Haramaya Unversity
12.4K subscribers
953 photos
9 videos
4 files
87 links
This channel is an official telegram channel of Haramaya University. Building the Basis for Development!
Download Telegram
የከፍተኛ ትምህርትና የምርምር ጥራትን ለማምጣት ያለሙ የለውጥ ስራዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ ተገለጸ፡፡
፡፡፡፡፡፡
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ እና ሚኒስትር ዴኤታዎች የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ የስራ እንቅስቃሴን ዛሬ ጎበኝተዋል።

ከጉብኝቱ በኃላ ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ እንዳሉት በከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ዘርፉ የሚካሄዱትን ዋና ዋና የለውጥ ስራዎች መሸከም የሚችሉ ተቋማትንና አደረጃጀቶችን መገንባት ይቻል ዘንድ የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ እና የከፍተኛ ትምህርት ስትራቴጂክ ማዕከልን ወሳኝ ሚና ሰጥቶ በማደራጀት ለማጠናከር ያለመ የለውጥ ስራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡

ሚኒስትሩ እንደገለፁት በሁለቱ ተቋማት ላይ የለውጥ ስራዎችን በመስራት እንደየተልዕኳቸው በተቋማቱ የመምህራን ምዘናና ጥራት ማዕከል፣ የማማከር አገልግሎቶች፣ የግብዓት መሟላትን የሚያጠና፣ የሚመዝንና የሚያረጋግጥ ከዚያም እውቅና የሚሰጥ ማዕከል፣ የብቃት ማረጋገጫ ላብራቶሪ፣ አማራጭ የትምህርት ቴክኖሎጂ አቅርቦት ላይ የሚሰራ እንዲሁም የሙያ ብቃት ማረጋገጫ እና የእውቀት አስተዳደር ስርዓት የሚፈጥር፣ የምርምር ሂደቱን የሚመዝንና የጆርናል ጥራት ላይ የሚሰሩ ማዕከላትን ወ.ዘ.ተ. በማደራጀት በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ጥራት ለማምጣት እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡

ለውጡ እውን ሲሆን ከመንግስትም ሆነ ከግል ተቋማት የሚወጡ የጥናትና ምርምር ውጤቶች እና ተመራቂዎች የሚመዘኑበት ሂደትም ይፈጠራል ብለዋል፡፡ አለምአቀፍ ተወዳዳሪ መሆን የሚቻለው የመምህራን ጥራት ላይ በመስራትና የመረጃ ቋት በማዘጋጀት መሆኑን ገልፀው ለዚህም የመምህራን አቅም ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራትና ከዚያም ምዘና አካሂዶ ውጤታማ የሆኑትን በመለየት የሙያ ፍቃድ በመስጠት በሚያገኙት ደረጃ መሰረትም ጥቅማ ጥቅሞችን በማመቻቸት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ እንዲሁም ኢትዮጵያውያን ፕሮፌሰሮችን ለይቶ እውቅና የሚሰጥ የሽልማት ተቋም ማቋቋም የእቅዱ አካል መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይም በአገሪቱ የሚገኙ የግልም ይሁን የመንግስት ዩኒቨርቲዎች ባላቸው ግብዓት፣ አቅርቦት፣ የሰው ኃይልና ሌሎች መመዘኛዎች መነሻነት ደረጃዎች እንደሚወጣላቸውና ደረጃውን ያላሟሉ እየተለዩ ተማሪዎች እንዳይቀበሉ የማድረግ ስራዎች እንደሚሰሩም አብራርተዋል፡፡

የለውጥ ስራዎቹ እውን እንዲሆኑ ተቋማት በቅንጅትና በኃላፊነት እንዲሁም በተጠያቂነት በማይደራረብ ሁኔታም ተልዕኳቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡ ይሄንንም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የህግ ማዕቀፍ፣ አዋጅ፣ መመሪያና ደንቦችን በማዘጋጀትና በማስጸደቅ ለውጡን የሚደግፍና የሚመራ ይሆናል ብለዋል፡፡

ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ የሰው ኃይላችንን የስልጠና መሳሪያዎች በተሟሉበትና ጥራቱን ባስጠበቀ ሁኔታ ማሰልጠን ከቻልን በሂደት የሰው ኃይል ለዓለም ገበያ የማናቀርብበት ምክንያት አይኖርም ለዚህም የስርዓተ ትምህርት ማዕቀፍ ማዘጋጀት፣ ማሻሻልና ጥራት ላይ ማተኮር ያስፈልጋል ሲሉ አብራርተዋል፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በበኩላቸው በከፍተኛ ትምህርትና ምርምር ስራችንን ለማሳካት ስኬቶቻችንን በማጉላት እና በጉድለታችን ላይ በመረባረብ ቀጣይ ጉዟችንን ውጤታማ ለማድረግ በቁርጠኝነት መነሳት ያስፈልጋል ብለዋል ፡፡ ኤጀንሲው ተልዕኮውን በመወጣት ወደ ትክክለኛ ገፅታው ለመመለስ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት አሳስበው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማመቻቸት ያለውን ቁርጠኝነት ጠቁመዋል፡፡
ጊዜው የዝግጅት ምዕራፍ ማጠቃለያ እንደመሆኑ በትኩረት ሊታይ የሚገባው ላይ እንዲያተኩር አሳስበው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ተልዕኮ መወጣትን ከመፈተሽ አንፃር ታቅዶ ሊሰራበት ይገባልም ብለዋል፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሙሉ ነጋ በበኩላቸው ኤጀንሲው በዩኒቨርስቲዎች የውስጥ የትምህርት ጥራት ቁጥጥርን ማጠናከር ላይ መስራት እንደሚገባው ገልፀው ኤጀንሲው የከፍተኛ ትምህርት አዕምሮ ሆኖ መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡ ጥራት ላይ ለመስራት ሁላችንም ዝግጁ ነን፡፡ የሰው ኃይል ብቻ ሳይሆን ተናባቢ እና ተጠያቂነት ያለበት ስርዓት ለመፍጠር መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በውይይቱ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ እንዳሉት እንደአገር ትላልቅ ኃሳቦችን ማድመጥም ሆነ መተግበር የሚችል አመራር ስላለ ጠቃሚ፣ የተመዘኑና የተጠኑ የለውጥ ኃሳቦችን በማመንጨት ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አንዷለም አድማሴ ኤጀንሲው የተቋቋመበት ዋና ዓላማ እና ተልዕኮን ለማስፈፀም ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች ጠቁመው በጋራ በመስራትና ችግሮቹን በመቅረፍ እንዲሁም የለውጥ ስራዎቹ ላይ በማተኮር የትምህርትና ምርምር ጥራት ለማምጣት የሚሰራውን ስራ እንደሚደግፍ ገልጸዋል፡፡

በማጠቃለያው ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ የተለያዩ የስራ መመሪያዎችን ያስተላለፉ ሲሆን የመምህራን አቅም ግንባታ ስራው ትኩረት ተሰጥቶት በቶሎ እንዲጀመር፣ ዓለማቀፋዊነት ላይ ትኩረት እንዲሰጥ እና በውይይቱ የተገለፁትን የለውጥ ስራዎች ወደመሬት ማውረድ የሚቻልበት ዝግጅት እንዲደረግም አሳስበዋል፡፡ ተቋምንና ስርዓትን መገንባት፣ ተልዕኮ መፈጸምና ማስፈጸም የሚችል አቅም ግንባታ ስራዎች ላይ ትኩረት ሰጥተን እንሰራለንም ብለዋል፡፡

በውይይቱ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱም ትምህርትን መልሰው ለማስቀጠል እንዲችሉ በተዘጋጀው ፕሮቶኮል መሰረት መገምገም ይቻል ዘንድ ግብረ ኃይል መቋቋሙም ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓታት በተደረገ ምርመራ 872 ሰዎች በኮሮናቫይረስ ተይዘዋል
////////////////////////////////////////////////////////////////////////////
ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በተደረገ 7,726 የላቦራቶሪ ናሙና ምርመራ 872 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸውን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በአጠቃላይ እስካሁን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 77,860 ደርሷል።
በሌላ በኩል 648 ሰዎች ከበሽታው ያገገሙ ሲሆን በአጠቃላይ እስካሁን ድረስ 32,325 ሰዎች ከበሽታው ማገገማቸውን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
ዩኒቨርስቲዎችን መልሶ ለመክፈት የሚያስችል የዝግጅት ምዕራፍ ግምገማ በሁሉም ዩኒቨርስቲዎች እየተካሄደ ነው፡፡
፡፡፡፡፡፡፡፡፡
ዩኒቨርስቲዎችን መልሶ ለመክፈት ውሳኔ ላይ መደረሱን ተክትሎ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የተቋቋመ ግብረኃይል ዩኒቨርስቲዎቹ ያሉበትን የዝግጅት ሁኔታ በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ እንዲቻል የመስክ ግምገማ እያካሄደ ይገኛል።

ግብረኃይሉ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከጤና ሚኒስቴር ጋር ሆኖ ባዘጋጀው የዝግጅት ፕሮቶኮል መሰረት የዩኒቨርስቲዎቹን የዝግጁነት ሁኔታ ይገመግማል፡፡

ማንኛውም ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን መቀበል የሚያስችል ሁኔታ ላይ መሆን አለመሆኑ የሚታወቀው በመስክ ግምገማው በተጠናቀረው መረጃ መሰረት ሲሆን ውጤቱ ግምገማው ከተጠናቀቀ በኃላ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ይገልጻል።
በኢትዮጵያ 959 ተጨማሪ ሰዎች ኮሮናቫይረስ ሲገኝባቸው፤ 735 ሰዎች ደግሞ አገግመዋል
***********************
ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በተደረገ 8 ሺህ 101 የላቦራቶሪ ምርመራ 959 ሰዎች ኮሮናቫይረስ እንደተገኘባቸው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
በኢትዮጵያ በአጠቃላይ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 78 ሺህ 819 ደርሷል።
በሌላ በኩል በትናንትናው ዕለት 735 ሰዎች ከበሽታው ማገገማቸውን ተከትሎ በአጠቃላይ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 33 ሺህ 60 ሆኗል።
ባለፉት 24 ሰዓታት በኮሮናቫይረስ የ8 ሰዎች ህይወት ማለፉ መረጋገጡን ተከትሎ በበሽታው የሞቱ ሰዎች ቁጥር 1 ሺህ 222 ደርሷል።
በአሁኑ ወቅት ቫይረሱ ካለባቸው 44 ሺህ 535 ሰዎች መካከል 285 ያህሉ በጽኑ ሕክምና ላይ መሆናቸው ተገልጿል።
በአገሪቱ እስካዛሬ ድረስ በአጠቃላይ ለ1 ሚሊዮን 301 ሺህ 570 ሰዎች የኮሮናቫይረስ የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጓል።
በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓት በተደረገው 6,062 የላብራቶሪ ምርመራ 618 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ሲረጋገጥ የ8 ሰዎች ህይወት አልፏል። በተጨማሪ በትላንትናው ዕለት 956 ሰዎች አገግመዋል።

በአጠቃላይ በሀገራችን በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች 79,437 የደረሱ ሲሆን የሟቾች ቁጥር 1,230 ደርሷል፤ ከበሽታው ያገገሙ አጠቃላይ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 34,016 ደርሷል።
በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓት በተደረገው 5,278 የላብራቶሪ ምርመራ 566 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ሲረጋገጥ የ8 ሰዎች ህይወት አልፏል። በተጨማሪ በትላንትናው ዕለት 944 ሰዎች አገግመዋል።

በአጠቃላይ በሀገራችን በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች 80,003 የደረሱ ሲሆን የሟቾች ቁጥር 1,238 ደርሷል ፤ ከበሽታው ያገገሙ አጠቃላይ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 34,960 ደርሷል።
በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት በትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ውስጥ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራን ለመምራት የሚያስችል መመሪያ መዘጋጀቱ ተገለፀ፡፡
፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ የ2013 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የስራ አፈፃፀም ላይ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫው ዶ/ር ሳሙኤል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ውስጥ ሆኖ ትምህርትና ስልጠና ለማስቀጠል የሚያስችል ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን ገልፀው በተለይም የኮቪድ 19 ወረርሽኝን እየተከላከሉ የትምህርትና ስልጠናውን ለማስቀጠል የሚደረገው ዝግጅት የሚገመገምበት ፕሮቶኮል መዘጋጀቱንና ግብረኃይልም ተቋቁሞ ወደዩኒቨርስቲዎች ወርዶ የዝግጅት ሁኔታቸውን እየገመገመ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በመግለጫቸው እንደሉትም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት በትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ውስጥ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራን ለመምራት የሚያስችል መመሪያ መዘጋጀቱን ገልፀዋል፡፡

ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርስቲዎች ለመመለስ ደጋግመው ጥያቄ ሲያቀርቡ እና ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸው ከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማትም በተመሳሳይ ላለፉት 3 ወራት ዝግጅት ሲያደርጉ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

ለግምገማ በተሰማራው ግብረኃይል እንደታየውም አብዛኞቹ ዩኒቨርስቲዎች ሙሉ በሙሉ ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውንና ቀሪዎቹም በቀጣይ ሳምንት እንደሚያጠናቅቁ ገልፀዋል፡፡

በወረርሽኝ ዘመን የሚቀጥለው ትምህርትና ስልጠና የሚኖረው ቆይታ ውጤታማ እንዲሆን የትምህርትና ስልጠና ማህበረሰቡ መመሪያውን ተከትለው እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡ ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ በቂ ዝግጅት አድርገናል፡፡ አብረን ሰርተናል፡፡ የሶስት ወራት አፈፃፀማችንም በቂ ዝግጅት የተደረገበት ነው ብለዋል፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ በበኩላቸው መመሪያው በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ውስጥ ሆነን ትምህርትና ስልጠና ለማስቀጠል የሚያስፈልጉንን ዝግጅቶች ፕሮቶኮል የያዘ ነው፡፡ በመመሪያው በተማሪዎች፣ የአስተዳደር ሰራተኞች፣ በመምህራንና አመራሩ የተከለከሉ ተግባራትን፣ ግዴታዎችን፣ ሃላፊነቶችንና በምን ደረጃ መማር ማስተማሩ እንደሚካሄድ ተቀምጧል ብለዋል፡፡ ክፍል ውስጥ፣ መመገቢያ ቦታ፣ ማንበቢያ ቦታ፣ መኝታ ቤቶችና ሌሎች ቦታዎች ላይ ስለሚኖሩ ጥንቃቄዎችም ማብራሪያ ያስቀምጣል ብለዋል፡፡
በመመሪያው መግቢያ በር ላይ ሙቀት ከመለካት ጀምሮ የሚሰሩ ስራዎችን እና ልዩ ምልክት የሚያሳዩትን በምን አግባብ መያዝ እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡ የማቆያ እና መለያ ቦታ ከማዘጋጀት ጀምሮ ከአከባቢው ጤና መዋቅር ጋር በቅንጅት እንዲሰሩ የሚያስገድድም ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡

ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የዩኒቨርስቲዎችን ዝግጅት ባማከለ ሁኔታ በተለይ የተማሪዎችን ደህነት ባስጠበቅ መልኩ የሚከፈቱ ይሆናል ብለዋል፡፡

ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሁኔታ መፍጠርን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ የተዘጋጀው መመሪያ ኮቪድ 19ን ከመከላከል ጎንለጎን የተቋማቱን ሰላማዊ ሁኔታ ለማስጠበቅም ያግዛል ብለዋል፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ቀድመው ካጋጠሙ ችግሮች ተሞክሮዎችን በመውሰድና በማረም እንዲሁም አዳዲስ አሰራር በመፍጠር ዝግጅት ማድረጉን ገልፀው አሁንም ከፀጥታ መዋቅሮች ጋር በቂ ዝግጅት እየተካሄደ ነው ብለዋል፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ኮቪድ 19 ወረርሽኝን እየተከላከሉ ትምህርት ለማስቀጠል ያለው ዝግጅት እየተገመገመ እንዳለው ሁሉ በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍም ተመሳሳይ የዝግጅት ምዕራፍ ግምገማዎች እየተካሄዱ ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡

የግል ተቋማቱም ተማሪዎቻቸውን ሲጠሩ ሙሉ ዝግጅት አድርገው ሊሆን ስለሚገባ በተዘጋጀው ፕሮቶኮል መሰረት በከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ በኩል እየተገመገሙ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በስልጠና ዘርፍ ያሉ ተማሪዎች ቁጥራቸው ከፍተኛ በመሆኑ በየደረጃው ካሉ የክልልና ከተማ አስተዳደር ቢሮዎች ጋር በመሆን እየሰሩ እንደሆነና ዝግጅታቸው ሲጠናቀቅ ስልጠና እንደሚጀምሩም ገልፀዋል፡፡

ትምህርትና ስልጠና ሲጀመር የኮቪድ 19 ጉዳይ የአከባቢው ማህበረሰብም ጉዳይ ስለሚሆን ያለፈውን ጊዜ ያከማቹትን እውቀት የሚጠቀሙበት ወቅት ይሆናል ብለዋል፡፡ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ውስጥም ሆነን የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት፣ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ስራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ ይሆናል፡፡ እነዚህም ወደስራ ፈጠራ ለመቀየር ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ ሲሉ ገልፀዋል፡፡

ፕሮፌሰር አፈወርቅ እንዳሉት ኮቪድ 19ን እየተከላከልን፣ ጥናትና ምርምሮችን እያካሄድን፣ ስራ እየፈጠርን፣ የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት እየሰጠን ትምህርትን የምናስቀጥል ይሆናል ብለዋል፡፡

በማጠቃለያው ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ እንደገለፁት ቅድሚያ ትኩረት የሚሰጠው የኮቪድ 19 ወረርሽኝን እየተከላከሉ ትምህርትና ስልጠና ማስቀጠል ላይ መሆኑን ገልፀው የሰላምና ፀጥታ ጉዳይ በጥንቃቄ የሚታይና እየተሰራበት ያለ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
ለዚህም እንዲያግዝ ተቋማት በቁርጠኝነትና በኃላፊነት መመሪያውን ተግባራዊ ሊያደርጉ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

ተማሪዎች በዩኒቨርስቲ ቆይታቸው ትኩረት ማድረግ ያለባቸው ተልዕኳቸው በሆነው በትምህርትና ስልጠናው ላይ ብቻ ሊሆን ይጋባል ብለዋል፡፡ ተማሪዎች ወደዩኒቨርስቲ ሲመለሱም መመሪያው ላይ ስልጠና እንደሚሰጥና ከባለድርሻ አካላትና የአከባቢው ማህበረሰብ ጋርም ውይይት እንደሚካሄድ ገልፀዋል፡፡

ተማሪዎች ወደዩኒቨርስቲዎች ሲመለሱ በሚኖረው የትራንስፖርት ሁኔታ ላይም በዩኒቨርስቲዎቹ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ከኮቪድ መከላከልም ሆነ ከሰላምና ፀጥታ አንፃር ከፍተኛ የጥንቃቄ ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀው ወላጆችና አሳዳጊዎች ልጆቻቸውን ወደ ዩኒቨርስቲዎች ለመላክ ስጋት እንዳይገባቸው አሳስበዋል፡፡

በዩኒቨርስቲዎች የሚኖረውን የሰላምና ደህንነት ጉዳይ የሚከታተል ግብረኃይል መቋቋሙንና በየ24 ሰዓት ውስጥ መረጃዎችን ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንደሚያቀርብም ገልፀዋል፡፡
በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ሪያላዝድ ቤኔፊት ፕሮጀክት ስልጠናና ድጋፍ በሐረማያ ወረዳ ለሞዴልነት የበቃው የቆርኬ ቀበሌ አርሶአደሮች ሰርቶ ማሳያ ማዕከል የአርሶአደሮች ቀን አዘጋጀ፡፡

ለሐረማያ ዩኒቨርሲቲም የዕውቅና የምስከር ወረቀት ተበርክቷል፡፡

የሐረማያ ወረዳ ተፈጥሮ ሀብትና ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሹክሪ መሐመድ አብዲ እንደተናገሩት ዘንድሮ እንደ ሐረማያ ወረዳ የአርሶአደሮች ቀን በቆርኬ ቀበሌ ገበሬ ማህበር እንዲከበር የተደረገው አርሶ አደሮች ከማዕከሉ እውቀት የሚቀስሙበትና እርስ በርስ ልምድ ተለዋውጠው ለግብርና ቴክኖሎጂ ሽግግር የጎላ ጠቀሜታ ስለሚኖረው ነው ብለዋል፡፡

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ሪያላዝድ ቤኔፊት ኃላፊ ዶክተር ቡልቲ ቴሶ በዘጠኝ ወረዳ ሰለሳ ስድስት ገጠር ቀበሌዎች ውስጥ እየሰሩ መሆኑን ገልጸው በሴፍትኔት የታቀፉ አርሶ አደሮችን ማሰልጠን ፣ መደገፍና ክትትል በማድረግ ፕሮጀከቱ ለሁለት ዓመታት ማስቆጠሩን ጠቁመው ስራውን ከመጀመራቸው በፊት ችግሮችን በጥናት ለይተው ሰላሳ ሺ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ ወደስራ መግባታቸውንና የቆርኬ ቀበሌ ስራም የዚሁ አካል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለአርሶአደሩ ከተሰራጩ የተሻሻሉ የአትክልት ፣ ፍራፍሬና ሰብል ዝርያዎች ዘር በተጨማሪ ዘመናዊ የድንች መጋዘንና ፍየሎችም ማከፋፈላቸውን ገልጸው አርሶአደሮች በወሰዱት ዘር የሰሩትን ለመገምገም ጉብኝቱ መደረጉን ዶክተር ቡልቲ ተናግረዋል።

በስነ ስርዓቱ ላይ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ጉዳዮች ተወካይ ምክትልፕሬዝዳንት ዶክተር ጫኔያለው ስዩም ፣ ተመራማሪዎችና አርሶአደሮች ተገኝተዋል፡፡
ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ልህቀት ማዕከል ተብለው ተለዩ

በኢትዮጵያ ስምንት የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ልህቀት ማዕከል በመባል መለየታቸውን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የልህቀት ማዕከል እንዲሆኑ የተመረጡት ዩኒቨርስቲዎች ሐረማያ ፣ አዲስ አበባ፣ ጎንደር፣ ባህርዳር፣ መቐለ፣ ጅማ፣ ሃዋሳ፣ አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው።

ሚኒስቴሩ ይህንን ያስታወቀው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በተመረጡ ትምህርት ቤቶች በትምህርት ጥራት ዙሪያ ባካሄደው የምርምር ግኝት ላይ ትናንት ከባለድርሻ አካላት ጋር በተወያየበት ወቅት ነው ተብሏል።

በወቅቱ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ አማካሪ ዶክተር ወርቁ ነጋሽ እንደገለጹት በሃገሪቱ የሚገኙ 46 ዩኒቨርሲቲዎች በምርምር፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በአጠቃላይ ትምህርት በሚል በሶስት ደረጃዎች ተለይተዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት በርካታ ችግር ፈቺ የምርምር ውጤቶችን ሲያበረክቱ የቆዩና ወደፊትም አስተዋጽዖ ይኖራቸዋል የተባሉ ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች በምርምር ዘርፍ የልህቀት ማዕከል እንዲሆኑ መለየታቸውን ነው የተናገሩት፡፡

ለአንድ ሀገር ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ችግር ፈቺ ምርምር ቁልፍ ሚና እንዳለው የገለጹት ዶክተር ወርቁ ያደጉ ሃገራት የእድገት ሚስጥርም ከዚህ የመነጨ ነው ብለዋል፡፡

የምርምር ዩኒቨርሲቲዎቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር አቻ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ አቅማቸውን ለመገንባት በትኩረት እንደሚሰራም አመላክተዋል፡፡

ሌሎች 15 የመንግሰት ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ትምህርትና ስልጠና እንዲሰጡ መለየታቸውን ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲዎቹ በቂ እውቀትና ክህሎት ያዳበረ ዜጋ ማፍራት እንዲችሉ ተከታታይ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አመላክተዋል።

ቀሪዎቹ 23 ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ አጠቃላይ ትምህርትና ስልጠና እንዲሰጡ የተለዩ መሆኑን ዶክተር ወርቁ ማስታወቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።