የጽርሐ ጽዮን ሐዋርያት ጎላ ቅዱስ ሚካኤል የፍኖተ ብርሃን ሰ/ት/ቤት (Official Channel)
2.62K subscribers
6.21K photos
67 videos
79 files
1.72K links
ይህ በጽ/ጽ/ሐ/ጎ/ቅ/ሚካኤል ቤ/ክ ፍ/ብ/ሰ/ት/ቤት እውቅና የተሰጠው የቴሌግራም ቻናል ነው።
Download Telegram
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ የመጀመሪያ ቀን ውሎው በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ውሳኔ ሰጠ።

የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በሰጠው ዕለታዊ መግለጫ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዓመት ሁለት ጊዜ የሚከናወነው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ የጥቅምት ወር ምልዓተ ጉባዔውን ጥቅምት 11 ቀን በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በመክፈቻ ጸሎት መጀመሩን አስታውሷል።

የቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤትን በመወከል መግለጫውን የሰጡት መምህር ዳንኤል ሰይፈሚካኤል ምልዓተ ጉባዔው ዛሬ ጥቅምት 12 ቀን የመጀመሪያ ቀን ጉባዔውን ያከናወነ ሲሆን 16 አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ማጽደቁን ገልጸዋል።

በጠዋቱ ውሎ 7 ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትን አጀንዳ እንዲቀርጹ ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን እነዚህም ሊቃነ ጳጳሳት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ፣ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ፣ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ፣ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፣ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ፣ ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል እና ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ናቸው ፡፡ ኮሚቴው በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ በሰብሳቢነት በብፁዕ አቡነ ዲዎስቆሮስ በአስረጂነት ተሰብስቧል።

ምልዓተ ጉባኤው በከሰዓቱ ውሎም ከ16ቱ አጀንዳዎች በ4ቱ ላይ ውሳኔ የሰጠ መስጠቱን ያስታወቀ ሲሆን እነዚህም ውሳኔዎች፦

1 ቅዱስነታቸው በጠዋቱ የመክፈቻ ጸሎት ያስተላለፉት መልዕክት በቀጣይ የሥራ መመሪያ አድርጎ ምልዓተ ጉባዔው አጽድቋል፡፡

2 ከጥቅምት 4-10 በነበረው የሰበካ መንፈሳዊ ዓለም ዓቀፍ ጉባኤ የነበሩ የቡድን ውይይቶች በቃለ ጉባኤ ቀርቦ ቃለ ጉባዔውን ምልዓተ ጉባዔው የ2018 ዓ.ም የሥራ መመሪያ አድርጎ አፅድቋል፡፡

3 ሀገራዊ ሰላምን አስመልክቶ ምልዓተ ጉባዔው በግንቦት ወር ተወያይቶ ሊቃነ ጳጳሳትን የያዘ ኮሚቴ ያዋቀረ ሲሆን ኮሚቴው የተሰጠውን ኃላፊነት አጠንክሮ እንዲቀጥል ተወያይቶ አጽድቋል፡፡

4 በትግራይ የተፈጠረው ወቅታዊ ክፍፍልን አስመልክቶ የተወያየ ሲሆን በውይይቱም ሕዝቡ ሕዝባችን አብያተ ክርስቲያናቱም የቤተክርስቲያን ሀብት እንደመሆናቸው ቀደም ብሎ የተዋቀረው የሰላም ኮሚቴ ሥራውን አጠንክሮ እንዲቀጥል በምልዓተ ጉባኤው ወስኗል፡፡

ጉባዔው በነገው ዕለትም ቀጥሎ በቀሪዎቹ 12 አጀንዳዎች ላይ ውይይት ያደርጋል፡፡
ደብሩሰ ለአባ አረጋዊ ትመስል ደብረ ሲና
ዘኀደረ በላዕሌሃ እግዚአብሔር ሐጹረ የዐውዳ
ወጽጌረዳ በትእምርተ መስቀል🌹

     🌹የአባ አረጋዊ ደብር እግዚአብሔር በላዩ ያደረ ደብረ ሲናን ትመስላለች እነሆ በጽጌረዳ ትእምርተ መስቀል ተከብባለች፡፡

በነገው እለት የጻድቁ አባታችን አቡነ አረጋዊ የተሰወሩበት ዓመታዊ ክብረ በዓል በደብራችን ታቦተ ሕጉ ወጥቶ በታላቅ ድምቀት ይከበራል።
ጻድቁአቡነ አረጋዊ

ጥቅምት ዐሥራ አራት በዚህች ቀን ታላቁና የከበረው አባታችን አቡነ አረጋዊ (ዘሚካኤል) የተሰወሩበት ነው።

እኚህ አባት ከ9 ቅዱሳን አባቶች አንዱ ሲሆኑ
አባታቸው ይስሐቅ የሮም ንጉስ ነበሩ፡፡ እናታቸው ንግስት እድና ይባሉ ነበር፡፡ የመጀመሪያ ስማቸው ዘሚካኤል ነው፡፡ ጥበብ መንፈሳዊ ሲማሩ አድገው ወደ እስክንድርያ ገዳም ገቡ፡፡ አበምኔቱ አባ ጳኩሚስ በፈቃደ እግዚአብሔር የመጡ መሆናቸውን አውቀው መዓረገ ምንኩስና ሰጥተዋቸዋል፡፡

የንጉሳዊ የቅንጦት ኑሮ ንቀው ትተው ገዳም ገብተው በምንኩስና ተወስነዋል፡፡ አባታችን በተጋድሏቸውም ከአባ እንጦንስ፣ ከአባ ጳውሊ እና ከአባ መቃርስ ቀጥሎ በአራተኛ ማዕረግ አበ መነኮሳት ሆነው ተመርጠዋል።

በገዳመ ዳውናስ 7 ዓመት ከቆዩ በኋላ ወደ ሮም ተመልሰው ሲያስተምሩ የሀገራችን ኢትዮጵያን ዜና ሰምተው ለመምጣት በ480 ዓ.ም ከአባ ፍሬምናጦስ በኋላ መንገድ ጀመሩ፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም በክንፉ ተሸክሞ አክሱም አድርሷቸዋል፡፡

ተመልሰውም ሄደው ስለ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ  መስክረዋል፡፡ ሐዋርያ ሳይላክላት በሃይማኖት በምግባር ጸንታ ትኖራለች ብለው ለሰባቱ ዘመዶቻቸው አበው መነኮሳት ነገሯቸው፡፡ ስምንቱም ጓዛቸውን ጠቅልለው በሮም ነግሶ የነበሩ ይስሐቅን (አባ ገሪማን) ጨምረው ንጉስ አልአሜዳ በነገሰ በአምስተኛ ዓመት ማለትም በ480 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ዘጠኝ ሆነው መጥተዋል፡፡

አባ አረጋዊ እናታቸው ቅድስት እድናን ደቀ መዝሙራቸውን ማትያስን አስከትለው እግረ መንገዳቸውን እያስተማሩና ድውያንን እየፈወሱ ደብረ ዳሞ ደረሰዋል፡፡

ከእግረ ደብር ሆነው አሁን ይህን ተራራ በምን ልወጣው እችላለሁ እያሉ ሲያወጡ ሲያወርዱ በንግግሩ ሐሰት የሌለበት አምላካችን በነቢዩ ዳዊት ላይ አድሮ በመዝሙር 90/91፥11-16 ላይ “በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና፤ እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሡሃል። በተኵላና በእባብ ላይ ትጫማለህ፤ አንበሳውንና ዘንዶውን ትረግጣለህ። እንዳለው የታዘዘ ዘንዶ መጥቶ ስድሳ ክንድ በሚያህል ጅራቱ ጠምጥሞ ቅዱስ ሚካኤል ሰይፈ እሳት ይዞ እየጠበቃቸው ከተራራው አናት አድርሷቸዋል፡፡

ወዲያው ሃሌ ሉያ ለአብ ሃሌ ሉያ ለወልድ ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ ብለው አመስግነዋል፡፡ ቦታውም ደብረ ሃሌ ሉያ ተብሏል፡፡ በዚያ ዕለት ግማሽ ህብስት በልተው ጠገቡ፤ ከዚያ በኋላ ግን ምድራዊ ሕብስት አልተመገቡም፡፡ በሰንበተ ክርስቲያን ከቅዳሴ በኋላ ሕብስተ ሰማያዊ እያመጡላቸው ይመገቡ ነበር እንጂ፡፡ ኋላም ዜና ጽድቃቸውን ሰምተው ከስድስት ሺህ ያላነሱ ደቀ መዛሙርት ተሰብስበውላቸዋል፡፡

ዘጠና ዘጠኝ አመት ሲሞላቸው ጌታ በመንፈቀ ሌሊት ተገልጾ ምድራዊ መንግስትህን ትተህ ስላገለገልከኝ ህልፈት ሽረት የሌለባት ሰማያዊ መንግስቴን አወርስሃለሁ ብሎ ቃልኪዳን ሰጣቸው፡፡ በስምህ የተማጸነውን እስከ አስራ አምስት ትውልድ ድረስ እምርልሃለሁ አንተም ከሞት ገጽ ትሰወራለህ ብሎ ተስፋቸውን ነገራቸው፡፡ እሳቸው መነኮሳቱን ሰብስበው ከእንግዲህ በሥጋ አታዩኝም ብለው ነግረዋቸው አበምኔት ሾመውላቸው በዚህች ዕለት በዚያው በደብረ ዳሞ ተራራ በስተምስራቅ አቅጣጫ ተሰውረዋል።

   የጻድቁ አባታችን አቡነ አረጋዊ ረድኤት በረከት አይለየን!!
የጻድቁ አባታችን አቡነ አረጋዊ  ዓመታዊ ክብረ በዓል በደብራችን በጽርሐ ጽዮን ሐዋርያትና ጎላ ቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክ በታላቅ ድምቀት ተከብሮ ዋለ ።

 የጻድቁ አባታችን አቡነ አረጋዊ የተሠወሩበት ዓመታዊ ክብረ በዓል በዛሬው እለት ጥቅምት 14/2018 ዓ.ም በደብራችን በጽርሐ ጽዮን ሐዋርያትና ጎላ ቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክ  የደብራችን ዋና አስተዳዳሪ መልአከ ብርሃናት አዕምሮ ምስጋናው እና ሌሎችም የቤተክርስቲያናችን ሊቃውንት በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተከብሮ ዋለ።

ይህ በጽ/ጽ/ሐ/ጎ/ቅ/ሚካኤል ቤ/ክ ፍ/ብ/ሰ/ት/ቤት እውቅና የተሰጠው የቴሌግራም ቻናል ነው።
https://t.me/finotebirhan12

የዩቲዩብ ቻናላችን
https://youtube.com/@finotebirhan12

የፌስቡክ ገጻችን https://www.facebook.com/Fbirhan?mibextid=2JQ9oc

የቲክቶክ አካውንታችን https://www.tiktok.com/@finotebirhan?_t=8i8eHwFI3Es&_r=1

የዌብሳይት ገጻችን
https://finotebirhan.com
የጻድቁ አቡነ አረጋዊ ዓመታዊ ክብረ በዓል 2018 ዓ.ም በደብራችን በፎቶ