የጽርሐ ጽዮን ሐዋርያት ጎላ ቅዱስ ሚካኤል የፍኖተ ብርሃን ሰ/ት/ቤት (Official Channel)
2.59K subscribers
6.11K photos
67 videos
60 files
1.7K links
ይህ በጽ/ጽ/ሐ/ጎ/ቅ/ሚካኤል ቤ/ክ ፍ/ብ/ሰ/ት/ቤት እውቅና የተሰጠው የቴሌግራም ቻናል ነው።
Download Telegram
ብሥራተ ቅዱስ ገብርኤል

ታኅሣሥ ሃያ ሁለት በዚህች ዕለት ብርሃናዊው መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ለእመቤታችን አምላክን እንደምትወልድ ያበሰረበት መታሰቢያ ነው፡፡ ይኸውም ‹‹ልዑል እግዚአብሔር ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤልን  ''ሂድና ለጽዮን ልጅ ለድንግል የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ ወደአንቺ መጥቶ ኃይለ ልዑል ወልድ ሥጋሽን ለብሶ ሰው ይሆናል፤ ይኸውም ካንቺ የሚወለደው ጽኑዕ ነው ብለህ ንገራት'' ለዳዊት ልጅ ''እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነውና ደስ ይበልሽ'' ብለህ አብሥራት ''ለዘለዓለም ነግሦ የሚኖረውን እነሆ ትፀንሳለሽ በላት'' አለው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም ይህን ሰምቶ ሰገደ፡፡ ልብሱንም በላዩ ይዞ በመስቀል ቀኝ ይወርድ ዘንድ ወደደ፡፡ ጌታም "መግባትህና መውጣትህ በፍቅር አንድነት ይሁን" ዘካርያስን ረግመህ አንደበቱን እንዳሰርህ እርሷን እንዳታሳዝናት ይልቁንም አብዝተህ ደስ አሰኛት አንጂ አለው፡፡ ቅዱስ ገብርኤልም ይህን ሰምቶ ፈጽሞ ደስ እያለው ሊባኖስ ከሚባል ተራራ እስኪሰማ ድረስ ክንፉን እያማታ ወረደ፡፡ በዚህም ጊዜ በዙሪያው ያሉ ሁሉ ‹ይህ የምንሰማው ምንድነው?› ይሉ ነበር፡፡ የተደረገበትንም ቦታ አላወቁትም ነበር፡፡
እመቤታችንን በ3 ዓመቷ እናትና አባቷ ብፅዓት አድርገው ለእግዚአብሔር ሰጥተዋታልና ካህናትም በቤተ መቅደስ ከመካነ ደናግል አስገብተዋት በመልአኩ በቅዱስ ፋኑኤል አማካኝነት ኅብስት ሰማያዊ ጽዋዕ ሰማያዊ እየመጣላት ያንን እየተመገበች ቅዱሳን መላእክት እየጎበኟት 12 ዓመት ኖራለች፡፡ በ15 ዓመቷ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ለእመቤታችን ጌታችንን እንደምትወልድ በዚህች ዕለት አብሥሯታል፡፡ በመጀመሪያ እመቤታችን ውኃ ቀድታ ስትመለስ የተጠማ ውሻ እያለከለከ ሲመጣ ብታየው ለፍጥረት ሁሉ የምትራራ ናትና በወርቅ ጫማዋ ለዛ ለተጠማው ውሻ ውኃ ስታጠጣ አብሯት የነበሩ ሴቶች ‹‹ማድጋሽን አጎደልሺው፣ ቀድቼ እሞላዋለሁ እንዳትይ ጉድጓዱ ጥልቅ ነው መቅጃም የለሽም›› አሏት፡፡ ክብርት እመቤታችንም ‹‹ውሃ የሚገኘው ከወደላይ ነው እንጂ ከወደታች ነውን? ፍጥረቱን ያጠጣ ጌታ ይሞላልኛል›› አለቻቸው፡፡ ማድጋዋም በተአምራት ሞልቶ ተገኘ፡፡ ሴቶቹም ዳግመኛ ‹‹በዚህ ዘመን አምላክ ከድንግል ይወለዳል ይላሉ ካንቺ ይሆን?›› እያሉ ሲዘብቱባት ወዲያው ከወደኋላዋ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል መጥቶ ‹‹እነሆ ትጸንሻለሽ›› አላት፡፡ እመቤታችንም ዞር ብትል የተናገራትን አጣችው፡፡ በዚህም ጊዜ ‹‹አባቴን አዳምን እናቴን ሔዋንን ያሳተ ጠላት ይሆናል›› ብላ ሄደች፡፡
ዳግመኛም እመቤታችን ከቤት ደርሳ ማድጋዋን ስታስቀምጥ መልአኩ አሁንም በድምፅ ‹‹እነሆ ትጸንሻለሽ›› አላት፡፡ እመቤታችንም ይህን ጊዜ ‹‹ምነው ይህስ ነገር ደጋገመኝ እንዲህ ያለውን ነገር ቤተ መቅደስ ሄደው ሊረዱት ይገባል›› ብላ ወደ ቤተ መቅደስ ሄዳ ወርቅና ሐር እያስማማች ስትፈት መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እሑድ ቀን በ3 ሰዓት በገሃድ ተገለጸላትና እጅ እየነሳ እየሰገደ አበሠራት፡፡ ‹‹የዕውነተኛ ንጉሥ እናቱ እመቤታችን ላንቺ ፍቅር አንድነት ይገባል›› አላት፡፡ ዳግመኛም ‹‹አንቺ ከሴቶች ይልቅ ተለይተሸ ንዕድ ክብርት ነሽ›› አላት፡፡ አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናች ክብርት እመቤታችንም የብርሃናዊውን መልአክ የቅዱስ ገብርኤልን ቃል በሰማች ጊዜ ‹‹እንዲህ ያለውን ሰላምታ እንደምን ይቀበሏል! እንዴትስ መቀበል ይቻላል? እንጃ›› አለችው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም ‹‹ማርያም ሆይ! መንፈስ ቅዱስ ያድርብሻል፣ ኃይለ ልዑል ወልድም ሥጋሽን ይለብሳልና አይዞሽ አትፍሪ›› አላት፡፡ ዳግመኛም ‹‹ይህ ካንቺ የሚወለደው ጽኑ ከሃሊ ነው፡፡ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ፣ እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፣ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፣ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለላም ይነግሣል፣ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም›› አላት፡፡ እመቤታችንም መልአኩን ‹‹ምድር ያለ ዘር ፍሬን አትሰጥምና እኔ ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል?›› አለችው፡፡ መልአኩም መልሶ ‹‹መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፣ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል። እነሆም ዘመድሽ ኤልሳቤጥ እርሷ ደግሞ በእርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች፡፡ ለእርስዋም መካን ትባል ለነበረችው ይህ ስድስተኛ ወር ነው፣ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና›› አላት፡፡ ክብርት እመቤታችንም ይህን ጊዜ ‹‹እነሆኝ የጌታ ባሪያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ›› አለችው፡፡ መልአኩም ከእርሷ ዘንድ ሄዶ ተሠወረ፡፡ አካላዊ ቃልም በማኅፀኗ አደረ፡፡ በዚያችም ቅጽበት የእመቤታችን የፊቷ መልክ ተለወጠ፣ እንደፀሐይም አሸበረቀ፡፡

የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ረድኤት በረከት አይለየን!!
“በሞት ጥላ መካከል እንኳ ብሄድ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም፤ በትርህና ምርኵዝህ እነርሱ ያጸናኑኛል።” መዝሙር 22፥4
በጋራ መታሰቢያቸውን ለማድረግ የተዘጋጀ ዝክረ ካህናት ወአባላት ልዩ ጉባኤ ይታደሙ አበረዋችሁ ያገለገሉትን አባላትና የምታውቋቸውን አባቶች ፎቶ ይላኩልን በዕለቱም በጉባኤው ይታደሙ
ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት

ታኅሣሥ ሃያ ሦስት በዚህች ዕለት ልበ አምላክ ነቢዩ ቅዱስ ዳዊት ዐረፈ፡፡ ይህም ንጉሥ ዳዊት በእግዚአብሔር ፊት መልካም ጒዞን የተጓዘ ከእስራኤልም ነገሥታት ሁሉ እውነተኛ ፍርድን ያደረገ ነው እርሱም አገሩ ቤተልሔም የሆነች ከይሁዳ ነገድ ነው ሳኦልም የእግዚአብሔር ትእዛዝ በተላለፈ ጊዜ ለእስራኤል ንጉሥ ይሆን ዘንድ መረጠው ነቢይ ሳሙኤልንም ቅብዐ መንግሥትን የእሴይን ልጅ ይቀባ ዘንድ ላከው። ሳሙኤልም ታላቁን ኤልያብን ተመለከተ መልኩ ያማረ አካሉም የጸና ነበርና እግዚአብሔር ግን አልመረጠውም። "የኤልያብ ፊቱን አትይ የመልኩንም ማማር አትመልከት እግዚአብሔር ሰው እንደሚያይ የሚያይ አይደለምና" አለው እንጂ "ሰው መልክ ያያል እግዚአብሔር ግን ልብን" ያያል።

ከእሴይ ከሰባቱ ልጆች በኋላ ነቢይ ሳሙኤል ዳዊትን በእስራኤል ልጆች ላይ ይነግሥ ዘንድ ቀባው እግዚአብሔርም በሥራው ሁሉ ከእርሱ ጋር ሆነ። ከልቡናው ንጽሕና ከየዋህነቱም ብዛት የተነሣ ጠላቱን ሳኦልን ብዙ ጊዜ ሲያገኘው በላዩ ምንም ምን ክፉ ነገር አላደረገበትም። በአንዲትም ዕለት ሳኦል ከእስራኤል ሁሉ የተመረጡ ሦስት ሺህ ሰዎችን ይዞ ዳዊትን ከሰዎቹ ጋር ይፈልገው ዘንድ ዋሊያዎች ወደሚታደኑበት ሔዶ በጐዳና አጠገብ ያሉ ዘላኖችም ወደሚሠማሩበት ደረሰ በዚያም ዋሻ ነበር ሳኦልም ይናፈስ ዘንድ ወደዚያች ዋሻ ውስጥ ተቀምጠው ነበር። ዳዊትም ተነሥቶ ቀስ ብሎ ከልብሱ ጫፍ ቆረጠ። በሁለተኛም ጊዜ በድንክ አልጋ ላይ ተኝቶ ወዳለበት ከአቢሳ ጋር ገብቶ ከራስጌው ጦሩንና ውኃ ያለበትን ረዋቱን ይዞ ተመልሶ ሔደ ክፉ ነገርንም አላደረገበትም ሰዎቹም ጠላትህ ሳኦልን ግደለው በአሉት ጊዜ እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጄን ልዘረጋ አይገባኝም ብሎ መለሰላቸው።

ስለ ሳኦልም መገደል አንድ ሰው በነገረው ጊዜ ዳዊትም "ያንን ሰው ማን ገደለው" አለው ሰውዬውም "እኔ ገደልሁት" አለው ዳዊትም እጅግ አዘነ ልብሱንም ቀደደ ያንንም ሳኦልን እኔ ገደልሁት ያለውን ሰው ገደለው። እግዚአብሔር በዚህ በጻድቅ ዳዊት ልብ ብዙ ትሩፋትን፣ ትሕትናን፣ የዋህነትን፣ ቅንነትን፣ ትዕግሥትን ፍቅርን አከማቸ ክብር ያለው ንጉሥ ሲሆን ራሱን ውሻ ትል እንስሳም አድርጎ ይጠራል ስለዚህም ከምድር ነገሥታት ሁሉ ከፍ ከፍ አደረገው እንዲህም ብሎ አመሰገነው "የእሴይን ልጅ ዳዊትን እንደ ልቤ ሆኖ አገኘሁት ፈቃዴን ሁሉ የሚያደርግ ታማኝ ሰው ነው"።

እግዚአብሔርም የእስራኤልን ልጆች ኢየሩሳሌምንም ስለ ዳዊት ደግነት ብዙ ጊዜ ጠበቃቸው እርሱ ካለፈ በኋላም በነቢያቶቹ አንደበት አከበረው ነገሥታትንም ከእርሱ ዘር አደረገ። እርሱም በሁሉ ዓለም የታወቀ የመዝሙሩን መጽሐፍ ደረሰ ይኸውም በሰይጣናት ላይ ጋሻና ጦር የሆነ መልካም ቃልንም የተመላ በሰማይና በምድርም ያሉ በእርሱ እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑበት ነው።

ቅዱስ ዳዊትም ፊቱ እንደ ሮማን ቀይ ነው ቁመቱም መካከለኛ የሆነ አካሉም የጸና ብርቱ ነበር ታናሽ ብላቴናም ሁኖ ሳለ እርሱ የአባቱን በጎች ሲጠብቅ አንበሳ ወይም ተኵላ መጥቶ ከመንጋው ውስጥ በግ ነጥቆ በሚወስድ ጊዜ ተከትሎ ገድሎ ከአፉ ያስጥለው ነበር ሊጣላውም ቢነሣበት ጒረሮውን ይዞ ይሠነጥቅዋል። ከፍልስጥኤማውያንም ጋራ ሰልፍ በሆነ ጊዜ ብርቱ ሰው ስሙ ጎልያድ የሚባል ከጌት ሰዎች የተወለደ ቁመቱ ስድስት ክንድ ከስንዝር የሆነ ከኢሎፍላውያን ሰፈር ወጣ። በራሱ ላይ የነሐስ በርቦርቴ ደፍቷል የነሐስ ጽሩርም ለብሷል በርሱ ላይ ያለ የብረቱና የነሐሱ ሁሉ ሚዛኑ አምስት ሽህ ወቄት ነበር። በእግሮቹ ባቶችም ላይ የነሐስ ሰናፊል ታጥቆ ነበር በጫንቃውም መካከል የነሐስ እባቦች ነበሩ። የጦሩም ዛቢያ እንደ ሸማኔ መጠቅለያ ሁኖ በላዩ ሽቦ ነበረበት የጦሩም ብረት መጠን ስድስት መቶ ወቄት ነበር ጋሻ ጃግሬውም በፊቱ ይሔድ ነበር።

ቁሞም ወደ እስራኤል ሰፈር ይጮህ ነበር "ከእኛ ጋር ትዋጉ ለምን ወጣችሁ እኔ የኤሎፍላውያን ወገን ነኝ ከእናንተ የሳኦል ባሮች አይደላችሁምን ከእናንተ አንድ ሰው መርጣችሁ ወእኔ ይውረድ ከእኔ ጋር መዋጋት ችሎ ቢገድለኝ ባሮች እንሆናችኋለን እኔ ከርሱ ጋራ ችዬ ብገድለው እናንተ ባሮች ሁናችሁ ትገዙልናላችሁ" አላቸው። ያም ኢሎፍላዊ ለወገኖቹ "ዛሬ በዚች ቀን አንድ ሰው ስጡኝና ሁለታችን ለብቻችን እንዋጋ ብሎ የእስራኤልን አርበኞች እነሆ ተገዳደራቸው" እስራኤል ሁሉና ሳኦልም ይህን የኢሎፍላዊውን ቃል በሰሙ ጊዜ ደነገጡ እጅግም ፈሩ የእራኤልንም ወገኖች እንዲህ እየተገዳደራቸውና እየተመካባቸው አርባ ቀኖች ያህል ኖረ ከእስራኤልም ወገን ወደርሱ ይወጣ ዘንድ የደፈረ የለም።

በዚያም ወራት ቅዱስ ዳዊት ወንድሞቹን ሊጐበኝ ወጣ ያንንም የኢሎፍሊ ወገን የሆነ ሰው የእግዚአብሔር ወገኖችን ሲገዳደራቸው በአየው ጊዜ አምላካዊ ቅናትን ቀና ሳኦልንም እንዲህ አለው "እኔ ሔጄ ይህን ያልተገረዘ ቈላፍ ገድዬ ዛሬ ከእስራኤል ሽሙጥን አርቃለሁ። ሕያው የሚሆን የእግዚአብሔርን አርበኞች ይገዳደር ዘንድ ይህ ቈላፍ ቁም ነገር ነው ከድብ አፍና ከአንበሳ አፍ ያዳነኝ እርሱ እግዚአብሔር ከዚህ ካልተገረዘ ኢሎፍላዊ እጅ ያድነኛል"። ሳኦል "ሒድ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሁን" አለው። ዳዊትም ወንጭፋን በእጁ ያዘ ከወንዝ መካከልም ሦስት ደንጊያዎችን መረጠና ወደዚያ ኢሎፍላዊ ሔደ። ጎልያድም ዳዊትን በአየው ጊዜ ናቀው እንዲህም አለው "ደንጊያና በትር ይዘህ ወደኔ ትመጣ ዘንድ እኔ ውሻ ነኝን" ዳዊትም "ከውሻ የምትሻል አይደለህም ከውሻ ትብሳለህ እንጂ" ቈላፍ  ጎልያድም ዳዊትን በጣዖቶቹ ስም ረገመው።

ያም ኢሎፍላዊ ዳዊትን "ወደ እኔ ና ሥጋህን ለሰማይ ወፎችና ለዱር አራዊት እሰጣሁ" አለው ዳዊትም ያንኑ ኢሎፍላዊ  "አንተ ጦር ሰይፍና ጋሻ ይዘህ ወደኔ ትመጣለህ እኔ ግን አሸናፊ በሚሆን በእግዚአብሔር ስም ወዳንተ እመጣለሁ። ዛሬ የእስራኤልን አርበኞች የተገዳደርክ አንተን ዛሬ እግዚአብሔር በእጄ ይጥልሃል እገድልህምአለሁ ራስህንም እቆርጣለሁ የኢሎፍላውያን ሠራዊት ሬሳና ያንተን ሬሳ ዛሬ ለዱር አራዊትና ለሰማይ ወፎች እሰጣለሁ ሰዎችም ሁሉ እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር እንዳለ ያውቃሉ ሠራዊትም ሁሉ እግዚአብሔር በጦርና በሰይፍ የሚያድን እንዳይደለ ያውቃሉ ድል የእግዚአብሔር ገንዘብ ነውና"።  

ቅዱስ ዳዊትም እጁን ወደ ድጉ ሰዶ አንዲት ደንጊያ አውጥቶ ወነጨፋት ያንንም ኢሎፍላዊ ግንባሩን ገመሰው ያቺም ደንጊያ  ከግንባሩ ገብታ ናላውን በጠበጠችው በምድር ላይም በግንባሩ ተደፋ። ዳዊትም ሩጦ የገዛ ሰይፉን አንሥቶ ራሱን ቆረጠው ከእስራኤልም ልጆች ስድብን አራቀ። ቅዱስ ዳዊትም መላው ዕድሜው ሰባ ነው መንግሥትን ሳይዝ ሠላሳ ዓመት ኖረ ከያዘ በኋላ አርባ ዓመት ኖረ። የክብር ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ከመምጣቱ በፊት በሺህ አንድ መቶ ሃያ ዓመት ውስጥ ትንቢት የተናገረበት ዘመን ነው በሰላምም ዐረፈ።

የልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በረከት አይለየን!!
“በሞት ጥላ መካከል እንኳ ብሄድ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም፤ በትርህና ምርኵዝህ እነርሱ ያጸናኑኛል።” መዝሙር 22፥4
በጋራ መታሰቢያቸውን ለማድረግ የተዘጋጀ ዝክረ ካህናት ወአባላት ልዩ ጉባኤ ይታደሙ አበረዋችሁ ያገለገሉትን አባላትና የምታውቋቸውን አባቶች ፎቶ ይላኩልን በዕለቱም በጉባኤው ይታደሙ