Finote Hiwot የቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኀኔ ዓለምና ደብረ ትጉሃን ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ሕይወት ሰንበት ትምህርት ቤት
15.4K subscribers
14.7K photos
78 videos
156 files
1.71K links
የቀጨኔ መድኃኔዓለም ፍኖተ ሕይወት ሰንበት ትምህርት ቤት ነሐሴ 26/ 1958 ዓ.ም ተመሠረተ።
Download Telegram
#የቀጨኔ_ደብረ_ትጉሃን_ቅዱስ_ገብርኤል_አመሠራረት

፨ በ1964 ዓ.ም አመጣጡ ያልታወቀ ባሕታዊ  ለዚህ ደብር ታላቅ ሞገስ የሚኾን  ለደብሩም ስመ ገናናነት የቅዱስ ገብርኤል ጽላት የገባ እንኾነ ነው ብሎ ለሊቃ ውንቱ ተናግሮ እንደሄደ ይነገራል ፡፡  ይኼም ባሕታዊ በዓመቱ መጥቶ ታቦተ ሕጉን እንዳልገባ ባየ ጊዜ ለኹለተኛ ጊዜ መልእክቱን አስተላልፏል ፡፡

፨ የደብሩ ሊቃውንትም የተነገራቸው የመንፈስ ቅዱስ መልእክት መኾኑን ተረድተው ከምእመናን ጋር ተመካክረው ታቦተ ሕጉን ከመድኀኔዓለም ጽላት ጋር አንድ ላይ በማድረግ በየወሩ በማኅሌት ፤ በቅዳሴ ፣  በውዳሴ ብቻ እየተከበረ እስከ 1967 ዓ.ም ቆየ ፡፡

፨ እማሆይ በለጡ ገብሬ የተባሉት መንፈሳዊ እናት ለቤ.ክርስቲያን በአበረከቱት ገንዘብ በጠላት ዘመን ለደብሩ አስተዳዳሪ #ሊቀ_ሊቃውንት_ገብረ_መስቀል ኋላ #ብፁዕ_አቡነ_ዮሐንስ ከደብሩ ምእመናን ጋር በመመካከር ለአብነት ት/ት ቤት እንዲኾን ብለው አዳራሽ አሠርተው እስከ #አፄ_ኃይለ_ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ድረስ አገልግሎት እየሰጠ  ሲቆይ የነበረውን አዳራሽ  ፤ የደርግ መንግሥት እንደተተካ  1968 ዓ.ም የቀበሌው አስተዳደር አዳራሹን  ለቀበሌው ኪነት መዝናኛ ማዕከል አንዲኹም ለአብዮታዊት ኢትዮጵያ  ወጣቶች ማኅበር  መሰብሰቢያ  ቦታ ለማድረግ ባለሥልጣኑ ወስዶት ስለነበር እስከ ጥቅምት 1972 ዓ.ም ለአራት ዓመታት በቤተ ክርስቲያኑ ውጪ ሆኖ  በወቅቱ ከፍተኛ 9 ቀበሌ 20 ትእዛዝ የአብነት ት/ት ቤቱ አገልግሎት እንዲቋረጥ ተደርጎ ስለነበር ፤ ካህናቱና ምእመናኑ በዚሁ ድርጊት ሲያዝኑና ሲቆረቆሩ ወደ እግዚአብሔር ጸሎት ሲያደረጉ ቆይተዋል ፡፡

፨ በዚህ እኩይ ድርጊት የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳደር ለሚመለካታቸው አካላት ቢያሳውቁም መልስ ፈጽሞ ሊያገኙ አልቻሉም ነበር ፡፡ ልዩ ልዩ የኪነ - ጥብብ ሥራዎች በቤተ-ክርስቲያኑ ቅፅር መካሄዱን እያደረ ሲቀጥል ፤ ልዩ ልዩ ተአምራቶች መታየት ጀመሩ ከእነዚህም መካከል አዳራሽ ውስጥ እኩይ ተግባራቶቹ በተደረጉ ጊዜ የእሳት ፈንዳት በተደጋጋሚ መነሳቱ ነው ፡፡ ከዚህም ቀጥሎ መድጋሚ በአቶ ታደሰ ወ/ኪዳን እና በመ/ሬ ታደሰ መልካሙ ለአ.አ ማዘጋጀ ቤት ጉዳዩን በድጋሚ በመጠየቅ አዳራሹ እንዲለቀቅ ኾኗል ፡፡

፨ ከዚም በኋላ አዳራሹን በድጋሚ ለሌሌች እኩይ ተግባራት እንዲውሉ ቢታሰብም ፤ የደብሩ አገልጋዮች የመድኀኔዓለም ቤተክርስቲያን ሊታደስ በመኾኑ ታቦታቱ ወደ እዛ እንዲገቡ በብፁዕ አቡነ ናትናኤልን ፍቃድ በመጠየቅ የተከናወነ ሲሆን በድጋሚ ከእሳቸው ፈቃድ በመጠየቅ እድሳቱ ካለቀ በኋላ የቅዱስ ገብርኤል ታቦት በዛው እንዲቀር ሆኗል ፡፡ ይህ የኾነውም በ1972 ዓ.ም በግንቦት ወር ሲኾን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በየዓመቱ ክብረ በዓሉ እየታሰበ ፣ ታቦቱ እየወጣ ሲከበር እስከ 1992 ዓ.ም  ቆይቷል ፡፡

፨ ይህ ገናና የቅዱስ ገብርኤል ታቦተ ሕግ በመቃኞ ቤት መኖር ስለሌለበት ቦታው በቋሚነት  የማያገልግ ስለኾነ አዲስ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ራሱን ችሎ እንዲሠራ ሃሳብ ቀርቦ የተለያዩ ውይይቶች ከተደረጉ በኋላ ሚያዝያ 25 ቀን 1989 ዓ.ም #በብፁዕ_ወቅዱስ_አቡነ_ጳውሎስ_ፓትርያርክ የመሠረት ድንጋይ ተቀመጦ ፤ ኅዳር 11 ቀን 1990 ዓ.ም የመሠረት ቁፋሮ ተጀምሮ በኹለት ዓመት ሊጠናቀቅ ችሏል ፡፡

፨ በዚህም  በአ.አ ከተማ በዘመናዊ የቤ.ክ ሕንፃ ሥራ ታሪክ በአጭር ጊዜ ተጠናቆ በመሠራት የመጀመርያነቱን ይዟል ፡፡
#ቅዳሴ_ቤቱም ሐምሌ 19 ቀን 1992 ዓ.ም ተከብሯል ፡፡ የቤተ ክርስቲያኑም ስያሜ #ደብረ_ትጉሃን_ቅዱስ_ገብርኤል  ተብሏል ፡፡

/በፍኖተ ሕይወት ሰ.ት.ቤት ሚድያና ሕዝብ ግንኙነት ዋና ማስተባበሪያ ክፍል የተዘጋጀ።/

• Facebook 👉 m.facebook.com/FinoteHiwotSundaySchool
• Telegram 👉 t.me/finotehiwott

• Tiktok 👉 tiktok.com/@finotehiwot 
• YouTube 👉 m.youtube.com/channel/UCWVKGH0mSJl47u44uopEb2w
👍103