Finote Hiwot የቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኀኔ ዓለምና ደብረ ትጉሃን ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ሕይወት ሰንበት ትምህርት ቤት
15.3K subscribers
14.7K photos
78 videos
156 files
1.71K links
የቀጨኔ መድኃኔዓለም ፍኖተ ሕይወት ሰንበት ትምህርት ቤት ነሐሴ 26/ 1958 ዓ.ም ተመሠረተ።
Download Telegram
ጾመ ነነዌ፤ ከየካቲት 5-7 (ከሰኞ-ረቡዕ)

#ነነዌ
በጤግሮስ ወንዝ ምሥራቃዊ ቆሬ፥ ከዛሬዋ የሞሱል ከተማ በተቃራኒ ከባግዳድ በሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ 350 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የነበረች ታላቅ ከተማ ነች፡፡
ነነዌን በመጀመሪያ የቆረቆራት ናምሩድ ነው፡፡ /ዘፍ. 10፥11/
በጣም ሰፊ ነበረች “የቅጥሯም ዙሪያ በእግር የሦስት ቀን መንገድ ያህል ነበረ” /ዮና. 3፥3/
እግዚአብሔር አምላካችን ነነዌን “ታላቂቱ ከተማ” በሚል ቅጽል ጠርቷል፤ /ዮናስ 3፥2፤ 4፥11/
ስለ መጥፋቷ ነቢዩ ሶፎንያስ “...ነነዌንም ባድማ እንደ በረሃም ደረቅ ያደርጋታል” በማለት ትንቢት ተናግሮባታል፡፡ /ትን. ሶፎ 2፥13/፡፡ እንደ ነቢያቱ ትንቢት ታላቋ ነነዌ ከ300 ዓመታት በኋላ ጠፍታለች፡፡
የነነዌ ሰዎች በስብከተ ዮናስ አምነው፥ ንስሐ ገብተው ድነዋል፤ በዚህም ጌታችን በወንጌል ላይ ስለ ንስሓቸውና ስለ እምነታቸው /‹‹...የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና፡፡›› በማለት አመስግኗቸዋል፡፡ ማቴ 12፥41/

#ዮናስ_ነቢየ_አሕዛብ_ወሕዝብ
ዮናስ ማለት ርግብ፥ የዋኅ ማለት ነው፡፡
በዳግማዊ ኢዮርብአም ዘመነ መንግሥት /825-784 ቅ.ል.ክ./ በሰማርያ የነበረ ነው፡፡ /2ነገሥ. 14፥25/፡፡
ቊጥሩ ከ12ቱ ደቂቀ ነቢያት አንዱ ነው፡፡
ነገዱ ከነገደ ይሳኮር ወገን ሲሆን፤ #አባቱ_አማቴ_እናቱም_ሶና(የሰራፕታዋ ደግ ሴት የሆነችውና ቅዱስ ኤልያስን በዚያ በረሃብ ዘመን የመገበችው ናት)፡፡
ኤልያስ በረሃቡ ዘመን ወደ ሰራፕታዋ መበለት ቤት በመሄድ "ውኃ አጠጪኝ ጥቂት ቁራሽም አምጪልኝ" አላት፡፡ ‹‹ሕያው እግዚአብሔርን እፍኝ ዱቄት አለችኝ ጋግሬያት አንተም እኔም ልጄም (ዮናስ) በልተናት እንሞታለን›› አለችው፡፡ ኤልያስም "የረሀቡ ዘመን እስኪያልፍ ይበርክት" አላት፤ ከቤቷ ብትገባ ዱቄቱ በማድጋው፣ ዘይቱ በማሰሮው መልቶ አገኘች፡፡ ከጥቂት ጊዜም በኋላ ልጇ ዮናስ ታሞ ሞተ፡፡ እናቱም ሄዳ ነቢየ እግዚአብሔር ኤልያስን "ሳይገባኝ ከቤቴ ገብተህ ኀጢአቴን ተመራምረህ ልጄን ትገድልብኝ?" አለችው፡፡ ነቢዩ ኤልያስም ወደ አምላኩ ሰባት ጊዜ ጸሎት አድርሶ ዮናስን ከሞተ በኋላ አስነሥቶታል፡፡
ዮናስ ትንሽ ከፍ ባለ ጊዜም ከነቢያት ጓደኞቹ አብድዩና ኤልሳዕ ጋር ሆነው የታላቁ ነቢይ የኤልያስ ደቀ መዛሙርት ሆኑ፡፡ /1ነገ.17፥1-24፤ 18፥10-24/ ነቢዩ ኤልያስ ካረገ በኋላ ደግሞ ሁሉም በተሰጣቸው አገልግሎት ተሠማርተው እግዚአቤሔርን አገለገሉ፡፡ ነቢዩ ዮናስ አርባ ዓመት ሲሞላው ሀብተ ትንቢት ተሰጥቶት ማስተማር ጀመረ፡፡
የሰማርያውን ንጉሥ ኢዮርብአምን ጠቃሚ ምክር በመለገስ የእሥራኤልን ድንበር ከሔማት እስከ ዐረብ ባሕር ድረስ እንዲይዝ አድርጎታል፡፡ /2ነገሥ. 14፥25/፡፡
ነቢዩ ዮናስ ምንም እንኳን የእስራኤል ነቢይ ቢኾንም ከምድረ እስራኤል ውጪ በነነዌ ስላስተማረ #ነቢየ አሕዛብ ወሕዝብ ይባላል፡፡ የትንቢት መጽሐፉም ዋና መልእክት እግዚአብሔር የእስራኤል ብቻ ሳይሆን የአሕዛብም አምላክ እንደሆነና በንስሐ ወደ እርሱ የተመለሱትን ሁሉ በምሕረት እንደሚጐበኝ ማሳየት ነው፡፡

#ዮናስና_ነነዌ_
የነነዌ ሰዎች ኀጢአት ከመሥፈርቱ በማለፉ፤ የእግዚአብሔር ቃል ወደ አማቴ ልጅ ወደ ዮናስ መጣ “ተነሥተህ ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፤ የክፋታቸውም ጩኸት ወደ ፊቴ ወጥቷልና ለእነርሱ ስበክ” አለው፤ ዮናስ ግን የፈጣሪው መሐሪነት፥ ቸርነት መስፈርት እንደሌለው ያውቃልና፤ እርሱ ቢምራቸው ማን ለቃሉና ለትንቢቱ ይገዛል፤ እኔም ሐሰተኛ ነቢይ ልባል አይደለምን? ብሎ አልሔድም አለ፤ እግዚአብሔር እየደጋገመ ሲናገረው ግን ዮናስ የዋሕ ነበረና እንዲህ የሚዘበዝበኝ ከፊቱ ብቀመጥ አይደል ብሎ ከፊቱ ለመሰወር ወደ ተርሴስ በመርከብ ኮበለለ፡፡
ዮናስ ወደ መርከብ ገብቶ ጕዞ ከተጀመረ በኋላ በእርሱ ምክንያት ታላቅ ማዕበል ተነሳ፤ በመርከቡ ውስጥ የተሣፈሩትም ሊያልቁ ሆነ፤ ሌሎች እንዲያ እየተናወጡ እርሱ ግን የእምነት ሰው፥ የዋሕና ቅን ስለሆነ ተረጋግቶ በመርከቡ ውስጥ ተኝቶ ነበር፡፡ መርከበኞቹም እጅግ ሲጨንቃቸው እያንዳንዳቸው ወደ አምላካቸው ጮሁ፤ መርከቢቱም እንድትቀልላቸው በውስጧ የነበረውን ዕቃ ሁሉ እያወጡ ወደ ባሕር ጣሉ፡፡ ባሕሩ ጸጥ ሊል ስላልቻለ ዮናስንም ቀስቅሰው “ይህ ክፉ ነገር በማን ምክንያት እንዳገኘን እናውቅ ዘንድ፤ ኑ ዕጣ እንጣጣል ተባባሉ፡፡” /ዮናስ 1፥7/፡፡ እጣ ቢጥሉ በዮናስ ላይ ወጣ፤ ዮናስም በራሱ ተጠያቂነት፤ ‹‹የእኔ ጥፋት ስለ ሆነ ወደ ማዕበሉ ጣሉኝ›› አላቸው፡፡ መርከበኞች ግን ዮናስን ለመታደግ የሚችሉትን ሁሉ አደረጉ፡፡ መርከቢቱ ወደ ምድር ትጠጋላቸው ዘንድ አብዝተው ቀዘፉ፤ የእርሱ ወደ ባሕር መጣል ፈቃደ እግዚአብሔር ስለሆነ ልፋታቸው ሁሉ ከንቱ ሆነ፡፡ ሁሉም አንድ ሆነው ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፡፡ “አቤቱ! አንተ እንደ ወደድህ አድርገሃልና ስለዚህ ሰው ነፍስ አታጥፋን፤ ንጹሕ ደምንም አታድርግብን፡፡” በማለት እያዘኑ በሐምሌ 15 ቀን ወደ ባሕሩ ጣሉት፤ ባሕሩም ከመናወጥ ጸጥ አለ፡፡
ነቢዩ ወደ ባሕር ቢጣልም የእግዚአብሔር ጥበቃ አልተለየውምና ዮናስን ይውጠው ዘንድ ታላቅ ዓሣ አንበሪን አዘዘለት፡፡ ነቢዩ ዳዊት ‹‹እግዚአብሔር የቀባውን እንዳዳነው ዛሬ ዐወቅሁ›› እንዳለ /መዝ. 19፥6/ የመረጠውን ነቢይ ለማዳን ዓሣ አንበሪን አዘጋጀለት፡፡
*ዮናስም በአሣ አንበሪ ሆድና በማዕበል ውስጥ ሆኖ ለ3 ቀናት ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ በመጽሐፍ ቅዱስም በዓሣ ሆድ ተጕዞ ያስተማረ፥ ትንቢትም የተናገረ የመጀመሪያ ነቢይ ሆነ፡፡ ዓሣ አንበሪው ዮናስን በሆዱ ቋጥሮ የሦስት ቀን ጎዳና በባሕር ውስጥ ገስግሶ በ3ኛው ቀን ነነዌ ዳር ደረቅ መሬት ላይ አራግፎ ተፋው፡፡ /ዮናስ 1፥4-16፤ 2፥1-11፣ መዝ. 138፥7-10/፡፡
ዮናስ በግዙፉ አሣ አነበሪ ውስጥም ያለ እንቅልፍ በጾም፥ በጸሎትና በምስጋና ለ3 ቀናት መቆየቱ ለክርስቶስ ትንሣኤ ምሳሌ ነው፤ ዮናስ በአሣ አንበሪ ሆድ 3 ቀን 3 ሌሊት ኑሮ፥ ሙስና (ጥፋት) ሳያገኘው መውጣቱ አዳምና ልጆቹን ለማዳን የመጣው ጌታችንም 3 መዓልትና 3 ሌሊት በከርሠ መቃብር አድሮ ከሙታን ተለይቶ የመነሣቱ ምሳሌ ነው፡፡ ለዚህም ራሱ ጌታችን በወንጌል ‹‹ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል፡፡ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም፡፡ ዮናስ በአሣ አንበሪ ሆድ 3 ቀንና 3 ሌሊት እንደ ነበረ፤ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ 3 ቀንና 3 ሌሊት ይኖራል፡፡ የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፡፡ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና፡፡ እነሆም ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ፡፡›› /ማቴ. 12፥39/
**እግዚአብሔር አምላክም ለሁለተኛ ጊዜ ዮናስን ወደ ነነዌ እንዲሄድ አዘዘው፤ “ተነሥተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፤ የነገርሁህንም የመጀመሪያውን ስብከት ስበክላት” አለው፡፡ ዮናስም እንቀድሞው ሳያንገራግር ወደዚህች ከተማ ገብቶ እንዲህ እያለ ‹‹እስከ ሠሉስ ዕለት ትትገፈታእ ነነዌ ዐባይ ሃገር›› (እስከ ሦስት ቀን ድረስ ነነዌ ትገለበጣለች) ንስሐን ሰበከ፥ አስተማረ፡፡
👍7
የነነዌ ሰዎችም ኃጢአታቸውን አምነው (ከኃጢአቱ የሌሉበትም ቢሆን መከራው ስለማይቀርላቸው) ከመሪ እስከ ተመሪ፤ እንደ አንድ ልብ መካሪ፥ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሁነው፤ ንጉሡም በከተማዋ የጾም አዋጅ አስነግሮ፥ ከዙፋኑ ወርዶ፤ ሕዝቡም ማቅ ለብሰው፥ አመድ ነስንሰው፥ በፍጹም ልባቸው አዝነው አልቅሰው፥ ሕፃናት ከጡት፥ ከብቶችም ከሣር መሠማራት ተከልክለው፥ ያለምግብ በበረት ተዘግተው፤ ጾሙንም በልባዊ ጸጸት፥ ራስን ዝቅ በማድረግና በማዋረድ ንስሓ ገቡ /“የነነዌ ሰዎችም እግዚአብሔርን አመኑ” ዮናስ 3፡5 ‹‹... ለጾም ዐዋጅ ነገሩ፤ ከታላቁም ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ማቅ ለበሱ፡፡ ወሬውም ወደ ነነዌ ንጉሥ ደረሰ፡፡ እርሱም ከዙፋኑ ተነሥቶ መጎናጸፊያውን አወለቀ፤ ማቅም ለበሰ፤ በአመድም ላይ ተቀመጠ...” ዮናስ 3፥5-9፡፡/ እንዳለ ከአምላካችን ምሕረትን አገኙ፡፡
ነቢዩ ዮናስም ይህን አይቶ በየዋሕነቱ ‹‹እንግዲህማ ሊምራቸው ነው፣ እኔም ሐሰተኛ ነቢይ ልባል ነው›› ብሎ እያዘነና ከሕይወት ሞት ይሻላል ነፍሴን ከእኔ ውሰድ እያለ ከከተማ ወጥቶ ዳስ ሠርቶ ተቀመጠ፡፡ እግዚአብሔርም በውኑ ትቆጣ ዘንድ ይገባሃልን አለው፡፡ /ዮናስ. 4፥3-11/ አምላካችን መሐሪ በመሆኑ /አባት ለልጆቹ እንደሚራራ እንዲሁ እግዚአብሔር ለሚፈሩት ይራራል ፍጥረታቸውን እሱ ያውቃልና መዝ. 102፥8-14፡፡ ጥበብ 3፡፡/ ብለዋል፤ አምላካችንም /እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠትን ካወቃችሁ በሰማይ ያለው አባታችሁ ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መልካም ነገርን አይሰጣቸው ብሏል ማቴ. 7፥12/ ቀጥሎም ነቢዩ ዮናስ እንቅልፍ እንቅልፍ ብሎት ተኝቶ ቢነቃ ከራስጌው ቅል በቅላ ፀሐይ ስትከለክልለት አየና እጅግ ደስ አለው፡፡ ሁለተኛም ተኝቶ ቢነሣ ቅሏ ጠውልጋ፥ ደርቃ አገኘና አዘነ፡፡ እግዚአብሔርም ‹‹አንተ ላልተከልካትና ውኃ ላላጠጣሃት ቅል እንዲህ ስታዝን እኔስ በዝናም አብቅዬ፥ በፀሐይ አብስዬ ለምመግባቸው ሕዝቤ አላዝንምን?›› አለው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር የዮናስን ፈቃዱን ይፈጽምለት (ሐሳዊ ነቢይ እንዳይሉት) ለምልክት እንዲሆን በሦስተኛው ቀን እሳት ከሰማይ ወርዶ ከፍ ከፍ ያሉትን ዕፅዋት ጫፍ ጫፋቸውን በልቶ ተመልሷል፡፡
ነቢዩ ቅዱስ ዮናስ በቀሪ ዘመኑ ፈጣሪውን እያገለገለ ኑሮ፤ በመልካም ሽምግልና በ170 ዓመት እድሜም መስከረም 25 አርፏል፡፡ ዮናስ በሕይወት ሥጋ ሣለ ሰማርያንና ነነዌን ብቻ ነበር ያስተማረው፤ ከሞተ በኋላ ግን ዛሬ ዓለምን የሚያስተምር ነቢይ ነው፡፡

ከጾሙ ረድኤት በረከት ይክፈለን፤
/በፍኖተ ሕይወት ሰ.ት.ቤት ሚድያና ሕዝብ ግንኙነት ዋና ማስተባበሪያ ክፍል የተዘጋጀ።/

• Facebook 👉 m.facebook.com/FinoteHiwotSundaySchool
• Telegram 👉 t.me/finotehiwott

• Tiktok 👉 tiktok.com/@finotehiwot
• YouTube 👉 m.youtube.com/@finotehiwot1958
👍6👏1🤝1
"ይእዜ ትስዕሮ ለገብርከ በሰላም እግዚኦ በከመ አዘዝከ ፡-አቤቱ ባሪያህን እንደ ቃልህ በሰላም አሰናብተው" ስምዖን አረጋዊ

#የካቲት_8  ፤ የጌታችን  ከከበርች ልደት በኋላ  ወደ ቤተመቅደስ የገባበት ዕለት ኾነ ፡፡ በዓሉ ከጌታችን ንዑስ በዓሎች መኻከል አንዱ ነው ፡፡
++++
የካቲት 8 ፤ ልደተ ስምዖን አረጋዊው  ፣ ካህን ፣ ጻድቅ ፣ ነቢይ ፡፡

+ በዓሉ የመድኀኔዓለም ቢሆንም ስምዖን አረጋዊ አማናዊ ድኅነት አግኝቶበታልና ፣  በእርጅና ምክንያት ከአልጋ ላይ ተጣብቆ ሲኖር ታድሶበታልና እንደ 30 ዓመት ጎልማሳም ዘሏልና  በዓሉ ይከብራል ። ስምዖን ብቻ ሳይሆን የሰው ልጅ ሁሉ የድኅነት ባለቤት ኾኖበታልና በዓሉ ይከብራል ።

++++

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከድንግል ማርያም በተወለደ በ40 ቀኑ የኦሪትን ሕግ ለመፈጸም ወደ ቤተ መቅደስ ገባ ። ይህም ሕግን ሊፈጽም እንጂ ሊያፈርስ አለመምጣቱን በቃልም ፣ በግብርም የገለጠበት በዓል መኾኑን ያስረዳናል። ሥርዓቱን ለመፈጸም እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያምና አረጋዊው ቅዱስ ዮሴፍ ጌታቸውን ይዘው፣ የርግብ ግልገሎችና ዋኖስ ጨምረው ወደ ቤተ መቅደስ ሔዱ ።

++++

የስምዖን አረጋዊ ነገርም እንዲኽ ነው ..
ዓለም በተፈጠረ በ5,200 ዓመታት በጥሊሞስ የተባለ ንጉሥ በግሪክ ነግሦ ነበር። ዓለሙን እንደ ሰም አቅልጦ፣ እንደ ገል ቀጥቅጦ የገዛው መሆኑን ገልጦ፣ የቀረው ነገር አለመኖሩን ሲናገር ባለሟሎቹ በእሥራኤል ጥበብ የመላባቸው 46 መጻሕፍት ስላሉ እነርሱን አላስተረጎምክም አሉት። እስራኤልን አስገብሮ ስለነበር 46ቱን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ከ72 የአይሁድ ሊቃውንት ጋር አስመጣ። አይሁድ ተንኮለኛ መኾናቸውን ስለሚያውቅ 36 ድንኳን እንዲዘጋጅ አድርጎ ኹለት ኹለቱን መድቦ፣ የየድንኳኑን ሊቃውንት የሚቆጣጠሯቸው አንዳንድ ጠባቂዎች ጨምሮ  እንዲተረጕሙ አዘዛቸው።

በዚህ ምክንያት በ284 ዓመት ከክርስቶስ ልደት በፊት 46ቱ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ከዕብራይስጥ ወደ ልሳነ ጽርዕ (ግሪክ) በ70ው ሊቃናት ተተረጐሙ። ከ70 ሊቃናት በመኻከል አንዱ የነበረው #ስምዖን ምሁረ ኦሪት ነበር። ይተረጕም ዘንድ መጽሐፈ ኢሳይያስ ደረሰው። ታዲያ ይህ ሊቅ የትንቢቱን መጽሐፍ እየተረጎመ ሳለ ምዕራፍ ፯ ላይ ሲደርስ የሕይወቱን አቅጣጫ ወደ ዘላለማዊ በረከት የሚያሳድግ ልዩ ገጸ ንባብ ገጠመው ።  እርሱም
“ ስለዚኽ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነኾ ፥ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች።” ኢሳ 7፥14 የሚል ነበር።
ስምዖንም "እንዴት ድንግል ትፀንሳለች?" ብሎ "ድንግል" የሚለውን "ሴት" ብሎ ቀይሮ " ሴት ትፀንሳለች " ብሎ ለማረም ይሞክርና አመሻሽ ላይ ስለነበር እንቅልፍ ሸለብ አድርጎት ሲነቃ የቀየረው ተቀይሮበት " ድንግል ትጸንሳለች" የሚል ሁኖ ያገኘዋል።  ተሳስቼ ነው ብሎ አሁንም ሊያበላሽ ሲሞክር መልአኩ ሦስት ጊዜ አርሞበት  በሦስተኛው መልአኩ ራሱ ተገልጦለት "ይህችን ድንግል ሳታይና ልጇንም ታቅፈህ ሳትባረክ አትሞትም"
( የተጠራጠርከውን ሳታይ አትሞትም ብሎ ብሎ ነግሮት )  ተሰወረ። አረጋዊ ስምዖንም ከዚያች ዕለት ጀምሮ መድኅን ክርስቶስ እስከሚወለድ ለ284 ዓመታት ከአልጋ ጋር ተጣብቆ ኖረ።
አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከድንግል ማርያም በተወለደ በ40 ቀኑ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና አረጋዊው ቅዱስ ዮሴፍ ወደ ቤተ መቅደስ ይዘውት ወጡ ። በዕለቱም መልአከ እግዚአብሔር አረጋዊ ስምዖንን ቀስቅሶ ተስፋ የሚያደርገው አዳኝ ክርስቶስ መምጣቱን ነገረው። በዚህ ጊዜ አረጋዊ ስምዖን አካሉ ታድሶ፣ እንደ 30 ዓመት ወጣት እምር ብሎ ከአልጋው ተነሣ። በፍጥነትም ወደ መቅደስ ገባ። መድኀኔዓለምን ከድንግል ማርያም ተቀብሎ በመታቀፍ "ይእዜ ትስዕሮ ለገብርከ በሰላም እግዚኦ በከመ አዘዝከ፡-አቤቱ ባሪያህን እንደ ቃልህ በሰላም አሰናብተው"

(" ጌታ ሆይ፥ አን እንደ ቃልህ ባሪያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ ፤ ዓይኖቼ በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን ማዳንህን አይተዋልና፤
ይኽም ለአሕዛብ ሁሉን የሚገልጥ ብርሃን ለሕዝብህም ፳ኤል ክብር ነው።" (ሉቃ 2÷29-32)  )
በማለት ጸለየ። 

አምላኩም ጸሎቱን ሰምቶት በዛሬው ዕለት ዐረፈ። ከበዓሉ በረከት ይክፈለን። አሜን!!

የሊቁ ስምዖን  አረጋዊ በረከት እና ምልጃ አይለየን !
በዓለ ስምዖን በዐይቢይነት  ሜላት ደብረ ገነተ ኢየሱስ  ይከብራል  ፡፡
ጐንደር   -- › አንዳቤቴ ወረደ   -- › ገነተ ኢየሱስ  
በ13ኛ መቶ ክፍለ  ዘመን በአጼ ሰይፈ አርዕድ ዘመነ መንግስት
ልዕልት ሜላተ ወርቅ ያሰተከለችው ደብር ነው ፡፡
+++
በዓሉ በኢየሱስ ስም የተሰየሙ አድባራትና ገዳማት ላይ ይከበራል !

/በፍኖተ ሕይወት ሰ.ት.ቤት ሚድያና ሕዝብ ግንኙነት ዋና ማስተባበሪያ ክፍል የተዘጋጀ።/

• Facebook 👉 m.facebook.com/FinoteHiwotSundaySchool
• Telegram 👉 t.me/finotehiwott

• Tiktok 👉 tiktok.com/@finotehiwot 
• YouTube 👉 m.youtube.com/@finotehiwot1958
👍75🥰1🙏1
የደብራችን አገልጋይ ቀሲስ ዮሐንስ ደምሴ ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል ቀብሩ ነገ የካቲት 10/ 2017 ዓ.ም ከቀኑ 9 - 10 በቀጨኔ መድኃኔዓለም ይፈጸማል።

    "እግዚኦ አዕርፍ ነፍሰ አቡነ ፍቅረ ዮሐንስ"
ለቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን ያድልልን የአባታችንን ነፍስ ከደጋግ አባቶች ጎን ያሳርፍልን።

t.me/finotehiwott
😢607👍5🙏4