የግቢ ጉባኤያት ምሩቃን ዓለም አቀፍ ኅብረት
10.8K subscribers
532 photos
12 videos
2 files
252 links
ሰላም እንደምን ሰነበታችሁ? ይህ ቻናል የተከፈተው በማኅበረ ቅዱሳን የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት መንፈሳዊ ትምህርት ሲከታተሉ ቆይተው ከግቢ ጉባኤያት ለተመረቁ በመላው ዓለም ለሚገኙ አባላት ሲሆን በዚህ ቻናል የሚተላለፉ መልዕክቶች፣ ትምህርታዊ ጽሑፎች እና ልዩ ልዩ የፕሮጀክት ሐሳቦች በማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማእከል አማካኝነት ሲሆን ምሩቃን ወደዚህ ቻናል እንዲቀላቀሉ የበኩልዎትን ድርሻ ይወጡ።
Download Telegram
በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደረጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ስዩም እና የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ መምህር ዋሲሁን በላይ ዛሬ ሚያዚያ 24/2016 ዓ.ም ከመኖሪያ ቤታቸው በጸጥታ አካላት መወሰዳቸው ታውቋል።

የሁለቱ አገልጋዮች መኖሪያ ቤት መፈተሹም ተገልጿል።

በአሁኑ ሰዓት ሜክሲኮ ፌዴራል ፓሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ የሚገኙ ሲሆን የተያዙበት ምክንያት አልታወቀም።

ዝርዝር እንደደረሰን እናቀርባለን።
የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ሥዩም እና የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ መ/ር ዋሲሁን በላይ በትናንትናው ዕለት ሚያዚያ 24 ቀን 2016 ዓ.ም በመንግሥት የጸጥታ አካላት ከመኖሪያ ቤታቸው ተወስደው ሜክሲኮ በሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ እንደሚገኙ አሳውቀን ነበር።


በዛሬው ዕለት ሚያዚያ 25 ቀን 2016 ዓ.ም ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን እየገለጽን፣ በሂደቱ ጉዳዩን በመረዳት አፋጣኝ ምላሽ የሰጡንን የመንግሥት የጸጥታ አካላት እናመሰግናለን።

በተጨማሪም በትዕግሥት ስትከታተሉና በጸሎት ስታስቡ ለነበራችሁ አባቶች፣ ምእመናን እና የማኅበረ ቅዱሳን አባላት እያመሰገንን፣ በዓሉ የሰላምና የበረከት እንዲሆንላችሁ እንመኛለን።

ማኅበረ ቅዱሳን!
እንኳን አደረሰን!

“በእምነት ትንሣኤ፣ በአምልኮተ እግዚአብሔር ትንሣኤ፣ ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ትንሣኤ፣ በፍቅር ትንሣኤ፣ በሰላም ትንሣኤ፣ በይቅርታ ትንሣኤ፣ በመከባበር ትንሣኤ፣ በአንድነት ትንሣኤ፣ በመተሳሰብ ትንሣኤ ወዘተ በመሳሰሉ ሃይማኖታዊና ግብረ ገባዊነት ጸንተን መኖር ከቻልን የፊተኛው ትንሣኤ ማለት እሱ ነው፡፡ “    ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

#ቃለ_በረከት_ዘብፁዕ_ወቅዱስ_አቡነ_ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ትንሣኤሁ ለእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘዕሥራ ምእት ዐሠርቱ ወስድስቱ ዓመተ ምሕረት፡፡
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፤
ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤

የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
በሕመም ምክንያት በየፀበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤
እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ሁሉ፡-
የትንሣኤ ሙታን በኲር በመሆን ቀድሞ የተነሣው አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለሁለት ሺሕ ዐሥራ ስድስት ዓመተ ምሕረት በዓለ ትንሣኤ በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ!
“ወይእዜኒ ክርስቶስ ቀደመ ተንሥኦ እምኲሎሙ ሰብእ ሙታን@ አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት ሁሉ በኲር ሆኖ ከሙታን ተነሥቶአል” (1 ቆሮ 05.!)
በዛሬው ዕለት በከፍተኛ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት የሚከበረው የጌታችን ትንሣኤ ለሰው ልጅ ያለው መንፈሳዊ ትርጉም እጅግ የላቀ ነው፤ እግዚአብሔር ፍጥረታትን በሙሉ በተለይም የሰው ልጅን ሲፈጥር በፍጹም ፍቅር ነው፡፡
ለዚህም የሰው በአርአያ እግዚአብሔር መፈጠር በቂ ማስረጃ ነው፤ ሰው በበደሉ ምክንያት ለሞት ቢዳረግም የእግዚአብሔር ፍጹም ፍቅር ጨርሶ አልተለየውም፤ እግዚአብሔር አንድ ቀን ሞትን ከሰው ጫንቃ አሽቀንጥሮ እንደሚጥል በየጊዜው ይገልጽ ነበረ፤ ያም በራሱ ልዩ ጥበብ እንደሚከናወን አረጋግጦ ለሰው ልጅ ተስፋውን አሳውቆ ነበር፤ ያም ልዩ ጥበብ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡
የእግዚአብሔር ዕውቀትና ጥበብ ድንበር የለውምና ከፍጥረተ ዓለም በፊት ሳይቀር የሰው ድኅነት በኢየሱስ ክርስቶስ ደም እንደሚፈጸም በእግዚአብሔር ዘንድ የተቈረጠ ነገር ነበረ፤ ጊዜው ሲደርስም በህላዌና በክዋኔ ከእርሱ ጋር አንድ የሆነ እግዚአብሐር ወልድ የሰውን ሰውነት ተዋሕዶ ሰውን የማዳን ስራውን አንድ ብሎ ጀመረ፡፡
ሰዎች በኃጢአትና በዲያብሎስ በደዌና በሞት ላይ ሥልጣን ያለው አዳኝ እሱ እንደሆነ ያውቁ ዘንድ የማዳን ስራውን በመዋዕለ ሥጋዌው በስፋት አከናወነ፡፡
ልዩ ልዩ ደዌና በሽታ የሚያሠቃያቸውን ፈወሰ፤ ኃጢአተኞችን በይቅርታ ተቀበለ፤ ኃጢአታቸውንም ደመሰሰ፤ አጋንንትንም በትእዛዝ አስወጣ፤ ወደ ጥልቁም አሰመጣቸው፤ ዲያብሎስንም ድል ነሥቶ አባረረ፤ ሙታንንም አነሣ፤ በባሕር ላይ በእግሩ ተራመደ፤ ነፋሳትን ገሠጸ፤ በአምስት እንጀራ ከአምስት ሺሕ ሕዝብ በላይ መገበ፤ ውሀውንም ወደ ጠጅ ለወጠ፡፡
ሰውን ሁሉ በፍቅርና በይቅርታ ይቀበልና ያገለግል ነበር እንጂ በአንዱ ስንኳ የመጨከንና የማግለል መንፈስ አላሳየም፤ ይህ ሁሉ ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔር ፍቅር ማሳያ ነበረ፡፡
በፍጥረት ሁሉ ላይ መለኮታዊ ሥልጣን እንዳለውም ማረጋገጫ ነበረ፤ መልእክቱም ዓለም መዳኛዋና አዳኝዋ እሱ መሆኑን አውቃ በአእምሮ እንድትከተለውና የድኅነቱ ተቋዳሽ እንድትሆን ማስቻል ነው፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!

በእግዚአብሔር አሠራር ኃጢአት ያለ ቤዛነት አይሰረይም፤ በመሆኑም ሰው በእግዚአብሔር ፊት ፍጹም ኃጢአተኛ ሆኖ ስለተገኘ ቤዛ ሆኖ የሚያድነው ያስፈልገው ነበር፤ ቤዛ መሆን የሚችለው አካል ደግሞ ራሱ ፍጹም ንጹህ መሆን ነበረበት፡፡

ከዚህም አንጻር በእግዚአብሔር ፊት ለሱ የሚመጥን ንጹህ ኣካል ከፍጡራን ወገን አልተገኘምና እሱ ራሱ ሰው ሆኖ የሰው ቤዛ ለመሆን በሥጋ ተገለጠ፤ በዚህም መሠረት የሰው ቤዛ ሆኖ በመስቀል ላይ በመሰቀል ንጹህ ደሙን አፈሰሰ፤ በዚህ ደም ምክንያት የሰው ኃጢአት በሥርየት ተዘጋ፤ ለዚህም ነው ቅዱስ መጽሐፍ “ያለ ደም ሥርየት ወይም ይቅርታ የለም” ብሎ የሚነግረን፡፡
ከዚህ ደም መፍሰስ በኋላ ወደ ሲኦል ወርዶ በዚያ የነበሩ የኃጢአት ግዞተኞችን በሙሉ ፈትቶ ወደ ቀደመ ስፍራቸው ወደ ገነት መለሰ፤ ከስቅለተ ክርስቶስ ጀምሮ እስከ መጨረሻ ያለው የሰው ኃጢአት በሙሉ በክርስቶስ ደም ይደመሰሳል፡፡

ሆኖም ይህ ሥርየት የሚገኘው በእምነት መሆኑን ቅዱስ መጽሐፍ አበክሮ ይነግረናል፣ በክርስቶስ አምኖ በደሙ የነጻ ሁሉ ክርስቶስ በተነሣው ዓይነት ትንሣኤ ይነሣል፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!
የጌታችንን ትንሣኤ ስናከብር የኛንም ትንሣኤ በማሰብ ሊሆን ይገባል፤ ትልቁ ነገርም የኛን ትንሣኤ ማሰቡ ላይ ነው፤ ምክንያቱም የክርስቶስ ትንሣኤ ለኛ ተብሎ የተደረገ በመሆኑ ነው፡፡

የሱ ትንሣኤ ለኛ ትንሣኤ በኲር ነው፤ ማሳያና ማረጋገጫም ነው፤ እግዚአብሔር በየዕለቱ የሚፈልገው የኛን ትንሣኤ ማየት ነው፤ የኛ ትንሣኤ በአንድ ቀን በቅፅበት የሚሆን አይደለም፤ ትንሣኤያችን አምነን ስንጠመቅ ተጀምሮ ከመቃብር ስንነሣ የሚጠናቀቅ ነው፡፡
እግዚአብሔር ዛሬም እያንዳንዱ ሰው በትንሣኤ ሕይወት እንዲመላለስ ይጠራል፤ ምክንያቱም የኋለኛው ትንሣኤ የሚገኘው በፊተኛው ትንሣኤ እንደሆነ እግዚአብሔር በመጽሓፉ ነግሮናልና ነው፤ በፊተኛው ትንሣኤ ዕድል ያለው ብፁዕ ነው፤ በሱ ላይ ሞት ሥልጣን የለውምና ነው፤ ለሰው ልጆች ተጠብቆልን ያለው ተስፋ ይህ ነው፡፡

ተስፋውን እውን ማድረግ የሚቻለውም በኛ ሃይማኖታዊና ተግባራዊ ተሳትፎ እንደዚሁም በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ ደም ነው፤ የነገውን ትንሣኤ ተሳታፊ ለመሆን ዛሬ መነሣት ግድ ይላል፤ ይህም የሚቻል እንጂ የማይቻል አይደለም፡፡

በእምነት ትንሣኤ፣ በአምልኮተ እግዚአብሔር ትንሣኤ፣ ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ትንሣኤ፣ በፍቅር ትንሣኤ፣ በሰላም ትንሣኤ፣ በይቅርታ ትንሣኤ፣ በመከባበር ትንሣኤ፣ በአንድነት ትንሣኤ፣ በመተሳሰብ ትንሣኤ ወዘተ በመሳሰሉ ሃይማኖታዊና ግብረ ገባዊነት ጸንተን መኖር ከቻልን የፊተኛው ትንሣኤ ማለት እሱ ነው፡፡ ዛሬ እግዚአብሔር እያንዳንዳችን ይህንን ትንሣኤ እውን አድርገን ስንኖርና ስንመላለስ ማየት ይፈልጋል፡፡
በአንጻሩም ክሕደትን፣ ከሕገ ተፈጥሮ ያፈነገጠ ጸያፍ ተግባርን፣ ጥላቻን፣ ጦርነትን፣ መለያየትን፣ ራስን ብቻ መውደድን፣ መጨካከንን፣ ግብረ ኃጢአትን፣ ፈሪሐ እግዚአብሔር ገንዘብ አለማድረግን፣ ፈጣሪን አለማመንን የተጸየፈ ምእመንን ማየት ይፈልጋል፡፡
ምክንያቱም ሁሉም ኃጣውእ አፅራረ ትንሣኤ ናቸውና ነው፤ ኃጣውእ በምድርም በሰማይም የሰው ጠላቶች ናቸው፤ በምድር ለሥጋዊና መንፈሳዊ በሽታ ይዳርጉናል፡፡

በተለይም በእግዚአብሔር ፊት እጅግ አስጸያፊ የሆነው የነውረ ኃጢአት ርኲሰትና በጋብቻ ያልታሰረ ሩካቤ ሥጋ ትውልድን እንደ ቅጠል እያረገፈው እንደሆነ፣ ምንም ዓይነት ፈውስ ላልተገኘለት የኤች አይ ቪ ኤድስ በሽታ ዋነኛ መተላፊያም ይህ ነውረ ኃጢአት እንደሆነ ተደጋግሞ ተነግሮአል፡፡
ይሁንና አሁንም ጥንቃቄ በጎደለው ድርጊት ስሕተቱ በመቀጠሉ በጦርነት ከሚያልቀው ሕዝብ ባልተናነሰ በዚህ ገዳይ በሽታ ብዙ ወገን እያለቀ ነውና እባካችሁ ሕዝበ እግዚአብሔር አንድ ለአንድ በመተሣሰርና በተቀደሰ የጋብቻ ሕይወት በመወሰን ትንሣኤያችንን እናብስር፡፡

በመጨረሻም
በዓለ ትንሣኤ የእግዚብሔር ፍቅር መገለጫና የተስፋችን ማሳያ መሆኑን በመገንዘብ ለእግዚአብሔር ክብርና ለሰው ልጆች ደኅንነት በአንድነት በመቆም ለተራቡት፣ ለተጠሙት፣ ለታረዙት፣ ለታመሙትና ለታሰሩትም ሁሉ ካለን ከፍለን በመስጠት ከኛ ጋራ በመንፈስና በሞራል በዓለ ትንሣኤውን እንዲያሳልፉ እናደርግ ዘንድ መንፈሳዊ ጥሪያችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን።
በድጋሚ በዓሉን የሰላም የዕርቅ የይቅርታ የትንሣኤ ኅሊና ወልቡና ያድርግልን፤
  እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!
አሜን።

አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ሚያዝያ 27 ቀን 2016 ዓ.ም
አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የልደት በዓል እና የማኅበረ ቅዱሳን ፴፪ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል በሰላም አደረሰን!

"ግቢ ጉባኤያት የአገልግሎት መሠረት" በሚል መሪ ቃል እሑድ ግንቦት 4 ቀን 2016 ዓ.ም ከ7፡00 ሰዓት ጀምሮ በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ በመገኘት የማኅበራችንን የምሥረታ በዓል በጋራ እናክብር።
‹‹ነገን ዛሬ እንሥራ››

ክፍል ስድስት


ውድ የእግዚአብሔር ቤተ ሰቦች! እንደምን ሰነበታችሁ? በዚህ ርእስ ቤተ ክርስቲያን ትናንት ለነበራት ድምቀት፣ ዛሬ ለገጠማት ተግዳሮት፣ ነገም ለሚኖራት ማንነት ክብረ ክህነትና ክብረ ምንኩስና የማይተካ አስተዋጽኦ እንዳላቸው እና እነዚህ ሁለት የክብረ ቤተ ክርስቲያን ምሰሶዎች የነገዋን ቤተ ክርስቲያን ሁኔታ ሊወስኑ እንደሚችሉ መንደርደሪያ ሐሳብ አንሥተን በመቀጠልም “ክብረ ክህነት ትናንት እንዴት ነበር? ዛሬስ ምን ሁኔታ ላይ ነው ? ነገስ ምን መሆን አለበት?” የሚሉ ጉዳዮችን ዳስሰን እስከ ክፍል አምስት አብረን ዘልቀናል፡፡ በክፍል ስድስትና ቀጣዮቹ ክፍሎች ደግሞ “ክብረ ምንኩስና ትናንት፣ ዛሬና ነገ ምን ይመስላልና መምሰል አለበት” የሚለውን እናጋራችኋለን፤ አብራችሁን ዝለቁ! መልካም ንባብ!

ክብረ ምንኩስና፡-

ምንኩስና ምንድን ነው?


‹‹መንኮሰ›› መለኮሰ፣ ተለየ፣ ሞተ፣ ከዓለም፣ ከሕዝብ ተለየ” ማለት እንደሆነ የግእዝ መዝገበ ቃላት ይናገራል፡፡

‹‹መነኮስ›› ማለት ደግም “መነኩሴ፣ መናኝ፣ ድኻ፣ ከዓለም ከዘመድ የተለየ፣ ለዓለም የማይጨነቅ፣ ጥሬ ቆርጥሞ አዳሪ፣ ለራሱ ጥላ ለእግሩ ጫማ የሌለው” ማለት ሲሆን መናኝ ይህን ዓለም የመነነ፣ የናቀ፣ የተወ ማለትም ነው፡፡ ‹‹መነነ ዘንተ ዓለመ፤ ይህን ዓለም ተወ›› እንዲል፡፡ (ገጽ ፺፱)

‹‹ምንኩስና›› ማለት ደግሞ “ቆብ መድፋት፣ ከዚህ ዓለም መለየት፣ ሥጋዊ ስሜትን መግደል” ማለት ነው፡፡ (ሕያው ልሳን፣ መዝገበ ቃላት ገጽ ፺፰-፻፵፱)
ከላይ ከተሰጠው የግእዝ ትርጉም ተነሥተን ስንመረምረው ምንኩስና ማለት ምን ማለት እንደሆነና ምን ያክል ከባድ ኃላፊነት እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ዓለሙንና አምሮቱን የናቀ፣ ስለ ጽድቅ ብሎ ራሱን ያደኸየ፣ “እኔ ለዓለም ሙት ነኝ፤ ዓለምም በእኔ ዘንድ ሙት ናት፤ የዓለም የሆነው ሹመቱ፣ ሽልማቱ፣ ሀብቱ፣ ንብረቱ አያስፈልገኝም፤ የሚስት ደስታ የልጅ ተስፋ ይቅርብኝ፤ ንጽሕ ጠብቄ፣ ከሴት ርቄ ራሴን ለመንግሥተ ሰማያት ጃንደረባ አድርጌ በጾም፣ በጸሎት፣ በትሩፋት ተወስኜ እኖራለሁ” ብሎ የወሰነ፣ ራሱን የለየ፣ ቁረንጮ አንጥፎ፣ ጠፍር ታጥቆ፣ ጥሬ ቆርጥሞ ለመኖር የማለ፣ ስለ ጽድቅ ብሎ ራሱን ያስራበ ያሰጠማ መሆኑን ተረድተናል፡፡ (ማቴ.፭፥፮)

‹‹ምንኩስናሰ ጥበበ ሕግ መሲሓዊት›› እንዳሉ ፫፻፣ ምንኩስና በወንጌል የተገኘች መሲሐዊት ሕግ ናት፤ ቀድሞ አልነበረችም፡፡ መነኮሳት በግብራቸው፣ በንጽሕናቸው ሰማያውያን መላእክት ተሰኝተዋልና፡፡ ‹‹መነኮሳት በምድር ያሉ መላእክት በሰማይ ያሉ ሰዎች ናቸው›› ይላል ፍትሐ ነገሥት፡። (ፍት መን አን ፲፥፫፻፵፬) ክርስቶስን የተከተሉ፣ ሐዋርያትን የመሰሉ ናቸውና፡፡ የመጀመሪያው የምንኩስና ሥርዓት ከዘመድ፣ ከእናት አባት መለየት፣ ከሀገር መውጣት ነው፡፡ ምክንያቱም መነኩሴ ማለት ‹‹ምውት ዘተፈልጠ እምዓለም፤ ከዚህ ዓለም የተለየ ሙት›› ማለት ነውና፡፡

ሲሰድቡት የማይሳደብ፣ ሲመቱት የማይማታ፣ ልቡ ክፉ ነገር ቂም በቀል፣ ልብስ ጉርስ የማያስብ ማለት ነው፡፡ የሞተ ሰው ይህ ሁሉ የለበትምና፡፡ ‹‹ልብስ ጉርስ ቢያስብ ጥቂት የሚበቃው ይሁን፡፡ ሰብአ ዓለምን ስንኳ አታስቡ›› ብሏል፡፡ መነኩሴ የነፍሱን ነገር ትቶ እንዴት ልብስ ጉርስ እያለ ያስብ፤ ይህ ምንኩስና አይባልም ከንቱ ነው፡፡ (መጽሐፈ ምዕዳን) እንዳለ፡፡ ምንኩስና ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተገኘ ሲሆን ቆቡ የአክሊለ ሶክ፣ ቀሚሱ የከለሜዳ፣ ቅናቱ የሐብል፣ አስኬማው የሰውነቱ ምሳሌ ነው፡፡ (የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ ፳፻ ዓ.ም)

የምንኩስና ዓላማ ምንድን ነው?

ምንኩስና የዘለዓለምን መንግሥት ለመውረስ ይቻል ዘንድ ፍጹም ሆኖ መገኘት ነው፡፡ መጽሐፍ እንደሚነግረን የምንኩስና ዓላማ ፍጹም መሆን ነው፡፡ አንድ ሰው “የዘለዓለምን ሕይወት እወርስ ዘንድ ምን ላድርግ?” ብሎ ለጠየቀው ጥያቄ ጌታችን ኢየሱስ ክረስቶስ እንዲህ ብሎ መለሰለት፤ ‹‹ፍጹም ትሆን ዘንድ ትወዳለህን? ያለህን ሁሉ ሂደህ ሽጠህ ለነዳያንም መጽውተህ ና ተከተለኝ›› አለው፡፡ (ማቴ. ፲፱፥፳፩) ሰው ከእግዚአብሔር ይልቅ እናቱን አባቱን፣ ሚስቱን ልጁን ከወደደ እንዲሁም ሀብትና ንብረቱን ከመረጠ መነኩሴ እንደማይሆን ፍጹምም ሊሆን እንደማይችል፣ ፍጹም ሊሆን፣ የዘለዓለምን ሕይወት በምንኩስና ሊወርሳት የሚሻ ደግሞ ሁሉን ትቶ መከተልን፣ መመነንን፣ ከዘመድ አዝማድ መለየትን፣ ከሀገር መውጣትን፣ ራስን መለወጥን የሚፈልግ እንደሆነ ከጥቅሱ እንረዳለን፡፡

የቀደሙ አባቶቻችንም ይህን ሥርዓት አብነት አድርገው ከሀገር ርቀው፣ ከቤተ ሰብ ተደብቀው፣ ራሳቸውን ለውጠው፣ ከቤተ ዘመድ ከሚመጣ ፈተናና ከውዳሴ ከንቱም ተጠብቀው፣ በማይታወቁበት ቦታ በአት አጽንተው በመኖር ሕገ መነከሳትን የጠበቁ ለክብርም የበቁ ብዙዎች ናቸው፡፡

ምንም እንኳን ብቸኛው የሕይወት መንገድ ባይሆንም ምንኩስና ትልቁና ከምድራዊ ዓለም ለይቶ ከሰማያዊ ዓለም የሚቀላቅል፣ ከሰው ተራ አውጥቶ ከመላእክቱ ጋር የሚያዛምድ፣ ሥጋዊ ደማዊ ከሆነው ምድራዊ አስተሳብና አኗኗር ለይቶ ከማኅበረ መላእክት የሚደምር፣ ፍጽም ሆኖ ፍጹም የሚያደርግ አምላካዊ ሕግ መሆኑን ከፍትሐ ነገሥቱም ከወንጌሉም ከሕንፃ መነኮሳቱም የምንረዳው እውነት ነው፡፡ በጥቅሉ የምንኩስና ዓላማው ፍጹም ሆኖ ፍጹም የሆነውን አምላክ ተከትሎ ዘለዓለማዊ ርስቱን (መንግሥቱን) መውረስ መቻል ነው፡፡

ምንኩስና ትናንት፡-

ምንኩስና ትናንት በነበረችው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ክብሩ እንደ ፀሐይ የሞቀ፣ እንደ ጨረቃ የደመቀ፣ እንደ ከዋክብት የተንቆጠቆጠ ነበር፡፡ ምንኩስና ትናንት በኢትዮጵያ ምድር እንኳን ተራውን ምእመኑን ነገሥታቱን፣ መኳንንቱን መሳፍንቱን፣ የነገሥታቱን እና የባለጸጋዎችን ልጆችና ሚስቶቻቸውን ሳይቀር መማረክ የቻለ፣ ዘውድ አስወልቆ አስኬማ ያስደፋ፣ ልብሰ መንገሥት አስወልቆ ቆዳ መልበስን፣ ሰሌን ማንጠፍን፣ ቅል አንጠልጥሎ፣ ጓዝን ጠቅሎ ገዳም በረሃ መውረድን ያስቻለ ታላቅ ቅቡልነትና ገዥነት የነበረው ሥርዓት እና አስተምህሮ ነበር፡፡ (ግንቦት ፳ ስንክሳር)

እንደ ቀድሞዎቹ እንደነ ኤልያስ፣ እንደ ኋለኞቹ እንደነ መጥምቀ መለኮት ዮሐንስ ንጽሕናዬን ጠብቄ፣ ከሴት ርቄ እኖራለሁ ብሎ ሰውነቱን ለእግዚአብሔር አደራ በሰጠው አባ እንጦንስ ላይ ያደረው ጸጋ ምንኩስና ያደረባቸው በርካታ መናንያን በኢትዮጵያ ገዳማት ነበሩ፤ አሁንም ጥቂቶች ይኖራሉ፡፡

ምንኩስና ትናንት በኢትዮጵያ ቤተ ክረስቲያን የቅድስና፣ የንጽሕና፣ የመንፈሳዊነት ማሳያ ጥግ ነበር፡ ፡ዘንዶ የሚጫሙ፣ በባሕር ላይ የሚራመዱ፣ አንበሳ የሚጋልቡ፣ ራሳቸውን ከመግዛት አልፈው ተፈጥሮን የገዙ፣ ሃይማኖታቸው የጸና፣ ምግባራቸው የቀና፣ ተባርከው የሚባርኩ የሚያስባርኩ ተቀድሰው የሚቀድሱ የሚያስቀድሱ፣ ትምህርታቸው ሕይወት፣ ጸሎታቸው በረከት የሚያሰጥ፣ በአጽንኦ በአት በቀኖና ገዳማት የጸኑ፣ ሁሉ የሚያከብራቸው የሚያፍራቸው፣ በነገሥታት ሹመት፣ በባለጸጎች ምጽዋት የማይታለሉ፣ የሴት ፊት የአገልግል ፍትፍት የማያውቁ መነኮሳት ነበሩባት፡፡ ‹‹ይሔሶ ለመነኮስ በሊዐ ኅምዝ ዘይቀትል እምይብላ ምስለ ብእሲት እመኒ እኅቱ አው እሙ፤ከሴት ጋር ከመብላት ለመነኩሴ መርዝ ቢበላ ይሻለዋል፤ እኅቱም እናቱም ብትሆን›› እንዳለ አባ ብንያሚን የተባለ አባት(መ/ምዕዳን)፡፡

በእፍኝ ጥሬ፣ በጥርኝ ውኃ የሚኖሩ ግብረ መነኮሳትን፣ ሥርዓተ ገዳማትን ሳያፋልሱ በትጋት ዘመናቸውን የፈጸሙ ብዙ መነኮሳት የነበረባት ቤተ ክርስቲያን ነበረች፡፡ (ነበረች ስንል አሁን ምንም የለም ለማለት አይደለም መጠኑን ለመግለጽ እንጂ) ምንኩስና ትናንት ትልቅ የበረከት ምክንያት ነበር፡፡ መነኮሳት ትናንት የከተማ ሕይወት፣ የነገሥታት ፊት፣ የአደባባይ ሙግት አያውቁም ነበር፡፡ ለሁሉም ነገር ሰይፋቸው፣ ዘገራቸው ጸሎታቸው ነበር፡፡ የምንኩስና ኑሮ ፈጣሪን ማገልገል፣ ሕገ ምንኩስናን መጠበቅ፣ ከማናቸውም ዓለማዊ ኑሮ መከልከል መሆኑን በደንብ ያውቃሉ፡፡

ምንኩስናን በኢትዮጵያ ካስተዋወቁትና ከአስፋፉት ዘጠኙ ቅዱሳን ጀምሮ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በኢትየጵያ ቤተ ክርስቲያን የክብረ ቤተ ክርስቲያን መታያ፣ የብዙኃን ምኞት የጥቂቶች ስኬትና ኑሮ፣ የክርስትናችን ዓምድ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ቅድስናቸው ከኢትዮጵያ አልፎ በሌሎች ዓለማት የታወቁ፣ ታላላቅ ገዳማትን መሥርተው፣ ደቀ መዛሙርት አፍርተው፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን ጽፈው፣ ደጉሰው፣ ሃይማኖት እንዲጸና፣ ምግባር እንዲቀና፣ ፍትሕ ርትዕ እንዲሰፍን፣ ፍቅረ እግዚአብሔር ፍቅረ ቢጽ ያስተማሩ፣ ቃላቸው ጦር ጸሎታቸው አጥር ሆኖ ቤተ ክርስቲያንን የጠበቀ በርካታ መነኮሳትን ቤተ ክርስቲያናችን አፍርታለች፡፡

በጥቅሉ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የነበሩ መነኮሳት የእግዚአብሔር መልአክ ለአባ ጳኩሚስ ያሳየው ዓይነት መነኮሳት ነበሩ፡፡የእግዚአብሔር መላክ ለአባ ጳጉሚስ አምስት መልካም የሆኑ ማኅበራተ መነኮሳትን አሳይቶት ነበር፡፡
በበጎች የተመሰሉ መነኮሳት ፡- እንደ በጎች በማኅበር በአንድነት ሳይለያዩ በፍቅር እንደ አንድ አካል ሆነው በማኅበር የሚኖሩ መነኮሳት፣ ባለመለያየት፣ በቅንነት፣ በአንድነት የሚኖሩ ቅዱሳን መነኮሳትን የሚወክሉ መነኮሳትን፣

በርግብ የተመሰሉ መነኮሳት፡- በየዋህነትና በቅንነት በፍቅርና በአንድነት የሚኖሩ፣ ቢጠሏቸው፣ ቢሰድቧቸው፣ ቢጸየፏቸው የማይቀየሙ መነኮሳትን፣

በዋኖስ የተመሰሉ መነኮሳት፡- በጣፈጠና ባማረ ጣዕመ ዜማ ያለ ትዕቢትና ትምክህት በትሕትናና በፈሪሃ እግዚአብሔር በመንቀጥቀጥና እንባቸውን እያፈሰሱ ለፈጣሪያቸው የሚዘምሩና የሚያመሰግኑ መነኮሳትን በዋኖሶች መስሎ አሳይቶታል፤ የዋኖስ ድምፅ ጥዑም ነውና፡፡

በተጨማሪም በንቦች የተመሰሉ መነኮሳት፡- እንደ ንቦች ጠቢባን፣ እንደ ንብ በትጋት የጽድቅ ሥራዎችን ከገድላት የሚቀስሙ መነኮሳትን፣

በፌቆዎች የተመሰሉ መነኮሳትን፡- ያለንዝህላልነትና ያለመታከት በትጋት እንደ ፌቆዎች እየሮጡ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ሥራ የሚፋጠኑ መላኩ ለአባ ጳኩሚስ አሳይቶት አባታችንም አይቶ ማድነቁን ሕንፃ መነኮሳት ይነግረናል፡፡ (ሕንፃ መነኮሳት ክፍል ሦስት ቁጥር ፲) ትናንት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም አባ ጳኩሚስ ያያቸው ዓይነት መነኮሳትና ማኅበረ መነኮሳት እንደ ምድር አሸዋ፣ እንደ ሰማይ ከዋክብት በዝተውና ደምቀው የነበሩበት መሆኑን የበርካታ ገዳማትና መናንያን ታሪኮች ያስረዱናል፡፡

ለመሆኑ “ክብረ ምንኩስና ዛሬ ምን ሁኔታ ላይ ነው?” የሚለውን በክፍል ሰባት እንዳስሰዋለን ቸር እንሰንብት!
አደራ አለብኝ!

ዓለም አቀፍ የግቢ ጉባኤ ምሩቃን ኅብረት ጉባኤ

የ2016 ዓ.ም 4 ኛ ዙር ቨርቹዋል ጉባኤ

ቀን፡ ግንቦት 11/2016 ዓ.ም

ሰዓት፡ ምሽት 2፡00-3፡00

ሁሌም በየወሩ በግቢ ጉባኤያት ምሩቃን ዓለም አቀፍ ኅብረት የቴሌግራም ቻናል

https://t.me/gibigubayat_mirukan_hibret
አደራ አለብኝ!

ዓለም አቀፍ የግቢ ጉባኤ ምሩቃን ኅብረት ጉባኤ

የ2016 ዓ.ም 4 ኛ ዙር ቨርቹዋል ጉባኤ

ቀን፡ ግንቦት 11/2016 ዓ.ም

ሰዓት፡ ምሽት 2፡00-3፡00

ሁሌም በየወሩ በግቢ ጉባኤያት ምሩቃን ዓለም አቀፍ ኅብረት የቴሌግራም ቻናል

https://t.me/gibigubayat_mirukan_hibret
Topic: International EOTC Tech Conference
Time: May 25, 2024 11:00 AM Eastern Time (US and Canada)

Join Zoom Meeting
https://us06web.zoom.us/j/82431135798?pwd=4cBszJvTvnaUB5rJ7vOADzGOw2vQbk.1

Meeting ID: 824 3113 5798
Passcode: 394961

---

One tap mobile
+12532050468,,82431135798#