የጽርሐ ጽዮን ሐዋርያት ጎላ ቅዱስ ሚካኤል የፍኖተ ብርሃን ሰ/ት/ቤት (Official Channel)
2.58K subscribers
6.1K photos
67 videos
60 files
1.7K links
ይህ በጽ/ጽ/ሐ/ጎ/ቅ/ሚካኤል ቤ/ክ ፍ/ብ/ሰ/ት/ቤት እውቅና የተሰጠው የቴሌግራም ቻናል ነው።
Download Telegram
ነገ ሐሙስ የማይቀርበት የሰንበት ት/ቤታች የአውደ ምህረት ጉባኤ
👉 ከእህታችን ጎን እንሁን በጸሎት፣ በገንዘብ እንዲሁም በተዘጋጀው የምሳ መርሐግብር ላይ በመገኝት
#ኅዳር_16

🔴 ስንክሳር #ኅዳር_16

በዚህች ቀን #የቅዱስ_አቡናፍር ቤተ ክርስቲያኑ የከበረችበት ነው፣ የእስክንድርያ ሀገር ሊቀ ጳጳሳት #ቅዱስ_ዮሐንስ ያረፈበት ነው፣ #ቅዱስ_ኪስጦስ በሰማዕትነት ያረፈበት ነው፣ #ቅድስት_ጣጡስ በሰማዕትነት ያረፈችበት ነው፣ የመነኰስ #አባ_ዳንኤልና_የንጉሥ_አኖሬዎስ የዕረፍታቸው መታሰቢያ ነው።

#ቅዱስ_አባት_አባ_ዮሐንስ

በዚህችም ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት አርባ ስምንተኛ የሆነ የእስክንድርያ ሀገር ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባት አባ ዮሐንስ አረፈ። ይህም ቅዱስ አባት የቆጵሮስ ሀገር ሰው ነው እጅግም ባለጸጋ ነው በእስክንድርያ አገርም የሚኖር ሆነ አባቱ አገረ ገዥ ነበርና ሚስትም አግብቶ ልጆችን ወለደ ከዚህም በኋላ ሚስቱም ልጆቹም ሞቱ።

በዚያንም ጊዜ ገንዘቡን ሁሉ ለድኆችና ለችግረኞች ሰጠ መጸወተ እርሱም መንኵሶ በታላቅ ገድል የተጠመደ ሁኖ በጎ ሥራዎችን ትሩፋትን ጨምሮ በመሥራት እግዚአብሔርን ደስ አሰኘው።

ከበጎ ሥራዎቹና ከትሩፋቱም ከቀናች ሃይማኖቱ ከአገልግሎቱና ከደግነቱ ከጽድቁ ማማር የተነሣ በግብጽ አገር የሚኖሩ ኤጲስቆጶሳት ሁሉም ተሰማምተው ይዘው ወሰዱት ያለ ፈቃዱም በእስክንድርያ አገር ላይ ሊቀ ጵጵስና ሾሙትና በወንጌላዊ ማርቆስ ወንበር ላይ አስቀመጡት ። ያን ጊዜ የከበረ ወንጌልን አነበበ በሹመቱና በክህነቱም ብርሃን ተገለጸ ብዙዎች ድንቆች የሆኑ ተአምራትንም አደረገ።

ለድኆችና ለችግረኞች ሁልጊዜ ያለማቋረጥ የሚሹትን የሚሰጣቸው ሆነ ስለዚህም የሚራራ ዮሐንስ ተብሎ ተጠራ ። በአይሁድና በአረማውያን ዘንድ የሚአስፈራ ሆነ በመጸሐፈ ገድሉ እንደተጻፈ እጅግ ይፈሩትና ያከብሩት ነበርና መንጋዎቹንም በበጎ አጠባበቅ ጠበቃቸው እግዚአብሔርንም አገልግሎ በሰላም አረፈ።

ለእግዚአብሔርም ምሰጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር እና #ከገድላት_አንደበት)
https://t.me/finotebirhan12
የእህታችን የሣምራዊት አለሙን ሕክምና ወጪ በኮሚቴውና በእርሷ ስም የንግድ ባንክ አካውንት ተከፍቷል ለመርዳት የምንፈልግ በተጠቀሰው አካውንት ቁጥር የአቅማችንን እናድርግ
🔴 ስንክሳር#ኅዳር_24

ኅዳር ሃያ አራት በዚች ቀን #የሃያ_አራቱ_ካህናተ ሰማይ የበዓላቸው መታሰቢያ ነው፣ #አቡነ_ተክለ_ሃይማኖትም ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ጋር የሥሉስ ቅዱስን መንበር ያጠኑበት ነው፣ #የአቡነ_ዜና_ማርቆስ ልደታቸው ነው፣ #ቅዱስ_አዝቂር_ሰማዕት ከአርባ ስምንት ሰዎች ጋር በሰማዕትነት ያረፈበት ፣ #ቅዱስ_አባ_ዮሴፍ_ዘሀገረ_ፃን ያረፈበት ዕለት ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ሃያ_አራቱ_ካህናተ_ሰማይ

ኅዳር ሃያ አራት በዚህች ቀን በእግዚአብሔር ዙፋን ዙሪያ የሚኖሩ የሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ የበዓላቸው መታሰቢያ ነው ።

እሊህም ሥጋ የሌላቸው ረቂቃን የእውነት ካህናት የሆኑ ከቅዱሳን ሁሉ በላይ የሆኑና ከሰማይ ሠራዊት ሁሉ ከፍ ከፍ ያሉ ናቸው እነርሱም ለእግዚአብሔር ቀራቢዎች በመሆን ለሰው ወገን የሚማልዱ ከእጃቸው ውስጥ ካለ ማዕጠንት ጋርነ እንደ ዕጣን የቅዱሳንን ጸሎት የሚያቀርቡ ናቸው ያለእነርሱም አቅራቢነት ጽድቅና ምጽዋት ወደ እግዙአብሔር አይቀርብም።

ወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ እንዲህ ብሎ እንደተናገረ። በዙፋኑ ዙሪያ ሃያ አራት መንበሮች አሉ በእነዚያ መንበሮች ላይም ሃያ አራት አለቆች ተቀምጠዋል ነጭ ልብስ ለብሰዋል በራሳቸውም ላይ የወርቅ አክሊል አለ።

ሁለተኛም እንዲህ አለ ሌላም መልአክ መጥቶ በመሠዊያው ፊት ቆሞ የወርቅ ጽንሐሕ ይዟል በመንበሩ ፊት ባለ በወርቁ መሠዊያ ላይም የቅዱሳንን ሁሉ ጸሎት ያሳርግ ዘንድ ብዙ ዕጣንን ሰጡት ። የዕጣኑም ጢስ ከቅዱሳኑ ጸሎት ጋር በዚያ መልአክ እጅ ወደ እግዚአብሔር ፊት ዐረገ ።

የነበረ የሚኖር የአማልክት አምላክ እግዚአብሔር ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ነው እያሉ በመዓልትና በሌሊት ዕረፍት የላቸውም ። እሊህም እንስሶቹ ለዘላለሙ ሕያው ለሚሆን በዙፋን ላይ ለተቀመጠ ለሱ እንዲህ እያሉ ክብር ምስጋና አቀረቡ ።

እሊህ ሃያ አራቱ አለቆች አክሊላቸውን በዙፋኑ ፊት አውርደው ለዘላለሙ ሕያው ለሚሆኑ በዙፋን ላይ ለተቀመጠ ለእሱ ሰገዱለት ። አክሊላቸውንም ወደ ዙፋኑ ፊት ወስደው አቤቱ ፈጣሪያችን ኃይልና ምስጋና ክብር ላንተ ይገባል ይሉታል አንተ ሁሉን ፈጥረሃል የተፈጠረውም ሁሉ በአንተ ፈቃድ ይኖራልና ።

እነርሱ በእግዚአብሔር ዘንድ በባለሟልነት እጅግ የቀረቡ መሆናቸውንና ስለሁላችን የአዳም ልጆች ስለሚለምኑና ስለሚማልዱ ከብሉይና ከሐዲስ የከበሩ መጻሕፍት ምስክር ሁነዋል ስለዚህም የበዓላቸውን መታሰቢያ እናደርግ ዘንድ የቤተ ክርስቲያን መምህራን አዘዙ ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አቡነ_ተክለ_ሃይማኖት

አቡነ ተክለ ሃይማኖትም ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ጋር የሥሉስ ቅዱስን መንበር እንዳጠኑ፡- አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወደ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ መጥተው በሐይቁ ዳር ቆመው ሳለ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ተገልጦላቸው ነው በእግሩ በውኃው ላይ እየሄደ እያሳያቸው ተከትለውት እንዲሄዱ የነገራቸው። አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖትም መልአኩን ተከትለው ሐይቁን በእግራቸው ተራምደው ተሻግረው አቡነ ኢየሱስ ሞዐን አገኟቸው፡፡ እርሳቸውም አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወደ እርሳቸው እየመጡ እንደሆነ በመንፈስ ዐውቀው ነበርና ሲያገኟቸው በጣም ተደስተው ከተቀበሏቸው በኋላ አመነኩሰዋቸዋል፡፡

ከዚህም በኋላ አባታችን በዚያው በሐይቅ በታላቅ ተጋድሎ መኖር ጀመሩ፡፡ አክፍሎትንም በየሳምንቱ ያከፍላሉ፣ ከእሁድና ከቅዳሜ በቀር ምንም አይቀምሱም ነበር፡፡ በእነዚህም ዕለት የአጃ ቂጣ ወይም የዱር ቅጠል ይመጉ ነበር፡፡ ወዛቸው እንደ ውኃ ፈስሶ ምድሪቷን እስኪያርሳት ድረስ እስከ 70 ሺህ ስግደትንም በመስገድ ራሳቸውን እጅግ አደከሙ፡፡ በእነደዚህ ዓይነቱ ተጋድሎ ላይ ሳሉ ነው ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ድንገት ነጥቆ ወስዶ ከሥሉስ ቅዱስ ዙፋን ፊት ያቆማቸው፡፡

ከዚህ በኋላ ስለሆነው ነገር ራሳቸው አባታችን ተክለ ሃይማኖት ሲናገሩ ‹‹…ከዚህ በኋላ መልአኩ ወደ ሰማይ አውጥቶ ከመጋረጃው ውስጥ አስገብቶ ከሥላሴ ዙፋን ፊት አቆመኝና ሰገድኩለት፡፡ ከዚያ አስቀድሞ በማላውቀው በሌላ ምስጋና አመሰገንኩት፡፡ ‹ተክለ ሃይማኖት ክፍልህ ከ24ቱ ካህናቶቼ ጋር ይሁን› የሚል ቃል ከዙፋኑ ውስጥ ወጣ፡፡ የወርቅ ጽና አምጥተው ሰጡኝና ከእነርሱ ጋር አንድነት አጠንሁ፡፡ ምስጋናዬ ከምስጋናቸው ጋር ልብሴም እንደልብሳቸው ሆነ፡፡ ፈጣሪዬንም በሦስትነቱ ተገልጦ አየሁት፡፡ በጸሎትህ የሚታመን ሰው ሁሉ ስለአንተ ይድናል አለኝ…..›› (ገድለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገጽ 216-223)

ይህንን ታላቅ በዓል ነው ዛሬ የምናከብረው፡፡ አቡነ ተክለሃይማኖት እንኳን አንደበታቸው የለበሱትም ልብሳቸውም ጭምር እግዚአብሔርን በሰው አንደበት እንደሚያመሰግን በቅዱስ ገድላቸው ላይ ተጽፏል።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኅ_ኅዳር እና #ከገድላት_አንደበት)
https://t.me/finotebirhan12
🔴ስንክሳር#ኅዳር_25

#ቅዱስ_መርቆሬዎስ_ሰማዕት (ፒሉፓዴር)

በዚህች ቀን የስሙ ትርጓሜ መርቆሬዎስ የሆነ ፒሉፓዴር በሰማዕትነት አረፈ። መርቆሬዎስም ማለት የአብ ወዳጅ ማለት ነው በሁለተኛ ትርጓሜ የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ማለት ነው።

ይህም ቅዱስ አስሊጥ ከምትባል አገር ነው እርሷም የአባቱና የአያቱ አገር ናት እርሱ ግን ተወልዶ ያደገው በሮሜ ከተማ ነው። የአባቱና የአያቱ ሥራቸው አውሬ ማደን ነበር በአንዲት ዕለትም እንደልማዳቸው ለማደን ወጡ ከገጸ ከለባት ወገንም ሁለት ወንዶች ተገናኙአቸውና የቅዱስ መርቆሬዎስን አያት በሉት። ሁለተኛም አባቱን ሊበሉት ፈለጉ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክም ከለከላቸው፤ ከእርሱ የሚወጣ መልካም ፍሬ ስለአለ አትንኩት አላቸው።

ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ ዙሪያቸውን በእሳት ከበባቸው። በተቸገሩ ጊዜም ወደ ቅዱስ መርቆሬዎስ አባት መጥተው ሰገዱለት። በዚያንም ጊዜ እግዚአብሔር ፍጥረታቸውን ወደገራምነት ለወጠውና እንደ በጎች የዋሆች ሆኑ። አብረውትም ወደ መንደር ገቡ።

ከዚህም በኋላ ቅዱስ መርቆሬዎስ በተወለደ ጊዜ ስሙን ፒሉፓዴር ብለው ጠሩት። የውሻ መልክ ያላቸውም በእነርሱ ዘንድ ብዙ ዘመናት የሚኖሩ ሆኑ ከዚህም በኋላ ክርስቲያኖች ሆኑ። የቅዱስ መርቆሬዎስ ወላጆች አስቀድሞ አረማውያን ነበሩና የክርስትና ጥምቀትንም ጸጋ በተቀበሉ ጊዜ የቅዱስ መርቆሬዎስን አባት ኖኅ ብለው ሰየሙት። እናቱንም ታቦት አሏት። ፒሉፓዴርንም መርቆሬዎስ ብለው ሰየሙት።

የውሻ መልክ ያላቸው ግን የእግዚአብሔር መልአክ በተገለጸላቸው ጊዜ እንደ ነገራቸው ለቅዱስ መርቆሬዎስ አባት የሚታዘዙና የሚያገለግሉ ሆኑ። ንጉሡም የኖኅንና የውሻ መልክ ያላቸውን ዜና በሰማ ጊዜ ወደርሱ አስቀረባቸው በዚያንም ጊዜ እግዚአብሔር በንጉሡ ፊት የቀድሞ ፍጥረታቸውን መልሶላቸው ንጉሡ ያቀረባቸውን ሁሉንም አራዊት አጠፏቸው።

ንጉሡም ይህን በአየ ጊዜ እጅግ ፈራ፤ የአራዊትንም ተፈጥሮአቸውን ያርቅ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እንዲማልድ የቅዱስ መርቆሬዎስን አባት ለመነው። እርሱም በለመነ ጊዜ ክብር ይግባውና ጌታችን ተፈጥሮአቸውን መልሶላቸው ገራሞች ሆኑ።

ከዚህም በኋላ የቅዱስ መርቆሬዎስን አባት ንጉሡ ወስዶ ገዥና የሠራዊት አለቃ አድርጎ ሾመው። የውሻ አርአያ ያላቸውም ይታዘዙለት ነበር። ከእርሳቸውም የተነሣ ሁሉም ይፈሩ ነበር።

ከዚህም በኋላ የቅዱስ መርቆሬዎስን አባት የሾመውን ንጉሥ ይወጋ ዘንድ ከሀዲ ንጉሥ ተነሣ። ንጉሡም ከጦር ሠራዊት ጋር የቅዱስ መርቆሬዎስን አባት ወደ ጦርነት ላከው። ከሀዲው ንጉሥ ግን እነዚያን የውሻ አርአያ ያላቸውን አባብለውና ሸንግለው ወደርሱ ያመጧቸው ዘንድ ወታደሮችን ላከ። በአመጧቸውም ጊዜ ሃይማኖታቸውን ይለውጡ ዘንድ አብዝቶ ሸነገላቸው፤ ባልሰሙትም ጊዜ ሊአሠቃያቸው ጀመረ አንዱ አምልጦ ሸሽቶ ወደ ጌታው ሔደ። ሁለተኛውም በሰማዕትነት ሞተ።

ከጦር ሜዳ የቅዱስ መርቆሬዎስ አባት በተመለሰ ጊዜ ሚስቱንና ልጁን ፈለጋቸው ግን አላገኛቸውም። ንጉሡ የሱ ወገኖች ድል እንደሆኑ በሰማ ጊዜ የቅዱስ መርቆሬዎስ አባት መኰንኑ የሞተ መስሎት ነበርና የቅዱስ መርቆሬዎስን እናት ወስዶ ሊአገባት ፈለገ። ከንጉሥ ወታደሮችም አንዱ ንጉሡ ያሰበውን በጽሙና ነገራት። እርሷም ይህንኑ ወታደር ከሀገር ውስጥ በሥውር ያወጣት ዘንድ ለመነችውና ከልጇ ከብፁዕ መርቆሬዎስ ጋር ወጥታ ወደ ሌላ አገር ሔደች።

ንጉሡም ከእርሱ የሆነውን የመኰንኑም የመርቆሬዎስን አባት ሚስቱን ለማግባት ማሰቡን እንዳይነግሩት አዘዘ። የውሻ መልኮች ያላቸው ከእርሱ ጋር እንዳሉ የተቆጣም እንደሆነ እንደሚአመጣቸውና አገሮችን ያጠፋሉ ብሎ ይጠራጠራልና ስለዚህ እጅግ ይፈራዋል።

ከዚህም በኋላ ደግሞ በንጉሡ ላይ ጦርነት ተነሣ። የቅዱስ መርቆሬዎስም አባት ወደ ጦርነቱ ወጣ በእግዚአብሔርም ፈቃድ ይዘው ማረኩት። ወደ ሮሜውም ንጉሥ አቀረቡት ንጉሡም ክርስቲያን ነበርና የተማረከው መኰንን ክርስቲያን መሆኑን በአወቀ ጊዜ አልገደለውም። በክብር አኖረው እንጂ እጅግም ወደደውና ከጥቂት ቀኖች በኋላ በመርዶሳውያን አገሮች ሁሉ ላይ ገዥ አድርጎ ሾመው።

ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ፈቃድ ሚስቱና ልጁ መርቆሬዎስ ወዳሉበት አገር ደረሰ። ሚስቱም በቤተ ክርስቲያን ደጃፍ በአየችው ጊዜ ባሏ አንደሆነ አወቀችው። እርሱ ግን አላወቃትም።

በአንዲትም ዕለት እርሱና ጭፍሮቹ ከእንግዳ ማረፊያ ቤት በወጡ ጊዜ ልጅዋን መርቆሬዎስን ወስዳ ያማሩ ልብሶችን አልብሳ ሒዶ ከመኰንኑ ፈረስ ላይ እንዲቀመጥ አዘዘችው። እርሱም አባቱ ነው። በተቀመጠ ጊዜም ጭፍሮች ይዘው ወደ መኰንኑ ፊት አቀረቡት መኰንኑም ልጁ እንደሆነ አላወቀምና በእርሱ ላይ ተቆጣ።

የመርቆሬዎስም እናት መጥታ ጌታዬ ሆይ እኛ መጻተኞች ነን አንተም መጻተኛ እንደሆንክ በአወቅሁ ጊዜ ልጅህ ሁኖ ልጄ ከአንተ ጋር እንዲሆን አሰብኩ አለችው። እርሱም ጠየቃት እንዴት እንደተሰደደችም መረመራት እርሷም ሚስቱ እንደሆነች ነገረችው በዚያንም ጊዜ አወቃት ልጁን መርቆሬዎስንም አወቀው እጅግም ደስ ብሏቸው እግዚአብሔርን አመሰገኑት ያንንም የእንግዳ ማረፊያ ቤት ቤተ ክርስቲያን አደረጉት እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ በአንድነት ኖሩ።

ከዚህም በኋላ አባቱና እናቱ በሞቱ ጊዜ ንጉሡ ቅዱስ መርቆሬዎስን ወስዶ በአባቱ ፈንታ በመርዶሳውያን አገር ላይ ሾመው። ቅዱስ መርቆሬዎስም መኰንንነትን በተሾመ ጊዜ ያ ገጸ ከልብ ከርሱ ጋር ነበር ወደ ጦርነትም አብሮት የሚወጣ ሆነ።

ለመዋጋትም በሚሻ ጊዜ የቀድሞ የአራዊት የሆነ ተፈጥሮውን እግዚአብሔር ይመልስለት ነበር ማንም ሊቋቋመው የሚችል የለም። ለቅዱስ መርቆሬዎስም ታላቅ የድል አድራጊነት ኃይል ተሰጠው ዜናውም በሁሉ ቦታ ተሰማ ከቤተ መንግሥት ሰዎችም ከፍ ከፍ አለ።

እንዲህም ሆነ ያን ጊዜ በዚያን ወራት በሮሜ አገር ጣዖትን የሚያመልክ ዳኬዎስ የሚባል ንጉሥ አለ። ጠላቶቹም የበርበር ሰዎች ተነሡበት። እርሱም ከእርሳቸው ጋር ሊዋጋ ሠራዊቱን ሰብስቦ ወጣ። እነርሱ ግን እንደ ባሕር አሸዋ ብዙ ነበሩ ብዛታቸውንም በአየ ጊዜ ደንግጦ እጅግ ፈራ። ቅዱስ መርቆሬዎስም እግዚአብሔር ያጠፋቸው ዘንድ በእጃችንም አሳልፎ ሊሰጣቸው አለውና አትፍራ አለው።

ከዚህም በኋላ ቅዱስ መርቆሬዎስ የእግዚአብሔርን መልአክ በውጊያው ውስጥ አየው የተሳለ ሰይፍም በእጁ ውስጥ አለ ያቺንም ሰይፍ ሰጠውና እንዲህ አለው ጠላቶችህን ድል በአደረግህ ጊዜ ፈጣሪህ እግዚአብሔርን አስበው።

ጠላቶቹንም ድል አድርጎ በሰላም ተመለሰ መልአኩም ዳግመኛ ተገልጦለት ለምን የፈጣሪህን የእግዚአብሔርን ስም መጥራት ረሳህ አለው።

ጦርነቱም ከተፈጸመ በኋላ ንጉሥ ዳኬዎስ ለጣዖታቱ ዕጣን በማሳረግ በዓልን ሊያደርግ ወደደ። ቅዱስ መርቆሬዎስም ለበዓል ማክበር አብሮት አልወጣም ወደ ቤቱ ሔደ እንጂ። ሰዎችም ቅዱስ መርቆሬዎስ እንዳልመጣና ዕጣንን በማሳረግም እንዳልተባበረ አስረዱት።

በዚያንም ጊዜ ንጉሥ መልእክተኞችን ልኮ ቅዱስ መርቆሬዎስን ወደርሱ አስመጣው። በመዘግየቱም አድንቆ ለአማልክት ዕጣን ለማሳረግ ከእኔ ጋር ያልመጣህ የእኔን ፍቅር እንዴት ተውህ አለው። በዚያንም ጊዜ ትጥቁንና ልብሱን ወረወረለትና ንጉሡን እንዲህ አለው። እኔ ክብር ይግባውና ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስን አልክደውም ለረከሱ ጣዖታትም አልሰግድም።
ንጉሥ ዳኬዎስም ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጣ። እርጥብ በሆኑ የሽመል በትሮች እንዲደበድቡት አዘዘ። ሁለተኛም ከላም ቆዳ በተሠራ ጅራፍ ይገርፉት ዘንድ አዘዘ ንጉሡ እንዳዘዘ ይህን ሁሉ አደረጉበት።

በዚያንም ጊዜ የአገር ሰዎች ስለ ቅዱስ መርቆሬዎስ እንዳይነሡበት ፈርቶ የቀጰዶቅያና የእስያ ክፍል ወደ ሆነች ወደ ቂሣርያ በብረት ማሠሪያ አሥሮ ላከው። በዚያም እንዲአሠቃዩት አዘዘ ከአሠቃዩትም በኋላ ንጉሥ ዳኬዎስ እንዳዘዘ ራሱን በሰይፍ ቆረጡትና ተጋድሎውን ፈጽሞ በመንግሥተ ሰማያት የሕይወት አክሊልን ተቀበለ።

የማይጠፋ ሰማያዊ አክሊልንም ተቀዳጅቶ ወደ ዘላለም ሕይወት ከገባ በኋላ በዓለሙ ሁሉ አብያተ ክርስተያናት ታነፁለት። እግዚአብሔርም ታላላቅ የሆኑ ድንቆች ተአምራትን በውስጣቸው ገለጠ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ መርቆሬዎስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር)
https://t.me/finotebirhan12
🔴 ስንክሳር#ኅዳር_26

ኅዳር ሃያ ስድስት በዚህች ዕለት #የአቡነ_ሀብተ_ማርያም ዕረፍት ነው፣ #አቡነ_ኢየሱስ_ሞዓ ዕረፍት ነው፣ #የሀገረ_ናግራን_ሰማዕታትና የአባታቸውም #የቅዱስ_ኂሩት መታሰቢያቸውም ነው፣ #የቅዱስ_ቢላርያኖስ_ሚስቱ_ኪልቅያና_እኅቱ_ታቱስብያ በሰማዕትነት ያረፉበት ነው።

#ቅዱስ_አቡነ_ሀብተ_ማርያም

በዚህችም ቀን የተመሰገነና የከበረ ንጹሕም የሆነ የኢትዮጵያዊ አባታችን የሀብተ ማርያም የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው።

የዚህ ቅዱስ አባት የትውልድ አገሩ የራውዕይ በምትባል በስተ ምሥራቅ ባለች ሀገር ውስጥ ነው በዚያም ስሙ ፍሬ ቡሩክ የሚባል አንድ ሰው ነበረ ይህም ክቡራንና ታላላቅ ከሚባሉት ከዚች አገር ታላላቅ ሰዎች አንዱ ነው ። እጅግም ሀብታም ነበር ብዙ ንብረትም አለው በሕጋዊ ጋብቻም ስሟ ዮስቴና የምትባል ብላቴና ድንግልን አገባ ይቺም የተመረጠች በበጎ ሥራ የተሸለመችና ያጌጠች ናት።

ነገር ግን አስቀድመን በዚህ ዓለም ከሕግ ባሏ ጋር በንጹሕ ጋብቻ እግዚአብሔርን በመፍራት ምጽዋትን በመስጠት የዋህነትን ትሕትናን ፍቅርን ትዕግሥትን ገንዘብ አድርጋ በጾም በጸሎት ተወስና እንደኖረች እንነግራችኋለን ። በእንደዚህም ሳለች ጌታችን በወንጌል ሰው ዓለሙን ቢያተርፍ ነፍሱን ካጠፋ ምን ይጠቅመዋል እንዳለ ላንቺ በዚህ ዓለም መኖር ምን ይረባሽ የሚል ሐሳብ መጣባት ።

ከዚህም በኋላ ወጣች ፈጥናም በሀገርዋ ትይዩ ወደሆነ ምድረ በዳ ደርሳ ወደ መካከሉ ገባች በዚያም በረሀ አራዊት እንጂ ሰው አይኖርበትም በዚያም ደጃፍዋ የተከፈተ ታናሽ ዋሻ አግኝታ ምንም ምን ሳትነጋገር ወደ ውስጧ ገብታ ቆመች የዳዊትንም መዝሙር የሚጸልይ ሰው አይታ ደነገጠች።

እርሱም ባያት ጊዜ ፍርሀትና መንቀጥቀጥ በላዩ ወረደበት በመስቀል ምልክትም በላይዋ አማትቦ የእግዚአብሔርን ስም ጠራ እንዳልሸሸችም አይቶ ሰው መሆንዋን አወቀ በአወቀም ጊዜ እንዲህ ብሎ ገሠጻት ወደዚህ ምን አመጣሽ ለእኔ እንቅፋት ልትሆኚ ነውን አሁንም ከዚህ ፈጥነሽ ሒጂ አላት ።

እርሷም አባቴ ሆይ አንተ እንዳሰብከው አይደለሁም እኔ ለሕያው እግዚአብሔር ልጅ ለኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋዩ ነኝ እንጂ በእርሱ ፍቅርና በእናቱ በእመቤቴ በቅድስት ድንግል ማርያም ፍቅር ያለኝን ሁሉ ትቼ ንቄ ከዓለም ወጥቼ ወደዚህ መጣሁ በዚህ ቦታም ከአራዊት በቀር ሰው እንዳለ አላወቅሁም አሁንም አባቴ ይቅርታ አድርግልኝ ወደ ሌላ ቦታ እሔዳለሁ አለችው ።

በዚያንም ጊዜ ከርሷ የሚሆነውን መንፈስ ቅዱስ ገልጾለት እንዲህ አላት ዜናው ወደ ዓለም ሁሉ የሚወጣ በሕይወተ ሥጋም እያለ የብዙዎች ሰዎች ነፍሳትን ከሲኦል የሚያወጣ እንደ መላእክትም ክንፎች ተሰጥተውት ወደ አርያም ወጥቶ የሥላሴን የአንድነትና የሦስትነትን ምሥጢር የሚያይ ልጅን ትወልጂ ዘንድ አለሽና ወደ ቤትሽ ተመለሽ አላት ።

ቅድስት ዮስቴናም ከዚያ ሽማግሌ ባሕታዊ ይህን በሰማች ጊዜ አድንቃ የፈጣሪዬ ፈቃዱ ከሆነ ብላ ወደቤቷ ተመለሰች።

ከጥቂት ቀኖችም በኋላ ፀንሳ ይህን ደም ግባቱ መልኩ የሚያምር ልጅን ወለደች በእናትና በአባቱ ቤትም ታላቅ ደስታ ሁኖ ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች ለዘመዶቻቸውና ለጎረቤቶቻቸው ታላቅ ምሳ አደረጉ እነርሱም በጠገቡ ጊዜ እነርሱንም ሕፃኑንም መረቋቸው ።

ሕፃኑም አርባ ቀን በሆነው ጊዜ እንደ ሕጉና እንደ ሥርዓቱ ወደ ቤተ ክርስቲያን ወሰዱት ካህኑም ተቀብሎ በአጠመቀው ጊዜ ስሙን ሀብተ ማርያም ብሎ ሰይሞ ለክርስትና አባቱ ሰጠው ሕፃኑም ጥቂት በአደገ ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ ሲሉ ሰምቶ ሕፃኑ ሀብተ ማርያም በልቡ ይቺ ጸሎት መልካም ናት እኔም መርጫታለሁ በዚህ ዓለም ስሕተትን አስቦ ከመሥራት በሚመጣውም ዓለም ከገሀነም እንደምድንባት አውቃለሁና አለ ። ይህንንም ብሎ የሚሠራውን ማንም ሳያውቅበት ይህን ጸሎት ከማዘውተር ጋር ሌሊቱን ሁሉ በመስገድ ይፀልይ ነበር ።

ከዚህም በኋላ አባቱ የበጎች ጠባቂ አደረገው በአንዲት ዕለትም በጎቹን አየጠበቀ ሳለ ብዙ የበግ ጠባቂዎች እሸት ተሸክመው መጥተው ና እንብላ አሉት እርሱ ግን ከወዴት እንዳመጣችሁት የማላውቀውን አልበላም አላቸው እነርሱም በቁጣ ዐይን ተመልክተው ተጠቃቀሱበት ።

እሸቱንም በልተው ከጨረሱ በኋላ የከበረ ሕፃን ሀብተ ማርያምም ታላቅ ዝናም ስለመጣ ወደየቤታችን እንመለስ ከዚህ የምንጠለልበትና የምንጠጋበት ቤት ወይም ዋሻ የለምና አላቸው ። እነርሱም እኛ የማናየውን የሚያይ ሌላ ዐይን አለህን በሰማይ ፊት ምንም ደመና ሳይኖር ሀገሩም ብራ ሆኖ ሲታይ እንዴት ይዘንማል ትላለህ አሉት እርሱም እኔ የማውቀውን እናንተ አታውቁትም ግን ወደ ቤታችሁ ግቡ አላቸው እረኞችም ባልሰሙት ጊዜ ፈጥኖ ተነሥቶ በጎቹን እያስሮጠ ወደ ቤቱ ገባ ። ወደ ቤቱም በገባ ጊዜ ታላቅ ዝናም መጣ ነፋሳትም ነፈሱ መብረቆችም ተብለጨለጩ ነጎድጓድም ተሰማ ደመናትም ተነዋወጹ ይህ ሁሉ በላያቸው ሲወርድ መሸሺያ አላገኙም ።

ከጥቂት ቀኖችም በኋላ በጎቹን እየጠበቀ ሳለ ብዙ የበግ እረኞችም አብረውት ነበሩ አንድ የበግ ጠባቂም መጥቶ የወጣት ሀብተ ማርያምን በትር ነጠቀውና ሔደ ብላቴና ሀብተ ምርያምም በትሬን ለምን ትቀማኛለህ አለው እረኛውም በትዕቢት ቃል በጉልበቴ ነጥቄሃለሁ አለው ብላቴና ሀብተ ማርያምም እኔ ኃይል የለኝም ነገር ግን በጎቼን የምጠብቅበትን በትሬን እንዳትወስድብኝ በሕያው እግዚአብሔር ስም አምልሃለሁ አለው ያም የበግ ጠባቂ እምቢ አልኩህ አለው ።

ብላቴናው ሀብተ ማርያምም አንድ ጊዜ በፈጣሪዬ ስም አማልኩህ ከእንግዲህ ወዲያ ደግሜ አላምልህም በአንተ ላይ የሚደረገውን ራስህ ታውቀዋለህ ይህንንም ተናግሮ ዝም አለ ። በዚያንም ጊዜ ያ የበግ ጠባቂ በአየር ውስጥ ተዘቅዝቆ ተሰቀለ የእግዚአብሔር አገልጋይ ሀብተ ማርያም ማረኝ እያለ ይጮህ ጀመረ የልዑል እግዚአብሔርን ስም አቃልሏልና ተሰቅሎ ዋለ እረኞች ሁሉም አይተው አደነቁ ፈሩትም ይህን ሰነፍ ማርልን እግዚአብሔር ያደረገልህን ኃይል አይተናልና አሁንም ስለ እምቤታችን ድንግል ማርያም ይቅር በለው አሉት ። ብላቴናው ሀብተ ማርያምም በውኑ እኔ የሰቀልኩት ነውን በእግዚአብሔር ስም አማልኩት እንጂ የኃይሉን ጽናት በላዩ ሊገልጥ እርሱ እግዚአብሔር ሰቀለው አሁን እርሱ ከፈቀደ ያውርደው እርሱ መሐሪና ይቅር ባይ ነውና ይህንንም በተናገረ ጊዜ ወርዶ በእግሩ ቆመ ወደርሱም መጥቶ ሰገደለት ።

ከረጂም ዘመናትም በኋላ ስሟ እለአድባር ወደምትባል ገዳም ሒዶ ከዚያም የምንኩስናን ሥርዓትና ሕግ በአበምኔቱ በተመረጠ አባ መልከጸዴቅ እጅ ተቀበለ ከዚያም ቅዱሳን መነኰሳት ወደሚኖሩበት ሔዶ ታላቅ ተጋድሎ ጀመረ ።

እርሱም በባሕር መካከል በመቆም የዳዊትን መዝሙር ሁሉንም ያነባል በባሕር ውስጥም ሰጥሞ ግምባሩ አሸዋ እስቲነካው አምስት መቶ ጊዜ ይሰግዳል ከሰንበት ቀኖችም በቀር እህል አይቀምስም ነበር ከዚህም በኋላ እህልን ትቶ እንደ ዋልያዎች የዱር ቅጠል የሚመገብ ሆነ ።

አርባ አርባ ሰማንያ ሰማንያ ቀን የሚጾምበት ጊዜ አለ በባሕር ውስጥ በሌሊት ቁሞ በማደር በቀንም አራቱን ወንጌላት ያነባል ሌሎች መጻሕፍትንም በእንዲህ ያለ ሥራ ብዙ ዘመን ኖረ።
ብዙ ተጋድሎንና ድካምንም በአስረዘመ ጊዜ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደርሱ ተገልጦ መጣ ከእርሱ ጋርም የመላእክት አለቆች የከበሩ ሚካኤልና ገብርኤል የመላእክት ማኅበርም ሁሉ በዙሪያው ሁነው እያመሰገኑት ነበር ወዳጄ ሀብተ ማርያም ሰላም ላንተ ይሁን አለው ። በዚያንም ጊዜ ከግርማው የተነሣ ወድቆ እንደ በድን ሆነ ጌታችንም በከበሩ እጆቹ አንሥቶ እፍ አለበትና ጽና ኃይልህን ላድሳት እንጂ ላጠፋህ አልመጣሁምና ተጋድሎህና ድካምህ ሁሉ በኢየሩሳሌም ሰማያዊት እንደ ተጻፈ በእውነት እነግርሃለሁ ።

እነሆ እኔ በጎ ዋጋህን በዚህም ዓለም በሚመጣውም ዓለም እከፍልሃለሁ የማቴዎስንና የማርቆስን ወንጌል በምታነብ ጊዜ በተራራዎችና በዋሻዎች በፍርኩታ ተሠውረው ወደሚኖሩ እንዳንተ ካሉ ቅዱሳን ጋር ለመገናኘት በላዩ ተቀምጠህ ወደ ምሥራቅ ወደ ምዕራብ ወደ ሰሜንና ደቡብ የምትበርበት የብርሃን ሠረገላ ሰጠሁህ ሉቃስና ዮሐንስ የጻፉትን ወንጌል ባነበብክ ጊዜ ሥጋዬንና ደሜን በዚያ ትቀበል ዘንድ በላዩ ተቀምጠህ ወደ ኢየሩሳሌም የምትሔድበት የእሳት ሠረገላ ሰጠሁህ አለው ።

ከብዙ ዘመናትና ከብዙ ተጋድሎ በኋላ የሚሞትበት ጊዜ ሲደርስ ለሞቱ ምክንያት የሚሆን ቸነፈር ያዘው ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደርሱ መጥቶ ወዳጄ ሀብተ ማርያም ሰላም ላንተ ይሁን ዛሬ ግን የመጣሁት ከድካም ወደ እረፍት ልወስድህ ነው እነሆ ሰባት አክሊላትን አዘጋጅቼልሃለሁና አንዱ ስለ ድንግልናህ ሁለተኛው ዓለምንና በውስጡ ያለውን ሁሉን ትተህ በመውጣትህ ሦስተኛው ፍጹም ስለሆነው ምንኩስናህ አራተኛው አራቱን ወንጌሎች አዘውትረህ የምታነብ በመሆንህ አምስተኛው ስለ እኔ ፍቅር መራብና መጠማትን ስለታገሥክ ስድስተኛው በልብህ ቂምና በቀልን ባለማሳደርህ ሰባተኛውም ስለ ንጹሕ ክህነትህና ስለምታሳርገው ያማረ የተወደደ ዕጣንህና መሥዋዕትህ ሰጠሁህ እሊህ ሰባቱ አክሊላትም ለየአንዳንዳቸው ዐሥራ አምስት ዐሥራ አምስት ኅብር አላቸው ።

መታሰቢያህን ካደረጉና በጸሎትህ ከተማፀኑ ጋር የምትገባበትን ቤት በውስጧ አምስት መቶ የወርቅ አምዶች የተተከሉባትን ሰጠሁህ ደግሞ የእሳት መስቀልን የወርቅ ጫማን የብርሀን ልብስን ሥውር የሆነ መና እሰጥሃለሁ አለው ።

መድኃኒታችንም ይህን ቃል ኪዳን ሲሰጠው በየነገዳቸውና በየሥርዓታቸው ዘጠና ዘጠኝ የመላእክት ሠራዊት መጥተው ወዳጃችን ሰላም ላንተ ይሁን ዛሬስ ከፀሐይ ሰባት እጅ ወደምታበራ ሀገራችን በዝማሬና በማኅሌት አክብረን ልንወስድህ መጣን አሉት ። አባታችን አባ ሀብተ ማርያምም በሰማያት ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በምድርም ሰላም ሆነ የሰው ነጻነቱ ሊሰጠው አለ ።

ይህንንም በተናገረ ጊዜ ጌታችን በሦስትነቱ ተገልጦ ታየውና የመጥምቁ ዮሐንስን ሀገር ተጠጋግታ ያለች ከፀሐይ ሰባት እጅ የምታበራ ሀገርን እሰጥህ ዘንድ በራሴ ማልኩልህ አለው ።

መታሰቢያህን የሚያደርገውን በስምህ ለቤተ ክርስቲያን መባ የሚሰጠውን ስምህንም የጠራውን ወደዚች አገር አገባዋለሁ አራቱን ወንጌሎችም እያነበብክ ስለኖርክ የየአንዲቱን ቃል ፍሬዋን አንዳንድ ሽህ አደረግሁልህ ይኸውም ካንተ በኋላ ለሚመጡ ልጆችህ መጽሐፈ ገድልህን ለሚያነቡና በእምነት ለሚሰሙ የገድልህ መጽሐፍ በተነበበበት ውኃ ለሚረጩ ለሚነከሩበት ይህን ቃል ኪዳን ሰጥቼሃለሁ ።

ከዚህም በኋላ መድኃኒታችን አፉን ሦስት ጊዜ ሳመው በዚያንም ጊዜ ከፍቅሩ ጣዕም ብዛት የተነሣ ነፍሱ ከሥጋው ተለየች ጌታችንም ተቀብሎ አቅፎ ከእርሱ ጋር አሳረጋት ። በመላእክት ጉባኤም ብዙ ምስጋና ተደረገ ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር#ገድለ_አቡነ_ኢየሱስ_ሞዐ እና #ከገድላት_አንደበት)
https://t.me/finotebirhan12
🔴 የዛሬን ሕዳር 26 እሁድ ውሎዋችንን ለእህታችን የሳምራዊት የሕክምና ወጪ ገንዘብ ማሰባሰቢያ የምሳ መርሐግብር ላይ እንሳተፍ በአካል መገኝት ያልቻልን ከዚህ በታች በተጠቀስው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አካውንት የምንችለውን እንለግስ
👉1000443049448
ሰሎሞን ክብረት፣ ሣምራዊት አለሙና ቤተልሄም ገነነው
🔴 ስንክሳር#ኅዳር_27

ኅዳር ሃያ ሰባት በዚህች ቀን አባታችን #አቡነ_ተክለ_ሐዋርያት ዕረፍታቸው ነው፣ ሕዋሳቱ የተቆራረጠ #ቅዱስ_ያዕቆብ_ዘግሙድ በሰማዕትነት አረፈ፣ ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ #ቅዱስ_ፊልሞና_ሐዋርያ ዕረፍቱ ነው፣ በንሑር ከሚባል አገር #ቅዱስ_ጢሞቴዎስ በሰማዕትነት አረፈ።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር#ከገድላት_አንደበት)
https://t.me/finotebirhan12
🔴ስንክሳር#ኅዳር_28

ኅዳር ሃያ ስምንት በዚህች ቀን #ቅዱስ_ሰረባሞን በሰማዕትነት ያረፈበት፣ በደብረ ቊንጽል ተጋድሏቸውን የፈጸሙ #አባ_ሊቃኖስ የተሰወሩበት ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባ_ሊቃኖስ

በዚችም ቀን በኢትዮጵያ ምድር በደብረ ቊንጽል ተጋድሏቸውን የፈጸሙ አባ ሊቃኖስ ተሰወሩ።

አቡነ ሊቃኖስ ከዘጠኙ ቅዱሳን ውስጥ አቡነ ሊቃኖስ ለየት የሚሉበት ነገር ቢኖር ዓሥሩም የእጆቻቸውና የእግሮቻቸው ጣቶች እንደፋና ያበሩ ነበር፡፡ ይህንንም ገድለ አቡነ አረጋዊ "ቆመው ጸሎት በሚጸልዩበት ጊዜ ዓሥሩ የእጆቻቸው ጣቶችና ዓሥሩ የእግሮቻቸው ጣቶች እንደፋና የሚያበሩበትና እንደመብረቅ የሚብለጨልጩበት ጊዜ አለ" በማለት ይገልጸዋል፡፡ በሥዕላቸውም ላይ ይህንኑ ለማሳየት አባቶቻችን የራሳቸውን ጥበብ ተጠቅመዋል፡፡

የአቡነ ሊቃኖስ ገዳማቸው በደብረ ቁናጽል አክሱም ከአባ ጰንጠሌዎን ገዳም አቅራቢያ ይገኛል፡፡ ጻድቁ ብዙ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን ያደረጉ ነበር፡፡ መላእክትም ዘወትር ባለመለየት ይጎበኙዋቸው ነበር፡፡ ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም ዘወትር እየተገለጠላቸው ይባርካቸውና ቃልኪዳን ይሰጣቸው ነበር፡፡

በጸሎታቸውም አጋንንትን አውጥተዋል፣ ድውያንን ፈውሰዋል፣ ዕውራንን አብርተዋል፣ ሙታንን አንሥተዋል፡፡ ስለዘጠኙ ቅዱሳን ሐዋርያዊ አገልግሎት ከአቡነ አረጋዊ ገድል ጋር ጥቅምት 14 በስፋት ስለተጻፈ ከዚያ ላይ ይመለከቷል፡፡

ከተስዓቱ ቅዱሳን ውስጥ አራቱ ሞትን ሳያዩ ተሰውረዋል፡፡ አቡነ አረጋዊ ጥቅምት 14 ቀን ተሰወሩ፡፡ አቡ ገሪማ ሰኔ 17 ቀን፣ አቡነ አፍጼ ግንቦት 29 ቀን፣ አቡነ ሊቃኖስ ህዳር 28 ቀን ተሰወሩ፡፡

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር እና #ከገድላት_አንደበት)
https://t.me/finotebirhan12
🔴 ስንክሳር#ኅዳር_29

በዚች ቀን #የአቡነ_እጨጌ_ዮሐንስ ዘጠገሮ ልደታቸው ነው፣ በዲዮቅልጥያኖስ ዘመን #የቅዱሳን_ሰማዕታተ_ክርስቶስ መታሰቢያቸው ነው፣ የሰማዕታት መፈጸሚያ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት #ቅዱስ_ጴጥሮስ በሰማዕትነት አረፈ፣ የሊቀ ሐዋርያት ጴጥሮስ ደቀ መዝሙሩ #ቅዱስ_ቀሌምንጦስ_ሐዋርያ በሰማዕትነት አረፈ።

#አቡነ_እጨጌ_ዮሐንስ_ዘጠገሮ
ኅዳር ሃያ ዘጠኝ በዚህች ቀን የአቡነ እጨጌ ዮሐንስ ዘጠገሮ ልደታቸው ነው።

ጻድቁ አባታችን የተወለዱት በኢየሩሳሌም አውራጃ ልዩ ስሙ ሳሬራ በሚባል ቦታ ነው፡፡ የካቲት 28 ቀን ተፀንሰው ህዳር 29 ተወለዱ፡፡ አባታቸው ድላሶር እናታቸው እምነ ጽዮን ይባላሉ፡፡ ሲወለዱ በወላጆቻቸው ቤት ውስጥ ብርሃን ወርዷል፡፡ አባታችን ገና በተወለዱ በ5 ዓመታቸው ወላጆቻቸው ወደ እግዚአብሔር ቤት ይዘዋቸው የእመቤታችንን ሥዕል ተመልክተው በደስታ ተመልተው ሳቁ፡፡ አምላክን የወለደች የብርሃን እናቱ እመቤታችንም ከምሥሉ ወጥታ ‹‹በምን አውቀኸኝ ነው?›› ብላ አቅፋ ሳመችውና ‹‹ከእንግዲ ወዲህ የልጄ አገልጋይ ትሆናለህ ኑሮህም እንደ መላእክት ይሆናል በአንተ ምክንያት ብዙ ሰዎች ይድናሉ በምድር ላይም 500 ትኖራለህ" ብላ ባርካው ተሰወረች፡፡

50 ዓመትም በበረሃ ሲጋደል ኖሮ ከ50 ዓመት በኃላ በደመና ተጭኖ በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል መሪነት ወደ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ መጡ፡፡ ጻድቁ አባታችን በአቡነ ተክለሃይማኖት ዘመን መጨረሻ የመጡ ሲሆን ምንኩስና ከደብረ ሊባኖስ ገዳም ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ተቀብለው በዚያው በድብረ ሊባኖስ ገዳም ለ50 ዓመት በጾምና በጸሎት በተጋድሎ ኖዋል፡፡ ከዚኽም በኋላ አባ ዩሐንስ ወደ ተዘጋቸላቸው ምድር በቅዱስ ገብርኤል አሳሳቢነት ወደ ጠገሮ መጡ፡፡ ይኽም ጠገሮ ያለው ገዳማቸው በሰሜን ሸዋ በመንዝና ይፋት ክልል መዘዞ በሚባል ቦታ ሲደርሱ በእግር አንድ ሰዓት ከተጓዙ በኃላ ይገኛል፡፡

ሕዝቡ በተለምዶ እጨ ዮሐንስ እያለ ይጠራቸዋል እንጂ ስማቸው እጨጌ ዮሐንስ ነው፡፡ አቡነ እጨጌ ዮሐንስ መስቀል ከሰማይ የወረደላቸው ታላቅ አባት ናቸው፡፡ መስቀሉም ሁልጊዜ ተአምር ይሠራል፡፡ በልደታቸው ቀን ኅዳር 29 ቀን መስቀሉ ከመቅደሱ ወጥቶ በካህናቱ ታጅቦ ወደ ጸበሉ ሲወርድ ከየት እንደመጣ ሳይታሰብ ደመና መጥቶ ከመስቀሉ ላይ ብቻ እረቦና እንደ ጃንጥላ ተዘርግቶ አብሮ ወደ ጸበሉ ይወርዳል፡፡ እዛው ቆይቶ መስቀሉ ሲመለስም አብሮ አጅቦ ይመለስና መስቀሉ ቤተ መቅደስ ውስጥ ሲገባ ደመናው ወዴት እንደተበተነ ሳይታወቅ ይጠፋል፡፡ ይህ በዘመናችንም ጭምር እየታየ ያለ ታላቅ ተአምር ነው፡፡

አባታችን በታላቀ ተጋድሎ ሣሉ ሰይጣን የሀገሩን ሰዎች በጠላትነት እንዲነሡባቸው አደረገ፡፡ ሰዎቹም አባታችንን እንዴት እንደሚያጠፏቸው ይማከሩ ጀመር፡፡ ሊገድሏቸው ፈልገው ቅድስናቸው በሁሉ ዘንድ የታወቀ ነውና ፈሩ፡፡ ከዚኽም በኋላ ‹‹ለምን ከመንደራችን ከወንድ ያረገዘች ሴት ፈልገን እሳቸው አስረገዟት ብለን በሐሰት እንከሳቸው?›› ብለው ተማከሩ፡፡ ብዙ ወርቅና ብርም ለአንዲት ሴት ሰጥተው በሐሰት ከእርሱ አርግዣለሁ ብላ እንድትመሰክር አደረጓት፡፡ አባታችንም በሕዝብ ፊት በሐሰት ተከሰሱ፡፡ ጻድቁም ‹‹አንቺ ሴት ከእኔ ነው ያረገሽው?›› አሏት እርሷም ‹‹አዎ ከአንተ ነው ልትክድ ነው እንዴ?›› አለቻቸው፡፡ አባታችንም በዚህ አዝነው ‹‹በአንቺና በእኔ መካከል እግዚአብሔር ይፍረድ›› ሲሉ ያች ሴት ወዲያው ለሁለት ተሰንጥቃ ሞተች፡፡ የአገሩ ሰዎችም እጅግ ፈሩ፡፡ አባታችንም ምድሪቱን እረገሟት፡፡ ‹‹የተዘራው ዘር አይብቀልብሽ፣ የተተከለው አይፅደቅ፣ ብርድና ውርጭ ይፈራረቅብሽ›› ብለው እረግመዋት በደመና ተጭነው ወደ ሰሜን ጎንደር እስቴ ጉንደ ተክለተሃማኖት ሔዱ፡፡

አቡነ ዩሐንስ በመላው ኢትዮጵያ ወንጌልን እየተዘዋወሩ ያስተማሩ ሲሆን ከቅድስናቸው የተነሣ በፀሐይ ላይ 50 ዓመት፣ በጨረቃ ላይ 50 ዓመት፣ በደመና ላይ 50 እንዲሁም ዓለምን በክንፋቸው በመዞር በደመና ላይ 50 የኖሩ ከሰው ተወልደው ከመላእክት የተደመሩ ታላቅ ጻድቅ ናቸው፡፡ በይፋት ጠግሮ በዓለወልድ፣ በአፋር አዘሎ፣ በመንዝ ፍርኩታ ኪዳነምሕረት፣ በደብረ ሊባኖስ፣ በጎንድ ተክለ ሃይማኖት በሌሎችም ቦታዎች በመዘዋወር በታላቅ ተጋድሎ ኖረዋል፡፡ አባታችን ከሰማይ መስቀል የወረደላቸው ሲሆን ዛሬም በገዳማቸው የሔደ ሰው በወረደው በእጃቸው መስቀል እየተዳበሰ ቆመው በጸለዩበት ባሕር በጠበላቸው ይጠመቃል፡፡ በተጨማሪም ይይዙት በነበረውም መቋሚያቸው በመዳበር በረከትን ማግኘት ይቻላል፡፡ ቆመው ከጸለዩበት ባሕር ውስጥ ደረቅ አሸዋ ይወጣል፡፡ አባ ዩሐንስ 500 ዓመት ከኖሩ በኃላ እረፍተ ዘመናቸው ሲደርስ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ከ15 ነቢያት፣ ከ12 ሐዋሪያት፣ ሄሮድስ ያስፈጃቸው ከመቶ አርባ አራት ሺ ሕፃናት፣ ከአብርሃም ከይስሐቅ፣ ከዕቆብ ጋር ሁሉንም ነገደ መላእክትን፣ ጻድቃን ሰማዕታትን ሁሉ አስከትሎ መጥቶ ታላቅ ቃልኪዳን ገብቶላቸዋል፡፡ "ስምህን የጠራ ገዳምህን የረገጠ፣ መባ የሰጠ፣ ቤተ ክርስትያንህን የሠራ ያሠራ የረዳ፣ ገድልህን የሰማ ያሰማ ያስተረጎመ፣ መታሰቢያን ያደረገ እስከ 10 ትውልድ እምርልሀለው፤ ንስሀ ሳይገባ አይሞትም፣ ልጅ መውለድ ባይችል እኔ ልጅ እሰጠዋለሁ፤ ገድልህን በቤትህ ያስቀመጠ እርኩስ መንፈስ፣ ክፉ አጋንንት ቸነፈር ወባ መልአከ ጽልመት አይነካውም፡፡ በገዳምህ መነኩሴ ቢቀበር በሰማይ ክንፍ አበቅልለታለሁ፤ አይሁድም አረማዊም ያላመነ ያልተጠመቀ በገዳምህ መጥቶ ቢያርፍ ይቅር እልልሃለሁ፣ እንደ መቃብሬ ጉልጎታ እንደተቀበረ አድርጌ እቆጥርልሃለሁ…" የሚል ቃል ኪዳን ከሰጣቸው በኃላ ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡

ቅዱስ አባታችንም በ500 ዓመታቸው ሐምሌ 29 ቀን ዐርፈው በጎንድ ተክለ ሃይማኖት ተቀብረዋል፡፡ በሰሜን ጎንደር የሚገኘውን ይህንን ገዳም ጻድቁ ራሳቸው ናቸው የመሠረቱት፡፡ ነገር ግን የገዳሙን ስያሜ በአባታቸው በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ስም አድርገውታል፡፡ አቡነ ዮሐንስ ካረፉ በኋላ በእርግማናቸው መሠረት በመንዝና በይፋት ብርዱ ድርቁ ስለበዛባቸው አንድ ብቁ ባሕታዊ ከበዓታቸው ወጥተው ‹‹በሐሜታችሁ ምክንያት እጨ ዮሐንስ ስለረገማችሁ ነው የእርሱን ዐፅም ካላመጣችሁ ብርዱ ውርጩ ድርቁም አይጠፋላችሁም›› አሏቸው፡፡ ሕዝቡም አባታችን በጉንድ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከተቀበሩ ከ134 ዓመት በኃላ በቅዱሳን እየተመሩ ሄደው በሌሊት ግማሽ ዐፅማቸውን አምጥተው በሀገራቸው አምጥተው ስላስቀመጡ ብርዱና ውርጩ በመንዝ እየቀነሰላቸው መጥቷል፡፡ ዛሬም በሀገሩ ብርዱና ውርጭ ሲበዛ የጻድቁን ታቦት ሲያወጡ ውርጩ ይጠፋል፡፡ ጠገሮ በሚባለው ገዳማቸው ውስጥ የሚገኘው ጠበላቸው እጅግ አስደናቂ ነው፡፡

ግማሽ ዐፅማቸውን ከጉንደ ተክለሃይማኖት አምጥተው አርባ ሐራ መዳኒዓለም አጠገብ በላይ በፍሩክታ ኪዳነምሕረት መጋቢት 18 ፍልሰተ ዐፅማቸው ተከናወነ፡፡ ምድሪቷም ተባረከች፣ የዘሩትንም አበቀለች፣ ውርጩም ብርዱም ቀነሰ፣ ዝናብ አልዘንብ ሲል ወይም ሰብል የሚጨርስ አንበጣ ሲመጣ ታቦታቸው ወጥቶ ምህላ ይያዛል። ወድያውም መቅሰፍት ይርቃል፣ ዝናብም ይዘንባል፡፡ ጻድቁ ደመናን፣ ጨረቃንና ፀሐይን በእጃቸው እየያዙ ይጸልዩ ነበር፡፡ በጠገሮ፣ በአዘሎ፣ በፍርኩታና በሌሎቹም ታላላቅ ቦታቦዎች ላይ በእያንዳንዱ ገዳም ሃምሳ ሃምሳ ዓመት በጸሎት ኖረው በአጠቃላይ በ500 ዓመታቸው ነው ያረፉት፡፡ ዐፅማቸው መንዝ ከአርባ ሐራ መድኃኔዓለም አጠገብ ፍርኩታ ኪዳነ ምሕረት ገዳም ውስጥ ይገኛል፡፡
🔴 ስንክሳር#ኅዳር_30

በዚህች ቀን ጻድቁ #ንጉሥ_አፄ_ገብረ_መስቀል ዕረፍቱ ነው፣ ሊቀ ጳጳሳት #ቅዱስ_አባት_አካክዮስ አረፈ፣ #የቅዱሳን_ቆዝሞስና_ድምያኖስ ቤተ ክርስቲያናቸው የከበረችበት ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አፄ_ገብረ_መስቀል_ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮዽያ)

ኅዳር ሠላሳ በዚህች ቀን ጻድቁ ንጉሥ አፄ ገብረ መስቀል ዕረፍቱ ነው።

ዐፄ ካሌብ የናግራንን ሰማዕታት ደም ተበቅሎ በድል ከተመለሰ በኋላ በአቡነ ጰንጠሌዎን እጅ መንኩሶ ገዳም ከገባ በኋላ ልጁ ገብረ መስቀል ነገሠ፡፡ ዐፄ ገብረ መስቀል በእውነትና በቅንነት ከነገሠ በኋላ አመራሩ ከአህጉሪቷ ጽንፍ እስከ ጽንፍ ደረሰ፡፡ በዘመኑም ሁሉ መንግሥቱን የሚቃወም አልተነሣም፤ እርሱም ቤተ ክርስቲያንን ከመሥራት በቀር ወደ ጦርነት የሄደበት ጊዜ የለም፡፡ መንግሥቱንም ይባርክለት ዘንድ ሠራዊቱን ይዞ ወደ አባታችን ወደ አቡነ አረጋዊ ዘንድ ደብረ ዳሞ ሄደና በፊቱ ሰግዶ ‹‹አባቴ ሆይ! እኔን ባሪያህን፣ መንግሥቴንና ሕዝቤን ሠራዊቴንም ሁሉ ባርክ›› እያለ አጥብቆ ማለደው፡፡ አባታችን አረጋዊም ‹‹የአባቶችህን የዳዊትንና የሰሎሞንን መንግሥት የባረከ፣ የአባትህን የካሌብንም መንግሥት የባረከ እግዚአብሔር የአንተንም መንግሥት ይባርክ…›› ብለው ባረኩት፡፡ ከዚህም በኋላ ንጉሥ ዐፀ ገብረ መስቀል አቡነ አረጋዊን የት ቦታ ላይ ቤተክርስቲያን እንደሚሠራ ጠይቋቸው ካሳዩት በኋላ ሲሠራ ሁለት ዓመት የፈጀበት ግሩም ቤተክርስቲያን ሠራላቸውና 12 የወርቅና የብር መስቀሎችን ጨምሮ ብዙ ንዋያተ ቅድሳቶችንና ሥጦታዎችን ሰጣቸው፡፡ ጳጳስም አስመጥቶ አስባረካትና ከማኅበረ በኩር ያመጣውን በወርቅ በብር የተለበጠች የእመቤታችንን ታቦት በውስጧ አስገባ፡፡ ጳጳሱና ንጉሡ ዐፄ ገብረ መስቀልም አቡነ አረጋዊን ‹‹ቀድሰህ አቁርበን›› ብለውት ይቀድስ ዘንድ በገባ ጊዜ መላእክት ሙቀት ያልተለየው ኅብስትና ወይኑን በጽዋ ለቅዳሴው የሚያስፈልገውንም ሁሉ ከሰማይ አወረዱለትና ቀድሶ ሲያበቃ ሁሉንም አቆረባቸው፡፡

ከዚህም በኋላ ንጉሡ ዐፄ ገብረ መስቀል ከተራራው ጫፍ በሚወርድበት ጊዜ አባታችንን ‹‹ይህን የተራራውን መውጫ መሰላል ላፍርሰው ወይስ ልተወው?›› አለው፡፡ አባታችንም ‹‹ለልጅ ልጅ መታሰቢያ እንዲሆን ይህን ድንቅ ሥራ እያየ በፍጥረቱ ሁሉ አንደበት እግዚአብሔር ይመሰገን ዘንድ የደረጃውን መሰላል አፍርሰው፣ ነገር ግን ስለዘንዶው ጅራት ፋንታ ገመድ አብጅ›› አለው፡፡ ንጉሡም እንደታዘዘው የደረጃውን መሰላል አፈረሰውና ወደ ቤተ መንግሥቱ ተመለሰ፡፡ ጻድቁ ንጉሥ በዐፄ ገብረ መስቀል ካበረከተልን ትልቅ ውለታው ውስጥ አንዱ ዛሬ በዩኔስኮ የተመዘገበውን የመስቀል በዓልን በአደባባይ እንዲከበር ያደረገ መሆኑ ነው፡፡ በዘመኑም ካህናቱ ሕዝቡ ሁሉ አደይ አበባ ይዘው ወደ አደባባይ በመውጣት በያሬዳዊ ዝማሬ የመስቀልን በዓል ያከብሩ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ብርሃኗ የሆነ ነገር ግን እርሷ እንደሚገባው መጠን ያላከበረችው ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በዚህ ጻድቅ ንጉሥ በዐፄ ገብረ መስቀል ዘመነ መንግሥት የነበረ ነው፡፡ አብረውም ብዙ ታሪኮችን ፈጽመዋል፡፡ ገዳማትን ላይ በመዟዟር ቅዱስ ያሬድ ዜማን ሲያስተምር ንጉሡ ደግሞ የቤተ ክርስቲያንን ይዞታ ያስፋፉና ቋሚ መተዳደሪያ ይሰጡ ገዳማቱን ያጠናክሩ ነበር፡፡ አቡነ አረጋዊ ደግሞ አብረው ምኩስናን ያስፋፉ ነበር፡፡ ሦስቱም ይህን ተግባራዊ እንዳደረጉ ለማሳያ ይሆን ይሆን ዘንድ ቅዱስ ያሬድ 3 ዓመት ዝማሬ መዋሥዕት ያስተማረባትንና ዛሬም ድረስ ማስመስከሪያ የሆነችውን እጅግ ጥንታዊቷን ዙር አባ ጽርዓ አርያም አቡነ አረጋዊ ገዳምን እንደምሳሌ ማየት እንችላለን፡፡ አቡነ አረጋዊና ቅዱስ ያሬድ በዘንዶ ታዝለው ዓምባው ላይ ከወጡ በኋላ ለንጉሡ ለዐፄ ገብረ መስቀል ደግሞ ተራራውን ባርከው ከፍለው መንገድ አበጅተውላቸው ወደ ዓምባው ወጥተው ሦስቱም በዚያ በጋራ ኖረው ብዙ መንፈሳዊ ሥራን ሠርተዋል፡፡

ጻድቁ ንጉሥ ዐፄ ገብረ መስቀል ከተስዓቱ ቅዱሳን ጋር ሆኖ ብዙ መንፈሳዊ ሥራን ሠርቷል፡፡ ሌላው በዐፄ ገብረ መስቀል ዘመነ መንግሥት ከነበሩት ቅዱሳት አንስት ውስጥ እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ዋነኛዋ ናት፡፡ ይኽችውም ቅድስት ከልጅነቷ ጀምራ በምግባር በሃይማኖት፣ በተጋድሎ በትሩፋት ያጌጠች ናትና ንጉሠ ነገሥቱ ዐፄ ገብረ መስቀል በሁለመናዋ የተመሰገነች መሆኗንና ዝናዋን ስለሰማ ‹‹በጸሎትሽ አስቢኝ›› በማለት ከአገልጋዮቹ ውስጥ እርሷን እንዲያገለግሏት 174 አገልጋዮችን ልኮላታል፡፡ ለነገሥታት ሚስቶች የሚደረገውን በሐርና በወርቅ የተሠሩ ልብሶችና ጫማ ልኮላታል፡፡ ዐፄ ገብረ መስቀል በጽድቅ ሕይወት እየተመላለሱ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን የዋሉት ውለታ እጅግ ብዙ ነው፡፡ ገርዓልታ አካባቢ ከዱጉም ሥላሴ በእግር የ2 ሰዓት መንገድ ርቀት ላይ የቅዱስ ዐፄ ገብረ መስቀል አስደናቂ ፍልፍል ቤተ መቅደስ ይገኛል፡፡

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር እና #ከገድላት_አንደበት)
https://t.me/finotebirhan12