Finote Hiwot የቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኀኔ ዓለምና ደብረ ትጉሃን ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ሕይወት ሰንበት ትምህርት ቤት
15.3K subscribers
14.7K photos
78 videos
156 files
1.71K links
የቀጨኔ መድኃኔዓለም ፍኖተ ሕይወት ሰንበት ትምህርት ቤት ነሐሴ 26/ 1958 ዓ.ም ተመሠረተ።
Download Telegram
Finote Hiwot የቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኀኔ ዓለምና ደብረ ትጉሃን ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ሕይወት ሰንበት ትምህርት ቤት
#ዜና_ዕረፍት ለበርካታ ዓመታት ከገጠር እስከ ከተማ ከሀገር ውስጥ እስከ ውጭ ሀገራት ቅዱሱን ሕያው ወንጌል በታማኝነትና በትጋት ያለዕረፍት ያገለገሉት #መምህር_ዘለዓለም_ወንድሙ በዛሬው ዕለት ከድካመ ሥጋ ዐረፉ። #ኦ እግዚኦ አዕርፍ ነፍሰ ገብርከ #ወልደ_ሰማዕት ሀገረ ሕይወት መንግስተ ሰማያት ያውርስልን፤ በአብርሃም በይስሐቅ በያዕቆብ ዕቅፍ ያኑርልን፤ ለቤተሰቦቻቸው ለወዳጅ ዘመዶቻቸው እንዲሁም ለኦርቶዶክሳውያን…
“በልዩ ልዩ ጊዜያት ዐረፍተ ዘመን የገታቸውን ወገኖች ልንሸኝ እንችላለን፤ የአንዳንድ ሰዎች ሞት ግን ከልብ ቶሎ የማይወጣ፤ ለዘመናትም በህሊና መዝገብ ላይ የሚቆይ ነው፡፡” ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

የካቲት 30 ቀን 2018 ዓ.ም (ተ.ሚ.ማ/አዲስ አበባ)


ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ቅዱስ ተክለሃይማኖት በመምህር ዘለዓለም ወንድሙ ዕረፍት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልጸዋል።


የቅዱስነታቸው መልእክት ከዚህ እንደሚከተለው ይቀርባል።


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
አሜን !!

‹‹ወነአምር ከመ ለእመሂ ተነሥተ ቤተ ማኅደርነ ዘበምድር ዘውእቱ ሥጋ ብነ ሕንጻ በኀበ እግዚአብሔር በሰማያት ዘኢገብሮ እደሰብእ፤ በምድር ያለው ማደሪያ ቤታችን ቢፈርስም በሰማይ በእግዚአብሔር ዘንድ የሰው እጅ ያልሠራው ዘለዓለማዊ ቤት እንዳለን እናውቃለን፡፡›› (2ቆሮ. 5፡1)

በልዩ ልዩ ጊዜያት ዐረፍተ ዘመን የገታቸውን ወገኖች ልንሸኝ እንችላለን፤ የአንዳንድ ሰዎች ሞት ግን ከልብ ቶሎ የማይወጣ፤ ለዘመናትም በህሊና መዝገብ ላይ የሚቆይ ነው፡፡

በመሆኑም የሚከተሉት ሃይማኖት ወይም መርጠው ያልተወለዱበት አካባቢ እንደበደል ተቆጥሮባቸው ከየአቅጣጫው በሚሰነዘረው ጥቃት በሚገደሉ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች፣ ምእመናን በአጠቃላይ የሰው ልጆች ኀዘን ልባችን በትካዜ ውስጥ በገባበት በዚህ ወቅት በመንፈሳዊ ሕይወቱ እና በትጋቱ ለቤተ ክርስቲያን ተስፋ የነበረው፤ ለበርካታ ዓመታትም በገጠር፣ በከተማ፣ በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ እየተዘዋወረ ወንጌለ መንግሥትን ሲያስተምር የቆየው የመንፈስ ቅዱስ ልጃችን መ/ር ዘለዓለም ወንድሙ ለመንፈሳዊ አገልግሎት በተጓዘባት ሰሜን አሜሪካ ባጋጠመው ሕመም ከዚህ ዓለም ድካም በሥጋ ማረፉን ስንሰማ ታላቅ ድንጋጤ ፈጥሮብናል፡፡

በእርግጥ መምህር ዘለዓለም ወንድሙ ስመ ጥምቀቱ ወልደ ሰማእት በሥጋ ከእኛ ቢለይም ያለዋጋ የተቀበለውን የእግዚአብሔር ቃል ለምእመናን በማስተማር አደራውን በሚገባ ተወጥቶአልና በሰማይ ወደሚጠብቀው ዘለዓለማዊ ስፍራ በክብር እንደሚገባ እናምናለን፡፡

የመልካም ሰዎች መጉደል ለሀገር በተለይም ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን የነገ ዕጣ ፈንታ የሚያስጨንቅ ቢሆንም ሁሉን የሚችል አምላክ ተተኪዎችን እንዲያዘጋጅልን በመጸለይ፤ ለመንፈስ ቅዱስ ልጃችን ቤተሰቦች፣ ወዳጅ ዘመዶችና ምእመናን መጽናናትን እየተመኘን አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡

እግዚአብሔር አምላክ የአገልጋዩ ወልደ ሰማዕትን ነፍስ በመንግሥቱ ያሳርፍልን፤

“እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ”

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ኣሜን!

+ አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ
ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣
የካቲት 30 ቀን 2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
29🙏11
ወተቀበልዎ መላእክት በስብሐት ወበማኅሌት፤
ወአብዕዎ ኢየሩሳሌም ሰማያዊተ አብዕዎ ገብረ ሕይወት፡፡
እንኳን #ለአቡነ_ገብረ_መንፈስ_ቅዱስ_በዓለ_ዕረፍት_በሰላምና_በጤና_አደረሳችሁ፡፡
አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ (አቦ፥ አቡዬ)፤
* እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ብርሃነ ዓለም የኾኑ፤
* እንደ ቅዱስ እስጢፋኖስ ጸጋንና ክብርን የተሞሉ፤
* ኰከበ ገዳም፥ መናኔ ዓለም፥ ምድራዊ መልአክ፤
* ስማቸውን ሊቀ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ያወጣላቸው፤
* በአክናፈ መባርቅት ተጭነው የሚጓዙ፤
* 60 አናብስትና 60አናብርት ይታዘዙላቸው የነበሩ፤ የእግራቸው ትቢያ ለአራዊቶቹ ምግብ የኾነላቸው፤
* ለብዙ አእላፍ ቅዱሳን ወላዴ የኾኑና በረከትን የሰጡ ታላቅ አባት (ለአብነትም፤ ለቅዱስ ላሊበላ፥ ለአቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ፥ ለአባ አንበስ ዘደብረ ሐዘሎ፥ ለአባ ብንያም ዘግብፅ)
፠፠፠ #ምድረ_ከብድ_፤ /ዝ_ምድር_ክቡድ_ውእቱ_/
( ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ለመጀመሪያ ጊዜ ያረፉባት ቦታ ናት ቀጥሎ ወደ ደብር ቅዱስ #ዝቋላ (#ዝ_ቆላ) ለጸሎት ሂደው ለሃገራችን ኢትዮጵያና ለዓለማችን ምሕረትና በረከትን ከአምላካችን ለ100 ዓመታት በባሕር ውስጥ ሆነው ለምነዋል፤ ወደ ምድረ ከብድ ተመልሰው ለ7 ዓመታት ጸልየዋል፤ ቊራም በሰይጣን ተመስሎ መጥቶ ዓይናቸውም ቢያጠፋውም ከ7 ሱባዔያት በኋላ ሊቀ መላእክት ሚካኤልና ገብርኤል ዓይናቸውን መልሰውላቸዋል፡፡ ወደ ዝቋላ በመመለስም አጋንንትም ከምድረ ዝቋላ አጥፍተዋል፤ ተመልሰው ወደ ምድረ ከብድ በነበሩበት ጊዜ ታላላቆቹና በአንበሳ ዘባን ላይ የሚሄዱት #አቡነ_ሳሙኤል_ዘዋልድባ#አባ_አንበስ_ዘደብረ_ሐዘሎ_አፋር)፣ #አባ_ብንያም ዘግብፅ ከአባታችን ቡራኬ ለመቀበል መጡ አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ተሰውረው ነበርና፤ የአቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ አናብስት የ3ቱን አባቶች አናብስት በሉባቸው፤ በ7ኛው ቀን አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ተገልጠው የኾነውን ነገር በማየት የተበሉትን አናብስት እንዲመልሱ የራሳቸውን አናብስት አዘዟቸው መልሰውም እንደነበሩ በተዓምራት አስነስተው ሰጧቸው፤ በደመና ጠቅሰው ቅዱስ ፋኑኤል 3ት ሰማያዊ ኅብስትና 3ት ጽዋዕ ይዞ ለእንግዶቻቸው ይዘው ሠረገላ በሚባለው ዋሻ አመጡላቸውና ሰጥተው ሸኟቸው፤ እነዚህን ቅዱሳን በሸኙ በ7ኛው ቀን ወደ ተለያዩ ሃገራት ሄደው አስተምረዋል፤ በግብፅ 300ዓመታት፥ በኢትዮጵያ ምድር ላይ 262ዓመታት (በዋነኛነት በምድረ ከብድና በዝቋላ ቢኖሩም ሌሎችም የመሠረቷቸውና የኖሩባቸው ገዳማት አሉ፤ ለአብነትም ደቡብ ወሎ የሚገኘውን ገዘዛ አቦን መጥቀስ ይቻላል) ከኖሩ በኋላ በንጉሥ ሕዝብናኝ(እንድርያስ) ዘመነ መንግሥት፤ መጋቢት 5 ቀን ቅዳሜ ለእሑድ አጥቢያ ብዙ ቃል ኪዳንን ጌታችን ሰጣቸው፥ 12 አክሊላትንም አቀዳጃቸው፤ የነበሩባትም ምድረ ከብድ ገዳም ራደች፥ ተንቀጠቀጠች፥ በብርሃንም ተጥለቀለች፤ ዝቅ እያለችም መንሸራተት ጀመረች፤ ጌታችንም አንቺ መሬት ሆይ ጽኚ ይህንን ኹሉ ስለቻልሽ ምድር ክቡድ /ኋላ ምድረ ከባድ/ ትብለሽ ተጠሪ አላት የጻድቁም ነፍስ ከሥጋቸው ከሌሊቱ 6 ሰዓት ተለየች፡፡ ይህችውም ምድረ ከብድ ጻድቁ የኖሩባትና የቀደሱባት፥ የመሠረቷትና ያነፅዋት፣ ሠራዊተ መላአክት የከተሙባት፣ ታላላቅ አበው መጥተው በረከት ከአባታችን የተቀበሉባት፣ አርምሞና ጸጥታ የማይለያት፤ አጸዷና ቅጥሯ ልቡናን የሚመስጥ፤ ከአ.አ 125 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ናት፡፡
አምላከ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ረድኤት፥ በረከትን ይክፈለን፡፡
(ሥርዐተ ማኅሌቱን የኢንተርኔት አቅርቦት በሌለባቸው ቦታዎች አድርሱልን፤ በተለይም ወደ ምድረ ከብድ፥ ዝቋላና ሌሎች የአባታችን ክብረ በዓል በሚከበርባቸው አድባራትና ገዳማት ያላችሁ አድርሱልን፡፡)

/በፍኖተ ሕይወት ሰ.ት.ቤት ሚድያና ሕዝብ ግንኙነት ዋና ማስተባበሪያ ክፍል የተዘጋጀ።/

• Facebook 👉 m.facebook.com/FinoteHiwotSundaySchool
• Telegram 👉 t.me/finotehiwott

• Tiktok 👉 tiktok.com/@finotehiwot 
• YouTube 👉 m.youtube.com/@finotehiwot1958
7🙏2
የመምህር ዘለዓለም ወንድሙ ግብዓተ መሬት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ብፁዓን ጳጳሳት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ቤተሰቦቹ፣ ወዳጅ ዘመዶች እና በርካታ ምእመናን በተገኙበት በታላቅ ክብር በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈፅሟል።
15😢9
#ደብረ_ዘይት ፨ የዐቢይ ጾም 5ኛ ሳምንት
※※※ ከዳግም ምጽአት በፊት የሚከሰቱት ድርጊቶች ※※※

፨ ደብረ ዘይት ማለት የወይራ ተራራ ማለት ነው፡፡ ይህም ቦታ ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ ካለው ከቄድሮስ ሸለቆ ራቅ ብሎ የሚገኝ፣ ርዝመቱ ፪ ኪሎ ሜትር፥ ከፍታው ደግሞ ከኢየሩሳሌም ከተማ በላይ 62 ሜትር ያህል ከፍታ ያለው ነው፤ቢታንያና ቤተ ፋጌ ከደ/ዘይት ተራራ ሥር የሚገኙ ቦታዎች ናቸው፡፡

በደብረ ዘይት ተራራ ላይ የተፈጸሙ ዋና ዋና ድጊቶች ከዚህ የሚከተሉት ናቸው፡-

⊚ በደብረ ዘይት ተራራ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ ጊዜ የሚያድርበት፣ የሚያስተምርበት፣ ውሎ የሚያርፍበት ሥፍራ ነበር። ሉቃ ፳፩፥ ፴፯፣ ሉቃ ፳፪፥ ፴፱፣ ዮሐ ፰፥፩፡፡
⊚ የጌታችን በዳግም ምጽአት እንደሚመጣ አስተማሮበታል /ማቴ.24፥1-36/
⊚ 33 ዓመት ከ3 ወር በዚህ ምድር ተመላልሶ ሞቶ ከተነሳ በኋላ ያረገበት ተራራ ነው፤ ‹‹ሁለት ሰዎች ነጫጭ ልብስ ለብሰው በአጠገባቸው ቆመው ታዩአቸው ‹እናንተ የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደ ሰማይ እያያችሁት ለምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ ያረገው ኢየሱስ፥ ከእናንተ ወደ ሰማይ ሲያርግ እንዳያችሁት እንዲሁ ዳግመኛ ይመጣል› አሏቸው፡፡ ከዚህም በኋላ ደብረ ዘይት ከሚባለው ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤›› ሐዋ.1፥11-12፣ ሉቃ.24፥51-52/፡፡
⊚ ዳዊት ከልጁ ከአቤሴሎም በሸሸ ጊዜ ወደ ደብረ ዘይት አቀበት ወጥሮ ነበር /2ኛ ሳሙ.15፥30/፣
⊚ ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ሆሳዕና ከደብረ ዘይት ወደ ኢየሩሳሌም ሒዷል /ማር.11፥1/
⊚ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ግርጌ በምትገኘው ለምለም ስፍራ በጌቴ ሴማኒ በአይሁድ ጭፍሮች ተያዘ፡፡ ማር.26፥30-36፤ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የተቀበረችበት ቦታም በጌቴሴማኒ ነበር፡፡
⊚ በደብረ ዘይት ተራራ ወገብ ላይ በሰፊው ተንጣሎ የሚታይ የአይሁድ መቃብር አለ። ይህን ስፍራ ለመቃብርነት የመረጡበት ምክንያት ወደፊት መሢሑ መጥቶ እስራኤልን ነፃ አውጥቶ ወደ አባቱ ያርጋልና ኋላ ለፍርድ ሲመጣ በመጀመሪያ የሚፈርድበት ስፍራና ሙታንም የሚነሱበትና የሚሰበሰቡበት ስፍራ ይህ በመሆኑ እኛ መሢሐችንን ለማግኘትና ከሙታንም ለመነሳት የመጀመሪያዎቹ እንሆናለን ብለው በማመናቸው ነው። አይሁድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መሢሕ እርሱ ነው ብለው አያምኑም። በመሆኑም እስራኤል ወደፊት አንድ ታላቅ መሢሕ እግዚአብሔር እንደሚልክላቸው ባላቸው ተስፋ መሠረት ገና አሁንም ድረስ መሢሐችንን እንጠብቃለን ይላሉ፤ ነገር ግን አይሁድ በዚህ በትልቁ ነገር ላይ ወደኋላ ቀርተው ተበድለዋል። ቀመረ አዝማናትን ቀንሰዋል፥ ቈነጻጸለዋል፤ የኦሪት መጽሐፋቸው ኦሪተ ብጡል ተብላለች፤ ይመጣል ያሉበትም ዘመን ሳይመጣ ዓለም ከተፈጠረ፥ ዘመን ከተቈጠረ 8ኛ ሺህ ላይ ደርሰናል፡፡ ይሁንና እግዚአብሔር እስራኤልን ብቻ ሳይሆን ዓለሙን ሁሉ እንዲያድን  አንድ  ልጁን  ጌታችን  መድኃኒታችን  ኢየሱስ  ክርስቶስን ልኮልን ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶልን በእርሱ ቁስል እኛ ተፈውሰናል፣ በእርሱ ሞት እኛ ሕይወትን አግኝተና/ኢሳ.፶፫፥፬-፮/። ከዚህ በኋላ ሌላ መሢሕ ሌላ አዳኝ ፈጽሞ የለም፡፡


※ ከዳግም ምጽአት በፊት የሚከሰቱት ድርጊቶች /ማቴ. ፳፬፥ ፫-፴፮/ እንደተገለጸው፡-

⊚ ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና ብዙዎችንም ያስታሉ
⊚ ጦርነትን የጦርነትንም ወሬ ትሰማላችሁ
⊚ ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣሉ
⊚ በየሀገሩም ረኃብ፣ ቸነፈርም፣ የምድር መናወጥም በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል
⊚ በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጧችኋል፤ ይገድሏችሁማል፤ ስለ ስሜም በሕዝብ ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ
⊚ በዚያን ጊዜም ብዙዎች ይሰናከላሉ እርስ በእርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ፣ እርስ በእርሳቸውም ይጣላሉ
⊚ ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያትም ይነሣሉ፤ ብዙዎችንም ያስታሉ
⊚ ከዐመፅም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች
⊚  የጥፋት ርኩሰት በተቀደሰችው ሥፍራ ቆሞ ታያላችሁ

⊚ በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናል ካለ በኋላ እስከመጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል በማለት ገልጾላቸዋል።
※የዐቢይ ጾም 5ኛ ሳምንት ደብረ ዘይት በመባል የሚታወቀው የደብረ ዘይት ሰንበት ምጽአት የተነገረበት ከመሆኑም በስተጀርባ በዚህ ዕለት ምጽአት እንደሚሆን ይታመናል፡፡ ከዐቢይ ጾም በ5ኛ ሳምንት መከበሩ በ5,500 ዓመተ ዓለም የመጣው ጌታ ከዚህም በኋለ በዚሁ ዕለት የሚመጣ መሆኑን ለማመልከት ነው፡፡

/በፍኖተ ሕይወት ሰ.ት.ቤት ሚድያና ሕዝብ ግንኙነት ዋና ማስተባበሪያ ክፍል የተዘጋጀ።/

• Facebook 👉 m.facebook.com/FinoteHiwotSundaySchool
• Telegram 👉 t.me/finotehiwott

• Tiktok 👉 tiktok.com/@finotehiwot 
• YouTube 👉 m.youtube.com/@finotehiwot1958
6🙏2