Finote Hiwot የቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኀኔ ዓለምና ደብረ ትጉሃን ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ሕይወት ሰንበት ትምህርት ቤት
15.3K subscribers
14.7K photos
78 videos
156 files
1.71K links
የቀጨኔ መድኃኔዓለም ፍኖተ ሕይወት ሰንበት ትምህርት ቤት ነሐሴ 26/ 1958 ዓ.ም ተመሠረተ።
Download Telegram
ወተቀበልዎ መላእክት በስብሐት ወበማኅሌት፤
ወአብዕዎ ኢየሩሳሌም ሰማያዊተ አብዕዎ ገብረ ሕይወት፡፡
እንኳን #ለአቡነ_ገብረ_መንፈስ_ቅዱስ_በዓለ_ዕረፍት_በሰላምና_በጤና_አደረሳችሁ፡፡
አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ (አቦ፥ አቡዬ)፤
* እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ብርሃነ ዓለም የኾኑ፤
* እንደ ቅዱስ እስጢፋኖስ ጸጋንና ክብርን የተሞሉ፤
* ኰከበ ገዳም፥ መናኔ ዓለም፥ ምድራዊ መልአክ፤
* ስማቸውን ሊቀ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ያወጣላቸው፤
* በአክናፈ መባርቅት ተጭነው የሚጓዙ፤
* 60 አናብስትና 60አናብርት ይታዘዙላቸው የነበሩ፤ የእግራቸው ትቢያ ለአራዊቶቹ ምግብ የኾነላቸው፤
* ለብዙ አእላፍ ቅዱሳን ወላዴ የኾኑና በረከትን የሰጡ ታላቅ አባት (ለአብነትም፤ ለቅዱስ ላሊበላ፥ ለአቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ፥ ለአባ አንበስ ዘደብረ ሐዘሎ፥ ለአባ ብንያም ዘግብፅ)
፠፠፠ #ምድረ_ከብድ_፤ /ዝ_ምድር_ክቡድ_ውእቱ_/
( ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ለመጀመሪያ ጊዜ ያረፉባት ቦታ ናት ቀጥሎ ወደ ደብር ቅዱስ #ዝቋላ (#ዝ_ቆላ) ለጸሎት ሂደው ለሃገራችን ኢትዮጵያና ለዓለማችን ምሕረትና በረከትን ከአምላካችን ለ100 ዓመታት በባሕር ውስጥ ሆነው ለምነዋል፤ ወደ ምድረ ከብድ ተመልሰው ለ7 ዓመታት ጸልየዋል፤ ቊራም በሰይጣን ተመስሎ መጥቶ ዓይናቸውም ቢያጠፋውም ከ7 ሱባዔያት በኋላ ሊቀ መላእክት ሚካኤልና ገብርኤል ዓይናቸውን መልሰውላቸዋል፡፡ ወደ ዝቋላ በመመለስም አጋንንትም ከምድረ ዝቋላ አጥፍተዋል፤ ተመልሰው ወደ ምድረ ከብድ በነበሩበት ጊዜ ታላላቆቹና በአንበሳ ዘባን ላይ የሚሄዱት #አቡነ_ሳሙኤል_ዘዋልድባ#አባ_አንበስ_ዘደብረ_ሐዘሎ_አፋር)፣ #አባ_ብንያም ዘግብፅ ከአባታችን ቡራኬ ለመቀበል መጡ አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ተሰውረው ነበርና፤ የአቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ አናብስት የ3ቱን አባቶች አናብስት በሉባቸው፤ በ7ኛው ቀን አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ተገልጠው የኾነውን ነገር በማየት የተበሉትን አናብስት እንዲመልሱ የራሳቸውን አናብስት አዘዟቸው መልሰውም እንደነበሩ በተዓምራት አስነስተው ሰጧቸው፤ በደመና ጠቅሰው ቅዱስ ፋኑኤል 3ት ሰማያዊ ኅብስትና 3ት ጽዋዕ ይዞ ለእንግዶቻቸው ይዘው ሠረገላ በሚባለው ዋሻ አመጡላቸውና ሰጥተው ሸኟቸው፤ እነዚህን ቅዱሳን በሸኙ በ7ኛው ቀን ወደ ተለያዩ ሃገራት ሄደው አስተምረዋል፤ በግብፅ 300ዓመታት፥ በኢትዮጵያ ምድር ላይ 262ዓመታት (በዋነኛነት በምድረ ከብድና በዝቋላ ቢኖሩም ሌሎችም የመሠረቷቸውና የኖሩባቸው ገዳማት አሉ፤ ለአብነትም ደቡብ ወሎ የሚገኘውን ገዘዛ አቦን መጥቀስ ይቻላል) ከኖሩ በኋላ በንጉሥ ሕዝብናኝ(እንድርያስ) ዘመነ መንግሥት፤ መጋቢት 5 ቀን ቅዳሜ ለእሑድ አጥቢያ ብዙ ቃል ኪዳንን ጌታችን ሰጣቸው፥ 12 አክሊላትንም አቀዳጃቸው፤ የነበሩባትም ምድረ ከብድ ገዳም ራደች፥ ተንቀጠቀጠች፥ በብርሃንም ተጥለቀለች፤ ዝቅ እያለችም መንሸራተት ጀመረች፤ ጌታችንም አንቺ መሬት ሆይ ጽኚ ይህንን ኹሉ ስለቻልሽ ምድር ክቡድ /ኋላ ምድረ ከባድ/ ትብለሽ ተጠሪ አላት የጻድቁም ነፍስ ከሥጋቸው ከሌሊቱ 6 ሰዓት ተለየች፡፡ ይህችውም ምድረ ከብድ ጻድቁ የኖሩባትና የቀደሱባት፥ የመሠረቷትና ያነፅዋት፣ ሠራዊተ መላአክት የከተሙባት፣ ታላላቅ አበው መጥተው በረከት ከአባታችን የተቀበሉባት፣ አርምሞና ጸጥታ የማይለያት፤ አጸዷና ቅጥሯ ልቡናን የሚመስጥ፤ ከአ.አ 125 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ናት፡፡
አምላከ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ረድኤት፥ በረከትን ይክፈለን፡፡
(ሥርዐተ ማኅሌቱን የኢንተርኔት አቅርቦት በሌለባቸው ቦታዎች አድርሱልን፤ በተለይም ወደ ምድረ ከብድ፥ ዝቋላና ሌሎች የአባታችን ክብረ በዓል በሚከበርባቸው አድባራትና ገዳማት ያላችሁ አድርሱልን፡፡)

/በፍኖተ ሕይወት ሰ.ት.ቤት ሚድያና ሕዝብ ግንኙነት ዋና ማስተባበሪያ ክፍል የተዘጋጀ።/

• Facebook 👉 m.facebook.com/FinoteHiwotSundaySchool
• Telegram 👉 t.me/finotehiwott

• Tiktok 👉 tiktok.com/@finotehiwot 
• YouTube 👉 m.youtube.com/@finotehiwot1958
👍9🙏2
መፃጕዕ፤ አራተኛው ሳምንት

#‹‹እኔ በሕመም የምሠቃይ በሽተኛ ነኝና አቤቱ ይቅር በለኝ!፤
#አጥንቶቼም ታውከዋልና ፈውሰኝ፤ ከዚህ የተነሣ ነፍሴ እጅግ ተጨነቀች››፡፡

አራተኛው ሳምንት መፃጕዕ ይባላል፡፡ በመፃጕዕ የተሰየመው የእርሱ ስህተት ለእኛ ትምህርት፥ ተግሳጽ እንዲሆነን እንጂ፤ በዚህ ሳምንት የሚታሰበው ጌታችን ሕሙማን መፈወሱን፣ ሙት ማስነሳቱንና ስለ ረቂቁ የነፍስ ደዌ ስለ ኀጢአትና ስለ ድኅነታችን የሚያዘክር ምስጋና ይቀርብበታል፡፡ ማቴ. 8፥1-37፣ ማር. 7፥13-37፣ ሉቃ. 17፥1-9፣ ዮሐ. 5፥1-18
በቤተክርስቲያን በሽተኞች በሦስት ስያሜ ይጠራሉ፡-
፨ በሽተኛ፤ የዕለት ሕመም ወይም እስከ አንድ ዓመት የታመመ ሰው፡፡
፨ ድውይ፤ እስከ አምስት ዓመት ሕመሙ የቆየበት፡፡
፨ መፃጕዕ፤ ከአምስት ዓመት በላይ ሕመሙ የጸናበት፤ ሲሆን ድውይ፥ በሕመም የሚማቅቅ፥ የዐልጋ ቊራኛ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ መፃጕዕ የተባለው ስለሕመሙ 38 ዓመታት መጽናት እንጂ ስሙ አይደለም፡፡

   በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ ትርጕሙ /የምሕረት ቦታ/፤ በግእዙ ቀላየ አባግዕ (የበጎች መዋኛ) በተባለች ምጥምቃት ዘጵሩጳጥቄ በምትባል የጠበል መጠመቂያ ኩሬ ዳር የውኃውን መንቀሳቀስ እየጠበቁ በሽተኞች፥ እውሮች፥ አንካሶች፥ ልምሾች፥ ሰውነታቸው የሰለለ የደረቀና ያበጠ ብዙ ድውያን ሕዝብ ይተኙ ነበር፡፡ ከእግዚአብሔር የተሰጠውን የምሕረት ፈውስ ይዞ በሳምንት አንድ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ውኃውን ባርኮ ሲሄድ ቀድሞ የገባው በሽተኛ ይፈወስ ነበር፡፡
ተስፋ ሳይቈርጥ ለ38 ዓመታት ድኅነትን እየጠበቀ በሕመሙም እተሰቃየ በዚያ የተኛ አንድ ሰው ነበር፡፡ ጌታችን ይህን ሁሉ ዓመት እንደተሰቃየ አውቆ ድኅነት ሊሰጠው ወዶ መጣ፡፡ ‹‹ልትድን ትወዳለህን?›› ብሎ ጠየቀው፡፡ መጠየቁ ፍጹም የሰውን ሥጋ እንደተዋሐደ ሲያጠይቅ ነው፡፡ በተጨማሪም በዕለተ ዐርብ ‹‹ራሱ አዳነኝ እንጂ መቼ አድነኝ አልኩት!›› ብሎ ለመክሰስ ምክንያት እንዳያገኝ ጠየቀው፡፡ ‹‹ጌታ ሆይ ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያው ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም›› አለው፡፡ ‹‹እንዲህ ያለው የ30 ዓመት ጎልማሳ ነውና አንስቶ ይጨምረኛል›› ወይም አምስት ገበያ የሚያህል ሕዝብ ይከተለው ነበርና ‹‹ከእነርሱ መካከል አዞልኝ ወደ መጠመቂያው ይጨምረኛል›› ብሎ ነው እንጂ እንዲሁ ይፈውሰኛል ብሎ አልነበረም፡፡ ጌታ ግን ለመዳን መውደዱን ተመልክቶ ‹‹ተነሳና አልጋህን ተሸክመህ ሒድ›› አለው፡፡ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚገኘው ፍጹም ድኅነት ነውና ወዲያው ሰውየው ዳነ፤ አልጋውንም ተሸክሞ ሔደ፡፡ ያን ሰውም ጌታችን በምኵራብ አገኘውና እነሆ ድነሃል፤ ግን ከዚህ የባሰ እንዳያገኝህ ዳግመኛ እንዳትበድል እወቅ አለው፡፡

አልጋውንም ተሸክመህ ሂድ ያለው 38 ዓመት የተሸከመችው ጠንካራና የብረት አልጋ ስለተሸከመ ፍጹም መዳኑ እንዲታወቅ ነው፡፡ መጻጕዕ የተፈወሰው በእለተ ቀዳሚት ስለነበረ ፤ በሰንበት ይህን ስላደረገ አይሁድ ኢየሱስን ያሳድዱት፣ ሊገድሉትም ይፈልጉ ነበር፡፡ በሽተኛው የተደረገለትን ተአምር ረስቶ በዕለተ ዐርብ ጌታን ከሰሰው፤ በጥፊም መታው ወዲያው እጁ ሰለለ፡፡

ቅዱስ ያሬድም ጌታችን ሰንበትን ለዕረፈት ስለፈጠራት፤ ሕሙማንን በመፈወስ (የመቶ አለቃውን ልጅ በመፈወስ ማቴ. 8፥1-15፤ የዕውራንን ዓይኖች በማብራት ማቴ. 20፥24-30፤ ዮሐ. 9፤ ሽባ የነበረውን በመፈወስ) #በዕለተ_ሰንበት_ከበሽታቸው_እንዲያርፉ_አደረገ፡፡

#በእኛ በሰው ልጆች ላይ በሽታ በተለያየ ምክንያት ይመጣል፡፡
፨ በኃጢአት ምክንያት የሚመጣ በሽታ፡፡ ዘኍ. 21፥4-9
፨ የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ ይገለጥ ዘንድ የሚመጣ በሽታ አለ፡፡ ዮሐ. 9፥13
፨ ሰዎች ከእግዚአብሔር ዋጋ እንዲያገኙበት ከዲቢያሎስ የሚመጣ የፈተና በሽታ አለ እንደ ጻድቁ ኢዮብ፡፡ መጽ.ኢዮብ
፨ ሰዎች በተሰጣቸው ጸጋ እንዳይታበዩ ማሳወቂያ የሚሆን በሽታ አለ፤ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ራስ ምታት፡፡
፨ የበደለውን የሚቀጣበት በሽታ አለ፤ እንደ ሳዖል አጋንንት አድሮበት ይሰቃይ ነበር፣ የመጻጕዕ እጁ የሰለለው በሁለተኛ በደሉ ነው፡፡
፨ ያልታመመው እግዚአብሔርን እንዲያመሰግን፥ የታመመው ምሕረትን እንዲለምን የሚመጣ በሽታ አለ፡፡

/ምንጭ፦ የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 5 አንድምታ/
      ፨፨፨ወስብሐት ለእግዚአብሔር፨፨፨

/በፍኖተ ሕይወት ሰ.ት.ቤት ሚድያና ሕዝብ ግንኙነት ዋና ማስተባበሪያ ክፍል የተዘጋጀ።/

• Facebook 👉 m.facebook.com/FinoteHiwotSundaySchool
• Telegram 👉 t.me/finotehiwott

• Tiktok 👉 tiktok.com/@finotehiwot 
• YouTube 👉 m.youtube.com/@finotehiwot1958
👍95
መዝሙር ዘመጻጉዕ

/ፍኖተ ሕይወት ሰ.ት.ቤት ሚድያና ሕዝብ ግንኙነት ዋና ማስተባበሪያ ክፍል።/

• Facebook 👉 m.facebook.com/FinoteHiwotSundaySchool
• Telegram 👉 t.me/finotehiwott

• Tiktok 👉 tiktok.com/@finotehiwot 
• YouTube 👉 m.youtube.com/@finotehiwot1958
🙏13👍4
ዝክረ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ

ፖለቲከኞች ያስጨነቋት የኮፕቲክ ቤተክርስቲያን ቅዳሜ መጋቢት 8 ቀን 2004 ዓ.ም /March 17, 2012/ ትልቅ ሐዘን ወደቀባት። ዕለቱ ለምድራችን ሚዲያዎች ሰበር ዜና ነበር፡፡ ባለብዙ ጸጋ ልጅዋን በሞት ያጣችው የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መጽናናት አልቻለችም፡፡

የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ቅዱስነታቸው አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ የተወለዱት በላዕላይ ግብፅ በምትገኘውና "አስዩት" ተብላ በምትጠራው ከተማ ውስጥ ሲሆን ሲወለዱ የተሰጣቸው ስም #ናዚር_ጋይድ የሚል ነበር። ለቤተሰባቸው 8ኛ ልጅ ነበሩ። በልጅነታቸው በአድባራት ሰንበት ት/ቤቶች በሕይወት ውኃ ምንጭ አደጉ፡፡

በ1939 ዓ.ም የመጀመሪያ ድግሪያቸውን ከካይሮ ዪኒቨርሲቲ ያገኙት በታሪክ ትምህርት ነው። ናዚር ጋይድ በቤተ ክርስቲያናቸው ውስጥ ንቁ ተሳታፊ ስለነበሩ በመጀመሪያ "ሾብራ" ውስጥ በሚገኘው የቅዱሥ እንጦንስ ቤተ ክርስቲያን ከዚያም "ማህማሻ" ውስጥ በምትገኘው የቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስትያን ውስጥ አገልግለዋል። ቀን ቀን ካይሮ ውስጥ በአንድ ከፍተኛ ሁለተኛ ደርጃ ትምህርት ቤት ውስጥ የእንግሊዝኛና የኅብረተሰብ ትምህርት ሲያስተምሩ ይውሉና ማታ ማታ የቅብጥ የሥነ መለኮት ትምህርት ይክታተሉ ነበር። ከዚህ ትምህርት ቤት እ.ኤ.አ በ1949 ዓ.ም ሲመረቁ የአዲስ ኪዳን ጥናት እንዲያስተምሩ ተመረጡ።እ.ኤ.አ በ1945ዓ.ም በገዳም ትምህርት ቤት ውስጥ አስተማሪ ሆነው ተመደቡ።

ቅዱስነታቸው ገና ከወጣትነታቸው ዘመን አንስቶ መጻፍ በተለይም ግጥም እጅግ በጣም የሚወዱ ስለ መሆናቸውና የተዋጣላቸው ጸሐፊ ለመሆናቸው የጻፏቸው ከመቶ የሚበልጡ መጻሕፍት ምስክር ናቸው።ለብዙ ዓመታት በሰንበት ትምህርት ቤት ውስጥ ለሚታተም መጽሔት ዋና አዘጋጅ ሆነው አገልግለዋል።በተመሳሳይ ጊዜ በአርኬዎሎጂ የድኅረ ምረቃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።

ሐምሌ 18 ቀን 1956 ዓ.ም ናዚር ጋይድ #የበረሐውን_ሕይወት ለመጀመር በግብጽ ምዕራባዊ ግዛት ውስጥ ወደሚገኘው #በዋዲ_ኤል_ናትሩን ወደሚገኘው የሶርያውያን ገዳም ገብተው ምንኩስናን ተቀበሉ አባ እንጦንዮስ ኤል-ሱሪያኒ የሚል ስም ተሰጥቷቸዋል። ከዚያም ለስድስት ተከታታይ ዓመታት (ከ 1948- 1954 ዓ.ም.)ከገዳሙ በሰባት ማይልስ ርቀት በሚገኘው ዋሻ ውስጥ ሙሉ ጊዜያቸውን ለተመስጦ፣ ለጸሎትና ለምናኔ በመስጠት የብሕትውናን ሕይወት አሳልፈዋል። ባሕታዊው የተሰኘውንና በኋላ እኤአ በ1946 የታተመውን ቅኔያቸውን የጻፉት በዚህ ጊዜ ነበር። ብዙ ጊዜያቸውንም የሚያሳልፉት #በዋሻቸው ውስጥ በጸሎት እና ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ ነበር፡፡ ለብዙ ጊዜያትም ወደ ኤጲስ ቆጶስነት እንዳይጠሩ ሲከላከሉ ኖረዋል፡፡

በ1962 ዓ.ም በቀድሞው የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ፓትርያርክ በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቄርሎስ 4ኛ አማካኝነት የመንፈሳዊ ትምህርት ጳጳስና የቅብጥ የሥነ መለኮት ትምህርት ቤት ፕሬዝዳንት ተብለው ተሰየሙ። አቡነ ሺኖዳ የሚለው ስም የተሰጣቸው መስከረም 20 ቀን 1955 ዓ.ም ነው። አቡነ ሺኖዳ አስቀድሞ የጀመሩትን የጽሑፍ ስራ ባለ ማቋረጥ ኤል-ኬራዛ የተባለውን ተከታታይ መጽሔት የመጀመሪያ እትም በአረብኛ ቋንቋ በ1958 ዓ.ም አሳተሙ።ቅዱስነታቸው እስከ እለተ እረፍታቸው ጊዜ የዚህ መጽሐፍ ዋና አዘጋጅ ነበሩ። ኅዳር 4 ቀን 1964 ዓ.ም ቅዱስነታቸው አቡነ ሺኖዳ ሳልሳዊ በማርቆስ መንበር 117ኛ የእስክንድርያ ፓትርያርክ ተብለው ተሾሙ።

#የቅዱስነታቸው ክርስቲያናዊ ተግባራት

፨ የእስክንድርያ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስን በዘመናዊ መልክ አደራጅተዋል፡፡ በ1985 ዓ.ም አላማ እና ፖሊሲዎችን ያቀፈ የሲኖዶስ ውስጠ ደንብ አፅድቀዋል፡፡

፨ ከግብጽ ውጪ 150 አብያተ ክርስቲያናትን ተክለዋል፡፡

፨ ከግብጽ ውጪ 8 ገዳማትን በአፍሪካ፣ በአውስትራሊያ፣ በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ መስርተዋል፡፡

፨ የነገረ መለኮት ኮሌጆችን ቁጥር ወደ 11 ከፍ አድርገዋል፡፡ የድህረምረቃ ተቋምም አቋቁመዋል፡፡

፨ 120 በላይ የእምነትና የሥነ ምግባር መጻሕፍትን ጽፈዋል በዚህም ምክንያት “የ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ዮሐንስ አፈወርቅ” ተብለዋል፡፡

፨ የዓለም፣ የአፍሪካ እና የመካከለኛው ምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤቶችን አጠናክረዋል፡፡

፨ ቅዳሴአቸውን በእንግሊዝኛ፣ በፈረንሳይኛ፣ በጀርመንኛ፣ በኢጣልያንኛ፣ በስዋሊና በደቡብ አፍሪካ ቋንቋዎች እንዲተረጎም አድርገዋል፡፡

፨ ምዕመናን በቤተክርስቲያን አስተዳደርና ማኅበራዊ ጉዳይ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው አድርገዋል፡፡ ቁጥራቸውንም 12 ሚልዮን አድርሰዋል፡፡

፨ ሀገራችን ኢትዮጵያን ሁለት ጊዜ ጎብኝተዋል፡፡ (በንጉሥ ኃ/ሥላሴ ግብዣ መስከረም 15 ቀን 1966 ዓ.ም እና በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ጋባዥነት ሚያዝያ 3-5 ቀን 2000 ዓ.ም)

፨ በሞት እስከተለዩበት እስከ መጋቢት 8 ቀን 2004 ዓ.ም ድረስ ለ41 ዓመታት በፓትርያርክነት አገልግለዋል፡፡

ቅዱስነታቸው ገዳማትን ያስፋፉ ለመናንያን አርአያ የሆኑ ባህታዊ (መነኮስ)፤ ቤተሰባዊ ችግሮችን በመፍታት የታወቁ መካሪ፤ መንጋውን ተግተው የመገቡ እረኛ፤ በደሙ በዋጃት ቤተክርስቲያን ላይ አለቃ አድርጎ የሾማቸውን ያልዘነጉ ጳጳስ፤ የእስክንድርያን ቤተክርስቲያንን እንደዋርካ ያሰፉና ቅዱስ ሲኖዶሷን በምሁራን ያደራጁ ፓትርያርክ ናቸው፡፡

ቤተክርስቲያንን በብዙ ጸጋ ያገለገሉ ብፁዕ ወቅዱስ ፖፕ ሺኖዳ ሣልሳዊ በተወለዱ በ88 ዓመታቸው መጋቢት 8 ቀን 2004 ዓ.ም በዕለተ ቅዳሜ አርፈው #በሚወዱት #በአባ_ብሾይ ገዳምም ተቀብረዋል፡፡ እረፍታቸውን ተከትሎ የዓለም የመረጃ መረቦች ስለበጎነታቸውና ሥራቸው ብዙ ዘግበዋል፡፡ ቢቢሲ ከካንሰር ጋር እንደኖሩ መረጃ ሰጥቷል፡፡ የቅርብ አማካሪያቸው አና አዚዝ ደግሞ “የሰነበተ ሕመም አባታችንን ነጠቀን” በማለት ገልጧል፡፡ ከግብጻውያን አስተያየት ሰጪዎች አንዱ “የክርስቲያኑ የሙስሊሙም የቅርብ ወዳጅ ስለነበሩ ሐዘኑ የጋራችን ነው” ሲል ፍቅራቸውን በእንባ ገልጧል፡፡

የአባታችን በረከት አይለየን

/በፍኖተ ሕይወት ሰ.ት.ቤት ሚድያና ሕዝብ ግንኙነት ዋና ማስተባበሪያ ክፍል የተዘጋጀ።/

• Facebook 👉 የቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኀኔዓለምና ደብረ ትጉሃን ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ሕይወት ሰንበት ትምህርት ቤት
• Telegram 👉 t.me/finotehiwott

• Tiktok 👉 tiktok.com/@finotehiwot
• YouTube 👉 m.youtube.com/@finotehiwot1958
👍14🙏127🥰2