ፍሬ ሀይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤት (mana dilbata firee amentaa)
188 subscribers
226 photos
8 videos
19 files
37 links
በዚህ መንፈሳዊ ቻናል የኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሐይማኖታችንን እንድናውቅ የሚረዱ :-

፨ ከተለያዩ መንፈሳዊ ቻናሎች የምናገኛቸውን መረጃዎች አናጋራቹሃለን።

፨ ጥያቄ አና መልስ አንጠያየቃለን።


፨ መንፈሳዊ መፃህፍትን በ አማርኛ ፣ Afaan oromoo አና English language እናካፍላቹሃለን።

ሐሳብ አስተያየት ካላቹ @ye_gebriel ላይ አሳውቁን።
Download Telegram
Forwarded from መንፈሳዊ ኪነ-ጥበብ💒 (²¹ዬሐንስ²¹....💜)
#መስማት_የተሳናት_እንቁራሪት!

በአንድ ወቅት የእንቁራሪቶች ውድድር እንደ ነበር ይነገራል፡፡ ውድድሩ አንድን አነስተኛ ተራራ ፈጥኖ የመውጣት ውድድር ነበር፡፡ ይህንን ውድድር ለመመልከት ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ እንቁራሪቶች ተሰብስበው ምርጫቸው ለሆኑ እንቁራሪት ተወዳዳሪዎች መጮህና ማጨብጨብ ጀምረዋል፡፡

ሩጫው (ዝላዩ) ተጀመረ! ቲፎዞው ሁኔታውን ገና ሲያየው የትኛውም እንቁራሪት ተራራው ጫፍ ላይ እንደማይደርስ ስለገመተ፣ ሁሉም አሉታዊ ነገርን ማሰማት ጀምሯል፡፡ “አይ፣ ገና ከመጀመራቸው እዚያው ነው የሚዘሉት . . . ይህንን ዳገት #አይችሉትም . . .  #አይሳካላቸውም . . .” ጩኸቱ ቀጥሏል፡፡

ይህንን የብዙዎች ጩኸት እየሰሙ እነዚህ ትንንሽ እንቁራሪቶች በግራና በቀኝ እየተዘረሩ ማለክለክ ጀምረዋል፡፡ ሩጫው ቀጥሎ፣ የቲፎዞው ተስፋ አስቆራጭ ድምጽ አይሎ፣ ሁሉም እንቁራሪቶች ዝለው ሳለ #አንዲት እንቁራሪት ግን ፍጥነቷን ሳትቀንስ በመገስገስ ጫፉ ደርሳ #አሸናፊ ሆነች፡፡

ጋዜጠኞችና ዘጋቢዎች በፍጥነት ደርሰው ጥያቄን መጠየቅ ጀመሩ፡፡ ሁሉም ያቃተውን ይህንን ተራራ የመውጣት ምስጢር ምን እንደሆነ ሲጠይቋት በዝምታ ተዋጠች፡፡ ደጋግመው ጥያቄያቸውን አቀረቡ፡፡ እሷ ግን መልስን አልሰጠችም፡፡ ለካ እንቁራሪቷ መስማት የተሳናት ነበረች፡፡ ምስጢሩ ያለው ያንን ሁሉ አሉታዊና ተስፋ አስቆራጭ ጩኸት #አለመስማቷ እንደ ሆነ የደረሱበት ያን ጊዜ ነው፡፡

👉🏾 አንዳንድ ጊዜ ከገጠመን የችግር ተራራ ይልቅ የበለጠ የሚያዝለንና ተስፋ የሚያስቆርጠን የምንሰማው አሉታዊ መልእክት እንደሆነ ጥሩ ማስታወሻ!

#እጠነቀቃለሁ፣ ለፍርሃት ግን ጆሮ የለኝም፡፡ ቆም ብዬ መንገዴን እንደገና እቃኛለሁ፣ ለተስፋ መቁረጥ ግን ጆሮ የለኝም፡፡ የሰዎችን ምክር እሰማለሁ፣ “አትችልም” ለሚል ድምጽ ግን ጆሮ የለኝም፡፡ ከብዙ አይነት ሰዎች የተለያዩ ሃሳቦችን ከመስማት ነጻ እንደማልሆን አውቀዋለሁ፣ ለአሉታዊዎችና ለአሸባሪዎች ግን ጆሮ የለኝም፡፡ እነዚህና መሰል መልእክቶችን አስመልክቶ እኔም ብሆን #መስማት_የተሳነኝ ነኝ፡፡

#ስብእና በልጅነት እንደ ተቦካ ሲሚንቶ፣ በአዋቂነት ደግሞ እንደ ደረቀ አርማታ ነው። የብዙ ሰው ስብእና እንደ ተቦካ ሲሚንቶ፣ በልጅነቱ በትክክል የሚቀርጸው ካላገኘ #ተንሻፎና_ተዛብቶ_ያድጋል
ዕድሜው ከገፋ በኃላ ደርቆ ስለሚጠነክር፣ ብዙ ጊዜ ለመከራ መዶሻና ለምክር መጥረቢያ
አዳግቶ ሀገር ያጠፋል። የልጅ ውበቱ በቀላሉ መሠራቱ ... ያዋቂ ክፋቱ ለመለወጥ አስቸጋሪ
የሆነ ክፉ እውቀቱ... ነው።

ሼር!         ሼር!             ሼር!
     
"ጌታ ሆይ አንተን ምን ብሎ መጥራት እንዳለበት የሚያውቅ ሰው ማን ነው? ጌታ ሆይ እናትህን ድንግል ብለን እንጥራትን? እንዲያ ብለን እንዳንጠራት የአንተ እናት መሆኑዋ ምስክር ይሆንብናል፤ ጌታ ሆይ እናት እንበላትን? እንዲህ እንዳንል ወንድ የማታውቅ ድንግል ናት፤ የእናትህ ነገር ለመረዳት የረቀቀ ከሆነ አንተን ሊረዳ የሚችል ሰው ማን ነው?"

ቅዱስ ኤፍሬም
#ሆሳዕና
(የዐቢይ ጾም ስምንተኛ ሳምንት)

ሆሣዕና ከስምንቱ የዐቢይ ጾም እሑዶች አንዱና የመጨረሻው ሳምንት ተብሎ የሚጠራ ከትንሣኤ ቀድሞ የሚገኝ የሕማማት መገቢያ ዋዜማ ነው።

ሆሣዕና አስቀድሞ ካለው ረቡዕ ጀምሮ የሚታሰብ ታላቅ የቤተክርስቲያን የበዓል ቀን እንደሆነ ይታወቃል። ይህን ስም በዚሁ ሰንበትና በዋዜማዎቹ ዕለታት የሚዘመረው ጾመ ድጓ ‘ሆሣዕና በአርያም’’ ‘ሆሣዕና ለወልደ ዳዊት’’ ‘ዕለተ ሆሣዕናሁ አርዓየ… ‘ ወዘተ. በማለት ሆሣዕና የሚለውን ቃል ቅዱስ ያሬድና ሌሎችም አባቶች በየቦታው እየጠቀሱና እየተዘመረለት በአህያ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ኢየሩሳሌም የገባበትን ሁኔታ እየተረከ ስለሚዘምር ይህ ሰንበት በጌትነትና በክብር በውዳሴና ቅዳሴ ሆሣዕና በአርአያም እየተባለ በሽማግሌዎችና በሕፃናት አንደበት በድንጋዮችም ልሳን ሳይቀር እየተመሰገነ ወደ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም በከብር ሲገባ ለሰጣቸው ለተቀደሰ ሰላሙና ፍቅሩ መታሰቢያ ሆኖ የተሰጠ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ሌላ ቀን እንደ ተራ ሰው ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም ይገባ ነበር፡፡

በዚህ ቀን ግን የአይሁድ ንጉሥ ሆኖ በክብር ገባ፡፡ ከቢታንያ ተነሥቶ ደብረ ዘይት ሲደርስ ከሐዋርያቱ ሁለቱን በቤተፋጌ ሰው ተቀምጦባት የማያውቅ ውርንጭላ እንዲያመጡለት ላካቸው፡፡ “በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሒዱ በዚያን ጊዜም የታሰረችን አህያ ውርንጫም ከእርሷ ጋር ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁም አምጡልኝ፡፡ ማንም አንዳች ቢላችሁ ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ" አላቸው፡፡ ማቴ.21፡1-17 ወደ ቤተፋጌም ሄደው አህያዪቱን አገኙአት፡፡ ሲፈቱአትም ሳለ ባለቤቶቹ መጡባቸውና አስቆሟቸው፡፡ እነርሱም ኢየሱስ እንደፈለጋት ነገሩአቸው፡፡ ባለቤቶቹ ይህንን ሲያውቁ ተዋቸው፡፡ ሐዋርያትም የአህያዪቱን ውርንጭላ ፈትተው ወደ ኢየሱስ ወሰዱ፡፡ አጠገቡም ሲደርሱ ልብሳቸውን በአህያዪቱ ውርንጭላ ላይ አንጥፈው ኢየሱስን አስቀመጡት፡፡

#ለምን_ዘንባባ_ያዙ_ቢባል፡-
ዘንባባ እሾሃም ነው ፤አንተም የኃይል የድል ምልክት አለህ ሲሉ፤በሌላም በኩል ዘንባባ እሳት ለብልቦ ይተወዋል እንጂ አይበላውም አንተም ባህርይህ አይመረመርም ሲሉ፤አንድም ዘንባባ ረጅም /ልዑል/ ነው አንተም ባሕርይህ ልዑል ነው ሲሉ ዘንባባ ይዘው ተቀብለውታል፡፡

#የተምር_ዛፍ_ዝንጣፊ_ነው_ቢሉ፡-
ተምር ፍሬው አንድ ነው አንተም ባህርይህ አንድ ነው
ሲሉ፡፡አንድም፤ተምር ልዑል/ረጅም/ ነው አነተም ልዑለ ባህርይ ነህ ሲሉ፡፡ አንድም፤የተምር ፍሬው በእሾህ የተከበበ ነው በቀላሉ መለቀም አይቻልም ፤ የአንተም ምስጢር አነተ ካልገለጠከው አይመረመርም ሲሉ ነው፡፡

#የወይራ_ዛፍ_ዝንጣፊ_ነው_ቢሉ፡-
ወይራ ጽኑዕ/ ጠንካራ/ ነው አንተም ጽኑዓ ባህርይ ነህ ሲሉ፤አንድም ወይራ ለመስዋዕት ይሆናል፤ አንተም መስዋዕት ትሆናለህ ሲሉ፤አንድም ወይራ ዘይቱ ለመብራት ይሆናል አንተም የዓለም ብርሃን ነህ ሲሉ ይህንን ይዘው አያመሰገኑ ተቀበሉት፡፡

#ልብሳቸውንም_ማንጠፋቸው፡-
እንኳን አንተ የተቀመጥክባት አህያ እንኳን መሬት መርገጥ አይገባትም ሲሉ ልብሳቸውን አነጠፉለት፡፡ እነዚያ ያላመኑ አይሁድ ለተቀመጠባት አህያ ይህንን ያህል ክብር ከሰጡ፤ በድንግልና ጸንሳ ለወለደችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምን ያህል ክብር ልናድረግለት ይገባን ይሆን?፡፡

#የዕለተ_ሰንበት_መዝሙር (ከጾመ ድጓ)
ወእንዘ ሰሙን በዓለ ፋሲካ ቀርቡ አርዳኢሁ ለአምላከ ጽድቅ ኀበ ደብረ ዘይት ሙራደ ዓቀብ ሀገረ እግዚአብሔር ወተቀበልዎ ሕዝብ ብዙኃን አዕሩግ ወሕፃናት ነሢኦሙ አዕፁቀ በቀልት እንዘ ይብሉ ሆሣዕና በአርያም ተፅዒኖ ዲበ ዕዋል ቦአ ሀገረ ኢየሩሳሌም በትፍሥሕት ወበሐሴት ይሁቦሙ ኃይለ ወሥልጣነ፡፡…..
ትርጉም: “በፋሲካ በዓል ሰሞን የእውነት አምላክ ደቀ መዛሙርት ወደ ደብረ ዘይት ቀረቡ፤ በሀገረ እግዚአብሔር (ኢየሩሳሌም) አቀበቱ ላይ ብዙ አረጋውያንና ሕፃናት የዘንባባ ቅጠል ይዘው ሆሣዕና በአርያም እያሉ ተቀበሉት፣ በአህያ ውርንጫ ላይ ተጭኖ በፍጹም ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ። ለእነዚህ ኃይልና ሥልጣንን ይሰጣቸዋል።

#መልዕክታት
ዕብ.8÷1-ፍጻ. ከተናገርነውም ዋናው ነገር ይህ ነው፤ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን፡፡ እርሱም የመቅደስና የእውነተኛይቱ ድንኳን አገልጋይ ነው፤ እርስዋም በሰው ሳይሆን በእግዚአብሔር የተተከለች ናት፡፡ (ተጨማሪ ያንብቡ)

1ኛ ጴጥ.1÷13 ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና ነቅታችሁ ኑሩ፤ ኢየሱስ ክርስቶስም ሲገለጥ የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ፡፡  (ተጨማሪ ያንብቡ)

#ግብረ_ሐዋርያት
የሐዋ.8÷26-ፍጻ. የእግዚአብሔር መልአክም ፊልጶስን ተናገረው፤ እንዲህም አለው÷ “በቀትር ጊዜ ተነሣና በደቡብ በኩል ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ በሚያወርደው በምድረ በዳው መንገድ ሂድ፡፡” ተነሥቶም ሄደ፡፡” እሆም÷   (ተጨማሪ ያንብቡ)

#ምስባክ
"ንፍሑ ቀርነ በዕለት ሠርቅ፡፡ በእምርት ዕለት በዓልነ፡፡ እስመ ሥርዓቱ ለእስራኤል ውእቱ" መዝ.80÷3
ትርጉም፦ በመባቻ ቀን በታወቀችው በዓላችን ቀን መለከትን ንፉ፤ ለእስራኤል ሥርዐቱ ነውና÷ የያዕቆብም አምላክ ፍርድ ነውና፡፡
ወይም
"እምአፈ ደቂቅ ወሕፃናት አስተዳሎከ ስብሓተ፡፡ በእንተ ጸላዒ፡፡ ከመ ትንሥቶ ለጸላዒ ወለገፋዒ፡፡" መዝ.80÷2
ትርጉም፦ ከሕፃናትና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ፡፡ ስለ ጠላት÷ ጠላትንና ግፈኛን ታጠፋው ዘንድ፡፡

#ወንጌል
ዮሐ.12÷1-11 ፋሲካ ከሚውልበት ከስድስተኛው ቀን አስቀድሞ ጌታችን ኢየሱስ ከሙታን ያስነሣው አልዓዛር ወደ ነበረበት ወደ ቢታንያ መጣ፡፡ (ተጨማሪ ያንብቡ)

ቅዳሴ ፡- ቅዳሴ ዘጎርጎርዮስ፡፡
#ንጉሥ_በአህያ_ላይ
(ሽራፊ ሃሳብ ከሆሳዕና ምንባብ)

"አህያ" ስምዋ ስድብ ከሆነ የቆየች እንስሳ ናት።  የዚህች  በዓለም ሁሉ የምትገኝ እንስሳ የሕይወት ታሪክዋ በአብዛኛው ተመሳሳይ ነው።  በሚበዙት ሀገራት አህያ ከባድ ሸክም ስትሸከም ትውላለች ፣  ደክሟት ለማረፍ ብትፈልግና ሸብረክ ብትል እንኳን በዱላ የሚመታት እንጂ "እስቲ አረፍ በይ" የሚላት የለም። ጀርባዋ በሸክም ብዛት የቆሰለ ፣ እግርዋ በጭነት ብዛት የተብረከረከ ፣ ዱላ ያስመረራት ፣ ዕረፍት የናፈቃት እንስሳ ናት።
ይህችን የተዋረደች እንስሳ በኪሩቤል ላይ የሚቀመጠው ሰማያዊው ንጉሥ ክርስቶስ በትሕትናው ዙፋኑ አደረጋት። ዱላ በለመደችው ፣ ዕረፍት በናፈቃት በዚህች ምስኪን ላይ "ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜ ቀሊል ነው" ያለው ንጉሥ ተቀመጠባት።

ኃያላን ነገሥታት ባማረ ሠረገላ ላይ ሆነው ፣ በሠራዊት ታጅበው ፣ ነጋሪት እያስመቱ ፣ መለከት እያስነፉ ፣ ሰይፍ  በታጠቁ ጦረኞች እየተፎከረላቸው ወደሚገቡባት ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በአህያ ላይ ተጭኖ ፣ በዓሣ አጥማጆች ተከብቦ ፣ በሕፃናት ዝማሬና በዘንባባ ዝንጣፊ ታጅቦ ገባ። 

ፈርተውት ሳይሆን ወደውት የሚዘምሩለት ንጉሥ ፣ ልብስ ገፍፎ የሚረግጥ ሳይሆን ልብሳቸውን አውልቀው ረግጠህ እለፍ የሚሉት ንጉሥ ፣ በቅንጦት ሠረገላ የሚሣፈር ሳይሆን "በአህያ ላይ ከተቀመጥኩ ይበቃኛል" የሚል ንጉሥ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ።

"የጽዮን ልጅ ሆይ ደስ ይበልሽ ፣ ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ በአህያና በውርጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል" የተባለላት ኢየሩሳሌም ምንኛ የታደለች ናት? "የዋህና ትሑት ንጉሥ" ያላት ሀገር ፣ ከተማይቱን  እያየ የሚያለቅስላት ንጉሥ ፣ መልካምነቱን ለመሸፈን የሚፈልጉ ሰዎች ስለ እሱ አትናገሩ ቢሉ እንኳን የቢታንያ ድንጋዮች አፍ አውጥተው የሚመሰከሩለት ንጉሥ ያላት ኢየሩሳሌም ምንኛ የታደለች ናት? የታሰሩትን አስታውሶ "ያስፈልጉኛል ፣ ፈትታችሁ አምጡልኝ" የሚል ንጉሥ የነገሠባት ፣ ዘንባባ ተይዞ ስለ ሰላም የተዘመረባት ፣ "ሰላምሽ ዛሬ ነው" የተባለላት  ያቺ ከተማ ምንኛ የታደለች ናት?

ወደ አህያይቱ ነገር እንመለስ ያቺን "ሸክም ያቆሰላትን ፣ ዕረፍት የናፈቃትን አህያ ክርስቶስ ፈትታችሁ አምጡልኝ ብሎ ዙፋኑ አደረጋት" የሚለው ታሪክ ለአህያ ብቻ ክብር የተሠጠበት ቀን መሆኑን የሚያሳይ ከመሰለን የዋሆች ነን። አህዮች አንብበው የማይጽናኑበት ወንጌል ላይ ይህ ክስተት የተጻፈው ለእኛ እንጂ ለምንም አይደለም።

እንደ አህያ ዕቃ ባንሸከምም ፣ ጀርባችን  ባይቆስልም የልባችን ጀርባ በኃጢአት ሸክም የጎበጠ ፣ በበደል ብዛት የቆሰለብን ብዙዎች ነን። "መቼ ነው ይህንን የኃጢአት ሸክም አራግፌ ዕርፍ የምለው?" እያልን የምንሠቃይ ሞልተናል።  መድኃኔ ዓለም ያኔ የላካቸውን ካህናት ዛሬም ወደ እኛ ልኮ "ፈትታችሁ አምጡልኝ" ብሎ እኛንም ቢያስፈታን ምናለ? ለነገሩ የእኛ የኃጢአት ማሠሪያ እጅግ ትብትብ ያለ ስለሆነ ካህናቱም ሥልጣኑ እያላቸው  በትሕትና "ከኃጢአት ማሠሪያ እግዚአብሔር ይፍታ" ሲሉ እንሰማቸዋለን።

#ዲያቆን_ሄኖክ_ኃይሌ
Forwarded from TIKVAH-ETHIOPIA
" ሆሣዕና '' (የዐብይ ጾም 8ኛ ሳምንት)

ሆሣዕና ከስምንቱ የዐቢይ ጾም እሁዶች አንዱና የመጨረሻው ሳምንት ተብሎ የሚጠራው ከትንሣዔ ቀድሞ የሚገኝ የሕማማት መግቢያ ዋዜማ ነው።

ሆሣዕና ማለት የቃሉ ትርጉም  " እባክህ አሁን አድን " ማለት ነው።

ዕለቱ ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ የሚቀድሙትና የሚከተሉት ሕዝብ በተለይም ሽማግሌዎች እና ሕፃናት '' ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ ፣ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው ፤ ሆሣዕና በአርያም '' በማለት በክብር መቀበላቸው የሚታወስበት ነው፡፡ 

ይህ ዕለት በቤተክርስቲያን ውስጥ ዘንባባ ተይዞ፣ እየተዘመረ እጅግ ልዩ በሆነ ሁኔታ ይታሰባል።

በዐብይ ጾም ከሰርክ ሆሣዕና ጀምሮ እስከ ትንሣዔ ሌሊት ያሉት ዕለታት የሚገኙበት ሳምንታት ሰሙነ ሕማማት ይባላል፡፡ ዕለታቱም የዓመተ ፍዳ ፣ የዓመተ ኩነኔ መታሰቢያ ናቸው፡፡

በዚህ ጊዜ በተለይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ስርዓት ካህናት መስቀል በእጃቸው አይዙም፣ አያሳልሙም ፣ ይፍቱኝ ተብሎ ወደካህን አይቀረብም፤ ይህ ሳምንት የጌታን የመጨረሻው ስቃይ የሚታሰብበት ነው።

#TikvahEthiopiaFamilyAddisAbaba

@tikvahethiopia
#የሰሙነ_ሕማማት_ሰኞ

#መርገመ_በለስ የተፈጸመበት ዕለት ነው

ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሆሣዕና ዕለት ቢታንያ አድሮ በማግሥቱም ከቢታኒያ ሲመጡ ተራበ፡፡ (ማር.11፤11-12) ቅጠል ያላት በለስ ከሩቅ አይቶ ወደ በለሲቱ ቀረበ፤ ነገር ግን ከቅጠል በቀር አንዳች ፍሬ አላገኘባትም፡፡ ከአሁን ጀምሮ ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ ብሎ ረገማት። በለስ የተባለች ቤተ እስራኤል ናት፤ ፍሬ የተባለች ሃይማኖትና ምግባር ናት፤ ከእስራኤል ፍቅርን፤ ሃይማኖትን፤ ምግባርን ፈለገ አላገኘም፤ እስራኤል (ሕዝበ እግዚአብሔር) መባልን እንጂ፤ ደግ ሰው አይገኝብሽ ብሎ ረገማት፤ በመርገሙ ምክንያት እርሱ ከለያቸው በስተቀር ደግ ሰው ጠፋባት፡፡

በለስ ኦሪት ናት፤ ኦሪትን በዚህ ዓለም ሰፍና ቢያገኛት ኦሪትና ነቢያትን ልሽር አልመጣሁም ልፈጽም እንጂ በማለት ፈጸማት፤ ሕገ ኦሪትን ከመፈጸም በቀር በእርሷ ድኅነት አላደረገባትምና፤ ፍሬ በአንቺ አይሁን አላት፤ ደኅነት በአንቺ አይደረግብሽ ብሏታልና እንደመድረቅ ፈጥና አለፈች፡፡

በለስ ኃጢአት ናት፤ የበለስ ቅጠል ሰፊ እንደሆነች ሁሉ ኃጢአት በዚህ ዓለም ሰፍታ ሰፍና አገኛት፡፡ በለስ ሲበሉት ይጣፍጣል፤ ቆይቶ ግን ይመራል፤ ኃጢአትም ሲሰሩት ደስ ደስ ያሰኛል፤ ኋላ ግን ያሳዝናል፤ ወደ እርሷም ሄዶ ማለትም ከኃጥአን ጋር ዋለ፤ ኃጥእ ከመባል በቀር በአንደበቱ ሐሰት፤ በሰውነቱ ክፋት እንዳልተገኘበት ለማመልከት ፍሬ አላገኘባትም አለ፤ በአንቺ ፍሬ አይገኝ የሚለውም፤ በኃጢአት ፍዳ ተይዞ የሚቀር አይኑር ለማለት ነው፤ ስትረገም ፈጥና መድረቋም፣ በአዳም ምክንያት ያገኘችን ዕዳ በደል በእርሱ ካሣነት እንደጠፋችልን ለመግለጽ ነው፡፡

#አንጽሆተ_ቤተ_መቅደስ የተፈጸመበት ዕለት ነው፦

ጌታችን በለስን ከረገማት በኋላ ወደ ቤተ መቅደስ ሄደ፤ ቤተ መቅደስ፣ ቤተ ጸሎት፣ ቤተ መሥዋዕት መሆኑ ቀርቶ ቤተ ምስያጥ (የንግድ ቤት) ሆኖ ቢያገኘው ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች፤ እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት ብሎ የሚሸጡበትን ሁሉ ገለበጠባቸው፤ ገርፎም አስወጣቸው፤ ይህም የሚያሳየው ማደሪያው ቤቱ የነበርን የአዳም ልጆች ኃጢአት ሰፍኖብን ስንኖር ቢያገኘን ኃጢአታችንን ሁሉ እንዳራቀልን የሚገልጽ ነው፡፡

በዚህ በሰሙነ ሕማማት ካህናትና ምእመናን በቤተክርስቲያን ተገኝተው ወዛቸው ጠብ እስኪል ድረስ በነግህ፤ በሠለስተ፣ በስድስቱ ሰዓት፤ በተሰዓቱ ሰዓትና በሠርክ መላልሰው ሲሰግዱና ሲጸልዩ ይሰነብታሉ፤ በተለይም ካህናት በማንኛውም አገልግሎት ጥቁር ልብስ ይለብሳሉ፤ ምክንያቱም የደረሰብን መከራ ኀዘኑን እና 5ሺ ከ5መቶ ዘመን የሰው ልጅ በጨለማ ይኖር እንደነበረ ለማዘከር ነው፡፡

@beteafework       @beteafework
@beteafework       @beteafework
@beteafework       @beteafework
#በሰሙነ_ሕማማት_የሚፈጸሙ_ሥርዓቶች

1, #ስግደት :-
በሰሙነ ሕማማት 41 ጊዜ ኪርያላይሶን 12 ጊዜ አቡነ ዘበሰማያት እየተዜመ እጅግ አብዝቶ ይሰገዳል።

2, #ጸሎት :-
በሰሙነ ሕማማት ከ24 ሰዓት ውስጥ 10 የጸሎትና የንባብ ሰዓታት ይገኛሉ እነዚህም ከጠዋቱ 1 ሰዓት; 3ሰዓት; 6ሰዓት; 9ሰዓት; 11ሰዓት እንዲሁም ከምሽቱ 1 ሰዓት; 3ሰዓት; 6ሰዓት; 9ሰዓት; 11ሰዓት ናቸው።
በእነዚህም ሰዓታት የጌታን ስቃይ ለማዘከር መዝሙረ ዳዊትና ግብረ ሕማማት ድርሳነ ማኅያዊ አብዝተው ይጸለያሉ።

3, #ጾም :-
በሰሙነ ሕማማት ብዙ አዝማደ መባልዕት / አዘውትረን የምንመገባቸው ምግቦች አይበሉም። በዚህም ሳምንት እስከ ምሽቱ #አንድ_ሰዓት እንድንጾም; ይኸውም ቆሎ;ዳቦ;ወኃና ጨው ብቻ እንደታዘዙ በግብረ ሕማማት ላይ ተጽፎ ይገኛል።

4, #አለመሳሳም :-
አይሁድ ጌታችንን ለመስቀል እየተንሾካሾኩ ስለተመካከሩና ይሁዳ ጌታችንን በመሳም አሳልፎ ስለሰጠው መሳሳም አይፈቀድም። መስቀልም በዘመነ ኦሪት የወንጀለኛ መቅጫ የእርግማን ምልክት ስለ ነበር ጌታችን በክቡር ደሙ ቀድሶ የድል አርማ እስኪያደርግልን ድረስ አንሳለመውም ገላ.3:13 ማቴ.10:38 ማቴ. 26:29

5. #አክፍሎት :-
እመቤታችን; ያዕቆብና ዮሐንስ የጌታችን ትንሳኤ ሳናይ እህልና ውኃ አንቀምስም ብለው እስከ ትንሳኤው መቆየታቸውን በማሰብ የሚጾም ነው።

6, #ጉልባን :-
ከባቄላ ከስንዴ ከገብስ የሚዘጋጅ በጸሎተ ሐሙስ ዕለት የሚበላ ንፍሮ ሲሆን ትውፊቱም የስቅለቱ ሐዘን መግለጫ ነው።

7, #ጥብጠባ :-
ይህ ምዕመናን በሰሙነ ሕማማት የፈጸሟቸውን ኃጢአቶች ለካህን እየተናዘዙ በወይራ ቅጠል ቸብቸብ እየተደረጉ ስግደት የሚቀበሉበት ነው። ይህም የጌታ ምሳሌ ነው።

8, #ቄጠማ :-
ጌታችን ብርሃነ ትንሳኤዉን እንደገለጠልን የምናስብበት ሲሆን የእሾህ አክሊል በመድፋቱ ምሳሌም በራሳችን ላይ እናስረዋለን።

እንበለ ደዌ ወሕማም እንበለ ጻም ወድካም ያብጽሐነ ያብጽሕክሙ ለብርሃነ ትንሳኤሁ እግዚአብሔር በፍስሐ ወበሰላም።

@beteafework       @beteafework
@beteafework       @beteafework
@beteafework       @beteafework
#​​ሰሙነ_ሕማማት💔

ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ሰሙነ ሕማማት የጾመ ሁዳዴ የመጨረሻው ሳምንት፤ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሕማም የሚታሰብበት፤ ካህናትና ምእመናን በአጸደ ቤተክርስቲያን ተሰብስበው የሕማሙን ነገር የሚያወሳውን ዜማ የሚያዜሙበት፤ ግብረ ሕማም በመባል የሚታወቀውን መጽፍ የሚያነቡበትና የሚሰሙበት፤ በነግህ፣ በሠልስት፣ በስድስት፣ በተሰዓት /ዘጠኝ /ሰዓት፣ በሰርክ /በዐስራ አንድ/ ሰዓት እየመላለሱ የሚሰግዱበትና የሚጸለዩበት ልዩ ሳምንት ነው ከሆሳዕና ማግስት እስከ ትንሳኤ።

በዚህ ሳምንት በተለይ ካህናት ጥቁር ልብስ ይለብሳሉ ምክንያቱም ጌታችን የደረሰበትን መከራና ስቃይ እንዲሁም የሰው ልጅ ፭ ሺ ፭ መቶ ዘመን በጨለማ ግዞት ይኖር እንደነበር ለማዘከርም ጭምር ነው። የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መከራና ሕማም በጽኑ እንድናስበው ያስተማሩን ሐዋርያት ናቸው። ለእነርሱም የነገራቸው ደግሞ ራሱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

ሰሙነ ሕማማት የጌታችንን ሕማማት ከማሰብ ጋር በየዕለቱ በርካታ ድርጊቶች መፈጸማቸውን የምናስታውስበት ሳምንት ነው፦

#ሰኞ
መርገመ በለስ የተፈጸመበት ሰኞ ይባላል፦

በዚህ ዕለት ጌታችን ከቢታኒያ ሲወጣ ተራበ ቅጠል ያለባትን በለስ ተመልክቶ ወደ በለሲቱ ቢቀርብ ከቅጠል በቀር ምንም ነገር ባለማግኘቱ “ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም ምንም ካንቺ ፍሬ አይበላ” ማር ፲፩፥፲፬ በማለት ስለረገማት መርገመ በለስ የተፈጸመበት ሰኞ ይባላል።

አንጽሖተ ቤተ መቅደስ ይባላል፡-
ጌታ ወደ ቤተመቅደስ ሄዶ በቤተመቅደሱ የሚሸጡትን እና የሚለውጡትን “ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች” ማቴ ፳፩፥፲፫ በማለት ከቤተመቅደስ ገርፎ አስወጥቷቸዋልና።

#ማክሰኞ
የጥያቄ ቀን ይባላል፦

ሰኞ ዕለት በቤተመቅደስ ሲሸጡ እና ሲለውጡ የነበሩትን ሁሉ እየገረፈ በማባረሩ ምክንያት ለሰው ልጅ ሹመትንና ስልጣንን የሰጠ ጌታ “በምን ስልጣን ይህንን ታደርጋለህ?” ማቴ ፳፩፥ ፳፫ ተብሎ በፈሪሳውያን ተጠይቋልና የጥያቄ ቀን ይባላል።

የትምህርት ቀን ይባላል፡-
በዚህ ዕለት በቤተመቅደስ ረጅም ትምህርት ስላስተማረም የትምህርት ቀን ይባላል። ሉቃ ፳፩ ፥፳፰ ፣ ማር ፲፪፥፪።

#ረቡዕ
ምክረ አይሁድ ይባላል፦

ረቡዕ እለት የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሐፍት ጌታን እንዴት መያዝ እንዳለባቸው የመከሩበትና ውሳኔ ያሳለፉበት ቀን በመሆኑ ምክረ አይሁድ ይባላል። ወቅቱ የፋሲካን በዓል የሚያከብሩበት ቀን በመሆኑ እና ብዙ ህዝብም ጌታን ይከተለው ስለነበር ሁከት እንዳይነሳ ስጋት ነበራቸው ። ነገር ግን ከአስራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ እንደሚሰጣቸው ስለነገራቸው ሉቃ ፳፪፥፩-፮ ጭንቀታቸው ተወግዶ በጌታ መያዝ ተስማምተዋል።

የመልካም መዓዛ ቀንም ይባላል፡-
ጌታችን በዚህ ዕለት በለምጻሙ በሰምዖን ቤት ተቀምጦ ሳለ መላ ሕይወቷን ለዝሙት አስገዝታ ትኖር የነበረችው ማርያም እንተ እፍረት/ባለሽቶዋ ማርያም/ ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ የአልባጥሮስ ሽቱ አምጥታ በራሱ ላይ በማርከፍከፍ ስለቀባቸው ማቴ ፳፮፥፮-፯ የመዓዛ ቀን ይባላል።

የእንባ ቀን ይባላል፡-
ባለሽቱዋ ሴት (ማርያም እንተ እፍረት) ኃጢአቷን ይቅር እንዲላት እየለመነች በእግሩ ስር ተደፍታ በእንባዋ እግሩን አርሳለችና ማር ፲፬፥፱ የእንባ ቀን ይባላል።

#ሐሙስ
ጸሎተ ሐሙስ ይባላል፦

ጌታችን ለአይሁድ ተላልፎ ከመሰጠቱ በፊት በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ ሲጸልይ በማደሩ ማቴ ፳፮፥፴፮ ጸሎተ ሐሙስ ይባላል።ጌታችን የደቀመዛሙርቱን እግር በፍጹም ትህትና ዝቅ ብሎ ያጠበበት ዕለት በመሆኑም ዮሐ ፲፫፥፫-፲፩ ሕጽበተ ሐሙስ ይባላል።

የምስጢር ቀን ይባላል፡-
ከሰባቱ ምስጢራት አንዱ የቅዱስ ቁርባን ምስጢር ማቴ፳፮፥፳፮-፳፱ በዚህ ዕለት ተፈጽሟልና የምስጢር ቀን ይባላል።

የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ ይባላል፡-
መሥዋዕተ ኦሪት /በእንስሳት ደም የሚቀርብ መሥዋዕት/ቀርቶ ለአለም ድኅነት ራሱን ያቀረበበት ቀን በመሆኑ ሉቃ ፳፪፥፳ የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ ይባላል።

የነጻነት ሐሙስ ይባላል፡-
ለኃጢአትና ለዲያቢሎስ ባሪያ ሆኖ መኖር ማብቃቱን እንዲሁም የሰው ልጅ ያጣውን ክብር መልሶ ማግኘቱ የተረጋገጠበት ቀን ስለሆነም ዮሐ ፲፭፥ ፲፭ የነጻነት ሐሙስ ይባላል።

#ዓርብ
የስቅለት ዓርብ ይባላል

ጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ቤዛ ሆኖ በመልዕልተ መስቀል ላይ ተሰቅሎ የዋለበት ዕለት ነውና ማቴ ፳፯፥፴፭ የስቅለት ዓርብ ይባላል።

መልካሙ ዓርብ ይባላል፡-
ከጌታ ስቅለት በፊት በተለይም በሮማውያን ህግ የወንጀለኛ መቅጫ ምልክት የነበረውን መስቀል ጌታችን በደሙ ቀድሶ የምህረት፣ የሕይወት አርማ፣ የዲያቢሎስ ድል መንሻ ስላደረገው፤ በሞቱ መልካሙን ሕይወት ስላገኘን መልካሙ ዓርብ ይባላል።

#ቅዳሜ
ቀዳም ስዑር ትባላለች ፦
ይህች እለት ከድሮ በተለየ መልኩ የጌታችንን መከራ በማሰብ በጾም ታስባ ስለምትውል የተሻረች ቅዳሜ ይባላል።

ለምለም ቅዳሜ ይባላል፡-
ካህናቱ ለምእመናን ለምለም ቀጤማ የሚያድሉበት ዕለት በመሆኑም ለምለም ቅዳሜ ይባላል። ምዕመናንም ይህንን ለምለም ቀጤማ እስከ ትንሣኤ ለሊት በራሳቸው ላይ ያስሩታል።

ቅዱስ ቅዳሜ ይባላል፡-
ቅዱስ የሆነው እግዚአብሔር በጥንተ ተፈጥሮ ፍጥረታትን አከናውኖ ያረፈበት ቀን ሲሆን በዘመነ ሐዲስ ደግሞ የማዳን ስራውን ሁሉ ፈጽሞ በሥጋው በመቃብር ሲያርፍ በነፍሱ ወደ ሲኦል ወርዶ ሲኦልን በርብሮ ባዶዋን ሲያስቀራት በዚያ የነበሩትን ነፍሳት የዘላለም ዕረፍትን ያወረሰበት ዕለት ስለሆነ ቅዱስ ቅዳሜ ይባላል።

መልካም የሰሞነ ሕማማት የጾምና የስግደት ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።🙏🙏🙏
እንበለ ደዌ ወሕማም ፣ እንበለ ጻማ ወድካም አመ ከመ ዮም ያብጽአነ  ያብጽአይክሙ ለብርሃነ ትንሳኤሁ በፍስሃ ወበሃሴት።
  " በመንገድም አጠገብ በለስ አይቶ ወደ እርስዋ መጣ፤ ከቅጠልም ብቻ በቀር ምንም አላገኘባትምና። ለዘላለሙ ፍሬ አይገኝብሽ አላት። በለሲቱም ያንጊዜውን ደረቀች።"
የማቴዎስ ወንጌል 21 : 19
This media is not supported in your browser
VIEW IN TELEGRAM
"እጅግም አዝነው እያንዳንዱ፦ “ጌታ ሆይ፥ እኔ እሆንን?” ይሉት ጀመር" ማቴ. 26:22

ስንት የአጥቢያ ኮከቦች ለአንተ
ዘምረውልህ ወደቁ
በሰማይ መቅደስህ አጥነው
በትዕቢት ረግፈው አለቁ
እፈራለሁ እኔም ለራሴ
መንገዴን ንገረኝ ጌታ
ጠዋት በዘመርሁበት አፍ
እንዳልሳደብ በማታ

#share
#share

▫️@diyakonhenokhaile
https://t.me/diyakonhenokhaile
+ የሚያምር እግር +

በጸሎተ ሐሙስ ልብን የሚሰውር አንድ ነገር ተፈጽሞ አለፈ፡፡ ይህም ጌታችን የደቀ መዛሙርቱን እግር የማጠቡ ነገር ነው፡፡ የሰውን የቆሸሸ እግር እያሸ የሚያጥብ አምላክ ፣ የተማሪዎቹን እግር የሚያጥብ መምህር ፣ የባሪያዎቹን እግር የሚያጸዳ ጌታ ማየት እንዴት ያስጨንቃል?

እስቲ ለአንድ አፍታ ወደዚያ ቤት በሕሊናችን ተጉዘን እንግባና ጌታን እግር ሲያጥብ አብረን እንመልከተው፡፡

የአምስተኛው ክፍለ ዘመን ባለቅኔ የቅዱስ ኤፍሬም ተማሪ ሶርያዊው ቄርሎና በመንፈስ ሆኖ ያንን ቤት በዓይነ ሕሊናው እንዲህ ቃኝቶት ነበር ፦

'ጌታ ውኃ ቀዳና መታጠቢያውን ተሸከመ። የማበሻ ጨርቅ ያዘና ታጠቀ፡፡ የደቀ መዛሙርቱን እግር ሊያጥብ ጀመረ፡፡ ሕሊናዬን አንዳች ነገር ሲወጋው ተሰማኝ ዕንባዬም ፈሰሰ። በፍርሃት ፊቴን ሸፈንኩ ዓይኖቼንም በመሳቀቅ ዞር አደረግሁ፡፡ ሲያጥባቸው ለማየት አቅም የለኝምና ብወጣ ተመኘሁ' ይላል፡፡ (Hymns of Cyrillona, On The Washing of the feet, Gorgias Press pg 72)እውነትም ጌታችን የደቀ መዛሙርቱን እግር አጎንብሶ ማጠብ ለማሰብ ይከብዳል፡፡
@diyakonhenokhaile

ጌታችን ሐሙስ ዕለት ያደረገውን ነገር መጥምቁ ዮሐንስ ቢያይ ኖሮ ምን ይል ይሆን? ጌታ ሊጠመቅ ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ ዮሐንስ 'አንተ እንዴት ልትጠመቅ ወደ እኔ ትመጣለህ?' ብሎ አልነበር? መጥምቁ ዮሐንስ ሆይ ና ተመልከት! በአንተ በባሪያው እጅ ሊጠመቅ ሲመጣ ስለ ትሕትናው የተደነቅህበት ጌታ ዛሬ ደግሞ አጥምቁኝ ከማለት አልፎ የባሪያዎቹን እግር ሲያጥብ አጎንብሶ ታየ፡፡ አንተ 'የጫማውን ጠፍር ተጎንብሼ ልፈታ አይገባኝም' ያልክለት ጌታ አጎንብሶ የሐዋርያቱን ጫማ ሲፈታና እግራቸውን ሲያጥብ ብታይ ምን ትል ይሆን? በዮርዳኖስ ዳር 'አንተ እንዴት ልትጠመቅ ወደ እኔ ትመጣለህ?' ያልከውን ጌታ ቅዱስ ጴጥሮስ 'አንተ እንዴት የእኔን እግር ታጥባለህ?' ሲለው ተመልከት! በእርግጥ በዮርዳኖስ ወንዝ ከታየው ትሕትና የበለጠ ትሕትና በዚያች የመታጠቢያ ወኃ ውስጥ ታየ፡፡ ውኃ በተሞላ በአንድ ማስታጠቢያ ውስጥ የፍጡር እግርና የፈጣሪ እጅ አንድ ላይ ሆነው የታዩበትን ያን ቅጽበት እጅግ ታላቅ ትሕትና ተማርንበት፡፡ ፍጡር ፈጣሪውን ሲያጠምቀው ከማየት በላይ ፈጣሪ የፍጡርን እግር ሲያጥብ ማየት ድንጋይ ልባችንን የሚሰብር ቅጽበት ነው፡፡

ከመጥምቁ ዮሐንስ በፊት የነበሩት ነቢያትስ ይህንን ቢያዩ እንዴት ይደነቁ ይሆን? ኢሳይያስ ሆይ 'ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ሆኖ አየሁት' ያልክለት ጌታ ዝቅ ባለ መቀመጫ ላይ ቁጭ ብሎ የአሳ አጥማጆችን እግር ሲያጥብ ተመልከተው፡፡ ነቢዩ ዳዊት ሆይ 'እግሮቹ በሚቆሙበት ሥፍራ እንሰግዳለን' ብለህ የዘመርክለት ጌታ እግር እያጠበ ነው፡፡ የሚገርመው እግር ከማጠቡ በፊትም ውኃ አስቀረበ አይልም ምክንያቱም ውኃውን የቀዳውም እርሱ ራሱ ነበረ፡። አብርሃም ለእንግዶቹ እንዳለው 'ጥቂት ውኃ ይምጣላችሁ' ብሎ ውኃ አላስቀዳም፡፡ (ዘፍ. 18፡4) ራሱ ወኃወን ቀድቶ በመታጠቢያው ሞልቶ የባሪያዎቹን እግር አጠበ። ለነገሩ በትሕትና የተጠመቀበትን የዮርዳኖስን ወንዝስ ቢሆን በወኃ የሞላው እርሱ አልነበረምን? ...

ጴጥሮስ ተጨነቀ ፤ 'ጌታ ሆይ አንተ እንዴት የእኔን እግር ታጥባለህ?' አለና ተከላከለ፡፡ የጴጥሮስ ጭንቀት ብዙ ነገር ከማሰብ የመነጨ ነው፡፡ 'ኪሩቤል በፊትህ ግርማ እንዳይቃጠል ፈርተው በፊትህ ሲቆሙ በክንፎቻቸው እግራቸውን ይሸፍናሉ፡፡ ታዲያ እኔ እጠብልኝ ብዬ እንዴት ደፍሬ እግሬን እሠጥሃለሁ? ሱራፌል የልብስህን ጫፍ የማይነኩህ ጌታ የእኔን እግር እንዴት ታጥባለህ? በባሕር ላይ በአንተ ትእዛዝ የተራመድሁት አይበቃኝም? እንዴት እግርህን ልጠብህ ትለኛለህ? ይህንን ዕዳ እንዴ እሸከመዋለሁ?' የሚል ጽኑ ጭንቀት ያዘለ ጥያቄ ነበር፡፡ ጌታ ግን ዕውር ባበራባቸው እጆቹ እግር አጠበባቸው፡፡ ሸክላ ሠሪው አጎንብሶ የሸክላውን እግር አጠበ፡፡ ሰውን ከምድር አፈር የፈጠረው አምላክ ትቢያውን በክብር አስቀምጦ እግሩን አጠበው፡፡

ጌታችን ያጠበው ከሰዓታት በኋላ እግሬ አውጪኝ ብለው ጥለውት የሚሸሹትን የደቀ መዛሙርቱን እግሮች ነበረ፡፡ ለአንድ ሰዓት እንኳን አብረውት ሊተጉ የማይችሉትን ተማሪዎቹን እግር አጠበ፡፡ ጥለውት እንደሚሔዱ እያወቀ 'ንጹሐን ናችሁ' ብሎ አወደሳቸው፡፡ 'ወደ አብ እንደሚሔድ አውቆ የወደዳቸውን እስከ መጨረሻው ወደዳቸው' እንደሚል ምድር ላይ በቀረችው ጊዜ ያልከፈለው የፍቅር ዕዳ እንዲኖርበት አልፈለገምና ጊዜውን ለመውደድ ተጠቀመበት፡፡ የሚወዳቸውን ደቀ መዛሙርት እግራቸውን አጥቦ በፍቅር ተሰናበታቸው፡፡

ጌታ ሆይ የእኔንስ እግር የምታጥበው መቼ ነው? በእውነት በምድር ላይ ከእኔ እግር በላይ የቆሸሸ አለ? ያልረገጥሁት የኃጢአት ጭቃ ፣ ያልነካሁት የበደል ቆሻሻ እንደሌለ አታውቅምን? 'በክፉዎች ምክር የሔደ' እግሬን የማታጸዳው ለምንድን ነው? (መዝ. 1፡2) 'የታጠበ እግሩን ከመታጠብ በቀር ሌላ አያስፈልገውም' ብለህ የለምን? እውነት ነው ፤ እግሬን ከኃጢአት ከከለከልክልኝ ሌላውን አካሌን ማዳንህም አይደል? አጥብቀህ ከምትጠላቸው ነገሮች መካከል አንዱ የሆነውን 'ወደ ክፉ የሚሮጥ እግሬን' የማታጥብልኝ ለምንድን ነው? (ምሳ. 6፡18)እባክህን እጠበኝ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ፡፡ በእርግጥ የሐዋርያትን የቆሸሸ እግር በውኃ እንዳጠብከው አስበን አደነቅን እንጂ በማግሥቱ ደግሞ የዓለምን ኃጢአት በደምህ አጥበሃል፡፡ ከዳንሁ በኋላ የቆሰልሁትን ፣ ከታጠብኩ በኋላ ያደፍሁትን እኔን በከበረ ሥጋና ደምህ ከኃጢአቴ እድፍ ታጥበኝ ዘንድ ነው ልመናዬ፡፡

በጌታ እጅ የታጠበው የሐዋርያት እግር እንዴት የታደለ ነው? በእሱ ስለታጠበ ዓለምን ዞሮ ወንጌል ለማዳረስ የቻለ እግር ሆነ፡፡ ጌታ ያላጠበው እግር ወንጌል ለዓለም አያደርስም፡፡ ባልታጠበ እግራችን ብንዞር እኛ እንጂ ወንጌል ዓለምን አይዞርም፡፡ ስለዚህ ሐዋርያ ሊሆን የሚሻ ሁሉ ጌታ ሆይ እግሬን እጠብልኝ ብሎ መለመን አለበት፡፡ ወንጌሉም 'የደቀ መዛሙርቱን እግር ሊያጥብ ጀመረ' ይላልና ክርስቶስ ደቀ መዝሙሩ ሊሆኑ ለሚወዱ ሁሉ እግራቸውን ማጠቡን አሁንም አያቋርጥም፡፡

ጌታ ያጠበው እግር ምን ይሆናል ካልከኝ 'የሚያምር እግር ይሆናል' እልሃለሁ፡፡ ሐዋርያት እግራቸው እጅግ ያምር ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ በእግሩ እብጠት የማይንቀሳቀሰው ቅዱስ ያዕቆብ ሳይቀር እግሩ ያማረ ነበር፡፡ ምክንያቱም 'መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው?' ተብሎ ተጽፎአል፡፡ ሮሜ 10፡15

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ

ሚያዝያ 24 2016 ዓ.ም.

ኢየሩሳሌም ፤ ፳ኤል
#share
#share

▫️@diyakonhenokhaile
https://t.me/diyakonhenokhaile
Forwarded from ኦርቶዶክስ ተዋህዶ መዝሙር (*•.¸♡ ㄒ乇ᗪᗪㄚ ♡¸.•*🇦🇷)
#የፍቅር_ ቀን#

እኔ የማከብረው ሁሌ ምዘክረው
አለኝ የፍቅር ቀን አለኝ የማረሳው
ልቤን አሸንፎት በእንባ የማወሳው
የኔ ውድ አፍቃሪ በቀጠሮው ሰአት በቀጠሮው ቦታ
ሳያረፍድ ተገኝቶ በዛች በከፍታ
በደሙ ቀለበት ገብቶልኝ ቃልኪዳን
በእውነተኛ ፍቅር ለእውነተኛ መዳን
ልሙትልሽ ብሎ በፅኑ መሀላ
መውደዱን ገልጦልኝ እንድኖር በተድላ
በዛች በለተ አርብ በፍቅር ቀናችን
ፍቅሩን ገልጦልኛል
ቀይ አበባ ሳይሆን ቀይ ደም ሰቶኛል
ስለዚህ ያቺ ናት እርሷ ናት
የኛ ቀን የኔና የውዴ
ለአለም የታየበት በርሱ መወደዴ።
      ወስብሐት ለእግዚአብሔር!


፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨
ክብርና ምስጋና ይግባው በእለተ አርብ ለተሰቀለው