የጽርሐ ጽዮን ሐዋርያት ጎላ ቅዱስ ሚካኤል የፍኖተ ብርሃን ሰ/ት/ቤት (Official Channel)
2.58K subscribers
6.1K photos
67 videos
60 files
1.7K links
ይህ በጽ/ጽ/ሐ/ጎ/ቅ/ሚካኤል ቤ/ክ ፍ/ብ/ሰ/ት/ቤት እውቅና የተሰጠው የቴሌግራም ቻናል ነው።
Download Telegram
🔴 ስንክሳር#ጥር_9

#አባ_አብርሃም_ገዳማዊ

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ጥር ዘጠኝ በዚህች ቀን የከበረ አባት አባ አብርሃም ዐረፈ፡፡ የዚህም ቅዱስ ሰው አባቱ ድኆችን የሚወዳቸውና የሚራራላቸው ነው። በዘመኑም በግብጽ አገር ታላቅ ረሀብ ሆነ እጅግ ባለጸጋ ነበርና ከደግነቱና ከታማኝነቱ ብዛት የተነሣ እርሱ በአለበት አገር ዙሪያ ያሉ አገሮች ሁሉም የምድራቸው ፍሬ በእርሱ ዘንድ አደራ ያስቀምጡ ነበር ረሀቡም በጸና ጊዜ በእርሱ ዘንድ በአደራ የተቀመጠውን እህል ሁሉንም ለድኆች ሰጠ እግዚአብሔርም ስለ ምድራቸው ፍሬ ሁሉንም ክፉ ቃልን እንዳይናገሩት አደረጋቸው። በእርሱ ዘንድ ያኖሩትን የምድራቸውን ፍሬ ሽተው ወደርሱ በሚልኩ ጊዜ ተነሥቶ ወደርሳቸው ይሔዳል እነርሱም በየራሳቸው ለያንዳንዱ የምድራቸው ፍሬ እንደደረሳቸው አድርገው ይጽፉለታል እንጂ ምንም ምን አይናገሩትም።

የዚህም ቅዱስ እናት እግዚአብሔርን የምትፈራ ምእመን ናት ሰይጣንም ቀናባት በአንድ ክፉ ሰው ልቡና አድሮ በፋርስ ሰዎች ዘንድ ነገር ሠራባት እነርሱም ማርከው ወደ አገራቸው ወሰድዋት በአንዲት ሌሊትም ራዕይን አየች ያ ነገር የሠራባት ሰው በሲኦል ውስጥ በእሳት ሰንሰለት ታሥሮ "እግዚአብሔር ያደረገልሽን ተመለከትሽን ነገር የሠራብሽን ያንን ሰው ተበቅሎታልና" ይላታል እርሷ ግን "ጌታዬ ሆይ መከራና ሥቃይ በርሱ ላይ እንዲደርስ አልሻም" ትላለች ያ የሚያሳያትም "አንቺ ግን ወደ አገርሽ ተመልሰሽ በቤትሽ ትኖሪ ዘንድ አለሽ" ይላታል እንዲሁም ሆነ።

ባሏም በሞተ ጊዜ አብርሃም ድኃ አደግ ሆነ እርሷም እናቱ ሚስት ልታጋባው አሰበች እርሱ ግን ይህን አልወደደም እናቱም እጅግ ደስ ተሰኘችበት። ወደ ገዳም ሒዶ ሊመነኵስ በፈለገ ጊዜ እናቱ ልትሸኘው ወጣች እጆቿንም ወደ ሰማይ አንሥታ በመጸለይ ልጇን ወደ እግዚአብሔር አደራ አስጠበቀች። "አቤቱ ጌታዬ ይህን ቊርባንን አድርገህ ተቀበለኝ" አለች።

በዚያንም ጊዜ አባ አብርሃም ሔደ በአስቄጥስ በረሀ ውስጥ ተጒዞ በአባ ዮሐንስ አበ ምኔትነት ዘመን ወደ አባ መቃርስ ገዳም ደረሰ ወደርሱም ወደ አባ ዮሐንስ ገባ ተወዳጅ ልጅንም ሆነለት። በጎ ተጋድሎንም ጀመረ በአንዲት ሌሊትም ራዕይን አየ የበዓቱ ጣሪያ ተሰነጠቀ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በኪሩቤል ሠረገላ ተቀምጦ ወደርሱ ሲወርድ አየው ኪሩቤልም ያመሰግኑት ነበር እርሱም ፈርቶ ተንቀጠቀጠ ፈጥኖም ሰገደ ጌታችንም ባረከውና በታላቅ ክብር ወደ ሰማይ ዐረገ። ጌታችንም የወረደባት በቤቱ ጣሪያ የተሠነጠቀችው ምልክት ሁና እስከ ዛሬ በመታሰቢያነት አለች እርሷም ለመንፈሳዊ አባቱ ለአበ ምኔቱ አባ ዮሐንስ መኖሪያ ቅርብ ናት እርሷም በግቢግ ትባላለች። የእግዚአብሔርም መልአክ ሁል ጊዜ ይጐበኘዋል ብዙ ምሥጢራትንም ይገልጥለታል ያስገነዝበዋልም።

ከዚህም በኋላ አባ አብርሃም ወደ ደብረ ኀርዮን ሔደ በዚያም አባ ገዐርጊን አግኝቶት ወደ አስቄጥስ ገዳም ከእርሱ ጋር ወሰደውና እስከ ዕረፍታቸው ጊዜ በዚያች በዓት ኖሩ።

አበ ምኔቱ አባ ዮሐንስም በዐረፈ ጊዜ በአባ አብርሃም ላይ ሰይጣን ታላቅ ደዌ አምጥቶበት ዐሥራ ስምንት ዓመት በዚያ ደዌ ውስጥ ኖረ ዕረፍቱም በቀረበ ጊዜ የጌታችንን ሥጋና ደም ያቀብሉት ዘንድ ወንድሞችን ለመናቸው ከተቀበለም በኋላ መንፈሳዊ አባቱ አባ ዮሐንስ ወደርሱ መጥቶ "እነሆ ወደ ታላቅ ሠርግ እግዚአብሔር ጠርቶሃል" አለው። ከዚህም በኋላ ዕድሜው ሰማንያ ዓመት ሁኖት በሰላም ዐረፈ፡፡ በዓታቸውም እስከ ዛሬ የታወቀች ሁና ትኖራለች።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር)
https://t.me/finotebirhan12
ነገ የከተራ በዓል ለበዓሉ ተመርጣችሁ ዝማሬ የምታቀርቡ ወጣት፣ ማዕከላውያንና ሕጻናተ አባላቶቻችን ከቀኑ 6:30 የሰንበት ት/ቤታችን አዳራሽ ሁላችንም እንገኝ ታቦተ ሕጉ ከመንበሩ በግዜ ተነስቶ ወደ ጥምቀተ ባሕሩ በግዜ እንዲደርስ ስለታሰበ ላልሰሙት በማሰማት ከቀኑ 6:30 እንድንገኝ በእግዚአብሔር ስም እንጠይቃለን
መልካም ዜና ለሰንበት ት/ቤታችን አባላት በሙሉ.... በከተራ ክብረ በዓል ፈሸቶ የተነሳችሁ እንዲሁም በጋራ እና በግል ለመነሳት የምትፈልጉ አባላት በጥምቀትና በቃና ዘገሊላ እለት ፍቶ መነሳት የምትፈልጉ ለ1ፎቶ 10 ብር ብቻ በመክፈል ሶፍት ኮፒ መውሰድ ትችላላችሁ
ጥር 12 እንደ ቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ በጥምቀት በዓል ማግስት የቃና ዘገሊላ በዓል ይከበራል በዓሉ ቃና ዘገሊላ የሚል ስያሜ ያገኝው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የገሊላ ሀገር ክፍል በምትሆን ቃና በተባለችው ቦታ በፈፀመው መነሻነት ነው።

የቃና ዘገሊላ ጥንተ ነገሩ ወይም ታሪኩ የተፈፀመው የካቲት 23 ቀን ነው። ነገር ግን አባቶቻችን የውሃን በዓል ከውኃ በዓል ጋር ለማክበር ብለው የየካቲቱን በዓል ወደ ጥር 12 አምጥተውታል። ይኽም ውኃ ወደ ወይን የተለወጠበትን በዓል ከጌታ ጥምቀት በዓል ጋር ለማስተሳሰር ነው።

በመሆኑም የቃና ዘገሊላ በዓል ጥር 12 ይከበራል
#መልካም_በዓል
የጌታችንና የአምላካችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል ቅዱስ ዮሐንስ እንደጻፈው...

ምዕራፍ ፪÷፩-፲፩


በሦስተኛውም ቀን በገሊላ ቃና ሰርግ ነበረ፥ የኢየሱስም እናት በዚያ ነበረች፤


ኢየሱስም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ታደሙ።


የወይን ጠጅም ባለቀ ጊዜ የኢየሱስ እናት፦ የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም አለችው።


ኢየሱስም፦ አንቺ ሴት፥ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም አላት።


እናቱም ለአገልጋዮቹ፦ የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ አለቻቸው።


አይሁድም እንደሚያደርጉት የማንጻት ልማድ ስድስት የድንጋይ ጋኖች በዚያ ተቀምጠው ነበር፥ እያንዳንዳቸውም ሁለት ወይም ሦስት እንስራ ይይዙ ነበር።


ኢየሱስም፦ ጋኖቹን ውኃ ሙሉአቸው አላቸው። እስከ አፋቸውም ሙሉአቸው አላቸው። እስከ አፋቸውም ሞሉአቸው።


አሁን ቀድታችሁ ለአሳዳሪው ስጡት አላቸው፤ ሰጡትም።


አሳዳሪውም የወይን ጠጅ የሆነውን ውሃ በቀመሰ ጊዜ ከወዴት እንደ መጣ አላወቀም፤ ውኃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር፤ አሳዳሪው ሙሽራውን ጠርቶ፦


ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል፥ ከሰከሩም በኋላ መናኛውን፤ አንተስ መልካሙን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቆይተሃል አለው።

፲፩
ኢየሱስ ይህን የምልክቶች መጀመሪያ በገሊላ ቃና አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ።
🔴#ጥር_13 በዚች ቀን #አቡነ_ዘርዓ_ቡሩክ ኢትዮዽያዊ አረፉ፣ #ቅዱሳን_ሰባቱ_ደቂቅ አረፉ፣ #አባ_ነካሮ አረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባ_ነካሮ

በዚችም ቀን አባ ነካሮ አረፈ ይህም ቅዱስ ሰው ሳያውቀው በስውር የሚጋደል ሆነ እርሱም ከምንጣፉ በታች እሾህ ይጎዘጉዛል ጤና አግኝቶ እንዳይተኛ ነው በቀንና በሌሊትም ለፀሎት ይተጋ ነበር።

ከትሑትነቱም የተነሳ የበር ጠባቂ አደረጉት ።በዚያም ገዳም በመንፈስ ቅዱስ የተሰወሩ ነገሮችን የሚያይ ባህታዊ መነኮስ አለ በአንዲትም ሌሊት በህልሙ በከፍታ ቦታ ላይ ቆሞ አየ ከበታቹም ፍሬው በየአይነቱ የሆነ አትክልት አለ ወንዞችም ከበውታል አባ ነካሮም በመካከላቸው ሆኖ በወዲያና በወዲህ ያጠጣቸው ነበር ።

ያ መነኰስም ወንድሜ ነካሮ ሆይ ይህ አትክልት የማን ነው አለው አባ ነካሮም እኔ የተከልኃት ናት ብሎ መለሰለት መነኩሴውም ከፍሬዋ ትሰጠኝ ዘንድ እሻለሁ አለው አባ ነካሮም ሶስት የሮማን ፍሬ ቆርጦ ሰጠው በልብሱም ቋጠረው።

በነቃም ጊዜ እነዚያን የሮማን ፍሬዎች አገኛቸው ወዲያውኑ ወደ አባ ነካሮ ሄደ ከበር ቆሞ አገኘውና ወንድሜ ነካሮ ሆይ በዚች ሌሊት አይተኸኛልን አለው እርሱም አዎን አይቼሀለሁ ሶስት የሮማን ፍሬዎችን ሰጥቼህ የለምን አለው። በዚያንም ጊዜ ያ መነኩሴ ወደ ገዳሙ ሄዶ የሆነውን ሁሉ ለአበምኔቱና ለመነኩሳቱ ነገራቸው እነዚያንም የሮማን ፍሬዎች አሳያቸው መነኰሳቱም ከአባ ነካሮ ቅድስና የተነሳ አደነቁ ያን ጊዜም የበጋ ወራት ነበርና የሮማንም ጊዜው አልነበረምና።

በዝቅተኛ ማእረግ ላይ ስለአደረጉት መነኮሳቱ አዘኑ በከፍተኛም ማእረግ ሊያደርጉት አዘኑ በከፍተኛም ማእረግ ሊያደርጉት ሽተው ወደርሱ በሄዱ ጊዜ አጡት ታላቅ ኀዘንንም አዘኑ ከዚህም በኃላ በዚች እለት እንዳረፈ መፃተኞች ነገሩአቸው።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ለዘለዓለሙ ከእኛ ጋር ትኑር አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር እና #መዝገበ_ቅዱሳን)
https://t.me/finotebirhan12
🔴 ስንክሳር#ጥር_14

በዚህች ቀን #ጻድቁ_አቡነ_አረጋዊ (ዘሚካኤል) የተወለዱበት እና ወደ ደብረ ዳሞ የወጡበት ነው፣ የከበረችና የተመረጠች #ቅድስት_ምህራኤል በሰማእትነት አረፈች፣ በገድል የተጠመደ የከበረ #ቅዱስ_አባ_አርከሌድስ አረፈ፣ የከበረች #ቅድስት_እምራይስ በሰማእትነት አረፈች።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ጻድቁ_አቡነ_አረጋዊ (ዘሚካኤል)

ጥር አሥራ አራት በዚህች ቀን ታላቁና የከበረው አባታችን አቡነ አረጋዊ (ዘሚካኤል) የተወለዱበት እና ወደ ደብረ ዳሞ የወጡበት ነው።

እኚህ አባት ከ9 ቅዱሳን አባቶች አንዱ ሲሆኑ አባታቸው ይስሐቅ የሮም ንጉስ ነበሩ፡፡ እናታቸው ንግስት እደና ይባሉ ነበር፡፡ የመጀመሪያ ስማቸው ዘሚካኤል ነው፡፡ ጥበብ መንፈሳ ሲማሩ አድገው ወደ እስክንድርያ ገዳም ገቡ፡፡ አበምኔቱ አባ ጳኩሚስ በፈቃደ እግዚአብሔር የመጡ መሆናቸውን አውቀው መዓረገ ምንኩስና ሰጥተዋቸዋል፡፡

የንጉሳዊ የቅንጦት ኑሮ ንቀው ትተው ገዳም ገብተው በምንኩስና ተወስነዋል፡፡ አባታችን በተጋድሏቸውም ከአባ እንጦንስ፣ ከአባ ጳውሊ እና ከአባ መቃርስ ቀጥሎ በአራተኛ ማዕረግ አበ መነኮሳት ሆነው ተመርጠዋል።

በገዳመ ዳውናስ 7 ዓመት ከቆዩ በኋላ ወደ ሮም ተመልሰው ሲያስተምሩ የሀገራችን ኢትዮጵያን ዜና ሰምተው ለመምጣት በ480 ዓ.ም ከአባ ፍሬምናጦስ በኋላ መንገድ ጀመሩ፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም በክንፉ ተሸክሞ አክሱም አድርሷቸዋል፡፡

ተመልሰውም ሄደው ስለ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ መስክረዋል፡፡ ሐዋርያ ሳይላክላት በሃይማኖት በምግባር ጸንታ ትኖራለች ብለው ለሰባቱ ዘመዶቻቸው አበው መነኮሳት ነገሯቸው፡፡ ስምንቱም ጓዛቸውን ጠቅልለው በሮም ነግሶ የነበሩ ይስሐቅን (አባ ገሪማን) ጨምረው ንጉስ አልአሜዳ በነገሰ በአምስተኛ ዓመት ማለትም በ480 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ዘጠኝ ሆነው መጥተዋል፡፡

አባ አረጋዊ እናታቸው ቅድስት እድናን ደቀ መዝሙራቸውን ማትያስን አስከትለው እግረ መንገዳቸውን እያስተማሩና ድውያንን እየፈወሱ ደብረ ዳሞ ደረሰዋል፡፡

ከእግረ ደብር ሆነው አሁን ይህን ተራራ በምን ልወጣው እችላለሁ እያሉ ሲያወጡ ሲያወርዱ በንግግሩ ሐሰት የሌለበት አምላካችን በነቢዩ ዳዊት ላይ አድሮ በመዝሙር 90/91፥11-16 ላይ “በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና፤ እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሡሃል። በተኵላና በእባብ ላይ ትጫማለህ፤ አንበሳውንና ዘንዶውን ትረግጣለህ። እንዳለው የታዘዘ ዘንዶ መጥቶ ስደሳ ክንድ በሚያህል ጅራቱ ጠምጥሞ ቅዱስ ሚካኤል ሰይፈ እሳት ይዞ እየጠበቃቸው ከተራራው አናት አድርሷቸዋል፡፡

ወዲያው ሃሌ ሉያ ለአብ ሃሌ ሉያ ለወልድ ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ ብለው አመስግነዋል፡፡ ቦታውም ደብረ ሃሌ ሉያ ተብሏል፡፡ በዚያ ዕለት ግማሽ ህብስት በልተው ጠገቡ፤ ከዚያ በኋላ ግን ምድራዊ ሕብስት አልተመገቡም፡፡ በሰንበተ ክርስታያን ከቅዳሴ በኋላ ሕብስተ ሰማያዊ እያመጡላቸው ይመገቡ ነበር እንጂ፡፡ ኋላም ዜና ጽድቃቸውን ሰምተው ከስድስት ሺህ ያላነሱ ደቀ መዛሙርት ተሰብስበውላቸዋል፡፡

ዘጠና ዘጠኝ አመት ሲሞላቸው ጌታ በመንፈቀ ሌሊት ተገልጾ ምድራዊ መንግስትህን ትተህ ስላገለገልከኝ ህልፈት ሽረት የሌለባት ሰማያዊ መንግስቴን አወርሰሃለሁ ብሎ ቃልኪዳን ሰጣቸው፡፡ በስምህ የተማጸነውን እስከ አስራ አምስት ትውልድ ድረስ እምርልሃለሁ አንተም ከሞት ገጽ ትሰወራለህ ብሎ ተስፋቸውን ነገራቸው፡፡ እሳቸው መነኮሳቱን ሰብስበው ከእንግዲህ በሥጋ አታዩኝም ብለው ነግረዋቸው አበምኔት ሾመውላቸው በደብረ ዳሞ ተራራ በስተምስራቅ አቅጣጫ ተሰውረዋል፡፡

አምላከ ቅዱሳን ለቅዱሳኑ ካደለው ፍቅራቸው ለእኛም አይንሳን:: በረከታቸውንም ያብዛልን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር_እና_ጥቅምት)
https://t.me/finotebirhan12
🌑 ሀዘን
የመምህር ተስፋዬ ተሾመ አባት አርፈዋል ሥርዓተ ቀብራቸው ገላን ሳሎ ጊዮርጊስ ቤ/ክ ከቀኑ 6ሰዓት ላይ ይፈፀማል የምንችል አባላት በመገኝት የመምህራችን ሀዘን ተካፋይ እንሁን ለመምህራችንም መጽናናቱን ይስጥልን
🔴 ስንክሳር#ጥር_15

ጥር 15 በዚህች ዕለት የከበረ ሕፃን #ቅዱስ_ቂርቆስና_ቅድስት_ኢየሉጣ በሰማዕትነት አረፉ፣ #ነብዩ_ቅዱስ_አብድዩ አረፈ፣ በሶርያ ክርስቲያን ወገኖች #የቅዱስ_ጎርጎርዮስን የዕረፍቱን መታሰቢያ በዓል ያከብራሉ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ጎርጎርዮስ_ዘኑሲስ

በዚህችም ቀን ዳግመኛ በሶርያ አገር ያሉ የክርስቲያን ወገኖች የቅዱስ ጎርጎርዮስን የዕረፍቱን መታሰቢያ በዓል ያከብራሉ። ይህም አባት በነፍስ በሥጋ በበጎ ሥራ ሁሉ ከወላጆቹ ጋር ፍጹም ነው። እርሱ እግዚአብሔርን መፍራትንና ትምህርቶችን ተምሮ ዐውቋልና የቋንቋም ትምህርት እጅግ የሚያውቅ የዮናናውያንንም ቋንቋ የሚያነብና የሚተረጒም ለቀና ሃይማኖትም የሚቀና ሆነ በውስጡም በጎ ሥራ በጎ ጠባይ ተፈጸመለት ኑሲስ በምትባል አገርም ላይ ሳይወድ በግድ መርጠው ኤጲስቆጶስነት ሾሙት እርሷም ደሴት ናት የእግዚአብሔርንም መንጋዎች ጠበቀ በትምህርቱና በድርሰቶቹም ልቡናቸውን ብሩህ አደረገ የብሉያትንና የሐዲሳትንም መጻሕፍት ተረጐመ።

ጳጳስ ሁኖ ስለነበረው ስለ ከሀዲው መቅዶንዮስ በንጉሥ ቴዎዶስዮስ ዘመን በቊስጥንጥንያ ከተማ የመቶ ሃምሳ ኤጲስቆጶሳት የአንድነት ስብሰባ በሆነ ጊዜ ይህ ጎርጎርዮስ ከአባቶች ኤጲስቆጶሳት ጋር ሁኖ የሰባልዮስን ወገኖች መቅዶንዮስንና አቡሊናርዮስን ተከራከራቸው መልስ አሳጥቶም አሳፈራቸው። ስሕተታቸውንም ገለጠ። ይህም የካቲት አንድ ቀን ተጽፎአል የእነዚህንም ክህደት አስወገደ በቃሉ ሰይፍነትም የንባባቸውን የስሕተት ሐረግ ቆራርጦ አጠፋ ከተሰበሰቡትም ጋር በሰላም ተመለሰ እነርሱ በድል አድራጊነት እነዚያም ከሀድያን በኀፍረት ሁነው ተመለሱ ።

ወደ መልካም እርጅና ደርሶ እግዚአብሔርንም ደስ አሰኝቶ አገልገሎ በሰላም አረፈ እነሆ በዚህ ወር ጥር ሃያ አንድ ቀን ከገድሉ ጥቂት ጽፈናል ይኸውም በግብጻውያን ዕረፍቱ ነው።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር)
https://t.me/finotebirhan12
🔴 ስንክሳር#ጥር_16

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ጥር ዐሥራ ስድስት በዚህች ቀን የከበረ #ቅዱስ_ፊላታዎስ በሰማዕትነት ሞተ፣ የከበረ አባት ተጋዳይ የሆነ #ቅዱስ_ጰላድዮስ አረፈ፣ የከበረ አባት #አባ_ዮሐንስ አረፈ፣ የሶሪያ ሰው ሊቅ #ማር_ዳንኤል አረፈ፡፡

#ማር_ዳንኤል_ሶርያዊ

በዚህችም ዕለት ዓምድ ከሚባል አገር የሶሪያ ሰው ሊቅ ዳንኤል አረፈ የዚህም ቅዱስ አባቱ በወርቅና በብር ባለጸጋ የሆነ ነው። አባቱም በሞተ ጊዜ የሀገረ ዓምድ ጳጳስ አባ ዲዮናስዮስ ይህን ቅዱስ አሳደገው የቤተ ክርስቲያንንም ትምርት አስተማረው ከዚህም በኋላ ዲቁና ቅስና ሾመው የምንኲስና ልብስንም አለበሰው ሀብተ ፈውስም እስከተሰጠው ድረስ ከሰንበት እስከ ሰንበት ሳይበላ በጾም በጸሎት ጸንቶ ኖረ።

ከዚህም በኋላ የሴቶችን ፊት እንዳያይ ፈጽሞ ስዕለት አደረገ እናቱም ወሬውን በሰማች ጊዜ ወደርሱ መጣች ታየውም ዘንድ ላከችበት እርሱም የሴቶችን ፊት እንዳላይ ስዕለትን ተስያለሁ አላት። እርሷም እኔ እናትህ አይደለሁምን እንዴት እንደ ሌሎች ሴቶች ታስመስለኛለህ አለችው እምቢ በአላትም ጊዜ ክንብንቧን ገልጣ ሁለት ሴቶች አንድ ልብስ ለብሰው እያዩህ ሲጠቃቀሱብህ እግዚአብሔር ያሳየኝ ብላ ረገመችው።

ከጥቂት ቀንም በኋላ አንድ ምእመን ሰው ለሊቅ ዳንኤል ሦስት መቶ የወርቅ ዲናር ወሰደለት በማታም ጊዜ ከሊቅ ዳንኤል ደጃፍ ሲደርስ ከእርሱ ጋር ያለ ወዳጁ ስለ ገንዘብ ፍቅር በላዩ ተነሥቶ ገደለው። ስለ ሟቹም የዓምድ ንጉሥ በሰማ ጊዜ አባ ዳንኤልን ያቀርቡት ዘንድ አዘዘ በውሽባ ቤት ያሉ ሁለት ሴቶች የአባ ዳንኤልን መምጣት ወሬ በሰሙ ጊዜ ከችኮላቸው ብዛት የተነሣ ያዩት ዘንድ አንድ ልብስ ለብሰው ወጡ አባ ዳንኤልም እናቱ የተናገረችው ስለደረሰበት ፈገግ ብሎ ሣቀ።

ንጉሡም ስለ ሞተው ሰው አባ ዳንኤልን በመረመረው ጊዜ እኔ አልገደልሁትም ነገር ግን የገደለውን ራሱ ይናገር አለ። በዚያንም ጊዜ ሟቹ በአባ ዳንኤል ጸሎት ተነስቶ ገዳዩን ተናገረ ይህንንም ድንቅ ተአምር ንጉሡና ሕዝቡ ሁሉ አይተው በአባ ዳንኤል ፊት ሰገዱ። በቅዱሳኑ ላይ ድንቅ ሥራ የሚሠራ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት።

ከዚህም በኋላ ለአባ ዳንኤል እጅ መንሻ ንጉሡ ብዙ ወርቅን አመጣ አባ ዳንኤልም ከርሱ መቀበልን እምቢ ባለ ጊዜ ንጉሥ ገዳምን ሠራለትና ብዙ መነኰሳት ተሰበሰቡ። ወደ መልካም ሽምግልናም በደረሰ ጊዜ ጥቂት ታመመና በሰላም አረፈ፡፡

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር)
https://t.me/finotebirhan12
#ጥር_17

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

#ቅዱስ_መክሲሞስ እና #ቅዱስ_ዱማቴዎስ

ጥር ዐሥራ ሰባት በዚህች ዕለት ለለውንድዮስ ለሮም ንጉስ ልጆቹ የሆኑ የከበሩና የተመሰገኑ መክሲሞስና ዱማቴዎስ መታሰቢያቸው ሆነ።ይህም ንጉስ ሃይማኖቱ የቀና እግዚአብሔርንም የሚፈራ በእውነትም የቀና ፍርድን የሚፈርድ ነበር ስለዚህም እሊህና ሁለት ቅዱሳን እግዚአብሔር ሰጠው እነርሱም ከታናሽነታቸው ጀምሮ በንጽህና እንደ እግዚአብሔር መላእክት ሆኑ።

ትሕትናን ፈሪሀ እግዚአብሔርን በማስተማር አሳደጋቸው የሚጾሙና የሚፀልዩ በቀንና በሌሊትም የብሉይና የሀዲስ መፃህፍቶችን የሚያነቡ ሆኑ። ከዚህም በኃላ ይህን አለም ይተውት ዘንድ የመላእከትንም ልብስ ይለብሱ ዘንድ እርሷም የከበረች የምንኩስና ልብስ ናት ከዚያም ሐሳብ መጣባቸው ሀይማኖታቸው የቀና ሶስት መቶ አስራ ስምንት አባቶች ወደ ተሰበሰቡባት ወደ ኒቅያ ሂደው ይፀልዩ ዘንድ እንዲአስናብታቸው ለአባታቸው ምክንያት አቀረቡ።

ይህንንም ከርሳቸው በሰማ ጊዜ እጅግ ደስ አለው ከብዙ አገልጋዮችና ከብዙ ሰራዊት ጋር አሰናበታቸው ከኒቅያ አገርም በደረሱ ጊዜ ከከበረ ቦታ በረከትን ተቀበሉ ሰራዊቱንም ወደ ንጉስ አባታቸው ጌታችን ንጉሥ ሆይ እኛ ከዚህ ጥቂት ቀን መቆየት እንሻለን ከሚል ጽሑፍ ጋር ጽፈው ላኩ።

ከዚህም በኃላ ለአንድ ፃድቅ መነኮስ ሐሳባቸውን ገለጡ እንዲህም አሉት ከአንተ ዘንድ የምንኩስናን ልብስ እንድንለብስ እንሻለን እርሱም እኔ ከንጉስ አባታችሁ የተነሳ እፈራለሁ ነገር ግን ወደ ሶሪያ ሂዱ ስሙ አጋብዮስ የሚባል ከዚያ ሀይማኖቱ የቀና ካህን ደግ መነኮስ አለ አላቸው። ይህንንም ሲላቸው ምክሩን ተቀብለው ወደ ሶሪያ ተጉዘው ወደ ቅዱስ አባ አጋብዮስ ደርሰው ኀሳባቸውን ገለጡለት እርሱም ተቀብሎ የምንኩስና ልብስን አለበሳቸው እስከሚአርፍበትም ቀን ከእርሱ ዘንድ ኖሩ።

ከዕረፍቱም አስቀድሞ ያየውን ራእይ ነገራቸው ታላቁ አባ መቃርስ ወደርሱ እንደመጣና ልጆችህ መክሲሞስና ዱማቴዎስ ለኔ ልጆቼ ይሆኑኝ ዘንድ ወደ እኔ ወደ አስቄጥስ ገዳም እንዲመጡ ከመሞቴ በፊት እዘዛቸው አለው።

ዳግመኛም እንዲህ አላቸው ልጆቹ እኔ ይህን ሰው አባ መቃርስን በስጋው አየው ዘንድ እመኝ ነበር እነሆ በመንፈስ አየሁት እናንተም ከሞትኩ በኃላ ወደርሱ ሒዱ።

ከአረፈም በኃላ አልሄዱም በዚያ በሶሪያ አገር ኖሩ እንጂ እግዚአብሔርም ሀብተ ፈውስ ሰጥቷቸው በሽተኞችን የሚፈውሱ ሆኑ ወሬያቸውም በሀገሮች ሁሉ ተሰማ በባህርና በየብስ ከሚነግዱ ነጋዴያንም የመርከብ መዛነቢያቸውን መስራት ተምረው ከድካም ዋጋቸው በየጥቂቱ የሚመገቡና የተረፈውን ለድሆችና ለችግረኞች የሚሰጡ ሆኑ።

እግዚአብሔርም በእጆቻቸው ከሚሰራቸው ድንቆች ተአምራቶች የተነሳ የቅዱሳን መክሲሞስንና ዱማቴዎስን ስም መናፍስት ርኩሳን በሚሰሙ ጌዜ ከሰዎች ወጥተው ይሻሻሉ ሰዎቹም ያን ጊዜ በጌታ ኃይል ይድናሉ ጤነኞችም ይሆናሉ።

እጅግ ታላቅ የሆነ በጎዳና አጠገብ የሚኖር ከይሲ ነበር ብዙዎች ሰዎች ሰዎችንም አጥፍቷል የአገር ሰዎችም ወደ ከበሩ መክሶሞስና ዱማቴዎስ መጥተው ከዚያ ከይሲ ያድኗቸው ዘንድ ለመኗቸው አባ መክሲሞስም ክርታስ አንስቶ እንዲህ ብሎ ፃፈ የብፁእ መቃርዮስ አምላክ በሆነ መንፈስ ቅዱስንም በለበሰ በአባታችን በአጋብዮስ አምላክ በህያው እግዚአብሔር አካላዊ ቃል በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይህ ደብዳቤ ከዋሻህ ደጅ ቢደርስ አንተ ወጥተህ ሙት የሰማይ ወፎችም ይብሉህ።

አንድ ሰውም ያቺን ደብደቤ ተቀበሎ ሄደ በዚያም የዘንዶ ዋሻ ደጃፍ አኖራት በዚያንም ጊዜ ዘንዶዉ ወጥቶ ሞተ የሰማይ ወፎችም በሉት ህዝቦችም ሁሉ እጅግ አደነቁ እግዚአብሄርንም አመሰገኑት የክብር ባለቤት ጌታችንም በእሊህ ቅዱሳን በመክሲሞስና በዱማቴዎስ እጆች ብዙ ድንቆች ተአምራቶችን አደረገ።

በአንዲትም ዕለት ከአባታቸው መኳንንቶች አንዱ ወደ ባህር ዳርቻ ደረሰ ከመርከቦችም በአንዱ መርከብ መዛገቢያ ላይ መክሲሞስና ዱማቴዎስ የሚል ፅሁፍ በአየ ጊዜ የመርከቡን ሹም ጠየቀው እርሱም እንዲህ አለው በፀሎታቸው ከስጥመት እግዚአብሔር ያድነኝ ዘንድ የእሊህን ሁለት ወንድማማቾች የከበሩ መነኮሳት ስማቸውን በመርከቤ ላይ ፃፍኩ መኮንኑም መልካቸው ምን ይመስላል አለው እርሱም የመልካቸውን ምልክት ነገረው የንጉሱ ልጆች እንደሆኑ አውቆ ያን ነጋዴ ወደ ንጉስ አባታቸው አደረሰው።

ንጉሡም ጠየቀው ነጋዴውም የመልካቸውን አምሳል አስረዳው ንጉሡም ልጆቹ እንደሆኑ በተረዳ ጊዜ እናታቸውንና እኅታቸውን ከብዙ ሠራዊት ጋር ወደነርሱ ላከ ደርሰውም በአዩአቸው ጊዜ ጩኸው አለቀሱ እናታቸውም ወደ ንጉስ አባታቸው ከእርሷ ጋር ይመጡ ዘንድ ለመነቻቸው።

እነርሱም ራሳችንን ስእለት አድርገን ለእግዚአብሔር ሰጥተናልና ቃል ኪዳናችንን ማፍረስ አይቻለንም ነገር ግን ሄጄ ለአንቺም ለአባታችንም ከመከራ ሁሉ እግዚአብሔር ያድናችሁ ዘንድ እንፀልይላችኋለን በዚህም አነጋገር አረጋጓት በመለየቷም ፈፅማ እያዘነች ተመለሰች።

ወደ ንጉሱም በደረሰች ጊዜ ከእነርሱ የሆነውን ነገረችው ንጉሱም ለሚስቱና ለባለሟሉቹ እንዲህ አለ በእግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ የሕይወት ድልብ ይሆኑን ዘንድ እንተዋቸው ፀሎታቸውም ይጠቅመናል በዓለም ውስጥ ያለ ክብር ሁሉ እንደ ሕልም ኃላፊ ጠፊ ነውና እነርሱ ግን የማያልፍ መንግስትን አተረፉ።

በዚያም ወራት የሮሜ ሀገር ሊቀ ጳጳሳት አረፈ ስለሚሾሙትም ሊቀ ጳጳሳት ይማከሩ ዘንድ ኤጲስቆጶሳት ጳጳሳትም ተሰበሰቡ የከበረ መክሲሞስንም አሰቡትና ሁሉም ለዚች ሹመት እርሱ በእውነት ይገባል ተባባሉ።በሽተኞችን ይፈውስ ዘንድ ብዙዎች የሆኑ ድንቆች ተአምራቶችንም ያደርግ ዘንድ እግዚአብሔር ታላቅ ፀጋ ሰጥቶታልና በእድሜውም ወጣት ቢሆን ክርስቶስ በውስጡ ወጣት ቢሆን ክርስቶስ በውስጡ ስለአደረ በዕውቀትና በበጎ ስራ በቤተ ክርስቲያንም ህግና ስርአት ሁሉ ፍፁም ነው።

ይህንንም በሰሙ ጊዜ አባቱና እናቱ ደስ አላቸው መኳንንቶችንም ላኩ የከበሩ መክሲሞስንና ዱማቴዎስን ወደ ሮሜ ይሰዳቸው ዘንድ ወደ ሶሪያ አገረ ገዢ ደብዳቤ አብረው ላኩ። እሊህም ቅዱሳን ሰምተው እጅግ አዘኑ አባታቸው አባ አጋብዮስም ያዘዛቸውን አሰቡ በዚያንም ጊዜ ተነሱ ልብሳቸውንም ለውጠው ወደ ኤርትራ ባህር ዳርቻ ተጓዙ ወደየትም እንደሚጓዙ አያውቁም ውኃን በሚጠሙ ጊዜም እግዚአብሔር መራራውን ውኃ ለውጦ ጣፋጭ አድርጎላቸው ይጠጣሉ ከዚህም በኃላ ከእርሱ ዘንድ ረድኤትን ኃይልን ላከላቸውና ከሶሪያ አገርም ተሸክማ ወደ አስቄጥስ ገዳም አደረሰቻቸው ወደ አባ መቃርስም ገብተው በእርሱ ዘንድ መኖርን እንደሚሹ ነረጉት።

እነርሱም በፀጋ የለመለሙ እንደሆኑ በአየ ጊዜ በገዳም መኖርን የማይችሉ መስለው በገዳም ያለውን ችግር ነገራቸውና በዚህ መኖር አትችሉም አላቸው እነርሱም አባታችን ሆይ ተወን ከዚህ መኖር ካልተቻለን እንሄዳለን ብለው መለሱለት።

ከዚህም በኃላ ሰሌን መስራትን አስተማራቸው ሰሌንም የሚቆርጡበትን ወንዝ አሳያቸው ማደሪያቸውንም እስከሚሰሩ ድረስ ረዳቸው የእጅ ስረቸውንም የሚሸጥና ምግባቸውን የሚያመጣላቸውን አንድ ህዝባዊ ሰው አምጥቶ አገናኛቸው። እንዲህም ሆነው ከቶ ከሰው ሳይገናኙ ሶስት አመት ኖሩ ነገር ግን በጭልታና በዝምታ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚገቡና ሥጋውንና ደሙን ተቀብለው ወደ ማደሪያቸው የሚመለሱ ሆኑ።
ሦስት አመት ያህል ወደርሱ ስለአልመጡና ስለአልጎበኙት አባታቸው አባ መቃርስ ከስራቸው የተነሳ አደነቀ ስራቸውንም ይገልጥለት ዘንድ ወደ ጌታችን ለመነና ተነስቶ ወደ ርሳቸው ሄደ እነርሱም በመምጣቱ ደስ ተሰኙበት በዚያች ሌሊትም ከርሳቸው ጋር አደረ። ለፀሎትም በተነሱ ጊዜ የእሳት ሐብል ከአፋቸው ሲወጣና ወደ ሰማይ ሲደርስ ሰይጣናትም እንደ ዝንቦች ሲከቡት የእግዚአብሔርም መልአክ በእሳት ሰይፍ ዝንቦቹን ሲያበርራቸው የከበሩ መክሲሞስንና ዱማቴዎስን አያቸው በነጋም ጊዜ አስኬማን አለብሳቸው ፀልዩልኝ ብሏቸውም ሊሄድ ተነሳ። እንርሱም ሰገዱለትና አባታችን ሆይ አንተ በእኛ ላይ ትፀልይ ዘንድ ትባርከንም ዘንድ የሚገባ ነው አሉት።

ተጋድሎአቸውንም በፈፀሙ ጊዜ እግዚአብሔር ከዚህ አለም ድካም ሊአሳርፋቸው ወደደ መክሲሞስም በፅኑ ህመም ታመመ ስጋውም እንደ እሳት ጋለ ወደርሱም ይመጣ ዘንድ ወደ አባ መቃርስ ላከ። አባ መቃርስም በመጣ ጊዜ በደዌ ሲሰቃይ አገኘው መክሲሞስም ፀልይልኝ ባርከኝም አለው። እርሱም በላዩ አማትቦ ይህ ደዌ ከአንተ ይርቃልና አይዞህ አለው መክሲሞስም አባቴ ሆይ በዚች ደዌ ከዚህ አለም እንደምወጣ እኔ አውቃለሁ ረድኤት አገኝ ዘንድ አንተ ፀልይልኝ አለው።

ይህንንም በተናገረ ጊዜ መሪር ልቅሶን አለቀሰ በዚያችም ጊዜ አባ መቃርስ የቅዱሳንን አንድነት ነቢያትን ሀዋርያትን መጥምቁ ዮሀንስን ንጉስ ቆስጠንጢኖስንም አያቸው። እነርሱም ነፍሱ በክብር እስከወጣች ድረስ በአባ መክሲሞስ ዙሪያ ነበሩ።

አባ መቃርስም አልቅሶ መክሲሞስ ሆይ የተመሰገንክ የከበርክ ነህ አለ። ዱማቴዎስም በውንዱሙ ላይ መራራ ልቅሶ በማልቀስ አባ መቃርስን የሚለምነው ሆነ ነፍሴን ይወስዳትና ወደ ወንድሜም ያደርሳት ዘንድ ስለ እኔ ወደ እግዚአብሔር ፀልይ አለው።

አባ መክሲሞስም ከተቀበረ በኃላ በሶስተኛው ቀን አባ ዱማቴዎስ ታመመ ስለርሱም ለአባ መቃርስ ነገሩት አባ መቃርስም ወደርሱ ሊሄድ ተነሳ በጉዞ ላይም ሳለ አስቀድሞ ወደ አባ መክሲሞስ የመጡትን የቅዱሳን አንድነት አየ የአባ ዱማቴዎስንም ነፍስ ተቀበለው በክብር ወደ ሰማይ አሳረጓት።

አባ መቃርስም ወደ በኣታቸው ሲደርስ ዱማቴዎስን አርፎ አገኘው ወስዶም ከወንድሙ ከመክሲሞስ ጋር በአንድ መቃብር በክብር ቀበረው። የመክሲሞስም እረፍት በዚህ ወር በአስራ አራት ነው ዳግመኛ የዱማቴዎስ እረፍት ጥር አስራ ሰባት በዚች ቀን ነው።

የከበረ አባ መቃርስም ያ ቦታ በስማቸው እንዲጣራ አዘዘ እንዲሁም ደብረ በርሞስ ተብሎ እስከ ዛሬ የሚጠራ ሆነ ለዘላለሙም መታሰቢያቸው ሆነ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ መክሲሞስና ዱማቴዎስ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር)