ቃለ ጽድቅ ዘመካነ ሕይወት | የመ/ሕ/ሰ/ት/ቤት ሰሌዳ መጽሔት ንዑስ ክፍል
1.02K subscribers
2.68K photos
44 videos
102 files
757 links
ይኽ የፈረንሳይ መካነ ሕይወት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያን መካነ ሕይወት ሰ/ት/ቤት ሰሌዳ መጽሔት ቻናል ነው። በዚኽ ቻናል በመንፈሳዊ ሕይወትዎ የሚበረቱባቸውን መንፈሳዊ ጽሑፎችና መልእክቶች ባሉበት ሆነው መከታተል ይችላሉ።
Download Telegram
=>+"+ እንኩዋን ለአጋእዝተ ዓለም #ሥላሴ እና ለቅዱሳን
አበው #አብርሃም: #አባ_ሲኖዳ እና #አባ_ጊዮርጊስ_ዘጋሥጫ
ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ +"+

+"+ #ሥሉስ_ቅዱስ +"+

=>በአንድነቱ ምንታዌ (ሁለትነት): በሦስትነቱ ርባዔ (አራትነት)
የሌለበት የዘለዓለም አምላክ: የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ
#እግዚአብሔር ነው:: #አብ : #ወልድ : #መንፈስ_ቅዱስ
በስም: በአካል: በግብር ሦስትነት: በባሕርይ: በሕልውናና
በፈቃድ አንድነት የጸኑ ናቸው:: በዚህ ጊዜ ተገኙ: በዚህ ጊዜ
ያልፋሉ አይባሉም:: መጀመሪያም መጨረሻም እነርሱ ናቸውና::

+ርሕሩሐን ናቸውና በእናት ሥርዓት " #ቅድስት_ሥላሴ "
እንላቸዋለን:: የሚጠላቸው (የማያምንባቸውን) አይጠሉም::
የሚወዳቸውን ግን እጽፍ ድርብ ይወዱታል:: በቤቱም መጥተው
ያድራሉ::

+ከፍጥረታት ወገን ከእመቤታችን ቀጥሎ የአብርሃምን ያህል
በሥላሴ ዘንድ የተወደደ ፍጡር የለም:: አባታችን
#ቅዱስ_አብርሃም የደግነት ሁሉ አባት ነውና በኬብሮን
በመምሬ ዛፍ ሥር ሥላሴን ተቀብሎ አስተናግዷል:: ሥላሴ
አኀዜ ዓለም (ዓለምን በእጁ የያዘ) ነው:: ነገር ግን በፍቅር
ለሚሻው በፍቅር ይመጣል::

+አባታችን አብርሃም በ99 ዓመቱ: እናታችን ሣራ በ89 ዓመቷ
ሥላሴን በድንኩዋናቸው አስተናገዱ:: አብርሃም እግራቸውን
አጠበ:: (ወይ መታደል!) በጀርባውም አዘላቸው:: (ድንቅ አባት!)
ምሳቸውንም አቀረበላቸው:: እንደሚበሉ ሆኑለት:: በዚያው
ዕለትም የይስሐቅን መወለድ አበሠሩት:: #ቅድስት_ሣራ ሳቀች::
እንደ ዘንድሮ ወገኖቻችን የማሾፍ አይደለም:: ደስታና ጉጉት
የፈጠረው እንጂ:: ሥላሴ "ምንት አስሐቃ ለሣራ በባሕቲታ"
ብለው ነበርና በዚህም ምክንያት ነው " #ይስሐቅ" የተባለው::

+ሥላሴን ያስተናገደች ድንኩዋን (ሐይመት) የድንግል
እመቤታችን ማርያም ምሳሌ ናት:: በድንግል ላይ #አብ
ለአጽንኦ: #መንፈስ_ቅዱስ ለአንጽሖ: #ወልድ በተለየ አካሉ
ለሥጋዌ በእርሷ ላይ አርፈዋል / አድረዋልና::

+"+ #ታላቁ_አባ_ሲኖዳ +"+

=>የባሕታውን ሁሉ አለቃቸው ታላቁ ቅዱስ ሲኖዳ:-
¤በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን የተወለደ
¤በእናቱ ማሕጸን ሳለ መላእክት በሰይፈ እሳት ይጠብቁት የነበረ
¤የታላቅነት ትንቢት የተነገረለት
¤ገና ሳይወለድ ሥውራን አበው የሰገዱለት
¤በሕጻን ሰውነቱ ጾምና ጸሎትን የጀመረ
¤የልጅነት ቁርስና ምሳውን ለነዳያን ያካፍል የነበረ
¤በ9 ዓመቱ ወደ በርሃ የመነነ
¤የአባ አብጐል ደቀ መዝሙር የሆነ አባት ነው::

+ሲመነኩስም በእግዚአብሔር ትእዛዝ #የሠለስቱ_ደቂቅ
አስኬማ: #የኤልያስ ቆብዕ እና የመጥምቁ #ዮሐንስ ቅናትን
(መታጠቂያ) ከያሉበት መላእክት አምጥተውለት የመነኮሰ
¤ዓለምን በሙሉ በጸሎቱ ይጠብቅ የነበረ
¤የግብፅን በርሃ በብርሃን የሞላ
¤በርካታ ድርሰቶችን የደረሰ
¤ያለ ማቇረጥ በየቀኑ ከ100 ዓመታት በላይ ከጌታችን ክርስቶስ
ጋር የተነጋገረ
¤ደመናትን ተጭኖ ይሔድ የነበረና
¤ያለ ዕረፍት ለ111 ዓመታት ከ2 ወራት ፈጣሪውን ያገለገለ
አባት ነው::

+በዚህም ምክንያት አንድ ቀን ገዳማውያን ሁሉ እየሰሙ
እንዲህ የሚል ቃል ከሰማይ መጣ:: "ሲኖዳ ተሠይመ
#አርሲመትሪዳ " (ሲኖዳ አርሲመትሪዳ ሆኗል:: ማለትም
ለባሕታውያን ሁሉ አለቃ ሁኖ ተመርጧል ማለት ነው:: )

+ቅዱሱ የጌታችንን እግር እያጠበም ይጠጣ ነበር::
+በዚህች ዕለት በ120 ዓመቱ ጌታችን ወርዶ ሲያሳርገው
#አቡነ_ኪሮስ "ታላቅ ምሰሶ (ታላቅ ዛፍ) ወደቀ" ብለው
አልቅሰዋል:: #ሲኖዳ ማለት "ደግ ሰው" ማለት ነው::

+"+ #አባ_ጊዮርጊስ_ዘጋስጫ ( #GIYORGIS_OF_SEGLA )
+"+

=>ታላቁ ኢትዮዽያዊ ሊቅና ጻድቅ የተወለደው ወሎ #ጋስጫ
ውስጥ በ1358 ዓ/ም ነው:: ከልጅነቱ ትምሕርት አልገባሕ
ቢለውም በልቡናው ግን ቅን እና ታዛዥ ነበር:: መምሕሩ
"ትምሕርት አይገባውምና ውሰዱት" ቢላቸው "የእግዚአብሔር
ነውና ያገልግላችሁ" ብለው መለሱት:: መገፋቱን የተመለከተ
#አባ_ጊዮርጊስ #እመቤታታችንን ከልቡ ይወዳት ነበረና
ይማጸናት ገባ::

+ቀን ቀን ገዳሙን ሲረዳ: እሕል ሲፈጭና ሲከካ: ላቡንም
ሲያፈስ ውሎ ሌሊት ደግሞ ሲጸልይ ያነጋ ነበር:: ድንግል
እመቤታችን ጸሎቱን ሰምታለችና #ቅዱስ_ዑራኤልን አስከትላ
መጣችለት:: በንጹሐት እጆቿ ባርካው ምሥጢርንም ነገረችው::
"ወነገረቶ ሐምስተ ቃላተ" እንዲል:: ጽዋዐ ልቡናን አጠጥታው
ተሠወረችው::

+ከዚህች ሰዓት ጀምሮ አባ ጊዮርጊስ ፍጹም ተለወጠ:: በጽድቁ
ላይ የሊቅነትን ካባ ደረበ:: ቅዱሳት መጻሕፍትን ይተነትናቸው:
መናፍቃንንም ምላሽ ያሳጣቸው ገባ:: የተረጐማቸውና
ያተታቸውን ሳይጨምር 41 ድርሰቶችን ደረሰ:: (መጽሐፈ
ሰዓታት: መጽሐፈ ምሥጢር: አርጋኖን: ኆኅተ ብርሃን: ውዳሴ
መስቀል: ወዘተ . . . የእርሱ ድርሰቶች ነበሩ)

+ስለ ሃይማኖትም ጠበቃ ነበር:: ስለ ቅድስናውና ውለታው የኢ/
ኦ/ተ/ቤ እንዲህ ትጠራዋለች:-
1. #ሊቀ_ሊቃውንት
2. #በላዔ_መጻሕፍት
3. #ዓምደ_ሃይማኖት
4. #ዳግማዊ_ቄርሎስ
5. #ጠቢብ_ወማዕምር

+ጻድቁ ሊቅ በተወለደ በ60 ዓመቱ በ1418 ዓ/ም በዚህች ቀን
ዐርፏል:: አባ ጊዮርጊስ የተወለደውም ያረፈውም ሐምሌ 7 ቀን
ነው::

=>የሥላሴ ቸርነት: የአብርሃም ደግነት: የአበው አባ ጊዮርጊስና
አባ ሲኖዳ በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን::

=>ሐምሌ 7 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱሳን አብርሃምና ሣራ (ሥላሴን ያስተናገዱ)
2.ብሥራተ ልደተ ይስሐቅ
3.ታላቁ አባ ሲኖዳ (የባሕታውያን ሁሉ አለቃ)
4.አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ (ሊቀ ሊቃውንት: ኢትዮዽያዊ
የሃይማኖት ምሰሶ)
5.ቅዱስ አግናጥዮስ ዘአንጾኪያ (ምጥው ለአንበሳ)
6.አባ መቃቢስ
7.አባ አግራጥስ

=>ወርሐዊ በዓላት
1.አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት
2.አባ ባውላ ገዳማዊ
3.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ

=>+"+ እግዚአብሔርም ለአብርሃም ተስፋ በሰጠው ጊዜ:-
'በእውነት እየባረክሁ እባርክሃለሁ:: እያበዛሁም አበዛሃለሁ'
ብሎ ከእርሱ በሚበልጥ በማንም ሊምል ስላልቻለ በራሱ ማለ::
እንዲሁም እርሱ ከታገሠ በሁዋላ ተስፋውን አገኘ:: +"+ (ዕብ.
6:13)
=>+"+ የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ: የእግዚአብሔርም ፍቅር:
የመንፈስ ቅዱስም ሕብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን:: አሜን:: +"+
(ቆሮ. 13:14)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >
††† እንኳን ለሐዋርያው ቅዱስ ናትናኤል ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ናትናኤል †††

††† በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት ከቅዱሳን ሐዋርያት መካከል ዘግይቶ ሰማዕትነትን የተቀበለ ይህ ቅዱስ ሐዋርያ ነው::

ቅዱሱ ሐዋርያ የተወለደው ከእሥራኤላውያን ወላጆቹ ጌታችን በተወለደበት ዘመን አካባቢ ነው:: ይህ በምን ይታወቃል ቢሉ እርሱ ሕፃን እያለ ሔሮድስ 144,000 ሕፃናትን ሲፈጅ እርሱ ግን በእግዚአብሔር ጥበብ ተርፏል:: እናቱ በቅርጫት ውስጥ አድርጋ የበለስ ዛፍ ላይ አስቀምጣው ተደብቃ ታጠባው ነበር::

ለሐዋርያው ወላጆቹ ያወጡለት ስም ስምዖን ሲሆን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ ናትናኤል ብሎታል:: በባልንጀሮቹ ሐዋርያት ደግሞ የቃናው ስምዖን (ገሊላ ቃና አካባቢ ስላደገ) አንዳንዴም ቀናተኛው ስምዖን ይሉት ነበር::

ምሑረ ኦሪት ነበርና ዘወትር ለሕግ ይቀና ነበር:: በገሊላ ቃና ሰርግ የደገሰው ዶኪማስ የቅዱስ ናትናኤል የአጎት ልጅ ነው:: ጌታና ደቀ መዛሙርቱን ዶኪማስ የጠራበት አንዱ ምክንያትም ይሔው ነው::

ቅዱስ ናትናኤል ኦሪትን ከገማልያል ተምሮ: ከበለስ ቁጭ ብሎ ይተክዝ ነበር:: "መሲሕ ምነው ቀረህ?" እያለም ይተክዝ ነበር:: ማዕምረ ኅቡዓት አምላካችን ክርስቶስ ይህንን አውቆ በፊልጶስ አማካኝነት ጠርቶታል::

ናትናኤል ለጊዜው ተከራክሮ ነበር:: በኋላ ግን የጌታችንን ማንነት በደቂቃዎች ተረድቶ አምኗል:: ጌታችንም "ክዳት ሽንገላ በልቡ ውስጥ የሌለበት ንጹሕ እሥራኤላዊ" ሲል አመስግኖታል::

ሐዋርያው ቅዱስ ናትናኤል ከጌታችን እግር ሥር ምሥጢረ መንግስተ ሰማያትን ተምሮ: በጸጋ መንፈስ ቅዱስም ሰክሮ: ብዙ አሕዛብን ከጨለማ (ጣኦት አምልኮ) ወደ ብርሃን (አሚነ ክርስቶስ) መልሷል:: እጅግ ብዙ መከራንም ተቀብሏል::

የጌታችን ወንድም የተባለ ቅዱስ ያዕቆብ በአይሁድ ከተገደለ በኋላም ቅዱስ ናትናኤል የኢየሩሳሌም ሁለተኛ ኤጲስ ቆጶስ ሆኖ አገልግሏል:: ከአይሁድም ዘንድ ብዙ መከራ ደርሶበታል:: በመጨረሻም በዚህች ዕለት በሰማዕትነት አልፏል:: በገድለ ሐዋርያት ላይ እንደተጠቀሰው ቅዱሱ ሰማዕት የሆነው በመቶ ሃምሳ ዓመቱ ነው:: ያ ማለት ደግሞ ከሐዋርያት አባቶች በመጨረሻ ያረፈው እርሱ ነው ያሰኛል::

††† አባ ብስንዳ †††

††† ዳግመኛ በዚህ ቀን ታላቁ አባ ብስንዳ ይታሠባል::
አባ ብስንዳ በዘመነ ጻድቃን ምድረ ግብጽ ውስጥ ከነበሩ ታላላቅ አበው አንዱ ነው:: ቅዱሱን ከገድሉ ጽናት የተነሳ መላእክት በእጅጉ ይወዱት ነበር:: "እኔ ልሸከምህ - እኔ ልሸከምህ" እያሉ ይሻሙበት: በተራ በተራም ተሸክመውት ይውሉ ነበር:: እርሱም ለበርካታ ዓመታት ውኃ የሞላበት ጉድጓድ ውስጥ ገብቶ ይጸልይ ነበር::

እንደ እሳት በሚባላው በረዶ ውስጥ ገብቶ መጸለዩ የፈጣሪውን ሕማማት ለመሳተፍ እና ለኃጥአን ምሕረትን ይለምን ዘንድ ነው:: ሁሌም በዘጠኝ ሰዓት መላእክት ተሠብስበው ይመጡና በብርሃን ሠረገላ ይሸከሙታል:: ከመሬትም ዘጠኝ ክንድ ከፍ ያደርጉት ነበር::
ከብዙ ዓመታት ተጋድሎ በኋላም በዚህች ቀን ዐርፎ ወደ ፈጣሪው ሒዷል::

††† እግዚአብሔር በቅዱስ ናትናኤል ምልጃ ሃገራችንን ከጥፋት: ሕዝቦቿንም ከመቅሰፍት ይሰውርልን:: ከሐዋርያው እና ከጻድቁ አባ ብስንዳ በረከትም አይለየን::

††† ሐምሌ 10 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ናትናኤል ሐዋርያ (ቀናተኛው ስምዖን)
2.ታላቁ አባ ብስንዳ ጻድቅ
3.አባ ከላድያኖስ ሊቀ ጳጳሳት

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ
2.ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሃገረ ሜራ
3.አቡነ መልክዐ ክርስቶስ
4.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ እልፍዮስ)
5.ቅድስት ዕሌኒ ንግስት
6.ቅዱስ ዕፀ መስቀል

††† "ጌታ ኢየሱስ ናትናኤልን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ ስለ እርሱ 'ተንኰል የሌለበት በእውነት የእሥራኤል ሰው እነሆ' አለ:: ናትናኤልም 'ከወዴት ታውቀኛለህ?' አለው:: ጌታ ኢየሱስም መልሶ 'ፊልጶስ ሳይጠራህ ከበለስ በታች ሳለህ አየሁህ' አለው:: ናትናኤልም መልሶ 'መምሕር ሆይ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ:: አንተ የእሥራኤል ንጉሥ ነህ' አለው::" †††
(ዮሐ. ፩፥፵፰-፶፩)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
††† እንኳን ለጻድቅና ሰማዕት ቅዱስ ዮሐንስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ዮሐንስ ጻድቅ ወሰማዕት †††

††† ቅዱስ ዮሐንስ በቀደመው ዘመን ከነበሩ ታላላቅ አበው አንዱ ሲሆን ሃገረ ሙላዱ መርባስ ትባላለች:: ወላጆቹ እግዚአብሔርን የሚወዱ: ምጽዋትን የሚያዘወትሩና በበጐው ጐዳና የሚኖሩ ነበሩ:: ነገር ግን ልጅ በማጣታቸው ምክንያት ፈጽመው ያዝኑ: ይጸልዩም ነበር:: በተለይ ለመጥምቁ ዮሐንስ ልዩ ፍቅር ስለ ነበራቸው ዝክሩን ይዘክሩ: በስሙም ይማጸኑ ነበርና መጥምቁ ሰማቸው::

ወደ ፈጣሪውም ልመናቸውን በማድረሱ መልክ ከደም ግባት የተባበረለት ደግ ልጅን ወለዱ:: እጅጉን ደስ ስላላቸው በአካባቢያቸው የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስን ቤተ ክርስቲያን በገንዘባቸው አነጹ:: ሕፃኑንም በመጥምቁ ስም "ዮሐንስ" አሉት:: ጻድቁ ቅዱስ ዮሐንስ ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ጸጋ እግዚአብሔር አድሮበታልና ሕይወቱ ግሩም ነበር::

በሕፃን ገላው ይጾምና ይሰግድ: በልጅ አንደበቱም ተግቶ ይጸልይ ነበር:: ወላጆቹ ወደ እረኝነት ባሰማሩት ጊዜም መፍቀሬ ነዳያን ነውና ቁርስና ምሳውን ለነዳያን እያበላ እርሱ ጾሙን ይውል ነበር:: አባቱ የሚያደርገውን ሰምቶ ለማረጋገጥ ተከተለው:: እንዳሉትም እናቱ ጋግራ የሰጠችውን ትኩስ ዳቦ ለነዳያን ሲሰጥ አየው::

ሊቆጣው ፈልጐ "ዳቦህ የታለ?" ቢለው ሕፃኑ ቅዱስ ዮሐንስ "በአገልግሉ ውስጥ አለ" ሲል መለሰለት:: አባት ለመቆጣት እንዲመቸው አገልግሉን ሲከፍተው ግን ያየውን ማመን አልቻለም:: በእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ ዳቦዎቹ ትኩስ እንደሆኑ ተገኙ::

አባትም ወደ ቤቱ ወስዶ "ልጄ! አንተ የእግዚአብሔር ሰው ስለሆንክ እኛን ሳይሆን እርሱን አገልግል" ብሎ ወደ ቤተ ክርስቲያን ላከው::

በዚህ ምክንያት ቅዱስ ዮሐንስ በአሥራ ሁለት ዓመቱ ወደ ትምህርት ገባ:: በስድስት ዓመታትም ብሉይ ከሐዲስ ጠነቀቀ:: አሥራ ስምንት ዓመት ሲሞላው ደግነቱን ወደዋልና በግድ ቅስና ሾሙት:: እርሱ ግን ለተወሰነ ጊዜ አስተምሮ ዘመዱ የሆነውንና ዲያቆኑን ቅዱስ ስምዖንን አስከትሎ መነነ::
በዚያም በፍጹም ገድል ሲኖር ብዙ ተአምራትን ሰርቷል::

¤አንድ ወታደር (አንድ ዐይና ነው) ሊባረክ ብሎ ሲጐነበስ የታወረች ዐይኑን የቅዱስ ዮሐንስ ልብስ ቢነካት በርታለታለች:: ከዚህ አልፎም ቅዱሱ ብዙ ድውያንን ፈውሷል: ለምጻሞችን አድኗል: አጋንንትን ከማደሪያቸው (ከሰው ላይ) አሳድዷል::

ታዲያ አንድ ቀን የወቅቱ የአንጾኪያ ንጉሥ የቅዱስ ዮሐንስን ዜና ይሰማል:: የእርሱ ልጅ ደግሞ አጋንንት አድረውባት ስቃይ ላይ ነበረችና የሚያድናት አልተገኘም:: ንጉሡ "ጻድቁን አምጡልኝ" ብሎ መልዕክተኛ ሲልክ ቅዱስ ዮሐንስ ደመና ጠቅሶ: በዚያውም ላይ ተጭኖ ከተፍ አለ:: ንጉሡ አይቶት ደነገጠ:: አባ ዮሐንስ ግን "እኔ ኃጢአተኛ የሆንኩ ሰው ለምን እንዲህ ትፈልገኛለህ?" ብሎ ታማሚዋን አስጠራ::

ጻድቁ እጆቹን አንስቶ ወደ ፈጣሪው ሲጸልይ በወጣቷ ላይ ያደረው ሰይጣን ሕዝቡ እያዩት ከሆዷ በዘንዶ አምሳል ወጥቶ ሔደ:: ንጉሡ ስለተደረገለት ውለታ ለቅዱስ ዮሐንስ ወርቅና ብር ብዙ ሽልማትም አቀረበ:: አባቶቻችን እንዲህ ዓይነት ነገር አይወዱምና ቅዱሱ "እንቢ አልወስድም" አለ::

ቅዱስ ዮሐንስ "ልሒድ" ብሎ ሲነሳ ንጉሡ "አባቴ ወድጄሃለሁና አትሒድ" ብሎ የልብሱን ዘርፍ (ጫፍ) ያዘው:: በቅጽበት ግን ደመና መጥታ ነጥቃ ወሰደችው:: የቀሚሱ ቁራጭም በንጉሡ እጅ ላይ ቀረች:: እርሱም ቤተ ክርስቲያን አሳንጾ ያችን የተባረከች ጨርቅ በክብር አኑሯታል::

ቅዱስ ዮሐንስና ቅዱስ ስምዖን (ደቀ መዝሙሩ) ግን ከብዙ የተጋድሎ ዓመታት በኋላ ሌላ ክብር መጣላቸው:: "ክርስቶስን ካዱ: ለጣዖት ስገዱ" የሚል ንጉሥ በመነሳቱም ሒደው በጌታችን ስም መሰከሩ:: በገድል በተቀጠቀጠ ገላቸው ላይ ግርፋትን: እሳትን ታገሱ:: በዚህች ቀንም አንገታቸውን ተቆርጠው በሰማዕትነት ዐርፈዋል::

††† ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምልጃቸው ይማረን:: ከበረከታችቸውም ያድለን::

††† ሐምሌ 11 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አባ ዮሐንስ (ሰማዕት ወጻድቅ)
2.ቅዱስ ስምዖን (ደቀ መዝሙሩ)
3.አባ ኢሳይያስ ዘገዳመ አስቄጥስ
4.አባ ገብርኤል ሊቀ ጳጳሳት

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ያሬድ ካህን
2.ቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት
3.ብፁዐን ኢያቄም እና ሐና
4.አቡነ ሐራ ድንግል ጻድቅ
5.ማር ገላውዴዎስ ሰማዕት

††† "ሒዳችሁም መንግስተ ሰማያት ቀርባለች ብላችሁ ስበኩ:: ድውዮችን ፈውሱ: ሙታንን አንሱ: ለምጻሞችን አንጹ: አጋንንትን አውጡ:: በከንቱ ተቀብላችሁ በከንቱ ስጡ:: ወርቅ: ወይም ብር: ወይም ናስ በመቀነታችሁ: ወይም ለመንገድ ከረጢት: ወይም ሁለት እጀ ጠባብ: ወይም ጫማ: ወይም በትር: አታግኙ:: ለሠራተኛ ምግቡ ይገባዋልና::" †††
(ማቴ. ፲፥፯)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

https://t.me/kaletsidkzm
✞✞✞✝️ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ✝️ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✝️ሐምሌ ፲፪✝️

✞✞✞ እንኩዋን ለቅዱስ "ሚካኤል ሊቀ መላእክት"
የተአምር በዓልና ለሰማዕቱ "አባ ሖር" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

+*" ተአምረ ቅዱስ ሚካኤል "*+

=>ቅዱስ መጽሐፍ እንደ ነገረን በዚህች ዕለት የመላእክት
ሁሉ አለቃቸው: የቅዱሳንም ረዳታቸው የሆነው ደጉ
መልአክ #ቅዱስ_ሚካኤል ንጉሡን ሕዝቅያስን ግሩም
በሆነ ተአምር ከከተማው #ኢየሩሳሌም ጋር ታድጐታል::
ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-

+ከመድኃኒታችን #ክርስቶስ ልደት 700 ዓመታት በፊት
#ሕዝቅያስ የሚባል ንጉሥ በይሁዳ ላይ ነግሦ ነበር::
ደጋጉ #ዳዊትና #ሰሎሞን ካረፉ በሁዋላ የሕዝቅያስን
ያክል ቅን እና የእግዚአብሔር ሰው በእሥራኤል ላይ
አልነገሰም:: ንጉሡ ጣዖት አምልኮን ነቃቅሎ አጥፍቶ
ሕዝቡ እግዚአብሔርን ብቻ እንዲያመልክ አድርጐም
ነበር::

+ነገር ግን ቅዱስ ሕዝቅያስ በነገሠ በ14ኛው ዓመት
የአሕዛብ (የአሦር) ንጉሥ ሰናክሬም በጠላትነት ተነሳበት::
ወደ አካባቢውም መጥቶ: ከቦ አስጨነቀው:: ሰናክሬም
በጦር እጅግ ኃይለኛ ነበር:: በዚያውም ላይ ጦር የሚመዙ
ከ185,000 በላይ ብርቱ ተዋጊዎች ነበሩትና ሕዝቅያስ
እንደማይችለው ተረድቶ መልእክተኛ ላከበት::

+"እገብርልሃለሁ:: የፈለግከውንም እሰጥሃለሁ:: ሃገሬን
ግን አታጥፋ:: ኢየሩሳሌምን አታቃጥል:: ሕዝቤንም
አትግደል" በሚል ለመነው:: እጅ መንሻ ግብሩንም
ከከተማዋ የተገኘውን ወርቅና ብር ሁሉ ጭኖ ላከለት::

+ሰናክሬም ግን ሰይጣን ያደረበት ነውና የሕዝቅያስን
ልመና ወደ ጐን ብሎ የእሥራኤልን አምላክ : ቅዱስ
ስሙንም ተገዳደረ:: ለሕዝቅያስም "ከእኔ እጅ የሚያድንህ
ማነው? ሕዝቡንም #እግዚአብሔር ያድናል ብለህ
አታታልላቸው" ሲል ላከበት:: ቅዱስ ሕዝቅያስ በዚህ ጊዜ
የፈጣሪው ስም ሲቃለል ሰምቷልና ፈጽሞ አዘነ::

+መልእክተኞችን ወደ ነቢዩ #ቅዱስ_ኢሳይያስ ልኮ እርሱ
ወደ ቤተ መቅደስ ገባ:: በእግዚአብሔር ፊት ልብሱን
ቀድዶ ማቅ ለበሰ:: ስለ ኢየሩሳሌምና ሕዝቡም ፈጽሞ
አለቀሰ:: በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር የሰናክሬምን
መገዳደርና የሕዝቅያስን ልመና ሰምቷልና በኢሳይያስ
አንደበት እንዲሕ አለ:- "ስለ ባሪያየ ስለ #ዳዊት
ከተማዋን አድናታለሁ::"

+በዚያች ሌሊትም ድንቅ መልአክ #ቅዱስ_ሚካኤል
ከሰማያት በግርማ ወረደ:: ወደ ሰናክሬም የጦር ሠፈር
ደርሶ አንድ ጊዜ የእሳት ሰይፉን መዝዞ ቢያሳያቸው
ከአሕዛብ ሠራዊት 185 ሺ ኃያላን እንደ ቅጠል ረገፉ::
በለኪሶ የነበረው ሰናክሬም በጧት ቢነሳ ሠራዊቱ ሁሉ
ወደ አስከሬን ክምር ተቀይሯል::

+በድንጋጤ ወደ #ነነዌ ሒዶ ወደ ጣዖት ቤቱ ሲገባ የራሱ
ልጆች (አድራማሌክና ሳራሳር) ገደሉት:: ትዕቢተኛው
ሰናክሬም ለአሕዛብ ሁሉ መዘባበቻ ሆነ:: ቅዱስ ሕዝቅያስ
ግን በፈጣሪው ታምኗልና ቅዱስ ሚካኤል ሞገስ ሆኖ
የዓለም ነገሥታት ሁሉ ፈሩት:: (1ነገ. 18:13, 19:1)

+*" ቅዱስ አባ ሖር ሰማዕት "*+

=>ዳግመኛ በዚህ ቀን #አባ_ሖር ሰማዕቱ ይታሠባል::

+ቅዱሱ:-

¤ስርያቆስ በምትባል የግብጽ አውራጃ ተወልዶ ያደገ:
¤ገና በልጅነቱ መንኖ እግዚአብሔርን ያገለገለ:
¤ዘመነ ሰማዕታት በመጣ ጊዜም በመኮንኑ ፊት ቀርቦ
በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ያመነ:
¤ከመኮንኑም ብዙ ስቃይ የደረሰበት:
¤ብዙ ተአምራትን በመስራቱ ያሰቃየው የነበረውን መኮንን
ወደ ክርስትና መልሶ ለሰማዕትነት ያበቃ አባት ነው::

+እርሱም የሰማዕትነትን ክብር በእጅጉ ሽቷታልና ወደ ሌላ
ሃገር ሒዶ በዚህች ቀን አንገቱን ተሰይፎ የክብርን አክሊል
ተቀዳጅቷል:: በሐዋርያዊ አገልግሎቱ ያሳመናቸው 127
ወንዶችና 20 ሴቶችም አብረውት ተሰይፈዋል::

=>እግዚአብሔር በሊቀ መላእክት ክንፍ ሃገራችንን
ከአሕዛብ ስውር ጦር ይጠብቅልን:: ከሰማዕቱም በረከት
ያሳትፈን::

=>ሐምሌ 12 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ሕዝቅያስ ንጉሥ
2.ቅዱስ ኢሳይያስ ልዑለ ቃል
3.ቅዱስ አባ ሖር ሰማዕት
4."147" ሰማዕታት (የአባ ሖር ማሕበር)

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት
2.ቅዱስ ላሊበላ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮዽያ)
3.ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ
4.ቅዱስ ድሜጥሮስ
5.ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
6.ቅዱስ ቴዎድሮስ ምሥራቃዊ (ሰማዕት)
7.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
8.አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ

=>+"+ እግዚአብሔር ይላል:- ስለ እኔም ስለ ባሪያየም
#ስለ_ዳዊት ይህችን ከተማ አድናት ዘንድ እጋርዳታለሁ::
በዚያችም ሌሊት የእግዚአብሔር መልአክ ወጣ::
ከአሦራውያንም ሠፈር መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ገደለ::
ማለዳም በተነሱ ጊዜ እነሆ ሁሉ በድኖች ነበሩ:: +"+
(1ነገ. 19:34)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
"የጾሙ ዐዋጅ ለገዳማውያን ብቻ ነው"
 
ሐምሌ 22 ቀን የሚጀመረውን የገዳማውያን ጾምን አስመልክቶ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት የተሰጠ ማሳሰቢያ፤

አንዳንድ የቤተ ክርስቲያናችን አባላት እያቀረቡት ካለው የግንዛቤ ጥያቄ አንጻር ሐምሌ 5 ቀን 2016 ዓ.ም በቋሚ ሲኖዶስ የተሰጠውን መግለጫ በተመለከተ አጭር ማብራሪያ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።

በመሆኑም ከአንድነት ገዳማት ኅብረት በቀረበው ጥያቄ መሠረት ከላይ በተጠቀሰው ቀን የተሰጠው መግለጫ ከሐምሌ 22 እስከ ሐምሌ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ በሁሉም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት የሚፈጸመውን የምሕላ ጸሎት አስመልክቶ ከቋሚ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ በሚል ገላጭ ርዕስ በሁሉም የሀገራችን ክፍልና በሌሎችም አህጉራተ ዓለም ለሚገኙ ገዳማውያን ብቻ የታወጀ የምሕላ ሱባኤ መሆኑን
እየገለጽን በዚህ የሱባኤ ሳምንት ከቤተ ክርስቲያናችን አገልጋዮችና ምእመናን የሚጠበቀው ለገዳማውያኑ ጸጥታ ሲባል ወደ ገዳማት የምታደርጉት ጉዞ ለጊዜው እንዲቆይ ሆኖ እግዚአብሔር የገዳማውያኑን ጸሎት ሰምቶ ለሀገራችንና ለሕዝባችን ሰላምን፣ ፍቅርንና አንድነትን ይሰጥልን ዘንድ በያላችሁበት ቦታ ሆናችሁ በጸሎት ብቻ እንድትተጉ የቋሚ ሲኖዶስን ውሳኔ በማስታወስ አደራ እያልን የፈቃድ ጾም ግን  ለኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች የማይከለከል መሆኑን ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ታሳስባለች።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
         ቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት

©የኢኦተቤ ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ
††† እንኳን ለአባታችን ቅዱስ ብስንድዮስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ብስንድዮስ ጻድቅ †††

††† ቅዱስ ብስንድዮስ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ድንቅ ሥራ ከሠሩት እንደ አንዱ ሆኖ ይዘከራል:: ቅዱሱ ግብጻዊ ሲሆን በልጅነቱ ወደ ትምሕርት ቤት ገብቶ ቅዱሳት መጻሕፍትን ተምሯል:: የሚገርመው የብሉይም ሆነ የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍትን በሙሉ ያጠናቸው በቃሉ ነበር::

በእርግጥ ይሕንን ማድረግ የቻሉ በርካታ የሃገራችን ሊቃውንት ዘንድሮም አሉ:: ልዩነቱ ግን ወዲህ ነው:: ቅዱስ ብስንድዮስ መጻሕፍቱን ያጠናቸው ለሕይወት እንጂ ለእውቀት አልነበረምና ሁሌም ነግቶ እስከ ሚመሽ እያንዳንዱን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እያጣጣመ ይጸልይ ነበር:: ይሕንን ሲያደርግ ደግሞ
ባጭር ታጥቆ
ጫማውን አውልቆ:
በባዶ ሆዱ ቁሞ ነው::

ታዲያ እያንዳንዱን የመጽሐፍ ክፍል ሲጸልይ ነቢይ ቢሆን ሐዋርያ ወደ እርሱ ይወርድለት ነበር:: ለምሳሌ ዘፍጥረትን ሲጸልይ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ይመጣና ከፊቱ ተቀምጦ ይሰማዋል:: ትንቢተ ኢሳይያስ ላይ ሲደርስ ኢሳይያስ: ወንጌለ ማቴዎስ ላይ ሲደርስ ቅዱስ ማቴዎስ ይመጡና ደስ እያላቸው ያደምጡት ነበር::

አንዱ ነቢይ: ወይ ሐዋርያ ሲወጣ ቅዱስ ብስንድዮስን ባርኮ ሌላኛውን ተክቶ ነው:: በዚህ ምክንያት የቅዱሱ ሕይወት በምድር እያለ ሰማያዊ ሆነ: ሰማንያ አንዱን አሥራው መጻሕፍት የጻፉ ቅዱሳንን ለማየት በቃ:
በእጆቻቸውም ተባረከ::

የቅዱስ ብስንድዮስ ቀጣይ የሕይወቱ ተግባር ብሕትውና ሆነ:: ዓለምንና ግሳንግሷን ትቶም ወደ በርሃ መነነ:: በአጽንዖ በዓት:
በጾምና በጸሎት:
በትሕርምትም ተጋደለ:: በየደረሰበት ቦታ ሁሉ እግዚአብሔር በእጆቹ ድንቅ ተአምር ይሠራ ነበር:: ብዙ ድውያንን ፈወሰ: አጋንንትንም ከአካባቢው አሳደደ::

በእነዚህ ሁሉ ጊዜያት ግን ስዕለት ስላለበት ሴቶችን ላለማየት ይጠነቀቅ ነበር:: በሆድ ሕመም ትሰቃይ የነበረችና ጥሪቷን በመድኃኒት የጨረሰች አንዲት ሴት ስለ ቅዱሱ ዝና ትሰማለች:: ችግሩ ግን እርሱ ከውዳሴ ከንቱና ከሴት የሚርቅ ነውና እንዴት ብላ ታግኘው? አንድ ቀን ከበዓቱ አካባቢ ተደብቃ ውላ ሲመጣ የልብሶቹን ዘርፍ ለመንካት በእምነት አሰበች::

ልክ ከበዓቱ ሲዘልቅ ስሉጥ(ፈጣን) ነበርና ገና እንዳያት ሩጦ አመለጣት:: እንዳትከተለው ድውይ ናትና አልቻለችም:: አዝና ዝቅ ስትል ግን የረገጠውን ኮቲ ተመለከተች:: በፍጹም ልቧ: በእምነት "የጻድቁ አምላክ ማረኝ" ብላ ከአፈሩ ቆንጥራ በላች:: ደቂቃ አልቆየችም:: ፈጥና ከደዌዋ ዳነች:: እንደ እንቦሳ እየዘለለች ወደ ከተማ ሔዳ ተአምሩን ተናገረች::

ከእነዚህ ዘመናት በኋላ በእግዚአብሔር ፈቃድ ቅፍጥ(Qift) በምትባል ሃገር ጵጵስናን (እረኝነትን) ተሹሟል:: ወደ ከተማ ሲገባ የቀደመ ተጋድሎውን ቸል አላለም:: ይልቁኑ ይተጋ ነበር እንጂ:: ከብቃት መዓርግ ደርሷልና ሲቀድስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በገሃድ ያየው: ሠራዊተ መላእክትም ይከቡት ነበር::

ሕዝቡ ሊቆርቡ ሲመጡ የእያንዳንዱ ኃጢአት በግንባራቸው ተጽፎ ይታየው ነበር:: የበቁትን እያቀበለ: ያልበቁትን እየመከረና ንስሐ እየሰጠ ይመልሳቸዋል:: እንዲሕ በጽድቅ: በሐዋርያዊ አገልግሎትና በንጽሕና ተመላልሶ ቅዱስ ብስንድዮስ በዚህች ቀን ዐርፏል::

ቅዱስ ብስንድዮስ ካረፈ በኋላ ደቀ መዝሙሩ ከመግነዙ ጥቂት ቆርጦ አስቀርቶ ብዙ ድውያንን ፈውሶበታል::

††† ቸር አምላክ ለአባቶቻችን የሰጠውን ጸጋ ለእኛ ለባሮቹም አይንሳን:: ከቅዱሱ በረከትም ያድለን::

††† ሐምሌ 13 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ብስንድዮስ ሊቅ ወጻድቅ
2.ቅዱስ አሞን ሰማዕት (ዘሃገረ ጡህ)

††† ወርኀዊ በዓላት
1.እግዚአብሔር አብ
2.ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀ መላእክት
3.ዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት
4.ቅዱስ አስከናፍር
5.አሥራ ሦስቱ ግኁሳን አባቶች
6.ቅዱስ አርሳንዮስ ጠቢብ ገዳማዊ
7.አቡነ ዘርዐ ቡሩክ

††† "አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር:: ከማን እንደተማርኸው ታውቃለህና:: ከሕፃንነትህም ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳት መጻሕፍትን አውቀሃል:: የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጐ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምሕርትና ለተግሣጽ: ልብንም ለማቅናት: በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል::" †††
(፪ጢሞ. ፫፥፲፬)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
እንዴት ሰነበታችሁ የቃለ ጽድቅ አንባቢያን እግዚአብሔር ቢረዳን ዕለት ዕለት ከሚለቀቁ ስንክሳር ጥያቄ እንጠያየቃለን እንድናነብና ከዕለቱ ቅዱሳን በረከት እንድናገኝ: ጥያቄው ማታ ምንለቅ ይሆናል እስከዛው የዕለቱ ስንክሳር እናንብብ።📖📖
🙏🙏 በተጨማሪ ያላችሁን ማንኛውንም አስተያየት እንቀበላለን።
መልካም ቀን!!!
💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫
ሰላም  ለእናንተ ይሁን የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እነሆ

የምሽቱ ጥያቄ

1.መጽሐፍ ቅዱስ የጻፉትን ቅዱሳን ለማግኘት እና ለመባረክ የበቃው ቅዱስ አባት ማነው?
ሀ.ቅዱስ እለ እስክንድሮስ
ለ.ቅዱስ ቴዎፍሎስ
መ.ቅዱስ በስንድዮስ

2. 4 ዐይና ሚባሉት ብፁዓን አባቶች የሚያስመሠክሩት  መጻሕፍት ምን  ምንድናቸው ?
ሀ. መጽሐፈ ብሉያት
ለ.መጽሐፈ መነኮሳት
መ. መጽሐፈ ሀይማኖተ አበው

3.ቅዱስ በስንድዮስ በጳጳስነት የተሾመባት ሀገር ማን ትባላለች?
ሀ. ሶርያ
ለ.አርመን
ሐ.ቅፍጥ


መልስዎትን በ @Liyu7 
ይላኩልን


"ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤" |ዕብራውያን 10 : 24|
@kaletsidkzm
††† እንኳን ለሰማዕቱ ቅዱስ አብሮኮሮንዮስ እና ለመነኮሳት አለቃ ቅዱስ መቃርስ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ አብሮኮሮንዮስ ሰማዕት †††

††† ቅዱሱ ተወልዶ ያደገው በአንጾኪያ (ሶርያ) በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን አካባቢ ነው:: አባቱ ደግ ክርስቲያን የነበረ ሲሆን ስሙ #ክርስቶፎሮስ ይባላል:: "ለባሴ ክርስቶስ" እንደ ማለት ነው:: እናቱ ግን #ቴዎዳስያ የምትባል አረማዊት ነበረች:: ምንም እንኩዋ አባቱ ክርስቲያን ቢሆን እናቱ ኃይለኛ የቤተ መንግስት ሰው ስለነበረች በልጅነቱ አብሮኮሮንዮስ ክርስትናን ሊማር አልቻለም::

የልጁን አረማዊ መሆን ያልወደደ አባት አማራጩ አንድ ብቻ ነበር:: እሱም ወደ ጌታ መለመን ነበር:: በእንዲሕ ያለ ግብር ዘመናት ጐርፈው አብሮኮሮንዮስ ክርስቶስን ሳያውቅ 20 ዓመት ሆነው:: እናቱ ወስዳ: አሰልጥና ለጣዖት አምላኪ ንጉሥ ሰጠችው:: ንጉሡም የጦር አለቃ አድርጐ ሾመውና አንድ ትዕዛዝ ሰጠው:: "ክርስቲያኖችን ሁሉ ባገኘህበት ቦታ ጨፍጭፍ:: ቤታቸውንም አቃጥል::"

#አብሮኮሮንዮስ የታዘዘውን ሊፈጽም ሠራዊት አስከትሎ ሲወጣ ግን የአባቱ የ20 ዘመናት ለቅሶና ጸሎት ፍሬ አፈራ:: ገና መንገድ ላይ ሳለ ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና መድኃኒታችን #ኢየሱስ_ክርስቶስ ድምጹን ከሰማይ ላከለት:: "ወደ እውነተኛ መንገድ ተመለስ:: ካልሆነ ግን ሾተሉን ብትረግጥ ላንተ ይብስብሃል" አለው::

አብሮኮሮንዮስም እየተንቀጠቀጠ "አቤቱ አንተ ማነህ?" አለው:: ጌታም "ኢየሱስ ክርስቶስ ነኝ" ሲል መለሰለት:: ዳግመኛም "ምልክት ስጠኝ" ቢለው የብርሃን #መስቀል በሰማይ ላይ ገለጠለት:: ቅዱስ አብሮኮሮንዮስ ጊዜ አላጠፋም::

ሠራዊቱን ይዞ ወደ ንጉሡ ከተማ ተመልሶ ንጉሡን በድፍረት አለው:- "እኔ ክርስቲያን ነኝ:: ክርስቶስንም አመልካለሁ::" ካነጋገሩ የተነሳ አባቱን ደስ ሲለው ንጉሡና እናቱ ግን ደነገጡ:: ንጉሡ ሊያስፈራራው ሞከረ:: ግን አልተሳካለትም:: ከዚያማ ያሰቃየው ገባ::

አንድ ቀን አካሉ እስኪቆራረጥ ገረፉት:: በእሳትም አቃጠሉት:: ሞተ ብለው አስበው ነበር:: ወደ እርሱ ሲመለሱ ግን ጌታችን አድኖታልና የሰንበር ምልክት እንኩዋ በአካሉ ላይ አልተገኘም:: እናቱ #ቴዎዳስያ ከዚህ በላይ ምልክትን አልፈለገችም:: በደቂቃዎች ልዩነት እርሷም ወደ #ክርስትና ተመለሰች:: ልጇንም ቀድማ ሐምሌ 6 ቀን ሰማዕት ሆነች::

ቅዱስ አብሮኮርዮስን ግን ለበርካታ ጊዜያት አሰቃይተው ከክርስቶስ ፍቅር ሊለዩት ባለመቻላቸው በዚህች ቀን ገድለውታል:: አባት: እናትና ልጅ (ክርስቶፎሮስ: ቴዎዳስያና አብሮኮሮንዮስ) ለሰማያዊ ርስት በቅተዋል:: አባት ይሏቹሃል እንዲህ ነው!

††† ታላቁ ቅዱስ መቃርስ †††

††† በገዳማዊ ሕይወቱ እንደ ዘንባባ ያፈራው: የመነኮሳት ሁሉም አለቃቸው ቅዱስ መቃርስ አንድ ቀን እንዲህ አደረገ:-
አንድ በከተማ የሚኖር ባለ ጸጋ ስለ ቅዱስ መቃርስ ዝና ሰምቶ ሊባረክ ወደ ገዳመ አስቄጥስ ይመጣል:: አባ መቃርስ ባለ ጠጋው ወደ እርሱ እየመጣ መሆኑን ሲያውቅ በወንድሞች መነኮሳት መካከል ልብሱን ጥሎ እንደ አበደ ሰው አለል-ዘለል እያለ ይጫወት ጀመረ::

ያ ከተሜ ባለ ጠጋ እንደ ደረሰ ወደ መነኮሳቱ ጠጋ ብሎ "የታላቁን መቃርስ ዝና ሰምቼ ልባረክ ነበር የመጣሁት:: ከእናንተ መካከል ማንኛው ነው?" ቢላቸው "ያውልህ" ብለው አሳዩት:: ሲያየው እንደ እብድና ሕጻን እየዘለለ ይጫወታል:: ባለጠጋውም "ወይኔ! እኔኮ ደኅና ሰው መስሎኝ ነው:: በከንቱ ደከምኩ" ብሎ እያዘነ ሔደ:: ወዲያው መነኮሳት ተሰብስበው ቅዱስ መቃርስን "ለምን እንደዚህ አደረግህ?" ቢሉት "መጀመሪያ እንደ ሰውነቴ ሊያከብረኝ ይገባል" በሚል መልሷል:: በርግጥም ከምንም ነገር በፊት ሰውን በሰውነቱ (በእግዚአብሔር አርአያ በመፈጠሩ) ብቻ ልናከብር ይገባል::

††† ታላቁ ቅዱስ መቃርስ በቤተ ክርስቲያን ዛሬ በዓሉ ይከበራል::

††† ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምልጃቸው ይማረን:: ከበረከታችቸውም ያድለን::

††† ሐምሌ 14 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አብሮኮሮንዮስ ሰማዕት
2.ቅዱሳን ክርስቶፎሮስና ቴዎዳስያ (ወላጆቹ)
3.ታላቁ ቅዱስ መቃርስ (የመነኮሳት አለቃ)
4.ቅዱስ አሞንዮስ

††† ወርሐዊ በዓላት
1.አቡነ አረጋዊ (ዘሚካኤል)
2.ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ መርዓዊ
3.ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋርያ
4.ቅዱስ ሙሴ (የእግዚአብሔር ሰው)
5.አባ ስምዖን ገዳማዊ
6.አባ ዮሐንስ ጻድቅ
7.እናታችን ቅድስት ነሣሒት

††† "ለአገልግሎቱ ሾሞኝ ታማኝ አድርጐ ስለቆጠረኝ ኃይል የሰጠኝን ክርስቶስ ኢየሱስን #ጌታችንን አመሰግናለሁ:: አስቀድሞ ተሳዳቢና አሳዳጅ: አንገላችም ምንም ብሆን ይህን አደረገልኝ:: ነገር ግን ሳላውቅ ባለማመን ስላደረግሁት ምሕረትን አገኘሁ:: የጌታችንም ጸጋ #በክርስቶስ_ኢየሱስ ካሉ: ከእምነትና ከፍቅር ጋር አብልጦ በዛ::" †††
(1ጢሞ. 1:12)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
ቃለ ጽድቅ ዘመካነ ሕይወት | የመ/ሕ/ሰ/ት/ቤት ሰሌዳ መጽሔት ንዑስ ክፍል
💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫 ሰላም  ለእናንተ ይሁን የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እነሆ የምሽቱ ጥያቄ 1.መጽሐፍ ቅዱስ የጻፉትን ቅዱሳን ለማግኘት እና ለመባረክ የበቃው ቅዱስ አባት ማነው? ሀ.ቅዱስ እለ እስክንድሮስ ለ.ቅዱስ ቴዎፍሎስ መ.ቅዱስ በስንድዮስ 2. 4 ዐይና ሚባሉት ብፁዓን አባቶች የሚያስመሠክሩት  መጻሕፍት ምን  ምንድናቸው ? ሀ. መጽሐፈ ብሉያት ለ.መጽሐፈ መነኮሳት መ. መጽሐፈ ሀይማኖተ አበው…
💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫💫
ሰላም  ለእናንተ ይሁን የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እነሆ

የምሽቱ ጥያቄ መልስ

1.መጽሐፍ ቅዱስ የጻፉትን ቅዱሳን ለማግኘት እና ለመባረክ የበቃው ቅዱስ አባት ማነው?
ሀ.ቅዱስ እለ እስክንድሮስ
ለ.ቅዱስ ቴዎፍሎስ
መ.ቅዱስ በስንድዮስ

💡መልስ:-መ

2. 4 ዐይና ሚባሉት ብፁዓን አባቶች የሚያስመሠክሩት  መጻሕፍት ምን  ምንድናቸው ?
ሀ. መጽሐፈ ብሉያት
ለ.መጽሐፈ መነኮሳት
መ. መጽሐፈ ሀይማኖተ አበው

💡መልስ:-መ

3.ቅዱስ በስንድዮስ በጳጳስነት የተሾመባት ሀገር ማን ትባላለች?
ሀ. ሶርያ
ለ.አርመን
መ.ቅፍጥ

💡መልስ:-መ

ለመለሳችሁ ቃለህይወት ያሰማልን

"ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤" |ዕብራውያን 10 : 24|
@kaletsidkzm
እንዴት አመሻችሁ ውድ የቃለ ጽድቅ ቤተሰቦች የምሽቱ ጥያቄ እነሆ:-

፩, በዕለቱ ከሚታሰቡ ቅዱሳን አባቶች ፫ቱ ጥቀሱ።
፪, በገዳማዊ ሕይወቱ መልካም ያፈራ የመነኮሳት አለቃ ቅዱስ አባት ማን ይባላል?
፫, #ክርስቶፎሮስ የሚለው ቃል ትርጉም ምን ማለት ነው?
*በምንባቡ መሠረት ጥያቄዎችን እስከ ነገ ምሽት

መልስዎን @Liyu7 ላይ ይላኩ።


' አንተ ግን በተማርህበት እና በተረዳህበት ነገር ፀንተህ ኑር' [፪ኛ ጢሞ ፫÷፲፬]
@kaletsidkzm
††† እንኳን ለታላቁ ሊቅና አፈ በረከት ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ማሪ ኤፍሬም ሶርያዊ †††

††† እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ቅዱስ ኤፍሬም የተወለደው ንጽቢን በምትባል የሶርያ ግዛት ውስጥ በ298 / 306 ዓ/ም ነው:: ወላጆቹ በክርስቶስ የማያምኑ አላውያን ነበሩ:: (ምንም አንዳንድ ምንጮች ክርስቲያኖች ነበሩ ቢሉም)

ቅዱሱ ተወልዶ ባደገባት ንጽቢን ጵጵስናን የተሾመ ቅዱስ ያዕቆብ የሚባል ታላቅ ሰው ነበር:: የሰማዕትነት: የሐዋርያነት: የጻድቅነትና የሊቅነት ግብር ያለው አባት ነው:: ታዲያ ቅዱስ ኤፍሬም ይሔ አባት ሁሌ ሲያስተምር ይሰማው ነበርና በስብከቱ ተማርኮ ደቀ መዝሙሩ ለመሆን በቃ::

ቅዱስ ኤፍሬም በቅዱስ ያዕቆብ እጅ ከተጠመቀ በኋላ ሙሉ የወጣትነት ጊዜውን ያሳለፈው በትምሕርት ነው:: የሚገርመው መምሕሩ ቅዱስ ያዕቆብ ዘንጽቢን እመቤታችን ድንግል ማርያምን በፍጹም ልቡ የሚወድና ጠርቷት የማይጠግብ አባት ነውና ለልጁ ለቅዱስ ኤፍሬም ይሕንኑ አጥብቆ አስተምሮታል::

ቅዱስ ኤፍሬም ክርስትናን ሲመረምር የእመቤታችን ፍቅር ይበዛለት ጀመር:: ምክንያቱም እመ ብርሃንን ሳይወዱ ክርስትና የለምና:: እንደ እርሱ የሚወዳት የለም እስኪባል ድረስ ያገለግላት: ይገዛላትም ገባ::

እንዲህ እንደ ዛሬ የድንግል ማርያም ምስጋና በአንደበት እንጂ በመጽሐፍ አይገኝም ነበር:: እርሱ ግን ከወንጌለ ሉቃስ በስድስተኛው ወርን (ይዌድስዋን) እና ጸሎተ ማርያምን(ታዐብዮን) አውጥቶ በየዕለቱ በዕድሜዋ ልክ ስልሳ አራት ስልሳ አራት ጊዜ ያመሰግናት ነበር::

በእንዲህ ያለ ግብር እያለ አርዮስ በመካዱ እርሱን ለማውገዝና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ለማጽናት በ317 (325) ዓ.ም ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ሊቃውንት በኒቅያ ሲሰበሰቡ አንዱ መምሕረ ኤፍሬም ቅዱስ ያዕቆብ ነበር:: በዚህ ምክንያት ቅዱስ ኤፍሬም ከሊቃውንቱ ትምሕርትና በረከትን አግኝቷል::

ከጉባዔ መልስ መንገድ ላይ በራዕይ የብርሃን ምሰሶ አይቶ "ጌታ ሆይ! ምንድን ነው?" ብሎ ቢጠይቅ "ይሕማ ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስ ነው::" አለው:: እርሱም መምሕሩን ቅዱስ ያዕቆብን ተሰናብቶ ወደ ቅዱስ ባስልዮስ (ቂሣርያ) ወረደ:: ተገናኝተውም በአንድ ሌሊት ቋንቋ ተገልጦላቸው ሲጨዋወቱ አድረዋል::

በቦታው ብዙ ተአምራት ተደርጓል:: ቅዱስ ኤፍሬም ከታላቁ ባስልዮስ ከተማረ በኋላ ሃገረ ስብከት ተሰጥቶት ያስተምር ጀመር:: ሁል ጊዜ ታዲያ ጸሎቱ ይሔው ነበር:: "እመቤቴ ሆይ! ምስጋናሽ እንደ ሰማይ ከዋክብት: እንደ ባሕር አሽዋ በዝቶልኝ: እንደ እንጀራ ተመግቤው: እንደ ውኃ ጠጥቼው: እንደ ልብስም ተጐናጽፌው" እያለ ይመኝ ነበር::

አፍጣኒተ ረድኤት: ፈጻሚተ ፈቃድ እመ ብርሃንም በገሃድ ተገልጻ የልቡን ፈቃድ ፈጸመችለት:: ዛሬ ጸጋ በረከት የምናገኝበትን ውዳሴ ማርያምን ደረሰላት:: ሲደርስላትም እርሷ አእላፍ መላእክትን: ጻድቃን ሰማዕታትን አስከትላ ወርዳ: በፊቱም ተቀምጣ ሲሆን እርሱ ደግሞ ባጭር ታጥቆ: በፊቷ ቆሞ: በመንፈስ ቅዱስም ተቃኝቶ ነው::

ውዳሴዋን በሰባት ቀናት ከደረሰላት በኋላ በብርሃን መስቀል ባርካው: ሊቀ ሊቃውንትም እንዲሆን ምሥጢር ገልጣለት ዐረገች:: ከዚህ በኋላ በምሥጢር ባሕር ውስጥ ዋኝቶ አሥራ አራት ሺህ ድርሰቶችንም ደርሷል:: ዛሬ ሶርያ ውስጥ የምንሰማውን ዜማም የደረሰው ይህ ቅዱስ ነው::

እንዲያውም አንድ ቀን የምሥጢር ማዕበል ቢያማታው "አሃዝ እግዚኦ መዋግደ ጸጋከ" ብሎ ጸልዩዋል:: (የጸጋህን ማዕበል ያዝልኝ) እንደ ማለት ነው:: ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ በመጨረሻ ሕይወቱ ተክሪት በምትባል ሃገር ኤጲስ ቆጶስ ሆኖ ተሹሟል::

በጣፋጭ ስብከቱ ብዙዎችን ካለማመን መልሷል:: የምዕመናንንም ሕይወት አጣፍጧል:: ለመናፍቃንና ለአርዮሳውያን ግን የማይጋፉት ግድግዳ ሆኖባቸው ኑሯል:: በዘመኑም ብዙ ተጋድሎ አፍርቷል:: ተአምራትንም ሠርቷል:: በተወለደ በስልሳ ሰባት ዓመቱ በ365 (373) ዓ.ም ዐርፎ ተቀብሯል::

††† ቅዱሱ ለሶርያ ብቻ ሳይሆን እመቤታችንን ለምንወድ የዓለም ክርስቲያኖች ሁሉ ሞገሳችን ሆኗል:: ስለዚህም እንዲህ እያልን እንጠራዋለን:-
1.ቅዱስ ኤፍሬም
2.ማሪ ኤፍሬም
3.አፈ በረከት ኤፍሬም
4.ሊቀ ሊቃውንት ኤፍሬም
5.ጥዑመ ልሳን ኤፍሬም
6.አበ ምዕመናን ኤፍሬም
7.ርቱዐ ሃይማኖት ኤፍሬም . . . አባታችን አንተ ነህ::

††† ጽንዕት በድንግልና: ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ለቅዱስ ኤፍሬም የሰጠሽውን ጸጋውን: ክብሩን: አእምሮውን: ለብዎውን በልቡናችን ሳይብን: አሳድሪብን . . . አሜን::

††† ጴጥሮስ ወጳውሎስ †††

††† ዳግመኛ በዚህ ቀን ብርሃናተ ዓለም ጴጥሮስ ወጳውሎስ ይታሠባሉ::

ቅዱሳኑ ሶርያ አካባቢ ውስጥ ወደምትገኝ አንዲት ሃገር ገብተው ሕዝቡን ከንጉሣቸው ጰራግሞስ ጋር አሳምነው አጥምቀዋል:: ነገር ግን እነርሱ ሲወጡ ሰይጣን አስቶት አጥፊ ሰው ወደ መሆን ተመልሶ ንጉሡ ሐዋርያትን አሰቃይቷቸዋል::

ስለ ቅዱሳኑ ግን ፈረሶቹ ሰግደው: በሰው አንደበት ቅድስናቸውን መስክረዋል:: በመጨረሻም ንጉሡን ከነ ሕዝቡና ሠራዊቱ በዓየር ላይ ሰቅለው ንስሐ ሰጥተውታል:: በእነዚህ ተአምራትም ሁሉም አምነው ለከተማዋና ለሕዝቡ ድኅነት ተደርጓል::

††† ከአባቶቻችን አበው ሐዋርያት በረከት ይክፈለን::

††† ሐምሌ 15 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ማሪ ኤፍሬም ሶርያዊ (አፈ በረከት)
2.ብርሃናተ ዓለም ቅዱሳን ሐዋርያት ጴጥሮስ ወጳውሎስ
3.አባ ሓርዮንና ደቀ መዛሙርቱ (ሰማዕታት)
4.አባ ፍሬምናጦስ መስተጋድል

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ኢየሉጣ
2.ቅዱስ ሚናስ (ማር ሚና) ሰማዕት
3.ቅድስት እንባ መሪና
4.ቅድስት ክርስጢና

††† "ለምኑ ይሰጣችሁማል:: ፈልጉ ታገኙማላችሁ:: መዝጊያ አንኳኩ ይከፈትላችሁማል:: የሚለምነው ሁሉ ይቀበላልና:: የሚፈልገውም ያገኛል:: መዝጊያንም ለሚያንኳኳ ይከፈትለታል::" †††
(ማቴ. ፯፥፯)

††† "የጻድቅ አፍ ጥበብን ያስተምራል::
አንደበቱም ፍርድን ይናገራል::
የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው::
በእርምጃውም አይሰናከልም::" †††
(መዝ. ፴፯፥፴)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

https://t.me/kaletsidkzm