Finote Hiwot የቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኀኔ ዓለምና ደብረ ትጉሃን ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ሕይወት ሰንበት ትምህርት ቤት
15.3K subscribers
14.7K photos
78 videos
156 files
1.71K links
የቀጨኔ መድኃኔዓለም ፍኖተ ሕይወት ሰንበት ትምህርት ቤት ነሐሴ 26/ 1958 ዓ.ም ተመሠረተ።
Download Telegram
#ደብረ_ታቦር

ደብረ ታቦር ከገሊላ ባሕር በምዕራባዊ በኩል 10 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኝ ተራራ ሲሆን፤ ከፍታው ከባሕር ወለል በላይ 572 ሜትር ይሆናል፡፡ በዚህ ተራራ ላይ ጌታችን መድኃኒታችን #ኢየሱስ_ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን እንደሚገልጽ ምሳሌና ትንቢት ተነግሯል፡፡ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በትንቢቱ “#ታቦርና #አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል” ብሎ የተናገረው ትንቢት እንዲፈጸም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተአምራቱን በዚህ ተራራ ላይ ገልጧል /መዝ. 88፥12/፡፡ በዘመነ መሳፍንት ባርቅ ሲሣራን ከነሠራዊቱ ድል ያደረገው በደብረ ታቦር ተራራ ላይ ነው፡፡ ምሳሌነቱም ባርቅ የጌታችን ሲሣራ ደግሞ የአጋንንት ነው፡፡ ጌታችን በደብረ ታቦር ክብሩን በመግለጥ በአይሁድ እያደረ አምላክነቱን እንዲጠራጠሩ ያደረጋቸውን አጋንንት ድል የማድረጉ ምሳሌ ነው /መሳ. 4፥6/፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን በቂሳርያ “የሰውን ልጅ ማን ይሉታል?” ብሎ ከጠየቃቸው ከስድስት ቀን በኋላ #አዕማድ ተብለው የሚጠሩ ሦስቱን ሐዋርያት ይዞ ወደ ረጅም ታቦር ተራራ ወጣ፡፡ በፊታቸውም ተለወጠ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ፡፡ እነሆም #ሙሴና #ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው፡፡ ቅዱስ #ጴጥሮስ መልሶ ጌታችን ኢየሱስን ጌታ ሆይ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፡፡ ብትወድስ በዚህ ሦስት ዳስ እንስራ አንዱን ለአንተ አንዱን ለሙሴ አንዱን ለኤልያስ አለ፡፡ በዚህ ጊዜ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፡፡ ከደመናውም በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት የሚል ድምፅም ተሰማ፡፡ ሐዋርያት ይህንን ሰምተው የጌታችንን መለኮታዊ ክብር አይተው በፊታቸው ወደቁ እጅግ ፈርተው ነበር፡፡ ጌታችንንም ተነሡ አትፍሩም አላቸው፡፡ በዚህ መልኩ አምላክነቱን ገለጠላቸው /ማቴ. 17፥1-10/፡፡
፠፠፠

#አዕማደ_ሐዋርያት_ለምን_ተመረጡ

"አዕማደ ሐዋርያት ተብለው የተጠሩት #ጴጥሮስ#ያዕቆብና #ዮሐንስ ናቸው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ጴጥሮስ፣ ዮሐንስና ያዕቆብን “አዕማድ ሐዋርያት” እያለ ጠርቷቸዋል /ገላ. 2፥9/፡፡ ስያሜውን ያገኙበት ዋናው ምክንያት የኢየሩሳሌምን ቤተ ክርስቲያን በሓላፊነት ያስተባብሩ ስለነበረ ነው፡፡ ከዚህን በተጨማሪ ጌታችን በኢያኢሮስ ቤት ልጁን ሲፈውስ፣ በጌቴ ሴማኒ ሲጸልይና በደብረ ታቦር ምስጢረ መለኮቱን ሲገልጥ ከእሱ ስላልተለዩና ይዟቸው ስለሔደ ነው /ማር.5፥37-43/፡፡
ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ሦስቱ ደቀ መዛሙርት የተመረጡበትን ምክንያት ሲያትቱ እንዲህ ብለዋል፡፡ ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ሹመት፣ ሽልማትና ክብር ፈላጊዎች ነበሩ፡፡ ከዚህ ሃሳብ እንዲወጡ ከብልየታቸው እንዲታደሱ ለይቶ አውጥቷቸዋል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ለድኅነተ ዓለም የመጣው በሕማማቱ በሞቱ ቤዛ የሚሆነን አምላክ “ልሰቀል ነው” ባላቸው ጊዜ “አይሁንብህ” ብሎት ነበር፡፡ እንዲህ ያለው ሃሳብ የጠላት እንጂ የሰው ልጆች ሊሆን አይችልም ከሞቱ በቀር ድኀነት ሊያስገኝልን የሚችል የለምና፡፡ ደቀ መዝሙሩ ግን ከሞተ ክብሬ ምንድን ነው ብሏልና “አይሁንብህ” አለ፡፡ /ማቴ. 16/ በሌላም ስፍራ እንዲሁ “ሁሉን ትተን ተከተልንህ እንግዲያስ ምን እናገኝ ይሆን?” በማለት ይጠይቃል፡፡ /ማቴ.19/፡፡ ጌታ ግን ዋጋችሁ #ሰማያዊ #ክብራችሁ ዘላለማዊ ነው ሲል እስከ ፍጹማን መዓርግ /ነጽሮተ #ሥሉስ ቅዱስ/ አድርሶ ብርሃነ መለኮትን ገልጦ ተስፋውን ነገራቸው፡፡

ሁለቱ ወንድማማች ደቀ መዛሙርትም እናታቸውን ልከው ሹመት ሽልማት መዓርግ ለምነዋል፡፡ ስለዚህም ጌታችን በደብረ ታቦር “በኢየሩሳሌም ስለሚሆነው ነገር” ስለሞቱ እንዲነጋገሩ አደረገ፡፡ ሞቱ እርግጥ ሆነ ማለት ነው፡፡ አባቱም “ኦሆ በልዎ ለክርስቶስ”፤ እሺ በሉት እርሱን ስሙት ሲል፡፡ ሞቱ እርግጥ በመሆኑ ከልባቸው እንዲጠፋ መርጦ ወደ ቅዱስ ተራራ ይዟቸው ወጥቷል፡፡

“እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም” እንዲል /ሚል 3፥6/ በእርሱ ዘንድ ወረት የለም፡፡ አስቀድሞ ከተዓምራቱ ከምሥጢሩ አይለያቸውም ነበርና ብርሃነ መለኮትን ለማየት አበቃቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ለማወቅ፣ ለመማር፣ ለመጠየቅ ያሳዩት ትጋት ምስጢር ተገልጦላቸዋል፡፡ ይህ ምስጢር ለሦስቱ ደቀ መዛሙርት ተገልጦ የሚቀር አይደለም፡፡ እስከ ዓለም ፍፃሜ እግዚአብሔር ለመረጣቸው ሲገለጥ፣ በመረጣቸውም ሲነገር የሚኖር ነው፡፡ደቀ መዝሙሩ ጴጥሮስ “አልክድህም አልተውህም” የሚለው /ማቴ. 26፥35/ ቢወድደው አይደለምን? ፍቅሩን መግለጡ ለክብር አብቅቶታል፡፡ ሁለቱ ደቀ መዛሙርትም “ጽዋዬን ልትጠጡ አትችሉም” ቢላቸውም /ማቴ. 20፥22/ አንዳችን በቀኝ ሌላችን በግራ ሆነን አብረንህ እንሞታለን ሲሉ በምስጢር ለምነዋል፡፡ ሞታቸውን ከሞቱ ጋር መደመራቸው ፍቅራቸውን መግለጣቸው ነው፡፡
፠፠፠

#Share #like

#The_feast_of_the_transfiguration_of_our_lord_on_mount_tabor #Nehhasee 13
17🙏1🤝1
#ከተራራው ግርጌ

ከቅዱሱ ተራራ ግርጌ ዘጠኙ ደቀ መዛሙርት ተቀምጠዋል፡፡ ነቢዩ “አቤቱ በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል? በተቀደሰውስ ተራራህ ማን ይኖራል” / መዝ.14፥1/ በማለት ጠይቆ ወደ ተቀደሰው ተራራ የሚወጡ ሰዎች ምን ዓይነት ሕይወት ያላቸው ሊሆን እንደሚገባ ሲገልጥ “… በአንደበቱ የማይሸነግል፤ በባልንጀራው ላይ ክፉትን የማያደርግ … በንፁሑ ላይ መማለጃን የማይቀበል ….” በማለት የጠቀሳቸው ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ /መዝ. 14፥1-5/ ወደ ቅድስናው ስፍራ ወጥቶ ምስጢር ለማየት ብቃት ያልነበረው ይሁዳን ለመለየት አምላክ ባወቀ ዘጠኙን ከተራራው ግርጌ አቆይቷቸዋል፡፡
“የኃጥእ ዳፋ ጻድቁን ያዳፋ” የሚል ብሂል አለ፡፡ ይህ አባባል ግን ከተራራዉ ግርጌ ለቀሩት ደቀ መዛሙርት አይሆንም፡፡ ይሁዳን በጥበብ ከምስጢር ለየው እንጂ ጌታ ስምንቱ ደቀ መዛሙርቱን የምስጢሩ ተካፋይ አድርጓቸዋል፡፡ ለጥፋቱ ምክንያት እንዳያገኝ ከምስጢሩ ቢለየኝ ከሞቱ ገባሁበት እንዳይል በጥበብ ይህን አደረገ፡፡ ስምንቱ ደቀ መዛሙርት ግን በንጹሕ ልቡና ከተራራው ግርጌ ተቀምጠውም ምስጢር አልተከለከላቸውም፡፡ ምክንያቱም “ልበ ንጹሐን ብፁዓን ናቸው እግዚአብሔርን ያዩታልና” /ማቴ.5/፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያ እግዚአብሔርን ለማየት ለሚወዱ “ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ ያለ እርሱ ጌታን ሊያይ የሚቻለው የለምና” እንዲል፡፡ /ዕብ.11/፡፡

#ሙሴና ኤልያስ ለምን ተመረጡ?

ሙሴንና ኤልያስን ወደ ደብረ ታቦር እንዲመጡ ያደረገበት ምክንያት የባሕርይ አምላክ መሆኑን እንዲመሰክሩ ነው፡፡ ሙሴን ከመቃብር ተነሥቶ ስለጌታችን እንዲህ የሚል ምስክርነት ሰጥቷል፡- “እኔ ባሕር ብከፍልም፤ ጠላት ብገድልም፤ ደመና ብጋርድም፤ መና ባወርድም እስራኤልን ከክፋታቸው መልሼ ማዳን ያልተቻለኝ ደካማ ነኝ፤ የእኔን ፈጣሪ እንዴት ሙሴ ይሉሃል? የሙሴ ፈጣሪ እግዚአብሔር ይበሉህ እንጂ!” ኤልያስም ደግሞ ከብሔረ ሕያዋን መጥቶ “እኔ ሰማይ ዝናብ እንዳይሰጥ ብለጉም፣ እሳት ባዘንብም፣ እስራኤልን ከክፋታቸው ማዳን የማይቻለን ነኝ እንዴት የእኔን ፈጣሪ ኤልያስ ነህ ይሉሃል? የኤልያስ ፈጣሪ እግዚአብሔር ይበሉህ እንጂ!” ብለው የባሕርይ አምላክነቱን በደብረ ታቦር ላይ መስክረዋል፡፡ በማቴ.16፡14 ላይ “አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ አሉት።” ይላልና፡፡
ሙሴና ኤልያስ የተመረጡበት ሌላው ምክንያት ሙሴ “ጀርባዬንም ታያለህ፤ ፊቴ ግን አይታይም” ተብሎ ስለተነገረለት /ዘጸ.33፡23/ ኤልያስ “በኋለኛው ዘመን ምስክሬ ትሆናለህ” ስለተባለ ያንን ለመፈጸም ነው፤ ካገቡት ሙሴን ከደናግል ኤልያስ ያመጣቸው መንግሥተ ሰማያት በሕግ የተጋቡ ሕጋውያንና ሥርዐት ጠብቀው የሚኖሩ ደናግላን እንደሚወርሷት ለማስተማር ሁለቱን መርጧቸዋል፡፡
12👍2🙏1
#ቡሄ ማለት ምን ማለት ነው ? #ችቦ ለምን እና መቼ ይበራል?  #ሙልሙል ልምን ይታደላል?  በቡሄ ወቅት #ጅራፍ ለምን ይጮሃል  ?

#ቡሄ
ቡሄ ማለት ብራ፣ ብርሃን፣ ደማቅ ማለት ነው፡፡ ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት በዓል የሚዘከርበት እና ለበዓሉም ችቦ ስለሚበራ የብርሃን በዓል በማለት የቡሄ በዓል እንላለን፡፡ ወቅቱ የክረምት ፤ጨለማ አልፎ የብርሃን የሚወጣበት፤ ሰማይ ከጭጋጋማነት ወደ ብሩህነት የሚለወጥበት የመሸጋገሪያ ወቅት ነው፡፡ “ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት፤ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት” እንዲሉ፡፡ በሌላ በኩልም “ቡኮ/ሊጥ” ተቦክቶ ዳቦ የሚጋገርበት “#ሙልሙል” የሚታደልበት በዓል በመሆኑ ቡሄ ተብሏል፡፡ 
፨፨፨

#ጅራፍ
  በደብረ ታቦር በዓል በትውፊታዊ መልኩ የሚታየው ምስጢር፤ በኢየሩሳሌም ስለሚሆነው የጌታችን ምስጢራዊ ሞቱ ነው፡፡ ጅራፍ መገመድ(መጥለፍ) እና ጅራፍ ማጮኽ ሁለት ዓይነት ምስጢር የያዘ ትውፊታዊ ተግባር ነው፡፡ የመጀመሪያው ግርፋቱንና ሞቱን እናስብበታለን፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ፤ድምፁን ስንሰማ የባሕርይ አባቱን የአብን ምስክርነት ቃል፤ እንደ ነጎድጓድ ድምፅ ያስታውሰናል፡፡
የጅራፍ ትውፊታዊነት /ውርስ/፣ መጽሐፋዊ ትምህርትና ምስጢር ጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ ጨዋታውን በተራራማ አካባቢ፣ ከመኖሪያ ቤት ርቆና፣ በሜዳ ማድረጉ ጠቃሚ ነው፡፡ ጅራፍን #በርችት መቀየር የሚያመጣውን የምስጢር ተፋልሶ ብቻ መመልከት ከማኅበራዊ ጎጂ ገጽታው በላይ እንድናስወግደው ያስገድደናል፡፡
፨፨፨

   
    #ችቦ
     ችቦ የጌታችንን ብርሃነ መለኮት መገለጥ የሚያመለክት ነው፡፡ በመሆኑም ችቦ ለኩሰን በዓሉን እናከብራለን፡፡ የዚህ ትውፊታዊ አመጣጥ በብርሃኑ ድምቀት የቀኑን መምሸት ያልተረዱ እረኞች በሜዳ ቀርተዋልና ወላጆች ከመንደር ችቦ ለኩሰው ልጆቻቸውን ፍለጋ ሔደዋልና ታሪኩን እያዘከርን በዓሉት እናከብራለን፡፡ የችቦው መንደድም ሌላ ትርጉም አለው፡፡ አንድ ምእመን ለሌላው ምእመን መካሪ አስተማሪ መሆኑን፣ መከራ እየተቀበለም አርአያ፣ ምሳሌ፣ ብርሃን መሆኑን ያሳያል፡፡ በሃይማኖትም አርአያ ምሳሌ ይሆንላቸዋል፡፡ ከዚህ ጋርም ተያይዘዞ ችቦ #በ13 ምሽት ይበራል ፣ብርሃኑ የተገለጠው በዚችው ዕለት ነውና ፡፡
፨፨፨

    #ሙልሙል
በችቦ ብርሃን ልጆቻቸውን ፍለጋ የወጡ ወላጆች ዳቦ ጋግረው ይዘውላቸው ወጥተዋል፡፡ ስጦታው ቤተሰባዊነትን፣ ፍቅርንና መተሳሰብን መግለጫ ነው፡፡ ወደ ቤታችን “ ቡሄ ” እያሉ ለሚመጡ አዳጊዎችም፤ ዘምረው እንዳበቁ የሚሰጥ “ሙልሙል” ዳቦ አለ፡፡ ሕፃናቱም ሊዘምሩ ሲመጡ ዳቦ መስጠት ልማዳዊ ብቻ አይደለም፡፡ ሕፃናቱ
የደቀመዛሙርት ምሳሌ ናቸው፡፡ መዝሙራቸው ደግሞ ሐዋርያት “የምሥራች” ይዘው የመምጣታቸው ምሳሌ ነው፡፡ ሐዋርያት በገቡበት አገር አስተምረው አጥምቀው የጸጋ ልጅነትን አሰጥተው በረከት አድለው እንደሚሔዱም፣ ልጆችም ዘምረው፣ አመስግነው፣ መርቀው “ውለዱ ክበዱ፣ ሀብት አግኙ፣ የመንግሥተ ሰማያት ወራሾች ያድርጋችሁ
….” ይላሉ፡፡
በአጠቃላይ በዓለ ደብረ ታቦር ከእነዚህ ምስክር ካላቸው ትምህርቶቹ፣ ምሥጢር ከሚራቀቅባቸው ትርጓሜያቱና ከትውልድ ትውልድ በቅብብል በተላለፈው ቅዱስ ትውፊት ጋር ሃይማኖታዊ ባሕል ሆኖ ሊቀጥል ይገባዋል፡፡ ይህን ማድረግ የሚቻለው ግን አዳጊዎች ሃይማኖታዊ ትውፊቱን ይዘው እንዲያድጉ ጥቆማ በመስጠት፣ ግጥም በመግጠምና
ምሥጢሩን በማብራራት የመጀመሪያዎቹ ባለድርሻዎች ወላጆች ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የሚሰሙ ግጥሞች ስድብ፣ ፌዝና ሥላቅ የተቀላቀለባቸው ይሆናሉ፡፡ ሕፃናቱም ዝማሬውን ሲጀምሩ “ከሰጡን እንነሣ ከነሱን እናርዳ” ብለው ይጀምሩታል፡፡ ከሰጡን እንመርቃለን ካልሰጡን እንራገማለን በማለት፡፡ አሳሳቢው ነገር ደግሞ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ወደ ገንዘብ ማግኛነት የቀየሩ ሁኔታዎች መታየታቸው ነው፡፡

ዳቦ /ሙልሙል/ ትምህርቱንም፣ ምስጢሩንም፣ ትውፊቱንም በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል ከዚም ጋር ተያይዞ ሰንበት ት/ት ቤታችን ለበረካታ ዓመታት ሰወረድ የመጣውን የዝማሬ ሥርዓት ለአጥብያው ምእምን በየቤቱ በመሄድ የብሄን ዝማሬ ከነሥርዓቱ በመዘመር አገልግሎት ይሰጣል ፤የደብር ታቦርን በዓል በተመለከትም የወረቀት ጽሑፎችን ይበትናል በዝማሬ መኃል ያድላል  ፡፡
ቤተክርስቲያን የምሥጢር ግምጃ ቤት ናት፤ የምታከናውነውን ሁሉ ከበቂ መረጃ ጋር ነው ተግባራዊ የምታደርገው፡፡

/በፍኖተ ሕይወት ሰ.ት.ቤት ሚድያና ሕዝብ ግንኙነት ዋና ማስተባበሪያ ክፍል የተዘጋጀ።/

• Facebook 👉 m.facebook.com/FinoteHiwotSundaySchool
• Telegram 👉 t.me/finotehiwott

• Tiktok 👉 tiktok.com/@finotehiwot 
• YouTube 👉 m.youtube.com/@finotehiwot1958
7🙏1
#አጋፋሪ_ይደግሳል

፩ኛ ትርጕም አጋፋሪ፤ አሁን በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ደረጃ የማኅሌቱን ሥርዐት ፥ የዝክር ሁኔታን የሚያስተባብር አጋፋሪ ሲባል፤ ምክትሉ መጨኔ ይባላል፡፡

፪ኛ ትርጕሙ፤ አጋፋሪ፤ በቀድሞ ዘመን በሃገራችን በተለይም በቤተ መንግሥት ያለ ሹመት ሲሆን፤ (በጎንደር ፥ በሸዋ ፥ በወሎ ፥ በኢሉአባቦር፥ በሐረርጌ፥  በትግሬ ፥ አጋፋሪ ተብሎ ሲጠራ በጎጃም መጨኔ ይባላል/
ሁለቱንም በቀድሞ ዘመንም ሆነ አሁን ባለው ሁኔታ ትርጕሙን እናያለን ፤

፠፠፩ኛ ፠፠ አሁን ካለው የቤ/ክን አገልግሎት አንጻር፤ አጋፋሪ ማለት የማኅሌቱን ሥርዐት ፥ የዝክር ሁኔታን የሚያስተባብር ሲሆን ምክትሉ መጨኔ ይባላል፡፡ ይህ አጋፋሪ በደብረ ታቦር በዓል ላይም በቅዱስ ሚካኤል ተመስሎ፤ ‹‹ሆያ ሆዬ›› ይባላል፡፡ ይኸውም
‹‹#ሆያ_ሆዬ_ሆ_››፤ ማለት ጌታው ሆዬ ፥ እሜቴ ሆዬ ለማለት ነው፡፡
‹‹#እዚያ_ማዶ_ጢስ_ይጤሳል_›› የተባለው፤ እስራኤላውያን በበረሃ ለ40 ዓመታት ሲጓዙ ደመና እየጋረዳቸው (እየጤሰ) ስለመራቸው ነው፡፡
‹‹#አጋፋሪ_ይደግሳል_››፤ የተባለው አጋፋሪው /አለቃው/ ቅዱስ ሚካኤል ሲሆን፤ ይደግሳል መባሉ እስራኤላውያንን ‹‹በዕደ መልአኩ ይዕቀበነ ፥ ሰላመ ዚአሁ የኀበነ›› እንዲል፤ በአምላክ ትዕዛዝ ቅዱስ ሚካኤል መናን ከደመናን ፥ ውኃን ከጭንጫ ዓለት እያፈለቀ (እየደገሰ) መርቷቸዋልና ነው፡፡

****እንዲሁም የአብነት (የቆሎ) ተማሪዎች በክረምት ሲለምኑ የቆዩትን አጠራቅመው፤ የደብረ ታቦር ዕለት ብርሃነ መለኮቱን የገለጠ ጌታ ለኛም እንዲገልጥልን ብለው፤ ደግሰው ለሕዝቡ ያበላሉ ፥ ያጠጣሉ፡፡ /ይህ ሥርዐት በደብራችንም የሚከናወን ድርጊት ነው፡፡/

‹‹#ያችን_ድግስ_ውጬ_ውጬ_››፤ የተባለውና በድግስ የተመሰለው መና ሲሆን፤ በደጋሹ ቅዱስ ሚካኤል አማካይነት እስራኤል 40 ዓመታት መመገባቸውን (መና መዋጣቸውን) መናገር ነው፡፡

‹‹#ከድንክ_አልጋ_ተገልብጬ_›› ፤ ድንክ አልጋ የምትመች እንደሆነች ሁሉ ፥ በድንክ የምትመሰለውንና የምትመቻቸውን ተስፋዪቱ ምድር ኢየሩሳሌምን መውረሳቸው መናገር ነው፡፡
‹‹#ያቺ_ድንክ_አልጋ_አመለኛ_#ያለአንድ_ሰው_አታስተኛ_››፤ መባሉ እስራኤል ከግብጽ ሲወጡ 600,000 ሆነው ሲሆን፤ ሁሉም በምድረ በዳ አልቀው ኢየሩሳሌምን የወረሳት ሴትና ሕፃናት ሳይቈጠሩ፤ አንድ ኢያሱና አንድ ካሌብ ናቸው ለማለት ነው፡፡

፠፠፪ኛ ፠፠ #አጋፈረ፤ግስ ሲሆን በቤተ መንግሥት ፥ በግብዣ ቦታ፥ …. በር ላይ ቆሞ የሚገባውንና የሚወጣውን ሰው አስተናበረ አስተናገደ፡፡
*አጋፋሪ፤ ቅጽል ሲሆን፤ ቃሉ የቀድሞ አማርኛ ሲሆን አስተናባሪ (ብዙውን ጊዜ በግብዣ ወይም በቤተ መንግሥት በር ላይ በመቆም ሥርዐት የሚያስከብር ማለት ነው፡፡

*አጋፋሪ፤ የድግስ አለቃ ፥ አስተናጋጅ  ነገሥታት ግብር ሲያገቡ (ግብዣ ሲጋብዙ ፥ ድግስ ሲደግሱ) ወደ አዳራሹ (ወደ ድግሱ) እንዲገቡ የሚፈቅድ ፥ የማይገባቸውንም የሚከለክል፤ ከገቡም በኋላ እንደ የክብራቸውና እንደየማዕርጋቸው አንተ በዚህ ሁን ፥ አንተ በዚህ ተቀመጥ እያለ የሚያስቀምጥ፤ ኋላ የድግሱ ምግብና መጠጥ መታደል ሲጀምርም፤ እንጀራና ጠጅ አሳላፊዎችን የሚያዝና የሚቈጣጠር ትልቅ ሹም ነው፡፡

*አጋፋሪ፤ የሚለው መጠሪያ በ17ኛወና በ18ኛው ክፍለ ዘመን የታወቀ የቤተ መንግሥት ሹም መጠሪያ ነው፡፡ ‹‹ህዱግ ራስ›› በመባል የሚታወቅም ነው፤ በቤተመንግሥት የሚካሄዱ ሥራዎችንና የፍርድ ሂደቶች ያስተባብራል፤ አንዳንዴ ደግሞ የክፍላተ ሃገር የፍርድ ሰጪ ሰዎች ስም ሆኖም ያገለግላል፤ የስሜን (ከጎንደር በስተሰሜን የሚገኝ ግዛት ነው) አስተዳደር የሚገዛ ሰው ደግሞ የሰሜን አጋፋሪ እየተባለም ይጠራል፤ (ለምሳሌም አፄ ሱስንዮስ ልጃቸውን ፋሲለደስን የስሜን አጋፋሪ ብለው ሹመወት ነበር፤ ይህ የስሜን አጋፋሪ የሚለው ሹመትም እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ቆይቶ ነበር፡፡

#ቡሄ_
ቡሄ ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን የገለጸበት የነሐሴ 13 ቀን መጠሪያ ስሙ ነው የሚሉ ሊቃውንት እንዳሉ ሁሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፤
ቡሄ የሚባለው፤ ከነሐሴ 13 በኋላ  እስከ መስከረም 17 መስቀል ድረስ ሲሆን፤  በተለይም ይህ በዓል የሚታወቀው በሸዋና ወሎ /እስከ ጋይንት ጫፍ መጋጠሚያ) ድረስ ሲሆን፤ በዚህ ወቅትም ክርስትና አባት ለክርስትና ልጁ ተማሪ ከሆነ መጻሕፍትን (ዳዊት፣ …)፣ እንዲሁም አልባሳትን፣ በግና ሙክት ፍየልን የሚሰጥበት ነው፡፡ ሕፃናትና ወጣቱም ‹‹ቡሄ ፥ ሆ ….. ›› እያለ ይጨፍራል ፤ የሚሰጠውንም ሙክትና በግ እስከ መሰቅል ድረስ ሲያጠራቅም ከርሞ ለመስቀል ዕለት አርዶ ይበላል ፥ ደስታን ያደርጋል፡፡

ምንጭ፤ የቃል ትምህርት

/በፍኖተ ሕይወት ሰ.ት.ቤት ሚድያና ሕዝብ ግንኙነት ዋና ማስተባበሪያ ክፍል የተዘጋጀ።/

• Facebook 👉 m.facebook.com/FinoteHiwotSundaySchool
• Telegram 👉 t.me/finotehiwott

• Tiktok 👉 tiktok.com/@finotehiwot 
• YouTube 👉 m.youtube.com/@finotehiwot1958
10🙏1
#ነሐሴ_፲፪
#ቅዱስ_ሚካኤል_ንጉሥ_ቆስጠንጢኖስን_ረደቶ_በድል_ያነገሠበት_ዕለት

ንግሥት ዕሌኒም በ272ዓ.ም ታላቁ ቆስጠንጢኖስን ወለደችለት፤ ቆስጠንጢኖስም ገና በወጣትነቱ የአባቱ እንደራሴ ሆኖ እንደሠራ አባቱ ሞተ፡፡ የአባቱ ባለሟሎችና ህዝቡ ተስማምተው የ፲፰ ዓመቱን ቆስጠንጢኖስን በአባቱ ቦታ ሐምሌ ፳፭ ቀን ፫፻ ዓ.ም በሮም ምዕራብ ክፍል በገላትያ አነገሡት፡፡ በጦር ሜዳዎች ብዙ የጀግንነት ሥራዎች ስለሠራ በሠራዊቱ ዘንድ ይወደድ ነበር፡፡

ንግሥት ዕሌኒ ልጅዋን ቆስጠንጢኖስን ከልጅነቱ ጀምሮ ስለክርስትና ሃይማኖትና ስለክርስቲያኖች መከራ ታስተምረው ስለነበር በክርስቲያኖች ላይ የነበረው አመለካከት በሮም ከነገሡት ቄሣሮች ሁሉ የተሻለ ነበር፡፡ በተለይም በ፫፻፲፪ ዓ.ም ከጠላቱ ከመክስምያኖስ ጋር ለመዋጋት "ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት" ብሎ ለዘመቻ እንደተሰለፈ በራእይ በሰማይ ላይ "በዚህ የመስቀል ምልክት ጠላትህን ድል ታደርጋለህ; የሚል መስቀልና ጽሑፍ ስላየ ለሠራዊቱ ሁሉ #የመስቀል_ምልክት በመሣሪያቸውና በሰንደቅ ዓላማው ላይ እንዲያደርጉ አዘዘ፡፡ ወደያው ጦርነት ቢገጥም #በቲቤር_ወንዝ_ድልድይ ላይ ጠላቱን ድል ነሥቶ በጠቅላላው የሮም መንግስት ግዛቶች ሁሉ ገዥ ሆነ፡፡ ይኸውም የሆነው በመላእክት አለቃ #በቅዱስ_ሚካኤል ረዳትነት ነው፡፡

#ሚካኤል ማለት #መኑ_ከመ_እግዚአብሔ "እንደ እግዚአብሔር ያለ ማን ነው?" ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ሚካኤል ለፍጥረታት ሁሉ የሚራዳና የሚያዝን የምሕረትና የመዳኛ፤ የሰላም መልአክ ነው፡፡ ‹‹በዚያም ዘመን ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሣል›› (ዳን.፲፪፥፩) በማለት በነቢዩ ዳንኤል የተነገረ ሲሆን በሌላ ቦታ ‹‹ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ›› (ዳን. ፲፥፲፫) በማለት ያስረዳል፡፡

በድርሳነ ሩፋኤል ላይ እንደተገለጸው ሰባት ሊቃነ መላእክት ቢኖሩም አለቃቸው #ቅዱስ_ሚካኤል ነው፡፡ ቅዱስ ሚካኤል አርምሞ ትዕግሥትን የሚወድ መልአክ ነው፡፡ ‹‹የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ስለ ሙሴ ሥጋ ሲነጋገር ጌታ ይገሥጽህ አለው እንጂ የስድብን ፍርድ ሊናገረው አልደፈረም፡፡››

ቅዱስ ሚካኤል ከእግዚአብሔር በተሰጠው ኃይል ዲያብሎስን ድል የነሣ መልአክ ነው፡፡ "በሰማይም ሰልፍ ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ። ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ፥ አልቻላቸውምም፥ ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም። ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፥ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ፡፡" ራእ ፲፪፥፯-፱፡፡

#ታላቁ_ቆስጠንጢኖስ በመላእክት አለቃ በቅዱስ ሚካኤል ረዳትነት ጠላቶቹን ሁሉ ድል ነሥቶ በጠቅላላው የሮም መንግሥት ግዛቶች ሁሉ ገዥ ከሆነ በኋላ በ፫፻ ዓመታት ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ ለክርስቲያኖች የነጻነት ዐዋጅ ዐወጀ፡፡ ክርስትናም ብሔራዊ ሃይማኖት ተባለች፡፡

ንግሥት እሌኒም በተፈጠረላት አመች ሁኔታ በመጠቀም #የጌታችን_መስቀል ከተቀበረበት ለማውጣት በ፫፻፳፯ ዓ.ም ወደ ኢየሩሳሌም ሔደች፡፡ ዕሌኒ ልጅዋ ቆስጠንጢኖስ ክርስቲያን ከሆነላት ወደ ኢየሩሳሌም ሔዳ መስቀሉን ለመፈለግ እንዲሁም በኢየሩሳሌም ያሉ ቅዱሳት መካናትንና አብያተ ክርስቲያናትን ለማነጽ ለእግዚአብሔር ተሳለች፡፡ ከዚህ በኋላ #ቆስጠንጢኖስ_አምኖ በ፫፻፴፯ ዓ.ም #ተጠመቀ፡፡ ቅድስት ዕሌኒ ወደ ኢየሩሳሌም ሔደች ከእርሷም ጋር ብዙ ሠራዊት ነበር፡፡
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፡፡ እኛንም በጸሎቱ የምንታመን ሁላችንን የመልአክት አለቃ የቅዱስ ሚካኤልን ረድኤት በረከቱን ያሳድርብን፡፡ በጸሎቱ ይማረን፡፡
ስንክሳር ዘወርሃ ነሐሴ

/በፍኖተ ሕይወት ሰ.ት.ቤት ሚድያና ሕዝብ ግንኙነት ዋና ማስተባበሪያ ክፍል የተዘጋጀ።/

• Facebook 👉 m.facebook.com/FinoteHiwotSundaySchool
• Telegram 👉 t.me/finotehiwott

• Tiktok 👉 tiktok.com/@finotehiwot 
• YouTube 👉 m.youtube.com/@finotehiwot1958
7👍2