Finote Hiwot የቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኀኔ ዓለምና ደብረ ትጉሃን ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ሕይወት ሰንበት ትምህርት ቤት
15.3K subscribers
14.7K photos
78 videos
156 files
1.71K links
የቀጨኔ መድኃኔዓለም ፍኖተ ሕይወት ሰንበት ትምህርት ቤት ነሐሴ 26/ 1958 ዓ.ም ተመሠረተ።
Download Telegram
ዜና ዕረፍት

የፍኖተ ሕይወት ሰንበት ት/ት ቤት ቀደምትና አንጋፋ አባል የሆነው አሰግደው ጌትዬ
ዛሬ ግንቦት ፳፭ ቀን ፳፻፲፯ዓ.ም ሌሊት ፰ ሰዓት ላይ ከዚህ ዓለም ድካም በሞተ ሥጋ ተለይቷል። ወንድማችን ለረጅም ዓመታት እናት ቤተክርስቲያናቸውን በሰንበት ት/ት ቤት በኩል በተለያዩ የአገልግሎት ደረጃዎች ያገለገለ እና በማገልገል ላይ የነበረ ታላቅ ወንድማችን ነበረ ። ለቤተሰቦቹና ለወዳጅ ዘመድ መፅናናትን እንመኛለን ።

ቀብሩ ዛሬ ግንቦት 25 ከ7:00 - 8:00
በቀጨኔ መድኃኔዓለም ቤ/ክር ይፈጸማል
😢8910
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፨
የወንድማችን አሰግደው ጌትዬ (አቡሽ) (ኀይለ ማርያም) አጭር የሕይወት ታሪክ፨
''ያገለገለህን ሰው ሞት ቸል አትበል'' /መጽ. ሲራ ፴፰፥፲፪/

‎እግዚአብሔር የሰውን ልጅ በአርአያው እና በአምሳሉ ፈጠረው፤ ከምድርም አፈር አበጀው፤ የሕይወት እስትንፋስንም እፍ አለበት፤ እንዲል፡፡ ወንድማችን አሰግደው ጌትዬ እንደ እግዚአብሔር መልካም ፈቃድ በ1967 ዓ.ም. ከአባቱ አቶ ጌትዬ እንዳለ እና ከእናቱ ወ/ሮ ዐባይነሽ ንጋቱ በአዲስ አበባ ከተማ፥ በጉለሌ ክፍለ ከተማ፥ ልዩ ስሙ ቀጨኔ 2ኛው መንገድ ተብሎ በሚጠራው መንደር ተወለደ፨
ወንድማችን አሰግደው በቤተሰብ እንክብካቤ እና መልካም አስተዳደግ አድጎ ትምህርቱን በአካባቢው በሚገኘው የቄስ(አብነት) ትምህርት ቤት በመግባት ከፊደል ቈጠራ እስከ ንባብ ተምሯል፤ በመቀጠልም በዐፄ ልብነ ድንግል ት/ቤት የመጀመሪያ  ትምህርቱን ተምሯል። ምንም እንኳን በዘመናዊ ትምህርት ዘልቆ ባይሄድም፤ ገና በሕፃንነቱ፥ በእናቱ እቅፍ፥ በአባቱ ድጋፍ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲመጣ፤ መንፈሱን የገዛው፥ ነፍሱን የመሰጠው የታላቁ ደብር የቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኀኔዓለም ቤ/ክ የዐፀዱ ሽታ፥ የደጀ ሰላሙ መዐዛ እና የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት ነበር፡፡ በዚህም በማኅሌትና ሰዐታት፥ በኪዳንና በቅዳሴ ከሕፃንነቱ ጀምሮ ተሳታፊ ሆኗል።

ቅዱስ ዳዊት በመዝሙር ፲፭ ''አርዓይከኒ ፍኖተ ሕይወት'' (የሕይወት መንገድን አሳየኸኝ) እንዲል በ1978 ዓ.ም.፥ በ፲፪ ዓመት ዕድሜው ወደ ሰንበት ትምህርት ቤታችን ፍኖተ ሕይወት በመግባት ከሕፃናት ክፍል እስከ ወጣት ክፍል በመማር እስከ ዕለተ ዕረፍቱ አገልግሏል።፨

ወንድማችን አሰግደው ጌትዬ ለ39 ዓመታት ያህል በቤተ ክርስቲያናችን በማኅሌትና ሰዐታት፥ በኪዳንና በቅዳሴ በመገኘት ማገልገሉን፤ እንዲሁም በሰንበት ት/ቤታችንም የዝማሬ አገልግሎቱ ዓለም ያወቀው፥ ፀሐይ የሞቀው ነው፨ በሕይወት ዘመኑ ካከናወናቸው ዐበይት ተግባራት የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፤

፨ በ1970ዎቹ መጨረሻ፤ ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል ከባድ በነበረበት ዘመን ወንድማችን አሰግደው ግን በሰንበት ት/ቤታችን ተመዝግቦ አገልግሎት ጀምሯል፡፡ በዝማሬ አገልግሎት በመሳተፍም ያለ ድካምና ያለ መሰልቸት በሕመም አልጋ ላይ እስከ ዋለበት ድረስ ለ39 ዓመታት ሳያቋርጥ አገልግሎት የሰጠ ወንድማችን ነው።፤ በዚህም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ.ክ. የሰንበት ት/ቤቶች ከተመሠረቱ ከ80 ዓመታት በላይ ቢሆናቸውም፤ ያለሟቃረጥ 39 ዓመታትን በማገልገል ግን በኢትዮጵያ ቀዳሚውን ቦታ ይይዛል፤ ይህንንም የሰ/ት/ቤቶች ታሪክ ሲዘክረውና ሲያስታውሰው የሚኖር ይሆናል፨

፨ በ1980ዎቹ ዘመን በሰ/ት/ቤታችን ቅዳሜ እና እሑድ በሕፃናት ክፍልም ሆነ በወጣት ክፍል፤ በጠዋት እና ከሰዐት የሚሰጠውን ትምህርት በ2ቱም ክፍሎች እየተገኘ በትጋትና በንቃት ይከታተል ነበረ፡፡

፨ በተለይ ከ1988 ዓ.ም. ከሰንበት ትምህርት ቤታችን ዳግም ምስረታ (የኪዳነ ምሕረት ማኅበር ምሥረታ) በኋላ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙር ፻፫ ''እሴብሖ ለእግዚአብሔር በሕይወትየ'' (በሕይወቴ እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ) እንዳለ በዝማሬ አገልግሎት እና በሌሎች አገልግሎቶች ላይ የሰንበት ትምህርት ቤታችን መለያ እስኪሆን ድረስ ታማኝ አገልጋያችን ነበረ።

፨ በ1990ዎቹ መጀመሪያ የደብረ ትጉሃን ቅዱስ ገብርኤል ሕንፃ ቤ.ክ ሲሰራ  ከደብራችን ሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ ጋራ የገቢ አሰባሳቢ በመሆን አገልግሏል፡፡ ይህን አገልግሎቱንም ከ2000-2012 ዓ.ም (ኮሮና እስገከባበት) ድረስ በመቀጠል፤ በዕለተ ሰንበት፣ በደብራችን በሚከበሩ ወርኀዊ እና ዓመታዊ በዓላት ከሌሎች አባቶች ጋራ ስዕለት ተቀባይ በመሆን በታማኝነት እና በቅንነት የማይተካ አገልግሎት አከናውኗል፨

፨ ሰንበት ትምህርት ቤት ለምንማር ሁሉ አብነት በሚሆን መልኩ በየቀኑ የሰርክ ጕባኤ ተገኝቶ የሚማር ወንድማችንም ነው፨

፨ ዕለት ዕለት በኪዳን እና ቅዳሴ በመገኘት የቅዳሴ ጠበል እንዲሁም በቅጽረ ቤ/ክ ግቢ ውስጥ የሚገኘውን የመድኀኔዓለም ጠበል በመቅዳት በትጋትና በትሕትና ምዕመናንን ያገለገለ ወንድማችን ነው፡፡

፨ ከምንም ከምንም በላይ ደግሞ ወንድማችን ሰላምተኛ፥ ከአንደበቱ ክፉ የማይወጣ፥ ታዛዥ ሲሆን አብዛኛውን ዕድሜውንም በሥጋ ወደሙ የኖረ፤ የተማረውን የተገበረ ነው፨

፨ ሰ/ት/ቤታችንም ለዚህ ለማይተካ አገልግሎቱ በ2004 ዓ.ም. የታማኝ እና ትጉህ አገልጋይ ምስክር ወረቀት እና ሽልማት ፤ እንዲሁም በ2008 ዓ.ም. የሰ/ት/ቤታችን 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ ሲከበር ደግሞ ከ25 ዓመታት በላይ በማገልገሉ እውቅናን ተችሮታል፨

ዞሮ ዞሮ ከቤት፤ ኖሮ ኖሮ ከሞት እንዲባል የበዓለ ጥምቀትን ካከበረ በኋላ ሕመም አግኝቶት አልጋ ላይ ውሏል፤ ቤተሰቦቹም በጠበልም በሕክምናም ሲያስታምሙት ቆይተዋል፡፡
ነገር ግን ''ዘጻመወ ለዓለም የሐዩ ለዝሉፉ እንዲል መዝሙረኛ
እኛ ካሰብነው እርሱ አምላካችን ያሰበው ይበልጣልና፤ ወንድማችን በተወለደ በ50 ዓመቱ ግንቦት 24 ለ25 አጥቢያ ከሌሊቱ 8 ሰዐት አምላካችን ጠርቶታል፨
+++ ሥርዐተ ቀብሩም ግንቦት 25 2017 ዓ.ም. ከ7-8 ሰዐት ተወልዶ ባደገበት፣ በተማረበት እና ባገለገለበት በቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኀኔዓለም ቤ.ክ. አባቶች ቀሳውስት፥ ወንድሞች ዲያቆናት፥ መዘምራን ካህናት፥ በአገልግሎት የሚመስሉት የሰ/ት ቤት አባላት፥ ቤተሰብ ወዳጅ ዘመድ ጎረቤት በተገኙበት ከመኖሪያ ቤቱ ጀምሮ በዝማሬ ሽኝት ተደርጎለት ሥርዐተ ግብዓተ መሬቱ ተከናውኗል፨

ለቤተሰብ ወዳጅ ዘመድ ለሰንበት ት/ቤታችን ፍኖተ ሕይወት መጽናናቱን አምላካችን ያድለን፨

መሐራ እግዚኦ ለነፍሰ እኁነ ኀይለ ማርያም

፨ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል አሜን ፨

/በፍኖተ ሕይወት ሰ.ት.ቤት ሚድያና ሕዝብ ግንኙነት ዋና ማስተባበሪያ ክፍል የተዘጋጀ።/

• Facebook 👉 m.facebook.com/FinoteHiwotSundaySchool
• Telegram 👉 t.me/finotehiwott

• Tiktok 👉 tiktok.com/@finotehiwot 
• YouTube 👉 m.youtube.com/@finotehiwot1958
15😢7👍1