Finote Hiwot የቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኀኔ ዓለምና ደብረ ትጉሃን ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ሕይወት ሰንበት ትምህርት ቤት
16.3K subscribers
15.6K photos
79 videos
172 files
1.81K links
የቀጨኔ መድኃኔዓለም ፍኖተ ሕይወት ሰንበት ትምህርት ቤት ነሐሴ 26/ 1958 ዓ.ም ተመሠረተ።
Download Telegram
#ጾመ ነቢያት (#የገና ጾም)

፠ ከ7ቱ አጽዋማት (ዐቢይ ጾም፣ ጾመ ፍልሠታ፣ ጾመ ሐዋርያት፣ ጾመ ነቢያት፣ ጾመ ድኅነት፣ ጾመ ነነዌ ና ጾመ ገሃድ) መካከል አንዱ ነው፡፡
፠ ኅዳር 15 ቀን ተጀምሮ እስከ ልደት ለአርባ ሦስት ቀናት የሚጾም ጾም ነው፡፡
፠ ይህንን ጾም በዘመነ ብሉይና በዘመነ ሐዲስ ብዙ ቅዱሳን ጾመውታል፤ በዚህም ምክንያት የሚከተሉት ስያሜዎች አሉት፡፡ እነርሱም፤

፩. ጾመ_አዳም፤ አዳም ዕፀ በለስን በልቶ ከገነት ከተባረረ በኋላ በፈጸመው በደል አዝኖ  ተክዞ አለቀሰ (እንባ ቢያልቅበት እዥ እስከሚያፈስ፤ እዥ ቢያልቅበት ደም በዓይኑ እስከሚፈስና ዓይኑ ይቡስ ወይም ደረቅ እስከሚሆን ድረስ አለቀሰ) ፥ ጾመ፣ ጸለየ፡፡ ከልብ የሆነ ጸጸቱን፣ ዕንባውን፣ በራሱ መፍረዱንም እግዚአብሔር አይቶ ተስፋ ድኅነት ሰጠው፡፡ ‹‹ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ፣ በደጅህ ድኼ፣ በዕፀ መስቀል ተሰቅዬ፣ ሞቼ አድንሃለሁ፡፡›› የሚል ነው፡፡ /ገላ. ፬፥፬፣ መጽ.ቀሌምንጦስ/ ስለዚህ ጾሙ የተሰጠው ተስፋ ፥ የተቆጠረው ሱባኤ ስለተፈጸመበት ‹‹ጾመ አዳም›› ይባላል፡፡

፪. ጾመ_ነብያት፤ ነቢያትም የምሥጢረ ሥጋዌ ነገር ተገልጦ ስለታያቸው፣ ክርስቶስ ለሰው ልጅ የሚከፍለውን የፍቅር ዋጋ በትንቢት ተመልክተው ጾመውታልና ጾመ ነቢያት ይባላል፡፡ ይህ ጾም ከአባታችን አዳም እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ድረስ የተነሱ አበውና እናቶች: ድኅነትንና ረድኤትን ሲሹ የጾሙት ጾም ነው:: በተለይ አባታችን አዳም: ቅዱስ ሙሴ: ቅዱስ ኤልያስ፣ ቅዱስ ዳንኤል ና ቅዱስ ዳዊት በጾማቸው የተመሰከረላቸው ቅዱሳን ናቸው:: (ዘዳ 9:19, ነገ. 19:8፣ ዳን. 9:3፣ መዝ. 68:10, 108:24) ቅዱሳን ነቢያት በጭንቅ በመከራ ሆነው የጾሙት ጾም ወደ መንበረ ጸባኦት ደርሶ ወልድን ከዙፋኑ ስቦታል፤ ለሞትም አብቅቶታል::

፫. ጾመ_ሐዋርያት፤ ሐዋርያት ‹‹ትንሣኤን ዐቢይ ጾምን ጾመን እናከብራለን፣ ልደትን ምን ሥራ ሠርተን እናከብረዋለን?›› ብለው ከልደተ ክርስቶስ በፊት ያሉትን ፵፫ ዕለታት ጾመዋልና፡፡

፬. ጾመ_ማርያም፤ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እግዚአብሔር አምላክ ቅድስናዋን አይቶ በቅዱስ ገብርኤል ብሥራት ወልደ አምላክን ያለ ሰስሎተ ድንግልና በግብረ መንፈስ ቅዱስ ጸንሳ እንደምትወልደው ቢነግራትም የትሕትና እናት ናትና ‹‹ምን ሠርቼ የሰማይና ምድርን ፈጣሪ እችለዋለሁ?›› ብላ ጌታን ከመውለዷ አስቀድማ ጾማለችና ‹‹ጾመ ማርያም›› ይባላል፡፡

፭. ጾመ_ፊልጶስ፤ ሐዋርያው ፊልጶስ በአረማውያን ዘንድ ገብቶ እያስተማረ ሳለ በሰማዕትነት ሲሞት፤ አስክሬኑ ከደቀ_መዛሙርቱ ስለተሰወረ፤ እግዚአብሔር የተሰወረውን የመምህራቸውን አስክሬን እንዲገለጽላቸው ከኅዳር ፲፮ ጀምረው ጾመው በሦስተኛው ቀን የመምህራቸው አስክሬን ተመልሶላቸዋል፤ ነገር ግን አስከሬኑ ቢመለስላቸውም ጾሙን ግን እስከ ልደት ቀጥለዋል፡፡

፮. ጾመ_ስብከት፤ የወልደ እግዚአብሔርን ሰው መሆን ያስተማሩበት፥ የሰው ልጆች ተስፋ የተመሰከረበት፥ የምስራች የተነገረበት ስለሆነ ጾመ ስብከትም ይባላል፡፡

፯. ጾመ_ልደት፤ የጾሙ መጨረሻ (መፍቻ) በዓለ ልደት ስለሆነ ‹‹ጾመ ልደት›› ይባላል፡፡

   ጾምን ትእዛዝ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን የፍቅርና የበረከት ምንጭ በመሆኑ ጭምር ደስ እያለን ብንጾመው የቅዱሳኑ በረከት ያድርብናል፡፡


/በቀጨኔ.ደ.ሰ መድኀኔዓለም ወደብረ.ት.ቅ.ገብርኤል ቤ.ክ ፍኖተ ሕይወት ሰ.ት.ቤት ሚዲያ እና ሕዝብ ግንኙነት ዋና ክፍል የተዘጋጀ/

#share
፨Facebook
https://www.facebook.com/FinoteHiwotSundaySchool
፨YouTube https://www.youtube.com/channel/UCWVKGH0mSJl47u44uopEb2w
፨Telegram
https://t.me/Finotehiwott
፨Tiktok
http://tiktok.com/@finotehiwot
፨Website www.finotehiwotsundayschool.com
#Share #like
❤16🙏5