የጽርሐ ጽዮን ሐዋርያት ጎላ ቅዱስ ሚካኤል የፍኖተ ብርሃን ሰ/ት/ቤት (Official Channel)
2.58K subscribers
6.1K photos
67 videos
60 files
1.7K links
ይህ በጽ/ጽ/ሐ/ጎ/ቅ/ሚካኤል ቤ/ክ ፍ/ብ/ሰ/ት/ቤት እውቅና የተሰጠው የቴሌግራም ቻናል ነው።
Download Telegram
ቅድስት :-  ዕለቱ ‹‹ቅድስት›› ተብሎ የተሰየመበት ምክንያት ስለ ዕለተ ሰንበት እንዲሁም ስለ እግዚአብሔር አምላክ ፍጹም ቅድስና የሚያወሳ በመሆኑ ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክም ፍጥረታቱ የእርሱን ስም በማመስገን ይኖሩ ዘንድ ለቅድስና ሕይወት ፈጥሯቸዋልና በሰንበት እሑድ ክርስቲያኖች የቅድስና ተግባራትን ከሌላው ቀን አብዝተው ይፈጽማሉ፡፡ ዕለት ከተግባር፣ ስም ከክብር የተባበረባት ክብርት ሰንበት ቅድስት ስለሆነች ቅዱስ ያሬድ “ቅድስት” ብሎ ጠራት። ይኸውም የምትቀድስ፣ ከብራ የምታከብረን፣ አክብረናት የምንከብርባት በመሆኗ ነው።

«እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ» የሚለውን መለኮታዊ ቃል መሠረት በማድረግ፣ በጾም ወቅት በቅዱስ ስፍራ (ቤተክርስቲያን) ተገኝተን ራሳችንን እንድንቀድስ ስለሚያዝ ነው።“ዛቲ ዕለት እንተ ገብረ እግዚአብሔር ንትፈሣሕ ወንትሐሠይ ባቲ”  ትርጉም፡- “ይህች ዕለት እግዚአብሔር የሠራት ቀን  ናት፤ ሐሤትን እናድርግ፥ በእርስዋም ደስ ይበለን።”  

ሁልጊዜ በቤተ ክርስቲያን ተሰብሰቡ፤ ይልቁንም በዕለተ እሑድ፣ በዕለተ ቀዳሚት፣ በጌታ በዓላት ወደ ቤተ ክርስቲያን ተሰብሰቡ” በማለት አዘውናል፡፡

“እግዚአብሔርሰ ሰማያተ ገብረ::አሚን ወሠናይት ቅድሜሁ፣ ቅድሳት ወዕበየ ስብሐት ውስተ መቅደሱ፤
እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ፈጠረ፡፡ እምነትና በጎነት በፊቱ፣ ቅድስናና የክብር ገናናነት በመቅደሱ ውስጥ ናቸው፡፡”

ጾመን፣ ጸልየን ርስቱን እንድንወርስ የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምልጃ፤ የቅዱሳን በረከት ይጠብቀን።
ኪዳነ ምሕረት

የካቲት ዐሥራ ስድስት በዚችም ዕለት የክርስቲያን ወገኖች ሁሉም አምላክን ለወለደች ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዓልን ያደርጋሉ። በዚች ዕለት መታሰቢያዋን ለሚያደርግ ስሟን ለሚጠራ ለድኆችና ለችግረኞች እስከ ቀዝቃዛ ውኃ ለሚሰጥ የክብር ባለቤት ከሆነ ከተወደደ ልጅዋ ከጌታችንና ከመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የምሕረት ቃል ኪዳንን ተቀብላለችና።

ይህችም የከበረች እመቤታችን ልጅዋ ንጹሕ ሥጋዋን ተዋሕዶ ከብቻዋ ኃጢአት በቀር የሰውነትን ሥራ ፈጽሞ ስለእኛ መዳን ወዶ ያደረገውን መከራ ተቀብሎ ሙቶ ተነሥቶ ከዐረገና በአባቱ ቀኝ ከተቀመጠ በኋላ እርሷን እናቱን ማርያምን በደቀ መዝሙሩ ዮሐንስ ዘንድ ትቷት ነበር እነሆ ልጅሽ እርሱንም እነኋት እናትህ ብሎ አደራ እንዳስጠበቀው።

ከዚያንም ጊዜ ጀምራ እመቤታችን ማርያም ትጸልይ ዘንድ ያለ ማቋረጥ ወደ ልጅዋ መቃብር ሁል ጊዜ ስትሔድ ኖረች ይኸውም ጎልጎታ ነው።

አይሁድም በአዩዋት ጊዜ ቍጣንና ቅናትን ተመልተው በድንጊያ ሊወግሩዋት ወደዱ እግዚአብሔርም ከዓይናቸው ሠወራት ከዚህም በኋላ ዳግመኛ መጥታ በዚያ እንዳትጸልይ ተማክረው ከመቃብሩ ዘንድ ጠባቂዎችን አኖሩ እርሷ ግን በየዕለቱ መሔድን አላቋረጠችም ጠባቆችም አያይዋትም የልጅዋ የጌትነቱ መጋረጃ ሠውርዋታልና መላእክትም መጥተው ያገለግሏታል ጌታችንም ዘወትር ይጐበኛታል የምትሻውንም ይፈጽምላት ነበር።

ከዚህም በኋላ መላእክት ወደ ሰማይ አሳረጓትና የጻድቃንን ማደሪያዎች አሳዩዋት አብርሃም ይስሐቅ ያዕቆብም ወዳሉበት አደረሱዋት ከአዳም ጀምሮ እስከዚያ ዕለት በአካለ ነፍስ ያሉ አባቶች ሁሉ አንቺን ከሥጋችን ሥጋን ከዐፅማችን ዐፅምን ለፈጠረልን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን የአምላክ ልጅ ከአንቺ ሰው በመሆኑ በአንቺ ድኅነት አግኝተናል ከጥፋትም የሕይወት ወደብ ሆነሽልናልና እያሉ ሰገዱላት።

ከዚያም ወደ ተወደደ ልጅዋ የእሳት መጋረጃ ወደተተከለበት ወደ ጌትነቱ ዙፉን አደረሷት ጌታችንም እጇን ይዞ ወደ ውስጠኛው መጋረጃ አስገብቶ ከጌትነቱ ዙፋን ላይ አውጥቶ ከእርሱ ጋር አስቀመጣት ያዘጋጀላትንም ዐይን ያላየው ጆሮ ያልሰማው በሰው ልቡና ያልታሰበ ተድላ ደስታን ሁሉ ነገራት።

ከጌትነቱ ዙፋንም በታች የእስራኤል ንጉሥ አባቷ ዳዊትን የነቢያትና የመላእክት ማኀበር እንደ ግድግዳ ከበውት በመሰንቆ ሲያመሰግን አየችው እንዲህም ይላል ልጄ ስሚ በጆሮሽም አድምጪ ወገንሽን የአባትሽንም ወገን ርሺ ንጉሥ ደም ግባትሽን ወዷልና እርሱም ጌታሽ ነውና።

ዳግመኛም የሥቃይን ቦታ ያሳዩዋት ዘንድ መላእክት ከዚያ ወሰዷት ለሰይጣንና ለሠራዊቱ በእርሱ ጐዳና ለሚጓዙ ሁሉ ወደተዘጋጀ ወደጨለማው ዳርቻ አደረሷት እመቤታችን ማርያምም ወዮልኝ ወደዚያ እንዳይመጡ ለሰው ልጆች ማን በነገራቸው አለች መልአኩም እመቤቴ ቡርክት ማርያም ሆይ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ይኖራልና ለአንቺም ከአንቺ በኋላም በቃል ኪዳንሽ ለሚታመኑ አትፍሪ አላት ከዚህም በኋላ ወደ ቦታዋ መለሷት።

ከዚያንም ጊዜ ጀምራ እመቤታችን ድንግል ማርያም ስለ ኃጥአን እጅግ እያዘነች ኖረች እንደ ዛሬይቱም የካቲት ዐሥራ ስድስት ቀን በጎልጎታ ቦታ ቁማ ወደ ልጇ እንዲህ ብላ ለመነች ልጄ ሆይ በእግዚአብሔር አባትህ በክርስቶስ ስምህ ከአንተ ጋርም ህልው በሆነ አጽናኝ መንፈስ ቅዱስ አማፅንሃለሁ ዓለም ሁሉ ሊሸከምህ የማይችል ሲሆን ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በተሸከመችህ ማሕፀኔ አማፅንሃለሁ ልጄ ሆይ ያለ ሕማም ያለ ድካም ከእኔ በመውጣትህ በመወለድህ በአሳደጉህ ጡቶቼ በሳሙህ ከንፈሮቼ በአቀፋህ እጆቼ ከአንተ ጋር በተመላለሱ እግሮቼ አማፅንሃለሁ ። በውስጡ በተኛህበት በረት በተጠቀለልክበት ጨርቅ አማፅንሃለሁ የምወድህ ልጄ ሆይ በልቡናዬ ያለውን ሁሉ ትፈጽም ዘንድ የልመናዬን ቃል ሰምተህ ወደእኔ ትመጣ ዘንድ ወዳንተ ፈጽሜ እማልድሃለሁ።

የብርሃን እናቱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንዲህ ብላ በጸለየች ጊዜ እነሆ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወረደ ከእርሱም ጋር አእላፍት መላእክት አሉ በዙሪያውም ሁነው ያመሰግኑታል እርሱም እናቴ ማርያም ሆይ ምን ላድርግልሽ አላት እመቤታችንም ለተወዳጅ ልጅዋ እንዲህ ብላ መለሰችለት ልጄ ወዳጄ ሆይጌታዬና ፈጣሪዬ አለኝታዬና መጠጊያዬ በእናቴ ማሕፀንም ሳለሁ ባንተ ጸናሁ አንተም ጠበቅኸኝ ሁልጊዜም ስም አጠራሬ አንተ ነህ።

አሁንም ጸሎቴንና ልመናዬን ስማኝ ቃሌንም አድምጥ እኔ እናትህ እኔም አገልጋይህ የምለምንህ ይህ ነው መታሰቢያዬን ለሚያደርጉ በስሜ አቢያተ ክርስቲያን ለሚሠሩ ወይም የተራቆተውን ለሚያለብሱ የተራበውን ለሚያጠግቡ የተጠማውንም ለሚያጠጡ የታመመውን ለሚጐበኙ ያዘነውን ለሚያረጋጉ የተከዘውንም ደስ ለሚያሰኙ ወይም ምስጋናዬን ለሚጽፉ ልጆቹንም በስሜ ለሚሰይም በበዓሌም ቀን በማኅሌት ለሚያመሰግን አቤቱ ዐይን ያላየውን ጆሮ ያልሰማውን በሰውም ልቡና ያልታሰበውን በጎ ዋጋ ስጣቸው በአማላጅነቴም የሚታመነውን ሁሉ ከሲኦል ነጻ አድርገው ከአንተ ጋር የደረሰብኝን ረኃቡንና ጥማቱን መከራውን ሁሉ አስብ አለችው።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እንዳልሽው ይሁንልሽ የሰጠሁሽም ቃል ኪዳን እንዳይታበል በራሴ ማልኩልሽ አላት። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በእመቤታችን ድንግል ማርያም በጸሎቷ ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።

ማስታወሻ :- የእመቤታችን የቅድስት ኪዳነ ምሕረት የቃልኪዳን ታቦት በደብራችን በድርብነት ስለሚገኝ እለተ በዓሉ በታላቅ ድምቀት ይከበራል።
የእናታችን የቅድስት ኪዳነ ምሕረት  ዓመታዊ ክብረ በዓል በደብራችን በጽርሐ ጽዮን ሐዋርያትና ጎላ ቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክ በታላቅ ድምቀት ተከብሮ ዋለ ።

 እናታችን ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ከልጇ ከወዳጇ ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ቃል ኪዳን የተቀበለችበት የሰባቱ ኪዳናት ማኅተም የየካቲት ኪዳነ ምሕረት ዓመታዊ  ክብረ በዓል በደብራችን በጽርሐ ጽዮን ሐዋርያትና ጎላ ቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክ የደብራችን ዋና አስተዳዳሪ መልአከ ብርሃን አዕምሮ ምስጋናው እና ሌሎች የቤተክርስቲያናችን ሊቃውንት፣ የሰንበት ት/ት ቤት አገልጋዮችና በርካታ ምዕመናን በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተከብሮ ዋለ።

ይህ በጽ/ጽ/ሐ/ጎ/ቅ/ሚካኤል ቤ/ክ ፍ/ብ/ሰ/ት/ቤት እውቅና የተሰጠው የቴሌግራም ቻናል ነው።
https://t.me/finotebirhan12

የዩቲዩብ ቻናላችን
https://youtube.com/@finotebirhan12

የፌስቡክ ገጻችን https://www.facebook.com/Fbirhan?mibextid=2JQ9oc

የቲክቶክ አካውንታችን https://www.tiktok.com/@finotebirhan?_t=8i8eHwFI3Es&_r=1

የዌብሳይት ገጻችን
https://finotebirhan.com