ቃለ ጽድቅ ዘመካነ ሕይወት | የመ/ሕ/ሰ/ት/ቤት ሰሌዳ መጽሔት ንዑስ ክፍል
1.02K subscribers
2.74K photos
44 videos
102 files
771 links
ይኽ በፈረንሳይ መካነ ሕይወት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያን መካነ ሕይወት ሰ/ት/ቤት መንፈሳዊ ጽሑፎችና መልእክቶች የሚለቀቁበት ሚዲያ ነው።
https://linktr.ee/kaletsidkizm
Download Telegram
🔔
✥✥✥
ሰዓት
✥ተንስኡ ለጸሎት✥

#መዝሙረ ዳዊት 118_25
አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አድን አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አቅና።

#በዚህ ሰዓት ይህንን የምታዩ የምታደርጉትን ለ2 ደቂቃም ብትሆን ተውና ልዑል እግዚአብሔርን እያሰብን አንድ አባታችን ሆይ እንጸልይ

የእግዚሐብሔር ልጅ ጌታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ማረን

የእግዚሐብሔር ልጅ ጌታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ማረን

የእግዚሐብሔር ልጅ ጌታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ማረን
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

❖ ግንቦት 6 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

+"+ አባ መቃርስ ካልዕ +"+

+ይህ ቅዱስ "መቃርዮስ: መቃርስ: መቃሬም" ይባላል::
ትርጉሙ በ3ቱም መንገድ አይለወጥም:: ምክንያቱም
ሥርወ ቃሉ
በዮናኒ ልሳን "ብጹዕ: ንዑድ: ክቡር" ማለት ነውና::

+ከስሙ ቀጥሎ "ካልዕ-2ኛው": አንዳንዴ ደግሞ
"እስክንድርያዊ" እየተባለ ይጠራል:: "ካልዕ-2ኛው"
የሚባለው ከቀዳሚው
(ታላቁ መቃርስ) ለመለየት ሲሆን "እስክንድርያ" ደግሞ
ተወልዶ ያደገባት ሃገር ናት::

+አባ መቃርስ በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን የነበረ ገዳማዊ:
ጻድቅና ትሩፈ-ምግባር ነው:: በዓለም ለ40 ዓመት ሲኖር
እንደ ሕጉ
ፈጣሪውን ደስ ያሰኘ ሰው ነው:: ጻድቃን እንደ ከዋክብት
በበዙበት በዚያ ዘመን የታላቁ መቃርስን ዜና ሰምቷልና
ይህቺን
ክፉ ዓለም ከነግሳንግሷ ንቋት በርሃ ገብቷል::

+እንደሚገባ ሥርዓተ ገዳምን ጠብቆ: ለአበው ታዞ:
በጾም: በጸሎት: በትሕትናና በስግደት ተጠምዶ ቢያገኘው
ፈጣሪ አከበረው::
በዚያ ጊዜም ለታላቁ ገዳመ አስቄጥስ መናንያን አበ
ምኔት ሊሆን መረጡት::

+እርሱም እረኝነትን ያውቃልና በጐቹን (መነኮሳትን)
ከተኩላ (ሰይጣናት) ይጠብቅ ዘንድ ብዙ ተጋ:: ከብቃቱ
የተነሳም
ሳያስታጉል: ሳይበላ: ሳይጠጣና ሳይቀመጥ እስከ 40 ቀን
ይጸልይ ነበር:: ሲጸልይ ደግሞ በልቡ እየተቃጠለ በፍቅረ
ክርስቶስ ነበርና አጋንንት ይርዱለት ነበር::

+እርሱ ጸሎት ሲጀምርም በገዳሙ ዙሪያ ያሉ አጋንንት
እየጮሁ ይሸሹ ነበር:: ከተጋድሎው ጽናትና ከትሕትናው
ብዛት የተነሳ
ያዩት ትዕቢተኞች ሁሉ ይገሠጹ ነበር:: በዘመኑም ብዙ
ተአምራትን ሠርቷል::

+አንድ ቀን በበዓቱ ሳለ ጅብ መጥታ ተማጸነችው::
አብሯት ወደ ዋሻዋ ቢሔድ ልጆቿ በሙሉ ዓይነ ሥውራን
ሆነው አገኛቸው::
እርሱም ወደ መሬት ምራቁን እትፍ ብሎ በጭቃ ለውሶ
ቢቀባቸው የሁሉም ዐይናቸው በርቷል::

+ስለ ውለታውም ጅቢቱ የበግ ቆዳ እየጐተተች አምጥታ
ሰጥታዋለች:: (ከሰው ልጅ በቀር እንስሳት ውለታን
አይረሱምና) ቅዱስ
መቃርስም ለወትሮው ባዶው መሬት (አፈር) ላይ ይተኛ
የነበረው ከዚያ ቀን በኋላ በአጐዛው ላይ የሚተኛ ሁኗል::

+በሃገሩ እስክንድርያም ለ2 ዓመታት ዝናብ በመጥፋቱ
ሕዝቡ ተጨንቆ ነበርና "ናልን" ሲሉ መልዕክት ላኩበት::
እርሱ መጥቶ
ሲጸልይም መብረቅ የቀላቀለ ዝናብ ጣለ:: ዝናቡም ያለ
ማቆም ለ2 ቀናት በመዝነቡ ሕዝቡ ፈርተው "አባታችን ስለ
ኃጢአታችን
እንዳንጠፋ ለምንልን?" አሉት:: እርሱም በጸሎቱ
(በፈጣሪው ኃይል) እንደ ወደዱት ዝናቡን አቁሞላቸዋል::

+የአባ መቃርስን ዜና ሕይወትና ተአምራት ተናግሬ
አልፈጽመውም:: ግን አንዲት ብቻ ላክል:: ሁሌ ሳስበው
ስለሚገርመኝም
ነው::

+ብዙዎቻችን የጌታችን ሥጋና ደም አንቀበልም:: ለምን
ያከበርነውና የፈራነው አስመስለን ኃጢአትን ለመጥገብ
ቦታን (
አጋጣሚን) ስለምንፈልግ:: በተቃራኒው ደግሞ
አንዳንዶቻችን መለኮት የተዋሐደውን የጌታ ሥጋና ደም
እንደ ተርታ ነገር (ያለ
ጥንቃቄ) ስንቀበል ይታያል:: 2ቱም ግን ስሕተት ነው::

+ፈርተን (ፍርሃቱ ጤነኛ ባይሆንም) ስለ ራቅን በፍርድ ቀን
ማምለጥ አንችልም:: "ሥጋየን ያልበላ: ደሜንም ያልጠጣ
የዘለዓለም ሕይወት የለውም" ይለናልና:: (ዮሐ. 6:52)

+በድፍረት ለምንቀበልም ሥጋው እሳት ሁኖ እንዳይበላን:
ደሙም ባሕር ሆኖ እንዳያሰጥመን ልናከብረው ይገባናል::
"ሳይገባው
ከጌታ ሥጋና ደም የተቀበለ የጌታ ሥጋ ዕዳ አለበት"
ይለናልና:: (1ቆሮ. 11:27)

<< ታዲያ የሚሻለው ለሁላችንም ንስሃ ገብቶ: በፍርሃት
ሆኖ መቅረቡ ነው:: >>

+ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና አባ መቃርስ ወደ በርሃ
እንደ ገባ ሥጋ ወደሙን ተቀብሎ ነበር:: ቅዱሱ ይህንን
እያሰበ
ለ60 ዓመታት ምራቁን ሳይተፋ ኑሯል:: ለዚያ አይደል
አበው "ብታከብሩት ያከብራቹሃል" ያሉት::

+ሊቃውንቱም ይህንን ሲያደንቁ:-
"ኢታስተማስልዎ ለቁርባን ከመ ሕብስት ዕራቆ::
አኮኑ ሥጋ መለኮት ዘይትላጸቆ::
መቃርዮስ አብ ዕበየ ቁርባን ለአጠይቆ::
ድኅረ ተወክፈ በአሚን እንበለ ያብዕ ናፍቆ::
መጠነ ዓመታት ስሳ ኢተፍአ ምራቆ::" ብለዋል::

+ቅዱስ መቃርስም በ100 ዓመቱ በ5ኛው ክ/ዘመን
መጀመሪያ አካባቢ በዚህች ቀን ዐርፏል::

❖ጌታችን ከክብሩ: ከበረከቱ አይለየን::

=>ግንቦት 6 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ አባ መቃርስ ገዳማዊ
2.እናታችን ቅድስት ሰሎሜ ኢትዮዽያዊት
3.አባ ይስሐቅ ጻድቅ
4.ቅድስት ዲላጊና 4 ሴት ልጆቿ (ሰማዕታት)
5.ቅዱስ ዳናስዮስ ሰማዕት
6.ቅዱስ በንደላዖስ ሰማዕት (የታላቁ ኤስድሮስ አባት)
7.አባ አሞን ጻድቅ (ዽዽስናን አልፈልግም ብሎ የሸሸ አባት)

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅድስት ደብረ ቁስቁዋም
2.አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን
3.አባታችን ኖኅና እናታችን ሐይከል
4.ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ
5.ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
6.ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ
7.ቅድስት ሰሎሜ
8.አባ አርከ ሥሉስ
9.አባ ጽጌ ድንግል
10.ቅድስት አርሴማ ድንግል

=>+"+ ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው:: እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሳዋለሁ:: ሥጋዬ እውነተኛ መብል: ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና:: ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል:: እኔም በርሱ እኖራለሁ:: +"+ (ዮሐ. 6:53-56)

   <<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
«ወደ እግዚአብሔር የምንጸልየው፥ መረጃ ወይም መመሪያ ልንሰጠው ሳይሆን፥ ወደ እርሱ እንድንቀርብና ከእርሱ ጋር ኅብረት ያለን እንድንሆን ነው።»
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

❖ እንኳን አደረሳችሁ ❖

❖ ግንቦት 7 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ

=>በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከሐዋርያት ቀጥሎ የቅዱስ
አትናቴዎስን ያሕል ስለ ሃይማኖት የተዋጋ ቅዱስ ፈልጐ
ማግኘት አይቻልም::

❖ቅዱስ አትናቴዎስ ማን ነው?

+ቅዱስ አትናቴዎስ በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት
በዘመነ ሰማዕታት መጠናቀቂያ በ300 አካባቢ(296)
እስክንድርያ
ግብፅ ውስጥ ነው የተወለደው:: ወላጆቹ አረማውያን
በመሆናቸው ክርስትናን አልተማረም ነበር::

+ሕጻን እያለ ለጭዋታ ከቤቱ ሲወጣ የክርስቲያን ልጆች
ሃይማኖታዊ ጨዋታ ሲጫወቱ ተመለከተ:: ሊቀላቀላቸው
ቢፈልግም
ክርስቲያን ባለመሆኑ ከለከሉት:: አትናቴዎስም ክርስቲያን
ልሁንና አጫውቱኝ ብሏቸው እሺ ስላሉት ሕጻናቱ ዕጣ
ተጣጣሉ::

+ላንዱ ቄስ: ላንዱም ዲያቆን መሆን ሲደርሳቸው
ለአትናቴዎስ ፓትርያርክ መሆን ስለ ደረሰው ሌሎቹ ሕጻናት
ይሰግዱለት ጀመር::
በአጋጣሚ ሕጻናቱ ይሕንን ሁሉ ሲያደርጉ የወቅቱ
ፓትርያርክ ቅዱስ እለ እስክንድሮስ በመገረም ያያቸው
ነበርና ለሕጻኑ
አትናቴዎስ ትንቢት ተናገረለት::

+ከዚያም የአትናቴዎስ አባቱ ሲሞት ሊቀ ዻዻሳቱ ከእናቱ
ወስዶ አጥምቆ: የሚገባውን መንፈሳዊ ትምሕርት ሁሉ
በልቡናው ላይ
ቀረጸበት:: ከዚሕ በኋላ ዲቁናን ሹሞ አስተምር አለው::
ምንም ሕጻን ቢሆንም ከሊቅነቱ: ከአመላለሱና ከአንደበቱ
ጣፋጭነት
የተነሳ የሰማው ሁሉ ይደነቅ ነበር:: ጸጋ እግዚአብሔር
በእርሱ ላይ አድራለችና::

+ቅዱስ አትናቴዎስ ሊቀ ዲቁና በተሾመ ወራት አርዮስ
ቤተ ክርስቲያንን በመረበሹ ኒቅያ ላይ 318ቱ ሊቃውንት
ሲሰበሰቡ
ጸሐፊ አድርገው ሾሙት:: በጊዜውም በዕድሜ የስንት
ጊዜ ትልቁ የሚሆነውን አርዮስን ተከራክሮ ምላሽ
አሳጣው::

ቅዱስ
አትናቴዎስ ከሊቃውንቱ ጋር ሆኖ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ
ወልደ አምላክ: እግዚአብሔር መሆኑን በአደባባይ
መሠከረ:: ጸሎተ
ሃይማኖትንም ያረቀቀው እርሱ ነው::

+ከዚሕ በኋላ የእስክንድርያ (የግብፅ) 20ኛ ፓትርያርክ
ሆኖ ተሾመ:: ቤተ ክርስቲያንን በመልካም እረኝነት ለ48
ዓመታት
ሲመግብ ብዙ መከራዎችን ተቀበለ:: ለ5 ጊዜ ከመንበሩ
አፈናቅለው ወደ በርሃ ሲያግዙት በስደት ከ15 ዓመታት
በላይ
አሳልፏል::

+በተሰደደባቸው ቦታዎች መከራን እየተቀበለ ያላመኑትን
አሳምኗል:: በጎቹ እንዳይባዝኑበት ደግሞ በጦማር
(በደብዳቤ)
ይጠብቃቸው ነበር:: ዛሬ በሃይማኖተ አበው የምናገኘው
ቃለ ሃይማኖት በዚሕ ዘመን የተጻፈ ነው::

+በወቅቱ የነበረው ንጉሥ (ትንሹ ቆስጠንጢኖስ) የአባቱን
(ታላቁ ቆስጠንጢኖስን) ዕረፍት ተከትሎ ነገሠ::

+ወዲያውም አርዮሳዊ መናፍቅ ሆነ:: ሃይማኖታቸው የቀና
አባቶችንም ያሳድድ ገባ:: ከአበው ቅዱሳን መካከል ግን
የዚህ
መከራ ቀዳሚው ገፈት ቀማሽ ታላቁ ሊቅ ቅዱስ
አንትናቴዎስ ነበር::

+በተለይ አንድ ጊዜ ንጉሡ ቅዱሱን ወደ በርሃ አግዞ:
መናፍቅ ዻዻስ በግብጽ ሹሞ: ብዙ ክርስቲያኖችን በግፍ
ሲያስገድል:
ቅዱሱን ለ6 ዓመታት አሰቃየው:: የወገኖቹ (የልጆቹን)
ስቃይ የሰማው ቅዱስ አትናቴዎስ ግን በድፍረት ወደ ቤተ
መንግስት
ገብቶ ተናገረው::

+2 አማራጭን አቅርቦ "ወይ ግደለኝና እንደ አባቶቼ
ሰማዕት ልሁን: ካልሆነ ግን ወደ መንጐቼ (ምዕመናን)
መልሰኝ" አለው::
መናፍቁ ንጉሥም ቢገድለው ብጥብጥ እንደሚነሳ
ስለሚያውቅ በስልት ሊያጠፋው ወሰነ::

+ቀዛፊ: መቅዘፊያ: ምግብና ውሃ በሌላት ጀልባ ውስጥ
ከቶም ሜዲትራኒያን ባሕር ውስጥ ጣለው:: ድንገት ግን
ከሰማይ
ጌታችን መላእክቱን አስከትሎ ወረደ::

+ሚካኤልና ገብርኤል ባሕሩን እየቀዘፍ: ሌሎች መላእክት
እየመገቡት በዚህች ቀን እስክንድርያ (ግብጽ) አድርሰውት
ተሠውረዋል:: ሕዝቡም በታላቅ ሐሴት እየዘመሩ
አባታቸውን ተቀብለውታል::

+ሐዋርያዊው ቅዱስ ስለ ኦርቶዶክስ ተዋግቶ: ብዙ
ስቃይንም ተቀብሎ በ373 ዓ/ም አካባቢ አርፏል:: ቤተ
ክስርቲያን
☞"ሊቀ
ሊቃውንት:
☞ርዕሰ ሊቃውንት:
☞የቤተ ክርስቲያን
(የምዕመናን) ሐኪም (Doctor of the Church):
☞ሐዋርያዊ" ብላ
ታከብረዋለች::

=>አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሊቁ በረከት አይለየን::
በምልጃውም ሃይማኖታችንን ይጠብቅልን::

=>ግንቦት 7 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ
2.የባሕታውያን አለቃ ታላቁ አባ ሲኖዳ (ጽንሰቱ)
3.ቅዱስ ዮሐንስ ጻድቅ (ሃብቱን: ንብረቱን: ልብሱን
ሳይቀር መጽውቶ ራቁቱን የተገኘ ደግ ሰው ነው)
4.አባ ሐርስዮስ ገዳማዊ

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ሥሉስ ቅዱስ (አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ)
2.አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
3.አባ ሲኖዳ (የባሕታውያን አለቃ)
4.አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት
5.አባ ባውላ ገዳማዊ
6.ቅዱስ አግናጥዮስ (ለአንበሳ የተሰጠ)

=>+"+ ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብጹዐን ናቸው:: መንግስተ
ሰማያት የእነርሱ ናትና:: ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ
በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ
ብጹዓን ናችሁ:: ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ
ይበላችሁ:: ሐሴትም አድርጉ:: ከእናንተ በፊት የነበሩ
ነቢያትን እንዲሁ አሳደዋቸዋልና:: +"+ (ማቴ. 5:10)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

https://t.me/kaletsidkzm
Forwarded from 𝚜𝚊𝚖𝚛𝚒-19
ለዝክረ ቅዱስ ያሬድ የሚዘመሩ መዝሙራት
††† እንኳን ለእናታችን ቅድስት እሌኒ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† እሌኒ ንግሥት †††

††† ቅድስት እሌኒ የታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ እናቱና እግዚአብሔር ለበጐ አገልግሎት የጠራት ቡርክት ሴት (ንግሥት) ናት::
ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
የቅድስቲቱ ሃገረ ሙላዷ ሮሃ (ሶርያ) አካባቢ ነው:: ነገዷ ከእሥራኤል ዝርዋን እንደሆነም ይነገራል:: ጣልያኖች "Helena" : በእንግሊዝኛው "Helen" ይሏታል:: እኛ ደግሞ "እሌኒ" እንላታለን:: ትርጓሜው "ጥሩ ምንጭ" : አንድም "ውብና ደግ ሴት" ማለት ነው::

ቅድስት እሌኒ በመልካም ክርስትና አድጋ እንደ ቤተ ክርስቲያን መተርጉማን ተርቢኖስ የሚባል ነጋዴ አግብታ ነበር:: ወቅቱም ዘመነ ሰማዕታት ነበር:: በማይሆን ነገር ጠርጥሮ ባሕር ላይ ጥሏት ንጉሥ ቁንስጣ አግኝቷታል:: እርሱም የበራንጥያ (የኋላዋ ቁስጥንጥንያ) ንጉሥ ነበር::

ቅድስት እሌኒ ከቁንስጣ የተባረከ ልጅን ወለደች:: ቆስጠንጢኖስ አለችው:: በልቡናው ፍቅርን : ርሕራሄን : መልካምነትን እየዘራች አሳደገችው:: ቅዱሱ አባቱ በሞተ ጊዜ ተተክቶ ነገሠ::

ቅድስት እሌኒንም ንግሥት አደረጋት:: ያንን የአርባ ዓመት ግፍ በአዋጅ አስቀርቶ ለክርስቲያኖች ነፃነትን : ክብርን በይፋ ሰጠ:: አንድ : ሁለት ብለን የማንቆጥረውን ውለታ ለምዕመናን ዋለ:: ከነዚህ መልካም ምግባራቱ ጀርባ ታዲያ ቅድስት እናቱ ነበረች::

ቅድስት እሌኒ ጾምን : ጸሎትን ከማዘውተሯ ባሻገር አጽመ ሰማዕታትን ትሰበስብ : አብያተ ክርስቲያንን ታሳንጽ : ለነዳያንም ትራራ ነበር:: በኢየሩሳሌምና አካባቢው ብቻ ከሰማንያ በላይ አብያተ መቃድስ አሳንጻለች:: እነዚህንም በወርቅና በእንቁ ለብጣቸዋለች::

በዘመኗ መጨረሻም የጌታችንን ቅዱስ ዕፀ መስቀል ከተቀበረበት አውጥታ ለዓለም በረከትን አስገኝታለች::

እናታችን ቅድስት እሌኒ እንዲህ በቅድስና ተመላልሳ በሰማንያ ዓመቷ በ330ዎቹ አካባቢ ዐርፋለች:: ቤተ ክርስቲያናችንም ስለ ቅድስናዋና ውለታዋ በዓል ሠርታ : ታቦት ቀርፃ ስታከብራት ትኖራለች::

††† ከቅድስት እናታችን ምልጃና በረከት አምላካችን ያድለን::

††† ግንቦት 9 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅድስት እሌኒ ንግሥት
2.ቅዱስ ስልዋኖስ

††† ወርኀዊ በዓላት
1.አባ በርሱማ ሶርያዊ (ለሶርያ መነኮሳት ሁሉ አባት)
2.አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ (ኢትዮጵያዊ)
3.ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ቅዱሳን ሊቃውንት (ርቱዐነ ሃይማኖት ዘኒቅያ)
4.የብሔረ ብፁዐን ጻድቃን
5.አባ መልከ ጼዴቅ ዘሚዳ (ኢትዮጵያዊ)
6.ቅዱስ ዞሲማስ ጻድቅ (ዓለመ ብፁዐንን ያየ አባት)

††† "ነገር ግን ለበጐ ነገር ጥበበኞች : ለክፉትም የዋሆች እንድትሆኑ እወዳለሁ:: የሰላምም አምላክ ሰይጣንን ከእግራችሁ በታች ፈጥኖ ይቀጠቅጠዋል:: የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን::" †††
(ሮሜ. ፲፮፥፲፱)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

https://t.me/kaletsidkzm