ቃለ ጽድቅ ዘመካነ ሕይወት | የመ/ሕ/ሰ/ት/ቤት ሰሌዳ መጽሔት ንዑስ ክፍል
1.03K subscribers
2.92K photos
44 videos
102 files
787 links
ይኽ በፈረንሳይ መካነ ሕይወት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያን መካነ ሕይወት ሰ/ት/ቤት መንፈሳዊ ጽሑፎችና መልእክቶች የሚለቀቁበት ሚዲያ ነው።
https://linktr.ee/kaletsidkizm
Download Telegram
††† እንኳን ለሐዋርያው ቅዱስ ናትናኤል ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ናትናኤል †††

††† በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት ከቅዱሳን ሐዋርያት መካከል ዘግይቶ ሰማዕትነትን የተቀበለ ይህ ቅዱስ ሐዋርያ ነው::

ቅዱሱ ሐዋርያ የተወለደው ከእሥራኤላውያን ወላጆቹ ጌታችን በተወለደበት ዘመን አካባቢ ነው:: ይህ በምን ይታወቃል ቢሉ እርሱ ሕፃን እያለ ሔሮድስ 144,000 ሕፃናትን ሲፈጅ እርሱ ግን በእግዚአብሔር ጥበብ ተርፏል:: እናቱ በቅርጫት ውስጥ አድርጋ የበለስ ዛፍ ላይ አስቀምጣው ተደብቃ ታጠባው ነበር::

ለሐዋርያው ወላጆቹ ያወጡለት ስም ስምዖን ሲሆን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ ናትናኤል ብሎታል:: በባልንጀሮቹ ሐዋርያት ደግሞ የቃናው ስምዖን (ገሊላ ቃና አካባቢ ስላደገ) አንዳንዴም ቀናተኛው ስምዖን ይሉት ነበር::

ምሑረ ኦሪት ነበርና ዘወትር ለሕግ ይቀና ነበር:: በገሊላ ቃና ሰርግ የደገሰው ዶኪማስ የቅዱስ ናትናኤል የአጎት ልጅ ነው:: ጌታና ደቀ መዛሙርቱን ዶኪማስ የጠራበት አንዱ ምክንያትም ይሔው ነው::

ቅዱስ ናትናኤል ኦሪትን ከገማልያል ተምሮ: ከበለስ ቁጭ ብሎ ይተክዝ ነበር:: "መሲሕ ምነው ቀረህ?" እያለም ይተክዝ ነበር:: ማዕምረ ኅቡዓት አምላካችን ክርስቶስ ይህንን አውቆ በፊልጶስ አማካኝነት ጠርቶታል::

ናትናኤል ለጊዜው ተከራክሮ ነበር:: በኋላ ግን የጌታችንን ማንነት በደቂቃዎች ተረድቶ አምኗል:: ጌታችንም "ክዳት ሽንገላ በልቡ ውስጥ የሌለበት ንጹሕ እሥራኤላዊ" ሲል አመስግኖታል::

ሐዋርያው ቅዱስ ናትናኤል ከጌታችን እግር ሥር ምሥጢረ መንግስተ ሰማያትን ተምሮ: በጸጋ መንፈስ ቅዱስም ሰክሮ: ብዙ አሕዛብን ከጨለማ (ጣኦት አምልኮ) ወደ ብርሃን (አሚነ ክርስቶስ) መልሷል:: እጅግ ብዙ መከራንም ተቀብሏል::

የጌታችን ወንድም የተባለ ቅዱስ ያዕቆብ በአይሁድ ከተገደለ በኋላም ቅዱስ ናትናኤል የኢየሩሳሌም ሁለተኛ ኤጲስ ቆጶስ ሆኖ አገልግሏል:: ከአይሁድም ዘንድ ብዙ መከራ ደርሶበታል:: በመጨረሻም በዚህች ዕለት በሰማዕትነት አልፏል:: በገድለ ሐዋርያት ላይ እንደተጠቀሰው ቅዱሱ ሰማዕት የሆነው በመቶ ሃምሳ ዓመቱ ነው:: ያ ማለት ደግሞ ከሐዋርያት አባቶች በመጨረሻ ያረፈው እርሱ ነው ያሰኛል::

††† አባ ብስንዳ †††

††† ዳግመኛ በዚህ ቀን ታላቁ አባ ብስንዳ ይታሠባል::
አባ ብስንዳ በዘመነ ጻድቃን ምድረ ግብጽ ውስጥ ከነበሩ ታላላቅ አበው አንዱ ነው:: ቅዱሱን ከገድሉ ጽናት የተነሳ መላእክት በእጅጉ ይወዱት ነበር:: "እኔ ልሸከምህ - እኔ ልሸከምህ" እያሉ ይሻሙበት: በተራ በተራም ተሸክመውት ይውሉ ነበር:: እርሱም ለበርካታ ዓመታት ውኃ የሞላበት ጉድጓድ ውስጥ ገብቶ ይጸልይ ነበር::

እንደ እሳት በሚባላው በረዶ ውስጥ ገብቶ መጸለዩ የፈጣሪውን ሕማማት ለመሳተፍ እና ለኃጥአን ምሕረትን ይለምን ዘንድ ነው:: ሁሌም በዘጠኝ ሰዓት መላእክት ተሠብስበው ይመጡና በብርሃን ሠረገላ ይሸከሙታል:: ከመሬትም ዘጠኝ ክንድ ከፍ ያደርጉት ነበር::
ከብዙ ዓመታት ተጋድሎ በኋላም በዚህች ቀን ዐርፎ ወደ ፈጣሪው ሒዷል::

††† እግዚአብሔር በቅዱስ ናትናኤል ምልጃ ሃገራችንን ከጥፋት: ሕዝቦቿንም ከመቅሰፍት ይሰውርልን:: ከሐዋርያው እና ከጻድቁ አባ ብስንዳ በረከትም አይለየን::

††† ሐምሌ 10 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ናትናኤል ሐዋርያ (ቀናተኛው ስምዖን)
2.ታላቁ አባ ብስንዳ ጻድቅ
3.አባ ከላድያኖስ ሊቀ ጳጳሳት

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ
2.ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሃገረ ሜራ
3.አቡነ መልክዐ ክርስቶስ
4.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ እልፍዮስ)
5.ቅድስት ዕሌኒ ንግስት
6.ቅዱስ ዕፀ መስቀል

††† "ጌታ ኢየሱስ ናትናኤልን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ ስለ እርሱ 'ተንኰል የሌለበት በእውነት የእሥራኤል ሰው እነሆ' አለ:: ናትናኤልም 'ከወዴት ታውቀኛለህ?' አለው:: ጌታ ኢየሱስም መልሶ 'ፊልጶስ ሳይጠራህ ከበለስ በታች ሳለህ አየሁህ' አለው:: ናትናኤልም መልሶ 'መምሕር ሆይ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ:: አንተ የእሥራኤል ንጉሥ ነህ' አለው::" †††
(ዮሐ. ፩፥፵፰-፶፩)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
††† እንኳን ለጻድቅና ሰማዕት ቅዱስ ዮሐንስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ዮሐንስ ጻድቅ ወሰማዕት †††

††† ቅዱስ ዮሐንስ በቀደመው ዘመን ከነበሩ ታላላቅ አበው አንዱ ሲሆን ሃገረ ሙላዱ መርባስ ትባላለች:: ወላጆቹ እግዚአብሔርን የሚወዱ: ምጽዋትን የሚያዘወትሩና በበጐው ጐዳና የሚኖሩ ነበሩ:: ነገር ግን ልጅ በማጣታቸው ምክንያት ፈጽመው ያዝኑ: ይጸልዩም ነበር:: በተለይ ለመጥምቁ ዮሐንስ ልዩ ፍቅር ስለ ነበራቸው ዝክሩን ይዘክሩ: በስሙም ይማጸኑ ነበርና መጥምቁ ሰማቸው::

ወደ ፈጣሪውም ልመናቸውን በማድረሱ መልክ ከደም ግባት የተባበረለት ደግ ልጅን ወለዱ:: እጅጉን ደስ ስላላቸው በአካባቢያቸው የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስን ቤተ ክርስቲያን በገንዘባቸው አነጹ:: ሕፃኑንም በመጥምቁ ስም "ዮሐንስ" አሉት:: ጻድቁ ቅዱስ ዮሐንስ ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ጸጋ እግዚአብሔር አድሮበታልና ሕይወቱ ግሩም ነበር::

በሕፃን ገላው ይጾምና ይሰግድ: በልጅ አንደበቱም ተግቶ ይጸልይ ነበር:: ወላጆቹ ወደ እረኝነት ባሰማሩት ጊዜም መፍቀሬ ነዳያን ነውና ቁርስና ምሳውን ለነዳያን እያበላ እርሱ ጾሙን ይውል ነበር:: አባቱ የሚያደርገውን ሰምቶ ለማረጋገጥ ተከተለው:: እንዳሉትም እናቱ ጋግራ የሰጠችውን ትኩስ ዳቦ ለነዳያን ሲሰጥ አየው::

ሊቆጣው ፈልጐ "ዳቦህ የታለ?" ቢለው ሕፃኑ ቅዱስ ዮሐንስ "በአገልግሉ ውስጥ አለ" ሲል መለሰለት:: አባት ለመቆጣት እንዲመቸው አገልግሉን ሲከፍተው ግን ያየውን ማመን አልቻለም:: በእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ ዳቦዎቹ ትኩስ እንደሆኑ ተገኙ::

አባትም ወደ ቤቱ ወስዶ "ልጄ! አንተ የእግዚአብሔር ሰው ስለሆንክ እኛን ሳይሆን እርሱን አገልግል" ብሎ ወደ ቤተ ክርስቲያን ላከው::

በዚህ ምክንያት ቅዱስ ዮሐንስ በአሥራ ሁለት ዓመቱ ወደ ትምህርት ገባ:: በስድስት ዓመታትም ብሉይ ከሐዲስ ጠነቀቀ:: አሥራ ስምንት ዓመት ሲሞላው ደግነቱን ወደዋልና በግድ ቅስና ሾሙት:: እርሱ ግን ለተወሰነ ጊዜ አስተምሮ ዘመዱ የሆነውንና ዲያቆኑን ቅዱስ ስምዖንን አስከትሎ መነነ::
በዚያም በፍጹም ገድል ሲኖር ብዙ ተአምራትን ሰርቷል::

¤አንድ ወታደር (አንድ ዐይና ነው) ሊባረክ ብሎ ሲጐነበስ የታወረች ዐይኑን የቅዱስ ዮሐንስ ልብስ ቢነካት በርታለታለች:: ከዚህ አልፎም ቅዱሱ ብዙ ድውያንን ፈውሷል: ለምጻሞችን አድኗል: አጋንንትን ከማደሪያቸው (ከሰው ላይ) አሳድዷል::

ታዲያ አንድ ቀን የወቅቱ የአንጾኪያ ንጉሥ የቅዱስ ዮሐንስን ዜና ይሰማል:: የእርሱ ልጅ ደግሞ አጋንንት አድረውባት ስቃይ ላይ ነበረችና የሚያድናት አልተገኘም:: ንጉሡ "ጻድቁን አምጡልኝ" ብሎ መልዕክተኛ ሲልክ ቅዱስ ዮሐንስ ደመና ጠቅሶ: በዚያውም ላይ ተጭኖ ከተፍ አለ:: ንጉሡ አይቶት ደነገጠ:: አባ ዮሐንስ ግን "እኔ ኃጢአተኛ የሆንኩ ሰው ለምን እንዲህ ትፈልገኛለህ?" ብሎ ታማሚዋን አስጠራ::

ጻድቁ እጆቹን አንስቶ ወደ ፈጣሪው ሲጸልይ በወጣቷ ላይ ያደረው ሰይጣን ሕዝቡ እያዩት ከሆዷ በዘንዶ አምሳል ወጥቶ ሔደ:: ንጉሡ ስለተደረገለት ውለታ ለቅዱስ ዮሐንስ ወርቅና ብር ብዙ ሽልማትም አቀረበ:: አባቶቻችን እንዲህ ዓይነት ነገር አይወዱምና ቅዱሱ "እንቢ አልወስድም" አለ::

ቅዱስ ዮሐንስ "ልሒድ" ብሎ ሲነሳ ንጉሡ "አባቴ ወድጄሃለሁና አትሒድ" ብሎ የልብሱን ዘርፍ (ጫፍ) ያዘው:: በቅጽበት ግን ደመና መጥታ ነጥቃ ወሰደችው:: የቀሚሱ ቁራጭም በንጉሡ እጅ ላይ ቀረች:: እርሱም ቤተ ክርስቲያን አሳንጾ ያችን የተባረከች ጨርቅ በክብር አኑሯታል::

ቅዱስ ዮሐንስና ቅዱስ ስምዖን (ደቀ መዝሙሩ) ግን ከብዙ የተጋድሎ ዓመታት በኋላ ሌላ ክብር መጣላቸው:: "ክርስቶስን ካዱ: ለጣዖት ስገዱ" የሚል ንጉሥ በመነሳቱም ሒደው በጌታችን ስም መሰከሩ:: በገድል በተቀጠቀጠ ገላቸው ላይ ግርፋትን: እሳትን ታገሱ:: በዚህች ቀንም አንገታቸውን ተቆርጠው በሰማዕትነት ዐርፈዋል::

††† ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምልጃቸው ይማረን:: ከበረከታችቸውም ያድለን::

††† ሐምሌ 11 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አባ ዮሐንስ (ሰማዕት ወጻድቅ)
2.ቅዱስ ስምዖን (ደቀ መዝሙሩ)
3.አባ ኢሳይያስ ዘገዳመ አስቄጥስ
4.አባ ገብርኤል ሊቀ ጳጳሳት

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ያሬድ ካህን
2.ቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት
3.ብፁዐን ኢያቄም እና ሐና
4.አቡነ ሐራ ድንግል ጻድቅ
5.ማር ገላውዴዎስ ሰማዕት

††† "ሒዳችሁም መንግስተ ሰማያት ቀርባለች ብላችሁ ስበኩ:: ድውዮችን ፈውሱ: ሙታንን አንሱ: ለምጻሞችን አንጹ: አጋንንትን አውጡ:: በከንቱ ተቀብላችሁ በከንቱ ስጡ:: ወርቅ: ወይም ብር: ወይም ናስ በመቀነታችሁ: ወይም ለመንገድ ከረጢት: ወይም ሁለት እጀ ጠባብ: ወይም ጫማ: ወይም በትር: አታግኙ:: ለሠራተኛ ምግቡ ይገባዋልና::" †††
(ማቴ. ፲፥፯)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

https://t.me/kaletsidkzm
✞✞✞✝️ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ✝️ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✝️ሐምሌ ፲፪✝️

✞✞✞ እንኩዋን ለቅዱስ "ሚካኤል ሊቀ መላእክት"
የተአምር በዓልና ለሰማዕቱ "አባ ሖር" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

+*" ተአምረ ቅዱስ ሚካኤል "*+

=>ቅዱስ መጽሐፍ እንደ ነገረን በዚህች ዕለት የመላእክት
ሁሉ አለቃቸው: የቅዱሳንም ረዳታቸው የሆነው ደጉ
መልአክ #ቅዱስ_ሚካኤል ንጉሡን ሕዝቅያስን ግሩም
በሆነ ተአምር ከከተማው #ኢየሩሳሌም ጋር ታድጐታል::
ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-

+ከመድኃኒታችን #ክርስቶስ ልደት 700 ዓመታት በፊት
#ሕዝቅያስ የሚባል ንጉሥ በይሁዳ ላይ ነግሦ ነበር::
ደጋጉ #ዳዊትና #ሰሎሞን ካረፉ በሁዋላ የሕዝቅያስን
ያክል ቅን እና የእግዚአብሔር ሰው በእሥራኤል ላይ
አልነገሰም:: ንጉሡ ጣዖት አምልኮን ነቃቅሎ አጥፍቶ
ሕዝቡ እግዚአብሔርን ብቻ እንዲያመልክ አድርጐም
ነበር::

+ነገር ግን ቅዱስ ሕዝቅያስ በነገሠ በ14ኛው ዓመት
የአሕዛብ (የአሦር) ንጉሥ ሰናክሬም በጠላትነት ተነሳበት::
ወደ አካባቢውም መጥቶ: ከቦ አስጨነቀው:: ሰናክሬም
በጦር እጅግ ኃይለኛ ነበር:: በዚያውም ላይ ጦር የሚመዙ
ከ185,000 በላይ ብርቱ ተዋጊዎች ነበሩትና ሕዝቅያስ
እንደማይችለው ተረድቶ መልእክተኛ ላከበት::

+"እገብርልሃለሁ:: የፈለግከውንም እሰጥሃለሁ:: ሃገሬን
ግን አታጥፋ:: ኢየሩሳሌምን አታቃጥል:: ሕዝቤንም
አትግደል" በሚል ለመነው:: እጅ መንሻ ግብሩንም
ከከተማዋ የተገኘውን ወርቅና ብር ሁሉ ጭኖ ላከለት::

+ሰናክሬም ግን ሰይጣን ያደረበት ነውና የሕዝቅያስን
ልመና ወደ ጐን ብሎ የእሥራኤልን አምላክ : ቅዱስ
ስሙንም ተገዳደረ:: ለሕዝቅያስም "ከእኔ እጅ የሚያድንህ
ማነው? ሕዝቡንም #እግዚአብሔር ያድናል ብለህ
አታታልላቸው" ሲል ላከበት:: ቅዱስ ሕዝቅያስ በዚህ ጊዜ
የፈጣሪው ስም ሲቃለል ሰምቷልና ፈጽሞ አዘነ::

+መልእክተኞችን ወደ ነቢዩ #ቅዱስ_ኢሳይያስ ልኮ እርሱ
ወደ ቤተ መቅደስ ገባ:: በእግዚአብሔር ፊት ልብሱን
ቀድዶ ማቅ ለበሰ:: ስለ ኢየሩሳሌምና ሕዝቡም ፈጽሞ
አለቀሰ:: በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር የሰናክሬምን
መገዳደርና የሕዝቅያስን ልመና ሰምቷልና በኢሳይያስ
አንደበት እንዲሕ አለ:- "ስለ ባሪያየ ስለ #ዳዊት
ከተማዋን አድናታለሁ::"

+በዚያች ሌሊትም ድንቅ መልአክ #ቅዱስ_ሚካኤል
ከሰማያት በግርማ ወረደ:: ወደ ሰናክሬም የጦር ሠፈር
ደርሶ አንድ ጊዜ የእሳት ሰይፉን መዝዞ ቢያሳያቸው
ከአሕዛብ ሠራዊት 185 ሺ ኃያላን እንደ ቅጠል ረገፉ::
በለኪሶ የነበረው ሰናክሬም በጧት ቢነሳ ሠራዊቱ ሁሉ
ወደ አስከሬን ክምር ተቀይሯል::

+በድንጋጤ ወደ #ነነዌ ሒዶ ወደ ጣዖት ቤቱ ሲገባ የራሱ
ልጆች (አድራማሌክና ሳራሳር) ገደሉት:: ትዕቢተኛው
ሰናክሬም ለአሕዛብ ሁሉ መዘባበቻ ሆነ:: ቅዱስ ሕዝቅያስ
ግን በፈጣሪው ታምኗልና ቅዱስ ሚካኤል ሞገስ ሆኖ
የዓለም ነገሥታት ሁሉ ፈሩት:: (1ነገ. 18:13, 19:1)

+*" ቅዱስ አባ ሖር ሰማዕት "*+

=>ዳግመኛ በዚህ ቀን #አባ_ሖር ሰማዕቱ ይታሠባል::

+ቅዱሱ:-

¤ስርያቆስ በምትባል የግብጽ አውራጃ ተወልዶ ያደገ:
¤ገና በልጅነቱ መንኖ እግዚአብሔርን ያገለገለ:
¤ዘመነ ሰማዕታት በመጣ ጊዜም በመኮንኑ ፊት ቀርቦ
በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ያመነ:
¤ከመኮንኑም ብዙ ስቃይ የደረሰበት:
¤ብዙ ተአምራትን በመስራቱ ያሰቃየው የነበረውን መኮንን
ወደ ክርስትና መልሶ ለሰማዕትነት ያበቃ አባት ነው::

+እርሱም የሰማዕትነትን ክብር በእጅጉ ሽቷታልና ወደ ሌላ
ሃገር ሒዶ በዚህች ቀን አንገቱን ተሰይፎ የክብርን አክሊል
ተቀዳጅቷል:: በሐዋርያዊ አገልግሎቱ ያሳመናቸው 127
ወንዶችና 20 ሴቶችም አብረውት ተሰይፈዋል::

=>እግዚአብሔር በሊቀ መላእክት ክንፍ ሃገራችንን
ከአሕዛብ ስውር ጦር ይጠብቅልን:: ከሰማዕቱም በረከት
ያሳትፈን::

=>ሐምሌ 12 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ሕዝቅያስ ንጉሥ
2.ቅዱስ ኢሳይያስ ልዑለ ቃል
3.ቅዱስ አባ ሖር ሰማዕት
4."147" ሰማዕታት (የአባ ሖር ማሕበር)

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት
2.ቅዱስ ላሊበላ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮዽያ)
3.ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ
4.ቅዱስ ድሜጥሮስ
5.ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
6.ቅዱስ ቴዎድሮስ ምሥራቃዊ (ሰማዕት)
7.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
8.አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ

=>+"+ እግዚአብሔር ይላል:- ስለ እኔም ስለ ባሪያየም
#ስለ_ዳዊት ይህችን ከተማ አድናት ዘንድ እጋርዳታለሁ::
በዚያችም ሌሊት የእግዚአብሔር መልአክ ወጣ::
ከአሦራውያንም ሠፈር መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ገደለ::
ማለዳም በተነሱ ጊዜ እነሆ ሁሉ በድኖች ነበሩ:: +"+
(1ነገ. 19:34)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
"የጾሙ ዐዋጅ ለገዳማውያን ብቻ ነው"
 
ሐምሌ 22 ቀን የሚጀመረውን የገዳማውያን ጾምን አስመልክቶ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት የተሰጠ ማሳሰቢያ፤

አንዳንድ የቤተ ክርስቲያናችን አባላት እያቀረቡት ካለው የግንዛቤ ጥያቄ አንጻር ሐምሌ 5 ቀን 2016 ዓ.ም በቋሚ ሲኖዶስ የተሰጠውን መግለጫ በተመለከተ አጭር ማብራሪያ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።

በመሆኑም ከአንድነት ገዳማት ኅብረት በቀረበው ጥያቄ መሠረት ከላይ በተጠቀሰው ቀን የተሰጠው መግለጫ ከሐምሌ 22 እስከ ሐምሌ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ በሁሉም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት የሚፈጸመውን የምሕላ ጸሎት አስመልክቶ ከቋሚ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ በሚል ገላጭ ርዕስ በሁሉም የሀገራችን ክፍልና በሌሎችም አህጉራተ ዓለም ለሚገኙ ገዳማውያን ብቻ የታወጀ የምሕላ ሱባኤ መሆኑን
እየገለጽን በዚህ የሱባኤ ሳምንት ከቤተ ክርስቲያናችን አገልጋዮችና ምእመናን የሚጠበቀው ለገዳማውያኑ ጸጥታ ሲባል ወደ ገዳማት የምታደርጉት ጉዞ ለጊዜው እንዲቆይ ሆኖ እግዚአብሔር የገዳማውያኑን ጸሎት ሰምቶ ለሀገራችንና ለሕዝባችን ሰላምን፣ ፍቅርንና አንድነትን ይሰጥልን ዘንድ በያላችሁበት ቦታ ሆናችሁ በጸሎት ብቻ እንድትተጉ የቋሚ ሲኖዶስን ውሳኔ በማስታወስ አደራ እያልን የፈቃድ ጾም ግን  ለኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች የማይከለከል መሆኑን ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ታሳስባለች።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
         ቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት

©የኢኦተቤ ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ
††† እንኳን ለአባታችን ቅዱስ ብስንድዮስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ብስንድዮስ ጻድቅ †††

††† ቅዱስ ብስንድዮስ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ድንቅ ሥራ ከሠሩት እንደ አንዱ ሆኖ ይዘከራል:: ቅዱሱ ግብጻዊ ሲሆን በልጅነቱ ወደ ትምሕርት ቤት ገብቶ ቅዱሳት መጻሕፍትን ተምሯል:: የሚገርመው የብሉይም ሆነ የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍትን በሙሉ ያጠናቸው በቃሉ ነበር::

በእርግጥ ይሕንን ማድረግ የቻሉ በርካታ የሃገራችን ሊቃውንት ዘንድሮም አሉ:: ልዩነቱ ግን ወዲህ ነው:: ቅዱስ ብስንድዮስ መጻሕፍቱን ያጠናቸው ለሕይወት እንጂ ለእውቀት አልነበረምና ሁሌም ነግቶ እስከ ሚመሽ እያንዳንዱን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እያጣጣመ ይጸልይ ነበር:: ይሕንን ሲያደርግ ደግሞ
ባጭር ታጥቆ
ጫማውን አውልቆ:
በባዶ ሆዱ ቁሞ ነው::

ታዲያ እያንዳንዱን የመጽሐፍ ክፍል ሲጸልይ ነቢይ ቢሆን ሐዋርያ ወደ እርሱ ይወርድለት ነበር:: ለምሳሌ ዘፍጥረትን ሲጸልይ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ይመጣና ከፊቱ ተቀምጦ ይሰማዋል:: ትንቢተ ኢሳይያስ ላይ ሲደርስ ኢሳይያስ: ወንጌለ ማቴዎስ ላይ ሲደርስ ቅዱስ ማቴዎስ ይመጡና ደስ እያላቸው ያደምጡት ነበር::

አንዱ ነቢይ: ወይ ሐዋርያ ሲወጣ ቅዱስ ብስንድዮስን ባርኮ ሌላኛውን ተክቶ ነው:: በዚህ ምክንያት የቅዱሱ ሕይወት በምድር እያለ ሰማያዊ ሆነ: ሰማንያ አንዱን አሥራው መጻሕፍት የጻፉ ቅዱሳንን ለማየት በቃ:
በእጆቻቸውም ተባረከ::

የቅዱስ ብስንድዮስ ቀጣይ የሕይወቱ ተግባር ብሕትውና ሆነ:: ዓለምንና ግሳንግሷን ትቶም ወደ በርሃ መነነ:: በአጽንዖ በዓት:
በጾምና በጸሎት:
በትሕርምትም ተጋደለ:: በየደረሰበት ቦታ ሁሉ እግዚአብሔር በእጆቹ ድንቅ ተአምር ይሠራ ነበር:: ብዙ ድውያንን ፈወሰ: አጋንንትንም ከአካባቢው አሳደደ::

በእነዚህ ሁሉ ጊዜያት ግን ስዕለት ስላለበት ሴቶችን ላለማየት ይጠነቀቅ ነበር:: በሆድ ሕመም ትሰቃይ የነበረችና ጥሪቷን በመድኃኒት የጨረሰች አንዲት ሴት ስለ ቅዱሱ ዝና ትሰማለች:: ችግሩ ግን እርሱ ከውዳሴ ከንቱና ከሴት የሚርቅ ነውና እንዴት ብላ ታግኘው? አንድ ቀን ከበዓቱ አካባቢ ተደብቃ ውላ ሲመጣ የልብሶቹን ዘርፍ ለመንካት በእምነት አሰበች::

ልክ ከበዓቱ ሲዘልቅ ስሉጥ(ፈጣን) ነበርና ገና እንዳያት ሩጦ አመለጣት:: እንዳትከተለው ድውይ ናትና አልቻለችም:: አዝና ዝቅ ስትል ግን የረገጠውን ኮቲ ተመለከተች:: በፍጹም ልቧ: በእምነት "የጻድቁ አምላክ ማረኝ" ብላ ከአፈሩ ቆንጥራ በላች:: ደቂቃ አልቆየችም:: ፈጥና ከደዌዋ ዳነች:: እንደ እንቦሳ እየዘለለች ወደ ከተማ ሔዳ ተአምሩን ተናገረች::

ከእነዚህ ዘመናት በኋላ በእግዚአብሔር ፈቃድ ቅፍጥ(Qift) በምትባል ሃገር ጵጵስናን (እረኝነትን) ተሹሟል:: ወደ ከተማ ሲገባ የቀደመ ተጋድሎውን ቸል አላለም:: ይልቁኑ ይተጋ ነበር እንጂ:: ከብቃት መዓርግ ደርሷልና ሲቀድስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በገሃድ ያየው: ሠራዊተ መላእክትም ይከቡት ነበር::

ሕዝቡ ሊቆርቡ ሲመጡ የእያንዳንዱ ኃጢአት በግንባራቸው ተጽፎ ይታየው ነበር:: የበቁትን እያቀበለ: ያልበቁትን እየመከረና ንስሐ እየሰጠ ይመልሳቸዋል:: እንዲሕ በጽድቅ: በሐዋርያዊ አገልግሎትና በንጽሕና ተመላልሶ ቅዱስ ብስንድዮስ በዚህች ቀን ዐርፏል::

ቅዱስ ብስንድዮስ ካረፈ በኋላ ደቀ መዝሙሩ ከመግነዙ ጥቂት ቆርጦ አስቀርቶ ብዙ ድውያንን ፈውሶበታል::

††† ቸር አምላክ ለአባቶቻችን የሰጠውን ጸጋ ለእኛ ለባሮቹም አይንሳን:: ከቅዱሱ በረከትም ያድለን::

††† ሐምሌ 13 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ብስንድዮስ ሊቅ ወጻድቅ
2.ቅዱስ አሞን ሰማዕት (ዘሃገረ ጡህ)

††† ወርኀዊ በዓላት
1.እግዚአብሔር አብ
2.ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀ መላእክት
3.ዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት
4.ቅዱስ አስከናፍር
5.አሥራ ሦስቱ ግኁሳን አባቶች
6.ቅዱስ አርሳንዮስ ጠቢብ ገዳማዊ
7.አቡነ ዘርዐ ቡሩክ

††† "አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር:: ከማን እንደተማርኸው ታውቃለህና:: ከሕፃንነትህም ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳት መጻሕፍትን አውቀሃል:: የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጐ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምሕርትና ለተግሣጽ: ልብንም ለማቅናት: በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል::" †††
(፪ጢሞ. ፫፥፲፬)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
እንዴት ሰነበታችሁ የቃለ ጽድቅ አንባቢያን እግዚአብሔር ቢረዳን ዕለት ዕለት ከሚለቀቁ ስንክሳር ጥያቄ እንጠያየቃለን እንድናነብና ከዕለቱ ቅዱሳን በረከት እንድናገኝ: ጥያቄው ማታ ምንለቅ ይሆናል እስከዛው የዕለቱ ስንክሳር እናንብብ።📖📖
🙏🙏 በተጨማሪ ያላችሁን ማንኛውንም አስተያየት እንቀበላለን።
መልካም ቀን!!!
💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫
ሰላም  ለእናንተ ይሁን የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እነሆ

የምሽቱ ጥያቄ

1.መጽሐፍ ቅዱስ የጻፉትን ቅዱሳን ለማግኘት እና ለመባረክ የበቃው ቅዱስ አባት ማነው?
ሀ.ቅዱስ እለ እስክንድሮስ
ለ.ቅዱስ ቴዎፍሎስ
መ.ቅዱስ በስንድዮስ

2. 4 ዐይና ሚባሉት ብፁዓን አባቶች የሚያስመሠክሩት  መጻሕፍት ምን  ምንድናቸው ?
ሀ. መጽሐፈ ብሉያት
ለ.መጽሐፈ መነኮሳት
መ. መጽሐፈ ሀይማኖተ አበው

3.ቅዱስ በስንድዮስ በጳጳስነት የተሾመባት ሀገር ማን ትባላለች?
ሀ. ሶርያ
ለ.አርመን
ሐ.ቅፍጥ


መልስዎትን በ @Liyu7 
ይላኩልን


"ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤" |ዕብራውያን 10 : 24|
@kaletsidkzm
††† እንኳን ለሰማዕቱ ቅዱስ አብሮኮሮንዮስ እና ለመነኮሳት አለቃ ቅዱስ መቃርስ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ አብሮኮሮንዮስ ሰማዕት †††

††† ቅዱሱ ተወልዶ ያደገው በአንጾኪያ (ሶርያ) በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን አካባቢ ነው:: አባቱ ደግ ክርስቲያን የነበረ ሲሆን ስሙ #ክርስቶፎሮስ ይባላል:: "ለባሴ ክርስቶስ" እንደ ማለት ነው:: እናቱ ግን #ቴዎዳስያ የምትባል አረማዊት ነበረች:: ምንም እንኩዋ አባቱ ክርስቲያን ቢሆን እናቱ ኃይለኛ የቤተ መንግስት ሰው ስለነበረች በልጅነቱ አብሮኮሮንዮስ ክርስትናን ሊማር አልቻለም::

የልጁን አረማዊ መሆን ያልወደደ አባት አማራጩ አንድ ብቻ ነበር:: እሱም ወደ ጌታ መለመን ነበር:: በእንዲሕ ያለ ግብር ዘመናት ጐርፈው አብሮኮሮንዮስ ክርስቶስን ሳያውቅ 20 ዓመት ሆነው:: እናቱ ወስዳ: አሰልጥና ለጣዖት አምላኪ ንጉሥ ሰጠችው:: ንጉሡም የጦር አለቃ አድርጐ ሾመውና አንድ ትዕዛዝ ሰጠው:: "ክርስቲያኖችን ሁሉ ባገኘህበት ቦታ ጨፍጭፍ:: ቤታቸውንም አቃጥል::"

#አብሮኮሮንዮስ የታዘዘውን ሊፈጽም ሠራዊት አስከትሎ ሲወጣ ግን የአባቱ የ20 ዘመናት ለቅሶና ጸሎት ፍሬ አፈራ:: ገና መንገድ ላይ ሳለ ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና መድኃኒታችን #ኢየሱስ_ክርስቶስ ድምጹን ከሰማይ ላከለት:: "ወደ እውነተኛ መንገድ ተመለስ:: ካልሆነ ግን ሾተሉን ብትረግጥ ላንተ ይብስብሃል" አለው::

አብሮኮሮንዮስም እየተንቀጠቀጠ "አቤቱ አንተ ማነህ?" አለው:: ጌታም "ኢየሱስ ክርስቶስ ነኝ" ሲል መለሰለት:: ዳግመኛም "ምልክት ስጠኝ" ቢለው የብርሃን #መስቀል በሰማይ ላይ ገለጠለት:: ቅዱስ አብሮኮሮንዮስ ጊዜ አላጠፋም::

ሠራዊቱን ይዞ ወደ ንጉሡ ከተማ ተመልሶ ንጉሡን በድፍረት አለው:- "እኔ ክርስቲያን ነኝ:: ክርስቶስንም አመልካለሁ::" ካነጋገሩ የተነሳ አባቱን ደስ ሲለው ንጉሡና እናቱ ግን ደነገጡ:: ንጉሡ ሊያስፈራራው ሞከረ:: ግን አልተሳካለትም:: ከዚያማ ያሰቃየው ገባ::

አንድ ቀን አካሉ እስኪቆራረጥ ገረፉት:: በእሳትም አቃጠሉት:: ሞተ ብለው አስበው ነበር:: ወደ እርሱ ሲመለሱ ግን ጌታችን አድኖታልና የሰንበር ምልክት እንኩዋ በአካሉ ላይ አልተገኘም:: እናቱ #ቴዎዳስያ ከዚህ በላይ ምልክትን አልፈለገችም:: በደቂቃዎች ልዩነት እርሷም ወደ #ክርስትና ተመለሰች:: ልጇንም ቀድማ ሐምሌ 6 ቀን ሰማዕት ሆነች::

ቅዱስ አብሮኮርዮስን ግን ለበርካታ ጊዜያት አሰቃይተው ከክርስቶስ ፍቅር ሊለዩት ባለመቻላቸው በዚህች ቀን ገድለውታል:: አባት: እናትና ልጅ (ክርስቶፎሮስ: ቴዎዳስያና አብሮኮሮንዮስ) ለሰማያዊ ርስት በቅተዋል:: አባት ይሏቹሃል እንዲህ ነው!

††† ታላቁ ቅዱስ መቃርስ †††

††† በገዳማዊ ሕይወቱ እንደ ዘንባባ ያፈራው: የመነኮሳት ሁሉም አለቃቸው ቅዱስ መቃርስ አንድ ቀን እንዲህ አደረገ:-
አንድ በከተማ የሚኖር ባለ ጸጋ ስለ ቅዱስ መቃርስ ዝና ሰምቶ ሊባረክ ወደ ገዳመ አስቄጥስ ይመጣል:: አባ መቃርስ ባለ ጠጋው ወደ እርሱ እየመጣ መሆኑን ሲያውቅ በወንድሞች መነኮሳት መካከል ልብሱን ጥሎ እንደ አበደ ሰው አለል-ዘለል እያለ ይጫወት ጀመረ::

ያ ከተሜ ባለ ጠጋ እንደ ደረሰ ወደ መነኮሳቱ ጠጋ ብሎ "የታላቁን መቃርስ ዝና ሰምቼ ልባረክ ነበር የመጣሁት:: ከእናንተ መካከል ማንኛው ነው?" ቢላቸው "ያውልህ" ብለው አሳዩት:: ሲያየው እንደ እብድና ሕጻን እየዘለለ ይጫወታል:: ባለጠጋውም "ወይኔ! እኔኮ ደኅና ሰው መስሎኝ ነው:: በከንቱ ደከምኩ" ብሎ እያዘነ ሔደ:: ወዲያው መነኮሳት ተሰብስበው ቅዱስ መቃርስን "ለምን እንደዚህ አደረግህ?" ቢሉት "መጀመሪያ እንደ ሰውነቴ ሊያከብረኝ ይገባል" በሚል መልሷል:: በርግጥም ከምንም ነገር በፊት ሰውን በሰውነቱ (በእግዚአብሔር አርአያ በመፈጠሩ) ብቻ ልናከብር ይገባል::

††† ታላቁ ቅዱስ መቃርስ በቤተ ክርስቲያን ዛሬ በዓሉ ይከበራል::

††† ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምልጃቸው ይማረን:: ከበረከታችቸውም ያድለን::

††† ሐምሌ 14 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አብሮኮሮንዮስ ሰማዕት
2.ቅዱሳን ክርስቶፎሮስና ቴዎዳስያ (ወላጆቹ)
3.ታላቁ ቅዱስ መቃርስ (የመነኮሳት አለቃ)
4.ቅዱስ አሞንዮስ

††† ወርሐዊ በዓላት
1.አቡነ አረጋዊ (ዘሚካኤል)
2.ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ መርዓዊ
3.ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋርያ
4.ቅዱስ ሙሴ (የእግዚአብሔር ሰው)
5.አባ ስምዖን ገዳማዊ
6.አባ ዮሐንስ ጻድቅ
7.እናታችን ቅድስት ነሣሒት

††† "ለአገልግሎቱ ሾሞኝ ታማኝ አድርጐ ስለቆጠረኝ ኃይል የሰጠኝን ክርስቶስ ኢየሱስን #ጌታችንን አመሰግናለሁ:: አስቀድሞ ተሳዳቢና አሳዳጅ: አንገላችም ምንም ብሆን ይህን አደረገልኝ:: ነገር ግን ሳላውቅ ባለማመን ስላደረግሁት ምሕረትን አገኘሁ:: የጌታችንም ጸጋ #በክርስቶስ_ኢየሱስ ካሉ: ከእምነትና ከፍቅር ጋር አብልጦ በዛ::" †††
(1ጢሞ. 1:12)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
ቃለ ጽድቅ ዘመካነ ሕይወት | የመ/ሕ/ሰ/ት/ቤት ሰሌዳ መጽሔት ንዑስ ክፍል
💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫 ሰላም  ለእናንተ ይሁን የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እነሆ የምሽቱ ጥያቄ 1.መጽሐፍ ቅዱስ የጻፉትን ቅዱሳን ለማግኘት እና ለመባረክ የበቃው ቅዱስ አባት ማነው? ሀ.ቅዱስ እለ እስክንድሮስ ለ.ቅዱስ ቴዎፍሎስ መ.ቅዱስ በስንድዮስ 2. 4 ዐይና ሚባሉት ብፁዓን አባቶች የሚያስመሠክሩት  መጻሕፍት ምን  ምንድናቸው ? ሀ. መጽሐፈ ብሉያት ለ.መጽሐፈ መነኮሳት መ. መጽሐፈ ሀይማኖተ አበው…
💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫
ሰላም  ለእናንተ ይሁን የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እነሆ

የምሽቱ ጥያቄ መልስ

1.መጽሐፍ ቅዱስ የጻፉትን ቅዱሳን ለማግኘት እና ለመባረክ የበቃው ቅዱስ አባት ማነው?
ሀ.ቅዱስ እለ እስክንድሮስ
ለ.ቅዱስ ቴዎፍሎስ
መ.ቅዱስ በስንድዮስ

💡መልስ:-መ

2. 4 ዐይና ሚባሉት ብፁዓን አባቶች የሚያስመሠክሩት  መጻሕፍት ምን  ምንድናቸው ?
ሀ. መጽሐፈ ብሉያት
ለ.መጽሐፈ መነኮሳት
መ. መጽሐፈ ሀይማኖተ አበው

💡መልስ:-መ

3.ቅዱስ በስንድዮስ በጳጳስነት የተሾመባት ሀገር ማን ትባላለች?
ሀ. ሶርያ
ለ.አርመን
መ.ቅፍጥ

💡መልስ:-መ

ለመለሳችሁ ቃለህይወት ያሰማልን

"ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤" |ዕብራውያን 10 : 24|
@kaletsidkzm
እንዴት አመሻችሁ ውድ የቃለ ጽድቅ ቤተሰቦች የምሽቱ ጥያቄ እነሆ:-

፩, በዕለቱ ከሚታሰቡ ቅዱሳን አባቶች ፫ቱ ጥቀሱ።
፪, በገዳማዊ ሕይወቱ መልካም ያፈራ የመነኮሳት አለቃ ቅዱስ አባት ማን ይባላል?
፫, #ክርስቶፎሮስ የሚለው ቃል ትርጉም ምን ማለት ነው?
*በምንባቡ መሠረት ጥያቄዎችን እስከ ነገ ምሽት

መልስዎን @Liyu7 ላይ ይላኩ።


' አንተ ግን በተማርህበት እና በተረዳህበት ነገር ፀንተህ ኑር' [፪ኛ ጢሞ ፫÷፲፬]
@kaletsidkzm
††† እንኳን ለታላቁ ሊቅና አፈ በረከት ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ማሪ ኤፍሬም ሶርያዊ †††

††† እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ቅዱስ ኤፍሬም የተወለደው ንጽቢን በምትባል የሶርያ ግዛት ውስጥ በ298 / 306 ዓ/ም ነው:: ወላጆቹ በክርስቶስ የማያምኑ አላውያን ነበሩ:: (ምንም አንዳንድ ምንጮች ክርስቲያኖች ነበሩ ቢሉም)

ቅዱሱ ተወልዶ ባደገባት ንጽቢን ጵጵስናን የተሾመ ቅዱስ ያዕቆብ የሚባል ታላቅ ሰው ነበር:: የሰማዕትነት: የሐዋርያነት: የጻድቅነትና የሊቅነት ግብር ያለው አባት ነው:: ታዲያ ቅዱስ ኤፍሬም ይሔ አባት ሁሌ ሲያስተምር ይሰማው ነበርና በስብከቱ ተማርኮ ደቀ መዝሙሩ ለመሆን በቃ::

ቅዱስ ኤፍሬም በቅዱስ ያዕቆብ እጅ ከተጠመቀ በኋላ ሙሉ የወጣትነት ጊዜውን ያሳለፈው በትምሕርት ነው:: የሚገርመው መምሕሩ ቅዱስ ያዕቆብ ዘንጽቢን እመቤታችን ድንግል ማርያምን በፍጹም ልቡ የሚወድና ጠርቷት የማይጠግብ አባት ነውና ለልጁ ለቅዱስ ኤፍሬም ይሕንኑ አጥብቆ አስተምሮታል::

ቅዱስ ኤፍሬም ክርስትናን ሲመረምር የእመቤታችን ፍቅር ይበዛለት ጀመር:: ምክንያቱም እመ ብርሃንን ሳይወዱ ክርስትና የለምና:: እንደ እርሱ የሚወዳት የለም እስኪባል ድረስ ያገለግላት: ይገዛላትም ገባ::

እንዲህ እንደ ዛሬ የድንግል ማርያም ምስጋና በአንደበት እንጂ በመጽሐፍ አይገኝም ነበር:: እርሱ ግን ከወንጌለ ሉቃስ በስድስተኛው ወርን (ይዌድስዋን) እና ጸሎተ ማርያምን(ታዐብዮን) አውጥቶ በየዕለቱ በዕድሜዋ ልክ ስልሳ አራት ስልሳ አራት ጊዜ ያመሰግናት ነበር::

በእንዲህ ያለ ግብር እያለ አርዮስ በመካዱ እርሱን ለማውገዝና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ለማጽናት በ317 (325) ዓ.ም ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ሊቃውንት በኒቅያ ሲሰበሰቡ አንዱ መምሕረ ኤፍሬም ቅዱስ ያዕቆብ ነበር:: በዚህ ምክንያት ቅዱስ ኤፍሬም ከሊቃውንቱ ትምሕርትና በረከትን አግኝቷል::

ከጉባዔ መልስ መንገድ ላይ በራዕይ የብርሃን ምሰሶ አይቶ "ጌታ ሆይ! ምንድን ነው?" ብሎ ቢጠይቅ "ይሕማ ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስ ነው::" አለው:: እርሱም መምሕሩን ቅዱስ ያዕቆብን ተሰናብቶ ወደ ቅዱስ ባስልዮስ (ቂሣርያ) ወረደ:: ተገናኝተውም በአንድ ሌሊት ቋንቋ ተገልጦላቸው ሲጨዋወቱ አድረዋል::

በቦታው ብዙ ተአምራት ተደርጓል:: ቅዱስ ኤፍሬም ከታላቁ ባስልዮስ ከተማረ በኋላ ሃገረ ስብከት ተሰጥቶት ያስተምር ጀመር:: ሁል ጊዜ ታዲያ ጸሎቱ ይሔው ነበር:: "እመቤቴ ሆይ! ምስጋናሽ እንደ ሰማይ ከዋክብት: እንደ ባሕር አሽዋ በዝቶልኝ: እንደ እንጀራ ተመግቤው: እንደ ውኃ ጠጥቼው: እንደ ልብስም ተጐናጽፌው" እያለ ይመኝ ነበር::

አፍጣኒተ ረድኤት: ፈጻሚተ ፈቃድ እመ ብርሃንም በገሃድ ተገልጻ የልቡን ፈቃድ ፈጸመችለት:: ዛሬ ጸጋ በረከት የምናገኝበትን ውዳሴ ማርያምን ደረሰላት:: ሲደርስላትም እርሷ አእላፍ መላእክትን: ጻድቃን ሰማዕታትን አስከትላ ወርዳ: በፊቱም ተቀምጣ ሲሆን እርሱ ደግሞ ባጭር ታጥቆ: በፊቷ ቆሞ: በመንፈስ ቅዱስም ተቃኝቶ ነው::

ውዳሴዋን በሰባት ቀናት ከደረሰላት በኋላ በብርሃን መስቀል ባርካው: ሊቀ ሊቃውንትም እንዲሆን ምሥጢር ገልጣለት ዐረገች:: ከዚህ በኋላ በምሥጢር ባሕር ውስጥ ዋኝቶ አሥራ አራት ሺህ ድርሰቶችንም ደርሷል:: ዛሬ ሶርያ ውስጥ የምንሰማውን ዜማም የደረሰው ይህ ቅዱስ ነው::

እንዲያውም አንድ ቀን የምሥጢር ማዕበል ቢያማታው "አሃዝ እግዚኦ መዋግደ ጸጋከ" ብሎ ጸልዩዋል:: (የጸጋህን ማዕበል ያዝልኝ) እንደ ማለት ነው:: ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ በመጨረሻ ሕይወቱ ተክሪት በምትባል ሃገር ኤጲስ ቆጶስ ሆኖ ተሹሟል::

በጣፋጭ ስብከቱ ብዙዎችን ካለማመን መልሷል:: የምዕመናንንም ሕይወት አጣፍጧል:: ለመናፍቃንና ለአርዮሳውያን ግን የማይጋፉት ግድግዳ ሆኖባቸው ኑሯል:: በዘመኑም ብዙ ተጋድሎ አፍርቷል:: ተአምራትንም ሠርቷል:: በተወለደ በስልሳ ሰባት ዓመቱ በ365 (373) ዓ.ም ዐርፎ ተቀብሯል::

††† ቅዱሱ ለሶርያ ብቻ ሳይሆን እመቤታችንን ለምንወድ የዓለም ክርስቲያኖች ሁሉ ሞገሳችን ሆኗል:: ስለዚህም እንዲህ እያልን እንጠራዋለን:-
1.ቅዱስ ኤፍሬም
2.ማሪ ኤፍሬም
3.አፈ በረከት ኤፍሬም
4.ሊቀ ሊቃውንት ኤፍሬም
5.ጥዑመ ልሳን ኤፍሬም
6.አበ ምዕመናን ኤፍሬም
7.ርቱዐ ሃይማኖት ኤፍሬም . . . አባታችን አንተ ነህ::

††† ጽንዕት በድንግልና: ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ለቅዱስ ኤፍሬም የሰጠሽውን ጸጋውን: ክብሩን: አእምሮውን: ለብዎውን በልቡናችን ሳይብን: አሳድሪብን . . . አሜን::

††† ጴጥሮስ ወጳውሎስ †††

††† ዳግመኛ በዚህ ቀን ብርሃናተ ዓለም ጴጥሮስ ወጳውሎስ ይታሠባሉ::

ቅዱሳኑ ሶርያ አካባቢ ውስጥ ወደምትገኝ አንዲት ሃገር ገብተው ሕዝቡን ከንጉሣቸው ጰራግሞስ ጋር አሳምነው አጥምቀዋል:: ነገር ግን እነርሱ ሲወጡ ሰይጣን አስቶት አጥፊ ሰው ወደ መሆን ተመልሶ ንጉሡ ሐዋርያትን አሰቃይቷቸዋል::

ስለ ቅዱሳኑ ግን ፈረሶቹ ሰግደው: በሰው አንደበት ቅድስናቸውን መስክረዋል:: በመጨረሻም ንጉሡን ከነ ሕዝቡና ሠራዊቱ በዓየር ላይ ሰቅለው ንስሐ ሰጥተውታል:: በእነዚህ ተአምራትም ሁሉም አምነው ለከተማዋና ለሕዝቡ ድኅነት ተደርጓል::

††† ከአባቶቻችን አበው ሐዋርያት በረከት ይክፈለን::

††† ሐምሌ 15 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ማሪ ኤፍሬም ሶርያዊ (አፈ በረከት)
2.ብርሃናተ ዓለም ቅዱሳን ሐዋርያት ጴጥሮስ ወጳውሎስ
3.አባ ሓርዮንና ደቀ መዛሙርቱ (ሰማዕታት)
4.አባ ፍሬምናጦስ መስተጋድል

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ኢየሉጣ
2.ቅዱስ ሚናስ (ማር ሚና) ሰማዕት
3.ቅድስት እንባ መሪና
4.ቅድስት ክርስጢና

††† "ለምኑ ይሰጣችሁማል:: ፈልጉ ታገኙማላችሁ:: መዝጊያ አንኳኩ ይከፈትላችሁማል:: የሚለምነው ሁሉ ይቀበላልና:: የሚፈልገውም ያገኛል:: መዝጊያንም ለሚያንኳኳ ይከፈትለታል::" †††
(ማቴ. ፯፥፯)

††† "የጻድቅ አፍ ጥበብን ያስተምራል::
አንደበቱም ፍርድን ይናገራል::
የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው::
በእርምጃውም አይሰናከልም::" †††
(መዝ. ፴፯፥፴)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

https://t.me/kaletsidkzm
††† እንኳን ለቅዱስ አባ ዮሐንስ ወንጌሉ ዘወርቅ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ዮሐንስ ጻድቅ (ወንጌሉ ዘወርቅ) †††

††† ቅዱሱ "ወንጌሉ ዘወርቅ" እየተባለ የሚጠራው ከሌሎች ዮሐንስ ከሚባሉ ቅዱሳን ለመለየት ቢሆንም ዋናው ምክንያት ግን እድሜ ልኩን የሚያነበው: ከእጁ የማይለየውና አቅፎት የሚተኛ በወርቅ የተለበጠ ወንጌል ስለ ነበረው ነው::

የቅዱስ ዮሐንስ ታሪኩ ከመርዓዊ (ሙሽራው) ገብረ ክርስቶስ እና ከቅዱስ ሙሴ ሮማዊ ጋር ተመሳሳይነት አለው::
ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
በሮም ግዛት ሥር የሚኖሩ አጥራብዮስና ብዱራ የሚባሉ ደጋግ ክርስቲያኖች ነበሩ:: እግዚአብሔር በቀደሰው ትዳር የሚኖሩና ነዳያንን የሚዘከሩ ነበሩና ይህንን ቅዱስ ወለዱ:: ስሙን ዮሐንስ ብለው: እንደሚገባም አሳድገው: ምሥጢረ መንግስተ ሰማያትን እንዲረዳ ለመምህር ሰጡት:: ቅዱስ ዮሐንስ ከመምህሩ ዘንድ ቁጭ ብሎ መጻሕፍተ ቤተ ክርስቲያንን ተማረ::

ለወላጆቹ ቅንና ታዛዥ ነበርና አባቱ "ልጄ! የምትፈልገውን ጠይቀኝ:: ምን ላደርግልህ ትወዳለህ?" አለው:: ቅዱስ ዮሐንስ ዘንድሮ እኛን የሚያምረን ሁሉ አላሰኘውም:: አባቱን "ቅዱስ ወንጌልን ግዛልኝ: በወርቅም አስለብጠው" አለው:: አባትም የተባለውን ፈጸመ::

ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ከዚህ ዓለም ተለይቶ እስካረፈባት ቀን ድረስ ቅዱስ ዮሐንስና የወርቅ ወንጌሉ ተለያይተው አያውቁም:: ሁሌም ያለመታከት ያነበዋል:: ሲቀመጥም ሲነሳም: ሲሔድም ሲተኛም አብሮት ነበር::

ቅዱስ ዮሐንስ ወጣት በሆነ ጊዜ ወላጆቹ ይድሩት ዘንድ ተዘጋጁ:: ልብሰ መርዐም (የሙሽራ ልብስ) አዘጋጁ:: በዚያው ሰሞን ግን አንድ እንግዳ መነኮስ ወደ ቤታቸው መጥቶ ያድራል:: በዚያች ሌሊት መነኮሱ በጨዋታ መካከል ስለ ቅዱሳን መነኮሳት ተጋድሎና ክብር ነገረው:: የሰማው ነገር ልቡናውን የማረከው ቅዱስ ዮሐንስ ከዚያች ቀን ጀምሮ ወደ ፈጣሪው ይለምን ነበር::

አንድ ቀን ግን ያ መነኮስ በድጋሚ መጥቶ አደረ:: ቅዱስ ዮሐንስ መነኮሱን ወደ ገዳም እንዲወስደው ቢጠይቀው "አይሆንም: አባትህ ያዝንብኛል" አለው:: ቅዱሱ ግን "በእግዚአብሔር ስም አማጽኜሃለሁ" ስላለው ሁለቱም በሌሊት ወጥተው ወደ ገዳም ሔዱ::

አበ ምኔቱ "ልጄ! የበርሃውን መከራ አትችለውም: ይቅርብህ" ቢለውም "አባቴ! አይድከሙ:: ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር አይለየኝም::'' ስላላቸው እንደሚገባ ፈትነው አመንኩሰውታል:: ቅዱስ ዮሐንስ ከመነኮሰ በኋላ በጾም: በጸሎት: በስግደትና በትሕርምት ያሳየው ተጋድሎ በርካቶችን አስደነቀ::

ለሥጋው ቦታ አልሰጣትምና በወጣትነቱ አካሉ ረገፈ:: ቆዳውና አካሉም ተገናኘ:: ሥጋውን አድርቆ ነፍሱን አለመለማት:: በእንዲሕ ያለ ሕይወት ለሰባት ዓመታት ከተጋደለ በኋላ በራዕይ "ወደ ወላጆችህ ተመለስ" እያለ ሦስት ጊዜ አናገረው::
ቅዱስ ዮሐንስ ወደ አበ ምኔቱ ሒዶ ቢጠይቀው "ራዕዩ ከእግዚአብሔር ነው" ብሎ ወደ ቤተሰቦቹ አሰናበተው::

ቅዱስ ዮሐንስ በላዩ ላይ የነበረችውን ልብስ በመንገድ ለነዳይ ሰጥቶ: በፈንታው ቆሻሻ ጨርቅ ለብሶ ከወላጆቹ በር ላይ ለመነ:: "እባካችሁ አስጠጉኝ" አላቸው:: ወላጆቹ በጭራሽ ሊለዩት አልቻሉም:: ነገር ግን አሳዝኗቸዋልና በበራቸው አካባቢ ትንሽ ቤት ሠሩለት::

በዚያች በዓት ውስጥ እንዳስለመደ በትጋት ለሰባት ዓመታት ተጋደለ:: በእነዚህ ዓመታት እንኳን ሌላው ሰው ወላጆቹም ቢሆኑ ፍርፋሪ ከመስጠት በቀር አይቀርቡትም ነበር:: ምክንያቱ ደግሞ "ይሸተናል" የሚል ነበር:: በመጨረሻም መልአከ እግዚአብሔር ከሰማይ ወርዶ "ከሰባት ቀናት በኋላ ታርፋለህ" አለው::

እናቱን ጠርቶ "አንድ ነገር ልለምንሽ" አላት:: "እሺ" አለችው:: "ከሞትኩ በኋላ በለበስኳት ጨርቅ እንድትገንዙኝ: በበዓቴ ውስጥም እንድትቀብሩኝ" አላትና የወርቅ ወንጌሉን አውጥቶ ሰጣት:: ያን ጊዜ አባቱም ደርሶ ነበርና ደነገጡ::

የወርቅ ወንጌሉን ለዩት:: ልጃቸውን ግን መለየት አልቻሉምና እያለቀሱ ስለ ልጃቸው የሚያውቀው ካለ እንዲነግራቸው ለመኑት:: እርሱም "ልጃችሁ ዮሐንስ እኔ ነኝ" አላቸው::

በዚያ ቅጽበት ወላጆቹ የሰሙትን ማመን አልቻሉም:: በፍጹም ዋይታ እየጮሁ አለቀሱ:: ለቅሷቸውን የሰሙ ሁሉ ተሰበሰቡ:: ለሰባት ቀናት እኩሉ እያለቀሰ: እኩሉ እየተባረከ በዓቱን ከበው ሰነበቱ:: በሰባተኛው ቀን መልአኩ መጥቶ በክብር ነፍሱን ተቀበለ::

እናቱ የልጇን አደራ ረስታ (እሷስ መልካም አደረግሁ ብላ ነው) ለሠርጉ ባዘጋጀችው የወርቅ ልብስ ገነዘችው:: ወዲያው ግን በጽኑ ታመመች:: አባት ግን ፈጠን ብሎ በዚያች ጨርቅ ገንዞ በበዓቱ ውስጥ ቀበረው:: ያን ጊዜ እናት ፈጥና ዳነች:: ከቅዱሱ መቃብርም ብዙ ተአምራትና ፈውስ ተደርጓል::

††† ቸሩ አምላካችን ከቅዱስ ዮሐንስ ወንጌሉ ዘወርቅ ጸጋ በረከትን ይክፈለን::

††† ሐምሌ 16 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አባ ዮሐንስ ጻድቅ (ወንጌሉ ዘወርቅ)

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ኪዳነ ምሕረት (የሰባቱ ኪዳናት ማሕተም)
2.ቅድስት ኤልሳቤጥ (የመጥምቁ ዮሐንስ እናት)
3.ቅዱስ ገብረ ማርያም ጻድቅ ንጉሠ ኢትዮጵያ (የቅዱስ ላሊበላ ወንድም)
4.ቅዱስ አኖሬዎስ ንጉሥ ጻድቅ
5.አባ አቡናፍር ገዳማዊ
6.አባ ዳንኤል ጻድቅ

††† "እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ: የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ: በሰላም ወንጌልም በመዘጋጀት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ:: በሁሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሱ:: የመዳንንም ራስ ቁር: የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ:: እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው:: በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ:: በዚህም አሳብ ስለ ቅዱሳን ሁሉ እየለመናችሁ በመጽናት ሁሉ ትጉ::" †††
(ኤፌ. ፮፥፲፬)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
ነገር ግን እነዚያን በላያቸው ልነግሥ ያልወደዱትን ጠላቶቼን ወደዚህ አምጡአቸው በፊቴም እረዱአቸው።" (ሉቃ.19:27) ምን ማለት ነው? 1፣ቃሉ እንዴት ባለ አገባብ ነው የተነገረው?

ታሪኩ የሰፈረበት ምንባብ እንደሚያስረዳው ጌታችን አስቀድሞ የጠፋውን ሊፈልግ ሊያድንም እንደመጣ በቃል አስተምሮ ሲያበቃ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት በምሳሌ ሲያስረዳ ከላይ ያነሳነው ቃል ገልጿል:: እንግዲህ አስተውሉ፡፡ አንደኛ ታሪኩ በምሳሌ የተነገረ ነው፡፡ ያም ብቻ ደግሞ አይደለም፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ለራሱም መንግሥት ይዞ ሊመለስ የሔደው መኮንን በመጣ ጊዜ የተናገረው መሆኑም ተቀምጧል፡፡ ስለዚህ እንዴትና መቼ ተነገረ የሚለውን በግልጽ ተቀምጧል:: ተመልከቱ ይህን በምሳሌ የተነገረ ቃል ነውና "ምሳሌንና ትርጓሜን የጠቢባን ቃልና የተሸሸገውን ነገር ለማስተዋል" ምን ያስፈልጋል ካልን ጠቢቡ ሰሎሞን መንፈሳዊ ዓይን ፈሪሃ እግዚአብሔርን ገንዘብ ማድረግ ይጠይቃል ይለናል (ምሳ.1:6-7)፡፡ ስለዚህ ቃል በቃል እንደወረደ አይፈታም:: ለነገሩ በምሳሌ የተነገረበት አንዱ አቢይ ምክንያት የማይረዱትንና ያለአገባቡም የሚተረጉሙትን ለመዝለፍ ነው:: ጌታችን ራሱ በምሳሌም ለምን እንደሚያስተምር ሲጠየቅ "እንዲህም አላቸው፦ ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ በውጭላሉትግን፥ አይተው እንዲያዩ እንዳይመለከቱም፥ ሰምተውም እንዲሰሙ እንዳያስተውሉም፥እንዳይመለሱ ኃጢአታቸውም እንዳይሰረይላቸው ነገር ሁሉ በምሳሌ ይሆንባቸዋል።" (ማር. 4:11-12) ይላል:: ስለዚህ ክርስትናችንን አይተው ለማይመለከቱ ሰምተውም ለማያስተሉ መፋረጃ ሲሆንባቸው ይኖራል:: በመንፈሳዊ መነጽር ይህንን መረዳት ለሚሻ ግን የምሳሌው ፍቺ የሚያሳየን በኀልቀተዓለም እውነተኛው ዳኛ ለፍርድ ሲመለስ የሚሰጠውን ፍትህ ነው:: ስለዚህ በዚህ የአምላካችን ትምህርት አንደኛ የተነገረበት መንገድ በምሳሌ እንጂ በቁሙ የተነገረ አለ መሆኑንና ሁለተኛ ደግሞ መቼ እንደሚፈጸም ስንመለከት ስለ ፍጻሜ ፍርድ እንጂ አሁን ስላለ ድርጊትም የሚያስረዳ አለመሆኑን ማጤን ይገባል::

2. እረዱ የተባሉትስ እነማን ናቸው?

በምሳሌ በተቀመጠልን ታሪክ ላይ እንደምንረዳው ያልታመነውን እንዲቀጡ ወይም "እንዲያርዱ" የታዘዙት "በዚያም ቆመው የነበሩትን" እያለ የጠቀሳቸውን ነው:: እነዚህም ቀድሞ ለምልጃ የቆሙ ኋላ በፍርድ ቀን ግን ፈቃዱን የሚፈጽሙ ቅዱሳን መላእክት ናቸው:: እነዚህን በሌላ ቦታ የፍርድ ቀን አጫጆች ይላቸዋል፡፡ "እንክርዳዱም የክፉው ልጆች ናቸው፥ የዘራውም ጠላት ዲያብሎስ ነው፤መከሩም የዓለም መጨረሻ ነው፥ አጫጆችም መላእክት ናቸው።" (ማቴ. 13:39) ስለዚህም ፍሬን ከገለባ ስንዴን ከእንክርዳድ ምርቱንም ከግርድ ሊለዩ ታዘው የሚላኩ መሆናቸውን መረዳት ይገባል:: እንዲሁም ደግሞ በሌላ ምሳሌ ወደ እሳት የሚጥሉ የሚያቃጥሉም ተብለው ተገልጸዋል "በእኔ የማይኖር ቢሆን እንደ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ ይጣላል ይደርቅማል፤ እነርሱንም ሰብስበው ወደ እሳት ይጥሉአቸዋል፥ ያቃጥሉአቸውማል።" (ዮሐ.15:6 ) እንዲል:: ስለዚህ በዓለም መጨረሻ ተልከው ያልታመነውን በምሳሌ እንደተቀመጠው የሚያርዱ የሚያቃጥሉና ከእሳት የሚጥሉ እነዚህ ቅዱሳን መላእክት ናቸው::

3. ማረድምንድርነው?

ሁላችን እንደምንረዳው እርድ የሚፈጸመው በሰይፍ በጎራዴ አልያም ይህን በመሰለው የስለት መሣርያነው:: ቅዱስ መጽሐፋችን ግን ደጋግሞ የሚነግረን በመጨረሻው ዕለት ቅን ፍርድ እንጂ የሰይፍ እርድ እንደሌለ ነው:: እንግዲህ የምሳሌውን ፍቺና የምስጢሩን አገባብ ማጤን ስለሚገባ በቁሙ ደም ማፍሰስ እንደሚኖር መጠበቅ የለብንም:: ስለዚህ በመጨረሻው ቀን የሚፈጸመውን ፍርድ በእሳት መቃጠል በሰይፍ መታረድ ነው ሲል በጽድቅ ያለ ፈታሂነቱን ርቱዕ የሆነ ኩነኔውን መግለጹ ነው:: ለዚህም ነው መጽሐፍ ይህን የፍትህ መንገድ የእሳትና የሰይፍ ብሎ የሚጠራው "እግዚአብሔርም በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ በእሳትና በሰይፉ ይፈርዳል" እንዲል (ኢሳ. 66:16)::
ሰይፍ ነፍስን ከሥጋ እንዲለይ ጻድቃንን ወደኔ ኑ ኃጥዓንን ከኔ ራቁ ብሎ በአፉ ሰይፍ እውነተኛው ዳኛ ይለያቸዋልና የአፉን ፍርድ ሰይፍ ይለዋል "እንግዲህ ንስሐ ግባ፤ አለዚያ ፈጥኜ እመጣብሃለሁ፥ በአፌም ሰይፍ እዋጋቸዋለሁ።"(ራእ.2:16)፡፡ በሌላም ሥፍራ "እኔ የተናገርሁት ቃል እርሱ በመጨረሻው ቀን ይፈርድበታል።" (ዮሐ. 12:48) ይላልና ቃሉም ሰይፍ እየተባለ ተጠርቷል፡፡ ለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ "የመዳንንም ራስ ቁር የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው።" (ኤፌ. 6:17) ይለናል:: መልሶም "የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፥ የሚሠራም፥ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፥ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፥" (ዕብ. 4:12)፡፡ እንግዲህ ልብ አድርጉ፡፡ እኛ በምንረዳው ስሜት ፍርዱን መመርመር ፈጽሞ አይገባም፡፡ ጥንቱን "ፍርዱ እንዴት የማይመረመር ነው፥" መባሉ ቅሉ ለዚህ ነውና (ሮሜ. 11:33):: አስተውሉ ደካሞች በሚሰሩት ድፍረትና በሚናገሩት ስህተት ሳይጸጸቱ በጥጋብ አውታሯ እንደበጠሰች በቅሎ ፋነው ከገደል እንዳይገቡ "ነገር ግን እነዚያን በላያቸው ልነግሥ ያልወደዱትን ጠላቶቼን ወደዚህ አምጡአቸው በፊቴም እረዱአቸው።" መባሉ ስለምን እንደሆነ እርሱ በረዳን መጠን ፈትተን አይተናል::