Finote Hiwot የቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኀኔ ዓለምና ደብረ ትጉሃን ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ሕይወት ሰንበት ትምህርት ቤት
15.3K subscribers
14.7K photos
78 videos
156 files
1.71K links
የቀጨኔ መድኃኔዓለም ፍኖተ ሕይወት ሰንበት ትምህርት ቤት ነሐሴ 26/ 1958 ዓ.ም ተመሠረተ።
Download Telegram
እንኳን ለእመቤታችን ኪዳነ ምሕረት ዓመታዊ ክብረ በዓል (ቃል ኪዳን ለተቀበለችበት) በሰላምና በጤና አደረሳችሁ፡፡
ሶበሰ ኪዳንኪ ምክንያተ ድኂን ኢሀሎ፤
ፈለገ እሳት ወደይን እምአስጠመ ኵሎ፡፡
(ድንግል ሆይ ቃል ኪዳንሽ ባይኖር ኖሮ የሲኦል እሳት ባሰጠመን ነበር፡፡)
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሲዖልን ካየች በኋላ ስለኃጥአን እጅግ እያዘነች ኖረች የካቲት አሥራ ስድስት ቀንም በጎልጎታ ቦታ ቆማ ወደ ልጇ እንዲህ ብላ ለመነች፡፡

ጸሎትና ልመናዬን ስማኝ ቃሌንም አድምጥ እኔ እናትህ አገልጋይህ የምለምንህን ይህ ነው፡፡ መታሰቢያዬን ለሚያደርጉ፣ አብያተ ክርስቲያኔን ለሚሠሩ፣ ወይም ለታረዙ ለሚያለብሱ፣ ለተራቡ ለሚያጠግቡ፣ የተጠማውንም የሚያጠጡ(በስሜ ለድሆችና ለችግረኞች ቀዝቃዛ ውኃ ለሚሰጡ) ፣ የታመመውንም የሚጎበኝ፣ ያዘነውንም የሚያረጋጉ፣ የተከዘውንም ደስ የሚያሰኙ ወይም ምስጋናዬን ለሚጽፉ፣ ልጆቹንም በስሜ ለሚሰይም፣ በበዓሌም ቀን በማኅሌት ለሚያመሰግን አቤቱ በዓይን ያልታየውን በጆሮ ያልተሰማውን በጎ ዋጋ ስጣቸው፡፡ በአማላጅነቴም የሚተማመኑትን ሁሉ ከሲዖል ነፃ አድርጋቸው ከአንተ ጋር የደረሰብኝን ረሃብና ጥማቱን መከራውን ሁሉ አስብ አለችው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እንዳልሽው ይሁንልሽ የሰጠሁሽን ቃልኪዳን እንዳይታበይ በራሴ በባሕርይ አባቴ በአብ በባሕርይ ሕይወቴ በመንፈስ ቅዱስ ማልኩልሽ ብሎ ቃል ኪዳን ሰጣት፡፡

#ሥርዐተ_ማኅሌት_ዘየካቲት_16#በዓለ_ኪዳነ_ምሕረት፡፡
በሃገራችን በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት የሚቆመው፤ የ3ት ዐበይት አድባራት አብነት ነው፡፡ እነዚህም፤
1ኛ) የላይ ቤት፤ የደብረ መድኀኒት ዐቢየ እግዚእ ኪዳነ ምሕረት
2ኛ) የታች ቤት አብነት፤ የደብረ ኃይል ወደብረ ጥበብ በዓታ
3ኛ) የደፈጫ ኪዳነ ምሕረት አብነት ናቸው፡፡
እኛም ከላይ ከተጠቀሱት ውስጥ የዐቢየ እግዚእንና የበዓታን ይትበሃል አንድ ላይ በቅደም ተከተል አድረገን አዘጋጅተንላችኋል፤ የደፈጫ ከላይ ከተጠቀሱት ከ2ቱ በጥቂት ቀለም ብቻ የሚለይ በመኾኑ አላካተትነውም፡፡ ስለዚህ እንደ የደብራችሁ ይተበሃል የላይ ቤት ከኾነ ‹‹ዘዐቢየ እግዚእ›› የሚለውን፤ የታች ቤት ከኾነ ‹‹ዘበዓታ) የሚለውን እንድትጠቀሙ እናሳስባልን፡፡
መልካም ማኅሌት፡፡

/በፍኖተ ሕይወት ሰ.ት.ቤት ሚድያና ሕዝብ ግንኙነት ዋና ማስተባበሪያ ክፍል የተዘጋጀ።/

• Facebook 👉 m.facebook.com/FinoteHiwotSundaySchool
• Telegram 👉 t.me/finotehiwott

• Tiktok 👉 tiktok.com/@finotehiwot 
• YouTube 👉 m.youtube.com/@finotehiwot1958
👍85
እንኳን ለዐቢይ ጾም አደረሳችሁ!
ጾሙ የካቲት 17 ይገባል

#የዐቢይ_ጾም_ሳምንታት_ስያሜዎች

፩ኛ)የመጀመሪያው እሑድ(ሳምንት)፥ #ዘወረደ (ሙሴኒ፣ ጾመ ሕርቃል) ይባላል፡፡ አምላክ ከሰማይ መውረዱን፣ ሰው መሆኑንና ነገረ መስቀሉን ስለሚያወሳ ነው፡፡
፪ኛ. የሁለተኛው እሑድ፥ #ቅድስት ይባላል፤ ስለ ዕለተ ሰንበት ቅድስና ስለሚያወሳ ነው
፫ኛ. የሦስተኛው እሑድ፥ #ምኲራብ ይባላል፤ በዚህ ሰንበት ጌታ በመዋዕለ ትምህርቱ በምኲራብ ገብቶ ማስተማሩ ይነገራል፡፡
፬ኛ. ዐራተኛው እሑድ፥ #መፃጉዕ ይባላል፤ ድውያንን መፈወሱን፣ ዕውራንን ማብራቱን፣ የሚያነሣ መዝሙር ይዘመርበታል፡፡
፭. አምስተኛው እሑድ፥  #ደብረ_ዘይት ይባላል፡፡ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሁኖ ያስተማረው ትምህርት፥ የዳግም ምጽአትን ነገር የሚያስታውስ መዝሙር ይዘመርበታል፡፡
፮. ስድስተኛው እሑድ፥ #ገብርኄር ይባላል፡፡ የጌታውን ብር ተቀብሎ ያተረፈበት፣ በጌታውም ፊት ምስጋናን ያገኘው ሰው ታሪክ ይዘመርበታል፡፡
፯. ሰባተኛው እሑድ፥ #ኒቆዲሞስ ይባላል፡፡ በሌሊት ወደ ጌታ እየመጣ ይማር የነበረውን የኒቆዲሞስን ታሪክ የሚያስታውስ መዝሙር ይዘመርበታል፡፡
፰. ስምንተኛው እሑድ፥ #ሆሣዕና ነው፡፡ ጌታ በአሕያ ውርንጭላ ሆኖ ሆሣዕና በአርያም እየተባለ ወደ ቤተ መቅደስ የገባበት ዕለት መታሰቢያ ነው፡፡
፨ ከሠርክ ሆሣዕና እስከ ትንሣኤ ያለው ሰባት ቀን #ሕማማት ይባላል:- የጌታን መከራና ስቃይ እንዲሁም ሞት የምናስታውስበት ሳምንት ነው ፡፡

#የዐቢይ_ጾም_ሌሎች_መጠሪያ_ስያሜዎች
፩. ዐቢይ ጾም ይባላል፤
፪. ጾመ ሁዳዴ ይባላል፤
፫. የካሣ ጾም ይባላል፤
፬. የድል ጾም ይባላል፤
፭. የመሸጋገሪያ ጾም ይባላል፤
፮. ጾመ አስተምህሮ ይባላል፤
፯. የቀድሶተ ገዳም ጾም፤
፰. የመዘጋጃ ጾም ይባላል፤
፱. የሥራ መጀመሪያ ጾም፤
፲. ጾመ አርብዓ ይባላል፡፡

/በፍኖተ ሕይወት ሰ.ት.ቤት ሚድያና ሕዝብ ግንኙነት ዋና ማስተባበሪያ ክፍል የተዘጋጀ።/

• Facebook 👉 m.facebook.com/FinoteHiwotSundaySchool
• Telegram 👉 t.me/finotehiwott

• Tiktok 👉 tiktok.com/@finotehiwot 
• YouTube 👉 m.youtube.com/@finotehiwot1958
👍11🥱1
#ዘወረደ_ወይም_ሕርቃል_ወይም_ሙሴኒ
    ጾም ማለት፤
፨ ከእህልና ከውኃ እንዲሁም ከሥጋ ፈቃድ ጾሙ እስኪፈጸም ድረስ መተው ማለት ነው።
፨ ጾም ማለት በጾም ወቅት ሥጋ ነክ ምግቦችንም ሆነ ወተትን፤ ቅቤን የመሳሰሉትን የምግብ እና የመጠጥ ዓይነቶችን ጥሉላትነት በሌላቸው ምግቦች መለወጥ ብቻ ሳይሆን የምንወደውን የሥጋ ፍላጎት ስለ እግዚአብሔር ብለን መተው ማለት ነው። ራስን መግዛት በክርስቲያናዊ ሕይወት ውስጥ ትልቅ ዋጋ እንዳለው ሁሉ አንድ ሰው የሥጋ ፍላጎቱን ወይም የዓለም ምኞቱን ትቶ እግዚአብሔርን እያሰበ የሚጾም ከሆነ በፈጣሪው ዘንድ ጾሙ ተቀባይነት አለው።
፨ ጾም ለእግዚአብሔር ያለንን ታዛዥነት የምንገልጽበት የፍቅር መገለጫ ነው፡፡ ስለዚህ ይህን ዐቢይ ጾም ስንጾምም፤
ዐይናችን ትጹም (ክፉ ከማየት)፤
ጆሮም ትጹም (ክፉ ከመስማት ወይም ሰውን ከማማት እንታቀብ)፤
አፋችን ትጹም (ከመሳደብ ሆነ ክፉ ከማውራት)፤
እጅም ትጹም (ከመስረቅም ሆነ ሰውን ከመደብደብ)፤
አግርም ትጹም (ወደ ኀጢአት ቦታዎች ከመሄድ ምሳሌ ከጭፈራ ወይም ዳንኪራ ቤቶች)፤
….. ሁላችንም በተሰበረ ልብ ሆነን እንጹም።
ዐቢይ ጾም ማለት ታላቅ ጾም ማለት ነው። ታላቅ ጾም የተሰኘበት ምክንያት ለ55 ቀናት መጾሙና ከሌሎች አጽዋማት ጋር ሲነጻጸር በቊጥር መብለጡ ብቻ ሳይሆን ፍጥረታትን የፈጠረ አምላክ፤ ስለ ሰው ልጅ ፍቅር ሲል ከዙፋኑ ወርዶ ከእመቤታችን ተወልዶ፤ መጾም ሳይገባው ለእኛ አርአያ ለመሆን ሲል በገዳመ ቆሮንጦስ የጾመው ጾም ነው።
የዐቢይ ጾም  የመጀመሪያው ሳምንት ዘወረደ ወይም ጾመ ሕርቃል በተጨማሪም ሙሴኒ በመባል ይታወቃል፤ ለምን እንደተባለ በዝርዝር ስንመከለከታቸው፤
፩ኛ. #ዘወረደ_ይባላል
‹‹ዘወረደ እምላዕሉ አይሁድ ሰቀሉ፤
ወሚመ ኢያእመሩ፤
እግዚአ ኵሉ ዘየሐዩ በቃሉ፡፡››
‹‹ዘወረደ እምላዕሉ እመልዕልተ ኵሉ››፡፡
«ዘወረደ» ማለትም በቀጥታ፣ ቃል በቃል ሲተረጐም «የወረደ» ማለት ነው፡፡ ይህም በምሥጢሩ አምላክ፥ ወልደ አምላክ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቤዛ ዓለም፥ እኛን  ለማዳንና ፍቅሩን ሊገልጽልን፤ በፈቃዱ ሰው ሆኖ ከሰማየ ሰማያት ከባሕርይ ልዕልናው በትሕትና መውረዱን፥ ከድንግል ማርያም መወለዱን፥ የእኛን ሥጋ መዋሐዱን የሚያዘክር ምስጋና የሚቀርብበት ሳምንት ነው፡፡ ይህ እንዲታወስበት፣ እንዲወሳበት የዐቢይ ጾም የመጀመሪያውን ሳምንትን ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓው ላይ ‹‹ዘወረደ›› ብሎ ሰይሞታል፡፡ /ዮሐ.3፥13፣ ጾመ ድጓ፡፡/
      ፪ኛ. #ጾመ_ሕርቃል_ይባላል፡፡
የዐቢይ ጾም የመጀመሪያ ሳምንት ሌላ መጠሪያ ስሙ ‹‹ጾመ ሕርቃል›› ነው፡፡ ሕርቃል ማን ነው? ለምንስ በስሙ ተሰየመ? በ614 ዓ.ም. ኪርዮስ የተባለ የፋርስ ንጉሥ ኢየሩሳሌምን በመውረር ጥቃት አደረሰ፡፡ በዚህ ወቅት በኢየሩሳሌም ንግሥት ዕሌኒ በሠራችው ቤተመቅደስ ውስጥ ንግሥቲቷ በክብር አስቀምጣው የነበረው የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል እንደ ፀሐይ ሲያበራ አገኘው፡፡ ቢነካው አቃጠለው ካህናትን አሸክሞ፥ ሌላውን ንዋያተ ቅድሳት ዘርፎ፥ 60ሺ የሚደርሱትን አቁስሎ ገድሎ፥ 3ሺ የሚሆኑትን ማርኮ፥ ከተማዋንም አቃጥሎ ወደ ፋርስ ባቢሎን ይመለሳል፡፡ በዚህ ጊዜ ከጦርነቱ ያመለጡ በየዋሻው በየጉራንጉሩ ገብተው የተሸሸጉ ተሰብስበው ከ14 ዓመት በኋላ በ628 ጩኸታቸውንና የደረሰባቸውን በደል ለክርስቲያኑ የሮም ንጉሥ ሕርቃል ይነግሩታል፤ እርሱም ሐዋርያት ሰውን የገደለ እድሜውን በሙሉ ይጹም ስላሉ እንዴት ላድርግ? አላቸው; እኛ የአንተን እድሜ ተከፋፍለን እንጾማለን ብለው አንድ አንድ ሳምንት ደርሷቸው ጾሙን ፩ ሱባኤ ጾመውታል፡፡ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀልና የተማረኩ ክርስቲያኖችን ለመመለስ ሕርቃል ጦር መዝዞ በኪርዮስ ላይ ተነሳበት ድል ለሕርቃል ሆነና መስቀሉ ያለበትን አጥቶ ሲቸገር ኪርዮስ መስቀሉን ሲቀብርና ዲያቆናቱን ሲያስገድል በመስኮት ሆና ያየችው ከኢየሩሳሌም የተማረከች አንዲት ብላቴና አሳይታው አውጥቶ በልብሰ መንግሥቱ ጠቅልሎ ወደ ቊስጥንጥንያ ተመለሰ፤ የተማረኩት በሙሉ ነጻ ወጡ፤ ይህንን ለማሰብ፥ ለማስታወስ የምንጾመው ሲሆን፤ ዛሬም እኛ በመስቀልህ ከምርኮ እንደተመለሰ እኛንም ከኃጢአት ምርኮ መልሰን እያልን፥ ለሕርቃል በጠላቶቹ ላይ ድል መንሳትንና በጠላቶቹ ላይ ኃይልን እንደሰጠኸው ለእኛም በኃጢአት ላይ ድል መንሳትን፥ መንፈሳዊ ኃይልን እንዲበዛልን እንጾመዋለን፡፡ በጌታ ጾም ላይ እንዲጾም የሆነበት ምክንያት ጾሙ የጌታ ጾም በሚጾምበት ወቅት ላይ ስለተጾመ ቤተክርስቲያናችን አብራ ደንግጋዋለች፡፡ የእኛ ጠላት የጨለማ ገዥ የሆነው ዲያቢሎስ ነውና እሱን ደግሞ በጾም እንደምናሸንፈው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሮናል፡፡
   ፫ኛ. #ሙሴኒ
የመጀመሪያው ሳምንት ሙሴኒ የተባለበት ምክንያትም፤ በዚሁ ሳምንት መጀመሪያ የሰኞ ዕዝል «ከመዝ ይቤ ሙሴ ፀዓቱ እምትእይንት (ሙሴ ከከተማ መውጣቱ እንደዚህ ነው አለ») ስለሚል እንደዚሁም የዚሁ ዕለት ማለት የሰኞ አቡን «ሙሴኒ ይቤ በውስተ ኦሪት ምድር ሰናይት» እያለ የሙሴን ታሪክ ስለሚጠቃቅስ ሳምንቱ ሙሴኒ ተባለ፡፡ ነቢያትም አርባ አርባ ቀን ጾመው ካለፉ በኋላ የሙሴ ሕግና ትንቢተ ነቢያት ፈጻሚ የሆነው አምላካችን እንደ እነሱ 40 ቀንና 40 ሌሊት መጾሙን  የሚያስታውስ ነው፡፡  /ዘፀ.24፥18፤  1ኛ.ነገ.19፥8፤  ማቴ.4፥1-4/፡፡

/በፍኖተ ሕይወት ሰ.ት.ቤት ሚድያና ሕዝብ ግንኙነት ዋና ማስተባበሪያ ክፍል የተዘጋጀ።/

• Facebook 👉 m.facebook.com/FinoteHiwotSundaySchool
• Telegram 👉 t.me/finotehiwott

• Tiktok 👉 tiktok.com/@finotehiwot 
• YouTube 👉 m.youtube.com/@finotehiwot1958
👍53🙏2
"የቃል ኪዳኗ እመቤት ሆይ! ለጽድቅ የሚያበቃ በጐ ምግባር ባይኖረኝም እንኳ የገሃነምን ደጅ እንዳታሳዪኝ እማልድሻለሁ፤ ቃል ኪዳንሽ እንዲሁ በከንቱ አይደለምና፡፡"

http://t.me/finotehiwott
🥰227👍4🙏1
/በፍኖተ ሕይወት ሰ.ት.ቤት ሚድያና ሕዝብ ግንኙነት ዋና ማስተባበሪያ ክፍል የተዘጋጀ።/

• Facebook 👉 m.facebook.com/FinoteHiwotSundaySchool
• Telegram 👉 t.me/finotehiwott

• Tiktok 👉 tiktok.com/@finotehiwot 
• YouTube 👉 m.youtube.com/@finotehiwot1958
8👍4
ከ1878-1888ዓ.ም. ከዓድዋ በፊት የነበሩ 8ቱ አድዋዎችና የዓድዋ ሶሎዳ ውጊያ፤

1ኛ) ራስ አሉላ ነጋ (የዐፄ ዮሐንስ ጦር አበጋዝና የሐማሴን ባላባት)፤ #ዶጋሊ ላይ ጠላትን ድባቅ በመምታት ወደ ምጽዋ የመለሰበት፡፡

2ኛ) ደጃች ደበብ፤ #ሰገነይቲ ላይ የተደረገ ውጊያ

3ኛ) ደጃች ባሕታ ሀጐስና ወንድማቸው አዝማች ሰንጋል፤ ከጄነራል ሳጎናይቲና ከተከታዩ ታንቲ ጋር ያደረጉት ውጊያ፡፡ ቀጥሎም ደጃች ባሕታና ዘመዳቸው ባሻይ ምስጉን የተሰዉበት #የሐላይ መንደር ውጊያ፡፡

4ኛ) ራስ መንገሻ ዮሐንስ #በኰዓቲት ከጥር 13 -15 የተዋጉበት፤ ጦርነቱ የተራዘመና በርካታ ኢትዮጵያውያን የተሰዉበት፤ የሟች ቊጥር በመበርከቱ አሸናፊና ተሸናፊው ሳይለይ፤ የራስ መንገሻ ጦር ወደ ሰነዓፌ የተበተነበት፡፡

5ኛ) የራስ መንገሻ ዮሐንስ የጦር አዝማቾች (እነ ተስፋይ ህንጣሎ አጋሜ፥ ወልደ ማርያም፥ ቀኛዝማች ኃይለማርያም ወምበርታ፥ ቀኛዝማች አብርሃ፥ ደጃች ረዳ አባ ጉብራ /የራስ አርአያ ልጅ/) መሪያችንን ራስ መንገሻን አናስነካም ብለው #በደብረ_አላ ላይ የተዋጉት ውጊያ፡፡

6ኛ) ልዑል ራስ መኰንን (የኢትዮጵያ ጠቅላይ ጦር አዛዥና የሐረርጌ ገዥ /የአፄ ኃይለ ሥላሴ አባት/)፤ #አምባ_አላጌ ላይ ጣሊያንን እንደ ንብ ወረው ትልቅ ጀብድ የሠሩበትና ለአድዋውም ወኔ ቀስቃሽ ውጊያ፡፡

7ኛ) ልዑል ራስ መኰንን፤ መቀሌ #እንዳ_ኢየሱስ (ዛሬ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ኢንጂነሪንግ ግቢ የሚገኝበት) ላይ፤ ቀድሞ በቦታው ላይ ጠላት ሸምቆ ስለበረ ዙሪያውን ከበው ስንቅ በማሳጣት መሪው ማጆር ጋሊያኖ ማሩኝ ለጄነራሌ ለባራታሪ ሂጄ ዕርቅ ይሆናል አስማማለሁ፤ ብሎ በዕርቅ ያለቀበት፡፡ (ኋላ ግን ማጆር ጋሊያኖ ቃሉን በማጠፉና ጣሊያንን ለጦርነት በማነሳሳቱ የአድዋ ጦር ሁኗል፡፡)

8ኛ) ራስ ስብሐትና ደጃች ሐጐስ ተፈሪ (ቀድሞ ባንዳ ነበሩ) ማጆር ጋሊያኖ ለጄነራሉ ከማስማማት ይልቅ ጠብን በመምከሩና የጣሊያን ጦር በእንትጮ በኩል ከኢትዮጵያ ጋራ ሊዋጋ ሲገሰግስ የአካለ ጉዛይን ባላሃገር በማስተባበር #እንትጮ ላይ ደጀን ሁነው መክተው የተዋጉት ውጊያ፡፡

9ኛ)  #አድዋ #ሶሎዳ፡፡
ዓድዋ የሚለውን ስም የሠየሙት ከተሰዐቱ ቅዱሳን በገቢረ ተአምራታቸው ገሪማ ገረምከኒ የተባለላቸው አባ ገሪማ ሲኾኑ፤ ዓድዋ ብዙ ተራሮችን የያዘች ሃገር ስትሆን፤ ከጣሊያን ጋር የመጨረሻው ፍልሚያ የተደረገው ከዓድዋ ተራሮች በግዙፉ #ሶሎዳ ተራራ ላይ ነው፡፡

"የኢጣሊያና የኢትዮጵያ ጦርነት መነሻ"
ለአድዋ ጦርነት መነሻው፤ የአውሮፓ ኃያላን ሃገር ነን ብለው ራሳቸውን የሰየሙ አፍሪካን ሊቀራመቱ በተስማሙት መሠረት ጣሊያን ከሚስዮኖቿ አንዱና ተኩላ በሆነው አባ ማስያስ ሰላይነት ያጠኗትን ኢትዮጵያን ልትቀራመት መወሰኗ፡፡
መጀመሪያ በ1861ዓ.ም. እግሯን ወደ ኢትዮጵያ በአሰብ በኩል አስገባች፤ በ17ዓመታት ቆይታ(እስከ 1878ዓ.ም.) ምጽዋን፣ የዳህላክ ደሴቶችንና የኤርትራን ቀይ ባሕር ያዘች፡፡ ምጽዋን በያዘች በ3ት ዓመታት ኤርትራን ያዘች፤ ኤርትራን በያዘች በ7 ዓመት መረብን ተሻግራ ወደ ሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች በመግባት ጦርነት ከፈተች፡፡ ራስ አሉላ አባነጋም ድባቅ መትቶ መለሳቸው፡፡

ይህ አልሆን ሲላቸው በተወካያቸው በአንቶኔሊ በሚያዝያ 25/1881ዓ.ም. በውጫሌ (ወሎ ቦሩ ሜዳ የምትገኝ) ላይ የተፈረመውን የውል ስምምንት አንቀጽ 17 በአማርኛና በጣሊያንኛ ቅጂው የተሳሰተ  (የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ከውጭ ሃገራት ጋር የሚያደርገውንግንኙነት በኢጣልያ በኩል ማድረግ ይገባዋል!!፡፡›› በሚል ሰበብ ሌሎች ጠርነቶች ተቀሰቀሱ፡፡

/በፍኖተ ሕይወት ሰ.ት.ቤት ሚድያና ሕዝብ ግንኙነት ዋና ማስተባበሪያ ክፍል የተዘጋጀ።/

• Facebook 👉 m.facebook.com/FinoteHiwotSundaySchool
• Telegram 👉 t.me/finotehiwott

• Tiktok 👉 tiktok.com/@finotehiwot 
• YouTube 👉 m.youtube.com/@finotehiwot1958
👍11🙏21