ፍኖተ ሕይወት ሰ/ት/ቤት ባሕር ዳር
251 subscribers
1.96K photos
16 videos
90 files
159 links
#እኛ_የአቡየ_ልጆች
ማንም አላዋቂ ምንም ቢል እኛ ግን እምናገለግለውን እናቃለን እርሱም እንደ ሰው ተወልዶ እንደ መላእክት የኖረ እንደ መላእክት ኑሮ በክብር እንደ ሰው ያረፈውን በነጎድጓድ ላይ ስልጣን የተሰጠውን አባ ገብረ መንፈስ ቅዱስን ነው።

ለማንኛውም አስተያየት👉 0902092705- @finotehiwotdk
Download Telegram
ታላቁ ዲማ ከፈራቸው ታላላቅ ስመ ጥር ሊቃውንት መካከል አንዱ ናቸው መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ፡፡ መልአከ ብርሃን ተወልደው ያደጉት በዚሁ በዲማ ነው፡፡ በመጽሐፎቻቸው መቅድም ላይ እንዳስቀመጡት “እኔ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ የተወለድኩበትና ያደግሁበት የተማርኩበት ሀገሬ በጎጃም ጠቅላይ ግዛት ዲማ ጊዮርጊስ መልአከ ብርሃን ተብየ የተሸምኩበት ብቸና ጊዮርጊስ ነው” ይላሉ፡፡ መልአከ ብርሃን አድማሱ የተወለዱት ነሐሴ ፩ ቀን ፲፰፻፹፭ ዓ.ም እግዚአብሔርን ይፈሩ ከነበሩት ደግና ርኅሩኅ ከሆኑት ከአባታቸው ከአቶ ጅነበሬ አዲሱ እና ከእናታቸው ወ/ሮ ወለተ ማርያም ኃይሉ በጎጃም ጠቅላይ ግዛት በእነማይ ወረዳ በታላቁ ዲማ ነው፡፡ እናታቸው ወለተ ማርያም በጀርባቸው አዝለዋቸው እያሉ ከየት እንደመጡ የማይታወቁ ባሕታዊ “ይህ ያዘልሽው ልጅ ቤተክርስቲያንን የሚጠቅም ነው እግዚአብሔርም የመረጠው ነውና በጥንቃቄ አሳድጊው በሰዓቱም ወደ ትምህርት ቤት አስገቢው” አሏቸው፡፡ ወለተ ማርያምም “እግዚአብሔር ያለው መቸም አይቀረም” በማለት ልጃቸውን “ያለው” ብለው ስም አወጡላቸው በተባሉት መሠረትም ያለው ጀንበሬ ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ እዚያው ከተወለዱበት ታላቁ ገዳም ዲማ ጊዮርጊስ እንዲማሩ አስገቧቸው፡፡ በዚህም መሠረት ሁሉንም የቤተክርስቲያናችንን ዕውቀት ሁሉ ከዚሁ ከታላቁ ገዳም ከዲማ ጊዮርጊስ ቀስመዋል፡፡ ከባህታዊው አባ ወንድሙ ከፊደል እስከ ዳዊት  ከተማሩ በኋላ ወደ አጎታቸው ሊቀ ጠበብት ክንፉ ሂደው ጾመ ድጓ፣ ምእራፍ፣ ድጓ፣ ዝማሬ መዋስእት እና ቅኔን ተምረዋል፡፡ ከዚያም በዚሁ ገዳም በዲቁና፣ በመዘምርነት፣ በቅኔም፣ በመምህርነትም አገልግለዋል፡፡ ያለው ጀንበሬን አባታቸው “አድማሱ” ብለው ይጠሯቸው ስለነበር ያለው በሚለው ስም እስከ ፲፱፻፬ ዓ.ም ሲጠሩበት ከቆዩ በኋላ ሊቅነታቸው እየጨመረ በሁሉ ዘንድ ታዋቂ ሲሆኑ በአባታቸው የወጣላቸው ስም እየገነነ እንደመጣ በቅርብ የሚያውቋቸው ታላቁ ሊቅ አለቃ አያሌው ታምሩ ተናግረዋል፡፡ በዚህ መሠረት እኔም መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ እያልኩ እጽፋለሁ፡፡

መልአከ ብርሃን አድማሱ ሁሉንም ትምህርታቸውን ከዲማ ከተማሩ በኋላ በተለያዩ ቦታዎች ተዘዋውረው አስተምረዋል ታላቅ ታሪክንም ፈጽመዋል፡፡ መልአከ ብርሃን በቁም ጽሕፈት በጣም የታወቁም እንደነበሩ ይነገራል፡፡ መልአከ ብርሃን ከትውልድ ሀገራቸው ዲማ ለመጀመሪያ ጊዜ በግንቦት ፲፪ ቀን ፲፱፻፬ ዓ.ም ለቀው ደብረ ሊባኖስ ገዳም ሂደው የጻፉትን የአርባዕቱን ወንጌል ንባብ በዚያ ሸጠው ለስንቃቸው እና ለጉዟቸው የሚሆን ገንዘብ ይዘው ወደ አዲስ አበባ አቀኑ፡፡

አዲስ አበባ ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን አካባቢ ከነበሩት ወልደ ሥላሴ ከሚባሉት የብሉይ ኪዳን  መምህር ዘንድ ትርጓሜ ዳዊትን፤ መጻሕፍተ ሰሎሞንን እና ትንቢተ ኢሳይያስን ከቀጸሉ በኋላ በወጡ በዓመታቸው ወደ ትውልድ ሀገራቸው ዲማ በግንቦት ወር  በ፲፱፻፭ ዓ.ም ተመለሱና ከመምህር ወልደ ጊዮርጊስና ከመምህር እንግዳሽት ዘንድ ቅኔና ልዩ ልዩ መጻሕፍትን ተምረዋል፡፡ ከዚያም ወደ ደሴ በ፲፱፻፮ ዓ.ም ሄደው ከመልአከ ገነት አፈወርቅ ፍትሐ ነገሥትን እንዲሁም ከቀለም ቀንዱ መምህር አካለ ወልድ ዘቦሩ ሜዳ ዘንድ በመሄድ ሐዲሳትንና መጻሕፍተ ሊቃውንትን ተማሩ፡፡ ከዚያም  በ፲፱፻፱ ወደ ጎጃም ደምበጫ ተመልሰው ከብሉዩ ሊቅ ከመምህር አለቃ ገብረ ኤልያስና ከቅኔው ሊቅ ከመልአከ ሰላም ገብረ ማርያም ዘንድ ብሉያቱን ሲቀጽሉ ቅኔውን ሲያስፋፉ እስከ  ፲፱፻፲፰ ዓ.ም ድረስ በዚያ ቆዩ፡፡

ከዚህ በኋላ ወደ ትውልድ ሀገራቸው ዲማ በመመለስ እስከ ፲፱፻፳፬ ዓ.ም ድረስ በቅኔ መምህርነት ሲያገለግሉ ቆዩ፡፡ መልአከ ብርሃን እስከዚህ ዘመን ድረስ መተዳደሪያቸው መጻሕፍትን በቁም ጽሕፈት በማዘጋጀት እርሱን በመሸጥ በሚያገኙት ገንዘብ ነበር፡፡ በ፲፱፻፲፰ ዓ.ም አካባቢ የልጆቻቸውን እናት ወ/ሮ አለሚቱ እሸቴ (በኋላ እማሆይ አለሚቱ እሸቴ) ን አግብተው ሰባት ልጆችን አፍርተዋል፡፡ ከዚህ በኋላ በ፲፱፻፳፭ ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው በዚያ መኖር ጀመሩ፡፡

****
የመልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ ታላላቅ ሥራዎች፡-
*

  ⚡️ ቤተክርስቲያናችን በመናፍቃን ስትደፈር እንደ ውርደት ይቆጥሩት ስለነበር ሌላው ዝም ቢል እንኳ እኔ ግን ዝም አልልም በማለት አቶ ዘመንፈስ የተባለ መናፍቅ “ተግሳጽና ምክር” በሚል  ምንፍቅናውን ሲዘራ  “ኰኲሐ ሃይማኖት”ን ዳግመኛም ዶ.ር አባ አየለ ተክለሃይማኖት የተባለ ካቶሊካዊ መነኩሴ “የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ስለ ክርስቶስ ባሕርያት የምታምነው ትምህርት” ብሎ ክህደትን ሲጽፍ “መድሎተ አሚንን” በመጻፍ ተገቢውን ምላሽ በመስጠት እንዲያፍሩ አድርገዋል፡፡ በዚህም በተለይም በመድሎተ አሚን የካቶሊካውያኑ ቅርንጫፎች የሆኑትን “ቅብዐትን” እና “ጸጋን” ድራሻቸው እንዲጠፋ በማድረጋቸው ታሪክ ሲዘክራቸው ይኖራል፡፡ ነገር ግን በመልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ መልስ የተቀበሩትን እነዚህን ምንፍቅናዎች ዛሬ በአዲስ መልኩ በአቡነ ማርቆስ እንዲያንሰራሩ ተደርጓል፡፡ 
⚡️ የመጨረሻ ልጃቸውን “ምኅርካ ክርስቶስ አድማሱን” ከሞት አስነሥተዋል፡፡ ትናንት የነበርህ አምላክ ዛሬም እንዳለህ አምናለሁ፡፡ “አዝዝ በቃልከ  ይሕየው ወልድየ ፤ ልጄ እንዲድን በቃልህ እዘዝ” በማለት ነበር ልጃቸውን ከሞት ያስነሡት፡፡ ይህ ሙትን የማንሣት ቅድስና በአንድ ጀንበር የሚመጣ እንዳልሆነ የታወቀ ነው፡፡ ምርጥ የጸሎት አባት ሊቅ ቅዱስ እንደሆኑ በዚህ መረዳቱ አይከብድም፡፡ 
  ⚡️ ጥሩ የንባብ ችሎታ ነበራቸው፡፡ መልአከ ብርሃን ምግብ እየተመገቡ እንኳ በአንድ እጃቸው መጽሐፍ ይዘው ያነብቡ ነበር፡፡ “እባክዎ ዓይንዎ ይጎዳል” ሲሏቸውም “ለመጽሐፍ መመልከቻ ያልሆነ ዓይን ይፍረጥ” ይሉ እንደነበር ይነገራል፡፡ የሚገርመው ነገር መልአከ ብርሃን አድማሱ ለንባብ የሚመች የተለየ ቦታ ሳይኖራቸው ሳሎን ላይ ቁጭ ብለው በተመስጦ ያነብቡ ነበር፡፡ በጣም የሚያዘወትሩት የሃይማኖት መጻሕፍትን ቢሆንም የታሪክ እና የምርምር ጽሑፎችን የግለሰብ ታሪክ መዛግብትን ልብወለዶችንም  ያነቡ ነበር፡፡ 
⚡️የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከራሷ ልጆች ሊቃነ ጳጳሳትን መሾም አለባት፡፡ ከግብጽ በሚመጡ ሊቃነ ጳጳሳት አገልግሎታችንን መፈጸም አልቻልንም፡፡ በቋንቋችን የሚያስተምሩ ሊቃነ ጳጳሳትን ከሐገራችን ልጆች መሾም አለብን የሚለውን ታላቁን ሀሳብ ከማመንጨት ጀምረው ጉዳዩን ዳር እስከማድረስ ድረስ ታላቅ የሆነ ተጋድሎን ፈጽመዋል፡፡ ይህም ተጋድሏቸው ዛሬ ፍሬ አፍርቶ ከመጀመሪያው ፓትርያርክ አቡነ ባስልዮስ እስከ አሁኑ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ድረስ ደርሷል፡፡ 
⚡️በቤተክህነቱ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳድር ላይ በመማክርት አባልነት አገልግለዋል፡፡ ከዚያም ይህ አስተዳድር ቀርቶ በመልአከ ብርሃን አድማሱ የታሪክና ድርሰት ክፍል ሹም የሊቃውንት ጉባዔ ፕሬዝዳንት በመሆን አገልግለዋል፡፡

   ⚡️ በ፲፱፻፵፱ ዓ.ም - ፲፱፻፶፱ዓ.ም በንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ሆነው ተሹመው በቤጌ ምድር፣ በወሎ እና በትግራይ ጠቅላይ ግዛቶች በመዘዋወር ከባድ እና አስቸጋሪ የሚባሉትን የፍርድ ውሳኔዎች ሁሉ በሚገባ ያለ አድልዎ በቀላል ጥበባዊ ዘዴ ወስነዋል፡፡ ከዚህም አገልግሎታቸው በኋላ በ፲፱፻፶፱ዓ.ም በጥሮታ ከዚህ ሥራ ለቅቀዋል፡፡ 
  ⚡️ በልዩ ልዩ ድርጅቶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ በኢትዮጵያ ሬዲዮና በብሥራተ ወንጌል ሬዲዮ ጣቢያዎች እየተገኙ መንፈሳዊ ትምህርቶችን ያስተላልፉ ነበር፡፡ ከተለያዩ አቅጣጫዎችም የሚቀርቡላቸውን ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎች በመመለስም ይታወቃሉ፡፡ 
  ⚡️ በጠቅላይ ቤተ ክህነት መጽሐፍትን እንዲመረምሩ እና እንዲተረጉሙ፣ በቤተክርስቲያናችን የሚነሡትን ዐበይት ችግሮችም እንዲመለከቱ ከጥሮታ በኋላ ወደ ጠቅላይ ቤተክህነት ተጠሩ፡፡ በዚህም አጋጣሚ ብዙ ሊቃውንትን የማግኘት እድሉን አገኙ፡፡ የኢትዮጵያ ሊቃውንት ታሪክ አልባ እንዳይሆኑ ሥራቸውም ተቀብሮ እንዳይቀር በማሰብ እነርሱን የሚዘክር መጽሐፍ “ዝክረ ሊቃውንት” በሚል ለኅትመት አብቅተዋል፡፡  ይህ መጽሐፍም የታተመው እርሳቸው ከዐረፉ በኋላ በ፲፱፻፷፫ ዓ.ም  ነው፡፡ 
 ⚡️  ስለኢትዮጵያ ባህልና ታሪክ ጥናትና ምርምር ለሚያደርጉ ሰዎችም የበኩላቸውን ከፍተኛ ድጋፍ ያደርጉ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት “የኢትዮጵያ የጥንት ቅርስ ጥበቃ ድርጅት” ባደረገው እንቅስቃሴ ላይ ተሳትፈው በጎጃም ጠቅላይ ግዛት አካባቢ ባሉ አድባራትና ገዳማት ያሉ መጻሕፍትን በድርጅቱ ከሚጠበቀው  በላይ መረጃውን በማሰባሰብ አቅርበዋል፡፡  ከዚህ በተጨማሪም የትምህርትና ሥነ ጥበብ ሚኒስቴር በየአብያተ ክርስቲያናቱ የሚገኙትን መጻሕፍት በማይክሮ ፊልም በሚያነሣበት ወቅት በጎጃም ጠቅላይ ግዛት በብቸና አውራጃ ያሉትን ምርጥና ጥንታውያን መጻሕፍትን በማስነሣት በኩል ከፍተኛ ሚና ነበራቸው፡፡ በዚህም ሥራ ተሳታፊ ነበሩ፡፡ 
 ⚡️  በዐቢይ ጾም ወቅት በኢትዮጵያ ሬዲዮ በመገኘት ተከታታይ ትምህርቶችን ሰጥተዋል ይህ ተከታታይ ትምህርታቸውም “ሐዲስ ሰውነት” በሚል መጽሐፍ ታትሟል፡፡ 
   ⚡️ መጻሕፍትን መመርመር ይወዱ ነበር፡፡ መጻሕፍትን ዝም ብለው ከመቀበል ይልቅ የያዙትን ፍሬ ነገር በሚገባ መረዳትን ይመርጡ ስለነበር ያገኙትን ሁሉ መጽሐፍ መመልከት ይወዱ ነበር፡፡ በዚህም በጣም አስቸጋሪ እና በቀላሉ ለመረዳት የሚከብዱ ቃላትን በመተርጎም ይታወቁ ነበር፡፡ ለዚህም መድሎተ አሚንን እና ኰኲሐ ሃይማኖትን ያነበበ ሰው ሁሉ ምስክር ይሆናል፡፡ 
  ⚡️ዲማ ጊዮርጊስ ለተቋቋመው የጀግኖች ማኅበር አባል ሆነውም አገልግለዋል፡፡ 
   ⚡️ ትጉህ፣ ትእግስተኛ፣ ለቤተክርስቲያን ተቆርቋሪ፣ የጸሎት አባት፣ ቅድስናን ከሊቅነት ጋር ያስተጻመሩ፣ ለሚጠይቃቸው ሁሉ መልስ የሚሰጡ ታላቅ አባት፣ አስተዋይ፣ ሐገር ወዳድ፣አርቆ አሳቢ፣ በጥልቀት መርማሪ፣ እግዚአብሔርን ፈሪ፣ ሰውን አክባሪ፣እውነትን ደፋሪ፣ ሰውን ሁሉ አስደሳች፣ የሰውን ክብር ጠባቂ  ነበሩ፡፡
ታዋቂውን ሊቅ አለቃ አያሌውን ወደ አዲስ አበባ ወስደው በማስተማርም ለቤተክርስቲያናችን ሌላ እርሳቸውን የሚተካ ታላቅ ሊቅ አበርክተዋል፡፡ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ የታላቁ ሊቅ አለቃ አያሌው አጎታቸውም ናቸው፡፡ ስለ አለቃ አያሌውም በትህትና ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ሲናገሩ “እኔን ማንም ይተካኛል እኒህን ዓይነ ሥውር ሊቅ ግን ተንከባከቧቸው እርሳቸውን የሚተካ መምህር ወደፊት አይገኝምና” እንዳሉም ይነገራል፡፡

በአቡነ ፊልጶስ ተመርጠው አድማሱ ጀንበሬ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀበሉት ሹመት “መጋቤ ምሥጢር” የሚል ነበር፡፡ ይህ የሹመት ስም ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰጣቸው ለአድማሱ ጀንበሬ ሲሆን ሹመቱ በእንደዚህ ዓይነት ሰው መጀመሩ ዕድለኛ የሆነው ተሿሚው ሳይሆን ራሱ ሹመቱ ነውም ተብሏል፡፡ ይህ ሹመትም ለመጀመሪያ ጊዜ ለእርሳቸው ከተሰጠ በኋላ ሌሎችም እየተጠቀሙበት ይገኛል፡፡ ከአድማሱ ጀንበሬ በፊት “መጋቤ ምሥጢር” የሚል ሹመት የለም ነበር ማለት ነው፡፡ 
  በ ፲፱፻፳፯ ዓ.ም ደግሞ በንጉሠ ነገሥቱ መልካም ፈቃድ የተቀበሉት ሁለተኛው ሹመት  “ሊቀ ጠበብት” የሚል ነበር፡፡ ይህን ሊቀ ጠበብትነት መዓርግ ይዘው ከአዲስ አበባ ወደ ሀገራቸው ዲማ ተመልሰዋል፡፡ 
መልአከ ብርሃን ተብለው የተሾሙበት ብቸና ጊዮርጊስ ደብር
  በ ፲፱፻፴፫ ዓ.ም ደግሞ በታላቁ ብቸና ጊዮርጊስ “መልአከ ብርሃን” ተብለው ተሾሙ፡፡ እስካሁንም ድረስ የሚጠሩት በዚሁ ስማቸው ነው፡፡ በመጽሐፎቻቸውም ውስጥ የሚጠቅሱት ይህንኑ መዓርግ ነው፡፡ 


🔥 መጋቤ ምሥጢር ሊቀ ጠበብት መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ የሀገራችንን ሊቃውንት ስም ለማስታወስ እና ሥራቸው ከመቃብር በላይ እንዲሆን ለማድረግ እንቅልፍ አጥተው ታሪከ ሊቃውንትን አሰባስበው “ዝክረ ሊቃውንት” የተሰኘው መጽሐፋቸውን በማዘጋጀት ላይ ሳሉ ነበር በድንገተኛ የአእምሮ ድካም (ስትሮክ) ሀምሌ ፳፬ ቀን ፲፱፻፷፪ ዓ.ም ይህ መጽሐፋቸው ሳይታተም ያረፉት፡፡ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፣ ቤተሰቦቻቸው እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበትም በእግዚአብሔር ወልድ ቤተክርስቲያን ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል፡፡ “ፍሬ ሊቃውንት” የተባለው የማኅበረ ቅዱሳን መጽሐፍ ግን ቀብራቸው ቅድስት ሥላሴ ተፈጽሟል ይላል፡፡

♡ ㅤ   ❍ㅤ      ⎙        ⌲
ˡᶦᵏᵉ  ᶜᵒᵐᵐᵉⁿᵗ   ˢᵃᵛᵉ   ˢʰᵃʳᵉ
ይወዳጁን
👇👇👇👇👇👇👇👇
https://linktr.ee/finotehiwot_sundayschool?utm_source=linktree_profile_share&ltsid=f62cf905-ffbd-4af4-bf12-2f29df393f8c
ለአርባ ቀን መታሰቢያቸው አለቃ ተገኝ የገጠሙላቸው ግጥም።

♡ ㅤ   ❍ㅤ      ⎙        ⌲
ˡᶦᵏᵉ  ᶜᵒᵐᵐᵉⁿᵗ   ˢᵃᵛᵉ   ˢʰᵃʳᵉ
ይወዳጁን
👇👇👇👇👇👇👇👇
https://linktr.ee/finotehiwot_sundayschool?utm_source=linktree_profile_share&ltsid=f62cf905-ffbd-4af4-bf12-2f29df393f8c
በዛሬው ዕለት የተመረቃችሁ ውድ የሰንበት ትምሕርት ቤታችን አገልጋዮች
ወንድም ሣሙኤል እና እኅት ሠናይት ፍኖተ ሕይወት ሰ/ት/ቤት እንኳን ደስ አላችሁ ከዚህ በላይ ፍሬያችሁን ያሳየን ትላለች።




♡ ㅤ   ❍ㅤ      ⎙        ⌲
ˡᶦᵏᵉ  ᶜᵒᵐᵐᵉⁿᵗ   ˢᵃᵛᵉ   ˢʰᵃʳᵉ
ይወዳጁን
👇👇👇👇👇👇👇👇
https://linktr.ee/finotehiwot_sundayschool?utm_source=linktree_profile_share&ltsid=f62cf905-ffbd-4af4-bf12-2f29df393f8c
ከ4 ዓመት እስከ 6 ዓመት ላሉ ሕጻናት "ተስፋ ቤተክርስቲያን" በሚል መጠሪያ በዘመናዊው የKG ሕጻናት የትምሕርት አሰጣጥ ሂደት በሀገረ ስብከታችን ሰ/ት/ቤታችን ቀዳሚ እንደሆነ ይታወቃል።

በዚህም  ሰ/ት/ቤታችን ለቅድመ መደበኛ ማስተማሪያ መጽሐፍትን እንዲያዘጋጅ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት በመመረጡ የተሰጠውን ኃላፊነት በመወጣት በአዘጋጅነት የተሳተፈበት የቅድመ መደበኛ "ሀ" እና "ለ" መጽሐፍትን በቀጣዩ የትምሕርት ዘመን በተግባር ላይ በማዋል በእትም ላይ ውሏል።

በዚህ አገልግሎት ላይ ጊዜያችሁን እና እወቀታችሁን ለበረከታችሁ የሰ/ት/ቤታችን የመጽሐፍ ዝግጅት ኮሚቴ አገልጋይ መምህራንን እያመሰገን ድካማችሁ ፍሬ ላይ እንደዋለ ለማብሰር እንወዳለን።


♡ ㅤ   ❍ㅤ      ⎙        ⌲
ˡᶦᵏᵉ  ᶜᵒᵐᵐᵉⁿᵗ   ˢᵃᵛᵉ   ˢʰᵃʳᵉ
ይወዳጁን
👇👇👇👇👇👇👇👇
https://linktr.ee/finotehiwot_sundayschool?utm_source=linktree_profile_share&ltsid=f62cf905-ffbd-4af4-bf12-2f29df393f8c
††† እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ የጽንሰት በዓል በሰላም አደረሳችኹ፤ አደረሰን። †††


††† ቁጽረታ (ጽንሰታ) ለማርያም †††

††† ይህችን ዕለት አበው ሊቃውንት "ጥንተ መድኃኒት፤ የድኅነት መነሻ ቀን" ሲሉ ይጠሯታል::
ስለ ምን ነው ቢሉ:-
ለዓለም ድኅነት ምክንያት የሆነች የአምላክ እናቱ የተጸነሰችበት ዕለት በመሆኑ ነው:: አንድም ከአዳም ስሕተት በኋላ ያለ ጥንተ አብሶ የተጸነሰች የመጀመሪያ ሰው እርሷ ናትና እንዲህ ይላሉ::
"ለጽንሰትኪ በከርሥ: እንበለ አበሳ ወርኩስ: ወለልደትኪ እማኅጸን ቅዱስ::"
"ድንግል ሆይ! መጸነስሽ ያለ በደል (ያለ ጥፋት) ነው: የተወለድሽበት ማኅጸንም ቅዱስ ነው::"
(መጽሐፈ ሰዓታት, ኢሳ. 1:9, መኃ. 4)

ይሕች ዕለት ለኢያቄምና ለሐና ብቻ ሳይሆን ለፍጥረት ሁሉ የተስፋ ድኅነት ቀን ናትና ሐሴትን ልናደርግ ይገባል::
የእመቤታችን መጸነስስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
ከነገደ ይሁዳ የሚወለድ ቅዱስ ኢያቄም የሚባል ደግ ሰው ከነገደ ሌዊ(አሮን) የተወለደች ሐና የምትባል ደግ ሴት አግብቶ: በሕጉ ጸንተው: በሥርዓቱ ተጠብቀው ይኖሩ ነበር:: ነገር ግን በዘመኑ ሰዎች "ልጅ የላችሁም" በሚል ይናቁ ነበር::

ኦሪታውያን ልጅ የሌለውን "ኅጡአ በረከት-ከጸጋ እግዚአብሔር የራቀ" ነው ብለው ያምኑ ነበር:: ኢያቄምና ሐና ልጅ እንዲሰጣቸው ሲያዝኑ: ሲጸልዩ ዘመናቸው አልፎ አረጁ:: እነሱ ግን የሚያመልኩት የአብርሃምና ሣራን አምላክ ነውና ተስፋ አልቆረጡም::

የለመኑትን የማይነሳ ጌታ በስተእርጅናቸው ድንቅ ነገርን አደረገላቸው:: አንድ ቀን ርግቦች ከጫጩቶቻቸው ጋር ሲጫወቱ የተመለከተች ቅድስት ሐና ፈጽማ አለቀሰች:: "እንስሳትና አራዊትን: እጽዋትን በተፈጥሯቸው እንዲያፈሩ የምታደርግ አምላክ ምነው ሐናን ድንጋይ አድርገህ ፈጥረሃታልን?" ብላ አዘነች::

ይህን የተመለከተ ቅዱስ ኢያቄም ወደ ተራራ ወጥቶ ሱባኤ ያዘ:: ለአርባ ቀናትም ሲጸልይና ሲማለል ቆየ:: በአርባኛው ቀን ሁለቱም ሕልምን ያልማሉ:: እርሱ:- ነጭ ርግብ ሰማያትን ሰንጥቃ ወርዳ: በሐና ቀኝ ጆሮ ገብታ: በማኅጸኗ ስትደርስ አየ::

እርሷ ደግሞ:- የኢያቄም በትር አብቦ: አፍርቶ: ጣፋጭ ፍሬውን ሰው ሁሉ ሲመገበው ታያለች:: ቅዱስ ኢያቄም ከሱባኤ እንደ ተመለሰ ያዩትን ተጨዋውተው "ፈቃደ እግዚአብሔር ይሁን" አሉ:: ለሰባት ቀናትም በጋራ እግዚአብሔርን ሲለምኑ ሰነበቱ::

በሰባተኛው ቀን (ማለትም ነሐሴ 7) መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ክንፉን እያማታ ወደ እነርሱ ወረደ:: "ዓለም የሚድንባት: የፍጥረት ሁሉ መመኪያ የሆነች ልጅ ትወልዳላችሁ" ብሏቸው ተሠወራቸው:: እነርሱም ደስ ብሏቸው እግዚአብሔርን አመሰገኑ::

እንደ ሥርዓቱም በዚህች ቀን አብረው አድረው እመ ብርሃን ተጸነሰች::
"ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተጸነስኪ"
"ድንግል ሆይ! ኃጢአት ባለበት ሥጋዊ ፍትወት የተጸነስሽ አይደለም" እንዳለ ሊቁ::
(ቅዳሴ ማርያም)

Ⓒ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ


♡ ㅤ   ❍ㅤ      ⎙        ⌲
ˡᶦᵏᵉ  ᶜᵒᵐᵐᵉⁿᵗ   ˢᵃᵛᵉ   ˢʰᵃʳᵉ
ይወዳጁን
👇👇👇👇👇👇👇👇
https://linktr.ee/finotehiwot_sundayschool?utm_source=linktree_profile_share&ltsid=f62cf905-ffbd-4af4-bf12-2f29df393f8c
ልጆቻችሁ በኦርቶዶክሳዊ እድገት ውስጥ ማለፍ እንዲችሉ በዚህ ሥርዓተ ትምሕርት ያስመዝግቡ።

♡ ㅤ ❍ㅤ ⎙ ⌲
ˡᶦᵏᵉ ᶜᵒᵐᵐᵉⁿᵗ ˢᵃᵛᵉ ˢʰᵃʳᵉ
ይወዳጁን
👇👇👇👇👇👇👇👇
https://linktr.ee/finotehiwot_sundayschool?utm_source=linktree_profile_share&ltsid=f62cf905-ffbd-4af4-bf12-2f29df393f8c
ነሐሴ 24 በልደታችን ቀን እንገናኝ።
🔆🔆+ ከታቦር ተራራ አትቅር + 🔆🔆

"አጣቢም በምድር ላይ እንደዚያ ሊያነጣው እስከማይችል በጣም ነጭ ሆነ። " ማር 9: 3
/ሽራፊ ሃሳቦች ከደብረ ታቦር ንባብ/

የወንጌላውያን ትሕትና ይደንቃል ፣ ማቴዎስ ማርቆስ ሉቃስ ስለ ደብረ ታቦር ሲጽፉ ዮሐንስ አልጻፈም። ዮሐንስ ተመርጦ የተገኘበትን ታሪክ "ተመርጬ" ብሎ አልጻፈም። የቀሩት ወንጌላውያን ደግሞ "እኛ የሌለንበትን ነገር አንጽፍም" አላሉም። አንድ ወንጌል እየሰበኩ የሚፎካከሩ ፣ የአንድ ቤት ጣሪያ እየሠሩ ቆርቆሮ የሚሻሙ የእኛ ዘመን አገልጋዮች አልነበሩምና እነርሱ ያልተመረጡበትን ታሪክ ለመናገር ተሯሯጡ። እኛን የማያካትት ክብር ፣ እኛን የማይጨምር ድግስ ጉዳይ ሲነሣ ለማይጥመን ፣ እኛ የሌለንበትን ፎቶ እንኳን ለማየት የማንፈልግ ፣ በእኛ በኩል ያለፈን ነገር ብቻ የምናራግብ ፣ የሌለንበትን ነገር ጥሩም ቢሆን እንኳን ለምናጣጥል "በእኔ በቀር ባዮች" ትምህርቱ ድንቅ ነው።

ሌላ ማሳያም አለ ማቴዎስ ወንጌላዊው ስለ ራሱ ታሪክ ሲጽፍ "ማቴዎስ የተባለ ቀራጭ በመቅረጫው ተቀምጦ" ብሎ በኃጢአት ከተዘፈቀበት ሥራ ላይ ወደ ክርስትና እንደተጠራ በግልጽ ሲጽፍ ሌሎቹ ወንጌላውያን ግን በሐዋርያት ዝርዝር ላይ ማቴዎስ ያሉትን ሰው ስለ ቀድሞ የቀራጭነት ሥራው ሲጽፉ ግን ሌዊ የሚል ተለዋጭ ስሙን ተጠቅመዋል። ትሑቱ ማቴዎስ ግን በሌሎች ወንጌላውያን የተሸሸገ የቀድሞ የኃጢአት አኗኗሩን ለእግዚአብሔር ይቅር ባይነት ማሳያ እንዲሆን ስለፈለገ ጭራሽ በሐዋርያት የስም ዝርዝር ላይ "ቀራጩ ማቴዎስ" ብሎ ራሱን ጠርቷል።

የሚገርመው ከቀራጭነት ከተጠራ በኋላ በቤቱ ታላቅ ድግስ ደግሶ ጌታችንን ከኃጢአተኞች ጓደኞቹ ጋር የተቀበለ መሆኑን በሌሎች ወንጌላውያን ሲጽፉ ማቴዎስ ግን ቀራጭነቱን አጉልቶ እንዳልጻፈ ሁሉ የግብዣው ነገር ደጋሹ እርሱ መሆኑን አድበስብሶ በመጻፍ አልፎታል።

★ ★ ★

ቅዱስ ጴጥሮስ "ጌታ ሆይ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው" አለ። "ለእኛ" መልካም ነው የሚለው ቃል ድንቅ ነው። በእግዚአብሔር ቤት መኖራችን መልካምነቱና ጥቅሙ ለእኛ ነው እንጂ ለእግዚአብሔር አይደለም። የማንጠቅም ባሪያዎቹ ስሙን በአሕዛብ ዘንድ ከማሰደብ በቀር ለእርሱ ምን እንጠቅመዋለን። ለዚህም ነው ቅዱስ ባስልዮስ "ጌታ ሆይ የአንተ አምላክነት ለእኔ ያስፈልገኛል እንጂ የእኔ ፍጡርነት ለአንተ አያስፈልግህም" ያለው።
ስለዚህ ጴጥሮስ "ለእኛ መልካም ነው" አለ።

"ብትወድስ ሦስት ዳስ እንሥራ" አለ ፣ ጌታ ካልወደደ እንኳን ሦስት አንድ ዳስ መሥራት አይቻልም ፣ እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ" ስለዚህ "ብትወድስ" አለ።

የዋሁ ጴጥሮስ ለእኔ ልሥራ አላለም ፣ የሐዲስ ኪዳን ሐዋርያ ነኝ ብሎ የብሉይ ኪዳን ነቢያትን ከማክበር ወደ ኋላ አላለም። "አንተ ዓለት ነህ በዚህች ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራታለሁ" በተባለ ማግስት ለነቢያቱ ድንኳን ሊቀልስ የጠየቀ ከጴጥሮስ በቀር ማን አለ?

ከእግዚአብሔር አብ ግን "አትሙት" እስከማለት ለደረሰው ለነጴጥሮስ ንግግር "የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት" የሚል ትእዛዝ መጣ። ሃሳቡ ድንቅ ቢሆንም ቃሉን ሳይሰሙ ዳስ መሥራት መጀመር አይቻልም።

በዚያ ላይ ጌታ የመጣው በደብረ ታቦር ድንኳን አስጥሎ ሊኖር ሳይሆን በቀራንዮ በተሰቀለበት በመስቀሉ ካስማ በደሙ ድንኳን ተክሎ ሊያስጠልለን ነው። ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ "ጴጥሮስ ሆይ ለአንተ የፊቱን ብርሃን እያየህ በዚህ መኖር መልካም ነው ፣ እኛ ግን የምንድነው በተራራው ሲኖር ሳይሆን ወርዶ ፊቱን በጥፊ ሲመታ ነው" ብሎታል።

ጴጥሮስ የዋሁ "በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ" ላለው ለክርስቶስ ድንኳን ሊቀልስ ጠየቀ። በሰማይ "በሰው ሳይሆን በጌታ የተተከለች ድንኳን" ላለችው ሊቀ ካህናት ድንኳን ሊሠራ ለመነ። እዚህ አለ ሲሉት እዚያ ለሚገኘው ፣ በመንፈስ እየተነጠቀ አድራሻውን ለመወሰን ያስቸግር ለነበረው ኤልያስ እንዲቀመጥ ተስፋ አድርጎ ድንኳን ልሥራ አለ። እጅግ የተዋበችና በወርቅ በሐር ያጌጠችን የኦሪት ድንኳን ለሠራው ሙሴ ዓሣ አጥማጁ ጴጥሮስ ድንኳን ልሥራለት አለ። ሐዋርያት ነቢያቱን ሊያስተናግዱ የለመኑባት ደብረ ታቦር ፣ ሐዋርያት ነቢያቱን ለጌታ ቀኝ አዝማች ግራዝማች አድርገው በድንኳን አስቀምጠው እነርሱ እንደ ሎሌ ከደጅ ሊኖሩ የጠየቁ እነ ጴጥሮስ እንደምን ይደንቃሉ? ጴጥሮስ ሆይ አሁን በሰማይ ድንኳኖች ውስጥ እያገለገልህ ይሆንን? ደብረ ታቦርን አይተህ በደስታ "እንኑር" ያልከው ጴጥሮስ ሆይ የገነት ደስታ ስታይ ምን ተሰምቶህ ይሆን?

በእሳት ድንኳን ለመኖር ተስፋ የምናደርግ "በነቢያትና በሐዋርያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል" የተባልን እኛስ ምንኛ የታደልን ነን?

★ ★ ★

በታቦር ተራራ ላይ የጌታችን ልብስ እንደ ፀሐይ አበራ ፣ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ "ከፀሐይም በላይ ነው ፣ ፀሐይ አይቶ የወደቀ የለም የጌታችንን ልብስ ሲያዩ ግን የወደቁት ያበራው ከዚያ በላይ ስለሆነ ነው" ይላል።

ከጌታችን በዚያ ተራራ ከሙሴና ኤልያስ ጋር ነበረ። ሙሴ እንደምናውቀው ጽላቱን ተቀብሎ ሲወርድ ሕዝቡ "እባክህን ተሸፈንልን" ብለውት ፊቱን በመጎናጸፊያው ሸፍኖ ነበር። የሙሴ አምላክ ክርስቶስ ግን ደቀ መዛሙርቱ ሲወድቁ አይቶ በልብሱ እንዳይሸፈን ያበራው ፊቱ ብቻ ሳይሆን ልብሱም ነበር።

" አጣቢም በምድር ላይ እንደዚያ ሊያነጣው እስከማይችል በጣም ነጭ ሆነ" ማር 9: 3
የሚለው ቃል ምንኛ የሚደንቅ ነው። በምድር ላይ ያለ አጣቢ ቢፈትግ ቢታገል የዚያን ያህል ሊያነጻው የማይችለው ነጭ እንዴት ያለ ነው? መቼም ሁላችን የምናውቀው ነጭ ነገር ሁሉ በምድር ላይ ባለ አጣቢ የታጠበ ስለሆነ እንዲህ ነው ማለት አንችልም። ብቻ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በምድር ያሉ አጣቢዎች ከሚያነጡት በላይ ልብስን ማንጣት ይችላል።

ይህ ቃል በኃጢአት እድፍ ልብሳችን ላደፈ ሁሉ መጽናኛችን ነው።

መቼም የምድር አጣቢዎች አቅማቸው ውስን ነው።
ቆሽሸን ያዩን ሰዎች ብንታጠብም አያምኑንም ፣ ቢያጥቡልንም በኅሊናቸው የሚያስቀሩብን ቆሻሻ አለ።
በሰው ዓይን አንዴ ቆሽሸህ አትገኝ እንጂ ከተገኘህ መቼም ነጭ አትሆንም። አንተ ግን የደብረ ታቦሩ ብርሃን መድኃኔ ዓለምን ብቻ "እጠበኝ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ" በለው "ኃጢአታችሁ እንደ አለላ ብትሆን እንደ አመዳይ ትነጻለች፤ እንደ ደምም ብትቀላ እንደ ባዘቶ ትጠራለች። " ብሎ በገባው ቃል መሠረት ነጭ ያደርግሃል።

እርሱ ወዳለባት የቅድስት ቤተክርስቲያን ተራራ በንስሓ ከደረስክና በታቦር ያበራውን ብርሃኑን ካበራልህ ነጭ ትሆናለህ። ከዚያ "አጣቢ የማያነጻውን ያህል ትነጻለህ" ከአብ የባሕርይ ልጅ ከብርሃኑ ፀዳል ስትቀርብ አንተም በጥምቀት ያገኘኸው የጸጋ ልጅነትህ ያንጸባርቃል። ነጭ በሆንህ ጊዜ የሚያዩህ ሁሉ "በበጉ ደም ልብስህ መታጠቡን"ና ነጭ መሆኑን አይተው ይደነግጣሉ ፣ ሊሰሙህ ያልወደዱ ሁሉ ለባሕርይ ልጁ "የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት" ብሎ እንዳዘዘለት ለአንተም ጆሮ እንዲሠጡህ ያደርግልሃል።

አንተ ብቻ ከደብረ ታቦር አትቅር ፣ ካልሞትህ እንደ ኤልያስ ፈጥነህ ና ፣ በበደል ከሞትክም እንደሙሴ ተነሥተህ ና። ብቻ ወደ ደብረ ታቦር ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለመምጣት ተስፋ አትቁረጥ ፣ እንደ ሙሴ ትሞታለህ እንጂ ምድረ ርስትን አታይም ብትባል ፣ እንደ ኤልያስ ትኖራለህ እንጂ ሞትን አታይም ብትባል ብቻ አንተ ከደብረ ታቦር አትቅር።

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ

🍂 @finotehiwet 🍂
በ2013 ዓ.ም ማለትም ከ5 ዓመት በፊት በሰ/ት/ቤቱ ሕጻናት ክፍል የደብረ ታቦር በዓል ሲከበር የሚያሳይ ፎቶ

♡ ㅤ   ❍ㅤ      ⎙        ⌲
ˡᶦᵏᵉ  ᶜᵒᵐᵐᵉⁿᵗ   ˢᵃᵛᵉ   ˢʰᵃʳᵉ
ይወዳጁን
👇👇👇👇👇👇👇👇
https://linktr.ee/finotehiwot_sundayschool?utm_source=linktree_profile_share&ltsid=f62cf905-ffbd-4af4-bf12-2f29df393f8c