Finote Hiwot የቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኀኔ ዓለምና ደብረ ትጉሃን ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ሕይወት ሰንበት ትምህርት ቤት
15.3K subscribers
14.7K photos
78 videos
156 files
1.71K links
የቀጨኔ መድኃኔዓለም ፍኖተ ሕይወት ሰንበት ትምህርት ቤት ነሐሴ 26/ 1958 ዓ.ም ተመሠረተ።
Download Telegram
እንኳን አደረሳቹሁ !
ጾመ ፍልሰታ

#ጾም_በሐዲስ_ኪዳን፡- የሐዲስ ኪዳን ጾም ከብሉይ ኪዳን ጾም የተለየ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን የነበረው ጾም ሥጋዊ ችግርን የሚመለከት ሲኾን፤ በሐዲስ ኪዳን ግን የምንጾመው ለጽድቅ ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ የመጀመሪያ ሥራ ያደረገው ጾምን ነው፤ እንደዚሁም ያስተማራቸው ደቀ መዛሙርት ከሥራቸው በፊት ጾምን እንደ ጌታቸው አስቀደሙ፡፡ የሚከተሉት ጥቅሶች በሐዲስ ኪዳን ጾም እንደታዘዘ የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ ማር.፱፣፳፱፣ ማር.፪፣፳፣ ማቴ.፮፣፮፣ ሉቃ.፮፣፳፩፣ የሐ.ሥራ.፲፫፣፫፡፡ ስለዚህ ቤተክርስቲያናችን እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል አብነት በማድረግ ጾምን በአዋጅ እንድንጾም በቀኖናዋ (በሥርዐቷ) ደንግጋለች፡፡
በቤተክርስቲያናችን የአዋጅ ጾም የሚባሉት ሰባት ናቸው፡፡ እነርሱም፡-
1. ✣ ዐቢይ ጾም (ጾመ ኩዳዴ) 5. ✣ ጾመ ነነዌ
2. ✣ ጾመ ድኅነት (የረቡዕና ዐርብ) 6. ✣ጾመ ጋድ
3. ✣ ጾመ ሐዋርያት (የሰኔ ጾም) 7. ✣ #ጾመ #ፍልሰታ
4. ✣ ጾመ ነቢያት (የገና ጾም)

#ጾመ_ፍልሰታ
ፍልሰታ የግእዝ ቃል ነው፤ #ፈለሰ ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጕሙም ተለየ፣ ሄደ፣ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ መሄድን ያመለክታል፡፡ ጾመ ፍልሰታ ሐዋርያትን አብነት አድርገን፤ ሐዋርያት የተቀበሉትን በረከት ለማግኘት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምዕመናን የምንጾመው ታላቅ ጾም ነው።
እመቤታችን እንደ ሰው ልማድ ሞትን ትቀምስ ዘንድ ግድ ስለኾነ፤ ጻዕርና ሕማም በሌለበት አሟሟት፤ ዕዝራ በመሰንቆ፥ ዳዊት በበገና እያጫወቷት፤ በተወለደች በ64 ዓመቷ ጥር 21 ቀን #በ48 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ አርፋለች። ሐዋርያትም እንደምታርፍ በመንፈስ ቅዱስ ስለተገለጸላቸው ከያሉበት (ከየሀገረ ስብከታቸው) ወደ መኖሪያ ቤቷ (የሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ቤት) ተሰባስበው ነበር። ነፍሷ ከሥጋዋ እንደተለየች ሥጋዋን ገንዘውና ሸፍነው ወስደው ለመቅበር ወደ #ጌቴሴማኒ ሲሄዱ አይሁድ ሰምተው መጡና ሐዋርያትን ከበቧቸው። የአይሁድ ተንኮል አስከሬኗን ከሐዋርያት እጅ ቀምተው በእሳት ለማቃጠል ነበር፤ ይህንንም ማድረግ የፈለጉበት ምክንያት፤ የሐዋርያት ትምህርት (የጌታችን ከሞት መነሳትና ለፍርድ ተመልሶ መምጣት)ከአይሁድ አልፎ ዓለም ሁሉ እያመነበት ስለመጣ እመቤታችንም ተነሥታ ዐርጋለች እያሉ ሐዋርያት ያስተምራሉ በሚል ስጋት ነበር። ‹‹የፈሩት ይነግሣል፥ የጠሉት ይወርሳል›› እንዲሉ አበው፤ የእመቤታችን ትንሣኤም ሆነ ዕርገት አይቀሬ ሁኗል። አይሁድ የእመቤታችንን ሥጋ ለመንጠቅ በሞከሩበት ጊዜም ታውፋኒያ የተባለ ጎልማሳ ሰው በጉልበቱና በድፍረቱ በአይሁድ ዘንድ ተመርጦ የእመቤታችንን ሥጋዋ ያረፈበትን ቃሬዛ ከሐዋርያት ነጥቆ መሬት ላይ ለመጣል ሲሞክር፤ የእግዚአብሔር መልአክ በእሳት ሰይፍ ሁሉቱንም እጆቹን ቀንጥሶ (ቆርጦ) ጥሏቸዋል። ነገር ግን ጥፋቱን አውቆ ወዲያው ስለተፀፀተና ይቅርታ ስለጠየቀ በአምላክ ፈቃድ በእመቤታችን አማላጅነት በቅዱስ ጴጥሮስ አማካኝነት እጆቹ እንደገና ተመልሰውለት የእመቤታችንን እመ አምላክነት (የአምላክ እናት መሆኗ)ና ክብርን ለመመስከር በቅቷል።

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋ በመላእክት ተነጥቆ ከተወሰደ በኋላ በገነት ውስጥ #በዕፀ ሕይወት ሥር መቀመጡ ከዮሐንስ በስተቀር ለሌሎች ሐዋርያት ለጊዜው ምሥጢር ሆኖባቸው ቆይቶ ነበር። ቆየት ብሎ ግን ሐዋርያው ዮሐንስ ስለ እመቤታችን ሥጋ ነገራቸው። ቅዱሳን ሐዋርያትም ለእመቤታችን ካላቸው ክብርና ፍቅር የተነሳ ለምን አልቀበርናትም? ለምንስ የሥጋዋ ምሥጢር ለዮሐንስ ተገልጾ ለኛ ይደበቅብናል? በማለት እያዘኑና እየለመኑ ከጥር 21 አንስተው ለስድስት ወራት ከዐሥር ቀናት ቆይተዋል። ከዚህም በኋላ ከነሐሴ 1 ቀን ጀምረው ሱባዔ ይዘው ለ14 ቀናት እግዚአብሔርን በጾምና በጸሎት ጠየቁት። በመጨረሻም የነገሩትን የማይረሳ፥ የለመኑትን የማይነሳ ልጇ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነሐሴ 14 ቀን ሥጋዋን አምጥቶ ስለሰጣቸው፤ ሳይውሉ ሳያድሩ በዕለቱ በጌቴሴማኒ በታላቅ ክብርና ዝማሬ ቀበሯት። በተቀበረችም በ3ኛው ቀን በነሐሴ 16 ከተቀበረችበት መቃብር ተነሥታ ወዲያውኑ በታላቅ ክብር በመላእክት አጃቢነት ወደ ሰማይ ዐርጋለች።

ጥበበኛው ሰሎሞንም “ውዴ እንዲህ ይለኛል ሙሽራዬ ውዴ ሆይ! ተነሺ የእኔ ውብ ሆይ ነዪ አብረን እንሂድ” በማለት አመሣጥሮ የተናገረው በጥበበ እግዚአብሔር ተመርቶ እንደ ክርስቶስ ሆኖ ውዴ ያላት እመቤታችን መሆኗንና ልጇ ተነሥቶ እንደ ዐረገ እሷም መነሣቷንና ማረጓን እንረዳለን። /መሓ.፪፥፲/። እመቤታችን ባረገችበት ጊዜ ሐዋርያው #ቶማስ በመንፈስ ቅዱስ ጥበብ በደመና ተጭኖ ከሀገረ ስብከቱ (ሕንድ) ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለስ እመቤታችን በመላእክት ታጅባ ወደ ሰማይ ስታርግ ተገናኙ። በዚህ ጊዜ ቶማስ ቀድሞ የልጇን ትንሣኤ ሳላይ አሁንም ደግሞ እርሷን ሳልቀብራት ከትንሣኤዋም ሳልደርስ ቀረሁ ብሎ አዘነ ከደመናው ላይ ሊወድቅም ፈለገ፤ ሆኖም እመቤታችን ዕርገቷን ከእርሱ በቀር ሌሎች አለማየታቸውን ገልጻ አረጋጋችው፤ ዕርገቷንም ለሐዋርያት እንዲነግርና ምልክትና ማስረጃ እንዲሆነው ተገንዛበት የነበረውን ሰበኗን/የከፈን ጨርቅ/ ሰጥታ አሰናበተችው።
ቶማስም መሬት ለይ ወርዶ መቀበሯን፣ ትንሣኤዋንና ዕርገቷን ያላወቀ መስሎ ሐዋርያትን ስለ እመቤታችን ሥጋ ጉዳይ ጠየቃቸው፤ እነርሱም ሱባዔ ገብተው እግዚአብሔርን በጸሎት መጠየቃቸውን፣ ከሱባዔያቸው በኋላ የእግዚአብሔር ፈቃዱ ሆኖ ሥጋዋን መላእክት አምጥተው እንደሰጧቸውና እንደቀበሯት አስረዱት። እርሱ ግን ‹‹ሞት በጥር ነሐሴ መቃብር›› እንዴት ሊሆን ይችላል? ሲል ተከራከራቸው። ሐዋርያትም ቶማስን ለማሳመንና ለማሳየት ወደ መቃብሯ ወሰዱት፤ ሆኖም መቃብሯ ባዶ ሆኖ አገኙትና ተደናገጡ፤ በዚህ ጊዜ ቶማስ የሆነውን ሁሉ ገልጾ ለምልክትና ለማረጋገጫ የሰጠችውን ሰበኗን /ተገንዛበት የነበረውን ጨርቅ/ አሳያቸው፤ የራሱን ድርሻም አስቀርቶ አከፋፍሎ ሰጣቸው፤ #ዛሬም_ካህናት ከእጅ መስቀላቸው ጋር የሚይዙት እራፊ ጨርቅ የሚይዙበት ምክንያት ሐዋርያት የተከፋፈሉት የእመቤታችን ሰበን ምሳሌ ነው።
ሐዋርያትም የዕርገቷን ምሥጢር ካመኑ በኋላ ዕርገቷን ለማየት በዓመቱ በተመሳሳይ ሁኔታ እንደገና ከነሐሴ 1 ቀን ጀምረው ለ፪ኛ ጊዜ ሁለት ሱባዔ ገቡ፣ እግዚአብሔርም ልመናቸውን ሰምቶ በነሐሴ ወር በ16ኛው ቀን ጌታችን ሐዋርያትን ወደ ሰማይ አውጥቷቸው እመቤታችንን አግኝተዋት ከሷ ተባርከው በታላቅ ደስታ ወደ ደብረዘይት ተመልሰዋል።
22🙏2🥱1
በአጠቃላይ #የእመቤታችን ለሐዋርያት በተለያዩ ጊዜያት መታየት፣ የሥጋዋና የነፍሷ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ፍልሰት ሲባል ከዚህ የተነሣ #የነሐሴ ጾም በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዐት መሠረት ሐዋርያት ያገኙትን በረከት ለማግኘት ጾመ ፍልሰታን እንጾማለን።

/በፍኖተ ሕይወት ሰ.ት.ቤት ሚድያና ሕዝብ ግንኙነት ዋና ማስተባበሪያ ክፍል የተዘጋጀ።/

• Facebook 👉 m.facebook.com/FinoteHiwotSundaySchool
• Telegram 👉 t.me/finotehiwott

• Tiktok 👉 tiktok.com/@finotehiwot 
• YouTube 👉 m.youtube.com/@finotehiwot1958
7
#ቃለ_በረከት_ዘብፁዕ_ወቅዱስ_አቡነ_ማትያስ_ፓትርያርክ

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ.ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ የ2017 ዓ/ም የጾመ ፍልሰታ መግባትን አስመልክተው ቃለ ምእዳንና ቡራኬ ሰጥተዋል። መግለጫው የሚከተለው ነው።

       መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ፡-
በስመ ኣብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ኣሓዱ ኣምላክ ኣሜን!!!

       በሀገራችን በኢትዮጵያና በመላው ዓለም የምትገኙ ሕዝበ ክርስቲያን በሙሉ፡-

የክብር ባለቤት እግዚአብሔር ኣምላካችን እንኳን ለሁለት ሺሕ ዐሥራ ሰባት ዓ.ም የቅድስት ድንግል ማርያም ጾመ ፍልሰታ በሰላም ኣደረሳችሁ!

  ‹‹ታዓብዮ ነፍስየ ለእግዚአብሔር፣ ነፍሴ እግዚአብሔርን እጅግ ታከብረዋለች›› (ሉቃ.፩÷፵፮)


ይህንን ዐረፍተ ነገር የተናገረችው ማኅደረ መንፈስ ቅዱስ የሆነችው ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፤ ቅድስት ድንግል ማርያም እግዚአብሔር ዓለምን ለማዳን በሰራው ስራ ሰውነታችንን ለመዋሓድ የመረጣት ምርጥ የፍጥረት ወገን ናት፤ፍጥረት ሁሉ በእግዚአብሔር ለእግዚአብሔር ተፈጥሮኣል፤የእግዚአብሔርም ነው፤ የቅድስት ድንግል ማርያም መመረጥም በእግዚአብሔር ለሰው የተደረገ ምርጫ ነው፤

የሰው መዳን ከጥንቱ ከጠዋቱ በእግዚአብሔር ልዩ ኣሰራር እንደሚከናወን በነቢያት የተገለጸ ነበረ፣‹‹ኣኮ በተንባል ወኣኮ በመልኣክ ኣላ ለሊሁ እግዚእ ይመጽእ ወያድኅነነ፤ በኣማላጅም ኣይደለም፤ በመልኣክም ኣይደለም እሱ ራሱ ጌታ መጥቶ ያድነናል እንጂ›› የሚለው የነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ ትንቢትም ይህንን ያስረዳል፤ ቃለ ትንቢቱ ድኅነታችን በጌታ ቤዛነት እንደሚከናወን ያረጋግጣል፤ይህም ሊሆን የቻለው ከፍጡራን ወገን በደሙ ቤዛነት ፍጡራንን የሚያድን ስለሌለ ነው፤ ከዚህ ኣንጻር የሰው መዳን በእግዚአብሔር ኣሰራር በደም ቤዛነት ከሆነ፣ በደሙ ቤዛነትም ዓለምን ማዳን የሚችል ከፍጡር ወገን ከሌለ፣ መዳናችን በእግዚአብሔርና በእግዚአብሔር እጅ ብቻ የተንጠለጠለ ነበረ፤ እግዚአብሔር በደሙ ቤዛ ሆኖ ዓለምን ለማዳን ደግሞ ደም ሊኖረው ይገባ ነበር፤ በመሆኑም እግዚአብሔር በክዋኔው ደም የሌለው ስለሆነ ለቤዛ ዓለም የሚፈስ ደምን ገንዘብ ማድረግ ነበረበት፤ይህንን ደም ለመዋሓድ ቅድስት ድንግል ማርያምን መረጠ፤ ለዚህ ብቁ እንድትሆንም በእስዋ ላይ ስራውን ሰራ፤በምርጫውም መሠረት ከቅድስት ድንግል ማርያም ደማዊ ሥጋንና ነፍስን ተዋሕዶ ለቤዛዊ መሥዋዕት መንገዱን ኣመቻቸ፤

ቅድስት ድንግል ማርያም በነገረ ድኅነት መሰላል ለመሆን በእግዚአብሔር የተመረጠች በመሆኗ ኣንቀጸ ኣድኅኖ ወይም የድኅነት በር ትባላለች ፤ ቅድስት ድንግል ማርያም ለዚህ ታላቅ ነገረ ድኅነት መመረጥዋ እጅግ ታላቅ ዕድል መሆኑን ስለተገነዘበች ‹‹ታላላቅ ስራዎችን ሰርቶልኛልና›› በማለት እግዚአብሔርን በመዝሙር ኣመስግናለች ኣክብራለችም፤

        የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!

የቅድስት ድንግል ማርያም የምስጋና እና የኣምልኮ መዝሙር የኛም መዝሙር ነው፤ እግዚአብሔር ለቅድስት ድንግል ማርያም ታላላቅ ስራዎችን እንደሰራ ለኛም ብዙ ታላላቅ ስራዎችን ሰርቶልናል፤ እየሰራልንም ነው፤ ለሰራልን ኣምላክም እንደ ቅድስት ድንግል ማርያም ታላቅ ክብርን መስጠት ይገባናል፤ ለእግዚአብሔር የምንሰጠው ክብርም በቃል ብቻ የሚገለጽ ሳይሆን በተግባር የሚታይ ሊሆን ይገባል፤ የድንግል ማርያም መንፈሳዊ ሕይወት በማስተዋል በትሕትና፣ በትዕግሥት በርኅራኄ በመታዘዝ በንጽህና በቅድስና በክብርና በበረከት የተሞላ እንደሆነ በቅዱስ መጽሓፍ ከተጻፈው ሥነ-ሕይወቷ መረዳት እንችላለን፤

ታድያ በእርሷ ክብርና ተማሕፅኖ የምንተማመን ልጆቿም የእሷን ያህል እንኳ ባንችል ወደእርስዋ የሚጠጋጋ መንፈሳዊ ሕይወት ሊኖረን ይገባል፤ ይህም የምናደርገው ለእግዚአብሔር ክብርና ለእኛ መዳን ሲባል ነው፤ እኛ እግዚአብሔርን ስናከብር እንከብራለን እንድንማለን፤ ለእግዚአብሔር ክብር የማንሰጥ ከሆነ ግን ውጤቱ መክበር ሳይሆን ሌላ ነው የሚሆነው፤

  የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!

እኛ በየጊዜው ጾምን እንድንጾም ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት ፈቃደ ሥጋችንን በመግራት ለእግዚአብሔር ታዛዦች እንድንሆን ነው፤ ጾም የኃጢኣት መግቻ መሳሪያ በመሆኑ ‹‹ልጓመ ኃጢኣት›› ተብሎ ይታወቃል፤ በዚህም ሰውነታችንን ለግብረ ኃጢኣት ከሚያጋግሉ ምግቦች ኣርቀን በሰከነ መንፈስ እግዚአብሔርን እያሰብን ኃጢኣታችንንም እያስታወስን በንስሓ ወደ እርሱ ለመቅረብና ለሱ ለመታዘዝ እንጾማለን፤

የጾም ጥቅም ከጥንት ጀምሮ የታወቀ በእግዚአብሔርና በሰውም ተቀባይነት ያለው ነው፤ እግዚአብሔር ከመሥዋዕት ይልቅ መታዘዝን ይወዳልና በጾምና በጸሎት ለሱ ልንታዘዝ ይገባል፤ እግዚአብሔር በቅድስት ድንግል ማርያም ማሕፀን ሊያድር የቻለው ‹‹እንዳልኸኝ ይሁንልኝ›› ብላ ታዛዥነትዋን በገለጸች ጊዜ ነው፤ እኛም እንዳልከን ይሁንልን እያልን እንደእስዋ ታዛዥ መሆን አለብን፤

ዛሬ በዓለማችን ያለው መተረማመስ ለእግዚአብሔር ያለመታዘዝ ያመጣው ጣጣ እንደሆነ ማንም ኣይስተውም፤ መታዘዙ ቢኖር ኖሮ የሰው ልጅ ሰውን የሚያድን ብቻ እንጂ ሰውን የሚገድል መሳሪያ ኣያመርትም ነበር፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ወንድምህን እንደራስህ ኣድርገህ ውደድ ኣለ እንጂ ግደል ብሎ ኣላዘዘምና ነው፤ኣሁንም በዚህ ባለንበት ዓለም በጣም ተባብሶ የሚገኘው የመጠፋፋት ዝንባሌ ለእግዚአብሔር በመታዘዝ በሰላምና በሰጥቶ መቀበል ካልተቋጨ ዳፋው ኣስከፊ መሆኑ ኣይቀርም ፤ ከዚህ አንጻር ዛሬም ለሰው ልጆች ሁሉ የምናስተላልፈው መልእክት ‹‹በፍቅር ከሆነ ትንሹም ለሁሉ ይበቃልና ያለውን በጋራ በመጠቀም በፍቅርና በሰላም እንኑር›› የሚል ነው፤ ‹‹ፍትሕና ርትዕም ለሰው ልጅ መነፈግ የበለትም፤ ሰው በምድር ላይ ሰርቶ የመኖር መብቱ ሊከበርለት ይገባል፤ይህንን ማድረግ ማለት ለእግዚአብሔር መታዘዝ ማለት ነው፤ስለሆነም ለእግዚአብሔር ክብርና ለራሳችን መዳን ስንል ለእርሱ በመታዘዝ በሕይወትና በሰላም እንኑር፡፡
             
            በመጨረሻም፡-
በጾመ ማርያም ሱባዔ ስለሀገር ሰላምና ስለሕዝብ ደኅንነት በመጸለይ፣ በልዩ ልዩ ምክንያት በመከራ ላይ ወድቀው የሚገኙ ወገኖቻችንን በሚያስፈልጋቸው ሁሉ በመርዳት ሱባዔውን እንድናሳልፍ ኣባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም ለመላው ሕዝበ ክርስቲያን እናስተላልፋለን።

   መልካም የሱባዔ ወቅት ያድርግልን
   እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
   ወስብሐት ለእግዚአብሔር ኣሜን!!

    አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

         ነሐሴ 1 ቀን 2017 ዓ.ም
            ዋሽንግተን ዲሲ
17👍2🤝2