ቃለ ጽድቅ ዘመካነ ሕይወት | የመ/ሕ/ሰ/ት/ቤት ሰሌዳ መጽሔት ንዑስ ክፍል
1.02K subscribers
2.66K photos
44 videos
102 files
754 links
ይኽ የፈረንሳይ መካነ ሕይወት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያን መካነ ሕይወት ሰ/ት/ቤት ሰሌዳ መጽሔት ቻናል ነው። በዚኽ ቻናል በመንፈሳዊ ሕይወትዎ የሚበረቱባቸውን መንፈሳዊ ጽሑፎችና መልእክቶች ባሉበት ሆነው መከታተል ይችላሉ።
Download Telegram
#የስቅለት በዓል በቀበና መካነ ህይወት አቡነገብረመንፈስቅዱስ ቤ/ክ #አክፍሎት ማለት

በሰሙነ ሕማማት ዕለተ አርብ ከስግደት በሗላ ምዕመናን በየቤታቸው ጥቂት ነገር ለቁመተ ሥጋ ቀምሰው እስከ እሁድ /የትንሳኤ ሰዓት/ ይሰነብታሉ፡፡ ይህ አክፍሎት ይባላል፡፡

ከአርብ እስከ ቅዳሜ ሌሊት ለእሁድ አጥቢያ ማክፈል የብዙዎች ነው። አንዳንዶች ግን ከሐሙስ ጀምረው ያከፍላሉ፡፡ ይህም እመቤታችን፣ ያዕቆብ እና ዮሐንስ የጌታን ትንሳኤ ሳናይ እህል ውሃ አንቀምስም ብለው እስከ ትንሳኤ መቆየታቸውን ተከትሎ የመጣ ትውፊት ነው፡፡

ይህንን ትውፊት አስመልክቶ ሄሬ ኔዎስ፣ አውሳብዮስ የተባሉ ጸሐፍት፣ ሐዋሪያት በሰሙነ ሕማማት ከደረቅ ዳቦ እና ከትንሽ ውሃ በቀር እንደማይመገቡ እና ከሐሙስ ጀምረው እንደሚያከፍሉ ጽፈዋል፡፡

ይህም ብቻ ሳይሆን ሐዋሪያት ሌሎቹንም እንድያከፍሉ እንዲያሳስቡና ከሐሙስ ጀምሮ ያልተቻላቸው ቢያንስ ከአርብ ጀምሮ እንዲያከፍል ማዘዛቸውን ጽፈዋል፡፡ የኛ ቤተክርስቲያን ትምህርትም ይሄው ነው፡፡

ምንጭ፦ ስምዐ ጽድቅ ልዩ እትም ዘሰሙነ ሕማማት
#ቀዳም_ሥዑር

የማትጾመዋ ቅዳሜ ስለምትጾም «ስዑር /የተሻረች/» ተብላለች በዓል መሻርን አይመለከትም፡፡ ቀዳም ሥዑር በጾም ምክንያት የተሻረችው ቀዳሚት ሰንበት ሌሊት ሥርዓቱ የሚጀመረው በመኀልየ ሰሎሞን ምንባብ ነው፡፡ ማኀሌቱም እዝሉ እየተቃኘ፣ እየተመለጠነ፣ እየተ ዘመመ እየተመረገደ እየተጸፉ ያድራል ጥዋት አቡን መዋሥዕት ውዳሴ ማርያም ዜማ ተደርሶ ወለመልአከ ሕይወትሰ ሰቀልዎ በሚለው ሰላም ይጠናቀቃል፡፡

ገብረ ሰላመ በመስቀሉ እየተባለ እየተ ዘመረ ቀጤማውም ቤተ መቅደሱን ዞሮ በካህኑ ተባርኮ ለምእመናን ይታደላል፡፡ የቀጤማው አመጣጥና ምስጢርም ከአባታችን ከኖኅ ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው ምድር በማየ አይኅ /በጥፋት ውኃ/ በጠፋችበት ወቅት የኖኅ ታማኝ መልእክተኛ ርግብ የውኃውን መጉደል ያበሰረችው ቀጤማ ይዛ በመግባት ነው፡፡

ዛሬም ለሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች የኃጢአት ውኃ ጐደለ፣ የኃጢአት ውኃ ጠፋ በክርሰቶስ ሞትና ትንሣኤ ነጻነት ተሰበከ ታወጀ በማለት ካህናት ቄጠማ ይዘው ምእመናንን ያበሥሩበታል፡፡ በአጠቃላይ ሥርዓተ ሕማሙን፤ ሰሙነ ሕማማት ብለው የተለየ ሥርዓት አውጥተው አባቶቻችን ተግተው ያቆዩልንን ሥርዓተ መላእክት ልንጠብቀውም ልንጠቀምበት ይገባል፡፡
እንኳን ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ
ትንሳዔ

“እግዚአብሔርም ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ፥ የወይን ስካር እንደ ተወው እንደ ኃያልም ሰው፤”
 
             መዝሙር 78፥65

“.... ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነሥቶአል እንጂ በዚህ የለም።”
                 ሉቃስ 24፥5

ክርስቶስ ተንስዓ እሙታን !
በዐቢይ ኃይል ወስልጣን !
አሠሮ ለሰይጣን !
አግዐዞ ለአዳም !
ሰላም !
እምይእዜሰ!
ኮነ!
ፍሥሐ ወሰላም !


#እንኳን_አደረሳችሁ
​​👉 ከትንሣኤ እሁድ በኋላ ያሉ ዕለታት ስያሜ

ሰኞ

👉ማዕዶት ይባላል፡- ማዕዶት ማለት መሻገር፣ ማለፍ ማለት ነው፡፡ በዚህ ዕለት በፋሲካችን በክርስቶስ ትንሣኤ ከድቅድቅ ጨለማ ወደ ሚደነቅ ብርሃን፣ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከሲኦል ወደ ገነት፣ ከሃሳር ወደ ክብር መሻገራችንን እናስባለን፡፡

ማክሰኞ

👉ቶማስ ይባላል፡- በዚህ ዕለት ቶማስ ጌታን አይቶ ማመኑ፤ ጌታዬና አምላኬ ብሎ መመስከሩ ይዘከራል፡፡ ዮሐ. 20፡27-29

ረቡዕ

👉አልአዛር ይባላል፡- በዚህ ዕለት ትንሣኤና ሕይወት የሆነው ጌታ ኢየሱስ አልአዛርን ከሞት እንዳስነሳው እናስባለን፡፡ ክርስቶስ የሞትን ስልጣን የሻረ የሕይወት ራስ፤ የመቃብርን ሥርዓት ያጠፋ ትንሣኤ፡ በድልም ያረገ ንጉሥ መሆኑን እንመሰክራለን፡፡

ሐሙስ

👉አዳም ሐሙስ ይባላል፡- በዚህ ዕለት ለአዳም የተሰጠው ተስፋ እና የተገባለት ኪዳን እንደተፈጸመ አዳምና ልጆቹ ነጻ እንደወጣን እናስባለን፡፡

ዓርብ

👉ቅድስት ቤተክርስቲያን ይባላል፡- በዚህ ዕለት ቤተክርስቲያን በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ስለመመስረቷ ይሰበካል፡፡ ክርስቶስ ስለ እርሷ ራሱን አሳልፎ ሰጥቶ ቤዛ ሆኖ በደሙ አንጽቶ በትንሣኤው ድል ሰጥቶ እንዳከበራት ይነገራል፡፡ ቤተክርስቲያን ስንል ሕንፃውን ሳይሆን አማኞችን ነው፤ ክርስቶስ ለሕንፃ አልሞተምና፡፡

ቅዳሜ

👉ቅዱሳት አንስት ይባላል፡- በዚህ ዕለት ቅዱሳት አንስት የክርስቶስን አካል ሽቶ ለመቀባት ጨለማ አቋርጠው ወደ መቃብር መምጣታቸውና ትንሣኤውንም ቀድመው ማየታቸው ይሰበካል፡፡

እሁድ

👉ዳግም ትንሣኤ ይባላል፡- በዚህ ዕለት ክርስቶስ ለሦስተኛ ጊዜ ለደቀመዛሙርቱ ተገልጦ ሰላምን መስበኩ እና ሥልጣንን መስጠቱ ይሰበካል፡፡
ሰኞ ማዕዶት
ማዕዶት ማለት (ዐደወ-ተሻገረ) ከሚል የግእዝ ግስ የተወረሰ ሲሆን በጥሬው "መሻገር" ማለት ነው:: ይሕም በደመ ክርስቶስ ተቀድሰን: በትንሳኤውም ድኅነት ተደርጐልን መከራን: መርገምን: የኃጢአትን ባሕር: አንድም ባሕረ እሳትን መሻገራችንን ያመለክታል::
+ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከበረ ደሙ
*ከባርነት ወደ ነጻነት
*ከጨለማ ወደ ብርሃን
*ከሞት ወደ ሕይወት
*ከኃጢአት ወደ ጽድቅ
*ከሲዖል ወደ ገነት
*ከገሐነመ እሳት ወደ መንግስተ ሰማያት
አዳምንና እኛን ልጆቹን አሸጋግሮናል::
+አባታችን አዳምና ልጆቹ ከሲዖል የወጡት በዕለተ ዐርብ በሠርክ ቢሆንም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዚሕ ዕለት እዲታሰብ ታዛለች::
+ጌታችን ምርኮን ማርኮ: ጥጦስ መንገድ ጠራጊ ሆኖለት ወደ ገነት ሲያስገባቸው ለድንግል ማርያም አሳይቷታል:: እመ አምላክም በፍጹም ልቧ ደስ ተሰኝታለች:: አዳምና ልጆቹ እመቤታችንን ከላይ ሆነው እጅ ነስተዋታል:: እርሷ የድኅነታቸው ምክንያት ናትና::
=>አማናዊው ብርሃን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ጨለማችንን በምሕረቱ ያብራልን::
=>+"+ ክርስቶስም እኮ ስለ ሰው ኃጢአት አንድ ጊዜ ሞቶአል:: ኃጢአት የሌለበት ክርስቶስ ጻድቁ ስለ እኛ ሞተ:: ስለ ኃጢአታችን እኛን ወደ እግዚአብሔር ያቀርበን ዘንድ::
በሥጋ ሞተ: በመንፈስ ግን ሕያው ነው:: ነፍሳቸው ታስራ ወደ ነበረችበት ሔደ:: ቀድሞ ክደውት ለነበሩት ነጻነትን ሰበከላቸው:: +"+ (1ጴጥ. 3:18)
Forwarded from 𝚜𝚊𝚖𝚛𝚒-19
ማክሰኞ ቶማስ

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ትንሣኤው ሐዋርያት ተሰብስበው በነበረበት በዝግ ቤት ገብቶ ሲገለጽላቸው ሐዋርያው ቶማስ ከእነርሱ ጋር አልነበረም፡፡ ሐዋርያትም የጌታችንን ከሙታን ተለይቶ መነሣት ቢነግሩት ‹‹እኔ ሳላይ አላምንም›› አላቸው፡፡ በሚቀጥለው ሳምንትም ጌታችን ቶማስ በተገኘበት በድጋሜ  ተገለጠላቸው፡፡ ጌታችንም ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስን ‹‹ጣትህን ወደዚህ አምጣና በጎኔ አግባው፤ ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን›› ብሎ በጦር የተወጋ ጎኑን ፥ በችንካር  የተቸነከረ እጁንና እግሩን እንዲዳስሰው በማድረግ ትንሣኤውን  አረጋገጠለት፡፡ ቶማስም ሲዳስሰው እጅ ከእሳት እንደገባ ጅማት ስለተኮማተረ ‹‹ጌታዬ አምላኬም›› ብሎ መሰከረ፡፡  በኋላ ግን ፈውሶታል፤ ኢየሱስም ‹‹ስለ አየኸኝ አምነሀል ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዐን ናቸው›› አለው፡፡  ምንም አንኳን ድርጊቱ የተፈጸመው በዳግም ትንሣኤ ቢሆንም የሐዋርያው መታሰቢያ ሆኖ ዕለተ ማክሰኞ ‹ቶማስ› ተብሎ ተሰይሟል፡፡ (ዮሐ. ፳ ፥ ፳፬ -፴)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
#ክፉ_አሳብ

ልጆቼ! ከመጀመሪያውኑ ክፉ አሳብ ባታስቡ መልካም ነው፡፡ ካሰባችሁ ግን ቢያንስ አትናገሩት፡፡ በዚያው በሕሊናችሁ ውስጥ እያለ ዝም አሰኙት፤ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላም ወዳለመኖር ይኼዳል፡፡

እኛ ሰዎች ነን፡፡ በመኾኑም ብዙውን ጊዜ ክፉ፣ ያልተገቡና ጸያፍ ነገሮችን እናስባለን፡፡ ነገር ግን ቢያንስ እነዚህን አሳቦች አንናገራቸው፤ ቢያንስ ወደ ቃል አንለውጣቸው፡፡ ወደ ውጭ እንዳይወጡ አምቀን እንያዛቸው፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ እየከሰሙና እየደከሙ እየጠፉም ይኼዳሉ፡፡ አንድን እንስሳ ወደ ጉድጓድ ብትጥሉትና ጉድጓዱንም በመክደኛ ብትከድኑት ያ ወደ ጕድጓድ የጣላችሁት እንስሳ የሚተነፍሰውን አየር አጥቶ ይሞታል፡፡ ምናልባት ጥቂት ቀዳዳ ካገኘ ግን በዚያች ቀዳዳ በምትገባው አየር በሕይወት መቆየት ይችላል፡፡ ሲጨንቀውም እናንተን ክፉኛ ለመጉዳት ይዝታል፤ ከወጣም በኋላ ይጎዳችኋል፡፡ ልክ እንደዚሁ እናንተም በልቡናችሁ የተመላለሰውን ኩላሊታችሁ ያጤሰውን ክፉ አሳብ መውጫ ቀዳዳ እንዳይኖረው አድርጋችሁ ብትከድኑት (ብታፍኑት) ይሞታል፤ ከመኖር ወዳለመኖር ይለወጣል፡፡ በአንደበታችሁ በመናገር ጥቂት ቀዳዳ ከከፈታችሁለትና እንደ እንስሳው እንዲተነፍስ ከፈቀዳችሁለት ግን ክፉው አሳብ ክፉ ግብርን ይወልዳል፡፡ ያቆጠቁጣል፡፡ በአሳብ ሳለ ከጎዳችሁ በላይም በገቢር ተወልዶና ተለውጦ ክፉኛ ይጎዳችኋል፡፡

(#የክርስቲያኖች_መከራ #በቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ ገጽ 7➛በገብረ እግዚአብሔር ኪደ የተተረጎመ)
#እንኳን_ለእመቤታችን_ቅድስት_ድንግል_ማርያም_የልደት_በዓል_በሰላም_አደረሳችኹ
🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏
''ኢያቄም ወሐና ወለዱ ለነ ሰማየ:
ሰማዮሙኒ አስረቀት ለነ ፀሐየ:: ''

" ኢያቄምና ሐና ሰማይን ወለዱልን:
ሰማያቸው ደግሞ ፀሐይን አወጣችልን (ወለደች-አስገኘችልን) "
እንኩዋን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ

+*" 🌷ልደታ ለማርያም ድንግል🌷 "*+

ኢያቄም ወሐና ወለዱ ለነ ሰማየ:
ሰማዮሙኒ አስረቀት ለነ ፀሐየ::
" ኢያቄምና ሐና ሰማይን ወለዱልን:
ሰማያቸው ደግሞ ፀሐይን አወጣችልን (ወለደች-አስገኘችልን) "

=>የዓለማችን ወላጆች ነቢያት ሐዋርያትን: ጻድቃን ሰማዕታትን ወልደው ከብረዋል: ተመስግነዋል:: ኢያቄምና ሐና ግን ፍጥረት ሁሉ በአንድነት ቢሰበሰብ በእግሯ የረገጠችውን ትቢያ እንኩዋ መሆን የማይችል: የሰማይና የምድር ንግሥት: የእግዚአብሔርን እናት: እመቤታችን ማርያምን ወለዱልን::

+ኢያቄም ወሐና ለእግዚአብሔር የሥጋዌ አያቶቹም ተባሉ:: እስኪያረጁ ድረስ በመካንነት አዝነው ፀልየዋል:: ንጽሕናቸውና ደግነታቸው ተመስክሮላቸው ድንግል ማርያምን አግኝተዋል::

+እመቤታችን ከአዳም ስሕተት በሁዋላ ያለ ጥንተ አብሶ የተወለደች የመጀመሪያዋ ሰው ድንግል ማርያም ሆናለች:: (ኢሳ. 1:9)

+ለጨለማው ዓለም የብርሃን መቅረዝ ሆና ትጠቅመን ዘንድ: አንድም ትንቢቱና ምሳሌው ይፈጸም ዘንድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ ቀን: በሊባኖስ ተራራ ከ2,022 ዓመታት በፊት ተወልዳለች::

"ሙሽራዬ ሆይ! ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነይ" (መኃልይ. 4:8)

=>ከነገደ ይሁዳ የሚወለድ ቅዱስ ኢያቄም የሚባል ደግ ሰው ከነገደ ሌዊ (አሮን) የተወለደች ሐና የምትባል ደግ ሴት አግብቶ: በሕጉ ጸንተው: በሥርዓቱ ተጠብቀው ይኖሩ ነበር:: ነገር ግን በዘመኑ ሰዎች ልጅ የላችሁም በሚል ይናቁ ነበር::

+ኦሪታውያን ልጅ የሌለውን "ኅጡአ በረከት-ከጸጋ እግዚአብሔር የራቀ" ነው ብለው ያምኑ ነበር:: ኢያቄምና ሐና ልጅ እንዲሰጣቸው ሲያዝኑ: ሲጸልዩ ዘመናቸው አልፎ አረጁ::
እነሱ ግን የሚያመልኩት የአብርሃምና ሣራን አምላክ ነውና ተስፋ አልቆረጡም::

+የለመኑትን የማይነሳ ጌታ በስተእርጅናቸው ድንቅ ነገርን አደረገላቸው:: አንድ ቀን እርግቦች ከጫጩቶቻቸው ጋር ሲጫወቱ የተመለከተች ቅድስት ሐና ፈጽማ አለቀሰች:: "እንስሳትና አራዊትን: እጽዋትን ሳይቀር በተፈጥሯቸው እንዲያፈሩ የምታደርግ አምላክ ምነው ሐናን ድንጋይ አድርገህ ፈጥረሃታልን?" ብላ አዘነች::

+ይህን የተመለከተ ቅዱስ ኢያቄም ወደ ተራራ ወጥቶ ሱባኤ ያዘ:: ለ40 ቀናትም ሲጸልይና ሲማለል ቆየ:: በ40ኛው ቀን 2ቱም ሕልምን ያልማሉ:: እርሱ:- ነጭ ርግብ ሰማያትን ሰንጥቃ ወርዳ: በሐና ቀኝ ጀሮ ገብታ: በማሕጸኗ ስትደርስ አየ::

+እርሷ ደግሞ:- የኢያቄም በትር አብቦ: አፍርቶ: ጣፋጭ ፍሬውን ሰው ሁሉ ሲመገበው ታያለች:: ቅዱስ ኢያቄም ከሱባኤ እንደ ተመለሰ ያዩትን ተጨዋውተው "ፈቃደ እግዚአብሔር ይሁን" አሉ:: ለ7 ቀናትም በጋራ እግዚአብሔርን ሲለምኑ ሰነበቱ::

+በ7ኛው ቀን (ማለትም ነሐሴ 7) መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ክንፉን እያማታ ወደ እነርሱ ወረደ:: "ዓለም የሚድንባት: የፍጥረት ሁሉ መመኪያ የሆነች ልጅ ትወልዳላችሁ" ብሏቸው ተሠወራቸው:: እነርሱም ደስ ብሏቸው እግዚአብሔርን አመሰገኑ::

+እንደ ሥርዓቱም አብረው አድረው እመ ብርሃን ተጸነሰች::
"ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተጸነስኪ . . .
ድንግል ሆይ! ኃጢአት ባለበት ሥጋዊ ፍትወት የተጸነስሽ አይደለም" እንዳለ ሊቁ:: (ቅዳሴ ማርያም)

+"ለጽንሰትኪ በከርሥ: እንበለ አበሳ ወርኩስ: ወለልደትኪ እማሕጸን ቅዱስ . . ."
"ድንግል ሆይ! መጸነስሽ ያለ በደል (ያለ ጥፋት) ነው: የተወለድሽበት ማሕጸንም ቅዱስ ነው . . ." (መጽሐፈ ሰዓታት, ኢሳ. 1:9)

+እመቤታችን ነሐሴ 7 ቀን ተጸንሳ ግንቦት አንድ ቀን ተወልዳለች::

=>የእመቤታችን የዘር ሐረግ:-
*አዳም-ኖኅ-አብርሃም-ይስሐቅ-ያዕቆብ=
*በእናቷ:-
-ሌዊ-ቀዓት-እንበረም-አሮን-ቴክታና በጥሪቃ-ሔኤሜን-ዴርዴን-ቶና-ሲካር-ሔርሜላና ማጣት-ሐና::
*በአባቷ በኩል:-
-ይሁዳ-ፋሬስ-ሰልሞን-ቦኤዝ-እሴይ-ዳዊት-ሰሎሞን-ሕዝቅያስ-ዘሩባቤል-አልዓዛር-ቅስራ-ኢያቄም ይሆናል::

+ለጨለማው ዓለም የብርሃን መቅረዝ ሆና ትጠቅመን ዘንድ: አንድም ትንቢቱና ምሳሌው ይፈጸም ዘንድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም: በሊባኖስ ተራራ ከ2,026 ዓመታት በፊት ተወልዳለች::

=>የእመቤታችን ድንግል ማርያም ጣዕሟ: ፍቅሯ: ጸጋዋና በረከቷ ይደርብን::

=>ግንቦት 1 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም (ልደታ)
2.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
3.ቴክታና በጥሪቃ
4.አባ ሕርያቆስ ዘሃገረ ብሕንሳ (የእመቤታችንን ቅዳሴ የደረሰበት)

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ራጉኤል ሊቀ መላዕክት
2.ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
3.ቅዱስ ሚልኪ ትሩፈ ምግባር

=>+"+ መሠረቶቿ በተቀደሱ ተራሮች ናቸው::
ከያዕቆብ ድንኩዋኖች ይልቅ እግዚአብሔር የጽዮንን ደጆች ይወዳቸዋል::
የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ! በአንቺ የተደረገው ድንቅ ነው . . .
ሰው እናታችን ጽዮን ይላል::
በውስጧም ሰው ተወለደ::
እርሱም ራሱ ልዑል መሠረታት:: +"+ (መዝ. 86:1-6)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

https://t.me/kaletsidkzm
#እንደ_ወሮቻችን_ኑ_በእርሷ_እንጀምር
(ዲ/ን ሕሊና በለጠ)

የወር መጀመሪያ የእርሷ ልደት ነው። ወሮቻችን ኹሉ በእርሷ ልደት ጀምረው በመጨረሻው የብሉይ ኪዳን ነቢይና የሐዲስ ኪዳን መንገድ ጠራጊ በመጥምቁ ዮሐንስ ያበቃሉ። እርሱ የብሉይን ማለፍና የሐዲስን መምጣት በማብሰር መንገድ እንደ ጠረገ ፣ የብሉይ ምሳሌ የኾነውን የአሮጌውን ዓመት ማለፍና የሐዲስ ምሳሌ የሚሆነውን የአዲሱን ዓመት መምጣት ያበሥር ዘንድ መስከረም አንድ ቅዱስ ዮሐንስ እንዲባል ኾነ። ልክ እንዲሁ ደግሞ የአሮጌው ወር መጨረሻ ላይ ወርኀዊው መታሰቢያው በመሆኑ በእርሱ ትምህርት ላይ ቆመው፣ እርሱ መንገድ ጠርጎላቸው ሐዲስን እንዳዩት የብሉይ ኪዳን ሰዎች፣ እኛም በእርሱ መታሰቢያ በዓል ላይ (በ30) ላይ ቆመን ሐዲስ ወርን እናያለን። እነርሱ በእርሱ ትምህርት ጸንተው የአሮጌውን ኪዳን መጨረሻነት ተረድተው የሐዲስ ኪዳንን ሐዲስ ሕይወት "1" ብለው እንደ ጀመሩ፣ እኛም 30 ላይ ቆመን የአሮጌው ወር ብልየታችንን መጨረሻነት ተረድተን የአዲሱን ወር ሐዲስ ሕይወት "1" ብለን እንጀምራለን። "1" ደግሞ ልደታ ለእግዝእትነ ነው - የኹሉ ነገር ጅማሬ የኾነችው የእመቤታችን ልደት።

ወሮቻችን ኹሉ በእርሷ ልደት ስለሚጀምሩ ቀና ናቸው። ወሩን እርሷን አክብሮ፣ ዘክሮ ስሟን ጠርቶ የሚጀምር ሰው መንገዱ የቀና ነው። በእርሷ ጀምሮ ያፈረ የለም።

የአዳም የመዳን ተስፋ "እምወለተ ወለትከ" በሚለው እርሷን በሚያነሣው ቃል ኪዳን ተጀምሮ ፍጻሜው ያማረ ሆነ። ኖሕ ከጥፋት ውኃ መዳኑን ለእርሷ ምሳሌ በሚሆን መርከቡ ጀምሮ አላፈረም። ሙሴ እስራኤልን ከፈርዖን የማዳን ሥራውን የጀመረው ሐመልማሉ እሳቱን ሳያጠፋው እሳቱም ሐመልማሉን ሳያቃጥለው ባየው ድንቅ ምሥጢር ነው፤ ይህ ደግሞ እሳተ መለኮት ሐመልማል የሆነች እርሷን ላለማቃጠሉና ላለመዋጡ፣ በእርሷ የተፈጸመውን ተዋሕዶ የሚያሳይ ነው።

ሠለስቱ ዮሐንሶችም እንዲሁ ናቸው። ዮሐንስ ፍቁረ እግዚእ የፍቅር እናትን ተቀብሎ የጀመረው ሕይወት "ነባቤ መለኮት" አስብሎታል። ዮሐንስ መጥምቅ በእናቱ ማህጸን ሳለ ለእርሷ ሰግዶ የጀመረው ሕይወት "ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከእርሱ የሚበልጥ አልተነሣም" አስብሎታል። (ማቴ.11:11)። አፈ በረከት ዮሐንስ ስለ እርሷ አመሥጥሮ የጀመረው ሕይወቱ "አፈ ወርቅ" አስብሎታል። (ግንቦት 1 ዓመታዊ በዓሏ እንደ ሆነው ግንቦት 12 የሊቁ ፣ ግንቦት 16ም የሐዋርያው በዓል መሆኑን ልብ ይሏል)

እርሷ የወራችን ብቻ ሳይሆን የሰማይና የምድርም መጀመሪያ ናት። (ሰማይና ምድር በውስጣቸውም ያሉት ስላንቺ ተፈጠሩ እንዲል ድርሳነ ማርያም)። ሰማይና ምድር ሳይጋፉ ፣ ሳይራበሹ "ይህ የኔ ክልል ነው፣ ይህ የኔ ወሰን ነው" ሳይባባሉ ሺህ ዘመናትን በፍቅር የጸኑት እርሷን መጀመሪያቸው ስላደረጉ ይሆን?

እርሷ የአዳምና ሔዋን መጀመሪያ ናት። ስለ እርሷ አዳምና ሔዋን ተፈጥረዋል። (መላእክትን ከፈጠረ በኋላ በጸፍጸፈ ሰማይ ቀጥሎ ማንን እንደሚፈጥር ያሳያቸው ነበር። ቀጥሎ የሚፈጠረው ሰው: አምላኩን እንደሚክድ ሲያዩ መላእክቱ "አትፍጠረው" አሉ። ድንግልን አሳያቸው፤ ሊያዩት የሚጓጉለትን አምላክን መውለዷን ሲያዩ "ይህችን ፍጠርልን" ብለው ተማጸኑ። "ካለ እርሱ (አዳም) እርሷ አትገኝም" ቢላቸው "እንግዲያውስ ስለ እርሷ እርሱን ፍጠርልን" አሉ። \ትርጓሜ. ኢዮብ? ኩፋሌ?)። ነገረ ልደቱ በእርሷ የጀመረለት አዳም ነገረ ልደቱ በእርሷ እንዳልጀመረለት ሳጥናኤል ወድቆ አልቀረም - ተነሣ እንጂ።

በእርሷ የሚጀምር ቢወድቅ እንኳን ይነሣል።

መጽሐፍ ቅዱስ ካምና ያፌትን ትቶ የሴም የትውልድ ሐረግን ለምን ተረከ? እመቤታችን ከሴም ዘር ስለምትወለድ ነው። ከሌሎች ሕዝቦች መኻል እስራኤልን መርጦ ለምን ቀጠለ? እመቤታችን ከእስራኤል ስለምትወለድ ነው። የካም ዘር የሆነውን መልከጼዴቅን ትቶ የሴም ዘር ስለ ሆነው ስለ አብርሃም እየተረከ ለምን ቀጠለ? አብርሃም ስለሚበልጥ ነውን? አይደለም። መልከጼዴቅ ታላቅ አብርሃም ታናሽ እንደ ሆነ ቅዱስ ጳውሎስ ነግሮናል። (ዕብ.7)። ታዲያ ምክንያቱ ምንድን ነው? እርሷ ከአብርሃም ዘር ስለምትወለድና ጌታችንና አምላካችንም ወልደ ዳዊት ወልደ አብርሃም ስለሚሆን ነው። መጽሐፍ ቅዱሳችን እንኳን እርሷን በሩቅ ዐይቶና በእርሷ ላይ ተመሥርቶ የተጻፈ ነው።

ድኅነታችን በእርሷ ምክንያትነት የተገኘ ነው። "አንዲት ዘር" የሆነች እርሷን ባያስቀርልን ኖሮ ከምድር በታች መውደቃችን ለመቀበር እንጂ ተዘርቶ ለማበብ አይሆንም ነበር።

ኢትዮጵያውያን በእርሷ በመጀመር አንታማም። በእርሷ እየጀመርን ከብዙ ውድቀትም ተርፈናል፣ ተነሥተናል።

እርስ በእርስ የመባላታችንም ሆነ የመጠላላታችን ነገር ምናልባት የፍቅር እናት የሆነች እርሷን ዘንግተን የመጡብን ይሆኑ ይሆን? ምናልባትም እርሷን የማይጠሩ ዜጎች በርክተው እኛም በዚህ ደክመን ይሆን?

ኑ ልክ እንደ ወሮቻችን በእርሷ እንጀምር። ያለፈውን ብልየት ኹሉ በመጥምቁ ትምህርት ላይ ቆመን እንሻገርና እርሷን ይዘን እንጀምር።

ባለፈው ወር ያለቀስን፣ ያዘንን፣ የወደቅን፣ የከፋን፣ ያቄምን፣ የሞትን፣ የዘረፍን፣ የገደልን፣ የዘሞትን በክፋትና በሥጋ ሥራ ያረጀን ኹሉ በመጥምቁ ትምህርት ላይ እንቁምና ብሉዩን እንሰናበተው፤ ሐዲሱን ሕይወት ልክ እንደ ወሮቻችን "1" ብለን በእርሷ እንጀምር።
🔔
✥✥✥
ሰዓት
✥ተንስኡ ለጸሎት✥

#መዝሙረ ዳዊት 118_25
አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አድን አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አቅና።

#በዚህ ሰዓት ይህንን የምታዩ የምታደርጉትን ለ2 ደቂቃም ብትሆን ተውና ልዑል እግዚአብሔርን እያሰብን አንድ አባታችን ሆይ እንጸልይ

የእግዚሐብሔር ልጅ ጌታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ማረን

የእግዚሐብሔር ልጅ ጌታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ማረን

የእግዚሐብሔር ልጅ ጌታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ማረን