Finote Hiwot የቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኀኔ ዓለምና ደብረ ትጉሃን ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ሕይወት ሰንበት ትምህርት ቤት
15.5K subscribers
15K photos
79 videos
169 files
1.77K links
የቀጨኔ መድኃኔዓለም ፍኖተ ሕይወት ሰንበት ትምህርት ቤት ነሐሴ 26/ 1958 ዓ.ም ተመሠረተ።
Download Telegram
Finote Hiwot የቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኀኔ ዓለምና ደብረ ትጉሃን ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ሕይወት ሰንበት ትምህርት ቤት
Photo
ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዓውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ዓሠርቱ ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፤

በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣
ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፣
የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፣
በሕመም ምክንያት በየፀበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፣
እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያት በሙሉ፣

በየዓመቱ የይቅርታ እጁን እየዘረጋ የሚመግበን እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ከዘመነ ማርቆስ ሁለት ሺሕ ዓሥራ ስምንት ዓመተ ምሕረት ወደ ዘመነ ሉቃስ ሁለት ሺሕ ዓሥራ ዘጠኝ ዓመተ ምሕረት በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ!
“ወይእዜኒ ነስሑ ወተጠመቁ፤ ወይደመሰስ ለክሙ ኃጢኣትክሙ፤ ወይመጽእ ለክሙ መዋዕለ ሣህል እምቅድመ ገጹ ለእግዚአብሔር፤ከጌታ ፊት የመጽናናት ዘመን እንዲመጣላችሁ፣ ኃጢአታችሁም እንዲደመሰስ አሁንም ንስሐ ግቡ ተመለሱም” (የሐ.ሥራ ፫፡፲፱)

የሰው ልጅ በስሑት ስራውና አእምሮው ምክንያት የኃጢአት ማዕበል በሚያናውጠው ባሕረ ዓለም እንደሚኖር ይታወቃል፤ የዓለሙ ባሕር በማዕበሉ በተናጠ ቁጥር በመርከቡ ተሳፍረው የሚጓዙ ሁሉ ጭንቀት ላይ መውደቃቸው የማይቀር ነው፤ በዚህ ጊዜ የሚያጽናና የቊርጥ ቀን ረዳትና ኃይል ያስፈልጋቸዋል፤ ሆኖም ረዳት በፍጥነት እንዲደርስላቸው መጮኽና መጣራት ከነሱ ያስፈልጋል፤ የምንኖርባት ዓለም ወይም ፕላኔት የክፋትና የጭካኔ ማዕበል በእጅጉ እየበረታባት መጥቶአል፤ ዓለማችን በስጋትና በፍርሓት፣ በራስ ወዳድነትና ባለመተማመን ተከባለች፣ በመሆኑም ዓለማችን ከምን ጊዜውም  በላይ የመጽናናት ዘመን እንዲመጣላት ትሻለች፤ እግዚአብሔር ለፍጥረቱ የሚያስፈልገውን ሁሉ አሟልቶ የሰጠ አምላክ እንደሆነ በግልጽ የሚታይ ነው፤ ይሁንና እግዚአብሔር ከኛ የሚፈልጋቸው ብዙ ነገሮች እንዳሉ በማያሻማ ሁኔታ አሳውቆአል፤ ከእነሱም መካከል በእውነተኛው መንፈስ ንስሐ መግባት፤ መጸጸትና መመለስ ናቸው፤ የዓለምን ሕዝብ በወሳኝነት ማጽናናት የሚችል እግዚአብሔር ብቻ ነው፤ እኛ ራሳችንን በራሳችን ለማጽናናት እንኳ በቂና ዘላቂ ዓቅም የሌለን ውሱኖች ነን፤ ይህንን እውነት ዓውቀን የእርሱን ርዳታ እንድንሻ እግዚአብሔር ይፈልጋል፤ ይህንንም ከልብ በመጸጸትና ከቀደመው ስሑት ተግባራችን በመመለስ በፊቱ ተንበርክከን መታዘዛችንን በተጨባጭ እንድናሳይ ይፈልጋል፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት!

እግዚአብሔር ከታላቅ ቸርነቱ የተነሣ የመታደስ ዘመንን በየዓመቱ ከመስጠት አልተቈጠበም፤ እንደ ሁሉጊዜ አሁንም አዲሱን ዘመን ባርኮ ሰጥቶናል፤ ሆኖም አዲሱ ዘመን የመጽናናት ዓመት እንዲሆንልን የእኛ ተሳትፎ ወሳኝ ሚና እንዳለው መዘንጋት የለብንም፤ ከሁሉ በፊት ያለፈውን ዓመት እንደ ግልም፣ እንደ ማኅበረ ሰብም፣ እንደ ሃገርም፤ እንደ ሃይማኖትም በኅሊናችን ልናስበውና ልንገመግመው ይገባል፤ ያለፈውን ዓመት በንጹህ ኅሊናችን በጥልቀት ስንገመግመው፤ የመጣንበትና ያለፍንበት ስለሆነ ኮለል ብሎ በፊታችን ይታያል፤ ጥቅሙም ሆነ ጉዳቱ በሙሉ ከኛ የራቀ ስለማይሆን ዳኝነት ለመስጠትና ውሳኔ ለመወሰን አንቸገርም፤ በመሆኑም ለፈጸምነው ስሕተት ይቅርታን ከመጠየቅ ባሻገር ድጋሚ ላንደግመው መወሰንና ለተግባራዊነቱ በጽናት መቆም አለብን፤ እኛ በዚህ ደረጃ ከቀደመው ስሕተታችን ተጸጽተን ንስሐ ከገባን እግዚአብሔር ከኛ የሚፈልገውን አግኝቶአል ማለት ነው፤ በመካከላችንም ትክክለኛ መግባባት ተፈጥሮአል ማለት ነው፤ በዚህ ጊዜ እሱም ዘላቂ የሆነ የመጽናናት ዘመን ለኛ ይሰጣል፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት!

በዓለሙ እንዳለው ሁሉ እኛም ወዲያና ወዲህ ከሚያወዛውዝ ፈተና አላመለጥንም ያለፈውን ዓመት በንጹሁ አእምሮአችን ስንመዝነው፤ ጥሩ የሚባል አልነበረም፤ በየአካባቢው ግጭቶች የቀጠሉበት፣ የሰው ደም የፈሰሰበት፣ ዕገታዎች የተፈጸሙበት፣ ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት የተቃጠሉበት፣ ምእመናን የተገደሉበትና የተፈናቀሉበት፣ ስጋት ያየለበት፣ ኑሮም የተወደደበት፣ ሌላም ሌላም ለሰው ልጅ የማይበጁ ነገሮች የተከሠቱበት ዓመት አሳልፈናል፤ ታዲያ አዲሱን ዘመን ስንቀበል እነዚህን ሁሉ እንዳሉ ይዘናቸው እንቀጥል ይሆን? ይህስ ከሆነ ‹‹እንኳን ለአዲሱ ዘመን አደረሳችሁ›› መባባሉ ትርጉም ይኖረው ይሆን? እንዲህስ ልንሆን ፈጽሞ አይገባም፤ ይልቁንም ባለፈው ዓመት የሆኑትን ሁሉ ላንደግማቸው ሁላችንም እንወስን፤ እነሱንም ማስቀረት እንችላለን፤ ምክንያቱም ችግሮቻችን በሙሉ ሰው ሰራሽ እንጂ የተፈጥሮ አይደሉም፤ ሰው ሰራሽ ችግሮች ደግሞ በሰው እንደመጡ ሁሉ በሰው ሊቀሩ የሚችሉ ናቸውና እናስቀራቸው፤ ጦርነቱን፣ ዕገታውን፣ ጥላቻውን፣ ፉክክሩን፣ እልከኝነቱን፣ ጭካኔውን ራስ ወዳድነቱን ግድያውን፣ አብያተ ሃይማኖት ማቃጠሉንና ማፍረሱን እኛው እንዳመጣነው እኛው ማስቀረት እንችላለን፤ ስንተወው እኮ ይቀራል፡፡

ስለሆነም ከልኂቅ እስከ ደቂቅ ያላችሁ ኢትዮጵያውያን ልጆቻችን ሁሉ ኢትዮጵያን እንዳለች የጋራ ዕድልና ሃብት አድርጋችሁ ተቀበሉ፤ ሌላውን ረጅም ጊዜ ሰጥታችሁም ቢሆን በውይይትና በመግባባት እየፈታችሁ በአንድነት ቀጥሉ፤ በይቅርታመንፈስ በአንድነት ተቃቅፎ ከመቀጠል ውጭ ሌላ የተሻለ ዕድል እንደሌለ በውል ተገንዘቡ፤ ለዚህ ሁላችሁም የበኩላችሁን ልባዊ ጥረት ከማድረግ አትቈጠቡ ብለን ከልብ እንመክራለን፡፡

በመጨረሻም፤

ለሁሉም መድኃኒቱ ቀና አእምሮ ነውና በአዲሱ ዓመት እግዚአብሔር ቅንና በጎ አሳቢ አእምሮ እንዲሰጠን በሱም ያሉብንን ጉድለቶች አርመንና አስተካክለን ሰላም የሰፈነበትን የመጽናናት ዘመን ማየት እንችል ዘንድ እግዚአብሔር አምላካችንን እንለምን፤ እኛም በንስሐ እንመለስ እያልን በድጋሚ እንኳን ለአዲሱ ዘመን በሰላም አደረሳችሁ በማለት አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን ፡፡    
እግዚአብሔር መልካም አዲስ ዘመን ያድርግልን፡፡
እግዚአብሔር ኣምላካችን ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ኣሜን!!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ
ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣
መስከረም ፩ ቀን ፳፻፲፱ ዓ.ም
አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ


• Facebook 👉 m.facebook.com/FinoteHiwotSundaySchool
• Telegram 👉 t.me/finotehiwott

• Tiktok 👉 tiktok.com/@finotehiwot 
• YouTube 👉 m.youtube.com/@finotehiwot1958
❤20🙏5
🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
“ወትባርክ አክሊለ ዓመተ ምሕረትከ ፤ በቸርነትህ ዓመታትን ታቀዳጃለህ” መዝ ፷፭ ፥ ፲፩

🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼

ለመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አማኞች ኢትዮጵያውያን በሙሉ እንኳን ከዘመነ ማርቆስ ወደ ዘመነ ሉቃስ ከ፳፻፲፰ ዓ.ም ወደ ፳፻፲፱ ዓ.ም አምላካችን አባታችን እግዚአብሔር በሰላም አሸጋገራችሁ እያልን የቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለምና ደብረ ትጉሃን ቅዱስ ገብርኤል አብያተክርስቲያናት መልካም ምኞቱን ይገልጻል።
ዓመቱን የተጣላን የምንታረቅበት፤ የተለያየን አንድ የምንሆንበት፤ ሥጋውን ደሙን የምንቀበልበት፤ በ፳፻፲፰ ዓ.ም ያልሰራነውን የመንፈስ ፍሬ የምናፈራበት፤ ከእግዚአብሔር ጋር የምንታረቅበት፤ ጦርነቱ ስደቱ ረሃቡ ከዓለማችን ከሀገራችን እንዲጠፋ እግዚአብሔርን የምንማጸንበት፤ ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት ዓመት እንዲሆንልን ምኞታችንን እንገልጻለን።

መልአከ ሰላም ዓምደወርቅ ደሴ
የቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለምና ደብረ ትጉሃን ቅዱስ ገብርኤል አብያተ ክርስቲያናት ዋና አስተዳዳሪ
ጷጉሜ ፭፥፳፻፲፰ ዓ.ም

🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼

• Facebook 👉 m.facebook.com/FinoteHiwotSundaySchool
• Telegram 👉 t.me/finotehiwott

• Tiktok 👉 tiktok.com/@finotehiwot 
• YouTube 👉 m.youtube.com/@finotehiwot1958
❤18🙏4
Finote Hiwot የቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኀኔ ዓለምና ደብረ ትጉሃን ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ሕይወት ሰንበት ትምህርት ቤት
Photo
💒🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼💒

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ውድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ተከታዮች ፤ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የፍኖተ ሕይወት ሰንበት ትምህርት ቤት አባላት በሙሉ፤
የአምላካችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ምሕረት አብሮን ሆኖ፣ አሮጌውን ዘመን አሳልፈን ለአዲሱ ዘመን ዘመነ_ሉቃስ
እንኳን በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ!
"የእግዚአብሔር ርኅራኄ አያልቅም። ማለዳ ማለዳም አዲስ ነው።" (ሰቆቃው ኤርምያስ 3፡22) እንዳለ፣ ይህንን አዲስ ዘመን በሰላም እንድናይ ያደረገንን፣ ባለፈውም ዓመት በቸርነቱ የጠበቀን እግዚአብሔር አምላካችን ስሙ የተመሰገነ ይሁን። ዘመናት እንደሚያረጁ ሁሉ በእግዚአብሔር ቸርነት ይታደሳሉና፣ ዘመኑ የተጨመረልን ልባችንን በንስሐና በመንፈሳዊ አዕምሮ አድሰን፣ በእምነታችን እንድንጠነክር፣ በጸሎት እንድንበረታና በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎታችን ሥር ሰደን እንድንቆም መሆኑን እያሰብን፣ የትላንቱን ስሕተታችንን አርመን፣ የተጣላን ታርቀን፣ ያለንን ለሌለው እያካፈልን፣ ስለ ተሰጠን ዘመንም በምስጋናና በንቁነት ኾነን ልንኖርበትና ልናገለግልበት  ይገባል።

የተወደዳችሁ ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን፤

ባለፈው ዓመት የሰንበት ትምህርት ቤታችን ፍኖተ ሕይወት የደረሰበትን ርቀት ስንዘክር፣ ከሁሉ በላይ የምናመስግነው እግዚአብሔርን ነው። ለረጅም ጊዜ ተስፋ ያደረግነውና የመማሪያና የአገልግሎት ቦታ እጥረታችንን በዘላቂነት የሚፈታው ባለ 5 ወለል ሕንፃችን ግንባታ በተያዘው ዘመን መጨረሻ የቁፋሮ ሥራ በመጀመሩ ለሁላችንም የተትረፈረፈ የምስጋና ምክንያት ሆኖናል።
ይህ ሕንፃ የእምነታችን፣ የትውልዳችንና የአደራችን ቤት ነው፤ ዛሬ ልጆቻችን ተምረውበት ነገ ሌሎችን የሚያስተምሩበት፣ ወጣቶቻችን በሃይማኖትና በምግባር የሚፀኑበት የጋራ ቤታችን ነውና ይህ ዓመት ከቀደመው ይልቅ መድኃኔዓለምን ረዳት በማድረግ ፍቅርና ትኅትናን ተላብሰን በአንድነት በመቆም የሕንፃውን ሥራ በጸሎታችን፣ በሙያችን፣ በሐሳባችን፣ በእውቀታችን፣ በገንዘባችንና በቁሳቁስ፣ እንዲሁም በምንችለው ሁሉ ተባብረን ለፍጻሜ የምናበቃበትን ዓመት ይሆን ዘንድ ወገባችንን ታጥቀን ቆርጠን እንድንነሳ ጥሪያችንን እና አደራችንን በአክብሮት እናቀርባለን።
በአዲሱ ዓመት ቸሩ መድኃኔ ዓለም ለሁላችን የማያልቀውን ቸርነቱንና ምህረቱን ያድለን፣ አገልግሎታችንን ይባርክልን፣ ሀገራችንና ቤተክርስቲያናችንን ይጠብቅልን።
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምድራችንን ሰላም፣ ሕይወታችንን ጥዑም ታድርግልን።


አቶ ጥላሁን ጸሐይ
የፍኖተ ሕይወት ሰ.ት/ቤት ዋና ሰብሳቢ
ጷጉሜ ፭፥፳፻፲፰ ዓ.ም

🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼

• Facebook 👉 m.facebook.com/FinoteHiwotSundaySchool
• Telegram 👉 t.me/finotehiwott

• Tiktok 👉 tiktok.com/@finotehiwot 
• YouTube 👉 m.youtube.com/@finotehiwot1958
❤30🙏3🔥1
#መዝሙር_ዘሰንበት
🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼

• Facebook 👉 m.facebook.com/FinoteHiwotSundaySchool
• Telegram 👉 t.me/finotehiwott

• Tiktok 👉 tiktok.com/@finotehiwot 
• YouTube 👉 m.youtube.com/@finotehiwot1958
🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼
❤25🙏4
#መዝሙር_ዘሰንበት
🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼

• Facebook 👉 m.facebook.com/FinoteHiwotSundaySchool
• Telegram 👉 t.me/finotehiwott

• Tiktok 👉 tiktok.com/@finotehiwot 
• YouTube 👉 m.youtube.com/@finotehiwot1958
🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼
❤13🙏5
Finote Hiwot የቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኀኔ ዓለምና ደብረ ትጉሃን ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ሕይወት ሰንበት ትምህርት ቤት
Photo
#መስከረም 10 ተቀጸል ጽጌ ፤ 
#ግማደ_መስቀሉ ከእስክንድርያ በንጉሥ ዳግማዊ ዳዊት አማካኝነት ወደ ኢትዮጵያ የገባበት ቀን 
፨
ተቀጸል ጽጌ የሚለውን ምስጢራዊ  መዝሙር የጀመረው የዜማና የቅኔ መሰራች የሆነው ቅዱስ ያሬድ ነው፡፡

የመሠረተውም በ6ተኛው መቶ ክፍለ ዘመን  #በአጼ #ገብረ_መስቀል ዘመነ መንግሥት ነው 
የክረምቱና የልምላሜው ጊዜ አልፎ የአበባውና የፍሬው ጊዜ በሚተካበት በመስከረም 25  ቀን ቅዱስ ያሬደ ውደ ንጉሡ  ዙፋን ቀረቦ #ተቀጸል_ጽጌ _ገብረ_መስቀል_አጼጌ በማለት ዘምራል ፡፡ 

ተቀጸል ጽጌ ብዙ ምስጢር ሲኖረው   ጽጌ (አበባ) የተባለ የንጉሠ ነገሥቱ #ዘውድ ነው ፤ እግዚአበሔር የንጉሡን ዘመን እንዲባርክለት ዘውዱን እንዲቀድስለት ፤ ተቀጸል ጽጌ  አጼጌ ፤ #ንጉሥ_ሆይ_ዘውድን_ተቀዳጅ_እያሉ_ለንጉሡ_ይጸልዩለታል ፡፡

ሌላዉ ትርጓሜ ደግሞ ጽጌ የተባለች #ሃይማኖት ናት  ፡፡ በኦሪት ቤተ መቅድስ #ያቁምና #በለዝ የሚባሉ ሁለት አዕማዶች  በቀኝና በግራ ተተክለው የቅዱስ #ጴጥሮስና  #ጳውሎስ ምሳሌ ሆነው ይኖሩ ነበር፡፡ በሁለቱ አዕማድ ራስ ላይ አንዲት አባባ ተቀርጻ ትታይ ነበር እሷም #የሃይማኖት ምሳሌ ነበረች፡፡ በዚሁ ዕለት በመዘምራኑ የሚነገረው ቀለም ፤ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ በሃይመኖት እልፍ ክርስቲያኖችን ማፍራታቸውን  በጉልህ ያስረዳል፡፡በሃይማኖተ አበው ላይ ፤ አሕዛብ አስተጋብኡ ጽጌ ረዳ ወሦኩሰ ተረፈ በኃበ አይሁድ ( አሕዛብ አበባ ሰበሰቡ እሾህ ግን በአይዱ ዘንድ ቀረ ) ተብሎ ስለተጻፈ ጽጌ የሚለውን ቃል ሃይማኖት ተብሎ እንደሚተረጐም ታሞኖበታል ፡፡

ከዚህም በመነሳት ሊቃውንት መዘምራን ሁል ጊዜ ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት ይህን ዝማሬ ለንጉሡ ያቀረባሉ ሊቃነ ጳጳቱም   ከቤቱ መንግሥቱ የቀረበላቸውን የተጐነገጐነ አበባ በመስቀላቸው ባርከው  ያማረውን አበባ  ለንጉሡ #ያድላሉ ከዛም ደግሞ  ለሌሎች አገልጋዮች እንደየ ማዕረጋቸው ይታደላል ፡፡

ይህ ስርዓት #ከአፄ_ገብረ_መስቀል ዘመነ መንግሥት እስከ #አፄ_ዳዊት_ዳግማዊ ድረስ በየዓመቱ መስከረም 25 ሲፈጸም ቆይቶ  በአፄ ዳግማዊ ዳዊት አማካኝነት ግማደ መስቀሉ መስከረም 10 ወደ ኢትዮጵያ ባስገባበት ቀን እንዲከበር  በሊቃውንት ተወስኖ  የአፄ መስቀል ( መስቀሉ ወደ ኢትዮጵያ የገባበት )ና የተቀጸል ጽጌ  በዓል እስከ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይል ሥላሴ ድረስ በቤተ መንግሥት እና በቤተ ክህነት ሲከበረ ቆይቶ  ኃላ ደግም በቤተ ክህነት እስከ አሁን ድረስ እየተከበረ ይገኛል ፡፡

  ለመጨረሻም ጊዜ ለንጉሠ ነገሥቱ የተዘመረው #ለቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሲሆን #ተቀጸል_ጽጌ_ኃይለ_ሥላሴ አጼጌ ተብሎ ተዘመሮ ሲያበቃ ለሊቀ ጳጳሳቱ  ድግሞ ጸሎቱን ማቅረብ ቀጥሏል፡፡ 

በዓሉ በቅድስት ሥላሌ ቤተክርስቲያ አሁን ድረስ ስርዓቱ በዓመት በዓመት መስከረም 10 እየተፈጸመ ይገኛል ፡፡


#መስቀሉ እንዴት ወደ ኢትዮጵያ እጅ ገባ ??

የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ #አባ ሚካኤል  በአሕዛብ ንጉሥ  በነበረው መርዋን ታሰሩ ይህ ንጉሥም ክርስቲያኖችን ማሰቃየትም ጀመረ  ፡፡ 

በዘመኑ የነበሩት  ንጉሥ አፄ #ሠይፈ አርዓድ የግብጽ ክርስቲያኖች ላይ መከራ እንዳበዛባቸው በሰሙ ጊዜ ፤ ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት ብለው ወደ ግብጽ ዘመቱ ፡፡ ንጉሡ  ከመድረሱም በፊት ደብዳቤ ጻፋ ፤ ሊቀ ጳጳሱን እንዲፈታና ክርስቲያኖችን እንዲተው አስተነቀቁት ፤ ደብዳቤውን ካየ በኃላ  እጅግ ፈርቶ ሊቀ ጳጳሱን ከእስራት  ፈታቸው  ንጉሱም ለበረከት እንዲሆናቸው ከጌታ ወርቅ(የሰበዓ ሰገል ወርቅ ) ጋር እንዲቀመጥ የእጅ መንሻ ወርቅ ለሊቀ ጳጳሱ ላኩላቸው ከዛ ወደ ሃገራቸው ተመለሱ ፡፡

ከዚህ በኃላ  እርሳቸው ሞተው የእመቤታቸን ወዳጅ የሆነው ልጃቸው ዳግማዊ ዳዊት ነገሠ  ፡ አሕዛቡ  ንጉሥ ሞታቸውን በሰማ ጊዜ አባ ሚካኤልን ዳግመኛ አሰራቸው ፤ ከዚያም የሮም የቁስጥንጥንያ የሶርያ የአርመን ፣ የግብፅ ክርስቲያኖች በአንድ ሆነው ለኢትዮጵያው ንጉሥ ለዓጼ ዳዊት፤ የክርስቶስን ሃይማኖት ለማጥፋት የአህዛብ ነገሥታት ቆመዋል የሚል  መልእክት ላኩ ፡ ዓጼ ዳዊት ይህን በሰሙ  ጊዜ መሃላ በመማፋረሱ ተናደዱ ፡፡መንፈሳዊ  ቅንዓትም አድረባቸው፡፡ 

ክተት ሠረዊት ብለው  ለጦር ዘምተው ካርቱም ሲደረሱ  #ግዮን (አባይ )ን መልስው ወደ ካሩተም በረሐ ሰደዱት የግብፅ ሰዎች ከእርሱ በቀር የሚጠጡት የለምና ፡፡
የምስሩ ንጉሥ እና መኳኳንንቶች ይህን በሰሙ ጊዜ ያረጉት ስህተት እንደሆነ ተረዱ ደንግጠው ሊቀ ጳጳሱን አባ ሚካኤልን ፈቱዋቸው ከሞት የተረፉትን ምእመናን ነጻ አወጧቸው ፡፡  ለዓለም ክርስቲያኖች ሁሉ ያማልዱት ዘንድ ለመነ። ክርስቲያኖችም ይህንን በሰሙ ጊዜ ነጻ ላወጣቸው ንጉስ  አመላካቸውን እግዚአብሔርን አመሰገኑ ፡፡

የግብፁ መኳንንት እጅ መንሻ ወደ ንጉሡ ላኩ   ፡ ንጉሥ ዳዊትም  ሊቀ ጳጳሱ መፈታታቸውን በሰሙ ጊዜ አስዋን ድረስ ወረዱ ይህም በጊዜው ለኢትዮጵያ እና ለግብጽ የወሰን ድካ የነበረው ነው ፡፡
ሰኔ 10 ቀን ከሊቀ ጳጳሳቱ እና ከመኳኳንንቱ ጋር ተገናኙ ፡፡  የአባይን ውሃ እንዲመልሱላቸው እልፍ ወርቅና ይዘው ቢጠይቋቸው ይህ ለኔ ነፍስ ለማዳን  አይጠቅመኝም አሉ   ፡፡ እኔ የምፈልገው የጌታቸንን መስቀል ነው አሉ ፡፡ እነርሱም ከተመካከሩ በኃላ መንፈሳዊ ንጉሥ መሆኑን አይተው ይገባዋል አሉ ፡፡  

መስቀሉንም  አስረከቧቸዉ  እርሱን ብቻ ሳይሆን #ሉቃስ የሣላቸውን ሰባቱን #የእመቤታችንን ሥዕሎች ፣ #ዮሐንስ ወንጌላዊ የሣለውን የጌታቸንን #የኵርዓተ ርእሱን ሥዕል ጭምር እንጂ ፡፡

ይህ ሁሉ የሆነው #መስከረም 10 ቀን ነው በዚችም ዕለት በመላው ኢትዮጵያ ብርሃን ሆነ ፤ የኢትዮጵያ ሕዝቦችም መስቀል ኃይልነ መስቀል ጽንዕነ  እያሉ ዘመሩ ይህን ልማድ በማድረግ አሁን ድረስ በዓሉ  ይከበራል የበዓሉም ስም #አጼ_መስቀል እየተባለ ይጠራል፡፡

ከዚህ ቦኃላ ወደ ጥንት ላማዱ እንዲሄድ የአባይን ወንዝ መለሰው ለግብጻዊያኑ ለቀቁላቸው ፡፡

ከቅዱስ መስቀሉ ረድኤት በረከት ይክፍለን    
   አሜን!
/በፍኖተ ሕይወት ሰ.ት.ቤት ሚድያና ሕዝብ ግንኙነት ዋና ማስተባበሪያ ክፍል የተዘጋጀ።/

• Facebook 👉 m.facebook.com/FinoteHiwotSundaySchool
• Telegram 👉 t.me/finotehiwott

• Tiktok 👉 tiktok.com/@finotehiwot 
• YouTube 👉 m.youtube.com/@finotehiwot1958
❤23🙏3
#መስከረም_16_የደመራ_በዓል_፣
#መስከረም_17_የመስቀል_በዓል_፤

    በሃገራችን ኢትዮጵያ መስቀልን በሚመለከት ከሚከበሩ በዓላት ውስጥ የደመራ መስቀል በዓል /መስከረም 16ና 17/ እንዲሁም መጋቢት 10 የመስቀለ ኢየሱስ በዓል ተያያዥነት ያላቸውና ዋነኞቹ ናቸው፡፡ የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ከጌታችን ሞትና ትንሣኤ በኋላ በቀራንዮ አደባባይ ጥቂት ጊዜ ከቆየ በኋላ ጌታችንን የገነዙት #ዮሴፍና #ኒቆዲሞስ ከቀራንዮ ወደ ጎልጎታ (ጌታችን ተቀብሮባት ወደነበረው መካነ መቃብር) ወስደው አኑረውታል፡፡

   አበው ሐዋርያት ወደየሀገረ ስብከታቸው ሲሄዱ የኢየሩሳሌሙ ጳጳስ ሐዋርያው #ያዕቆብ በኃላፊነት እንዲጠብቀው አድርገዋል፤ ከየአህጉረ ስብከታቸው ሲመለሱም በእግረ መስቀሉ ሥር እየተሰበሰቡ ይጸልዩ ነበር፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል #ማርያምም ጠዋትና ማታ በመስቀሉ ሥር ትጸልይ ነበር፡፡ ብዙ ሰዎች ታሪኩንና ቦታውን በክርስቶስ ደም የተቀደሰውን ክቡር መስቀሉን ለማየት ያመኑትም በረከት ለማግኘት ከየአቅጣጫው ይመጡ ነበር፡፡ በመስቀሉ ተዓምራት ብዙዎች ከተለያዩ ደዌ /በሽታ/ ተፈውሰዋል፡፡ ይህም በጣም ብዙ ሰዎች ክርስቶስን ወደ ማመን ስቧቸዋል፡፡ ይህን ድንቅ ሥራ የተመለከቱ የክርስቶስ ሰቃዮች /ሰቃልያነ ክርስቶስ/ በሁኔታው ባለመደሰታቸው ሕይወት የሆነውን የጌታ መስቀሉን ከጎልጎታ አንስተው ቀብረውት #ለ300 ዓመታት ያህል የከተማው ጉድፍና ጥራጊ እየጣሉበት የተቀበረበት ቦታ ኮረብታ እስኪሆን ድረስ ቆይቷል ‹‹በቀራንዮ መካን ዘደፈኑ አይሁድ፤ መስቀልከ ዕፀ ሕይወት፥ ዕፀ መድኀኒት›› እንዲል፡፡ ሆኖም #በ4ኛው መ/ክ/ዘመን ለክርስቲያኖች ነፃነት የሚያስብና የሚያስከብር ንጉሥ በሮም ተነሣ፡፡ የንጉሡም ስም ቈስጠንጢኖስ ይባል ነበር፡፡ ይህ ንጉሥ ክርስቲያኖችን ይበልጥ እንዲወድ ያደረገው በጠላቱ በማክሴንዲዩስ (መክስምያኖስ) ላይ በዘመተበት ጊዜ ገና በጉዞ ላይ እያለ ‹‹በዝንቱ ትእምርተ መስቀል ትመውዕ ፀርከ (በዚህ የመስቀል ምልክት ጠላትህን ድል ታደርጋለህ)›› የሚል በመስቀለኛ ቅርፅ የተጻፈ ጽሑፍ በጠፈር ሰማይ አይቶ በመስቀል ምልክት #ድል በማድረጉ ነው፡፡

     የንጉሥ #ቈስጠንጢኖስ እናት ንግሥት #እሌኒ የመስቀሉ ፍቅር ያደረባት፥ ታሪኩ በውስጧ የሰረጸባት ቅድስት እናት ነበረች ቈስጠንጢኖስም በዘመነ መንግሥቱ በትዕምርተ መስቀል ብዙ የድል ሥራ ስለሠራ ለመስቀሉ ታላቅ አክብሮትና አድናቆት ነበረው፡፡ ንግሥት እሌኒም መስቀሉን ለማግኘት ሰው ብትጠይቅ የሚያውቅ አላገኘችም፡፡ በመጨረሻ ግን የመስቀሉ መውጣት የእግዚአብሔር ፈቃድ በመሆኑ ኪራኮስ የሚባል አረጋዊና መቃርስ የሚባል ኤጲስ ቆጶስ አገኘች፡፡ ከእነዚህም አረጋዊው ኪራኮስ ዕድሜው የሸመገለና በእስራኤል ባህልና ደንብ ያደገ ነበር፡፡ እሌኒም እሱን ጠይቃ መስቀሉን ለማግኘት እንዲተባበራት ጠየቀችው ሆኖም ሊተባበራት ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ ረሃብና ጽም ስታበዛበት ግን የረሃብና የጽሙን መጽናት ተመልክቶ ከእነዚህ ከሦስት ተራሮች አንዱ እንደሆነ ነገራት፤ ከሦስቱ ተራራ የትኛው እንደሆነ ለማወቅ በእግዚአብሔር ፈቃድ ሱባኤ እንድትይዝ ነገራት፤ ሱባኤም ያዘች፡፡ ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር #መልአኩን ልኮ እንዲህ አላት ‹‹አንቺም ሰውም በከንቱ አትድከሙ እንጨት አሰብስበሽ፥ ደመራ አስደምረሽ፥ በእሣት አያይዘሽ፥ በፍሕሙ ላይ ዕጣን አፍስሽ፤ የዕጣኑ ጢስ ወደ ላይ ወጥቶ ወደ ታች ሲመለስ አቅጣጫውን ተመልክተሽ ጢሱ ያረፈበትን ቦታ አስቆፍሪው›› አላት፡፡ እርሷም መልአኩ እንዳላት እንጨት አሰብስባ #ደመራ አስደመረች ዕጣንም አፈሰሰችበት #ጭሱም ሰማይ ደርሶ ቅድመ ሥላሴ ሰገዶ  ወደ ምድር ሲመለስ ቦታውን አመለከታት ይህም የሆነው #መስከረም_16 ቀን ነው፡፡ እኛ ደመራ ብለን የምናከብረው ይህን አብነት በማድረግ ነው፡፡

    #መስከረም 17 ቀን ማለትም የደመራ በዓል ማግስት የምናከብረው የመስቀል በዓል ደግሞ ንግሥት እሌኒ ደመራ አስደምራ እጣን አጢሳ (አስጢሳ) የመስቀሉን ቦታ ካወቀች በኋላ #ቁፋሮውን_ያስጀመረችበት ዕለት ስለሆነ ነው፡፡ ከቁፋሮውም በኋላ የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ዳግመኛ በእግዚአብሔር ፈቃድ፤ በእሌኒ ተነሳሽነት፤ በረዳቶቿ አጋዥነት ቁፋሮ በተጀምረ ከ5 ወር ከ23 ቀን በኋላ መስቀሉ መጋቢት 10 ተገኝቷል፤ ከ10 ዓመት በኋላም ቤተ መቅደሱ ታንጾ ቅዳሴ ቤቱ ተከብሯል፡፡ መስቀሉም እንደቀድሞ ድውያንን ሲያድን፣ ለምጻምን ሲያነጻ፣ ሽባዎችን ሲያቀና፣ ሙታንን ሲያስነሳ፣ የማያምኑትን ወደ ማመን ሲመልስ ነበር፡፡ ዛሬም የክርስቶስ መስቀል በዓለም እያበራ ሕሙማንን እየፈወሰ ይገኛል፡፡ ይህ የጌታ #ዕፀ መስቀልም በዓፄ #ዳዊት ዘመን ወደ ሃገራችን ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በተለያዩ ቅዱሳት መካናት (እንጦጦ #ማርያም፣ ጋራ #መድኃኔዓለም፣…..) ሲያርፍ ቆይቶ በስተመጨረሻው ‹‹አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል›› ተብሎ ለዓፄ #ዘርዓ ያዕቆብ በተነገረው መሠረት በደብረ ከርቤ ግሸን ማርያም በክብር አርፏል፡፡ እኛንም በመስቀሉ ፈዋሽነት ይማረን የመስቀሉን ፍቅር በልባችን ይሳልብን አሜን፡፡

* "መስቀል መልዕልተ ኩሉ ነገር: ያድኅነነ እምጸር" /ሊቁ ቅዱስ #ያሬድ/
* ‹‹ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ።›› /ብርሃነ ዓለም ቅዱስ #ዻውሎስ ገላ.6፥14፣ 1ኛቆሮ.1፥18/

፠፠፠ #የመስቀል_ክብረ_በዓላት_

#መስከረም_16_የደመራ_በዓል_፤
#መስከረም_17_የመስቀል_በዓል_፤
#መስከረም_10_ተቀጸል_ጽጌ_፤
#መጋቢት_10_መስቀሉ_የተገኘበት_በዓል፤

/በፍኖተ ሕይወት ሰ.ት.ቤት ሚድያና ሕዝብ ግንኙነት ዋና ማስተባበሪያ ክፍል የተዘጋጀ።/

• Facebook 👉 m.facebook.com/FinoteHiwotSundaySchool
• Telegram 👉 t.me/finotehiwott

• Tiktok 👉 tiktok.com/@finotehiwot 
• YouTube 👉 m.youtube.com/@finotehiwot1958
🙏5❤2
(መስከረም ፲፯ን ከ፲፰ አብያተ ክርስቲያናት የት ሊያከብሩ ዐስበዋል?)
#መስከረም ፲፯፤ #በዓለ_አስተርእዮተ_መስቀለ_ኢየሱስ፡፡
#በአዲስ_አበባ_የመስቀለ_ኢየሱስ_ክብረ_በዓል_የሚከበርባቸው_ #፭ #ገዳማትና_አድባራት፡፡

፩. ቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኀኔ ዓለምና ደብረ ትጉሃን ቅዱስ ገብርኤል ቤ/ክ፤
አድራሻው፤ ጉለሌ ክፍለ ከተማ፥ ቀጨኔ፤
ታክሲ፤ ከፒያሳ(መርካቶ) → ቀጨኔ (መድኀኔ ዓለም)፤

፪. ደብረ ዕንቊ ልደታ ለማርያም ቤ/ክ፤
አድራሻ፤ የካ ክፍለ ከተማ፥ ቀበና (ራሽያ/እንግሊዝ/ ኤምባሲ ጀርባ)፤
ታክሲ፤ ከፒያሳ (መገናኛ) → ቀበና፤

፫. ደብረ ከዋክብት አቡነ አረጋዊና ገብረ ክርስቶስ ቤ/ክ፤
አድራሻው፤ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ፥ ዘነበ ወርቅ (አለርት ሆስፒታል)፤
ታክሲ፤ ከፒያሳ ሸዋ ዳቦ ቤት → ዘነበ ወርቅ (አየር ጤና በሚለው ታክሲ)
ወይም ከሜክሲኮ (ጦር ኃይሎች) → ዘነበ ወርቅ

፬. ደብረ ሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤ/ክ፤
አድራሻው፤ መስቀል አደባባይ፤
ታክሲ፤ ከፒያሳ (ሽሮሜዳ) → መስቀል አደባባይ (ቦሌ በሚወስደው ታክሲ)፤

፭. መካነ ጎልጎታ ረጲ መድኃኔዓለም ቤ/ክ፤
አድራሻ፤ ካራ ቆሬ፤
ታክሲ፤ ከፒያሳ(ሜክሲኮ፤ መርካቶ፤ መገናኛ) → አየር ጤና ካራ፤

#በኢትዮጵያና_በዓለም_አቀፍ_ደረጃ_የመስቀለ_ኢየሱስ_ክብረ_በዓል_የሚከበርባቸው_ #፲፫ #ገዳማትና_አድባራት፡፡
፩. ደብረ ከርቤ ግሸን ማርያም፤ መስቀሉ በክብር ያረፈባት፤ ባለ መስቀልኛ ቦታ
አድራሻው፤ ደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት፥ አምባሰል፤
ትራንስፖርት፤ ከአ.አ. ጉርድ ሾላ አውቶቡስ ተራ → ደሴ → አምባሰል (ግሸን)፡፡

፪. ዓሲምባ መስቀለ ኢየሱስ ቤ/ን ፤ በዐፄ ገብረ መስቀል ዘመን የተመሠረተ፤ በአባ ዘወንጌል አስተባባሪነት ሕንፃ ቤ/ኑ በአዲስ መልክ የታነጸ፡፡
አድራሻው፤ ምሥራቅ ትግራይ ሀገረ ስብከት ፥ ኢርብ ወረዳ → ዓሲምባ፤
ትራንስፖርት፤ ከአ.አ. ጉርድ ሾላ አውቶቡስ ተራ → መቀለ → ዓዲግራት → 80 ኪ.ሜ. ዓሲምባ፡፡

፫. ደብረ ሊባኖስ ገዳም መስቀል ቤት፤ (በዓመት አንዴ ብቻ የሚቀደስበት)፡፡
አድራሻው፤ ሰሜን ሸዋ ሰላሌ ሀገረ ስብከት ፥ ደብረ ሊባኖስ ገዳም፤
ትራንስፖርት፤ ከአ.አ. ጉርድ መርካቶ አውቶቡስ ተራ → ደብረ ሊባኖስ (ገዳም)፡፡

፬. ደብረ ብርሃን ጎሽባዳ አዳኙ መስቀለ ኢየሱስ፤ (መስቀሉ ያረፈበት)
አድራሻው፤ ሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት፥ ደብረ ብርሃን፤
ትራንስፖርት፤ ከአ.አ. ጉርድ ሾላ አውቶቡስ ተራ → ደብረ ብርሃን → (17 ኪ.ሜ.) ጎሽ ባደ፡

፭. ባሶና ሞይ ሜዳ መስቀለ ኢየሱስና ቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክ፤ (መስቀሉ ያረፈበት)
አድራሻው፤ ሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት፥ ባሶና ወረዳ ሞይ ሜዳ ቀበሌ፥ መስቀለ ኢየሱስ ንዑስ ቀበሌ፤
ትራንስፖርት፤ ከአ.አ. ጉርድ ሾላ አውቶቡስ ተራ → ደብረ ብርሃን → ባሶና /ሞይ ሜዳ/፡፡

፮. ቡልጋ ሀገረ ማርያም ግርማ አገር መስቀለ መስቀለ ኢየሱስ ቤ/ክ፤
አድራሻው፤ ሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት፥ ቡልጋ ሀገረ ማርያም ወረዳ፥ ግርማ አገር ቀበሌ፤
ትራንስፖርት፤ ከአ.አ. ጉርድ ሾላ አውቶቡስ ተራ → በደብረ ብርሃን መስመር → ቡልጋ/ግርማ አገር ቀበሌ/፡፡

፯. አንኮበር መስቀለ ኢየሱስ፤
አድራሻው፤ ሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት፥ አንኮበር፤
ትራንስፖርት፤ ከአ.አ. ጉርድ ሾላ አውቶቡስ ተራ → ደብረ ብርሃን → (42 ኪ.ሜ.) አንኮበር፡፡

፰. ደራ ቁላላ መስቀለ ኢየሱስ ከምትባል አጥቢያ
አድራሻው፤ ደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት፥ ደራ ወረዳ፥ ቁላላ፤
ትራንስፖርት፤ ከአ.አ. መርካቶ አውቶቡስ ተራ → ባሕር ዳር → ወረታ → ደራ ወረዳ /ቁለላ/፡፡

፱. ደራ ጉንደ መስቀል መካነ ሰላም መስቀለ ኢየሱስ ገዳም፤
አድራሻው፤ ሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት፥ ደራ፤
ትራንስፖርት፤ ከአ.አ. ጉርድ ሾላ አውቶቡስ ተራ → ደራ መካነ ሰላም፡፡

፲. ወላይታ ኮንታ አደ ኦፋ መስቀለ ኢየሱስ እና ቁስቋም ማርያም ቤ/ን ፤
አድራሻው፤ ወላይታ ኮንታ ሀገረ ስብከት ፥ በዳሞት ጋሌ ወረዳ፥ አደ ኦፋ ፤
ትራንስፖርት፤ ከአ.አ. አየር ጤና አውቶቡስ ተራ → ወላይታ፡፡

፲፩. ሐዋሳ ሎቄ ደብረ መድኀኒት መስቀለ ኢየሱስ ቤ/ን ፤
አድራሻው፤ አዋሳ ሲዳሞ ሀገረ ስብከት ፥ አዋሳ ፤
ትራንስፖርት፤ ከአ.አ. ቃሊቲ አውቶቡስ ተራ → አዋሳ፡፡

፲፪. ሰባት ቤት ጉራጌ እዣ ኩበና ሚካኤል፤ (በድርብነት ይከብራል)፡፡
አድራሻው፤ ጉራጌ ሀገረ ስብከት ፥ እዣ (ከደቡቡ ቁልቢ ደብረ ወርቅ አትርፎ ጊዮርጊስ ቤ/ን አጠገብ)፡፡
ትራንስፖርት፤ ከአ.አ. አየር ጤና አውቶቡስ ተራ → ጉራጌ/እዣ/፤

፲፫. ዶዶላ መስቀለ ኢየሱስ፤
አድራሻው፤ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ፥ ዶዶላ፤
ትራንስፖርት፤ ከአ.አ. ቃሊቲ አውቶቡስ ተራ → ሻሸመኔ → ዶዶላ፡፡
🙏6❤3