የጽርሐ ጽዮን ሐዋርያት ጎላ ቅዱስ ሚካኤል የፍኖተ ብርሃን ሰ/ት/ቤት (Official Channel)
2.58K subscribers
6.1K photos
67 videos
60 files
1.7K links
ይህ በጽ/ጽ/ሐ/ጎ/ቅ/ሚካኤል ቤ/ክ ፍ/ብ/ሰ/ት/ቤት እውቅና የተሰጠው የቴሌግራም ቻናል ነው።
Download Telegram
...............የቦታ ለውጥ
ሜክሲኮ በተፈቀደልን የሽያጭ ቦታ ጊዜው ስለተጠናቀቀ አሁን በደብራችን ውስጥ ግርሞችን ቅዱሳን መጻሕፍቶችን በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ዘርግተን በድንኳን እያከፋፈልን እንገኛለን
#አድራሻ: ከኢሚግሬሽን ከፍ ብሎ ጽርሐ ጽዮን ሐዋርያት ጎላ ቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክ
🔴#ስንክሳር_ታህሳስ_22
~~~~~~~~~~
ታህሳስ 22 በቤተክርስቲያን አስተምህሮ ብስራተ ገብርኤል ይባላል፤ ይህም ቅዱስ ገብርኤል ለእመቤታችን ጌታን እንደምትወልድ ብስራቱን የነገረበት ቀን ነው፤ እንዴት ብስራቱንማ የነገራት መጋቢት 29 ቀን ነው ቢሉ ብስራቱን የነገራት መጋቢት 29 ቀን በዕለተ እሁድ ከቀኑ ሦስት ሰዓት ላይ ነው።

ታዲያ ዛሬ ለምን እናከብረዋለን ካሉ ምክንያቱ እንዲህ ነው፤ ምንግዜም ወርሃ መጋቢት ታላቁ ዓቢይ ጾም የሚውልበት ወር ነው በዚህ በዓቢይ ጾም ደግሞ ሐዘን፤ ለቅሶ፤ ጾም፤ ጸሎት እንጂ ደስታ፤ ፌሽታ እልልታ፤ ጭብጨባ የለም ፍጹም የሐዘን ወራት ነው ፍትሃ ነገስት አንድምታ አንቀጽ 15 ፡፡

የመጋቢት 29 ብስራቱን ደግሞ ታህሳስ 22 ቀን ዞሮ እንዲከበር ያደረገው ታላቁ አባት የጥልጥልያ ኤጲስ ቆጶስ ደቅስዮስ ይባላል በእመቤታች ፍቅር ልቡ የነደደ ታላቅ ጻድቅ ነው የእመቤታችንን ተአምራቷን የሚናገር መጽሐፍ የሰበሰበ አባት ነው፡፡

የጌታን ልደት ከመከበሩ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ብስራቱ መከበር አለበት ብሎ ስርዓት ሰራ አገሬውንም ሰብስቦ ታላቅ የደስታ በዓል አደረገ እመቤታችን ተገለጸችለት ወዳጄ ደቅስዮስ ባንተ ደስ አለኝ እንዳከበርከኝ እኔም አከብርሃለው አለችው ሰማያዊ ልብስና ሰማያዊ ወንበር ሰጠችው ይህችን ልብስ ካንተ ሌላ ማንም አይለብሳትም ይህችንም ወንበር ካንተ ሌላ ማንም አይቀመጥባትም አለችው፡ የዚህ ታላቅ አባት እረፍቱ ታህሳስ 22 በዛሬዋ ቀን ነው፡ ከእርሱ በኃላ ሌላ ኤጲስ ቆጶስ ተሾመ ልብሱን እለብሳለው በወንበሩም እቀመጣለው አለ ተው ይቅርብህ እመቤታችን እንዲህ ብላ ተናግራለች ይሉታል እርሱም ሰው እኔም ሰው እርሱም ኤጲስ ቆጶስ እኔም ኤጲስ ቆጶስ ብሎ በትዕቢት ልብሱን ለበሰው በወንበሩም ተቀመጠ ክፉኛ አወዳደቅ ወደቀ ደቅስዮስ ሰርቶልን ያለፈውን ስርዓት ቤተክርስቲያን ተቀብላ ይኸው ዛሬም ድረስ ታከብረዋለች በተለይም በመዲናችን አዲስ አበባ ብስራተ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ታቦተ ህጉ ወጥቶ በደማቁ ተከብሮ ይውላል፡፡

ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን፡፡
https://t.me/finotebirhan12
🔴#ስንክሳር_ታኅሣሥ_23
† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን †

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ታኅሣሥ ሃያ ሦስት በዚች ቀን የከበረ ተጋዳይ አባት ገዳማዊ አባ ጢሞቴዎስ አረፈ። የዚህም ቅዱስ አባት ወላጆቹ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ናቸው የቤተ ክርስቲያንንም ትምህርት እያስተማሩ አሳደጉት የምንኵስናንም ልብስ ሊለብስ ሽቶ ከአባቱ ዘንድ ወጥቶ ወደ አንድ ገዳም ሒዶ በዚያ የሚኖር ሆነ በውስጧም መነኰሰ።

ከዚህም በኋላ የተራቡ ድኆችን መጻተኞችን ተቀብሎ ይመግባቸው ዘንድ በገዳሙ አቅራቢያ ለብቻው መኖርን አሰበ ከገዳሙም ወጥቶ ማደሪያውን ሠራ። እየተጋደለና እጅ ሥራውንም እየሠራ በውስጡ አምስት ዓመት ያህል ኖረ የበጎ ሥራ ጠላት ሰይጣንም ከእርሱ እጅ ሥራውን ትገዛ ዘንድ በምክንያት ጋለሞታ ሴትን ወደርሱ አመጣ ብዙ ጊዜ ወደርሱ ከመመላለሷ የተነሣ የኃጢአት ፍቅር አድሮባቸው በመብል ጊዜ በአንድነት የሚበሉ ሆኑ ከዚህም በኋላ ከእርሷ ጋር በኃጢአት ወደቀና በኃጢአት ሥራ ውስጥ ሰባት ወር ያህል ኖረ።

በዚያንም ጊዜ እግዚአብሔር እርሷንም እርሱንም ፈጽሞ አልጣላቸውም የሞትን ጊዜ በምታስፈራና በምታስደነግጥ ቀን በንጉሠ ነገሥት ኢየሱስ ክርስቶስ ፊት መቆምን አሳሰባቸው እንጂ። ከዚያም ቦታ ተነሥቶ ጥቅጥቅ ካለ ዱር ውስጥ ገባ ልዑል እግዚአብሔር መርቶታልና በዚያም ጣፋጭ የውኃ ምንጭና ተምር አለ በዚያም ቦታ እየተጋደለ ብዙ ዘመን ኖረ።

ከዚህም በኋላ ሰይጣን በእርሱ ቀንቶ አስጨናቂ የሆነ የሆድ በሽታ አመጣበት ከሕማሙም ጽናት የተነሣ በግንባሩ በምድር ላይ የወደቀ ሁኖ ኖረ እርሱም ሲጸልይ ነፍሱን እንዲህ ይላት ነበር። ነፍስ ሆይ ይህ የሠራሽው የኃጢአት ፍሬ ነውና በዚህ ደዌ ላይ ታገሺ በዚህ ሕማምም አራት ዓመት ኖረ። ከዚህም በኋላ መሐሪና ይቅር ባይ እግዚአብሔር ራራለት መልአኩንም ላከለት እርሱም በእጁ ሆዱን አሸው ጐኑንም በጣቱ ሠነጠቀ ጨጓራውንና አንጀቱንም አፀዳ ከዚህም በኋላ ወደቦታው መልሶ እንደቀድሞው አያይዞ አዳነው። እነሆ እንግዲህ ጤነኛ ሆንክ ዳግመኛ አትበድል ከዚህ የከፋ እንዳይደርስብህ አለው።

በበረሀም ውስጥ እየተጋደለ አርባ ዓመት ኖረ ከዚህ በፊት በገዳም ዐሥራ ሰባት ዓመት በዋሻም ዐሥር ዓመት ኖሮዋል በዚህም ረጂም ዘመን ከልብስ የተራቈተ ነው ልዑል እግዚአብሔርም የራሱን ጠጕር አስረዘመለት በርሱም በፊቱም በኋላውም ተሸፈነበት።

ለዚህም አባት ስለ አገልግሎቱ ስለ ተጋድሎው ስለ በጎ አምልኮቱ አራዊት እስከሚጐበኙትና የእግሩን ትቢያ እስከሚልሱ ድረስ ታላቅ ጸጋ ተሰጠው እግዚአብሔርንም ከአገለገለ በኋላ አክሊሉን እንደተሸከመ በሰላም አረፈ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ አባት ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
https://t.me/finotebirhan12
🔴ስንክሳር_ታኅሣሥ_24
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን

ቅዱስ #‎ተክለ_ሃይማኖት ሐዋርያዊ

#ልደት

መልካም ዛፍ መልካም ፍሬን ያፈራልና ተክለ ሃይማኖትን የወለዱት ደጋጉ #‎ጸጋ_ዘአብ ካህኑና #‎እግዚእ_ኃረያ ናቸው:: እርሱ በክህነቱ እርሷ በደግነቷ በምጽዋቷ ጸንተው ቢኖሩ እግዚአብሔር ጣፋጭ ፍሬን ሰጥቷቸዋል::

በዳሞቱ ገዢ በሞተለሚ አደጋ ቢደርስባቸው #‎ቅዱስ_ሚካኤል ጸጋ ዘአብን ከሞት እግዚእ ኃረያን ከትድምርተ አረሚ (ከአረማዊ ጋብቻ) አድኗቸዋል:: በኋላም የቅዱሱን መወለድ አብስሯቸዋል::

አቡነ ተክለ ሃይማኖት የጸነሱት መጋቢት 24, በ1206 (1196) ሲሆን የተወለዱት ታሕሳስ 24, በ1207 (1197) ዓ/ም ነው:: በተወለዱበት ቀንም ብዙ ተአምራት ተገልጸዋል:: ቤታቸውም በበረከት ሞልቷል::

#ዕድገት

የጻድቁ የመጀመሪያ ስማቸው " #‎ፍሥሃ_ጽዮን " ይሰኛል:: ይሕንን ስም ይዘው አባታቸው ጸጋ ዘአብን ተከትለው አድገዋል:: በተለይ ቅዱሳት መጻሕፍትን (ብሉያትና ሐዲሳትን) ተምረዋል በሥጋዊው ጐዳናም ብርቱ አዳኝ እንደ ነበሩ ይነገራል ዲቁና ከወቅቱ ዻዻስ #‎አባ_ጌርሎስ ተቀብለዋል::

#መጠራት

አንድ ቀን ፍሥሃ ጽዮን ለአደን ወጥቶ ሲያነጣጥር ድንገት ከሰማይ አስደንጋጭ ድምጽ ተሰማ:: የክብር ባለቤት #‎ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ አእላፍ መላእክት እያመሰገኑ በሚካኤል ክንፍ ተቀምጦ ወረደ::

የወጣቱን አዳኝ ፍርሃቱን አርቆ ጌታችን ተናገረ

"ከዛሬ ጀምሮ ስምህ ተክለ ሃይማኖት (ተክለ ሥላሴ) ይሁን:: አራዊትን ሳይሆን ነፍሳትን ታድናለህ:: ዘወትር ካንተ ጋር ነኝ" ብሎ በግርማ ዐረገ:: ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከዚህ ጊዜ በኋላሰዓትን አላጠፉም:: ንብረታቸውን ለነዳያን በትነው በትር ብቻ ይዘው ቤታቸው እንደ ተከፈተ ወደ ምናኔ ወጡ::

#አገልግሎት

ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከዻዻሱ ቅስና ተቀብለው የወንጌል አገልግሎትን ጀመሩ:: በመጀመሪያ ስብከታቸው እዚያው ሽዋ ( #‎ጽላልሽ ) አካባቢ ብቻ በ10ሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን አሳምነው አጠመቁ:: ያንጊዜ #‎ኢትዮዽያ 2 መልክ ነበራት::

1.ዮዲት (ጉዲት) በፈጠረችው ጣጣና በእስላሞች ተጽዕኖ ወደ ደቡብ አካባቢ ያለው ነዋሪ አንድም ሃይማኖቱን ክዷል: ወይም በባዕድ አምልኮ ተጠምዷል::

2.ደግሞ በዛግዌ ነገሥታት ጥረት ክርስትናና ምናኔ ተነቃቅቶ ነበር::

ግማሹ ሃገር በጨለመበት ወቅት የደረሱት #‎ሐዲስ_ሐዋርያ አባ ተክለ ሃይማኖት በወጣት ጉልበታቸውና በኃይለ መንፈስ ቅዱስ ብዙ ቦታዎችን አደረሱ:: ሕዝቡን: መሣፍንቱን ወደ ሃይማኖት መልሰው: ማርያኖችን (ጠንቁዋዮችን) አጥፍተዋል::

#ገዳማዊ ሕይወት

ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት በወንጌል ብርሃን ኢትዮዽያን ከማብራታቸው ባለፈ ገዳማዊ ሕይወትንም አስፋፍተዋል:: እርሳቸው ከሁሉ የተሻሉ ሳሉም በ3 ገዳማት በረድዕነት አገልግለዋል::

እነዚህም በአቡነ #‎በጸሎተ_ሚካኤል ገዳም ለ12 ዓመታት: በአቡነ #‎ኢየሱስ_ሞዐ_ዘሐይቅ ገዳም ለ7 ዓመታት: በደብረ ዳሞ ከአቡነ #‎ዮሐኒ ጋር ለ7 ዓመታት: በአጠቃላይ ለ26 ዓመታት አገልግለዋል::

በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ከመነኮሱ በኋላም ወደ ምድረ ሽዋ #‎ዞረሬ ተመልሰው በአንዲት በዓት ውስጥ ለ22 ዓመታት ቆመው ጸልየዋል:: በተሰበረ እግራቸውም 6 ጦሮችን በግራና በቀኝ ተክለው ለ7 ዓመታት ጸልየዋል::

#ስድስት_ክንፍ

ኢትዮዽያዊው ጻድቅና ሐዋርያ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከኢትዮዽያ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዘው ከቅዱሳት መካናት ተባርከዋል:: ጻድቁ ምድረ #‎እሥራኤል የገቡት በየመንገዱ መንፈሳዊ ዘርን እየዘሩ: እያስተማሩና እያሳመኑ ነበር::

የወቅቱ ሊቀ ዻዻሳት #‎አባ_ሚካኤል ጋርም ተገናኝተው ቡራኬን ተሰጣጥተዋል:: ዋናው ጉዳይ ግን ከዚህ በኋላ ነው:: ጻድቁ እመቤታችንና ጌታችን ከጽንሰታቸው እስከ ዕርገታቸው የረገጧቸውን ቦታዎች ሲመለከቱ በፍጹም ተደሞ እንባቸው ይፈስ ነበር::

ምክንያቱም እግዚአብሔር ስላበቃቸው ተክለ ሃይማኖት የሚያዩት ቦታውን አልነበረም:: በገሃድ:-
¤በቤተ መቅደስ ብስራቱን
¤በቤተ ልሔም ልደቱን
¤በቤተ ዮሴፍ ግዝረቱን
¤በፈለገ ዮርዳኖስ ጥምቀቱን
¤በቤተ አልዓዛር ተአምራቱን ይመለከቱ ነበር::

የጉብኝታቸው የመጨረሻ ክፍል ወደሆነው #‎ቀራንዮ ደርሰው ጌታቸውን እንደ ተሰቀለ ሆኖ ቢመለከቱት ከዓይናቸው ይፈስ የነበረው ቁጡ እንባ መልኩን ቀየረና ዓይናቸው ጠፋ::
በዚያች ቅጽበት ስም አጠራሯ የከበረ #‎እመቤታችን_ድንግል_ማርያም ፈጥና ደርሳ ተክልየን ወደሰማይ አሳረገቻቸው::

+በዚያም:-
¤ የብርሃን ዐይን ተቀብለው
¤ 6 ክንፍ አብቅለው
¤ የወርቅ ካባ ላንቃ ለብሰው
¤ ማዕጠንተ ወርቁን ይዘው
¤ ከ24ቱ ካህናተ ሰማይም ተደምረው
¤ ሥላሴን በአንድነቱና ሦስትነቱ ተመልክተው
¤ "ስብሐት ወክብር ለሥሉስ ቅዱስ ይደሉ" ብለው መንበረ ጸባኦትን አጥነው ወደ መሬት ተመልሰዋል::

#ተአምራት

=>የተክልየ ተአምራት እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛ ነው::
• ሙት አንስተዋል
• ድውያንን ፈውሰዋል
• አጋንንትን አሳደዋል
• እሳትን ጨብጠዋል
• በክንፍ በረዋል
• ደመናን ዙፋን አድርገዋል::

ብዙ ደቀ መዛሙርትን አፍርተው ደብረ ሊባኖስን መሥርተዋል:: በዚያም ሴትና ወንድ መነኮሳት እንደ ሕጻናት አብረው ኑረዋል:: በዘመናቸው ሰይጣን ታሥሯልና::

#ዕረፍት

ጻድቅ: ሰማዕትና ሐዋርያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ብርሃን ሆነው መከራን በብዙ ተቀብለው አእላፍ ፍሬን አፍርተው በተወለዱ በ99 ዓመት ከ8 ወር ከ1 ቀናቸው ነሐሴ 24, በ1306 (1296) ዓ/ም ዐርፈዋል:: ጌታ ድንግል ማርያምና ቅዱሳን ከሰማይ ወርደው ተቀብለዋቸዋል:: 10 ትውልድ የሚያስምር ቃል ኪዳንም ተቀብለዋል::

=>የጻድቁ አባታችን ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት የቅድስናና የክብር ስሞች :-

1. ተክለ አብ: ተክለ ወልድ: ተክለ መንፈስ ቅዱስ
2. ፍስሐ ፅዮን
3. ሐዲስ ሐዋርያ
4. መምሕረ ትሩፋት
5. ካህነ ሠማይ
6. ምድራዊ መልዐክ
7. እለ ስድስቱ ክነፊሁ (ባለስድስት ክንፍ)
8. ጻድቅ ገዳማዊ
9. ትሩፈ ምግባር
10. ሰማዕት
11. የኢትዮዽያ መነኮሳት አለቃ
12. ፀሐይ ዘበፀጋ
13. የኢትዮዽያ ብርሃኑዋ
14. ብእሴ እግዚአብሔር (የእግዚአብሔር ሰው)
15. መናኒ
16. ኤዺስ ቆዾስ (እጨጌ)

=>እነዚህ የአባታችን ስሞች እንደዘመኑ ሰው ለመሞጋገስ የወጡ ሳይሆኑ ሁሉም በትክክል ሥራዎቹንና ለቤተ ክርስቲያን የሆነላትን የሚያዘክሩ ናቸው:

=>ታሕሳስ 24 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት
2.ቅዱሳን ጸጋ ዘአብና እግዚእ ኃረያ
3.ቅዱስ አግናጥዮስ ሐዋርያ
4.ቅድስት አስቴር
5.አባ ፊሎንጐስ ሊቀ ዻዻሳት
6.አባ ዻውሊ ጻድቅ
7.ጻድቃን ቅዱሳን ዘከዲህ

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ቶማስ ዘመርዐስ
2.አቡነ ዘዮሐንስ ጻድቅ ዘክብራን
3.ቅዱስ አጋቢጦስ (ጻድቅ ኤዺስቆዾስ)
4.ቅዱስ አብላርዮስ ታላቁ
5."24ቱ" ካኅናተ ሰማይ (ሱራፌል)
6.ቅዱስ አባ ሙሴ ጸሊም (ኢትዮዽያዊ)
7.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ

አምላከ ቅዱሳን ወዳጆቹን ባጸናበት ቅዱስ መንፈሱ እኛንም ያጽናን ከበረከታቸውም ይክፈለን::
https://t.me/finotebirhan12
🔴ስንክሳር#ታኅሣሥ_25

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ታኅሣሥ 25 በዚህች ዕለት #የአቡነ_ዮሐንስ_ከማ_ዘግብጽ፣ ኢትዮጵያዊው ጻድቅ #አቡነ_ዮሐንስ_ከማ_እጨጌ#አምስቱ_መቃባውያን ዕረፍታቸው ነው፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_ዮሐንስ_ከማ_ዘእጨጌ_ኢትዮጵያዊው

በዚህችም ዕለት ኢትዮጵያዊው አቡነ ዮሐንስ ከማ ዘእጨጌ ዐረፉ፡፡ ይኸውም ጻድቅ አባት አገራቸው ሰሜን ጎንደር ነው፡፡ በብዙዎቹ ቅዱሳን ገድል ላይ ታሪካቸው ተደጋግሞ የተጠቀሰ ሲሆን ቅዱስ ያሬድ በድርሰቱ ደጋግሞ ያመሰገናቸው ታላቅ አባት ናቸው፡፡ ከቀደምት አንጋፋ ቅዱሳን ውስጥ አንዱ ሲሆኑ መጽሐፍ "ኮከብ ዘገዳም" ይላቸዋል፡፡ ብዙ ሰዎች ይህኛውንም አባት ግብፃዊ ናቸው ይሏቸዋል፡፡ ነገር ግን ስማቸውን ከላይ ከጠቀስናቸው ከግብፃዊው አባት ከአባ ዮሐንስ ከማ ጋር አንድ አይደሉም፡፡ ኢትዮጵያዊው አቡነ ዮሐንስ ከማ ትግራይ የሚገኘውን ቀብፅያ ገዳምን የቆረቆሩ ሲሆን ብዙ ቅዱሳን አባቶችንም በማመንኰስ የቤተ ክርስቲያን ከዋክብት የተባሉትን ቅዱሳን መነኰሳትን አፍርተዋል፡፡ በገዳማቸው ቀብፅያ የምትገኘው እጅግ አስገራሚዋና ተአምራትን የምትሠራው መቋሚያቸው ዛሬም ድረስ አለች፡፡

1250 ዓመት ያስቆጠረችውን ይህችን የጻድቁን ተአምረኛ መቋሚያ ሀገሬው በጠመንጃ ይጠብቃታል፡፡ እንደ ሰው ድምፅ የምታሰማበት ጊዜ አለ፡፡ ጻድቁ ሰሜን ጎንደር ምድረ ጸለምት ትልቅ ገዳም አላቸው። ዕረፍታቸው በዚህች ቀን ነው።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ እና #ከገድላት_አንደበት)
https://t.me/finotebirhan12
...............4 ቀን ብቻ ቀረው................
የፊታችን ሐሙስ ድረስ ብቻ የሚቆይ ሽያጭ ግርግሞችን መጥተው ይግዙ በደብራችን ያገኛሉ
#አድራሻ: ከኢሚግሬሽን ከፍ ብሎ ጎላ ሚካኤል ቤ/ክ ውስጥ
Share
🔴 ስንክሳር#ታኅሣሥ_26

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

#ቅድስት_አንስጣስያ

ታኅሣሥ 26 በዚህች ዕለት ከሮሜ አገር የከበረች ቅድስት አንስጣስያ በሰማዕትነት ዐረፈች፡፡ የዚችም ቅድስት አባቷ ጣዖትን የሚያመልክ ነው እናቷ ግን ክርስቲያን ናት ይቺንም ቅድስት በወለደቻት ጊዜ አባቷ ሳያውቅ የክርስትና ጥምቀትን በሥውር አጠመቀቻት አውቆ ቢሆን ማጥመቅ ባልተቻላትም ነበር። ከዚህም በኋላ በበጎ አስተዳደግ አሳደገቻት በቀናች ሃይማኖት እስከ አጸናቻት ድረስ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት አስተማረቻት ጠባይዋን መለወጥ ለማንም አልተቻለውም።

አድጋም አካለ መጠን በአደረሰችም ጊዜ አባቷ እንደርሱ ላለ ከሀዲ ሰው አጋባት እርሷ ግን እጅግ ጠላችው ልትገናኘውም አልፈለገችም በሴቶች ላይ በሚሆነው ግዳጅና አንዳንድ ጊዜም በደዌ የምታመካኝ ሆነች እንዲጠላትና ከእርሷ እንዲለይ ያደፈና የቆሸሸ የተጐሳቈለ ልብስ ትለብስ ነበር። ባሏም ወደ ሥራው ወጥቶ በተሰማራ ጊዜ እርሷም ስለ ቀናች ሃይማኖት የታሠሩ እስረኞችን ትጐበኝ ዘንድ ትሰማራለች ታገለግላቸውና የሚሹትን ትሰጣቸዋለች። ባሏም ይህን የምትሠራውን በአወቀ ጊዜ ወደ ውጭ እንዳትወጣ በቤት ውስጥ ዘጋባት እርሷም ከእጁ ያወጣት ዘንድ አዘውትራ በመረረ ልቅሶ ወደ እግዚአብሔር የምትለምን ሆነች ጌታችንም ልመናዋን ሰምቶ ያንን ሰው አጠፋው። እርሷም በሞቱ ደስ አላት ከዚህም በኋላ ለድኆችና ለምስኪኖች ስለ ቀናች ሃይማኖትም በመታመን ለታሠሩ እሥረኞች ገንዘቧን ሁሉ ሰጠች።

የሮሜ አገር ገዢም ዜናዋን በሰማ ጊዜ መልእክተኞችን ልኮ ወደርሱ አስመጣት ስለ ሃይማኖቷም ጠየቃት ክርስቲያን እንደሆነች በፊቱ ታመነች ቃል ኪዳን በመግባትም ተናገራት ከበጎ ምክርዋ አውጥቶ ወደ ክህደት ሊያዘነብላት አልቻለም። በዚያንም ጊዜ በብዙ በተለያየ ሥቃይ አሠቃያት።

ከዚህም በኋላ ወደ ባሕር ያሠጥሟት ዘንድ አዘዘ ባሕሩም በሕይወቷ ተፋት ዳግመኛም በአራት ካስማ መካከል አስተኝተው ዘርግተው አሥረው ታላቅና ጽኑዕ የሆነ ግርፋትን ይገርፋዋት ዘንድ አዘዘ መኰንኑም እንዳዘዘ አደረጉባት ግን ምንም ምን ጉዳት አልደረሰባትም። ከዚህም በኋላ ወደ አዘጋጁላት የእሳት ማንደጃ ውስጥ ይጨምርዋት ዘንድ አዘዘ በጨመርዋትም ጊዜ ነፍሷን በእግዚአብሔር እጅ ሰጠች በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊል ተቀበለች።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድስት አንስጣስያ ጸሎት ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን ።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ)
https://t.me/finotebirhan12
🔴 ስንክስር#ታኅሣሥ_27

ታኅሣሥ 27 በዚህች ዕለት ኢትዮጵያዊው #ጻድቅ_አባ_በግዑ_ዘሐይቅ ዐረፈ፣ የከበረ ኤጲስ ቆጶስ #አባ_አብሳዲ ሰማዕትነት ዐረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_በግዑ_ዘሐይቅ

ታኅሣሥ ሃያ ሰባት በዚህች ዕለት ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አባ በግዑ ዘሐይቅ ዐረፈ፡፡ ይኸውም በመጀመሪያ ሽፍታ የነበረ ሲሆን በመንገድ ላይ ንብረት የያዘን ሰው ማንንም የማያሳልፍ ቀማኛ ሰው ነበር፡፡ ከኃይለኛነቱ የተነሳ ሕዝቡም ሁሉ ይፈራው ነበር፡፡ በእጁ ሰይፍና ጦር ይዞ ሊዘርፍ ወደ ወደደው አገር ይገባል፡፡ እየዘረፈ በሚያገኘው ገንዘብም ራሱን በተለያዩ ምግቦችና መጠጦች ያስደስት ነበር፡፡ ባማሩ ልብሶችም ይዋብ ነበር፡፡ ገንዘቡ የተወሰደበት ሰውም እርሱ እንደወሰደበት ባወቀ ጊዜ ዳግመኛ መጥቶ የተረፈውን ቀምቶ እንዳይወስድበት ምንም አይከሰውም ነበር፡፡ በጉልምስናው ኃይለኛና ብርቱ ስለነበር ወደ እርሱ ማንም አይቀርብ ነበር፡፡

በእንደዚህ ያለ የውንብድና ሥራ ብዙ ዓመታት ከኖረ በኋላ አባ በግዑ በስም ክርስቲያን ነበረና ከዕለታት በአንደኛው ቀን መንፈስ ቅዱስ አነሳስቶት ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄደ፡፡ ካህኑም ባየው ጊዜ ከመንገድ ገለል አደረገውና " የሕይወት ዘመንህን ሁሉ በከንቱ አሳለፍክ ዛሬ ስማ ልንገርህ፣ በዘመንህ ፍጻሜ እግዚአብሔር ይጎበኝሃል፣ በመንፈስ ቅዱስም ያድርብሃል፣ ፍጹም መነኵሴ ትሆናለህ፣ በብዙ መከራና ተጋድሎ ትኖራለህ በዚያም የነፍስህ መዳኛ ይሆናል፣ እግዚአብሔርንም ደስ ታሰኘዋለህ" አለው፡፡ ከዚህም የበዛውን ብዙ ነገር ነገረው፡፡ ከዚህም በኋላ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ቁርባን ተቀበለ፡፡ ወደቤቱም ከተመለሰ በኋላ ካህኑ የነገሩትን እያሰበ "እስከ መቼ በስንፍናዬ እኖራለሁ? እስከ መቼስ የነፍሴን መዳኛ ሳላስብ እኖራለሁ? …" እያለ አሰበ፡፡

ከዚህም በኋላ ከዘመዶቹ ተለይቶ ከሀገሩ ወጥቶ ሄደና ወደ ባሕር ዳርቻ ደርሶ የቅዱስ እስጢፋኖስን ቤተ ክርስቲያን እጅ ነሣ፡፡ ከመነኰሳትም ማኅበር ገብቶ እነርሱን ማገልገል ጀመረ፡፡ አባ በግዑ በእግዚአብሔር ጥሪ ወደ ልቡ ተመልሶ ከመነነ በኋላ ግን እስከሞተበት ዕለት ድረስ የላመ እህል ሳይቀምስ ኖረ፡፡ ምግቡን የዛፍ ፍሬና ሜዳ ላይ የሚበቅል ቅጠል አደረገ፡፡ ዓቢይ ጾም ሲመጣም ከሰኞ እስከ ቀዳሚት ሰንበት ምንም ሳይቀም የሚጾም ሆነ፡፡ ውኃንም ሳይጠጣ ኖረ፣ ማንም ሰው ሳያውቅበት ለ5ወር ምንም ውኃ ሳይጠጣ ተቀመጠ፡፡ ከ5ወር በኋላም የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ወደ አባ በግዑ መጣና "የእግዚአብሔር ሰው ሰላም ለአንተ ይሁን! በምን ትታወካለህ? ምንስ ያሳዝንሃል?" አለው፡፡ አባ በግዑም "ጌታዬ ከውኃ ጥም የተነሣ በጣም ስለተጨነቅሁ ነው"አለው፡፡ መልአኩም ነጥቆ ወደ ገነት ወሰደውና ከገነት ቅጠል አንሥቶ አቀመሰው፡፡ ወዲያም የአባ በግዑ ሰውነት ታደሰች፡፡ ከዚህም በኋላ" ውኃ ሳልጠጣ ተጋድሎዬን እፈጽም ይሆን!" የሚለው የኅሊና መታወክ ከእርሱ ጠፋለት፡፡

ከዕለታትም በአንደኛው ቀን አባ በግዑ ለሚወደው ለአንድ ወዳጁ ለማንም እንዳይናገር በእግዚአብሔር ተስም ካስማለው በኋላ ለ5ወር ምንም ውኃ እንዳልጠጣ ምሥጢሩን ነገረው፡፡ ያ ወዳጁም ይህን ሲሰማ ደንግጦ አለቀሰ፡፡ አባ በግዑም አብሮት አለቀሰ፡፡ ወዳጁም "እስከ ዛሬ ከውኃ የተከለከለ በማን ዘንድ ሰማህ? አሁንም ቅዱሳን መነኰሳትና አበምኔቱ አያምኑህም፡፡ ይህን ምሥጢር ዛሬ ብሸሽግ በመጨረሻ ይገለጣል፡፡ ሕዝቡ፣ ነገሥታቱና መኳንንቱም ይህን ነገር ይሰማሉ ነገር ግን አያምኑም። አሁንም የምነግርህን ስማኝና ትኅርምቱን ትተህ ውኃ ጠጣ" አለው፡፡ አባ በግዑም "የነገርከኝ ሁሉ እውነት ነው ሐሰት የለውም ነገር ግን እኔ ከዚህ በኋላ እስክሞት ድረስ ዳግመኛ ውኃ እንዳልጠጣ ስለ እግዚአብሔር ትቻለሁ፡፡ ሰዎች ባያምኑ እኔ ምን ገዶኝ፣ ነገር ግን፣ በዚህ ገድል እግዚአብሔር ረዳት ይሆነኝ ዘንድ ጸልይልኝ"አለው፡፡

ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር ሰው አባ በግዑ ብረት አመጣና ሰንሰለቶችን ይሠራለት ዘንድ ለአንጥረኛ ሰጥቶ አሠራ፡፡ ያንን ወዳጁን ጠራውና እጆቹንና እግሮቹን በብረት ችንካር እንዲያስረው አዘዘው፡፡ "አበምኔቱን ጥራልኝ" አለውና ጠራለት፡፡ አባ በግዑም አበምኔቱ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ሲመጣ በፊቱ ሰገደለትና "አባቴ ሆይ! የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እፈጽም ዘንደ በላዬ ላይ ጸልይልኝ" አለው፡፡ "ከዛሬ ጀምሮ ከበዓቴ አልወጣም፣ ሰውም ወደኔ አይገባም" አለው፡፡ አቡነ ኢየሱስ ሞዐም በላዩ ከጸለየለት በኋላ "ለእኔም ጸልይልኝ" አለው፡፡ አባ በግዑም በቅዱስ ሚካኤል በዓል ቀን በአባ ኢየሱስ ሞዐ እጅ ቅዱስ ቊርባንን ከተቀበለ በኋላ እጆቹንና እግሮቹን በብረት ችንካር ታስሮ ብቻውን ዘግቶ በጽኑ የተጋድሎ ሕይወት ኖረ፡፡ በዓቱንም ዙሪያውን መውጫ መግቢያ እንዳይኖረው መረገው፡፡ ለምግብ የሚሆነውን የዛፍ ፍሬና የሜዳ ቅጠል ማስገቢያ የሚሆን ትንሽ ቀዳዳን አበጃና ያ ወዳጁ ያስገባለታል፡፡ አባ በግዑም ያንን በሦስት ቀን አንድ ጊዜ ብቻ ይመገባል፡፡

የእግዚአብሔር ሰው አባ በግዑ በእንዲህ ዓይነት ጽኑ በሆነ የተጋድሎ ሕይወት ሲኖር ሰውነቱ ላይ ከቆዳውና ከአጥንቱ በቀር የሚታይ ነገር እስኪጠፋ ድረስ ታላቅ ተጋድሎን ተጋደለ፡፡ ውኃንም እስከ ሰባት ዓመት ድረስ አልጠጣም፡፡ መቆምም አይችልም ነበርና መነኰሳቶቹ ለቅዱስ ቊርባን በቃሬዛ አድርገው ወደ ቤተ ክርስቲያን ይወስዱት ነበር፡፡ አባ በግዑ በእንደዚህ ዓይነቱ ለመስማት በሚከብድ እጅ የበዛ ጽኑ ተጋድሎ ካደረገ ከብዙ ድካም በኋላ ታኅሣሥ27 ቀን ዐረፈ፡፡ በዕረፍቱ ጊዜ ጌታችንም ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ከድንግል ማርያምና ከአእላፍ ቅዱሳን መላእክቶቹ ጋር መጥቶ እንዲህ የሚል ቃል ኪዳን ገባለት "ስምህን ለጠራ ፣መታሰቢያህን ላደረገ፣ ወደ ተቀበርክበት ቦታ ሄዶ ለተሳለመ፣ በበዓልህ ቀን ምፅዋት ለሰጠ እስከ ሰባት ትውልድ እምርልሃለሁ ዳግመኛም በጸሎትህ አምኖ ከመልካም ሥራ የሠራ የገድልህን መጽሐፍ የሰማ ሁሉ የእሳቱን ባሕር በግልጽ ይለፍ። ወደ መንግሥተ ሰማያትም ይግባ" አለው።

ለሰው ምንም ውኃ ሳይጠጣ ሰባት ዓመት መኖር ይቻለዋልን!?" በብዙ ሲጋደሉ እንደኖሩ የቅዱሳንን ገድላቸውን ሰምተናል፡፡ ነቢይ ዕዝራ የዱር ዛፍ ፍሬ እየተመገበ ውኃም እየጠጣ በምድረ በዳ እየጾመ ኖረ፡፡ ነቢይ ኢሳይያስም የሜዳ ጎመን እየቆረጠ ከእርሱም እየተመገበ ውኃም እየጠጣ በተራራ እየጾመ ኖረ፡፡ እግዚአብሔር ስሙን "የበረሃ፡ኮከብ" ብሎ የጠራው የመነኰሳት በኩር የሆነ አባ እንጦንስና አባ መቃርስም በደረቅ ኅብስትና በውኃ ብቻ ሲጋደሉ ኖሩ፡፡ እኚህ ምድራዊያን ሲሆኑ ሰማያውያን ሆኑ፡፡ ነቢይ ኤልያስም በኅብስትና በውኃ ብቻ በምድረ በዳ ሲጋደል ኖረ፡፡ ይህ አባ በግዑ ግን ሰባት ዓመት ሙሉ ውኃ ሳይቀምስ ኖረ፡፡ ከመነነ በኋላ እስከ ሞተበት ዕለት ድረስ እህል የሚባል አልቀመሰም፡፡ እርሱ ግን ራሱን በእግዚአብሔር ፊት ዝቅ ያደርግና በትሕትናም ሆኖ ስለ ኃጢአቱ ሁል ጊዜ ያለቅስ ነበር፡፡ ይህም የእግዚአብሔር ሰው አባ በግዑ ይህን ሁሉ የተጋደለ በራሱ ኃይል አይደለም፤ በእግዚአብሔር ኃይል ነው እንጂ፡፡
"አንተም ወንድሜ ሆይ ራስህን ዕወቅ፡፡ ምንም ተጋድሎን ብታደርግ ጾምኩ፣ ተራብኩ፣ ስለ እግዚአብሔርም ብዬ ራሴን አደከምኩ፣ እግዚአብሔርንም ስላገለገልኩ በሥራዬም እድናለሁ አትበል፡፡ መጨረሻህን አታውቅም፡፡ አንተ ግን ስለ እግዚአብሔር ብለህ ራስህን ኃጥእ አድርግ ያን ጊዜ እግዚአብሔር ያጸድቅሃልና፡፡ ወዳጄ ሆይ በእግዚአብሔር ዘንድ እንድትመሰገን ራስህን አታመስግን፤ ሌሎችም ያመሰግኑህ ዘንድ አትውደድ፡፡ ክብር ታገኝ ዘንድ ትሕትናን ገንዘብ አድርግ መጨረሻውን ሳታውቅ ሰው ሲበድል ብታይ አትጥላው አትናቀውም። አንተ ግን ስለ እርሱ ወደ እግዚአብሔር በጸሎትህ ይምረው ዘንድ ጸልይ። የእግዚአብሔር ምሕረት ብዙ ነውና ኃጥአንን ይምራቸዋል። ክርስቲያኖችን ያሳድድ የነበረ ጳውሎስንም ሐዋርያ አደረገው። ቀራጭ የነበረውን ማቴዎስንም የወንጌል ጸሐፊ አደረገው። እግዚአብሔር ሽፍታ ሆኖ የሰውን ገንዘብ ሲዘርፍ የኖረ ለአባ በግዑ ምሕረት እንዳደረገለት አስተውል። እግዚአብሔር በቀኙ እንደተሰቀለው ሽፍታ በመጨረሻ ዘመኑ መረጠው የመንግሥተ ሰማያትም ወራሽ አደረገው"።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ እና #ከገድላት_አንደበት)
https://t.me/finotebirhan12
🔴 ስንክሳር#ታኅሣሥ_28

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ታኅሣሥ 28 በህች ዕለት #የጌና_በዓል ሆነ። ይኸውም የልደት በዓል ነው፣ ከእንዴናው አገር ሰዎች መቶ ሃምሳ ወንዶች ሃያ አራት ሴቶች በሰማዕትነት ሞቱ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ዕለተ_ገና

ታኅሣሥ ሃያ ስምንት በዚህች ዕለት የገና በዓል ሆነ። ይኸውም የልደት በዓል ነው”። ይህም እንዲህ ነው በአምላካችን በረቀቀ ጥበቡ ሰዎች ሁሉ ይቈጠሩ ዘንድ ስማቸውንም ይጻፋና ይመዘገቡ ዘንድ ከንጉሥ ቄሣር ትእዛዝ መጣ። ስለዚህም ከእመቤታችን ከከበረች ድንግል ማርያም ጋር ሊቆጠር ዮሴፍ ከናዝሬት ወደ ቤተልሔም የርሱንና የቡርክት ድንግል ማርያምን ስም ሊስመዘግብ ወጣ እርሱ ከይሁዳ ነገድ ከዳዊት ወገን ነውና ቤተልሔምም የዳዊት ቦታው ናትና።

የከበረ ወንጌል እንደተናገረ ከዚህም በኋላ ከዚያ ሳሉ የምትወልድበት ቀን ደረሰ የበኵር ልጇንም ወለደች አውራ ጣቱንም አሠረችው በጨርቅም ጠቅልላ በበረት አስተኛችው ለማደሪያቸውም ቦታ አልነበራቸውምና። በዚያ ሰፈር እረኞች ነበሩ ሌሊትም በየተራቸው ተግተው መንጋቸውን ይጠብቁ ነበር። እነሆ የእግዚአብሔር መልአክ አጠገባቸው ቆመ የእግዚአብሔርም ብርሃን በላያቸው በራ ታላቅ ፍርሀትም ፈሩ መልአኩም "ለእናንተና ለመላው ዓለም ደስታ የሚሆን ታላቅ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ" አላቸው።

"እነሆ ዛሬ በዳዊት አገር መድኅን የሆነ ጌታ ክርስቶስ ተወልዶላችኋልና። ለእናንተም ምልክት እንዲህ ነው ሕፃኑ አውራ ጣቱን ታሥሮ በጨርቅ ተጠቅልሎ በበረት ውስጥ ተኝቶ ታገኙታላችሁ" አላቸው። ድንገትም ከዚያ መልአክ ጋር ብዙ የሰማይ ሠራዊት እግዚአብሔርን እያመሰገኑ "በሰማይ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በምድርም ሰላም በሰው በጎ ፈቃድ እያለ መጡ።

ከዚህም በኋላ መላእክት ከእነርሱ ዘንድ ባረጉ ጊዜ እነዚህ እረኞች ሰዎች እርስበርሳቸው "ኑ ወደ ቤተ ልሔም ሔደን ይህን እግዚአብሔር የገለጠውንን ነገር እንወቅ" አሉ። ፈጥነውም ሔዱ ማርያምንና ዮሴፍን ሕፃኑንም በበረት ውስጥ ተኝተ አገኟቸው። አይተውም የነገሩዋቸው ስለዚህ ሕፃን እንደሆነ አወቁ እረኞች የነገሩዋቸውን የሰሙ ሁሉ አደነቁ። እረኞችም ለሕፃኑ ሰግደው እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ወደ ቦታቸውም ተመለሱ።

ከወገናችን ሰው ሁኖ ለጐበኘንና ይቅር ላለን እግዚአብሔር ምስጋና ይሁን ለዘላለሙ አሜን።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በሰማዕታት ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።
https://t.me/finotebirhan12