ቃለ ጽድቅ ዘመካነ ሕይወት | የመ/ሕ/ሰ/ት/ቤት ሰሌዳ መጽሔት ንዑስ ክፍል
1.03K subscribers
2.92K photos
44 videos
102 files
787 links
ይኽ በፈረንሳይ መካነ ሕይወት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያን መካነ ሕይወት ሰ/ት/ቤት መንፈሳዊ ጽሑፎችና መልእክቶች የሚለቀቁበት ሚዲያ ነው።
https://linktr.ee/kaletsidkizm
Download Telegram
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞✞✞ እንኩዋን #ለብርሃነ_መስቀሉ እና #ለቅዱሳኑ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

✞✞✞ #ቅዱስ_ዕፀ_መስቀል ✞✞✞

=>ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና ቸር አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳን ከሰማያዊ ክብሩ ወደ ምድር ወርዶ: በማሕጸነ #ማርያም_እግዝእት በኪነ ጥበቡ ተጸንሶ: በኅቱም ድንግልና ተወልዶ: በፈቃዱ መከራ መስቀልን ተቀብሎ:
¤ከግራ ቁመት:
¤ከገሃነመ እሳት:
¤ከሰይጣን ባርነት:
¤ከኃጢአት ቁራኝነትም አድኖናል::

=>+"+ እምእቶነ እሳት ዘይነድድ አንገፈነ +"+ እንዳለ ሊቁ::

+ምንም መስቀል በብሉይ የወንጀለኞች መቅጫ ሆኖ ቢቆይም እግዚአብሔር ለዓለም መዳኛነት የመረጠው ነውና ሕብረ ትንቢቶች ሲነገሩለት: በብዙ ሕብረ አምሳልም ሲመሰል ኑሯል:: ከተፈጥሯችን ጀምሮ ዓለም ራሷ አርአያ #ትዕምርተ_መስቀል ናት::

+እግዚአብሔር ለቃየን እንዳይገድሉት ከሰጠው ምልክት (ዘፍ. 4:15) ጀምሮ
¤#ይስሐቅ ሊሰዋ የተሸከመው እንጨት (ዘፍ. 22:6):
¤#ቅዱስ_ያዕቆብ ያያት የወርቅ መሰላል (ዘፍ. 28:12):
¤ያዕቆብ የዮሴፍን ልጆች የባረከበት መንገድ (ዘፍ. 48:14):
¤ባሕረ ኤርትራን የከፈለችው #የሙሴ_በትር (ዘጸ. 14:15):
¤#የናሱ_ዕባብ የተሰቀለበት እንጨት (ዘኁ. 21:8) ጨምሮ በርካታ ምሳሌዎች ለቅዱስ መስቀሉ መኖራቸውን መተርጉማን ተናግረዋል::

+#ቅዱስ_ዳዊትን የመሰሉ ነቢያት ደግሞ "ለሚፈሩሕ ከቀስት ያመልጡ ዘንድ ምልክትን ሰጠሃቸው" እያሉ መስቀሉን ከርቀት ተመልክተዋል:: (መዝ. 59:4)

+በሐዲስ ኪዳን ግን ምሳሌው ገሃድ ሆኖ: ጌታ በዕፀ መስቀል ላይ ተሰቅሎ ሥጋውን ቆረሰበት: ደሙን አፈሰሰበት: ዓለምንም አዳነበት:: ስለዚህም "#መስቀል_ብርሃን_ለኩሉ_ዓለም: #መሠረተ_ቤተ_ክርስቲያን" ተብሎ የሚመሰገን ሆኗል::

+#ቅዱስ_ያሬድ ሊቁ አክሎ "መስቀል መልዕልተ ኩሉ ነገር: ያድኅነነ እምጸር" ብሎ ጠላትን ማሳፈሪያ መሆኑን ይነግረናል:: #ብርሃነ_ዓለም #ቅዱስ_ዻውሎስም ስለ መስቀሉ አምልቶ አጉልቶ አስተምሯል:: መመኪያችን ነውና:: (1ቆሮ. 1:18, ገላ. 6:14)

+አንዳንዶቹ እኛን 'የተሰቀለውን ትታቹሃል' ይሉናል:: የተሰቀለውማ የጌቶች ጌታ: የነገሥታት ንጉሥ: የአማልክት አምላክ: ሁሉ በእጁ የተያዘ: #ኢየሱስ_ክርስቶስ ነውና ከኦርቶዶክስ በላይ የሚያመልክ በወዴት አለና::

+ነገር ግን መስቀሉን ንቆ የተሰቀለውን ማክበር አይቻልምና እኛ ለመስቀሉ የጸጋ ስግደትን እንሰግዳለን: እናመሰግነዋለን: እናከብረዋለን: ቤዛ: ጽንዕ: መድኃኒት: ኃይል እያልንም እንጠራዋለን:: አባቶቻችን በመስቀሉ ምርኩዝነት ማዕበለ ኃጢአትን: ባሕረ እሳትን ተሻግረዋል::

+በመስቀሉ ቢመኩ አጋንንትን ድል ነስተዋል:: ጠላትንም አሳፍረዋል:: እኛም በመስቀሉ አምነን ከብረን: ገነን እንኖራለን:: ተጠቅመንበታልና ከራሳችን ሕይወት በላይ ምስክርን አንፈልግም::

+"+ #በዓለ_መስቀል +"+

=>#መድኃኔ_ዓለም ክርስቶስ ካረገ ከዓመታት በሁዋላ አይሁድ በአንድ ነገር ተቸገሩ:: የክርስቶስን ሐዋርያት እያሳደዱ ቢገድሉም ከመስቀሉና ሥጋ ክርስቶስ አርፎበት ከነበረው ጐልጐታ ላይ የሚደረገውን ተአምር ግን መግታት አልተቻላቸውም::

+መቼም ለተንኮል አያርፉምና ቅዱስ መስቀሉን ሽፍቶቹ ከተሰቀሉባቸው ጋር ደርበው አርቀው ቀበሩት:: አካባቢው የጉድፍ መጣያ እንዲሆንም አዋጅ ነገሩ:: ለክፋት ሲሆን ተባባሪው ብዙ ነውና ለ270 ዓመታት ያህል ቆሻሻ ቢጥሉበት ተራራ ሆነ::

+ከዚህ ሁሉ ነገር በሁዋላ እናታችን ቅድስት #እሌኒ (ሔለና) በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት: በቅዱስ #ኪራኮስ መሪነት: በቅዱስ #ሚካኤል ረዳትነት ደመራ አስደምራ: እጣን አጢሳ መካነ መስቀሉን አገኘች::

+መስከረም 17 ቀን የተጀመረው ቁፋሮ መጋቢት 10 ቀን ተጠናቆ: ንጹሕ መስቀሉ ወጥቶ ብርሃን በርቷል: ሙታን ተነስተዋል:: ከ10 ዓመት በሁዋላም የመስቀሉ ቤተ መቅደስ ታንጾ መስከረም 17 ቀን ተቀድሷል::

+ይህ ቅዱስ ዕፀ መስቀልም በደጉ #አፄ_ዳዊት ዘመን ወደ ሃገራችን መጥቶ: በጻድቁ #አፄ_ዘርዓ_ያዕቆብ አማካኝነት በደብረ ከርቤ (#ግሸን_ማርያም) ተለብጦ ተቀምጧል::

+"+ #ቅዱስ_አውዶኪስ_ቀሲስ +"+

=>ይህ ቅዱስ ሰው ለቅዱስ መስቀሉ ከነበረው ፍቅር የተነሳ በብዙ ድካም ወደ #ኢየሩሳሌም በእግሩ ተጉዞ ነበር:: ከብዙ መንገደኞች ጋር በጐዳና ላይ ሳሉ ታዲያ አንድ አይሁዳዊ (ሰማርያዊ) ተቀላቀላቸው:: በወሬ በወሬ የት እንደሚሔዱ ሲጠይቃቸው "መካነ መስቀሉን ለመሳለም ወደ #ጐልጐታ ነን" አሉት::

+እሱ ግን ከት ብሎ ስቆ "እንዴት እንጨት ትሳለማላችሁ" በሚል አፌዘባቸው:: የፀሐዩ ሐሩር እጅግ ጠንቶ ነበርና ቅዱስ አውዶኪስ ኃይለ መስቀሉን ሊያሳይ ወደደ:: በመንገድም መርዝነት ያለው ውሃ ነበርና ቅዱሱ ቀርቦ ጸልዮ በመስቀሉ ባረከውና ፈጥኖ ወደ ጣፋጭነት ተቀየረ::

+ምዕመናኑ ደስ ብሏቸው ሲጠጡ ያ አይሁዳዊ 'እጠጣለሁ' ብሎ ቢቀርብ ወደ ነበረው ተመለሰበት:: 'በኮዳ የያዝኩትን እማልጠጣ' ብሎ ቢከፍተው ደግሞ ተልቶ አገኘው:: እጅግ ደንግጦ አለቀሰ:: በጣም ጠማው: ግን ምኑን ይጠጣ!

+አማራጭ ሲያጣ ወደ ቅዱስ አውዶኪስ ሒዶ እግሩ ላይ ወድቆ አለቀሰ:: በመስቀሉ ቢማጸን መራራው ጣፈጠለት:: በዚህ ምክንያትም ወደ ክርስትና ተመልሷል:: ቅዱሱ በመልካም ሽምግልና ሲያርፍ ውሃው የተቀየረበት ቦታ ላይ ቤተ መቅደስ ታንጾ በዚህ ቀን ተቀድሷል::

+"+ #ቅድስት_ታኦግንስጣ +"+

=>በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን የነበረችው ሮማዊቷ እናት መንገድ ላይ ቁማ #ወንጌል ስታነብ በንጉሥ ወታደሮች ተማርካ ወደ #ሕንድ ተወስዳለች:: በዚያም በመስቀል አማትባ ሙት በማስነሳቷ የሃገሩ ሰው ወደ ክርስትና ከነ ንጉሡ ተመልሰዋል:: እርሷም ገዳም አንጻ: ደናግሉን ሰብስባ በንጽሕና ኑራለች:: በዚህ ቀን ዐርፋ ሲቀብሯት የብርሃን መስቀል መቃብሯ ላይ ተተክሏል::

=>አምላከ ቅዱሳን በኃይለ መስቀሉ: በሞገሰ መስቀሉ ይጠብቀን:: ከበረከቱ አሳትፎ በዓሉን የሰላም ያድርግልን::

=>መስከረም 17 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ዕፀ መስቀል
2.ቅድስት እሌኒ ንግስት
3.ቅዱስ ኪራኮስ አረጋዊ
4.ቅዱስ መቃርስ ሊቀ ዻዻስ
5.ቅዱስ አውዶኪስ ቀሲስ
6.ብጽዕት ታኦግንስጣ ሮማዊት
7.ቅዱስ ዲዮናስዮስ ሊቀ ዻዻሳት

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት (ቀዳሜ ሰማዕት)
2.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ ዘብዴዎስ)
3.ቅዱሳን አበው መክሲሞስና ዱማቴዎስ
4.አባ ገሪማ ዘመደራ
5.አባ ዸላሞን ፈላሢ
6.አባ ለትጹን የዋህ
7.ቅዱስ ኤዺፋንዮስ ሊቅ (ዘደሴተ ቆዽሮስ)

=>+"+ የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና . . . መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ:: የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ:: እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን:: +"+ (1ቆሮ. 1:18-23)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
@kaletsidkzm