የጽርሐ ጽዮን ሐዋርያት ጎላ ቅዱስ ሚካኤል የፍኖተ ብርሃን ሰ/ት/ቤት (Official Channel)
2.58K subscribers
6.1K photos
67 videos
60 files
1.7K links
ይህ በጽ/ጽ/ሐ/ጎ/ቅ/ሚካኤል ቤ/ክ ፍ/ብ/ሰ/ት/ቤት እውቅና የተሰጠው የቴሌግራም ቻናል ነው።
Download Telegram
🔴#ስንክሳር_#ጥቅምት_28

በዚህች ቀን ከዘጠኙ ቅዱሳን አንዱ የሆኑት #ጻድቁ_አቡነ_ይምዓታ አረፉ፣ዳግመኛም በዚህች ቀን #ቅዱስ_መርትያኖስና_ቅዱስ_መርቆሬዎስ በሰማዕትነት አረፉ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_ይምዓታ_ጻድቅ

ጥቅምት ሃያ ስምንት በዚህች ቀን ከዘጠኙ ቅዱሳን አንዱ የሆኑት ጻድቁ አቡነ ይምዓታ አረፉ።

አባ ይምዓታና 8ቱ ቅዱሳን ወደ ሃገራችን እንደ ገቡ የመጀመሪያ ሥራቸው ቋንቋን መማር ነበር። ልሳነ ግዕዝን በወጉ ተምረው እዛው አክሱም አካባቢ ሥራቸውን አንድ አሉ። በወቅቱ በአቡነ ሰላማ፣ በአብርሃ ወአጽብሐና በአቡነ ሙሴ ቀዳማዊ የተቀጣጠለው ክርስትና በተወሰነ መንገድ ተቀዛቅዞ ነበርና እነ አባ ይምዓታ እንደ ገና አቀጣጠሉት።

ሕዝቡን በራሱ ልሳን ለክርስትና ይነቃቃ ዘንድ ሰበኩት። የካደውን እየመለሱ የቀዘቀዘውን እያሟሟቁ ለዓመታት ወንጌልን ሰበኩ። ቀጣዩ ሥራቸው ደግሞ መጻሕፍትን መተርጐም ሆነ።

ከሃገራቸው ያመጧቸውን ቅዱሳት መጻሕፍት ተከፋፍለው ወደ ግዕዝ ልሳን ተረጐሟቸው። በዚህም ለሃገራችን ትልቁን ውለታ ዋሉ። ይህ ሁሉ ሲሆን እነ አባ ይምዓታ የሚመገቡትም ሆነ የሚጸልዩት በማሕበር ነበር። በመካከላቸውም ፍጹም ፍቅር ነበር። ጸጋ እግዚአብሔር አልተለያቸውም።

የነ አባ ይምዓታ ቀጣዩ ተግባራቸው ደግሞ ገዳማዊ ሕይወትን ማስፋፋት ሆነ:: ይህንን ለማድረግ ግን የግድ መለያየት አስፈለጋቸው:: እያንዳንዱም መንፈስ ቅዱስ ወደ መራው ቦታ ሔደ:: ዸንጠሌዎን በጾማዕት፣ ገሪማ በመደራ፣ ሊቃኖስ በቆናጽል፣ አረጋዊ በዳሞ፣ ጽሕማ በጸድያ፣ ሌሎችም በሌላ ቦታ ገዳማትን መሠረቱ።

አባ ይምዓታ ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ምርጫቸው ገርዓልታ (እዛው ትግራይ) ሆነ። ጻድቁ ወደ ቦታው ሲሔዱ ወንዝ (ባሕር) ተከፍሎላቸዋል። ወደ ቦታው ደርሰውም ገዳም አንጸዋል። በቦታውም ብዙ ተአምራትን ሠርተው በርካታ ደቀ መዛሙርትን አፍርተው፣ ለዘመናት ተጋድለው በገርዓልታ በዚህች ቀን አርፈዋል።

የአቡነ ይምዓታ ፍልፍል ዋሻ ቤተ መቅደስ ትግራይ ገርዓልታ ልዩ ስሙ ‹‹ጎሕ›› ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ይገኛል፡፡ ቤተ መቅደሱ ሰማይን እንደ ምሰሶ ደግፈው የያዙ የሚመስሉ በጣም ረጃጅም ተራሮች መካከል በአንደኛው ጭፍ ላይ ይገኛል፡፡ ቤተ መቅደሱ ከባሕር ወለል በላይ በ2300 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኝ ሲሆን ቤተ መቅደሱ ያለበት የተራራው ርዝመት ብቻውን 300 ሜትር ነው፡፡ ቤተ መቅደሱ በር ላይ ለመድረስ በጭንቅና በፍርሃት ሆኖ ተራራውን እንደዝንጀሮ በእጅ እየቧጠጡ መውጣት ይጠይቃል፡፡ እርሱም ቢሆን በገዳሙ አባቶች እገዛና ድጋፍ ካልሆነ መውጣት የማይቻል ነው፡፡

ቤተ መቅደሱ እጅግ የሚደንቀው በተፈጥሮአዊ አቀማመጡ ብቻ አይደለም ውስጡ ያሉት የግድግዳ ላይ ሥዕሎችም እጅግ ድንቅና ጥንታዊ ናቸው፡፡ ስለዚሁ የአቡነ ይምዓታ እጅግ አስደናቂ ቤተ መቅደስ ገድለ አቡነ አረጋዊ "በሞት በዐረፉ ጊዜ የሥጋቸው ሥርዓተ ግንዘት በመላእክት እጅ ነው የተከናወነው፡፡ ይልቁንም ቁመቱና ርዝመቱ ከታላላቅ ገደል እጅግ በጣም የሚበልጥ የድንጋይ ዓምድ ከወንዝ ማዶ ዘንበል ብሎ መጥቶ ሥጋቸውን በክብር ተቀብሎ በተራራው ጫፍ ላይ እስከዛሬም ድረስ ፈጽሞ ሳይነቃነቅና ሳይናወፅ ቀጥ ብሎ ቆሞ ይገኛል በማለት ይገልጻል፡፡

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኅ_ጥቅምት እና #ዲያቆን_ዮርዳኖስ_አበበ)
https://t.me/finotebirhan12
https://t.me/finotebirhan12
https://t.me/finotebirhan12
🔴#ስንክሳር #ጥቅምት_29
በዚህች ቀን #አቡነ_ሳሙኤል_ዘደብረ_ወገግ አረፉ፣ በከሀዲው ንጉሥ በመክስምያኖስ ዘመን #ቅዱስ_ድሜጥሮስ ዘተሰሎንቄ በሰማዕትነት አረፈ፣ የደብረ ዘኸኝ #መምህር_ጸቃውዐ_ድንግል አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ድሜጥሮስ_ሰማዕት
በዚህችም ቀን በከሀዲው ንጉሥ በመክስምያኖስ ዘመን ቅዱስ ድሜጥሮስ በሰማዕትነት አረፈ።

ይህም ቅዱስ ከተሰሎንቄ ሀገር ነው የከበረች የቤተ ክርስቲያንንም ትምህርት ተምሮ በቀናች ሃይማኖት ጸና ሕዝቡንም የሚያስተምር ሆነ ክብር ይግባውና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሃይማኖት በመስበክ ብዙዎችን ከስሕተት መለሳቸው። ስለዚህም በከሀዲው ንጉሥ ዘንድ ወነጀሉት ንጉሡም ወደርሱ እንዲአመጡት አዘዘ በንጉሡም ዘንድ አንድ ሥጋው የደነደነ የጸና ዐጥንቱ የሰፋ ሰው ነበረ ለሰዎችም ሁሉ እሱ ሁሉን የሚያሸንፍ እሱን የሚያሸንፈው የሌለ ይመስላቸው ነበር ንጉሡም ይወደዋል ይመካበታል እንዲህም ይል ነበር ይህን አካሉ ግዙፍ የሆነ ሰው ለሚያሸንፍ እኔ ብዙ ገንዘብ እሰጠዋለሁ። በዚያንም ጊዜ ስሙ በስጥዮስ የሚባል አንድ ክርስቲያናዊ ሰው ተነሥቶ ወደ ቅዱስ ድሜጥሮስ ሔደ እንዲጸልይለትና በሥጋውም ሁሉ አሸናፊ በሆነ በመስቀል ምልክት እንዲአማትብበት ለመነው።

እርሱም በላዩ ጸለየለት በሥጋውም ሁሉ ላይ በመስቀል አማተበበት ከዚህም በኋላ ወደ ንጉሥ ገብቶ ከዚያ ሥጋው ግዙፍ ከሆነው ጋር ያታግለው ዘንድ ለመነው ንጉሡም ፈቀደለት በታገሉም ጊዜ ሥጋው የደነደነውን ያ ክርስቲያናዊ ሰው አሸንፎ ጣለው ንጉሡም አዘነ አደነቀም ሥጋው የደነደነውም በመሸነፉ አፈረ ተመክቶበት ነበርና። ንጉሡም ስለዚህ ነገር ወታደሮቹን ጠየቀ እነርሱም ቅዱስ ድሜጥሮስ በላዩ እንደጸለየለትና በሥጋውም ላይ በመስቀል ምልክት እንዳማተበበት ነገሩት።

ንጉሡም ይህን በሰማ ጊዜ በቅዱስ ድሜጥሮስ ላይ እጅግ ተቆጣ ለአማልክትም ዕጣን እስከሚአሳርግ ድረስ እንዲገርፉት አዘዘ ንጉሡም እንዳዘዘ እንዲሁ አደረጉበት የንጉሡንም ትእዛዝ ባልሰማ ጊዜ እስከሚሞት በጦሮች እንዲወጉት ሁለተኛ አዘዘ።
ለቅዱስ ድሜጥሮስም ይህን ፍርድ ነገሩት ሃይማኖቱን ትቶ ለአማልክት የሚሰግድ መስሏቸው ነበርና ቅዱስ ድሜጥሮስም እኔ ከዕውነተኛ አምላክ ከሕያው እግዚአብሔር ልጅ ከጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ለረከሱ አማልክት እሰግድ ዘንድ ዕጣን ማሳረግም አልፈቅድም የወደዳችሁትን አድርጉ አላቸው።

በዚያንም ጊዜ ንጽሕት ነፍሱን በእግዚአብሔር እጅ እስከ ሚሰጥ በጦር ወጉት ሥጋውንም በጣሉት ጊዜ ምእመናን ወደ ርሳቸው ወሰዱት የስደቱም ወራት እስከሚያልፍ በሣጥን አድርገው በቤታቸው ውስጥ ሠውረው አኖሩት። የስደቱም ወራት ከአለፈ በኋላ እግዚአብሔር ገለጠውና ከዚያ አወጡት ያማረች ቤተ ክርስቲያንንም በተሰሎንቄ አገር ሠሩለት ሥጋውንም በውስጧ አኖሩ ድንቅ የሆነ ታላቅ ተአምርን እያደረገ እስከ ዛሬ አለ።

ሽታውም እጅግ ጣፋጭ የሆነ የሽቱ ቅባት ከእርሱ ይፈሳልና በእምነት የሚቀቡትን በሽተኞች ሁሉንም ያድናቸዋል። ይልቁንም በዕረፍቱ መታሰቢያ ቀን ከሌሎቹ ዕለታት ተለይቶ በብዛት ይፈሳል ከአውራጃው ሁሉ ብዙዎች ሰዎችም ይመጣሉ ከዚህም ቅባት ወስደው በማሰሮቻቸው ያደርጋሉ ይቺ ምልክትም እስከ ዓለም ፍጻሜ በመኖር እንደምትገኝ ደጋጎች ካህናት ምስክሮች ሆኑ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት እና #ከገድላት_አንደበት)
https://t.me/finotebirhan12
https://t.me/finotebirhan12
https://t.me/finotebirhan12
🌑 ሀዘን

የሰንበት ት/ቤት አባላችን የዳንኤል ተስፋዬ አህት ስላረፈች ዛሬ ሰኞ ጥቅምት 29 በደብረ አሚን አቡነ ተክለሃይማኖት ቤ/ክ ከቀኑ 6:00 በቀብር ሥርዓት ላይ ተገኝተን የወንድማችን ሀዘን ተካፋይ እንሁን

ለወንድማችንና ለቤተሰቡ መጽናናትን እግዚአብሔር ይሰጥልን
ነፍስ ይማር
🔴ማስታወቂያ
በሰንበት ትምህርት ቤታችን እየተገነባ ባለው ሕንጻ የ1ኛ(ግራውንድ )ፍሎር ስላብ ሙሌት ዛሬ ጥቅምት 30, 2014 ከጠዋቱ 3:00 ሰዓት ጀምሮ እናከናውናለን በመሆኑም ሥራው በሚከናወንበት ቀን የሚመቻችሁ አባላት ተገኝታችሁ እንድትሳተፉ ከበረከቱ ተሳታፊ ሁላችንም እንሁን

አግዚአብሔር ማኅበራችንን ይባርክ
🔴#ስንክሳር_#ኅዳር_3

#የአቡነ_መድኃኒነ_እግዚእ - እረፍት
#የአቡነ_ፍሬ_ካህን - እረፍት
#የቅዱስ_አባት_ኪርያቆስ - እረፍት
#የአባ_አትናቴዎስና_እኅቱ_ኢራኢ - እረፍታቸው
#የቅዱስ_ዓምደ_ሚካኤል - እረፍት ቀን ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ዓምደ_ሚካኤል

በዚችም ቀን ለኢትዮጵያ ነገሥታት ለዘርዐ ያዕቆብ፣ ለበእደ ማርያም፣ ለእስክንድር የሠራዊት አለቃ የሆነ ቅዱስ ዓምደ ሚካኤል አረፈ።

የዚህም ቅዱስ የአባቱ ስም ገላውዴዎስ የእናቱም ስም ኤልሳቤጥ ነው እነርሱም በዚህ ዓለም ገንዘብ ይልቁንም በሃይማኖትና በበጎ ሥራ የበለጸጉ ናቸው። ይህንንም ቅዱስ በቅዱሳን አርባዕቱ እንስሳ በዓል ወለዱት ስሙንም ዓምደ ሚካኤል ብለው ሰየሙት።

ከተወለደም አንድ ዓመት ሲሆነው ከቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ከመንበሩ ከርሠ ሐመር ውስጥ ማንም ያየው ሳይኖር እየዳኸ ገብቶ ሦስት ቀን ሰነበተ ወላጆቹም እርሱ እንደሞተ ተጠራጥረው እያለቀሱለት ኖሩ።

ከዚህም በኋላ በሦስተኛው ቀን ቄሱ ሊዓጥን ገባ ዕጣንንም ሲፈልግ በከርሠ ሐመሩ ውስጥ ሕፃኑን በሕይወት አገኘው በበታቹም ምንም ምን ጉድፈት አልነበረም። ቄሱም ለወላጆቹ ነገራቸው እነርሱም እጅግ ደስ እያላቸው መጥተው ከዚያ ወሰዱት።

ከዚያንም ጊዜ ጀምሮ በጥበብና በዕውቀት አደገ ነገሥታት ገዥ እስከ አደረጉት ድረስ በቤት ውስጥ በሚሠራው ላይ ሁሉ አሠለጠኑት። እርሱም ለድኆች በፍርዱና በምጽዋቱ አባት ሆናቸው በገንዘቡም አብያተ ክርስቲያናትን ሁሉ አደሰ በዘመኑም ሰላም ሆነ በጾሙና በጸሎቱ በምጽዋቱም በቅዱሳንም የጸሎት ርዳታ በወዲያም በወዲህም አገሮችን የሚያጠፉ ጠላቶችንና ዐመፀኞች ጠፉ። ጠላቶችም ሁሉ ለነገሥታቱ ተገዙና ግብርን ገበሩ።

የዚህም ቅዱስ ዓምደ ሚካኤል ልቡ በእግዚአብሔር ፍቅር የታሠረ ነው በተጸለየበት ውኃ ሳይጠመቅና ሳይጠጣ አይመገብም ነበር ገንዘቡንም ሁሉ በምጽዋት ጨረሰ።

እግዚአብሔርም በጎ ሥራውን በአየ ጊዜ እንዲፈተን ፈቀደለት ዐመፀኞች ሰዎችም በእርሱ ላይ ተነሡ እንዲገድለውም በንጉሥ ዘንድ በሐሰት ነገር ወነጀሉት ንጉሡ ግን እጅግ ስለሚወደው ራራለት በነገራቸውም በዘበዘቡትና በአስጨነቁትም ጊዜ ከጭንቀት የተነሣ ወደ ሩቅ አገር አሥሮ አጋዘው። የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም የሚራዳው ሆነ ሰማያዊ ኅብስት የወይን ጽዋ እያመጣለት ይመግበዋል።

ቅዱስ ቁርባንንም መቀበል በሚሻ ጊዜ የክብር ባለቤት የሆነ የክርስቶስን ሥጋውንና ደሙን አምጥቶ ይመግበዋል። ከዚህም በኋላ እሊያ ነገረ ሠሪዎች ይገድሉት ዘንድ ንጉሥ እንዲፈቅድላቸው ተማከሩ በፈቀደላቸውም ጊዜ ወደ ንጉሥ የፍርድ ሸንጎ አምጥተው ገደሉት።

በዚያችም ሌሊት እግዚአብሔርን የሚፈራ አንድ መነኵሴ በድኑን ሊያይ ተነሥቶ ሔደ ሥጋውንም ሲያጥኑ ሦስት መላእክትን አገኛቸው። እርሱም እንዳልዋሸ በሕያው እግዚአብሔር ስም እየማለ ይህን ተናገረ። ዳግመኛም የብርሃን ፋና ከሰማይ ሲወርድለት ብዙ ቀን የተመለከቱም አሉ።

ንጉሡም ይህን በሰማ ጊዜ አዘነ ተጸጸተም በጎ ሥራውንም ሁሉ አሰበ እነዚያንም ሐሰተኞች ረገማቸው በሞትም ቀጣቸው ቅዱስ ዐምደ ሚካኤልም በአባቶቹ መቃብር አክብረው እንዲቀብሩት አዘዘ። እርሱ ቅዱስ እንደሆነ በበጎ ስም አጠራር እንዲጠሩት እንጂ ስሙን በክፉ እንዳይጠሩ አዋጅ አሳወጀ። መታሰቢያውንም አቆመለት ልጆቹንም አከበራቸው እጅግም ወደዳቸው።

ከዚህም በኋላ ልብነ ድንግል በነገሠ ጊዜ ከእርሱ ጋር ያለውን የአባቱ የበእደ ማርያምን ቃል ኪዳን ሰምቶ ከዚያ አፍልሰው ወደ አትሮንስ ማርያም እንዲወስዱትና በዚያ በነገሥታት መቃብር እንዲቀብሩት አዘዘ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ሁሉ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር እና #ከገድላት_አንደበት)
https://t.me/finotebirhan12
👉 ነገ ሕዳር 4 የሕዳር ሚካኤል ጥናት ይካሄዳል 11:30 ጀምሮ ሁላችንም እንገኝ
👉 ለበለጠ መረጃ የሰንበት ት/ቤታችን የመዝሙር ክፍልን ቴሌግራም ይከታተሉ
https://t.me/finotewereb
https://t.me/finotewereb
🔴#ስንክሳር_#ኅዳር_4

በዚህችም ቀን
የደማስቆው #ቅዱስ_ቶማስ አረፈ
#ቅዱስ_ያዕቆብና_ዮሐንስ በሰማዕትነት አረፉ፣
#ቅዱሳን_አቢማኮስና_አዛርያኖስ በሰማዕትነት አረፉ፣
የአባ ዮሐኒ ደቀ መዝሙር የሆኑት #አቡነ_አበይዶ ዕረፍታቸው ነው፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱሳን_ያዕቆብ_ወዮሐንስ

በዚህችም ቀን ያዕቆብና የሀገረ ፋርስ ኤጲስቆጶስ ዮሐንስ የሐርመዝ ልጅ በሆነ በፋርስ ንጉሥ በሳቦር እጅ በሰማዕትነት አረፉ።

አሁን ደግሞ ወደ 4ኛው መቶ ክ/ዘመን ተመልሰን ወደ ምድረ ፋርስ (ኢራን) ወርደን ቅዱሳንን እናዘክር። እነዚህ ቅዱሳንም በሃገረ ፋርስ (ኢራን) በመንግስተ ሳቦር ዘመን የነበሩ አበው ናቸው። ሳቦር ማለት ጸሐይንና እሳትን የሚያመልክና እጅግ ጨካኝ የነበረ ንጉሥ ነው።

ቅዱሳኑ ያዕቆብና ዮሐንስ የሐዋርያትን ስም ብቻ ሳይሆን ግብራቸውን ቅድስናቸውንም የያዙ ነበሩ። ዘመኑ ዘመነ ሰማዕታት ባይሆንም ፋርስ ግን በዚህ ዘመንም ለክርስቲያኖች የግፍ ከተማ ነበረች።

ከቅዱስ ጊዮርጊስ እስከ ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ ከቅዱስ መርምሕናም እስከ ቅዱስ ኮቶሎስ ሰማዕትነትን የተቀበሉት በዚህችው ሃገር ውስጥ ነው። ቅዱሳን ያዕቆብና ዮሐንስም ትምሕርተ ቤተ ክርስቲያንን በልኩ ተምረው መጻሕፍትንም ተረድተው ለክህነት ተመርጠዋል።

በሁዋላም ቤተ ክርስትያን "ይገባቹሃል" ስትል ዻዻሳት አድርጋ ሾመቻቸው:: እነርሱም አላሳፈሯትም። የክርስቶስን መንጋ እያስተማሩ እየናዘዙ ጠበቁላት። ንጉሡ ሳቦር ግን ሕዝቡን ለፀለሐይና ለእሳት ሊያሰግድ ላደረገው ጥረት እንቅፋት ሁነውበታልና ጠላቸው።

በወታደሮቹ አስይዞም በፍርድ አደባባይ አቆማቸው። ሕዝቡን በአዋጅ ጠርቶ። አስፈሪ እሳት አስነድዶ "ሕዝቡ ለፀሐይ እንዲሰግድ እዘዙ" ቢላቸው "እንቢ" አሉት።

ከነ ልብሳቸው አንስተው ወደ እሳቱ ወረወሯቸው። ቅዱሳኑም በመከራው (በነደደው እሳት) መካከል ሆነው ለሕዝቡ ተናገሩ።
"አምላክ አንድ እግዚአብሔር ነውና እንዲህ በሃይማኖታችሁ ጽኑ" አሏቸው። እሳቱም አቃጥሎ ገድሏቸው የክብርን አክሊል ተቀዳጁ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር እና #ከገድላት_አንደበት)
https://t.me/finotebirhan12
https://t.me/finotebirhan12
🌹 #ተፈፀመ_ማኅሌተ_ጽጌ_ኅዳር 5

ነግሥ
ሰምዓኒ እግዚኦ ጸሎትየ፤ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ ወይብጻሕ ቅድሜከ ገዓርየ፤ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ ወኢትሚጥ ገጽከ እምኔየ፡፡በዕለተ ምንዳቤየ አጽምእ እዝነከ ኅቤየ፤ሃሌ ሉያ (፪) እመ ዕለተ አጽውአከ ፍጡነ ስምዓኒ፡፡ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ ለዓለመ ወለዓለመ ዓለም፡፡ሃሌ ሉያ ዘውእቱ ብሂል፡፡ንወድሶ ለዘሀሎ እግዚአብሔር ልዑል፡፡ስቡሕ ወውዱስ ዘሣረረ ኵሉ ዓለመ በአሐቲ ቃል፡፡

፩) ለኲልያቲክሙ

ሰላም፡ ለኵልያቲክሙ፡ እለ፡ ዕሩያን፡ በአካል፤
ዓለመክሙ፡ ሥላሴ፡ አመ፡ ሐወፀ፣ ለሣህል፤
እምኔክሙ፡ አሐዱ፡ እግዚአብሔር፡ ቃል፤
ተፈጸመ፡ ተስፋ፡ አበው፡ በማርያም፡ ድንግል፤
ወበቀራንዮ፡ ተተክለ፡ መድኃኒት፡ መስቀል ፡፡

ዚቅ

ዛቲ: ይእቲ: እኅተ: ትጉኃን: መላእክት፤
ወለተ፡ ኄራን፡ ነቢያት፤
እሞሙ፡ ለሐዋርያት፤
ሞገሶሙ፡ ለጻድቃን፡ ወሰማዕት።

፪) ኢየኃፍር ቀዊመ

ኢየኃፍር፡ ቀዊመ፡ ቅድመ፡ ስዕልኪ፡ ወርኃ፡ ጽጌረዳ፡ አመ፡ ኃልቀ፤
ዘኢየኃልቅ፡ ስብሐተኪ፡ እንዘ፡ እሴብሐኪ፡ ጥቀ፤
ተአምርኪ፡ ማርያም፡ ከመ፡ አጠየቀ፤
ጸውዖ፡ ስምኪ፡ ያነሥእ፡ ዘወድቀ፤
ኃጥአኒ፡ ይሬሲ፡ ጻድቀ፡፡

🌹 ወረብ

ኢየኃፍር፡ ቀዊመ፡ ቅድመ፡ ስዕልኪ፡ ወርኃ፡ ጽጌረዳ፡ አመ፡ ኃልቀ፤
ዘኢየኃልቅ፡ ስብሐተ፡ ስብሐተ፡ እንዘ፡ እሴብሐኪ።

ዚቅ

እለ፡ትነብሩ፡ ተንሥኡ፤
ወእለ፡ ታረምሙ፡ አውሥኡ፤
ማርያምሃ፡ በቃለ፡ ስብሐት፡ ጸውዑ፤
ቁሙ፡ ወአጽምዑ፡ ተአምረ፡ ድንግል፡ ከመ፡ ትስምዑ፤
ጸልዩ፡ ቅድመ፡ ስዕላ፡ ለቅድስት፡ ድንግል፤
መርዓተ አብ ወእመ በግዑ፡፡

፫) እንዘ ተሐቅፊዮ

እንዘ፡ ተሐቅፊዮ፡ ለሕጻንኪ፡ ጽጌ፡ ፀዓዳ፡ ወቀይሕ፤
አመ፡ ቤተ፡ መቅደስ፡ ቦእኪ፡ በዕለተ፡ ተአምር፡ ወንጽሕ፤
ንዒ፡ ርግብየ፡ ትናዝዝኒ፡ እምላህ፤
ወንዒ፡ ሠናይትየ፡ ምስለ፡ ገብርኤል፡ ፍሡሕ፤
ወሚካኤል፡ ከማኪ፡ ርኅሩኅ፡፡

🌹 ወረብ

እንዘ፡ ተሐቅፊዮ፡ ለሕጻንኪ፡ ጽጌ፡ ፀዓዳ፡ ወቀይሕ፤
ንዒ፡ ርግብየ፡ ምስለ፡ ገብርኤል፡ ወንዒ፡ ሠናይትየ፡ ምስለ፡ ሚካኤል።

ዚቅ

ይዌድስዋ፡ ትጉኃን
ይቄድስዋ፡ ቅዱሳን፤
ሰሎሞን፡ ይቤላ፡ ርግብየ፡ ሠናይት፤
ጳውሎስኒ፡ ይቤላ፡ ደብተራ፡ ፍጽምት፤
ዳዊትኒ፡ ይቤላ፡ ስምዒ፡ ወለትየ፡ ወርእዪ፡ ወአጽምዒ፡ ዕዝነኪ።

፬) ሶበ ዴገነኪ አርዌ

ሶበ፡ ዴገነኪ፡ አርዌ፡ በሊዓ፡ ሕጻንኪ፡ ዘኀለየ፤
በዘትሠርሪ፡ ገዳመ፡ ወታፈጥኒ፡ ጐይየ፤
አመ፡ ጸገይኪ፡ አክናፈ፡ ከመ፡ ዮሐኒ፡ ጸገየ፤
ብእሲተ፡ ሰማይ፡ ማርያም፡ ዘትለብሲ፡ ፀሐየ፤
ተአምረኪ፡ ጸሐፈ፡ ዮሐንስ፡ ዘርእየ፡፡

🌹 ወረብ

አመ፡ አመ፡ ጸገይኪ፡ አክናፈ፡ ከመ፡ ዮሐኒ፤
ተአምረኪ፡ ጸሐፈ፡ ዮሐንስ፡ ዘርእየ፡ ዘርእየ፡ ተእምረኪ፡፡

ዚቅ

በሊዓ፡ ሕጻናት፡ ሶበ፡ ኀለየ፡ ሄሮድስ፡ አርዌ፡ ሰማይ፤
ዘምስለ፡ ዮሴፍ፡ አረጋይ፤
ነገደት፡ ቍስቋመ፡ ናዛዚተ፡ ኃዘን፡ ወብካይ፤

፭) ክበበ ጌራ ወርቅ

ክበበ፡ ጌራ ወርቅ፡ ጽሩይ ፡ እምዕንቈ ባሕርይ ፡ ዘየኃቱ፤
ዘተጽሕፈ፡ ብኪ፡ ትእምርተ፡ ስሙ፡ ወተዝካረ፡ ሞቱ፤
አክሊለ፡ ጽጌ፡ ማርያም፡ ለጊዮርጊስ፡ ቀጸላ፡ መንግሥቱ፤
አንቲ፡ ኵሎ፡ ታሰግዲ፡ ሎቱ፤
ወለኪኒ፡ ይሰግድ፡ ውእቱ፤

🌹 ወረብ
ክበበ፡ ጌራ ወርቅ፡ ጽሩይ፡ ክበበ፡ ጌራ ወርቅ፡ዘየኃቱ፡ እም፡ ዕንቈ፡ ባሕርይ፤
አክሊለ፡ ጽጌ፡ ማርያም፡ ቀጸላ፡ መንግሥቱ፡ ለጊዮርጊስ፡ መንግሥቱ፡ ለመፍቀሬ፡ አምላክ ፡፡

ዚቅ

አክሊሎሙ፡ ለሰማዕት፤
ተስፋ፡ መነኮሳት፤
ሠያሚሆሙ፡ ለካህናት፤
ነያ፡ ጽዮን፡ መድኃኒት።

፮) ኅብረ ሐመልሚል

ኅብረ፡ ሐመልሚል፡ ቀይሕ፡ ወፀዓድዒድ፤
አርአያ፡ ኮሰኮስ፡ ዘብሩር፤
ተአምርኪ፡ ንጹሕ፡ በአምሳለ፡ ወርቅ፡ ግቡር፤
ተፈጸመ፡ ናሁ፡ ማኅሌተ፡ ጽጌ፡ ሥሙር፤
አስምኪ፡ ቦቱ፡ ንግሥተ፡ ሰማያት፡ ወምድር፤
ከመ፡ በሕጽንኪ፡ ያሰምክ፡ ፍቁር ።

🌹 ወረብ

ናሁ፡ ተፈጸመ፡ ተፈጸመ፡ ናሁ፡ ማኅሌተ፡ ሥሙር፡ ተፈጸመ፡ ናሁ፤
አስምኪ፡ ቦቱ፡ አስምኪ፡ ቦቱ፡ ንግሥተ፡ ሰማያት፡፡

ዚቅ

ሃሌ ሃሌ፡ ሉያ፡ ሃሌ፡ ሉያ፤
ጥቀ፡ አዳም፡ መላትሕኪ፡ ከመ፡ ማዕነቅ፤
ይግበሩ፡ ለኪ፡ ኮሰኮሰ፡ ወርቅ፡፡

፯) ተመየጢ

ተመየጢ፡ እግዝእትየ፡ ማርያም፡ ሀገረኪ፡ ናዝሬተ፤
ወኢትጎንድዪ፡ በግብጽ፡ ከመ፡ ዘአልብኪ፡ ቤተ፤
በላዕሌኪ፡ አልቦ፡ እንተ፡ ያመጽእ፡ ሁከተ፤
ለወልድኪ፡ ዘየኃሥሦ፡ ይእዜሰ፡ ሞተ፤
በከመ፡ ነገሮ፡ መልአክ፡ ለዮሴፍ፡ ብሥራተ።

🌹 ወረብ

ተመየጢ፡ ተመየጢ፡ እግዝእትየ፡ ማርያም፡ ሀገረኪ፤
ወኢትጎንድዪ፡ በግብፅ፡ በግብፅ፡ ከመ፡ ዘአልብኪ፡ ቤተ፡፡

ዚቅ

ሃሌ፡ ሉያ፤ ተመየጢ፡ ተመየጢ፡ ሰላመ፡ ሰጣዊት፤
ወንርዓይ፡ ብኪ፡ ሰላመ፡ ምንተኑ፡ ትኔጽሩ፡ በእንተ፡ ሰላመ፡ሰጣዊት፤
እንተ፡ ትሔውፅ፡ እምርኁቅ፡ ከመ፡ መድበለ፡ ማኅበር፤
ሑረታቲሃ፡ ዘበስን፡ ለወለተ፡አሚናዳብ።

🌹 መዝሙር

ሃሌ (በ፮)
ክርስቶስ፡ ሠርዓ፡ ሰንበተ፡ ክርስቶስ፡ ሰንበተ፡ ወጸገወነ፡ ዕረፍተ፡ ከመ፡ ንትፈሣሕ፡ ኅቡረ፤
አዕጻዳተ፡ ወይን፡ ጸገዩ፡ ቀንሞስ፡ ፈረዩ፡ ሰሎሞን፡ ጥቀ፡ ኢለብሰ፡ ከመ፡ አሐዱ፡ እምእሉ።

https://t.me/finotebirhan12
🔴#ስንክሳር_#ኅዳር_5

በዚህች ቀን የደብረ ዓሣው #አባ_ዮሐኒ የተሰወሩበት፣ #አባ_አሞኒ_ዘናሕሶ ያረፉበት፣ #የቅዱስ_ለንጊኖስ ራሱ የታየችበት፣ የሐዋርያው #ቅዱስ_ጢሞቴዎስ መታሰቢያ፣ #የቅዱስ_ቴዎድሮስ_ሰማዕት ሥጋው የፈለሰበት ዕለት ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ለንጊኖስ

በዚህች ቀን ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕንጨት መስቀል ላይ ተሰቅሎ ሳለ ጐኑን የወጋ የቅዱስ ለንጊኖስ ራሱ የታየችበት ነው። ይህም ቅዱስ በጌታችን ከአመነ በኋላ በቀጰዶቅያ አገር ወንጌልን የሚሰብክ ሆነ ከሀድያን አይሁድም በላዩ ተነሡበት በመኳንንት ዘንድ በሐሰት ወንጅለው በቀጰዶቅያ አገር ራሱን አስቆረጡት ራሱንም ብቻውን ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱዋት። በኢየሩሳሌም የሚኖሩም አይሁድ በአዩዋት ጊዜ እጅግ ደስ አላቸው ከዚህም በኋላ ከኢየሩሳሌም ከተማ ውጭ በአንድ ኮረብታ ላይ ቀበሩዋት።

ከብዙ ቀኖችም በኋላ እንዲህ ሆነ በቅዱስ ለንጊኖስ ስብከት ያመነች አንዲት ሴት በቀጰዶቅያ አገር ነበረች ራሱን ከቆረጡበት ጊዜ ጀምራ በተቆረጠበት ቦታ በመቆም ስለርሱ ታለቅስ ነበር ክብር ይግባውና በእግዚአብሔርም ፈቃድ የዚያች ሴት ዐይኖቿ ታወሩ።

ከዚህም በኋላ ምናልባት ዐይኖቿ ቢገለጡላት በማሰብ ከከበሩ ቦታዎችና ክብር ይግባውና ከጌታችን መቃብር ለመባረክና ለመለመን ተነሥታ ልጅዋን ይዛ ወደ ኢየሩሳሌም ሔደች። ወደ ኢየሩሳሌምም በደረሰች ጊዜ በዚያ ልጅዋ ሞተ ኀዘንም ተጨመረባት ወደ አገርዋም መርቶ የሚያደርሳት አጣች ስለዚህም የመረረ ልቅሶን አለቀሰች ከኀዘኗም ብዛት የተነሣ ተኛች።

ከዚህም በኋላ ቅዱስ ለንጊኖስን ከሞተው ልጅዋ ጋር በሕልሟ አየችው። ዕገሌ ከሚባልም ቦታ ሒደሽ ራሴን ከዚያ ውሰጂ አላት። ከእንቅልፍዋም በነቃች ጊዜ ስለዚያ ቦታ ጠየቀች ሰዎችም ወደርሱ አደረሱዋት። ያንንም ቦታ በቆፈረች ጊዜ መዓዛው እጅግ ጣፋጭ የሆነ የሽቱ መዓዛ ወጣ። ራሱ ወደአለችበትም ስትደርስ ታላቅ ብርሃን ተገለጠላትና ዐይኖቿም በዚያን ጊዜ ተገለጡላት እግዚአብሔርንም አመሰገነችው።

ከዚህም በኋላ ከልጅዋ ሥጋ ጋር የቅዱስ ለንጊኖስን ራስ ወደ አገርዋ ወሰደቻት። በታላቅ ክብርም በአማረ ቦታ አኖረቻት።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር_ጥርና_ሐምሌ እና #ከገድላት_አንደበት)
https://t.me/finotebirhan12
🔴ስንክሳር_ኅደር 6

ኅዳር 6 ቀን ክብርት #እመቤታችን_ከተወደደ_ልጇ ጋር ደብረ ቁስቋም ገብተው ካገኛቸው ድካም ያረፉበት፣ የአረጋዊ #ቅዱስ_ዮሴፍ#የቅድስት_ሰሎሜ#የአባ_ጽጌ_ድንግል መታሰቢያቸው ነው፤ የሮሜ አገር ሊቀ ጳጳሳት #ቅዱስ_ፊልክስ እረፍቱ ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ደብረ_ቁስቋም

ኅዳር ስድስት በዚህች ዕለት ክብርት እመቤታችን ከተወደደ ልጇ ጋር ከስደት በሚመለሱበት ጊዜ ደብረ ቁስቋም ገብተው ካገኛቸው ድካም ዐረፉ፡፡

አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናች ክብርት እመቤታችን ከስደት በተመለሰች ጊዜ እንዲህ ሆነ፡- የብርሃን እናቱ ክብርት እመቤታችን ልጇን ይዛ ከእነ ዮሴፍ ጋር ወደ ምድረ ግብፅ ስትሰደድ ግብፅ ደርሰው በዚያ ቢቀመጡም ነገርን ግብፅ አልተመቸቻውም፡፡ ሕዝቡም በሰላም አልተቀበላቸውም፡፡ እንዲያውም በምድረ ግብፅ ብዙ ተሠቃይተዋል፡፡ ከግብፅም ተነሥተው ወደ ኢትዮጵያ በመጡ ጊዜ ግን ኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ በሰላምና በፍቅር ተቀበላቸው፡፡ ከመንገዱና ከርሃብ ጥሙ ጽናት የተነሣ እጅግ ደክማለችና የኢትዮጵያ ሰዎች እመቤታችንን አይተው እጅግ አዘኑላት፡፡ ‹‹ይህችስ የነገሥታት ዘር ትመሥላለች ነገር ግን አንዳች ችግር አጋጥሟት ተሰዳ ወደ ሀገራችን መጥታለች..›› ብለው እንክብካቤን አደረጉላት፡፡ እግራቸውን አጥበው በክብር ማረፊያዎች ላይ አሳረፏቸው፡፡ መልካም መስተንግዶም አደረጉላቸው፡፡ እመቤታችንም ከድካሟ ካረፈች በኋላ ሀገሪቱን በእጅጉ ወደደቻትና የተወደደ ልጇን ‹‹ይህን ሀገርና ሕዝቧን በመላ ወድጃቸዋልሁና በዚህ እስከ መጨረሻው እንኑር›› አለችው፡፡ ጌታችንም ክብርት እናቱን ‹‹ይህች ቅድስት ሀገር ናት፣ በኋለኛው ዘመን የቅዱሳን መነኮሳት ቦታ ትሆናለች፡፡ በውስጧም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ እመሰገንባታለሁ፤ የአንቺም ስም ሳይጠራ አይውልባትም›› አላት፡፡

ከዚህም በኋላ ጌታችን ደመና ጠቅሶ በእርሷ ላይ ተቀመጡ፡፡ መልአኩ ቅዱስ ዑራኤልም መጣና እየመራቸው መላ ኢትዮጵያን ጎበኟት፡፡ እመቤታችንም ሀገሪቱንና ሕዝቦቿን ወዳቸዋለች ደስም ተሰኝታባቸዋለችና ጌታችን ለክብርት እናቱ ‹‹ይህችን ቅድስት ሀገር አሥራት አድርጌ ሰጠሁሽ›› አላት፡፡ እመቤታችንም እጅግ ተደስታ ‹‹ልጄ አምላኬ›› ብላ አመሰገነችው፡፡ ከዚህም በኋላ ከአንዱ ቦታ ወደ አንዱ ቦታ እየተዘዋወሩ መላዋ ኢትዮጵያን በኪደተ እግራቸው ባረኳት፡፡ ጌታችንም ‹‹በዚህ ቦታ እንዲህ ዓይነት ቤተ ክርስቲያን ይታነጻል፤ እከሌ የሚባል እንዲህ ዓይነት ቅዱስ ይነሣል…›› እያለ ብዙ ምሥጢራትን ለክብርት እናቱ ነገራት፡፡ ከዚህም በኋላ የስደቱ ዘመን ሲያልፍ ሄሮድስም በመጨረሻ ክፉ አሟሟትን ሲሞት መልአኩ ወደ ገሊላ አውራጃ እንዲመለሱ ነገራቸው፡፡ እመቤታችንም ‹‹ከዚህች ሀገርስ ባንሄድ እመርጣለሁ›› ስትለው የተወደደ ልጇ ግን ‹‹እናቴ ሆይ ጽድቅንና ፈቃድን ሁሉ ልንፈጽም ይገባናል›› ብሎ አጽናናትና ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ሄዱ፡፡

ተመልሰውም ሊሄዱ ሲነሡ የኢትዮጵያ ሰዎች ልዩ ልዩ አምሐ እጅ መንሻ ሰጧቸው፡፡ ልዩ ልዩ ልብሶች፣ ወርቅ፣ ዕጣን፣ ከርቤ፣ ሽቱ እና ሥንቀቸውን በግመሎች ላይ ጭነው እመቤታችንንና የተወደደ ልጇንም በበቅሎ ላይ አስቀምጠው በክብር ሸኟቸው፡፡ እመቤታችንም ልጇን ታቅፋ በበቅሎ ተቀምጣ በበረሃው በመጓዝ ወደ መጣችበት አገር ሄደች፡፡ ኢትዮጵያንም የሰጧትን ብዙ እጅ መንሻዎች በግመሎች ጭና ይዛ ወደ አገሯ በተመለሰች ጊዜ ከአንድ ባሕር ዳር ደረሰች፡፡ ከዚያም የጀልባውን ባለቤት ‹‹እግዚአብሔርን ስለመውደድ አሻግረኝ›› ብላ ለመነችው፡፡ ባለጀልባውም ‹‹እነሆ ዕቃ የተጫኑ አምስት ግመሎችና ከአንቺ ጋር ከዚህም ሕፃን ጭምር አምስት ሰዎች እመለከታለሁ፣ አንቺ የተቀመጥሽባት በቅሎም አለች፡፡ ጀልባዋም ታናሽ ናት፣ የመቀመጫ ክፍሏም በውስጧ የተሳፈሩት ሰዎችም ተጨናንቀው ነው ያሉት፡፡ ስለዚህ እንዴት ላሻግርሽ እችላለሁ? ነገር ግን እመቤቴ ሆይ! ይቅርታ አድርጊልኝ ይህን በክፋት አላደረግሁትምና›› አላት፡፡

ክብርት እመቤታችንም የጀልባው ባለቤት ሊያሻግራት እንዳልቻለ በተረዳች ጊዜ ‹‹ልጄ ሆይ የእግዚአብሔር ልጅ እንደመሆንህ ይህን ትልቅ ወንዝ ለመሻገር የአምላክነትህን ሥራ ትሠራ ዘንድ እለምንሃለሁ›› ስትል ማለደችው፡፡ ያንጊዜም ጌታችን ክብርት እናቱን ‹‹የወለደሽኝ እናቴ ሆይ! አትዘኝ›› ብሎ አረጋጋት፡፡ ዳግመኛም ‹‹በእኔ ፈቃድ በአባቴ ፈቃድ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ካንቺ ሰው ሆኛለሁና ሰው መሆኔንም ከአባቴ በቀር መስተፍሥሒ ከሚሆን ከመንፈስ ቅዱስም በቀር ያወቀ የለም፡፡ ዳግመኛም በሕያዋንና በሙታን ለመፍረድ ለሁሉም እንደየሥራው እከፍለው ዘንድ እመጣለሁ፡፡ ያችንም ሰዓት የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ የአዳም ልጆችም ቢሆኑም ከእኔና ከአባቴ ከመንፈስ ቅዱስም በቀር የሚያውቃት የለም፡፡ ያንጊዜ ‹ዐመፅን የሚናገር አንደበት ሁሉ ይዘጋል› ብሎ አባትሽ ዳዊት እንደተናገረ እከራከራለሁ የሚል አንደበት እንደድዳ ምላሽ ያጣል›› አላት፡፡

ክብርት እመቤታችን ማርያምም ይህንን ሁሉ ምሥጢር የተወደደ ልጇ የነገራትን ታስተውለው በልቧም ትጠብቀው ነበር፡፡ ጌታችንም አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለክብርት እናቱ ይህንን ከነገራት በኋላ ቀኝ እጁን ዘርግቶ ከወንዙ ማዶ ጢር በሚባል ተራራ ያሉትን ድንጋዮች ጠቀሳቸው፡፡ ያንጊዜም እነዚህ ድንጋዮች እየተገለባበጡ መጥተው እንደ ጀልባ ሆነው በወራጁ ወንዝ ላይ ተንሳፈፉ፡፡ ከዚያም እመቤታችንን ከሕፃኑ ጋር ከነቤተሰቧና ከነጓዟ አሻገረሯት፡፡

እነዚህንም ድንጋዮች ያዩ ሰዎች ሁሉ እጅግ አድንቀው ‹‹ብቻውን ድንቅ ተአምራት ያደረገ፣ እስራኤልን የፈጠረ እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን የጌትነቱም ስም የተመሰገነ ነው›› እያሉ አመሰገኑ፡፡ እነዚህም የተባረኩ ሰዎች ወንዙን ከተሻገሩ በኋላ በዚህች አገር ለስምንት ቀን ተቀመጡ፡፡ ከዚህም በኋላ አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናች ክብርት እመቤታችን ስለደረገላት መልካም ሥራ ሁሉ እግዚአብሔርን ፈጽማ እያመሰገነች ወደ አባቷ ወደ ዳዊት አገር ተመለሰች፡፡

ዳግመኛም በኋለኛው ዘመን ጌታችን በዚህ በደብረ ቍስቋም ቅዱሳን ሐዋርያቶቹን ሰበሰባቸውና ታቦትንና ቤተ ክርስቲያንን አክብሮ የቍርባን መሥዋዕትንም ሠርቶ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለወገኖቹ ሰጣቸው፡፡ ለዚህም ነገር የእስክንድርያ አገር ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱሳን አባቶቻችን ቄርሎስና ቴዎፍሎስ ምስክሮቹ ሆኑ፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አረጋዊ_ቅዱስ_ዮሴፍ እና #ቅድስት_ሰሎሜ

ዳግመኛም በዚህች ቀን የአረጋዊ ቅዱስ ዮሴፍ እና የቅድስት ሰሎሜም መታሰቢያቸው ነው።

#አረጋዊ_ቅዱስ_ዮሴፍ፦ መልካም ሽምግልና የነበረው የእመቤታችን ድንግል ማርያም እጮኛዋ ድካሟን ለመሳተፍ ክብር ይግባውና ለጌታችንም አሳዳጊው ለመሆን የተገባው መታሰቢያው ነው።

እርሱም እምቤታችንን በርሱ ዘንድ ካስጠበቋት ጀምሮ በሁሉ ነገር ያገለግላት ነበር። በመከራዋም ሁሉ አልተለያትም። በወለደችም ጊዜ በቤተ ልሔም ከርሷ ጋራ ነበረ። ወደ ግብጽም በተሰደደች ጊዜ ከእርሷ ጋራ ብዙ መከራ ደረሰበት። ከዚህም ዓለም የሚለይበት ጊዜው በደረሰ ጊዜ ወንዶችና ሴቶች ልጆቹን ተሰናበታቸው እጆቹንም ጠርቶዘርግቶ ነፍሱን በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ። የዘላለምንም ሕይወት ወረሰ።

በአረፈበትም ጊዜ ጌታችን ወደርሱ መጥቶ እጆቹን በላዩ ጫነ ለሥጋውም መፍረስና መበስበስ እንዳያገኘው ኃይልን ሰጠው በአባቱ በያዕቆብም መቃበር አኖሩት።
👇👇👇👇🌹🌹🌹👇👇👇👇
#ቅድስት_ሰሎሜ፦ አምላክን የወለደች የቅድስት ድንግል የእመቤታችን የአክስቷ ልጅ መታሰቢያዋ ነው። እርሷም የማጣት ልጅ የሌዊ ልጅ የሚልኪ ልጅ የካህን አሮን ልጅ ናት። ለማጣት ሦስት ሴቶች ልጆች አሉት የታላቂቱ ስም ማርያም ነው የሁለተኛዪቱ ስም ሶፍያ የሦስተኛዪቱም ሐና ነው ይቺም ማርያም ሰሎሜን ወለደቻት ሶፍያም ኤልሳቤጥን ወለደቻት ሐናም አምላክን የወለደች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ወለደቻት።

እመቤታችንም ድንግል ስትሆን የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በወለደችው ጊዜ ይቺ ቅድስት ሰሎሜ የእመቤታችንን አወላለድ እንደ ሴቶች ሁሉ አወላለድ መስሏት ተጠራጠረች ከዚህም በኋላ የድንግል እመቤታችን ገላዋን ዳሠሠቻት ያን ጊዜ እጇ ተቃጠለ ሕፃኑን በዳሠሠችው ጊዜ ደግሞ ዳነች።

በዚህም በኅቱም ድንግልና አምላክን እንደወለደች አወቀች። ከተረገመ ኄሮድስ ፊት እመቤታችን በሸሸች ጊዜ ከዮሴፍ ጋራ በመሆን አብራ በመሰደድ የእመቤታችንን ድካሟን ተካፍላ አገለገለቻት ከስደት እስከ ተመለሱ ድረስ ሕፃኑን ታዝለዋለች የምታጥብበትም ጊዜ አለ።

መድኃኒታችን ሰው በሆነበት ወራት ሁሉ አልተለየችም በመከራውም ቀን ከእመቤታችን ጋራ ከከበሩ ሁሉ ሴቶች በትምህርቱ ወራት ከተከተሉት ጋራ እያለቀሰች ነበረች።

በተነሣባት ዕለት ወደ መቃብር ገሥግሣ ከሐዋርያት ቀድማ ያየች ናት። በኃምሳኛውም ቀን መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜ ከባልንጆሮቿ የከበሩ ሴቶች ጋራ ሰማያዊ ሀብትን ተቀብላ በክብር ባለቤት መድኃኒታችን ስም ሰበከች ብዙዎችንም አሳመነች። ከአይሁድም ብዙ ስድብና ሽሙጥ አገኛት ከዚያም አረፈች።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም ከስደቱ በረከትም ያድለን። በቅዱሳኑም ጸሎቱ ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኅ_ኅዳር_ግንቦትና_ሐምሌ#ከዲያቆን_ዮርዳኖስ_አበበ እና #ከገድላት_አንደበት)
https://t.me/finotebirhan12
የሰንበት ት/ቤታችን ዩትዩብ ቻናል 500 ሊሞላ ጥቂት ሰብስክራይበር ይጠብቃል ስለሆነም ይህንን መልዕክት የምታነቡ ሰብስክራይብ በማድረግ በቅርቡ መንፈሳዊ ዜናዎችን ትረካዎችን እንዲሁም ትምህርተ ወንጌልና ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን እያሰናዳን ነው.. ከዚህ በታች ያለውን link በመጫን ሰብስክራይብ የሚለውን ይጫኑ አብራችሁን ስላላችሁ እናመሰግናለን

መልካም ቀን

Youtube Channel: https://m.youtube.com/channel/UCXMG9oO5j1M-lRbAn0OdVdQ
🔴ስንክሳር_ኅደር 7

በዚህችም ቀን #የቅዱስ_ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕት ቅዳሴ ቤቱ፣ ከእስክንድርያ አገር የሆነ #ቅዱስ_ጊዮርጊስ በሰማዕትነት አረፈ፣ #አባ_ናህርው በሰማዕትነት አረፈ፣ #የአባ_ሚናስ_ዘተመይ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፣ #ቅዱሳን_ዘኖቢስ እና እናቱ #ቅድስት_ዘኖብያ እንዲሁም #ቅዱስ_ሐዲስ_መርቆሬዎስ እና ወንድሙ #ቅዱስ_ዮሐንስ በሰማዕትነት አረፉ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ጊዮርጊስ_ሊቀ_ሰማዕት

ኅዳር ሰባት በዚህችም ቀን የልዳ ሀገር የሆነ የሰማዕታት አለቃ የታላቁ መስተጋድል የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የከበረችበት ነው ዳግመኛም ጌታችን በውስጧ ላደረገው ድንቅ ተአምር መታሰቢያ ሆነ።

ይህም እንዲህ ነው በውስጧ ድንቆች ተአምራት እንደሚሠሩ ከሀዲ ዲዮቅልጥያኖስ በሰማ ጊዜ ሊአፈርሳት አሰበ ስሙ አውህዮስ የሚባለውንም መኰንን ከብዙ ሠራዊት ጋር ላከው፤ ያም መኰንን በደረሰ ጊዜ የቅዱስ ጊዮርጊስ ሥዕል ወዳለበት አዳራሽ በትዕቢት ሆኖ ገባ። በሥዕሉም ፊት በብርጭቆ መቅረዝ መብራት ነበረ በቤተ ክርስቲያኒቱና በቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ እየዘበተ በእጁ በያዘው በትር የመብራቱን መቅረዝ መትቶ ሰበረው የመቅረዙም ስባሪ ወደ ከሀዱው ራስ ደርሶ መታው ራሱንም ታመመ ፍርሃትና እንቅጥቅጥም መጣበት ወድቆም ተዘረረ ባልንጀሮቹም ወደ አገሩ ሊወስዱት ተሸከሙት በክፉ አሟሟትም ተጐሳቊሎ ሞተ ወስደውም ከባሕር ጣሉት ወገኖቹም ወደ ሀገራቸው አፍረው ተመለሱ።

ከሀዲ ዲዮቅልጥያኖስም ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጣ በልዳ ሀገር ያለች የቅዱስ ጊዮርጊስን ቤተ ክርስቲያን ያፈርሳት ዘንድ ራሱ ተነሥቶ ሔደ በዚያንም ጊዜ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ መታው ሰባት ዓመት ያህልም ዐይኖቹ ታውረው አእምሮውንም አጥቶ ቁራሽ እንጀራም እየለመነ ኑሮ ሞተ።

ክብር ይግባውና ጌታችንም የቤተ መንግሥቱን ሰዎች አስነሣበት እርሱን አስወግደው ጻድቅ ሰው ቁስጠንጢኖስን በእግዚአብሔር ፈቃድ አነገሡት እርሱም በአዋጅ የጣዖታትን ቤቶች ዘግቶ አብያተ ክርስቲያናትን ከፈተ ለክርስቲያን ወገኖችም በሁሉ ዓለም ተድላ ደስታ ሆነ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ሰማዕታት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር)
https://t.me/finotebirhan12