Finote Hiwot የቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኀኔ ዓለምና ደብረ ትጉሃን ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ሕይወት ሰንበት ትምህርት ቤት
15.3K subscribers
14.7K photos
78 videos
156 files
1.71K links
የቀጨኔ መድኃኔዓለም ፍኖተ ሕይወት ሰንበት ትምህርት ቤት ነሐሴ 26/ 1958 ዓ.ም ተመሠረተ።
Download Telegram
ኢያቄምና ሐና ሰማይን ወለዱልን፤
ሰማያቸው ደግሞ ፀሐይን አስገኘችልን።

እንኳን አደረሳችሁ

/ፍኖተ ሕይወት ሰ.ት.ቤት ሚድያና ሕዝብ ግንኙነት ዋና ማስተባበሪያ ክፍል።/

• Facebook 👉 m.facebook.com/FinoteHiwotSundaySchool
• Telegram 👉 t.me/finotehiwott

• Tiktok 👉 tiktok.com/@finotehiwot 
• YouTube 👉 m.youtube.com/@finotehiwot1958
38🥰5
በአሰቦት ደብረ ወገግ ቅድስት ሥላሴና አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንድነት ገዳም በታጣቂዎች በተከፈተ ተኩስ አንድ ካህን ተገደሉ።

ተኩሱ የተከፈተው ከገዳሙ ታችኛው የእናቶች ገዳም ሲሆን ዛሬ ግንቦት 3 ቀን 2018 ዓ.ም 9:00 አካባቢ ነው ሲሉ  በስልክ ለማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

ታጣቂዎቹ ዙሪያውን ከበው በከፈቱብን  ተኩስ አንድ ካህን ተገድለዋል አስከሬንም ማንሳት አልቻልንም ያሉት መረጃ ሰጫችን እስካሁኗ ሰዓት የጸጥታ ኃይሎች አልደረሱም ብለዋል።

ገዳማውያኑ “እኛ ገዳማውያን ነን መሳሪያ የለንም፤ አባቶቻችን ለሚመለከታቸው አካላት መረጃውን በፍጥነት ያድርሱልን” በማለትም ጥሪ አቅርበዋል።

በአሰቦት ደብረ ወገግ ቅድስት ሥላሴና አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንድነት ገዳም ተመሳሳይ ጥቃቶች እየተፈጸሙ ገዳማውያኑ እና የአካባቢው ምእመናንን እየተሰደዱ መሆኑን ማኅበረ ቅዱሳን በተደጋጋሚ መረጃ ማድረሱ ይታወቃል።
©ማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን
😢425
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሳዑዲ ዓረቢያ የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው በአስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን በማስመልከት ለኢትዮጵያና ለሳዑዲ መንግሥታት፣ ለዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት እና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አባታዊ መልእክት አስተላለፉ።

ግንቦት 4 ቀን 2018 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

ቅዱስነታቸው ያስተላለፉት አባታዊ መልእክት እንደሚከተለው ነው፦

መልእክተ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

‹‹ተዘከሩ መቁሓነ ዘከመ ተሞቃሕክሙ ምስሌሆሙ ወእለ ተሣቀዩ ከመ ዘሀለውክሙ በሥጋክሙ፡-
ከእነርሱ ጋር አብራችኋቸው እንደታሰራችሁ ሆናችሁ እስረኞችን ዐስቡ፤ መከራ የጸናባቸውንም በሥጋችሁ ከእነርሱ ጋር እንዳላችሁ ሆናችሁ ዐስቡ››
(ዕብ. 13፡3)

እውነተኛ እምነትም ሆነ ጤናማ አመለካከት የሚመዘነው መከራ ስለሚቀበሉ ሰዎች ሰምቶና አይቶ በዝምታ ባለማለፍ፤ ይልቁንም በእነርሱ ሕመም ውስጥ ራስን በማስገባት በሚሰማው ጥልቅ ኀዘን እና በሚደረገው ድጋፍ ነው፡፡ ይልቁንም በዚች ዓለም የምንኖር ለችግርና ለመከራ ቅርብ እንደመሆናችን የታሰሩትን መጎብኘት፣ የተገፉትን ማጽናናት፣ በስደት ምድር ላይ ሆነው በሞት ፍርድ የሚጨነቁትን ወገኖች ስቃይም እንደራሳችን ስቃይ በመቁጠር ስለእነርሱ ድምፅ መሆንና ማዘን ስንችል በሰማያዊው መንግሥት የማይጠፋ የጽድቅ ዋጋን እናከማቻለን፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን!

እረኛ በበረት ውስጥ ያለችው አንዲት በግ ስትጠፋ ወይም ለአደጋ ስትጋለጥ ዝም ብሎ እንደማያይ ሁሉ፣ በሳዑዲ ዓረቢያ ምድር በሞት ጥላ ሥር ሆነው ‹‹የፍትሕ ያለህ›› እያሉ የሚጮኹ፤ በጭንቀት ቀናትን የሚቆጥሩና ድምፅ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ልጆቻችን የተሻለ ኑሮ እናገኛለን ብለው በተሰደዱበት ሀገር ሕይወታቸው በጅምላ ሊቀጠፍ እንደሆነ መረጃውን ከልዩ ልዩ መገናኛ ብዙኃን የተገነዘብን በመሆኑ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ጠቀሜታው የሰው ልጆችን ሕይወት ለመጠበቅ ነውና የኢትዮጵያ መንግሥት በከፍተኛ ደረጃ ከሚገኙ ከሳዑዲ ባለሥልጣናት ጋር በመነጋገር በግፍ የተፈረደባቸው ልጆቻችን የሞት ፍርድ እንዲነሳላቸውና ወደ ሀገራቸው የሚመለሱበት መንገድ ይመቻች ዘንድ የተጀመሩ ሥራዎች ልዩ ትኩረት እንዲሰጥባቸው፤ ወገኖቻችንም በቋንቋ እጥረትና በሕግ አማካሪ እጦት ለሞት እንዳይዳረጉ ከአደራ ጭምር እናሳስባለን ፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ለሰው ልጅ የሰጠው ታላቅ ስጦታ ሕይወት ነው፤ "አትግደል" የሚለው ሕግም በማንኛውም ምድርና ቋንቋ የሚሠራ ሲሆን ፍርድ ያለ ምሕረት ከሆነ አምላካዊ ቁጣን ይጋብዛልና የሳዑዲ ባለሥልጣናት የሁለቱን ሀገራት የቆየ ታሪክና ወዳጅነት አስበው፣ በሞት ፍርድ ጥላ ሥር ላሉት ወገኖቻችን ምሕረትን እንዲያደርጉ፣ ቅጣቱንም ወደ እስራት እንዲቀይሩ በአባታዊ ርኅራኄ እንጠይቃለን ፡፡

ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችም በማያውቁት ቋንቋ እንዲሁም ባልተረዱት የሕግ ሂደት ሞት የተፈረደባቸውን ወገኖች ስቃይ ተመልክተው የፍትሕ መዛባትን እንዲቃወሙና የንጹሐንን ነፍስ እንዲታደጉ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

በመጨረሻም፣ ማንኛውም በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ ሰው ሕይወቱ ሊጠፋ አይገባምና ኦርቶዶክሳውያን ልጆቻችን የክርስትናችን አንዱ መገለጫ የአንደኛው ወገን ሕመምን በጋራ መካፈል እንደሆነ ተረድታችሁ ወደ ፈጣሪያችን በጸሎት እንድትማጸኑ፤ መላው ኢትዮጵያውያንም ለመፍትሔው የበኩላችሁን ጥረት እንድታደርጉ ስንል አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን።

እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ!!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!
አሜን።

አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ግንቦት 4 ቀን 2018 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
© የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት
20
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

#ግንቦት_5_በእናቱ_ማኅፀን_ሳለ_የተመረጠ_ታላቁ_ነቢይ_ቅዱስ_ኤርምያስ_በሰማዕትነት_ዐረፈ፡፡

ይኽም ዕውነተኛ የእግዚአብሔር ነቢይ የካህኑ ኬልቅዩ ልጅ ነው፡፡ የስሙ ትርጓሜ ‹‹እግዚአብሔር ከፍ ያደርጋል›› ማለት ነው፡፡ አባቱ ኬልቅዩ እግዚአብሔርን የሚያገለግል ካህን ሲሆን እናቱ ማርታ ትባላለች፡፡ ሀገሩ ይሁዳ ሲሆን ልዩ ስሙ አናቲት  ይባላል፡፡

ነቢዩ ኤርምያስ ገና በእናቱ ማኅጸን ሳለ የተመረጠና የተቀደሰ ነቢይ ሲሆን የአሞጽ ልጅ የይሁዳ ንጉሥ ኢዮስያስ በነገሠ በ13 ዓመቱ ማስተማር ጀመረ፡፡ ከዚያም በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም ዘመን ዓሥራ አንዱ የሴዴቅያስ ዘመነ መንግሥቱ እስኪፈጸም በ5ኛው ወር ኢየሩሳሌም እስከተማረከችበት ጊዜ ድረስ ያስተምር ነበር፡፡

ነቢዩም ስለራሱ ሲናገር ‹‹የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ መጣ፣ እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፡- ‹በእናትህ ማኅጸን ሳልፈጥርህ ወደድኩህ፣ ከእናትህም ማኅጸን ሳትወጣ መረጥኩህ፤ ለአሕዛብም መምህር አደረግሁህ› አለኝ፡፡›› ኤር 1፡4፡፡

ነቢዩ ቅዱስ ኤርምያስ እንደነቢዩ ኢሳይያስ በበትር የምትመሰል የአምላክን እናት የቅድስት ድንግል ማርያምን ምሳሌ በለውዝ በትር አምሳል ተመልክቷታል፡፡ ኤር 1፡11፡፡ በተጨማሪም ከሁለት ደቀመዛሙርቱ ከባሮክና ከአቤሜሌክ የእመቤታችን ምሳሌ የሆነች ዐጽቀ በለስ በንስር አንገት የተላከለት ታላቅ ነቢይ ነው፡፡

ቅዱስ ኤርምያስ የእግዚአብሔርን አምልኮና ሕግ በመተዋቸው ‹‹ተጠበቁ፣ ንስሓም ግቡ፣ የእግዚአብሔር ቁጣው በላያችሁ እንዳይመጣ›› ብሎ የእስራኤልን ልጆች ገሠጻቸው፡፡ ሁለተኛም ‹‹ወደ ፈጣሪያችሁ እግዚአብሔር ካልተመለሳችሁ የከላዴዎንን ንጉሥ ናቡከደነጾርን በላያችሁ እርሱ ያስነሣዋል›› ብሎ ትንቢት ተናገረ፡፡ እንደቃሉም ሆነ፡፡

ዳግመኛም ሕዝቡ ተማርከው ሰባ ዘመን በምርኮ እንደሚኖሩ ትነቢት ተናገረ፡፡ ደግሞም የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኩነተ ሥጋ እንደሚመጣና መከራ እንደሚቀበል፣ የአስቆሮቱ ይሁዳ እንደሚሸጠውና የሽያጩን ዋጋ 30 ብር እንደሚቀበል ተናገረ፡፡

ስለ ብዙ ሥራዎችም ትንቢትን በተናገረ ጊዜ አይሁድ ሊገድሉት ፈልገው ይዘው አሥረው ገርፈው ከጉድጓድ ውስጥ ጣሉት፡፡ እግዚዚአብሔርም አዳነው፡፡ ነቢዩ ግን ስለ አይሁድ ይለምንና ይማልድ ነበር፣ እግዚዚአብሔርም ‹‹ስለ እነርሱ ወደእኔ አትማልድ፣ እነርሱ ከክፋታቸው አይመለሱምና›› አለው፡፡

ንጉሥ ናቡከደነጾርም የኢየሩሳሌምን ሕዝብ በማረከ ጊዜ ከእርሳቸው ጋራ አልማረከውም፡፡ ነገር ግን ከምርኮ የቀሩት ወደ ግብጽ አገር ወሰዱት፡፡ ነቢዩም የግብጽን ሰዎች ሲያጠፏቸው የነበሩ በወንዞች የሚኖሩ አራዊትን በጸሎቱ አጠፋቸው፡፡

ከዚያም ወደ ባቢሎን አገር ወሰዱት፡፡ በዚያም የእስራኤል ልጆች ከምርኮ እስኪመለሱ ትንቢት እየተናገረ ሕዝቡን ሲያስተምር ኖረ፡፡

ነቢዩ ቅዱስ ኤርምያስ ነገረ ሥጋዌን ማለትም የጌታችንን ሰው መሆን በትንቢት ሲናገር ክፉዎች የእስራኤል ልጆች የትንቢቱ ወራት ሲፈጸም ‹‹የአምላክን ልጅ አምላክን አየሁት›› ይለናል ብለው በድንጋይ ወገሩትና በዚያው በሰማዕትነት ዐረፈ፡፡
ተ ኤር 11፡54፤ ዕብ 11፡37፡፡

የነቢዩ የቅዱስ ኤርምያስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን፡፡

/ፍኖተ ሕይወት ሰ.ት.ቤት ሚድያና ሕዝብ ግንኙነት ዋና ማስተባበሪያ ክፍል።/

• Facebook 👉 m.facebook.com/FinoteHiwotSundaySchool
• Telegram 👉 t.me/finotehiwott

• Tiktok 👉 tiktok.com/@finotehiwot 
• YouTube 👉 m.youtube.com/@finotehiwot1958
13
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡፡

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

የእግዚአብሔር ሕዝብ ጉባኤ፣ የጌታችንና የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አካልና የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ የሆነችው ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ሲኖዶሳዊ በመሆኗ አበው ቅዱሳን በፍትሕ መንፈሳዊና በጉባኤ አድያም ዘአንጾኪያ “ወይኩን ሲኖዶስ ዘጳጳሳት ፪ተ ጊዜያተ በበዓመት - የጳጳሳት ጉባኤም በዓመት ሁለት ጊዜ ይሁን” ብለው በደነገጉት ቀኖና መሠረት፤ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የሚመራው፣ የሐዋርያት መንበር ወራሽ የሆነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የርክበ ካህናት ምልዓተ ጉባኤውን በኅብረተ መንፈስ ቅዱስ ከሚያዝያ 28 እስከ ግንቦት 6 ቀን 2018 ዓ/ም ድረስ አካሄዷል፡፡

ምልዓተ ጉባኤው ስለ ሀገር ሰላም፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን አንድነት፤ ስለ ሰው ልጅ ሁሉ ደኅንነትና ክብር፣ በአጠቃላይ ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ሰፊ ውይይቶችን በማድረግ ዘመኑን የዋጁ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡ ከውሳኔዎቹም መካከል፡-

የቤተ ክርስቲያናችንን አንድነት መጠበቅና ማስጠበቅ የቅዱስ ሲኖዶስ ተግባር በመሆኑ ጥንታዊትና ሐዋርያዊት የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን በአንድነቷና በሉዓላዊነቷ እንደተረከብናት ለወደፊቱም ሉዓላዊ ክብሯ ተጠብቆ እንድትቀጥል በምልዓተ ጉባኤው የተሠየመው በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የሚመራው “የሀገራዊ ሰላምና የቤተ ክርስቲያን አንድነት” ኮሚቴ ሥራውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ፍጹም ሰላማዊ ሆኖ በተረጋጋ መንገድ እንዲካሄድ፣ ለሀገር ሰላምና ለሕዝብ አንድነት በሚጠቅም ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምትጸልይ ሲሆን ምርጫው በሁሉም ወገን ለኢትዮጵውያን ዘላቂ ሰላምንና መረጋጋትን የሚያስገኝ ሆኖ እንዲፈጸም ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንዖት ያሳስባል፡፡

ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የአርሲ ሀገረ ስብከትን በሊቀ ጵጵስና በቋሚነት እንዲመሩ፣ ሕዝቡን እንዲያጽናኑ እየደረሰ ያለውን ችግር ከቋሚ ሲኖዶስና በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ከሚመራው የሰላም ኮሚቴ ጋር በመሆን የሚመለከተውን የመንግሥት አካል በማነጋገር ዘላቂ መፍትሔ እንዲያፈላልጉ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ወስኗል፡፡

ከጥንት ጀምሮ “ቅዱስ ሲኖዶስ” በሚል ርእስ እየተዘጋጀ ይታተም የነበረው ታሪካዊ መጽሔት የቅዱስ ሲኖዶስ ቀኖናዊ ውሳኔዎችን በማካተት በቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት አስፈጻሚነት ሕትመቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

የቤተ ክርስቲያናችንን ደንቦች መመሪያዎች መርምሮ ማጽደቅ የቅዱስ ሲኖዶስ ሉዓላዊ ሥልጣን በመሆኑ፡-

የስብከተ ወንጌል ሐዋርያዊ ተልእኮ ማስፈጸሚያ ደንብ በብፁዕ አቡነ ማርቆስ ሰብሳቢነት

የአንድነት ገዳማት ኅብረት መተዳደሪያ ደንብ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስና ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ባሉበት በድጋሚ እንዲታይና ሌሎቹም ለውሳኔ የቀረቡ ደንቦች በሊቃውንትና በሕግ ባለሙያዎች ታርመው ለጥቅምት 2019 ዓ/ም ምልዓተ ጉባኤ እንዲቀርቡ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል

የቀድሞው የሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ “የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ”ና “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ” በሚሉ አርእስት አዘጋጅተው ያሳተሟቸው መጻሕፍትን የማሳተምና የማሰራጨት የባለቤትነት መብት ከሚያዝያ 29 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ለዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም እንዲሆን ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

ከተለያዩ አህጉረ ስብከት በቀረቡ ጥናቶችና የማጣራት ውጤቶች መሠረት፡-

የደቡብ ሱዳን ሀገረ ስብከት ከምሥራቅ አፍሪካ ሀገረ ስብከት ጋር ተደርቦ በብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ሊቀ ጳጳስ እንዲመራ፤
ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል ሊቀ ጳጳስ የጋምቤላንና የቤንሻንጉል ጉምዝ አህጉረ ስብከትን ብቻ እንዲመሩ፤
ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጰስ የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከትን እንደያዙ እንዲቀጥሉ፤
ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም የቡኖ በደሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቄለም ወለጋ ሀገረ ስብከትን ደርበው በአባትነት እንዲመሩ፣
የኮንታ ዞን ሀገረ ስብከት እንዲሆን የቀረበው ጥያቄ የጸደቀ በመሆኑ ሀገረ ስብከቱ ራሱን ችሎ እንዲደራጅና በብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ሊቀ ጳጳስ እንዲመራ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፤
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የልማት ተግባራትን ምልዓተ ጉባኤው በከፍተኛ ደረጃ በማድነቅ፣ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ/ ዋና ሥራ አስኪያጅ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ሲቲ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ በአባታዊ አመራር የፈጸሙት አስደናቂ የሥራ አፈጻጸም በጉልህ የሚታይ ለውጥ፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የሚጠቅም፣ ሉዓላዊ ክብሯን የሚያስጠበቅ፣ ለሁሉም አበው ምሳሌነት ያለው በመሆኑ ምልዓተ ጉባኤው እጅግ ከፍ ባለ ክብር አመስግኗል፡፡

በዚህም መሠረት በብፁዕ ጠቅላይ ዋና ሥራ አስኪያጁ አባታዊ መሪነት እየተከናወኑ ያሉት ተግባራት ማለትም፡-

የቤተ ክርስቲያንን ቀደምት ሠነዶች በዲጂታል ቴክኖሎጅ እንዲደራጁ የተደረገበት ሥልት ተጠናክሮ እንዲቀጥል፤

ከ1970 ዓ/ም ጀምሮ በመጋዝን ተከማችተው የቆዩ በርካታ ልዩ ልዩ መጻሕፍትን የማሠራጨት ሂደት በተጀመረው መንገድ እንዲጠናቀቅ፤

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የኢንፎርሜሽንና ኮምኒኬሽን ተጠቃሚ እንድትሆን የተጀመረው ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂ በሁሉም የቤተ ክርስቲያናችን መዋቅር በየደረጃው ተጠናክሮ ተግባራዊ እንዲሆን፤

በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥር የተጀመሩ የሕንፃ ግንባታዎችና አጠቃላይ የልማት ሥራዎች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ ሁሉም አህጉረ ስብከትና ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦና ትብብር እንዲያደርጉ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንዖት ያሳስባል፡፡

በሰሜን አሜሪካ የሰሜን ካሊፎርኒያ፣ ኔቫዳና አሪዞና ሀገረ ስብከት ኆኅተ ሰማይ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስና ቅድስት አርሴማ ገዳም የመንፈሳዊ ኮሌጅ፣ የአብነት ት/ቤት ሥርዓተ ትምህርት የቤተ ክርስቲያንን ዶግማ፣ ቀኖና፣ ታሪክና ትውፊት በጠበቀ መልኩ ተጠናክሮ መዋቅራዊ ተጠሪነቱም በአግባቡ ተጠብቆ ሥራ ላይ እንዲውል ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ያቀረበውን የ2019 ዓ/ም በጀት በማጽደቅ በተገቢው መንገድ ሥራ ላይ እንዲውል ምልዓተ ጉባኤው ወስኗል፡፡

በመጨረሻም ቅዱስ ሲኖዶስ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በተነጋገረባቸው ጉዳዮች በትኩረት የተወያየው የቤተ ክርስቲያናችንን ሁለንተናዊ ዕድገትና ተቋማዊ ሕልውና ስለማስጠበቅ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ሀገራችንን ጨምሮ በመላው ዓለም እየታየ ያለው ግጭትና የሰላም መታጣት በእጅጉ አሳስቦታል፡፡

በመሆኑም ስለ ዓለምና ስለ ሀገራችን ሰላም፣ ስለ ሰው ልጆች ደኅንነት፣ በየቦታው በሃማኖታቸው ምክንያት መከራ የሚደርስባቸውን በየቦታው የሚገኙና ግጭት ባለባቸው ቦታዎች ያሉ ኦርቶዶክሳውያንን በማሰብ በመጪው የ2018 ዓ/ም ጾመ ሐዋርያት በመላው ዓለም ባሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት፣ አድባራትና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ጸሎተ ምሕላ እንዲደርስ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
10🙏1🤝1
በመላው ዓለም፣ በደቡብ አፍሪካና በሳውዲ ዐረቢያ የሚኖሩ ዜጎቻችን ሰብዓዊ መብት እንዲከበር፣ የርኅራኄ ምሕረትና ፍትሕ እንዲያገኙ የሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን ክትትል እንዲያደርጉ ቅዱስ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ጥሪውን በማቅረብ ለሰባት ቀናት ሲያካሂድ የሰነበተውን ቀኖናዊ ጉባኤ ዛሬ ግንቦት 6 ቀን 2018 ዓ.ም. በጸሎት አጠናቋል፡፡

“እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ”

አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም
ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት
አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ

ግንቦት 6 ቀን 2018 ዓ/ም
36
ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ

#፩)#የቅዱስ_ያሬድ_ልደትና_የስሙ_ትርጓሜ

ꔰ  ኢትዮጵያዊው ቅዱስ ያሬድ ሚያዚያ 5 ቀን በ505 ዓ.ም. ከአባቱ ይስሐቅ(አብድዩ) ከእናቱ ክርስቲና (ታውክልያ) በአኵሱም ከተማ ተወለደ፡፡ (አንዳንዶች ልደቱን 493 ዓ.ም. ነው ይላሉ፤ እንዲሁም አባቱ ኖኅ ነው ይሉና መሪጌታ ይስሐቅ የቀለም አባቱ /መመህሩ/ ነው ይላሉ፡፡)
ꔰ  የስሙም ትርጓሜም ያሬድ ማለት እንዚራ፣ በገና፣ መሰንቆ ማለት ነው ፡፡ እነዚህ መሣሪያዎች በስልት በስልት ሲመቱ ለሚሰማቸው ደስ እንዲያሰኙ የያሬድም ዜማ በንጉሠ ነገሥቱ ክርስቶስ አደባባይ በቤተ ክርስቲያን ሲሰማ መላእክትን፥ ሰውንና እንስሳትን ደስ ያሰኛልና፡፡
፨ አንድም ያሬድ ርደት፣ ወሪድ፤ መውረድ ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ ሰማያዊውን ልዩ ጣዕመ ዜማ ወደ ኢትዮጵያ አውርዷልና፡፡
፨ አንድም ያሬድ ማለት ንብ ማለት ነው፤ ንብ የማይቀስመው አበባ እንደሌለ ሁሉ ቅዱስ ያሬድም ከመጻሕፍት የማይጠቅሰው የማይቀሰመው የለም፤
፨ አንድም ያሬድ ማለት ረአዬ ምሥጢር፥ ነጻሬ ኅቡአት ማለት ነው፤ የመላእክት ምሥጢራት የነበሩትን ጸዋትወ ዜማ አምልቶ አስፍቶ ተናግሯልና፣ ነጻሬ ኅቡአት አለ፥ ኅቡእ (ስውር) የሆነ የጻድቃን፣ የሰማዕታት የነቢያት የሐዋርያትን ገድል አምልቶ አስፍቶም ይናገራልና፡፡
-ዐፄ ካሌብ ቤተ እስራኤል፣ ገብረክርስቶስና ገብረ መስቀል የሚባሉ ልጆች ነበሩት፤ ቅዱስ ያሬድ የተነሳው ከእነዚህ ውስጥ በዓፄ ገብረመስቀል ዘመን ነው፡፡

#፪)#የቅዱስ_ያሬድ_አስደናቂ_ነገሮች
#፠ከጌዴዎን ዘንድ ትምህርቱን አቋርጦ ሄደ ስንል፤ በአንድ ሾላ ዛፍ ላይ በትል አማካይነት ትዕግስትንና ማስተዋልን ቀስሞ፤ ወደ አጎቱ ተመልሶ ተምሮና ትምህርትን አምላክ ገልጾለት መምህረ መምህራን ሁኖ እንገኘዋለን፤ /እግዚአብሔር አምላክ ለቅዱስ ያሬድ ያንን ኹሉ ጥበብ ቶሎ ያልገለጸለት በቀላሉ ቢያገኘው ኋላ እንዳይታበይ ብሎ ነው፤ የሐዊራ ብስድር እስክንድራን ታሪክ ልብ ይሏል)
#፠መምህር ነው ስንል፤ መናኝ ባሕታዊ ኾኖ እናገኘዋለን፤ /በደብረ ሐዊ ለ22ዓመታት መመኑን ልብ ይሏል/
#፠መናኝ ነው ስንል የተለያዩ የሃገራችንን ክፍሎች ገዳማትና አድባራት ሲጎበኝ እስከ ኢየሩሳሌም ድረስ ሲጓዝ እንገኘዋለን፤ /ጣና ቂርቆስ፤ ዙር አባ አቡነ አረጋዊ፣ …. ሌላውንም ልብ ይሏል)
#፠ወደ ገዳማትና አድባራት ይጓዛል ስንል፤ ወደ ደብረ ዳሞ አቡነ አረጋዊ በደመና ተጭኖ ሂዶ ምሽቱን ወደ በዓቱ ሲመለስ እንገኘዋለን፡፡
#፠በሃገራችን በዋና ከተማ አኵሱም ተወልዶ ያደገ ነው ስንል፤ ሰው ሊኖርበት በማይችለው፥ በረድ በሚፈላበት፥ የነፋስ እሩምታ በሚያይልበት፥ ቅዝቃዜው አጥንት በሚሰነጥቅበት፥ ውርጩ እጅጉን በሚቀዘቅዝበት፥ ደመና በሚፈስስበት በራስ ደጀን ተራራ አጠገብ በደብረ ሐዊ መንኖ እናገኘዋለን፡፡
#፠ከሰዎች ጋር አብሮ ኑሯል ስንል፤ ከሰው የማይቀርቡና በዐለማችን ላይ ብርቅዬ ኾነው በሃገራችን የሚገኙ ከሃገራችን ኢትዮጵያም በሰሜን ተራሮች በአብዛኛው ከሚገኙት ዋልያ ጋር አብሮ ሲኖር፤ ዋልያዎችንም እንደ መጓጓዣና እንደ መጫኛ ሲያገለግሉት እንገኛለን፡፡
#፠በሙራደ ቃል የመላእክት ዜማ ተገልጾለት ተማረ ስንል፤ የግእዝ ቋንቋ ምሁርና ጠበብት ሁኖ እናገኘዋለን፡፡ (ለተሰዓቱ ቅዱሳን መምህር መሆኑን ልብ ይሏል)
#፠የዜማ ጀማሪ አባት ነው ስንል ባለቅኔ ኾኖ እንገኘዋለን (ሕንፄሃ ወሡራሬሃ …. የሚለው ቅኔውን ልብ ይሏል)፤
#፠ባለቅኔ ነው ስንል መተርጕም ኾኖ እንገኘዋለን፤ (ድጓው የብሉይና የሐዲስ ትርጓሜ መሆኑን ልብ ይሏል)
#፠መተርጕም ነው ስንል ባለታሪክ፥ የታሪክ ምሁር ኹኖ እናገኘዋለን፤
#፠የታሪክ ምሁር ነው ስንል፤ የመርሐ አዝማን ሊቅ ኹኖ እናገኘዋለን፤ (ዓመቱን በሚገርም ሁኔታ ከወቅታቱ ጋራ አገናዝቦ መሠየሙን ልብ ይሏል)
#፠የመርሐ አዝማን ሊቅ ነው ስንል ቅዱስ ኾኖ እንገኘዋለን፤ የቅዱሳንም ጓደኛ ኹኖ እንገኘዋለን፡፡ /የአቡነ አረጋዊ፣ የአጼ ገብረ መስቀልን ታሪክ ልብ ይሏል፡፡/
#፠ነቢይ ነው ሰንል ሐዋርያ ሁኖ እናገኘዋለን፡፡ (ስለ ዳግም ምጽአት፣ ስለ መንግሥተ ሰማያትና …. ሌሎችንም ልብ ይሏል)
#፠ሐዋርያ ነው ስንል ሰማዕት ኹኖ እናገኘዋለን፡፡ (እግሩን በጦር መወጋቱን ልብ ይሏል)፤  ሌላም ሌላም ….
፠#፠በአጠቃላይ ምድራዊ ነው ስንል ሰማያዊ፤ ሰማያዊ ነው ስንል ምድራዊ (ብእሲ ሰማያዊ ወመልአክ ምድራዊ) ሁኖ እናገኘዋለን፡፡
#ዜማውን በግዕዝ ዕዝል አራራይ የዜማ ስልት የደረሰ፤
#በዓለም ደረጃ የዜማ ምልክቶች ባልታወቁበት ጊዜ ዜማዎቹን በምልክት የቀመረ፤
#የዜማ ሥርዓትን በመንደፍ የዓመቱን ቀለም ያዘጋጀ፤
#ዜማውን በ4ት ዘመናት ከፋፍሎ፤ ዘመናቱን በንዑሳን ዘመናት ከፋፍሎ ለወራቱና ለሰሙኑ ለእለቱ የሚገባውን ቀምሮ የደረሰ፤
#እንኳን በእርሱ ዘመን ዛሬ እንኳን ብዙ ነገሮች ተሰባስበዋል በተባለበት ዘመን ሊሠራ አይደለም ሊታሠብ በማይችሉ መልኩ መጽሕፍትን እንደ ንብ እየቀሰመ፤ እንደ ወይን እየጨመቀ፤ እንደ አረቂ እያጣራ፤ እየተረጐመ ላሰበው ድርሠት ያዋለ፤ … ስለ ቅዱሱ ምኑን ተናግረን እንጨርሰዋለን፡፡ …
##.. ይኼማ ኢትዮጵያዊ ሊኾን አይችልም ብለው ብዙ የውጭ ሃገራት ወደ ራሳቸው ለመውሰድ የሚዳዳቸው፡፡
/የቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኀኔዓለምና ደብረ ትጉሃን ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ሕይወት ሰንበት ትምህርት ቤት/

#፫#የቅዱስ_ያሬድ_ድርሰቶች
#1ኛ) ምዕራፍ (ውዳሴ ማርያም በዜማን፣ መስተጋብዕ፣ አርባዕት፣ አርያም፣ ሠለስት፣ ክስተተ አርያምን) ያጠቃልላል፡፡
፠የውዳሴ ማርያም ዜማ ቅዱስ ኤፍሬም ሦርያዊ የደረሰውን ለቅዱስ ያሬድ እየነገረው ልብን የሚመስጥ ዜማ ደርሶለታል፡፡
፠መስተጋብዕ፤ ስብስብ ማለት ሲኾን፡፡ ከዳዊት መዝሙር (ከ180ው የመስተጋብእ ድርሰት 1ድ ድርሰት በስተቀር) ለጸሎትና ለዝማሬ ተስማሚ የኾነው እየተውጣጣ ለመዝሙር ተስማሚ የኾነው የተቀመረ ነው፡፡ መስተጋብዕ ሲጀምር ‹‹ወለቡ ጽራኅየ (ጩኸቴን ልብ አድርግ›› ብሎ ነው፡፡ በዐቢይ ጾም ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ጠዋት ጠዋት ይዘመራል፤ የቀድሞ መምህራን በፍልሠታም ይዘምሩት ነበር፤ ዜማው በዋነኛነት በግዕዝና በዕዝል ሲኾን በአራራይ ከሐሙስ ‹‹አንተሰ እግዚኦ ለዓለም›› የሚለውና ከቅማዴ ‹‹መንግሠትከሰ መንግሥት›› የሚለው ይገኙበታል፡፡ በየእለቱ እንዲደርስ (ከእሑድ በስተቀር) አድርጎ የደረሰው ነው፤

፠አርባዕት፤ አራት አራተኛ ማለት ሲን በዳዊት መዝሙር በአራተኛው መሥመር ውስጥ እየገባ የሚዘመር ነው፤ ‹‹ቃልየ አጽምእ እግዚኦ ወለቡ ጽራኅየ፤ ወአጽምአኒ ቃለ ስእለትየ፤ ንጉሥየኒ ወአምላኪየኒ፡፡ ከፈጸመ በኋላ አርባዕት ይገባል፡፡ አርባዕት ሲጀመር ‹‹ቃልየ፤ ከመ ያፈቅርለ ጐሥዓ፤ ዐቢይ፤ ተሣሃለኒ›› ብሎ ነው (በዳዊት መዝሙር ጀምሮ ቀጥሎ በቅዱስ ያሬድ ድርሠት በኾነው በአርባዕት ያጠናቅቃል፡፡አብዛኛው በግጥም መልክ የተቀመረ ሲኾን አልፎ አልፎም በስድ ንባብ መልክ ይገኛል፡፡ ግእዝ ዕዝልና አራራይ ዜማ አለው፡፡ አርያም፤ አርያም ልዑል፥ ከፍተኛ ማለት ሲኾን፤ ቅዱስ ያሬድ ከአርያም ሰምቶ ‹‹ቀዳሚ ዜማ፤ አንድም ቀዳሚሃ ለጽዮን ሰማየ ሣረረ›› ስላመጣው ነው፡፡ ሃሌ ሉያ ለአብ ሃሌ ሉያ ለወልድ ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ ብሎ የግጥም መል ባለው አእያም በተባለው ይጀምራል፡፡ በግጥም መልክና በስድ ንባብ ሲገኝ የግጠም አገጣጠሙ ከፍ ያለ የግጥም አገጣጠምን የተከተለነው፡፡ የሚባልበት ጊዜ በጾም ጊዜ በጾመ ድጓው እየገባ፣ በተለይ ደግሞ በክብረ በዓል ክሥተተ አርያም ሲደርስ ይዘመራል፡፡ 
5
ሠለስት፤ ስምዐኒ ብሎ የሚጀምር ባለ ብዙ ሃሌታ ያለው፤ በዳዊት መዝሙር በሦስተኛው መሥመር እየገባ የሚዘመር፤ አንድም 3 መዝሙሮች ብቻ የሚዘመሩለት ብዙውን ጊዜ በግጥም የሚቀርብ ሲኾን፤ ይኽ ዜማ የሚደርሰው በክብረ በዓላት ዋይዜማ፤ በስብሐተ ነግህ፣ በአርያም፣ በጾመ ድጓ ውሎ፣ በአርያም፣ በሰንበት፣ በፍትሐት ጊዜ ነው፡፡
ክስተተ አርያም፤ የሰማይ መከፈት ማለት ሲኾን በታላላቅ በዓል ቀን እንዲሁም ታላላቅ? ሰዎች ሲሞቱ የሚዘመር ነው፤ ክስተትን ቅዱስ ያሬድ ያዘጋጀው ከዳዊት መዝሙራት፥ ከጸሎተ ነቢያትና ከራሱም ጭምር ኀይለ ቃል ያላቸውን ባለሁለት መስመሮች ሐረግ በመውሰድ ሲኾን ዜማው እጅጉን ነፍስና ሥጋን፥ ልብንና ኅሊናን የሚመስጥ ነው፡፡
2ኛ) ጾመ ድጓ፤ በዐቢይ ጾም የሚባል ነው፡፡
3ኛ) ድጓ፤ በ4ት ክፍላተ ዘመናት የተቀመረ ነው፡፡
4ኛ) ዝማሬ፤ ቅዱስ ቊርባን ድርገት ሲወርድ ለቅዱስ ቊርባን ክብር የሚዘመር ነው፡፡
5ኛ) መዋሥዕት፤ ሰው ሥጋው ከነፍ ስትለይ ፍትሐት የሚደረግበት ጸሎት ነው፡፡
6ኛ) የ14ቱን ቅዳሴያት ዜማ፤ 14ቱን ቅዳሴያት 14ት አባቶች የደረሷቸው ቢሆንም ዜማ የደረሰላቸው ግን ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ነው፡፡
7ኛ) አንቀጸ ብርሃንን፤ ድርሰቱ ነው፡፡ /ይቀጥላል……/
በተጨማሪም ደግሞ፤
የቅዱስ ያሬድ የዜማ ዐይነቶች ግእዝ፣ ዕዝልና ዓራራይ በመባል ይታወቃል፡፡እነዚህ የዜማ ዐይነቶች የአንዱ ድምፅ ከሌላኛው ድምፅ ያልተደባለቀ፣ ወጥ የሆነ ድምፅ አላቸው፡፡ በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምሳሌና ትርጉም ያላቸው
በሆኑ የዜማ ምልክቶች (ድፋት፤ ሂደት፤ ቅናት፤ ይዘት፤ ቁርጥ፤ ጭረት፤ ርክርክና ደረት) ደርሷል፡፡
የቅኔ ጀማሪም ነው፡፡ ‹‹ሕንፄሃ …›› የሚለውን ቤት መምቻ ያለውን ቅኔ ልብ ይሏል፤ አንድ ባለቅኔ ግን ይህን ሳይረዳ ‹‹ተትሕተ ያሬድ …›› የሚል ቅኔን ተቀኝቷል፡፡

#፬#የቅዱስ_ያሬድ_ድርሰቶች#የዜማው_ይዘት_የዜማው_ጠባያት_ከሌሎች_ዓለማዊ_ዜማዎች_የሚለይበት_ጠባይና_የዜማው_ጥቅም
#ሀ_የቅዱስ_ያሬድ_የዜማው_ይዘት
፠ቅዱስ ያሬድ ዜማውን ያዘጋጀው ከብሉያት፣ ከሐዲሳት፣ ከሊቃውንት መጻሕፍት እየመረጠ ለምስጋናና ለጸሎት እንዲኾኑ አድርጎ ነው፡፡
፠ዜማው ምስጢሩ የማይጠገብ፥ቃሉ የሚያረካ፥ አነጋገሩ የተሳካ፥ ጣዕመ ቃሉና ኀይለ ቃሉ ደስ የሚያሰኝ፥ ልብን የሚነካ ነው፡፡
፠በይዘቱም የሥነ ፍጥረት ውበትን በማድነቅና የሥነ ፍጥረት አስገኝ የኾነውን እግዚአብሔርን በማመስገን ላይ ያተኮረ ነው፡፡
፠በአጠቃላይ የቅዱስ ያሬድ ድርሰት ጌታ ለሰው ልጆች ሲል በዚህ ዓለም የፈጸመውን የማዳን ሥራ ሁሉ ገልጦ የሚያስረዳ ነው፤ የቅድስት ድንግል ማርያምን፣ የቅዱሳን መላእክትን፣ የነቢያትን፣ የሐዋርያትን፣ የጻድቃንና የሰማዕታትን ክብርና ቅድስና በማውሳት በስማቸው መማፀንና መጸለይ የሚያስገኘውን ጥቅም የሚያስረዳ ታላቅ ዜማዊ ሀብት ነው፡፡
፠ከእርሱ በፊት የነበሩና በእርሱ ዘመን የተጻፉ የቅዱሳን ገድላትና ድርሳናትን እንዲሁም የበዓላትን ጥንታዊ አመሠራረት ውስጠ ምሥጢር በማስረዳት በዜማ ድርሰቱ አካቷል፡፡
፠ምስጋናውንም ለአራቱ ክፍላተ ዘመን ለክረምት፣ ለመፀው (ለጥቢ)፣ ለሐጋይ (ለበጋ)፣ ለጸደይ (ለበልግ) እንዲኾን አዘጋጅቶታል፡፡
#ለ_የዜማው_ጠባያት
፨የቅዱስ ያሬድ ዜማ ሰማያዊ በመኾኑ ኅሊናን የመመሠጥ፣ ሥጋዊ ደስታንና ኀጢአትን ከማሰብ የመጠበቅ፣ ሰማያዊውን ድንቅ የምስጋና ምስጢር የማሳወቅ ኀይል አለው፡፡
፨ከእግዚአብሔር የተገኘ ስጦታም በመኾኑ ብልየት (እርጅና)፣ ውላጤ (መለወጥ) የማይታይበት ዘወትር ሕያው የኾነ ብቸኛ ዜማ ነው፡፡
፨የመንፈስ ቅዱስ ስጦታም በመኾኑ ዘወትር አዲስና የማያልቅ ጥልቅ ምንጭ ያለው ሕይወትን የሚያለመልም ነው፡፡
፨ዜማውም ሰማያዊና መንፈሳዊ፣ ከእግዚአብሔር የተገኘ ለመኾኑ ማስረጃ የሚኾነን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ውጪ ያሉ ሰዎች ዜማውን ለተለያየ ዐላማ ይመኙታል፤ ነገር ግን ለመያዝም ኾነ ለመወሰን አይችሉም፡፡ ምክንያቱም በምድራዊ ጥበብና ፍልስፍና የሚያዝ የሚወሰን ሳይኾን ታላቅ መሥዋዕትነትን የሚጠይቅ፣ ሌት ተቀን ልቡናን ለሥላሴ ሰጥተው ከእግዚአብሔር የሚያገኙት በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ የሚያጸኑት፣ የሚማሩትና የሚያዜሙት እንጂ በገንዘብ የማይገዛ ታላቅ ጸጋ መኾኑ ነው፡፡
#ሐ.#የቅዱስ_ያሬድ_ዜማ_ከሌሎች _ዓለማዊ_ዜማዎች_የሚለይበት_ጠባይ፤
፨ ዜማው አሳብን የሚገዛ፣ ከሥጋ ይልቅ በመንፈስ መመላለስን የሚያስተምር በመኾኑ፤
፨ በአቀራረቡም የተወሰነ የዜማ ስልትና ቀመር ያለው በመኾኑ፤
፨ ዜማው በአዝማናት ተለይቶ በወቅት ተከፋፍሎ የሚዜም መኾኑ፤
፨ ማንኛውም ሰው ከተወሰነ የዜማ ስልትና ቀመር ውጪ በራሱ ፍላጎት የድምፅ ቅላጼውን ለማሳመር ስለፈለገ የሚያሻሽለው ወይም የሚለውጠው አለመኾኑ፤
፨ ዜማው በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ምሳሌና ምሥጢር የተሞላ መኾኑና
፨ የዜማው ምልክቶችና ዐይነቶች ጥልቅ ምሳሌና ምስጢር ያላቸው መኾናቸው ነው፡፡
#መ_የቅዱስ_ያሬድ_ዜማ_ጥቅም
ሀ. የቤተ ክርስቲያንን አንድነት በመጠበቅ፤ በየትኛውም አካባቢ የምትኖር የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አንድ ዓይነት መዝሙር፣ አንድ ዓይነት ቅዳሴ፣ አንድ ዓይነት ማኅሌት፣ አንድ ዐይነት ሥርዐት በአንድ ዓይነት ጊዜ በአንድ ቀን ማቅረብና መፈጸም እንድትችል አስችሏታል፡፡
ለ. በነገረ መለኮት ትምህርት፤ ሊቁ የትርጓሜ መምህር ስለሆነ ከብዙ መጻሕፍት ስለሚጠቅስና የሃይማኖት ትምህርቱትንም በዜማ አቀነባብሮ መድረሱ በጣም ተወዳጅ ትምህርት እንዲሆን አድርጎታል፡፡
ሐ. በሥርዓተ ጸሎት፤ ከዓመት እስከ ዓመት ለሚከናወኑ (የዘመናትና የሳምንታትን ጨምሮ) ማንኛውም ሥርዐተ ጸሎት ዋና መሪው የቅዱስ ያሬድ ድርሰት ነው፡፡ ማኅሌቱ፣ ቅዳሴው፣ ፍትሐቱ፣ ጥምቀተ ክርስትናው ሁሉ በዜማው መሪነት የሚከናወኑ አገልግሎቶች ናቸው፡፡
መ. ለቱሪዝም ሀብት (መስህብነት)፤ ክርስቲያናችን በየወሩና በየዓመቱ ከምታከብራቸው በዓላት ላይ ከሚቀርቡት ዝግጅቶች አብዛኛውን ክፍል የሚይዘው በቅዱስ ያሬድ ዜማ የሚቀርበው የዝማሬና የቅዳሴ አገልግሎት ነው፡፡

/በፍኖተ ሕይወት ሰ.ት.ቤት ሚድያና ሕዝብ ግንኙነት ዋና ማስተባበሪያ ክፍል የተዘጋጀ።/

• Facebook 👉 m.facebook.com/FinoteHiwotSundaySchool
• Telegram 👉 t.me/finotehiwott

• Tiktok 👉 tiktok.com/@finotehiwot 
• YouTube 👉 m.youtube.com/@finotehiwot1958
5