የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ሕዝብ ግንኙነት-Holy Trinity University PR
2.39K subscribers
1.6K photos
8 videos
54 links
Download Telegram
ለትምህርት ፈላጊዎች በሙሉ!!
❤6🥰1👏1
ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን መመረቃቸውን አስመልክቶ በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ መርሐ ግብር ተካሔደ
____
ቅስዩ፣ ነሐሴ 30 ቀን 2018 ዓ.ም. — በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ/ፕሬዚዳንት ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ (ዶ/ር) የዶክትሬት ዲግሪ ምርቃት መርሐ ግብረሰ በዩኒቨርሲቲው አዳራሽ በልዩ ሁኔታ ተከበረ።

በምርቃት መርሐ ግብሩ ላይ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያና የድርጅት ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅና የክፍል ኃላፊዎች፣ የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ የአስተዳደር ሓላፊዎችና ሠራተኞች፣ የተጋበዙ እንግዶች፣ ቤተሰቦችና ወዳጆች ተገኝተዋል።

የበዓሉ መርሐ-ግብር በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሊቃውንትና ካህናት በቀረበ ጸሎተ ወንጌል ተጀምሯል። በመቀጠልም በመልአከ ኃይል አባ ጽጌ ድንግል ፈንታሁን የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ም/ፕሬዚዳንት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ቀርቧል።

በመርሐ-ግብሩ የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሊቃውንትና መምህራን ያቀረቡት ወረብ የዝግጅቱን መንፈሳዊ ድባብ ያጎላ ሲሆን፣ "ፍኖተ ሕይወት" መጽሔት ምርቃትም በመስተንግዶ ኮሚቴ አቅራቢነት በብፁዓን አባቶች ተከናውኗል።
በዕለቱ የብፁዕ አቡነ ፊልጶስን የትምህርት ጉዞ፣ የአካዳሚክ ዝግጅትና የዶክትሬት ምረቃ ሂደት የሚያስቃኝ ዘጋቢ ፊልም በራማ ሚዲያ ቀርቧል። ፊልሙም ብፁዕነታቸው በትምህርት የተጓዙበትን ሂደትና በእውቀት ፍለጋ ያሳለፉትን የትጋት ጉዞ በምስልና በድምፅ ዳስሷል።

በመቀጠልም የብፁዕነታቸው የዶክትሬት ዲግሪ መመረቂያ ጽሑፍ ዳሰሳ የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ም/ፕሬዚዳንት በሆኑት በፕሮፌሰር አባ ኃይለ ገብርኤል ግርማ፣ የዶክትሬት ጥናቱን ይዘትና አካዳሚክ ጠቀሜታ ያስቃኘ ሆኖ ቀርቧል።

በዚሁ መርሐ-ግብር መምህር ክነፈ ርግብ ያቀረቡት ቅኔ ለዝግጅቱ ያማረ ድባብ ሰጥቷል። ከዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብና ከተለያዩ አካላት የተዘጋጀው የስጦታ መርሐ-ግብርም ተከናውኗል።

ከስጦታ መርሐ-ግብሩ በኋላ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ (ዶ/ር) መልእክትና ምስጋና አስተላልፈዋል። ብፁዕነታቸው በመልእክታቸው በትምህርት ቆይታቸው ያሳለፉትን ሂደት፣ በጥናት ያገኙትን ዕውቀትና የዶክትሬት ጥናታቸውን በማስመልከት ገለጻ አድርገዋል። እምነት፣ እውነትና ዕውቀት የትምህርት መሠረታዊ መርሆች መሆናቸውንም አጽንዖት ሰጥተዋል።

በተለይም በትምህርት ሒደት ላይ ያለ ሰው ለስኬት ሊከተላቸው የሚገቡ አምስት ዋና ዋና ነጥቦችን አብራርተዋል። እነዚህም፦
1. ግልጽ ዓላማና ግብ መያዝ፤
2. ጽናትና ራስን መግዛት፤
3. ጊዜን በውጤታማነት መጠቀም፤
4. ትክክለኛ የጥናት ስልትና ዕቅድ መከተል፤
5. የአካባቢና የማኅበራዊ ድጋፍን በአግባቡ መጠቀም ናቸው።
ብፁዕነታቸው እነዚህ መርሆች በትምህርት ጉዞ ላይ ላሉ ተማሪዎችና ዕውቀትን ፍለጋ ላይ ለሚገኙ ሁሉ አስፈላጊ መሠረቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በመጨረሻም ብፁዕነታቸው በዶክትሬት ትምህርታቸውና በምረቃው ሂደት የተሳተፉ መምህራንን፣ የዩኒቨርሲቲውን ማኅበረሰብ፣ በዕለቱ የተገኙ አባቶችን፣ ዕንግዶችንና በሒደቱ የተሳተፉትን ሁሉ አመስግነዋል።

የመርሐ-ግብሩ መጨረሻ ላይ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስን ቃለ ምዕዳንና ቃለ በረከት እንዲሰጡ ጋብዘዋል።

ብፁዕ አቡነ ማርቆስም በቃለ ምዕዳናቸው ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የደረሱበት የትምህርት ደረጃ ለሌሎች ወጣት ሊቃነ ጳጳሳትና ለትውልዱ አርአያ መሆኑን ገልጸዋል። ብፁዕነታቸው በትምህርትና በአገልግሎት የተገነባው የብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ጉዞ፣ "ዘመኑን ዋጁ" የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል በተግባር የሚያሳይ ምሳሌ መሆኑን መስክረዋል።

የዶክትሬት ዲግሪውን በማግኘታቸውም ብፁዕ አቡነ ፊልጶስን አድንቀውና አመስግነው፣ ይህ ስኬት ለሌሎች ወጣት ሊቃነ ጳጳሳትና ለቤተ ክርስቲያን ልጆች በትምህርት የበለጠ እንዲገሰግሱ የሚያነሣሣ አርአያ መሆኑን ገልጸዋል። ብፁዕነታቸውም ቃለ በረከት በመስጠት መርሐ-ግብሩን በጸሎት አጠናቀዋል።

ይቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ሕዝብ ግንኙነት
“ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ (ኤፌ. 5፡16)።

ዕድሜ ለንስሓ እየሰጠ፤ አገልግሎታችንን እየባረከ፤ በአባትነት ፍቅሩ ከዘመን ወደ ዘመን የሚያሸጋግረን ልዑል እግዚአብሔር እንኳን ከዘመነ ቅዱስ ማርቆስ 2018 ዓ.ም ወደ ዘመነ ቅዱስ ሉቃስ 2019 ዓ. ም በሰላም አሸጋግራችሁ።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በስብከተ ቃሉ ላመኑ፣ በሞተ እስጢፋኖስ በዓለም ሁሉ ለተበተኑ ምእመናን በላከላቸው መልእክት ውስጥ ያለፉበትን የኃጢአት ዘመን ትተው፣ በንስሓ ታጥበው፣ ዘመኑን እየተመለከቱ በማስተዋል በሃይማኖት እንዲኖሩ የጻፈላቸው የሕይወት ቃል ነው።

የተወደዳችሁ የልዑል እግዚአብሔር ልጆች! ዘመን ተለውጦ አዲስ ዘመን ሲተካ ለንስሓ አዲስ ጊዜ እየተሰጠን መኾኑን መዘንጋት የለብንም። እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጅ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንደት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ “ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ (ኤፌ. 5፡16) እንድል ቅዱስ መጽሐፍ በዚህ ከፉ ዘመን ራስን በመግዛትና በመቆጣጠር ቸግርን መጋፈጥና ማለፍ የክርስትና ግደታችን መሆኑን መዘንጋት የለብንም።

​የሰው ልጅ ያለፈ ሕይወቱን እየገመገመ፣ መተው ያለበትን እየተወ፣ ከስሕተቱ ተምሮ ንስሓ እየገባ፣ በምክረ ካህን ራሱን እየለወጠ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውን ነገር ፈትኖ እየመረጠ ክርስቲያናዊ ሥርዓትን ጠብቆ እንዲኖር በእግዚአብሔር ታዝዟል።

ነቢዩ ዳንኤል “ጥበብና ኃይል ለእርሱ ነውና የእግዚአብሔር ስም ከዘላለም እስከ ዘላለም ይባረክ፤ ጊዜያትንና ዘመናትን ይለውጣል” (ዳን 2፥20) በማለት እግዚአብሔር በጥበቡ ጊዜያትንና ዘመናትን እንደሚለውጥ ነግሮናል። አምላካችን በጥበቡ ዘመንን ሲለውጥ የሰው ልጅም ከቆመበት ሥፍራ እግዚአብሔርን ደስ ወደሚያሰኝ ተግባር እንዲቀርብና በተሰጠው ዘመን ሰውንም እግዚአብሔርንም እንዲያገለግል እንጂ የዚህ ዓለም ምርኮኛ እንዲሆን አይደለም።

​በመጽሐፍ እንደተነገረን የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኙት ነገሮች ማለትም ፍቅርን፣ በጎነትን፣ የዋሕነትን፣ ከኃጢአት ርቆ በንስሐ ጸንቶ መኖርንና በጥበብ መመላለስን የማንነቱ መገለጫ ያደርግ ዘንድ ነው። በአዲሱ ዓመትም በልባችን መታደስ ተለውጠን ከኃጢአት ርቀን በንስሐ ጸንተን ሕገ እግዚአብሔርን እየጠበቅን ዘመኑን መስለን ሳይሆን ዘመኑን ዋጅተን የእግዚአብሔር መንግሥት ወራሾች ለመሆን መዘጋጀት ይኖርብናል።

​የተወደዳችሁ በሩቅም በቅርብም የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያዊያት “በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ”(ኤፌ 4፥3) ብሎ እንደተናገረው በአዲሱ ዓመት አሮጌውን የመለያየት የዘረኝነት፣ የምንደኝነት፣ የጸብ፣ የመወሻሸት፣ የመገፋፋት፣ የመጠፋፋት፣ ወዘተ... አመል ፀባያችንንና ልምዳችንን በማስወገድ ለአንድነት፣ ለፍቅር ለሰላም፣ ለይቅርታ፣ ለእውነት፣ ለበረከት የተዘጋጀን የክርስቶስ መለእክተኞች መሆን እንደሚገባን በአጽናዖት ለማሳሰብ እወዳለሁ። አዲሱ ዓመት የንስሓ፣ የይቅርታ፣ የሰላም፣ የደስታ፣ የፍቅር ይሁንልን!

አባ ፊልጶስ
የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት፤
የደቡብ ኦሞና አሪ ዞኖች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
መስከረም 1 ቀን 2019 ዓ.ም
🙏4❤3
Media is too big
VIEW IN TELEGRAM
በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ለምትገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናት እና ምዕመናን በሙሉ!


በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርስቲ በ2018 ዓ.ም በርቀት እና በኦንላይን ዘርፍ በዲግሪ መርሐ ግብር የነገረ መለኮት ትምህርትን ለማስተማር ከነሐሴ  20 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ጥቅምት 19 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ የአዲስ ተማሪዎችን ምዝገባ እያካሄደ ይገኛል፡፡


ስለሆነም መስፈርቱን የምታሟሉ በዩኒቨርስቲው የርቀት እና በይነ መረብ ኮሌጅ በአካል ወይም በወኪል በመቅረብ ዋናውን የትምህርት ማስረጃችሁንና የማይመለስ ፎቶ ኮፒ በማቅረብ መመዝገብ የምትችሉ መሆኑን እናሳውቃለን፡፡


ማሳሰቢያ፡ ሁሉም አመልካቾች ከሚኖሩበት አጥቢያ ቤተ ክርስቲን የሰበካ አባልነት የድጋፍ ደብዳቤ እና 4 ጉርድ ፎቶ ግራፍ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል

ለበለጠ መረጃ በስልክ ቁጥር +251949000333 እና +251949000777 ይደውሉ፡፡

በቴሌግራም ቻናላችን @HTUCODEE ይከታተሉን
❤7