Finote Hiwot የቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኀኔ ዓለምና ደብረ ትጉሃን ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ሕይወት ሰንበት ትምህርት ቤት
15.3K subscribers
14.7K photos
78 videos
156 files
1.71K links
የቀጨኔ መድኃኔዓለም ፍኖተ ሕይወት ሰንበት ትምህርት ቤት ነሐሴ 26/ 1958 ዓ.ም ተመሠረተ።
Download Telegram
እንኳን ለቅዱስ ያሬድ በዓለ ስዋሬ በሰላምና በጤና አደረሳችሁ አደረሰን፡፡
#14ቱ_የቅዱስ_ያሬድ_ገዳማትና_አድባራት፡፡
እሑድ ግንቦት 11 ከዋይዜማው ጀምሮ ቀጠሯችሁን የት ለማድረግ አስባችኋል???፤ በአቅራቢያችሁ በሚገኙ የቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን ታደርጉ ዘንድ 12ቱን የቅዱስ ያሬድ ገዳማትና አድባራት እናስተዋውቃችሁ፡፡
፠ (#ቅዱስ_ያሬድን_ያልዘከረ_ኢትዮጵያዊ_ምኑን_ኢትዮጵያዊ_ኾነ!?)
፠ (#ቅዱስ_ያሬድን_ያልዘከረ_ካህን_ምኑን_ካህን_ኾነ!?)
፠ (#ቅዱስ_ያሬድን_ያልዘከረ_ሰንበት_ተማሪ_ምኑን_ሰንበት_ተማሪ_ኾነ!?)
1.  #ደብረ_ሐዊ_ቅዱስ_ያሬድ_ገዳም፤ (ሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት በበየዳ ወረዳ ቤተ ክህነት ከራስ ደጀን ተራራ አጠገብ የሚገኝ)፡፡ እመቤታችን በስደቷ ወቅት ያረፈችበት፤ ጃንደረባው ባኮስ የተሠወረበት፤ ቅዱስ ያሬድ ለ22 ዓመታት የመነነበት፥ ያስተማረበትና የተሠወረበት፤ በሀገራችን ትልቁ የሱባዔ መግቢያ ቅዱስ መካን፤ በዓለም ላይ በሃገራችን ብቻ፤ ከሀገራችንም በአብዛኛው በሰሜን ተራሮች ላይ ብርቅዬ ኾነው የሚገኙት ዋልያና ጭላዳ በአብዛኛው የሚገኙበት ቦታም ነው፡፡ በዚህ ቦታ ቅዱስ ያሬድ ያስተማረበትና የተማሪዎቹ ወንበር ጕባኤ ቦታና የደንጊያ ወንበር፤ ጽዮንን ከሩቅ እያየ ያለቀሰበት ቦታ ላይ የፈለቀ ጠበልና በዘንጉ ያፈለቀው ፈዋሽ ጠበል፤ የተሠወረበት የዋሻ ቤተ ክርስቲያን፣ እንዲሁም አበውና እማት የሚኖሩበት ገዳም ይገኛል፡፡)
2.  #በየዳ_ደብረ_ገነት_ቅዱስ_ያሬድ_ቤተ_ከርስቲያን፤ በደብረ ሐዊ ተራራ በስተጀርባ የሚገኝ ሲኾን፤ ቅዱስ ያሬድ በደብረ ሐዊ በምናኔ እንደመኖሩ መጠን በተራራው ጀርባ በገጠሩ መንደር የሚገኙ ምዕመናን እኛም ቅዱስ ያሬድን ልንዘክረው ይገባል፤ የቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን ደብረ ሐዊ ላይ ብቻ ሳይኾን በኹሉም ቦታ መኖር ይገበዋል በሚል መንፈሳዊ ቅንዓት ተነሣሥተው የሠሩት ነው፡፡)
3.  #ጣና_ቂርቆስና_ቅዱስ_ያሬድ_ገዳም፤ (ከፎገራ ከመንገዱ የ3 ሰዓት መንገድ እንደተጓዙ፤ በመርከብ ደግሞ ከባሕር ዳር፣ ከጎርጎራ፣ ከደልጊ፣ ከቁንዝላ ተሣፍረው ከጣና ክርስቶስ ሠምራ አጠገብ የሚያገኙት ታላቅ ገዳም ነው፤ መስዋዕተ ኦሪት ይሰዋበት የነበረ፤ ታቦተ ጽዮን ለበርካታ ዓመታት ያረፈችበት፤ ቅዱስ ያሬድ ምልክት ያለውን ድጓ የጻፈበት ቦታ ነው)
4.  #ወገራ_ደልደሊት_ቅዱስ_ያሬድ_ቤተ_ክርስቲያን፤ (በሰሜን ጎንደር ወገራ አውራጃ አምባ ጊዮርጊስ ወረዳ የሚገኝ ሲኾን፤ በቅዱስ ያሬድ ዜማ ከብቶች ኹሉ ተመስጠው ሳያርሱ በመቆማቸው ምክንያት ቅዱስ ያሬድ የተገረፈበት ቦታ ነው)
5.  #አኵሱም_ደብረ_ዝማሬ_ቅዱስ_ያሬድ_ቤተ_ክርስቲያን፤ (ከአኵሱም ዩኒቨርሲቲ አጠገብ የሚገኝ ሲኾን፤ የአኵሱም ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንዴት ቅዱስ ያሬድ ተወልዶ ባደገባት፥ ተምሮ ባስተማረባት፤ ሰማያዊ ምሥጢራትና በተገለጡለት፤ የተሰዓቱ ቅዱሳንን የበርካታ ቅዱሳን መናኸሪያ በኾነችው፤ የገዳማትና የአድባራት ራስ፤ የምዕመናን ሁሉ አምባ መጠጊያ በኾነችው ከተማ እንዴት መታሰቢያ ቤተ ከርስቲያን ሳይሠራለት እስካሁን ቀረ ብለው በመንፈሳዊ መነሣሣት በአጭር ጊዜ ውስጥ ያሠሩት ቤተ ክርስቲያን ነው)
6.  #አኵሱም_ማይኪራህ_ደብረ_መድኀኒት_ወፈለገ_ጥበብ_ቅዱስ_ያሬድ_ቤተ_ክርስቲያን፤ (ከአኵሱም ከተማ በ4 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በቅዱስ ያሬድ የትውልድ ቦታ አጠገብ በዋናው መንገድ ዳር የሚገኝ ቤተ ክርስቲያን ነው፤ ቅዱስ ያሬድ ከትሏ መውደቅና መነሳት በመመልከት ማስተዋልን የተማረባት ቦታ ስትኾን ሾላዋ እስካሁንም ድረስ እየተካች ትገኛለች፤ ከሾላው ሠር የሚፈልቅ ፈዋሽ ጠበልም አለ፡፡ ይህ ቤተ ክርስቲያን የተሠራው የአኵሱም ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የደብረ ዝማሬን ቤተ ክርስቲያን ሲሰሩ የሃገሬው ሰው ተመልክቶ እንዴት የትውልድ ቦታው ላይ እኛ ቤተ ክርስቲያን ሳንሠራ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ቀድመውን ሠሩ በሚል መንፈሳዊ ቅንዓት ተነሣሥጠው በተፋጠነ ሁኔታ ያነጹት ነው፡፡)
7.  #አዲስ_አበባ_ደብረ_ይባቤ_ቅዱስ_ያሬድ_ቤተ_ክርስቲያን (አዲስ አበባ ጎተራ ማሰለጫ መንገድ አጠገብ የሚገኝ ቤተ ክርስቲያን ሲኾን፤ የቅዱስ ያሬድ ፍቅር በልባቸው ባደረባቸው እናት ወ/ሮ ደስታ ሞላ በ1948 የተሠራ ሲሆን ኋላ ላይ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት የፓትርያርክነት ዘመን በምዕመናን አሁን ያለው ሕንፃ ቤ/ክ ተሠርቷል፤ የቅዱስ ያሬድ ትምህርቶች እየተሰጡበት የሚገኝና ወደፊትም በኮሌጅ ደረጃ አስፋፍቶ በርካታ ደቀመዛሙርትን ለማስተማር እቅዱ አለ፤ በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ፈዋሽ ጠበልም ይገኛል፡፡)
8.  #ጎንደር_ደብረ_ሣህል_ቅዱስ_ሩፋኤል_ወአቡነ_ሐራ_ድንግል_ቤተ_ክርስቲያን፤ (ይህ ቤተ ክርስቲያን በጎንደር ከተማ የሚገኝ ከ44ቱ ታቦታተ ጎንደር አንዱ ሲኾን፤ በዚህ ቦታ ታቦተ ቅዱስ ያሬድ በድርብነት ይከበራል)
9.  #ደብረ_ብርሃን_አንሳስ_ማርያም_ቤተ_ክርስቲያን (በደብረ ብርሃን ከተማ የምትገኝ ቤተ ክርስቲያን ስትኾን ፈዋሽ ጠበል ያለባትና፤ የአቋቋሙ ሊቅ፣ የቅዳሴና የሌሎች ዜማ ትምህርቶች መምህር የኾኑት  የመምህር ለምኔ ማስተማሪያ ደብር ነች፤ በዚህ ቦታ ታቦተ ቅዱስ ያሬድ ያሬድ በድርብነት ይከበራል)
10.  #ጀርመን_ክሮምበርግ_ቅዱስ_ዑራኤልና_ቅዱስ_ያሬድ_ቤተ_ክርስቲያን (በጀርመን ሃገር በክሮምበርግ ከተማ የሚገኝ ቤተ ክርስቲያናችን ነው፡፡)
11.  #ዋሽንግተን_ዲሲ_ኆኅተ_ምሥራቅ_ኪዳነ_ምሕረት_ቤተ_ክርስቲያን፤ (በአሜሪካ ሃገር ዋሽንግተን ዲሲ የምትገኝ ቤተ ክርስቲያን ስትኾን፤ በዚህ ቦታ ታቦተ ያሬድ በድርብነት ይከበራል)
12.  #ርዕሰ_አድባራት_ዱባይ_ሻርጃ_አጅማን_ሰአሊተ_ምሕረት_ቅድስት_ማርያም_ቤ/ክ (በዱባይ ሃገር ሻርጃ አጅማን የምትገኝ ቤተ ክርስቲያን ናት፤ በዚህ ቦታ ታቦተ ቅዱስ ያሬድ በድርብነት ይከበራል)
13.  #ባሕር_ዳር_ፈለገ_ጥበብ_ቅዱስ_ማርቆስና_ቅዱስ_ያሬድ ቤ/ክ፤ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ይባብ ካምፓስ አጠገብ የሚገኝ፡፡
14.  #ደቡብ_አፍሪካ_የቅድስት_ሥላሴና_የቅዱስ_ያሬድ_ገዳም፤ በደቡብ አፍሪካ የሚገኝ፡፡
ከላይ በተጠቀሱት በአቅራቢያችን ባሉ ገዳማትና አድባራት እንድንገናኝ መድኀኔ ዓለም ይፍቀድልን፡፡

/በፍኖተ ሕይወት ሰ.ት.ቤት ሚድያና ሕዝብ ግንኙነት ዋና ማስተባበሪያ ክፍል የተዘጋጀ።/

• Facebook 👉 m.facebook.com/FinoteHiwotSundaySchool
• Telegram 👉 t.me/finotehiwott

• Tiktok 👉 tiktok.com/@finotehiwot 
• YouTube 👉 m.youtube.com/@finotehiwot1958
10
#ሥርዐተ_ማኅሌት_ዘግንቦት_11ና_የቅዱስ_ያሬድ_ሌሎች_መጠሪያ_ስሞች

#ማሕሌቱን_ለማሕሌት_አባት_እናቅርብለት

፠ ጥዑመ ልሳን፤
፠ የሱራፌል አምሳያ፤
፠ የቤተ ክርስቲያን እንዚራ፤
፠ የቤተ ክርስቲያን ብርሃን፤
፠ መዓርዒረ ዜማ፤
፠ ካህን (ካህነ ስብሐት)
፠ ማኅሌታይ፤
፠ መዘምር ዘበድርሳን፤
፠ ሊቅ (ርእሰ ሊቃውንት)
፠ ዓርከ ሊቃውንት፤
፠ ደራሲ፤
፠ የመጽሐፍ መምህር፤ (ብሉያትንና ሐዲሳትን የሊቃውንትንም መጻሕፍት አስማምቶ የተረጐመ)
፠ ባለቅኔ (የቅኔ ጀማሪ)፤
፠ የቤተክርስቲያን ጌጧና መሠረቷ ሕይወቷና እስትንፋሷ
፠ ልዑለ ስብከት፤
፠ ሰማዕት፤
፠ ባሕታዊ፤
፠ መናኝ
፠ የዜማ አባት፤
፠ የኢትዮጵያ ብርሃን፡፡
፠ አንደበቱ ጣፋጭ (ጥዑም) የኾነ::
፠ እግሮቹ በመልካም መንገድ የሚጓዙና ወደ መልካም መንገድ የሚያስጕዙ
፠ ልቡናው የቅድስና ማኅደር የኾነ::
፠ ሕሊናው የምሥጢራት ሠረገላ የኾነ::
፠ አእምሮው የመጠቀ፤
፠ ድርሰቱ የተራቀቀ፤
፠  እስከ አርያም ተነጥቆ ዕፁብ ድንቅ ምሥጢራትን የተመገበ ማን እንደርሱ:: …...

/ማኅሌቱን በአ.አ ደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤ/ክ የምትቆሙ በደብረ ይባቤ የሚለውንና በሰማየዊ ቀለም የተቀባውን እየመረጣችሁ መጠቀም ስትችሉ፤ በሌሎች አድባራት ግን ሰማያዊ ቀለም የሌለበትን (በቢጫና እንዲሁ ያለቀለም የተቀመጠውን) እየመረጣችሁ መጠቀም ትችላላችሁ፡፡/

፨*፨(ሥርዐተ ማኅሌቱን ስናዘጋጅ #የደብረ_ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያንን ይትበሃል በመስጠት ለተባበራችሁን ለሊቀ ጠበብት አባ ኤርምያስና አርድዕቶቻቸው በተለይም ለዲ.ን አውራሪስ አምላከ ቅዱስ ያሬድ መድኀኔ ዓለም ይስጥልን፡፡)

/በፍኖተ ሕይወት ሰ.ት.ቤት ሚድያና ሕዝብ ግንኙነት ዋና ማስተባበሪያ ክፍል የተዘጋጀ።/

• Facebook 👉 m.facebook.com/FinoteHiwotSundaySchool
• Telegram 👉 t.me/finotehiwott

• Tiktok 👉 tiktok.com/@finotehiwot 
• YouTube 👉 m.youtube.com/@finotehiwot1958
14
ዕርገተ እግዚእ
እንኳን ለጌታችን በዓለ ዕርገት አደረሳችሁ፥ አደረሰን፤ በዓሉን የሚመለከት ጽሑፍና ሥርዐተ ማኅሌቱን እንደተለመደው አቅርበንላችኋል፡፡ መልካም ንባብ፤ መልካም የምሥጋና ማኅሌት፡፡

‹‹አልቦ ዘዓርገ ውስተ ሰማይ ዘእንበለ ዘወረደ እምሰማይ ወልደ ዕጓለመሕያው፤ ከሰማይ ከወረደው የሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም፡፡›› ዮሐ.3፥13
ከሰማይ ከወረደው የሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም፡፡ እርሱም በሰማይ የሚኖረው ነው፡፡ ይህ ኃይለ ቃል ክብር ምስጋና ይግባውና ስለጌታችን፣ አምላካችን፣ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት መውረድ ከድንግል ማርያም መወለድ እና የሰውነቱን ሥራ ጨርሶ በክብር ወደ ሰማይ ማረጉን የሚገልጽ ነው፡፡ እንደሚታወቀው አምላካችን ስለሁለት ዐቢይ ጉዳዮች ሰው ሆኗል፡፡
1.  *ለቤዛነት /ዓለምን ለማዳን/
2.  *ለአርአያነት /ምሳሌነት/

የሰውን ልጅ በመውደዱ ልዑል ባሕርዩን ዝቅ አድርጎ ከሰማይ ወረደ ሥጋ ለበሰ በምድር ላይ ተመላለሰ፤ ምድርን በኪደተ እግሩ ቀደሰ፤ ድውያንን ፈወሰ፤ ፍጹም ሰው እንደ መሆኑ ተራበ ፍጹም አምላክ መሆኑንም ያስረዳ ዘንድ አምስት ገበያ ሕዝብ በአምስት እንጀራ በሁለት ዓሣ አጠገበ ማቴ.14፥19 ለእኛ አርአያና ምሳሌ ለመሆን ዝቅ ብሎ የደቀ መዛሙርቱን እግር አጠበ ዮሐ.13፥14 እኛም ፍለጋውን እንከተል ዘንድ አንትሙኒ ከመዝ ግበሩ ለቢጽክሙ እናንተም ለባልንጀሮቻችሁ እንዲሁ አድርጉ ብሎ አዘዘ፡፡ መምሕረ ትሕትና ነውና በዚህ ዓይነት መልኩ ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር በዚህ ዓለም ኖረ ለሐዋርያት ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ወንጌልን አስተማራቸው ትምህርት በሚገባ ከተረዳለት በኋላ ለድኅነተ ዓለም በማዕከለ ምድር በቀራንዮ ተሰቀለ፡፡

#ወገብረ_መድኀኒተ_በማዕከለ_ምድር_እንዲል_በምድር_መካከል_መድኀኒትን_አደረገ_መዝ.73፥12
‹‹እስመ ኢይደልዎ ለነቢይ መዊት በአፍአ ዘእንበለ በኢየሩሳሌም፤ ነቢይ በኢየሩሳሌም ነው እንጂ በውጭ ሊሞት አይገባውም፡፡›› ብሎ እንደተናገረ፡፡ ሉቃ.13፥33 በሞቱ ዓለምን አድኖ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሰ መቃብር አድሮ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ብርሃነ መለኮቱን ገልጾ ተነሣ፡፡ ነቢያት እንደተናገሩ ‹‹እግዚአብሔር ይነሣል ጠላቶቹም ይበተናሉ››� መዝ.67፥1 ‹‹እኔ ተኛሁ አንቀላፋሁ እግዚአብሔርም አስነሥቶኛልና ተነሣሁ፡፡›› መዝ.3፥5 ‹‹እግዚአብሔር አሁን እነሣለሁ ይላል መድኀኒትንም አደርጋለሁ በዕለቱም እገለጣለሁ››� መዝ.11፥5፡፡

‹‹ሥጋየ ደግሞ በተስፋ /በትንሣኤ/ ታድራለች ነፍሴን በሲዖል /በመቃብር/ አትተዋትምና/ እነሣለሁ ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትተወውም፡፡›› መዝ.15፥9 ‹‹አቤቱ ንቃ ለምንስ ትተኛለህ ተነሥ ለዘወትርም አትጣለን›› መዝ.43፥23 ‹‹እግዚአብሔር ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ›› መዝ.77፥65 ተብሎ የተተነበየውን ትንቢት ፈጽሞ ተነሣ፡፡ በሞቱ ሞታችንን ሻረልን፤ በመቀበሩም ሙስና መቃብርን አጠፋልን፡፡  ‹‹በሞቱ ሞትን አጠፋው›› እንዲል መጽሐፈ ኪዳን፡፡ ሕንፃ መነኮሳት ‹እርሱ በሁሉ ምሉዕ ሲሆን በመቃብር ለመቀበር ዮሴፍ ኒቆዲሞስ ገንዘውት ታየ፡፡ ከመሬት ውስጥ በመቀበሩም ሙስና መቃብርን አጠፋ፤ ከሥሩም ነቀለው ከተነሣ በኋላ ትንሣኤውን መጀመሪያ ለማርያም መግደላዊት ገለጸ ማር.16፥9፡፡  ቅዱስ ጳውሎስም ስለ ትንሣኤው ሲመሰክር ‹‹ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፤ ተቀበረም፤ መጽሐፍ እንደሚል፤ በሦስተኛው ቀን ተነሣ፡፡ ለኬፋም ታየ በኋላም ለአሥራ ሁለቱ ከዚያም በኋላ ከአምስት መቶ ለሚበዙ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታየ፡፡ ከዚያም በኋላ ለያዕቆብ ኋላም ለሐዋርያት ሁሉ ታየ›› 1ቆሮ.15፥3-8 ብሎ ክርስቶስ ትንሣኤውን ለተከታዮቹ በሙሉ የገለጠ መሆኑን መስክሯል፡፡ የሚያምኑ ፈሪሳውያንም ‹‹ትንሣኤው ምትሐት ነው›› እንዳይሉ እየታየ እያስተማረ እስከ 40 ቀን ድረስ መቆየቱን ይገልጽልና፡፡ በዚህም የአርባ ቀን ከትንሣኤ በኋላ ቆይታው ሦስት ቀን ጉባኤ አድርጎ ደቀ መዛሙርቱን እንዳስተማረ ቅዱስ ወንጌል ይነግረናል፡፡ ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ሲገለጥላቸው ይህ ሦስተኛ ጊዜ ነበረ እንዲል ዮሐ.21፥14 ይህንም ሊቃውንት አባቶቻችን፡-
1.  *የትንሣኤ
2.  *የአግብኦተ ግብር /ዳግም ትንሣኤ/
3.  *የጥብርያዶስ ነው ብለው አስቀምጠውታል በዚህ 40 ቀን ቆይታ መጽሐፈ ኪዳንን ለደቀ መዛሙርቱ አስተምሯል፡፡

ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስም ዕርገቱን ለመናገር ከሰማየ ሰማያት መውረዱን አስቀድሞ ከሰማይ ከወረደው ከሰው ልጅ በቀር ማንም ወደ ሰማይ የወጣ የለም እርሱም በሰማይ የሚኖረው ነው ብሎ ከዕርገቱ በኋላ በየማነ አብ፤ በዘባነ ኪሩብ በአምላክነት ሥልጣን ለመኖር ወደሰማይ የወጣ ከእርሱ በቀር ሌላ እንደሌለ አስረግጦ ነገረን፡፡ ሲጀምር ከሰማይ መውረዱን ማስቀደሙ ወረደ ብሎ ዐረገ ለማለት ይመቻል፡፡ ተጸነሰ ተወለደ ለማለት ጥንቱ ከሰማያት ወረደ ማለት እንደሆነ ሁሉ፤ ‹‹ተሰቀለ፤ ሞተ፤ ተቀበረ፤ ተነሣ'››ለማለት ‹‹ጥንቱ:- ተጸነሰ፤ ተወለደ፤ አደገ ተመላለሰ ሠላሳ ዓመት ኖረ›› የሚለው ነው፡፡ ስለሆነም ቅዱስ ዮሐንስ ጠርዝና ጠርዙን ይዞ ተናገረ፡፡ ‹‹ወረደ ዐረገ›› የሚሉት ሁለት ቃላት የዓለም ድኅነት መነሻና መድረሻ ናቸው፤ እነዚህን ሁለት ቃላት ስናይ በሁለቱ መካከል የተፈጸሙትን የአምላክ ሥራዎች ልብ ማለት ይገባል፡፡ ቤት በመሠረት ይጀመራል በጣሪያ ይፈጸማል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ይህን የቤዛነት ሥራ ሲያስረዳ በዮሐ.1፥14 ‹‹ቃል ሥጋ ኮነ፤� ቃል ሥጋ ሆነ›› ብሎ ጀምሯል ይህንም ቃል ‹‹ከሰማይ ከወረደው የሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም›› በማለት ሰው መሆኑን ብቻ ሳይሆን በአርያም የሚኖር መሆኑን አስተማረን፡፡ እንግዲህ ጌታችን ዕርገት እንዲሁ እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ አለመሆኑን ቀድሞ በነቢያት የተነገረ ኋላም በሐዋርያት የተመሰከረ መሆኑን ማወቅ ያስፈለጋል፡፡

#የክርስቶስ_ዕርገት_በትንቢተ_ነቢያት
‹‹ሰማዮችን ዝቅ ዝቅ አደረገ ወረደም ጨለማ /ዲያብሎስ/ ከእግሩ በታች ነበር በኪሩቤል ላይ ተቀምጦ በረረ በነፍሳትም ክንፍ በረረ››� መዝ.17፥9 ‹‹አምላክ በእልልታ እግዚአብሔር በመለከት ድምጽ ዐረገ መዝ.46፥5 ወደላይ ዐረግህ፥ ምርኮን ማረክህ ፥ስጦታንም ለሰዎች ሰጠህ›› መዝ.67፥18፡፡
‹‹ዘምሩ ለእግዚአብሔር ዘዓርገ ውስተ ሰማይ ዘመንገለ ጽባሕ፤ በምሥራቅ በኩል ወደ ሰማየ ሰማያት ለወጣ ለእግዚአብሔር ዘምሩ›› መዝ.67፥33፡፡

#የክርስቶስ_ዕርገት_በትምህርተ_ሐዋርያት
ጌታ ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ከተነጋገረ በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ፡፡ ማር.16፥19 ‹‹እስከ ቢታንያ አወጣቸው እጆቹንም አንሥቶ ባረካቸው ሲባርካቸውም ከእነርሱ ተለየ ወደ ሰማይም ዐረገ እነርሱም ሰገዱለትና በብዙ ደስታ ወደኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ ዘወትርም እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እየባረኩ በመቅደስ ኖሩ፡፡››� ሉቃ.24፥50 ‹‹ይህንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ ደመናም ከዐይናቸው ሰውራ ተቀበለችው፤ እርሱም ሲሄድ ወደ ሰማይ ትኩር ብለው ሲመለከቱ ሳሉ እነሆ ነጫጭ ልብስ ለብሰው ሁለት ሰዎች /መላእክት/ በአጠገባቸው ቆሙ ደግሞም ‹‹የገሊላ ሰዎች ሆይ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ስለምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት ዳግመኛ ይመጣል፡፡›› አሏቸው››� ሐዋ.1፥9-12 በማለት ሐዋርያት የክርስቶስን ዕርገት ከመላእክት ጋር ሆነው
21🤝1
እንደተመለከቱ ደስታውን እንደተካፈሉ ቅዱስ ሉቃስ ጽፎልናል፡፡ በትንሣኤው ነጭ ልብስ ለብሰው የታዩ መላእክት የደስታ ዘመን ነው ሲሉ በእርገቱም ነጭ ልብስ ለብሰው የዕርገቱን የምሥራች ለሐዋርያት አብስረዋል፡፡
/ምንጭ፤ የቃል ትምህርትና በመምህር ምሥጢረ ሥሳሴ ማናየ/
የአምላካችን ቸርነቱ ረድኤቱ አይለየን፡፡፠ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ፠

/በፍኖተ ሕይወት ሰ.ት.ቤት ሚድያና ሕዝብ ግንኙነት ዋና ማስተባበሪያ ክፍል የተዘጋጀ።/

• Facebook 👉 m.facebook.com/FinoteHiwotSundaySchool
• Telegram 👉 t.me/finotehiwott

• Tiktok 👉 tiktok.com/@finotehiwot 
• YouTube 👉 m.youtube.com/@finotehiwot1958
11🙏2👍1