨረሻ የማይገኝ ከሆነ ከአቅም በላይም የሆነ ችግር ከገጠመ ሁለቱ ወይም አንዱ ብቻ ቀድሰው ማቁረብ ይችላሉ፡፡ 1ኛ ቆሮ. 14፥40፡፡ 2ኛተሰ. 3፥6-7 ቀኖና (ሥርዐት) የሚወሰነው በሃይማኖት አባቶች እንደሆነና ወንጌልን የሚያስተምር ሰው ለሚያስተምራቸው ክርስቲያኖች በሃይማኖት አባቶች የተወሰነ ቀኖና ማስተማርና መሰጠት እንዳለበት መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል ያስረዳል፡፡ “በየከተማውም ሲሄዱ፥ ሐዋርያትና ቀሳውስት በኢየሩሳሌም ያዘዙትን /የወሰኑትን/ ሥርዐት አስተማሯቸው፡፡ አብያተ ክርስቲያናትም በሃይማኖት ጸኑ ዕለት ዕለትም ቁጥራቸው ይበዛ ነበር፡፡” ሐዋ. 16፥4-5፡፡

#join or #share መንፈሳዊ ህይወት (ሰው)

https://t.me/joinchat/WPlEyEeAttNFBvZK
ቤተክርስቲያን፡ እንደ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አመሥጥሮ ቤተ ክርስቲያን ማለት እግዚአብሔር ግዕዛን ካላቸው ፍጥረታት ጋር ያለው ግንኙነት ነው፡፡ ይህም ሦስት አይነት ትርጉም አለው፡፡ ቤተክርስቲያን ማለት የክርስቲያኖች ኅብረት፡ የክርስቲያኖች አንድነት ነው (1ኛ ቆሮ 11፡28)፡፡ ቤተክርስቲያን ማለት የክርስቲያኖች መኖሪያ፡ የእግዚአብሔር ቤት ነው፡፡ “ቤት” ማለት መኖሪያ ማለት እንደሆነ ሁሉ “ቤተክርስቲያን” ማለት የክርስቲያኖች ቤት/መኖሪያ የእግዚአብሔር ቤት ማለት ነው (ዮሐ 2፡ 16)፡፡  እዚህ ላይ ህንፃ ቤተክርስቲያን ስንል አገልግሎቱንም ጭምር የሚያመለክት መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ በተጨማሪም ቤተክርስቲያን ሲል ምዕመናንን ነው፡፡ የእያንዳንዱን ክርስቲያን ሰውነት የሚያመላክት ነው (1ኛ ቆሮ 3፡16)፡፡ ይህም ማለት ቤተክርስቲያን ከክርስቶስ የተገኘ እንደሆነ ነው፡፡

የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የእምነትና የሃይማኖት መሠረት የሆኑት አምስቱ አዕማደ ምስጢራት ናቸው፡፡ ሃይማኖት የሚባለውም እነዚህን ምስጢራት ተቀብሎ ሁሉን ማድረግ ከሚችል ከእግዚአብሔር ጋር መኖር ነው፡፡ አምስት መሆናቸው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ነገር ግን ሌሎችን ደግሞ አስተምር ዘንድ በማኅበር እልፍ ቃላት በልሳን ከመናገር ይልቅ አምስት ቃላት በአእምሮዬ ልናገር እወዳለሁ።” (1ኛቆሮ 14፡19) ያለውን መነሻ ያደረገ ሲሆን የስያሜያቸው ትንታኔ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡

ይቀጥላል .....

#join or #share

https://t.me/joinchat/WPlEyEeAttNFBvZK
አዕማድ ማለት ምን ማለት ነው?

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት መፍቻ ቁልፍ የግእዝ ቋንቋ እንደ መሆኑ መጠን በተለይም በቤተክርስቲያን ጥቅም ላይ የሚውሉ ቃላት ምንጫቸው ግእዝ ነው፡፡ “አዕማድ” የሚለውም ቃል መገኛው “አምድ” የሚለው የግዕዝ ቃል ነው፡፡ “አምድ” የሚለው ቃል የነጠላ ቁጥርን የሚገልፅ ሲሆን “አዕማድ” ሲሆን ደግሞ ብዙ ቁጥርን ይገልፃል፡፡ ትርጉሙም በቃላዊ ፍቺው ለቤት ሲሆን ምሰሶ ማለት ነው፡፡ ምሰሶ ቤትን ደግፎ እና አቅንቶ እንደሚይዝ ሁሉ አምስቱ አዕማደ ሚስጥራትም የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖትን አቅንተውና ደግፈው ስለሚይዙ የተሰጠ ስያሜ ነው፡፡ ዐምድ ለጽሕፈትም ይውላል፡፡ የገጽ ስፋትንም በመክፈል ለንባብ መመጠኛነት ያገለግላል፡፡ በዚህ ፍቺም ባህርየ ሥላሴን ከልክ አልፈን እንዳንመረምር የተሰጠ ስያሜ ነው፡፡

አምድ በቁሙ ምሰሶ ብለን የምንጠራው እና ቤቱ እንዳይዘም ወይም ወደ አንድ ጎን እንዳያዘነብል፤ ሚዛኑን እና ልኩን ጠብቆ እንዲቆም የሚያደርግ ነው። በአምድ የተሠራ ቤት አይዛባም ያለዓምድ የተሠራ ቤት ግን ይፈርሳል አይጸናም፡፡ ቤት በአምድ (በኮለም) እንደሚጸና ሃይማኖትም በእነዚህ አዕማደ ምሥጢራት ተጠቃሎ ይገለጻል፤ ምዕመናንም እነዚህን ምሥጢራት በመማር ጸንተው ይኖራሉ። እንደዚህም ሁሉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አዕማድ የተባሉ ምሥጢራት ይዞ የተገኘ ሰው ልቡናው በፍቅረ እግዚአብሔር በተስፋ መንግስተ ሰማያት ይጸናል፡፡ እነዚህን አምስቱን እምነታት ሳይዝ የተገኘ ልቡናው በፍቅረ እግዚአብሔር በተስፋ መንግስተ ሰማያት አይጸናም፡፡

“ሁሉም ነገር ድጋፍ ያስፈልገዋል” የሚለው ሃሳብ ለቤቶች ብቻ ሳይሆን ከዚያም ባለፈ ለብዙ ነገሮች ያገለግላል፡፡ ብዙ የፍልስፍና ሊቃውንት ሰዎች ሁሉ ህይወታቸው በተገቢው መንገድ ለመምራት ሲሉ የሚቀበሏቸው መሰረታዊ እምነቶች (fundamental beliefs) እንዳሉ ይናገራሉ፡፡ በዓለም ላይ ከፍተኛ ህዝብ ይከተላቸዋል የሚባሉት ሃይማኖቶችም ሳይቀሩ መሰረታዊ እምነት የሚሏቸው አሏቸው፡፡ ለአብነትያህል፡- በእስልምናው ሃይማኖት አምስቱ የእስልምና መሰረቶች (The Five Pillars of Islam) ሲኖሩ በቡድሂዝም እምነት ደግሞ አራቱ እውነታዎች (The Four Noble Truths) ይገኛሉ፡፡

በቅድስት ተዋህዶ ቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ ምሰሶዎች አንድን ቤት ደግፈው እንደሚይዙት ሁሉ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖትንም ቀጥ አድርገው የሚይዙ ምሰሶዎች አምስቱ አዕማደ ምስጢራት ናቸው፡፡ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት እንደሚያስተምሩት ከሆነ አንድ ሰው አምስቱን አዕማደ ምስጢራት በጥንቃቄ ካወቀ የኑፋቄ ማዕበል አይጥለውም፡፡ ከእምነቱም አይናወጽም፡፡ በህይወቱ የተለያዩ መከራዎች ቢመጡበትም በእነዚህ ትምህርቶች በኩል ራሱን ያፀናል፡፡ እነዚህን አዕማድ ያላወቅ በሙሉ ልቡ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኝ ነኝ ማለት አይችልም፡፡ በዚህም ምክንያት እነዚህን ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡

#share #share #share በማረግ ለሌሎች አድርሱ
#link

https://t.me/joinchat/WPlEyEeAttNFBvZK
ለምን ምስጢራት ተባሉ?

ቅድስት ቤተክርስቲያን አምስቱን አዕማድ “የምስጢር ትምህርቶች” ትላቸዋለች፡፡ “ምሥጢር” የሚለው ቃል “አመሠጠረ” ከሚለው ግስ የተገኘ ቃል ሲሆን ስውር ፣ ድብቅ ፣ ሽሽግ ማለት ነው፡፡ ምሥጢር በሁለት ይከፈላል፡፡ እነርሱም የፈጣሪ ምሥጢር (ሊገለጥ የማይችል፤ ከ እስከ የሌለው ምሥጢር) እና የፍጡራን ምሥጢር (በጊዜ የሚገለጥ /የሚታወቅ/፤ የሰውና የመላእክት ምሥጢር) ናቸው፡፡ ሊቃውንቱም አምስቱ አዕማደ ምስጢራት ስለምን ምሥጢር እንደተባሉ ሲያብራሩ በዓይኔ ካላሣያችሁኝ በእጄ ካላሲዛችሁኝ ብሎ አላምንም አልማርም ይሉ ዘንድ አይገባም በቃል ተምሮ በልቡና ተመራምሮ አዎን ብሎ የሚማሯቸው ስለሆኑ ምሥጢር ተባሉ በማለት ገልጸዋል፡፡(ሃይ. አበው ዘአትናትዮስ 14÷ 39 ሃይ. አበው ዘኤራቅሊስ 11÷24 1ኛ ቆሮ 14፥19 1ኛ ሳሙ 17፥40)፡፡ እግዚአብሔር መንፈስ በመኾኑ፣ በመንፈሳዊው አእምሮና ዓይን፣ ጆሮና እጅ ካልሆነ በቀር በነፍሳዊውና በስጋዊው አእምሮና ዓይን፣ ጆሮና እጅ ብቻ ሊታሰብና ሊታይ፣ ሊሰማና ሊዳሰስ ስለማይቻል ትምህርቱና እውቀቱ “ምስጢር” ተባለ። አምስቱ አዕማደ ምስጢራት “ምስጢር” የተባሉበት ምክንያት በሚከተሉት ሦስት ቁም ነገሮች በበለጠ ይብራራል።

አንድ፡ ረቂቅ እና ስውር ስለሆነው አምላክ የሚናገሩ አስተምህሮቶች ስለሆኑ ነው። የእግዚአብሔርን የአንድነትና የሦስትነት ነገር፣ ቀጥሎ ከሦስቱ አካላት አንዱ ሰው የመሆኑ ነገር፣ እንዲሁም ሰው ከእግዚአብሔር በመንፈስ የመወለዱን ነገር፣ ደግሞም ሰው የሆነውን አምላክ ሥጋውን በመብላትና ደሙን በመጠጣት በእግዚአብሔር መንግስት ለዘለአለም ሕያው ሆኖ የመኖርን ነገርና በመጨረሻም ሰው ለዘላለማዊው ህይወት ወይም ሞት በማይበሰብስ አዲስ አካል እንደገና የመነሳቱን ነገር የሚያስረዳ ጥልቅ የሆነ መንፈሳዊና ሃይማኖታዊ ትምህርት የሚያስረዱ በመሆኑ ነው።

ሁለት፡ ትምህርቶቹን በሥጋዊ ጥበብ ለመረዳት የማይቻል በመሆኑ ነው። ትምህርቱና እውቀቱ እንደሥጋዊ ትምህርትና እውቀት ተፅፎ የሚቀርብና ተነቦ የሚጠና፣ በሥጋዊው ቁሳቁስ ግዙፍ ማስረጃነት እየተደገፈ የሚሰጥ ሳይሆን በአንድ ወገን ከሃይማኖታዊና መንፈሳዊ ልቦና በእውነተኛ አምልኮ ፈልቆ የሚናገሩትና የሚያስተምሩት፣ በሌላው ወገን ደግሞ በእውነተኛ ፍላጎት በተመሰረት ሃይማኖታዊና መንፈሳዊ ልቦና ሆነው የሚሰሙትና የሚማሩት ረቂቅ የእግዚአብሔር ነገር ስልሆነ ነው።

ሦስት፡ ቤተክርስቲያን ለአማንያን ብቻ የምትነግረው እና የምታስተምረው በመሆኑ ነው። ለማያምኑ የማይገለጥ፣ ለሚያምኑ ግን በእውነተኛው መንፈሳዊና ሃይማኖታዊ የእውቀት ቁልፍ ከፍተው በዚያው በፍፁም ብርሃን ካዩት በኋላ አክብረው የሚጠብቁት “የማይጠፋ እንቁ” በመሆኑ ነው። (ማቴ. 7፡6፣ ማቴ. 13፡11)

#join or #share

https://t.me/joinchat/WPlEyEeAttNFBvZK
ኒቆዲሞስ

ሰባተኛው ሳምንት ‹ኒቆዲሞስ› የሚል ስያሜ ያለው ሲኾን፣ የስያሜው መነሻም በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ፫ የተመዘገበው ኒቆዲሞስ የተባለው የአይሁድ አለቃ ታሪክ ነው፡፡ ኒቆዲሞስ በሦስት መንገድ የአይሁድ አለቃ ነበር፤ በሥልጣን፣ በዕውቀትና በሀብት፡፡ ሰው ሥልጣን ቢኖረው ሀብትና ዕውቀት ላይኖረው ይችላል፡፡ ዕውቀት ቢኖረው ደግሞ ሀብትና ሥልጣን ላይኖረው ይችላል፡፡ ሀብት ቢኖረውም ዕውቀትና ሥልጣን ላይኖረው ይችላል፡፡ ኒቆዲሞስ ግን ሦስቱንም አንድ ላይ አስተባብሮ የያዘ የአይሁድ አለቃ ነበር፡፡ ኒቆዲሞስ ወንጌልን ለመማር ከአይሁድ ዅሉ ቀድሞ በሌሊት ወደ ጌታችን ይሔድ ነበር፡፡ ኒቆዲሞስ ፈሪሳውያን ማመን ባልቻሉበት በዚያን ዘመን ጆሮውን ለቃለ እግዚአብሔር፤ ልቡን ለእምነት የከፈተ ሰው ነው፡፡ ብዙ ሰዎችን እናውቃለን ማለት ከመልካም ነገር ሲከለክላቸው ኒቆዲሞስ ግን ዐዋቂ ሳለ ራሱን ዝቅ አድርጎ፣ እምነት በማጣት የነጠፈችውን የፈሪሳውያንን ኅብረት ጥሎ፣ ሐዋርያትን መስሎ ጌታውን አግኝቶታል፡፡ ጌታችን ዓለምን ለማዳን ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው በለየባት በዚያች አስጨናቂ ሰዓት፤ ሐዋርያት በተበተኑባት አይሁድ በሠለጠኑባት በዕለተ ዓርብ የጌታችንን ቅዱስ ሥጋውን በድርብ በፍታ ገንዞ የቀበረ፣ እሱን ያገኘ ያገኘኛል ሳይል በድፍረት ከእግረ መስቀሉ የተገኘ ሰው ነው – ኒቆዲሞስ፡፡ ስለዚህም ሰባተኛው ሳምንት በእርሱ ስም ተሰይሟል፡፡

#join or #share
https://t.me/joinchat/WPlEyEeAttNFBvZK
መንፈሳዊ ህይወት pinned «ኒቆዲሞስ ሰባተኛው ሳምንት ‹ኒቆዲሞስ› የሚል ስያሜ ያለው ሲኾን፣ የስያሜው መነሻም በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ፫ የተመዘገበው ኒቆዲሞስ የተባለው የአይሁድ አለቃ ታሪክ ነው፡፡ ኒቆዲሞስ በሦስት መንገድ የአይሁድ አለቃ ነበር፤ በሥልጣን፣ በዕውቀትና በሀብት፡፡ ሰው ሥልጣን ቢኖረው ሀብትና ዕውቀት ላይኖረው ይችላል፡፡ ዕውቀት ቢኖረው ደግሞ ሀብትና ሥልጣን ላይኖረው ይችላል፡፡ ሀብት ቢኖረውም ዕውቀትና ሥልጣን…»
አዕማደ ምስጢራት ምን ምን ናቸው?

አዕማደ ምስጢራት አምስት የሆኑት አራቱ ባህርያተ ሥጋና (አፈር፣ ውኃ፣ እሳትና ነፋስ) አምስተኛው ባህርየ ነፍስ (ልባዊት፣ ነባቢት፣ ሕያዊት የሆነች) ምሳሌ ያደረገ ሲሆን በዮሐ 5፡1 ያለችው አምስት እርከኖች የነበራት መጠመቂያም የእነዚህ ምሳሌ ናት፡፡ ያቺ መጠመቂያ ለድኅነተ ሥጋ ነበረች፤ አዕማደ ምሥጢር ግን ለድኅነተ ነፍስና ለድኅነተ ሥጋ ናቸው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አምስቱን አዕማደ ምስጢራት በረቂቅነታቸው እና በአኳሃን ቅደም ተከተላቸው እንደሚከተለው ታስቀምጣቸዋለች፡፡ እነዚህም ምሥጢረ ሥላሴ (የሥላሴን አንድነትና ሦስትነት የምንማርበት)፣ ምሥጢረ ሥጋዌ (የአምላክን ሰው መሆን የምንማርበት)፣ ምሥጢረ ጥምቀት (ስለ ዳግም መወለድ የምንማርበት)፣ ምሥጢረ ቁርባን (ስለ ክርስቶስ ሥጋና ደም የምንማርበት) እና ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን (ስለ ዳግም ምጽዓት የምንማርበት) ናቸው። አምስቱ አዕማደ ምሥጢር በአፈጻጸማቸው በሦስት ይከፈላሉ ። እነዚህም ምሥጢረ ሥላሴና ምሥጢረ ሥጋዌ አምነን የምንቀበላቸው፤ ምሥጢረ ጥምቀትና ምሥጢረ ቁርባን አምነን የምንተገብራቸው፤ ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን አምነን በተስፋ የምንጠብቀው ናቸው። ከዚህ ቀጥሎ ያሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ምስጢራቱን ያብራራሉ፡፡

1.✍️ምስጢረ ሥላሴ፡  “አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፡፡” ማቴ 28፡20

2.✍️ምስጢረ ሥጋዌ፡  “ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን።” ዮሐ 1፡14

3.✍️ምስጢረ ጥምቀት፡ “ያመነ የተጠመቀም ይድናል፥ ያላመነ ግን ይፈረድበታል።” ማር 16፡16

4.✍️ምስጢረ ቁርባን፡ “ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፡፡” ዮሐ 6፡54

5.✍️ምስጢረ ትንሣኤ ሙታን፡  “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፡፡” ዮሐ 11፡23

#join or #share
@linkortodoxe21
@linkortodoxe21
@linkortodoxe21
የአዕማደ ምስጢራት መሠረት ምንድን ነው?

አዕማደ ምስጢራት ይዘት ምንጭ የጌታና የሐዋርያት ትምህርት ነው፡፡ ይሁን እንጅ አነሳሱ በጸሎተ ሃይማኖት ወይም አባቶቻችን ምዕመናንን በትክክለኛው ሃይማኖት ለማጽናትና መናፍቃንን ድል ለመንሳት በተካሄዱ በጉባዔ ኒቂያና ጉባዔ ቁስጥንጥንያ ነው፡፡ ‎ከዚህ በኋላ አባቶቻችን ጸሎተ ሃይማኖትን መሰረት በማድረግ ከብሉያት ከሐዲሳትና ከሊቃውንት መጽሃፍት በማውጣጣት አምስቱ አዕማደ ምሥጢራትን አዘጋጅተዋል፡፡ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ መሰረት የሆኑት አምስቱ አዕማደ ምስጢራት መሰረታቸውን ከመጽሐፍ ቅዱስ ያድርጉ እንጂ ስያሜ መሰረታቸው 318ቱ ሊቃውንት በኒቂያ አርዮስን ካወገዙ ቦኋላ ካስታወቁት የሃይማኖት ቀኖና (ጸሎተ ሃይማኖት) ነው፡፡

በጸሎተ ሃይማኖት “ነአምን በአሃዱ አምላክ እግዚአብሔር(በአንድ አምላክ በእግዚአብሔር አብ እናምናለን)” ሲል በእግዚአብሔር አብ ያለውን እምነት፣ “ወነአምን በአሃዱ እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ (በአንድ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን)” ሲል በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን እምነት፣ “ወነአምን በመንፈስ ቅዱስ እግዚእ (በመንፈስ ቅዱስም እናምናለን)” ሲል በመንፈስ ቅዱስ ያለውን እምነት በመግልጽ ምስጢረ ሥላሴን ያጸናል፡፡ እንዲሁም “ዘበእንቲአነ ለሰብእ ወበእንተ መድኃኒትነ ወረደ እምሰማያት፣ ተሰብእ ወተሠገወ እመንፈስ ቅዱስ፤ ወእማርያም እምቅድስት ድንግል (ስለእኛ ስለ ሰዎች ስለመዳናችን ከሰማይ ወረደ፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ፈጽሞ ሰው ሆነ)” በማለት ምስጢረ ሥጋዌን ያጸናል፡፡ በተጨማሪም “ወነአምን በአሃቲ ቅድስት ቤተክርስቲያን (በአንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን እናምናለን)” በማለት ሥጋ ወደሙ የሚፈተትበትን ቤተ-ክርስቲያን በመጥቀስ ምስጢረ ቁርባንን ያጸናል፡፡ “ወነአምን በአሃቲ ጥምቀት (በአንዲት ጥምቀትም እናምናለን)” በማለት ምስጢረ ጥምቀትን ያጸናል፡፡ “ወንሴፎ ትንሳኤ ሙታን (የሙታንንም መነሳት ተስፋ እናደርጋለን)” በማለት ምስጢረ ትንሳኤ ሙታንን ያጸናል፡፡

#join or #share
ለሌሎች ሼር በማረግ ያድርሱ
@linkortodoxe21
@linkortodoxe21
@linkortodoxe21
አዕማደ ምስጢርን ማወቅ ለምን ይጠቅማል?

በሥጋዊ ዐይን እግዚአብሔርን ማየትና በውስን አዕምሮ ሐልዎተ እግዚአብሔርን መመርመር አይቻልም፡፡ ምክንያቱም የሰው ልጅ  ስለራሱም ይሁን ለእርሱ አንክሮና ተዘክሮ ስለተፈጠሩት ፍጥረታት ገና ያልደረሰባቸው ነገሮች አሉ፡፡ እግዚአብሔር ግን እርሱ በወደደው መጠን ለአባቶቻችን ለቅዱሳን ነቢያትና ሐዋርያት አዕምሮአቸው ሊረዳው በሚችለው መጠን በብዙ ምሳሌና በብዙ ጎዳና ማንነቱን ገልጾላቸዋል (ዕብ 1፡1-2)፡፡ እግዚአብሔርንም የምናውቀው እርሱ ራሱን ለሰው ልጆች በገለጠው መጠንና የሰው ልጅ መረዳት በሚችለው መጠን ብቻ ነው፡፡

አንድ ሰው በዚህ ዓለም ሲኖር አምስቱን አዕማደ ምስጢራት በሚገባ ከተማረ በሕይወቱ ምንም እንኳን ነፋሳት ቢነፍሱ ጎርፍም ቢጎርፍ ከእምነቱ ምንም ሊያናውጠው አይችልም፡፡ እነዚህ ትምህርቶች ከደሙና ከአጥንቱ ተዋሕደው የዚህን ዓለም ፈተና እንዲቋቋም ያስችሉታል፡፡ አዕማደ ምስጢራትን ያወቀና ያመነ እና የሥላሴ ልጅነትን በጥምቀት ያገኘ አባት እናት ቢሞቱበት በሥላሴ አባትነት ይጽናናል፡፡ መከራ ቢደርስበት አምላክ ሰው ሆኖ በዚህ ምድር ላይ የደረሰበትን መከራ እያሰበ ከምንም አይቆጥረውም፡፡ ረኀበ ነፍስ ቢደርስበት ቅዱስ ሥጋውን ይበላል፤ ክቡር ደሙንም ይጠጣል፡፡ በእምነቱ ምክንያት እንገድልሀለን ቢሉት ትንሣኤ ዘጉባዔን (ትንሣኤ ሙታንን) ተስፋ ያደርጋል፡፡ ይህም በመሆኑ ቅድስት ቤተክርስቲያን ከኅሊና እግዚአብሔር እንዳይርቅና ከእግዚአብሔር ጋር በእምነት እንዲጸና እነዚህን ምሰሶዎች (ምስጢራት) ታስጨብጠዋለች፡፡ በእነዚህ ምሰሶዎች (ምስጢራት) የተደገፈ ጠላቶቹን አጋንንትንና መናፍቃንን ድል ያደርጋል፡፡ በአጠቃላይ አዕማደ ምስጢራትን በሚገባ ማወቅ ሃይማኖትን በሚገባ ለመረዳት፣ ከጥርጥርና ከኑፋቄ ለመጠበቅና በሃይማኖት ጸንቶ ጽድቅን ለመፈጸም ይጠቅማል፡፡

ሼር ሼር ሼር ይደረግ
#join
@linkortodoxe21
@linkortodoxe21
@linkortodoxe21
❤️እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ልዩ የሚያደርጋትን መገለጫዎችን እናቀርብላችኋለን፡፡ ሁላችንንም በአማላጅነቷ ትጠብቀን፡፡🙏🙏🙏
ቤተክርስቲያን ድንግል ማርያም ያላትን ክብር ለመግለጥ የተለያዩ ምሳሌዎችን ትሰጣለች። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በቅዱሳን ሁሉ ስትመሰገን የምትኖር ናት። እመቤታችን ያላትን ክብር እንዴት እንደሚገልጹት ተጨንቀው በምን በምን እንመስልሻለን በማለት ያላትን ክብር ለመግለጽ በሰው ህሊና የሚለካ ምሳሌ ማጣታቸውን ብዙ ቅዱሳን ተናግረዋል። በተለይም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን በማመስገን በቤተክርስቲያናችን ዘወትር የሚነሱት የሶርያው ቅዱስ ኤፍሬም፤ የብህንሳው አባ ሕርያቆስ እና ኢትዮጵያዊው አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ይገኙበታል። የእመቤታችንን ክብር ያለተረዱ ሰዎች ለምን እኛ ኦርቶዶክሳውያን እንደምናመሰግናት ዘወትር በጸሎታችን እንደምናነሳት ጥያቄ የሚያቀርቡ አሉ። ሁሉም ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ከሕጻንነቱ ጀምሮ የእመቤታችንን ምስጋና ይማራል ሁልጊዜም ኣባታችን ሆይ ብሎ ጸሎት የጀመረ በመልኩ ቅዱስ ገብርኤል ሰላምታ ሰላም እንልሻለን ብሎ ድንግል ማርያምን ሳያመሰግን የሚቀር የለም። ቤተክርስቲያናችን ድንግል ማርያምን ከፈጣሪ በታች ከፍጡራን ሁሉ በላይ በማለት ክብሯን ትገልጻለች። እኛም የእመቤታችንን ክብር ስንናገር ስለ እርሷ የተነገረውን በመረዳት መሆን ይገባል። ድንግል ማርያምን ልዩ የሚያደርጋትና የክብሯ መገለጫ ከሆኑት መካከል እናቀርብላችኋለን ለጋደኞቻችሁ ሼር በማረግ ወደ ቻናሉ ይጋብዙ 🙏🙏🙏

#join or #share
@linkortodoxe21
@linkortodoxe21
@linkortodoxe21
መንፈሳዊ ህይወት pinned «❤️እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ልዩ የሚያደርጋትን መገለጫዎችን እናቀርብላችኋለን፡፡ ሁላችንንም በአማላጅነቷ ትጠብቀን፡፡🙏🙏🙏 ቤተክርስቲያን ድንግል ማርያም ያላትን ክብር ለመግለጥ የተለያዩ ምሳሌዎችን ትሰጣለች። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በቅዱሳን ሁሉ ስትመሰገን የምትኖር ናት። እመቤታችን ያላትን ክብር እንዴት እንደሚገልጹት ተጨንቀው በምን በምን እንመስልሻለን በማለት ያላትን ክብር ለመግለጽ…»
ወላዲተ አምላክ መሆኗን
እመቤታችን ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ ናት። አንዳንዶች የአምላክ እናት የኢየሱስ እናት በማለት ይጠራሉ በእርግጥ ይህ አጠራር በበጎ ህሊና አነጋገር ችግር ባይኖርበትም የትርጉም ፍቺ ላይ ችግረ እንዳያመጣ ወላዲተ አምላክ ብሎ መጥራት የበለጠ የተዋሕዶን ምሥጢር የሚገልጥ ይሆናልና ሁሉም ሰው ይህንን መጠሪያ ቢለምደውና ቢጠቀምበት ይመረጣል። አንዳንድ የመናፍቃን ድርጅቶች የኢየሱስ እናት ብለው እመቤታችንን የተቀበሉ ለማስመስል በራሪ ጽሑፍ የሚያሰራጩበት ጊዜ ነበር ምክንያቱም ወላዲተ አምላክ መባሏን የሚቃወሙ ነገር ግን የኢየሱስ እናት ብለው የሚጠሩ ከዚህ በፊት ነበሩና ያሳደገም እናት ተብሎ ሊጠራ ይችላልና። በተለይም ንስጥሮስ የተባለው ከሃዲ ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ ልትባል አይገባም ብሎ በክህደት በመነሳቱ ዓለማቀፋዊ ጉባኤ እንዲጠራና ውግዘት እንዲተላለፍበት ሆኗል። እመቤታችን ወላዲተ አምላክ ናት የሚለው አነጋገር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሰው መሆኑን ስለሚገልጽ ነው ። በመጽሐፍ ቅዱስ ከተጠቀሱት ውስጥ ጌታችን የተዋሐደው ሥጋ ከእመቤታችን መሆኑን አንዱን ለምሳሌ ያህል አንስተን መመልከት እንችላለን። ቅዱስ ጴጥሮስ የተናገረውን ማስተዋል ለዚህ መልስ ይሰጣል
“ዳዊት ስለ እርሱ እንዲህ ይላልና። ጌታን ሁልጊዜ በፊቴ አየሁት፥ እንዳልታወክ በቀኜ ነውና።ስለዚህ ልቤን ደስ አለው፥ ልሳኔም ሐሤት አደረገ፥ ደግሞም ሥጋዬ በተስፋ ያድራል፤ ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፥ ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትሰጠውም። የሕይወትን መንገድ አስታወቅኸኝ፤ ከፊትህ ጋር ደስታን ትሞላብኛለህ።ወንድሞች ሆይ፥ ስለ አባቶች አለቃ ስለ ዳዊት እንደ ሞተም እንደ ተቀበረም ለእናንተ በግልጥ እናገር ዘንድ ፍቀዱልኝ፤ መቃብሩም እስከ ዛሬ በእኛ ዘንድ ነው።ነቢይ ስለ ሆነ፥ ከወገቡም ፍሬ በዙፋኑ ያስቀምጥ ዘንድ እግዚአብሔር መሐላ እንደ ማለለት ስለ አወቀ፥ ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ አስቀድሞ አይቶ፥ ነፍሱ በሲኦል እንዳልቀረች ሥጋውም መበስበስን እንዳላየ ተናገረ። ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሣው ለዚህም ነገር እኛ ሁላችን ምስክሮች ነን”  /ሐዋ 2፥25—32/
በዚህ ቃል ላይ እንደተነገረው ቅዱስ ዳዊት ሥጋዬ ብሎ የሚጠራው በእርግጥ የማንን ሥጋ ነው? ብለን ብንጠይቅ ክርስቶስ የተዋሐደውን ሥጋ መሆኑን ምንባቡ ይናገራል ። ዳዊት ሥጋዬ ብሎ የተናገረው በእርግጥም የእርሱ ሥጋ ነው ነገር ግን ሥጋዬ አይበሰብስም ብሎ ሲናገር ደግሞ ምሥጢራዊ ትርጉም እንዳለው ያመለክታል ፤ ይህ ሊሆን የሚችለው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ሲነሳ ብቻ ነውና ። ወንጌላዊ ቅዱስ ማቴዎስ እና ቅዱስ ሉቃስ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት አቆጣጠር ብለው ያስቀመጡት ጌታችን ከእመቤታችን ቅድሰት ድንግል ማርያም የተዋሐደውን ሥጋ መሠረት አድርገው ነውና፤ ይህ ባይሆን ኖሮ የትውልድ ሐረግ ለመቁጠር ባልተነሱ ነበር ። ስለዚህ እኛ ኦርቶዶክሳውያን በሙሉ ወላዲተ አምላክ ብለን እናታችንን እንጠራታለን በዚህም የተዋሕዶን ምሥጢር እንመሰክራለን።

#join or #share💎💎💎
@linkortodoxe21
@linkortodoxe21
@linkortodoxe21
📌ግብረ አውናን ምንድነው

📌ግብረ አውናን ተገቢ ነውን

📌ግብረ አውናን በመፅሐፍ ቅዱስ

📌ከግብረ አውናን ለመውጣት ምን ላድርግ

📌ግብረ አውናን እንዳያገኘኝ ምን ላድርግ

ሁሉን ለማግኘት
@senbet_tmehert_bet
 እንካን ለበዓለ ሆሣዕና በሰላም አደረሳችሁ/አደረሰን

የዐቢይ ጾም ሳምንት ሲኾን፣ የሰሙነ ሕማማት መጀመሪያ ነው፡፡ ሆሣዕና ስያሜው በማቴዎስ ወንጌል ፳፩፥፱ ከሚገኘው ትምህርት የተወሰደ ሲኾን ትርጕሙም ‹መድኀኒት ወይም ‹አሁን አድን› ማለት ነው፡፡ ክብር ይግባውና አምላካችን በአህያ ጀርባ ላይ ተቀምጦ ‹‹ሆሣዕና በአርያም›› የሚሉ የአዕሩግ፣ የሕፃናት ምስጋና እየቀረበለት ወደ ኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ጉዞ ያደረገበት፤ ትሕትናውን የገለጠበት፤ ይህን ዓለም ከማዕሠረ ኃጢአት መፍታቱን በምሳሌ ያስረዳበት ዕለት ነው፡፡ ‹‹ተጽዕኖ›› ተብሎ ከሚጠራው የዐቢይ ጾም መጨረሻ (ዕለተ ዓርብ) እና ከሰሙነ ሕማማት መግቢያ ጀምሮ ያለው ሳምንት ሆሣዕና ይባላል፡፡ የክርስቶስን ነገረ ሕማሙን፣ ስቅለቱን፣ ሞቱን፣ ትንሣኤውን ሆሣዕና ተብሎ ዓለምን ማዳኑን የሚናገሩ ቅዱሳት መጻሕፍት የሚነበቡበት፤ አምላካችን ለሰው ልጅ መዳን መከራ መቀበሉና የማዳን ሥራው በሰፊው የሚታወጅት፤ በሰሙነ ሕማማት ለሚያርፉ ምእመናን ጸሎተ ፍትሐት የሚደረግበት፤ ወንጌል በአራቱ ማዕዘን የሚሰበክበት ሳምንት ነው – ሆሣዕና፡፡ ከዚያው አያይዞም ሰሙነ ሕማማት ይቀጥላል፤ ወቅቱም የክርስቶስን ነገረ ሕማሙንና ዓለምን ያዳነበት ጥበቡን የምንሰማበት ሳምንት ነው፡፡ በሞቱ ሞታችንን አጥፍቶ መንግሥቱን እንድንወርስ የፈቀደልን ልዑል እግዚአብሔር ስሙ የተመሰገነ ይኹን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር
አሜን!!!

#join በማለት ተቀላበሉን
@linkortodoxe21
@linkortodoxe21
@linkortodoxe21
መንፈሳዊ ህይወት pinned « እንካን ለበዓለ ሆሣዕና በሰላም አደረሳችሁ/አደረሰን የዐቢይ ጾም ሳምንት ሲኾን፣ የሰሙነ ሕማማት መጀመሪያ ነው፡፡ ሆሣዕና ስያሜው በማቴዎስ ወንጌል ፳፩፥፱ ከሚገኘው ትምህርት የተወሰደ ሲኾን ትርጕሙም ‹መድኀኒት ወይም ‹አሁን አድን› ማለት ነው፡፡ ክብር ይግባውና አምላካችን በአህያ ጀርባ ላይ ተቀምጦ ‹‹ሆሣዕና በአርያም›› የሚሉ የአዕሩግ፣ የሕፃናት ምስጋና እየቀረበለት ወደ ኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ…»